July 1, 2023
22 mins read

ወልቃይት፤ በቦታው ነበርኩ – አንዱ ዓለም ተፈራ

Wekait

ቅዳሜ፣ ሰኔ   ቀን     ዓ. ም.  (07/01/23)

ወልቃይት ወደ ትግራይ እንድትገባ የተደረገው፤

አንድም ለመሬቷ ልምላሜ፣ ሌላም ለሱዳን ወሰንነቷ ሲሆን፤

ያ ሲደረግ፤ ሕገ−መንግሥቱም ሆነ ፓርላማው አልነበሩም፣ አልተሳተፉበትም።

 

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ወልቃይትን ወሮ ከያዘበት ከዛሬ አርባ ሶስት ዓመታት (፲ ፱ ፻ ፸ ፪ ዓ. ም. – [1979−1980 በአውሮፓዊያን አቆጣጠር]) ጀምሮ፤ ወልቃይትን፣ ራያንና ጠለምትን ከሰማይ በታች የሚችለውን ሁሉ በማድረግ፤ የትግራይ አካል አስመስሎ ሲያስቀምጣቸው፤ በነዋሪዎች ላይ የኅብረተሰብ ምሕንድስና ሠርቷል። እንግዲህ ይሄን የፈጠራ ትርክቱን ይዞ፤ ውስጥ ለውስጥ የትግራይ አካል አለመሆናቸውን እያወቀ፤ ባደባባይ ግን የትግራይ አካል ናቸው በማለት፤ ባገር ቤት ውስጥ በሕገ−መንግሥቱና በየቦታው ባስቀመጣቸው ተቀጣሪ ሆድ አደር ባለሙያዎቹ፤ በውጪ አገራት ደግሞ በዲፕሎማሲዊ ሥራው፤ “ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ!” ጨዋታ ይዞ ቆይቷል። ለመሆኑ የዚህ ትርክቱ መሠረት ምንድን ነው? ሕጋዊነትስ አለው ወይ? ታሪካዊ መረጃና አግቦትስ ይገኛል ወይ? ስለሕጋዊነቱና ስለ ታሪካዊ መረጃው ብዙ የተባለ ስለሆነ፤ እኒያን አዋቂዎች መመልከቱ የበለጠ ይረዳል። እኔ እዚህ ላይ ላቀርብ የፈለግሁት፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መጀመሪያ ወልቃይት ሲገባ፤ የነበረውን እውነታ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ወልቃይት ሲገባ፤ በቦታው ነበርኩ። ይህ የሆነው የዛሬ አርባ ሶስት ዓመት ነበር። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የታጠቀ ክፍል፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሕአሠ)፤ አባል ሆኜ፤ በወልቃይት እንቀሳቀስ ነበር። በወልቃይት ከተመደበው የሠራዊቱ ክፍል፤ አብዛኛው በበለሳ ሠራዊቱ ሊያደርገው  ካቀደው የማጥቃት ዘመቻ ጋር በተያያዘ፤ ለእርዳታ ወደዚያ ተልኮ ነበር። ይሄንን የሠራዊቱ አብዛኛው ክፍል ወደ በለሳ መሄድ በሰላዮቹ የተረዳው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ቁጥሩ እጅግ የበዛ የታጠቀ ክፍሉን ወደ ወልቃይት ላከ። በወቅቱ ቦታውን ክፍት ላለማድረግ ወልቃይት የቀረነው በጣም ትንሽ ቁጥር ያለን የኢሕአሠ ታጣቂዎች (ከሃያ አምስት የማንበልጥ)፤ ከሁለት ተከፍለን ነበር። በዚያ ወቅት ጠገዴ በኛ ቁጥጥር ሳይሆን፤ በደርግ እጅ ነበር። አውራ በኛ እጅ ነበር። በጠገዴ በኩል ያለውን ለመከታተል አንዲት ትንሽ ቡድን (አስራ አንድ ጓዶችን የያዘች) በጠለሎ እንድትዘዋወር ተደረገች። ሌላዋ እኔ ያለሁባት ክፍል (አስራ አራት ጓዶች)፤ በሶስቱ ብላምባዎች አድርገን ወደ ቀብትያ ተንቀሳቀስን። የቡድኗ የፖለቲካ ኃላፊ ነበርኩ። ከቀብታያ ዋና ከተማ፤ ከአዲ ሕርጻን ወደ ሑመራ በሚወሰደው መንገድ ወጣ ብለን በምንንቀሳቀስበት ወቅት፤ አንድ የአካባቢው አርሶ አደር ወደኔ ጠጋ ብሎ፤ “አያ ጓዱ፤ እንዲህ ወደ አዲ ረመጥ የመጣው ነፋስ እንዲያው ደስ አይልም!” አለኝ። ከጓዶች ነጠል አድርጌ ወስጄ፤ “ምን ወሬ ተገኘ?” ስል ጠየቅሁት። “ኧረ! ይቺ የከብት ሌባ አዲ ረመጥ ገባች!” አለኝ። ይሄን አባባሉን ልብ በሉልኝ!

ይሄን ስሰማ፤ በጠለሎ ያለችው ቡድን አደጋ እንደተጋረጠባት ገባኝ። ዋናው ግን፤ ወደ ቆላው መዘጋ ሄጄ፤ ጠለምት ካለው ዋናው የሠራዊቱ ክፍል ጋር ግንኙነት መፍጠር መሆኑን አሰብኩ። በኛና በቆላው መዘጋ መካከል፤ ትሕነግ ከትግራይ ወደ ወልቃይት የምትመጣበት ዋናው መንገድ አለ። ከሁሉ በላይ አስጊው ደግሞ፤ ከቆላው መዘጋ ወደ ደጋው ወልቃይት ለመውጣት የምትጠቀምበት ቀጥ ያለው የብላምባ ዳገት በር፤ የኛም ወደ መዘጋ መውረጃ የዳገት በራችን መሆኑ ነው። ይሄ የማያፈናፍን ግጥጥሞሽ ሊያመጣ እንደሚችል አውቃለሁ። በፍጥነት አዲ ሕርጻን ከተማዋን ወደ ግራ ትተን፤ ከከተማዋ አጠገብ ያለውን ቁጢጥ ብሎ የቆመ ትንሽ ተራራ ታከን ለማለፍ ገሰገስን። ሁለት ትግርኛ ተናጋሪዎች አብሪ አድርገን፤ ሌሎቻችን የማታ  ልብሳችን የሆነችውን ቁራጭ ነጠላ (ኩሽክ) ጠመንጃችንን በሚደብቅ መልኩ ለብሰን፤ በጣም በተራራቀ ሁኔታ አንዳንድ ሆነን እየተንጠባጠብን ገፋን። ተራራዎ አጠገብ ስንደርስ፤ “ጠጠው በል! ማኒሃ!” (ቁም ማነህ!) የሚል ትዕዛዝ ከተራራው አናት ላይ ከቆሙት የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ታጣቂዎች፤ ለሁለቱ አብሪዎቻችን ተወረወረ። እነሱም በትግርኛ፤ “ንዕና ኢና!” (እኛ ነን!) ብለው ወደኋላ በማፈግፈግ ወደኛ ተቀላቀሉ። ጠባቂዎቹ፤ አርሶ አደሮች ናቸው ብለው አላስተባቋቸውም። አካባቢውን በደንብ ስለምናውቀውና፤ ጠባቂዎቹ ሁለቱን ጓዶቻችንን እንጂ ሌሎቻችንን ስላላዩን፤ በሰርጓዳው በኩል አድርገን መንገዱን ቶሎ በማቋረጥ፤ በቀብትያና በአዲ ረመጥ መካከል የሚኖሩትን ፊታውራሪ የሺወንድምን ለማግኘት፤ ባፋጣኝ ቀብትያን ለቀን ወደ ሾኔ የሳቸው መኖሪያ ቤት አመራን። እዚያ ስንደርስ ፊታውራሪ የሺወንድም በጣም ደስ አላቸው።

እሳቸው በልጅነታቸው ካባታቸው ጋር እዚሁ ሾኔ በገደሉ መሽገው ጣልያንን እንዳላስገቡት ነግረውኝ፤ “አሁን በዚህ በቆላው በዱሩ ምሽግ መያዝ አለብን! ሸመዶቼን አሰባስቤ፤ ይቺን የከብት ሌባ ድርሽ አናስደርጋትም!” በማለት፤ የራሳቸው የመከላከል ዕቅድ አውጥተው፤ እኔንና ጓዶቼን ሊያግባቡ ሞከሩ። እኔ ደግሞ ያለብኝን ኃላፊነት፣ የሠራዊቱ እኔን መረጃ እንድሠጣቸው መጠበቅና፣ በጠለሎ የሚንቀሳቀሱ ጓዶችን ጉዳይ አንስቼ፤ ላግባባቸው ሞከርኩ። አልተዋጠላቸውምና፤ አድሮ ሃሳቡን ይለውጣል በማለት፤ ከሳቸው ቤት አሳደሩን። በመጨረሻ ከኔ ዕቅድ እንደማልወጣ ሲረዱ፤ “በሉ እኔን አስቡኝ!” ብለው ሸኚ ሠጥተው ቆላውን ወርደን፤ ብላምባ ላይ እንድንወጣ፣ ከዚያ የማገኛቸውን ሰው በጥንቃቄ እንድቀርብ፤ ነገሩኝና ተሰነባበትን። ብላምባ የማገኛቸውን ሰው ስጠጋቸው፤ በድንጋጤ፤ “ለምን መጣህብኝ! የሷኮ ሠራዊት ቁጥር ስፍሩ አይታወቅም! በየቀኑ ሲጎርፉ ነው የሚውለው! በል ቶሎ ምግባችሁን ያዙና ከዚህ ጥፉልኝ!” በማለት ፍርሃታቸውን ገለጡልኝ። ወዲያው ሴቶቹ፤ “እኒህስ የኛዎቹ ናቸው!” ብለው በጥድፊያ ምግባችንን አዘጋጁልን። ከመካከላቸው አንዷን ትልቅ ሴትዮ ስለሁኔታው ጠየቅኋቸው። እሳቸውም፤ “አዬ ጓዱ፤ ምኑን ብለኸው ነው! ትናንት አዲ ረመጥ ገበያ እንድንገኝ ትዕዛዝ ሠጥተውን፤ እዚህ ገበያው ላይ ሰው በተሰበሰበበት፤ አዋጅ ነገሩ።” አሉኝ። በዚህ ወቅት ሌሎችን ቶሎ ቶሎ ምግባችን እንዲያዘጋጁልን አዘዋቸዋል።

“ምን ነበር አዋጁ?” ብዬ ጠየቅኋቸው። “አዬ አያ ጓዱ፤ ‘ከዛሬ ጀምራችሁ ትግሬዎች ናችሁ! ለቅሷችሁን በትግርኛ ማድረግ አለባችሁ! ዘፈናችሁን በትግርኛ ማድረግ አለባችሁ! አቤቱታ ለኛ ነው በትግርኛ ጽፋችሁ የምታቀርቡት!’ አሉን። ደሞ ማነው ትግሬ ናችሁ ብሎ የሚያዘን! ማነው በማናውቀው የትግርኛ ዘፈንና የትግርኛ ለቅሶ እንድናደርግ የሚያዘን! መንግሥት ይሁኑና ከከተማቸው ይቀመጡ! ግብር እንከፍላለን! እኛ ዳቧቸውን አልቀማናቸው! ሻሂያቸውን አልወሰድንባቸው! አልደረስንባቸው!” በማለት ንዴታቸውን ዘረገፉት። ማመን አቅቶኛል። በአዋጅ ትግሬ መሆን ምን ማለት እንደሆነ፤ ማሰቡ ቸገረኝ። ግን ይሄን ነው ወልቃይት ሲገቡ ያወጁት። የሕዝቡን ማንነት በአንድ አዋጅ መቀየር! የኅብረተሰብ ምሕንድስና ያልኩት ይሄን ነው። ተመልከቱ፤ ያኔ ገና ተከዜን መሻገራቸው ነው። ፓርላማ የለም። ሕገ−መንግሥት የለም። ወልቃይት የተወሰደው፤ አዲስ አበባ ከመግባታቸው ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት ነው።

ወዲያው ምግባችን ስለደረሰና ቶሎ ቦታውን ለቀን እንድንሄድ መፈለጋቸውን ስለተረዳሁ፤ ብዙ ዝርዝር ሳልጠይቃቸው ተሰናብቼ ወደ ቁልቁለቱ ገሰገስን። አጋጣሚ ሆኖ፤ እኛ በደረሰንበት ጊዜ የትሕነግ ሠራዊት በቦታው አልነበረም። ወርደን መዘጋ ገባን። መዘጋ ሰሊጥ እየበላን ወደ ጠገዴ አቅጣጫ በፍጥነት ተጓዝን። መሸት ብሎ ወደ ሸረላ ስንጠጋ፤ የተኩስ ልውውጥ ሰማን። የኛ ጓዶች ከትሕነግ ጋር መገናኘታቸው መሆኑን ማወቁ አላስቸገረንም። አስራ አንድ ጓዶች ከሁለት ሺህ በላይ የተገመተን የትሕነግ ታጣቂ ገጥመዋል። ስንገሰግስ፤ ከበለሳ የኛ ጓዶች ተመልሰው እነሱም ወደ ተኩሱ ሲሮጡ ተገጣጠምን። ሁኔታውን ከኛ በኩል አስረዳናቸው። መረጃው ደርሷቸው ቶሎ ገስግሰው እንደመጡ ነገሩን። እነሱ አንድ መቶ ይሆናሉ። በደስታ በሩጫ ተራራውን ወጥተን ጫፉ ላይ ስንወጣ፤ ካስራ አንዶቹ ጓዶቻችን ጋር ተገናኘን።

ፊታቸው ፈግቷል። የደስታ ሲቃ ይዟቸዋል። እነሱም፤ “ከአዲ ረመጥ እየተግተለተለ የሚመጣ ሰልፍ ዓየን። ግራ ገብቶን፤ ለሁሉም ቦታ እንያዝ አልንና፤ መሸግን። ሰልፉ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ሲሆን፤ እንደጎርፍ ቅደምና ተከተል ይዞ የተደራረበ ነበር። እየቀረቡ ሲሄዱ፤ የታጠቁ እንደሆኑ ገባን። ከተ.ሀ.ሕ.ት. (የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር − ትሕነግ) ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችል አውቀናል። ማፈግፈግ ፈለግንና፤ የለም! የኛን ቁጥር ስለማያውቁ፤ ለምን አንተኩስባቸውም! አልን። የመግደያ ሜዳው ላይ ሲገቡ፤ ተኩስ ከፈትንባቸው። እንዳልጠበቁት ግልጥ ነበር። ሲደናበሩ፤ የምንችለውን ያህል ረፍርፈን ወደ ሸረላ አቀናን። ከኛ በኩል ምንም ጉዳት አልደረሰም። የትስ ብለው ይተኩሳሉና!” አሉን። ሸረላ ተኩስ ከተከፈተበት ወደ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራማ ገጽ አለው። “እነሱ ባሉበት ሆነው ምሽጋቸውን ማጠናከር ያዙ። እኛ ተራራማውን ቦታ ተቆጣጥረን እነሱን መከታተል ያዝን።” በማለት ያለፉበትን ሁኔታ አስረዱን።

በበነጋታው ሸረላ ላይ ከባድ ጦርነት ተድርጎ፤ ከኛ በኩል አስራ ሰባት ቁስለኞች (እኔን ጨምሮ) ከነሱ ደግሞ፤ ከአራት ቀን በኋላ፤ “ቅበሩ!” ተብለው የታዘዙ አርሶ አደሮች እንደነገሩን፤ ሰማንያ አስከሬኖችን ቀብረዋል። መብዛታቸው አይገርምም። ምክንያቱም፤ የግጥሚያ ስልታቸው ውጤት ነው። እኔ ባደፈጥኩበት ጉብታ፤ ትንንሽ ልጆች በገፍ ሲግተለተሉ መጡ። እስኪቀርቡ ድረስ፤ ከላይ እየተመከትን ዝም አልናቸው። ከኋላ ያለ አንድ አዛዣቸው፤ “ንቅድሚት! ወዲዛ ሸራሙጥ!” ሲል ሰማሁት። በጣም የሚያሳዝን ነበር። እሱ የትግራይ ወጣቶችን ለመማገድ ግድ የለውም። ከኋላ ሆኖ “ወደፊት! የሸርሙጣ ልጅ ሁላ!” ይላል። ወዲያው እሱን ስመታው አልወደቀም ግን እጆቹን በፊቱ ላይ ከልሎ፤ ወደኋላው ሩጫ ያዘ። እንደመታሁት እርግጠኛ ነበርኩ። ወጣቶቹ ረገፉ። ተከታትለን ሶስት ሆነን በመገስገስ፤ ከምሽጋችን በጣም ራቅን። ያን ጊዜ እኔ ቆሰልኩ። ሁለቱ ጓዶቼና እኔ ወደኋላ ተመለስን። በዚህ ዓይነት ሁለቱም ወገን ባለበት ቆመ። ቁስለኞች ወደ ኋላ ተላክን። ይሄንን ጦርነት

ይህ ነበር የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የወልቃይት አገባብ። አንባቢ እንዲያውቅ የፈለግሁት፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ በፖለቲካ ግቡ ተመርቶ፤ አንድም የሱዳንን በር ለማግኘት፤ ሌላም ለም መሬት ለመውሰድ ሲል፤ ያደረገው ወረራ መሆኑን ነው። ከሕዝቡ ማንነትና ፍላጎት፣ ከመሬቱ የመልክዓ መድር አቀማመጥ ወይንም የታሪክ መሠረት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በወቅቱ የወልቃይት ሕዝብ ራሱን አማራ እንጂ፤ ትግሬ ብሎ አልቆጠረም። አንድ ምሳሌ ላቅርብ። እኔ በነበርኩበት ወቅት፤ አንድ ሰው ሞቷል ብሎ ከጉብታ ላይ ነጋሪ ከወዲያ ሲያሰማ፤ “ሰው ነው ትግሬ!” የሚል ከወዲህ ተቀባይ ይጠይቃል። ይህ ማለት፤ ሰው የሚሉት ወልቃይቴውን ነው። ትግሬ የሚሉት መጤ የሆነውን ትግሬ ነው። ትግሬዎች ሥራ ፍለጋ ለተወሰነ ጊዜ መጥተው፤ በወልቃይት ተቀጥረው ይሠራሉ። ገንዘባቸውን ሰብስበው፤ ሥራው ሲያልቅ ወደ ትግራይ ይመለሳሉ። አንዳንዶቹ ይጥማቸውና፤ ወይ ተጋብተው አለያም ቤተሰባቸውን ይዘው መጥተው ወልቃይት ይሠፍራሉ። ማንም ከልካይ አልነበረባቸውም። ይህን ነው፤ አማራውን ወልቀቴ ሰው በአዋጅ ገድለው፣ ትግሬነትን በአዋጅ አስፍረው፣ ወልቀቴን ትግሬ አድርገው ፈጥረው፤ ወልቃይትን የትግራይ መሬት ያደረጉት። ይህ የኅብረተሰብ ምሕንድስና ነው። ፈጣሪ መሆን!

በመጨረሻ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ በትውልድ ማንነት የአገራችን ኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት መሾፈሩን ከጀመረበት ሰዓት አንስቶ፤ መፈራራትና መጠላላት፣ በየጎጆው መደበቅና “እኛ” እና “እነሱ” የሚል ክፍፍልን ዘርቶ ወደማያልቅ መተላለቅ ደንጉሮናል። ከዚህ በቀላሉ የማንወጣበት አዘቅት ውስጥ ሆነን፤ አንዱን ወይንም ሌላውን፣ በዚህ ወይንም በዚያ መንገድ እያልን ስንዳክር፤ በመካከላችን ያለው የተካፋፈልንበት ምክንያት እየበዛ፤ ርቀቱ እየከፋ፤ “ደህና ሁኚ እትዮጵያ!” ልንል አንድ ሐሙስ ቀርቶናል። ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሥልጣኑን የተረከበው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ ከተረከበበት መንገድ በከፋና ጋጠ ወጥ በሆነ መንገድ አባብሶ፤ እየገዛ ነው። አሁን አማራውን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር አጠፋለሁ ብሎ ዘምቶበታል። ለሆዳቸው ያደሩ የ”አማራ ብልፅግና!” ነን ባዮች፤ መንገድ መሪና ጠራጊ ሆነው እያገለገሏቸው ነው። የአማራዎች ጠላት፤ አንድም ኦነግ ብልፅግና፤ ሌላም የ“አማራ ብልፅግና” ናቸው። ኦነግ ብልፅግና ጠላት ነው። የ“አማራ ብልፅግና” አሾክሻኪ ነው። እናማ! “ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው! አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው!” የተባለው ለቀልድ አይደለም።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop