በስዊድን የኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ የስነጽሑፍ ክፍል የቀረበ አገር ሳይኖረን ወደብ አይመረን!

ሰኔ 18 ቀን 2015 ዓም(25-06-2023)

ዓለም ከሦስት እጅ በላይ በውሃ የተሸፈነች መሆኗንና የሰው ልጅ ኑሮም ከውሃ ጋር በተያያዘ  እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚክድ ፍጡር አለ ተብሎ አይታመንም።የውሃን ጥቅም በሚገባ የሚያውቀው ምላሱን ለማድረቅ፣ጥሙን ለመቁረጥ  አንድ ጠብታ ውሃ ለማግኘት የሚንከራተት የበረሃማ  ከባቢ ነዋሪ የሰው ልጅ ብቻም ሳይሆን ውሃ ለማግኘት ወቅቱን ተከትለው አገር አቋርጠው የሚሄዱ  እንስሳት፣አውሬዎችና አእዋፎች፣  ጭምር ናቸው። የሰው ልጅም ሰውነቱ ሶስት አራተኛው(3/4) ውሃ መሆኑን የስነፍጥረት ሊቃውንቱ በጥናታቸው አረጋግጠዋል። ከመጠጣት ባለፈ ካለውሃ አርሶና ተክሎ ፣አርብቶ መብላት አይችልም።ለዚያም ነው ውሃ ህይወት ነው፣ካለውሃም ህይወት የለም የሚባለው።

ሌላው አስገራሚ የሰው ልጅ ችሎታ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትን ነፍሳት በተለይም አሳና አሳ መሰሎችን ተመልክቶ  በውቅያኖስና በባሕር የተለያዩ ህዝቦች ለመገናኘት ያስቻላቸውን የመጓጓዣ  መስመር የመዘርጋቱ ጥበብ ነው።በዚህ የባሕር ጉዞ የኤኮኖሚ፣የባሕልና የእውቀት ልውውጦች ለማድረግ ችሏል።የአዬርና የዬብስ  መጓጓዣዎች ሳይኖሩ በጥንት ጊዜ የመጀመሪያውና ብቸኛው የተራራቁ ሕዝቦች መገናኛው ብቸኛ መንገድ የባህር ላይ ጉዞ ነበር። እንደ ህብረተሰቡ ንቃትና የእድገት ደረጃ  በከባቢ ወንዞችና ኩሬዎች አሳ ለማጥመድ ሲል ዋናን ከመማር ባለፈ ፣ ወደ ትናንሽ ታንኳዎች ተሻግሮ፣ከቅርብ ወደ እሩቅ ቦታ ለመድረስ ፣በነፋስ አቅጣጫ የሚቀዝፉ ድንበር ተሻጋሪ  ጀልባዎች፣ከዚያም  በሞተር የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችና ሰርጎ ገብ (ሰብመሪንስ) በመጠቀም አሁን ካለንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።በመጀመሪያው ላይ በሰላማዊ ጉዞ የግንኙነትና የንግድ መስመር ላይ ያተኮረው የባሕር ጉዞ ቀስ በቀስ እያዘናጋና እያለማመደ አገራትን ለመውረር የሚያስችል የጦር ሃይል መሣሪያ  ለመሆን በቅቶ ለአገራት መወረርና ቅኝ ግዛትነት የውሃ ላይ ጉዞ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።ለወረራ የሚጋለጡት በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ አገሮች ቢሆኑም፣ከወደብ ተሻግሮ ወደ ውስጥ ሰርጎ በመግባት ወደብ አልባ የሆኑትንም አገሮች ለመውረርና ለመቆጣጠር ተችሏል።ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት የአውሮፕላን ጉዞ ሳይጀመርና እንደ አሁኑ ሳያድግ የአገራት በተለይም የቀድሞ ታላላቅ መንግሥታት(ኢምፓዬርስ)፣የሮማ፣የፋርስ፣የቻይና፣የግሪክ፣የአክሱም ከዚያም በዃላ የተነሱት የኦቶማንና ሌሎቹ  ድንበራቸው የሰፋውና የነበራቸው አቅም የሚለካው በባሕር ሃይላቸው ጥንካሬ ነበር። የአሁኖቹ አውስትራሊያ፣አሜሪካ፣ኒውዝላንድ፣ካናዳ የመሳሰሉት አገራት በእንግሊዞች በተደረገ የመርከብ ጉዞ የቅኝ ግዛት ወረራ ውጤቶች ናቸው።ነባሩን ሕዝብ ከመጨረስ ባለፈም የቦታውን ስም በመቀዬር የወራሪው እንግሊዝ  የትውልድ ሃረግ ያገሩ ባለቤቶች ሆነዋል።የወረራውን መጠን ለመግለጽ “The Sun Never Set in The British Empire”የሚለውም የመጣው ያንኑ የእንግሊዞችን  የወረራ ስፋት ለማሳዬት ሲባል ነው። እንግሊዞችም ብቻ ሳይሆኑ ፖርቱጋሎች፣ኔዘርላንዶች፣ጀርመኖች፣ፈረንሳዮች፣እስፓኒሾች፣ቤልጅጎች፣ጣልያኖች በነበራቸው የመርከብ አቅምና  አሰሳ በአፍሪካ በደቡብ አሜሪካ፣በኤሽያ፣በካሪቢያን—ወዘተ ብዙ አገሮችን በቅኝ ግዛትነት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ይዘዋል።

አገራትን ለመውረር የባሕር በርና የባሕር ሃይል ጠቃሚ እንደሆነ ሁሉ ላለመወረርም የባሕር በር ያላቸው አገራት የባሕር ሃይል ማቋቋሙ የማይዘነጋ ግዴት ሆኖ መጥቷል።ስለሆነም የባሕር በርንና የባሕር ሃይልን ጠቀሜታ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምራ የምታውቀውና ያለፈችበት የታሪክ ጉዞ ነው።ኢትዮጵያ አሁን ታላላቅ አገራት ተብለው የሚመደቡት አገራት ሳይሰለጥኑ ቀድማ የሰለጠነች፣እነሱ በባሕር ላይ መጓጓዝ ቀርቶ በመሬት ላይ መኖር ሳይጀምሩ ቀድማ የከባቢ የዓለምን ክፍል ለመቆጣጠር የሞከረች፤ባለ ብዙ ወደቦችና የባሕር ሃይል ባለቤት የነበረች አገር ናት። ዘይላ፣አዶሊስ፣ምጽዋ፣አሰብ፣በርበራ፣ጅቡቲ፣ከነበሯት የባሕር በሮች የሚታወቁት ናቸው።የአገር ስፋት፣እድገትና ጥንካሬ ወይም ውድቀት ከመንግሥት ጥንካሬ ጋር የተያያዘ ነው።የመንግሥት ጥንካሬ ደግሞ ከሕዝቡ ድጋፍና እውቅና ጋር ይያያዛል።የሕዝቡን ተቀባይነትና ቅቡልነት ለማግኘት የመንግሥት ታማኝነትንና አገር ወዳድነትን ይጠይቃል።

ከላይ እንዳሳዬነው የአገራት እድገት፣ስፋትና ጥንካሬ ወይም ውድቀት ከመንግሥቱ ጥንካሬና ድክመት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥታት በነበሯት ጊዜ የነበራት ክብር በታሪክ መጽሃፍት በሰፊው ተጽፎ ይገኛል።ጊዜ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ መጠን በጊዜም የአገራት አቅምና እድገትም አብሮ ይለዋወጣል።በታሪክ ታላቅ ተብለው የሚሞገሱ አገሮች አሁን ላይ አንሰውና ኮስሰው ይገኛሉ።ከነዚያም አንዷ ኢትዮጵያ አገራችን ነች።ለመኮሰሷ ዋና ምክንያት የሆነው በውስጧ የሚኖሩ ልጆቿ ለሥልጣን በሚያደርጉት ሽኩቻና በዃላ ቀር አስተሳሰብ ተተብትበው ለእድገት አመች የሆነ ሁኔታ ለመፍጠር አለመቻላቸው ነው።ከመገንባት ይልቅ የተገነባውን በማፍረስ ላይ በመጠመዳቸው ነው።ፉክክራቸው አገር በማሳደጉ ሳይሆን አገር በመዝረፍ፣አንዱ በሌላው ላይ ገዝፎ ለመታዬት በሚያደርገው የጉልበት ዘመቻ ላይ በማተኮሩ ነው። የውስጡን ንትርክና የስልጣን ግብግብ ተከትሎ የውጭ ወራሪዎች በልዩ ልዩ ምክንያት እዬገቡ ያለውን ልዩነት እያሰፉ ችግር መፍጠራቸውና የሕዝቡ ኑሮ በጦርነት እንዲሸፈን ማድረጋቸው ለምታደርገው እድገት ተጨማሪ እንቅፋት ሆኗል።ያንን የውጭ ተጽእኖና ጣልቃ ገብነት ተከትሎ የዘመነ መሳፍንት መምጣት ከነበረችበት ከፍታ ላይ አውርዶ የከሰከሳት አንዱ ምክንያት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ቃል በወዳጅነት አደባባይ ስለተካሄደው ወለፈንዴ ተወኔት የግል ምልከታ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

ነጻነቷንና አንድነቷን አስከብራ ለተወሰኑ ዓመታት እረገብ ብሎ የነበረው የእርስ በርስ ግጭት በማይተኙላት የአውሮፓ ጠላቶቿና የውስጥ ተባባሪዎቻቸው ሴራ ድንበሯ ሲደፈር ከጎረቤት ሕዝቦች ጋር በቅራኔ ግጭት ውስጥ መግባትና አልፎ አልፎም በጦር ሜዳ መሰለፍ ለእድገቷና ለልማቷ መዋል  የነበረበት ሃብትና የሰው ሃይል በከንቱ እንድታፈስ ከመሆኑም በላይ የዃላ ዃላም የነበራትን የግዛት አንድነት እንድታጣ አድርጓታል።የሰላም ኑሮ እንዳትኖር   ዘላቂ የጎሳ  በሽታ ተክለውባታል።

ከጎረቤት አገራት የበለጠው ትልቁ መቅሰፍት በራሷ ልጆች ከሃዲነት የተፈጸመባት በደል ነው።በልጆቿ ክህደት ዳርድንበሯ ተደፍሮ የነበራትን የባሕር በር ተነጥቃ በምዕራባውያን ቁጥጥር ስር ባሉ የደቃቃ አገሮች ጥገኛ ሆናለች።ያች የብዙ ወደብ ባለቤት አገር ተከርችማ የደረቅ መሬት እስረኛ ሆናለች።የንግድ ልውውጧን በሌሎች ፈቃድና ፍላጎት እንዲሁም ያላትን መጠነኛ ገቢ እዬከፈለች እንድትኖር ተፈርዶባታል።ከዚህም በላይ ለቀሩት የአፍሪካ አገራት የአንድነትና የነጻነት ምሳሌ የሆነችው አገር የመገነጣጠል፣የድህነት፣የጭካኔ፣የጭፍጨፋ፣የስደት፣የርሃብ ምሳሌ ሆናለች።አፍሪካን አንድ ለማድረግ የተሳካ ሥራ የሠራችው ኢትዮጵያ፣ የራሷን አንድነት ለማስጠበቅ ተስኗታል።

በውጭ ሃይሎች ቅስቀሳና እርዳታ ሕዝቧ በጎሳና በሃይማኖት ፣በቋንቋና በሰፈር ማንነት ተለያይቶ አገሩን አፍርሶ አገረቢስ እንዲሆን የፈረዱባት ያስተማረቻቸው የራሷ ልጆች ናቸው።በነዚህ ከሃድያን ከተፈረደባት ሃምሳ ዓመት ሊሞላው ነው።የነበረው ሥርዓት ሁሉንም የበደለ መሆኑ እዬታወቀ የአንድ ማህበረሰብ በተለይም የአማራው ጥፋት ተደርጎ አማራው እንደ ዜጋ ቀርቶ እንደሰው እንዳይኖር ተፈርዶበት በነዚሁ አገር ጠሌዎች እንደ አውሬ እዬታደነ ይገደላል ፣ይፈናቀላል፣ሃብት ንብረቱን ብቻ ሳይሆን በማህጸን ውስጥ ያለ ጽንሱን በጭካኔ ካራ ይነጠቃል።ለዚህ ሁሉ የዳረገው አገር ወዳድ በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ ከሌሎቹ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ኖሮት አይደለም።

ኢትዮጵያዊ ስሜት የሌለው ቡድን ሥልጣኑን በእጁ ካስገባ በቀላሉ እንደማይወርድ ባለፉት 32 ዓመታት አይተናል።በስልጣኑ ላይ ለመቆዬት ከቻለ በማታለልና በመደለል፣ካልቻለም በጉልበት ከፋፍሎ እዬገደለና እያጋደለ ለመኖር ይመርጣል።ለእንዲህ አይነቱ ጸረሕዝብ ቡድን ሥልጣኑን ከሚያጣ ሕዝብና አገር ገደል ቢገቡ ምርጫው ነው።ከትልቅ አገር ዜግነት ይልቅ የትንሽ መንደር ምስለኔ መሆኑን ይመርጣል።ያንንም ለማግኘት የማይፈጽመው ወንጀልና የማይጠቀምበት የማጭበርበሪያ ዘዴ አይኖርም።አገር አፍራሹ ቡድን የራሱን ኑሮ በውጭ አገር አደላድሎ ለመሸሽ የተዘጋጀ ሆኖ ለእልቂት የሚዳረገው የፈረደበት በስሙ የሚጠቀምበትና መሣሪያ ያደረገው በጎሳ ማንነቱ የሚነዳውን መንጋ ነው።ኢትዮጵያ ብትፈርስ ሁሉም  ጎሳ እርስ በርሱ ለማያባራ ጦርነት ይዳረጋል እንጂ በሰላም አይኖርም።

ኢትዮጵያ ላይ የመፈራረስ ደመና ካንጃበበ ውሎ አድሯል።ሕዝቡ በድህነት አሮንቋ ውስጥ ተዘፍቋል፤ወጣቱ ተስፋ ቢስ ሆኖ ለአደጋ ተጋልጧል፣ለመኖር ሲል በእኩይ ተግባራት ላይ እንዲውል፣ በዬአረብ አገሩ ለባርነት ኑሮ ለመሰደድ ተገዷል።የማህበረሰብ እሴቶች በሙሉ ተፍቀው የአውሬነት ዝንባሌ እየተስፋፋ መጥቷል።ሁሉም እራሱን ለማዳን እንጂ አብሮ ለመዳን አያስብም።ቤተ እምነቶችና የእምነት አባቶች ሳይቀሩ ለሰይጣናዊ ሥርዓት አጎብድደዋል።ቤተእምነቶቻቸው ሲወድሙና ምእመናን ሲጨፈጨፉ ድምጻቸውን ለማሰማት አልደፈሩም፤ከምእመናኑ ይበልጥ የፍርሃትና የአድርባይነት ቆፈን ይዟቸዋል።ይባስ ብሎም ከወንጀለኛው የጎሰኞች ስርዓት ጋር ሽርጉድ ይላሉ።እነዚህ ሁሉ የአገር መፍረስ ምልክቶች ናቸው።

ይህንን የአገር መፍረስ የማይቀበል ግን አልጠፋም፤አርፎም አልተቀመጠም።አብዛኛው በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የአማራው ማህበረሰብ ጥቃቱ ሲበዛበት እምቢ በማለት ስርዓቱን ለማሶገድ ቆርጦ መነሳቱን በልጆቹ በፋኖ በኩል እያሳዬ መጥቷል።በዚህ የተደናገጠው አገር አጥፊው የኦሮሙማ መራሹ ቡድን አማራ ነው የተባለውን ምሁር፣ነጋዴ፣ጋዜጠኛ፣ተማሪ፣አስተማሪ፣ልጅ አዛውንት ሴት ወንድ ሳይለይ በመግደልና በማፈን የጭካኔ መጠኑን ለማሳዬትና ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ሞክሯል፤እዬሞከረም ነው።ግፍና በደሉ በጨመረ ቁጥር ግን የመውደቂያው ቀን እዬተቃረበ መምጣቱን አልተገነዘበም።

እብሪት የነፋው የኦሮሙማ ቡድን ኢትዮጵያን አፍርሼ የራሴን ኦሮሙማ የተባለች አገር እመሰርታለሁ በሚል ቅዠት ያገሪቱን ነባር ቅርሶች እዬሸጠና በወለድ አግድ እያሲያዘ ቤተመንግሥት እገነባለሁ ይላል።ለዚያም ነባሩን ሕዝብ ከኖረበት ቦታ ሕገ ወጥ በማለት እያፈናቀለ ሕጋዊ ተፈናቃይ አድርጌአለሁ በማለት በድፍረት ይመጻደቃል።የጥንቱ የሮማ ንጉስ ኔሮ የእብሪቱ ደረጃ መረን ሲለቅ ፈጣሪን ከመፈታተኑ ባለፈም  ዋና ከተማዋን በእሳት እንዳጋዬና በሕዝቡ ቅልቂት ላይ መዝናናቱን ተከትሎ የእርሱም መጨረሻ እንዳላማረ ታሪክ ይናገራል።የእብሪተኞች መጨረሻው ይኸው ነው።የኦሮሙማ መራሹ ቡድንም መጨረሻው ከዚህ ቢከፋ እንጂ ያነሰ አይሆንም።በጫረው የጎሳ ክብሪት እራሱ ተቃጥሎ አመድ መሆኑ አይቀሬ ነው።ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሞክሮ የተሳካለት የለም።ይብዛም ይነስም፣ትጥበብም ትስፋም ኢትዮጵያን ከተመሰረተችበት መሬት ላይ የሚፍቃት ሃይል አይኖርም።በአማራው ላይ የሚደርሰው በደል ተጠራቅሞ  ምናልባትም እንደ እስራኤል ለማደግና ለመከበር  ምክንያት ሊሆንላት ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምነው ነገረ ሥራችን ሁሉ ላይ ላዩን ሆነ? - ጠገናው ጎሹ

የአማራው መነሳሳት ምን ሊያስከትልበት እንደሚችል የተገነዘበው የአገር አጥፊው ቡድን በሃይልና በሴራ ሂደቱን ለማጨናገፍ የማይገለብጠው ድንጋይ የለም።ኢትዮጵያዊ በተለይም አማራው ለአገሩ ያለውን ፍቅር ስለሚያውቅ፣በሴራ የተነጠቀውን የባሕር በሩን በሚመለከት ያለውን ስስ ብልቱን መጠቀሚያ በማድረግ የአሰብ ወደብን አስመልስልሃለሁ የሚል አዲስ ነጠላ ዜማ አውጥቶ ለማስጨፈርና አጃቢው ለማድረግ ዳር ዳር እያለ መጥቷል።ይህንን ቅኝት የጀመረው ከአሜሪካኖቹ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ከፍታ ለአሜሪካኖች ያላጎበደደውን ያገሪቱን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን ለማሶገድና በተላላኪ መንግሥት ለመለወጥ ነው ።አሜሪካኖቹና ምዕራባውያን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለመዋጥና እያደገ ከመጣው የቻይናዎች የኤኮኖሚና የፖለቲካ ትስስር ለማላቀቅ የሚያደርጉት የጥቅም ግጭት እንጂ ለኢትዮጵያ አስበው እንዳልሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው ይገባል።ኤርትራ እንድትገነጠል፣አገራችንም በወያኔ መሪነት በጎሰኞች ክንድ እንድትወድቅ ያደረጉት በአሜሪካ ግንባር ቀደምትነት የሚሽከረከሩት እነዚሁ የምዕራቡ ዓለም አገሮች ናቸው።የኦነግ መራሹ ቡድንም ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ቅድመ ዝግጅትና ስልጠና የሰጡት እነዚሁ ናቸው።አሜሪካ በተለያዬ ጊዜ በጸረ ኢትዮጵያዊነት መቆሟን የምናውቀው ነው።ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት፣ከዚያም ከተገንጣዮች ጋር በተደረገው ትግልና አሁን ደግሞ ወያኔ አገር እመሰርታለሁ ብሎ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲቃጣ፣ኦነግ በበኩሉ ኢትዮጵያን አፍርሼ ሌላ አገር እመሰርታለሁ ብሎ ሲነሳና ውድመት ስፈጽም አሜሪካኖችና ምዕራባውያኑ በስውርና በቀጥታ መደገፋቸውን አይተናል።ፊትም ሆነ አሁን ወያኔ   ያሰበውን እንዲፈጽም  መሬት ለመቀማት የሚያደርገውን ወረራ በመደገፍ አማራውን ወንጅለው ቆመዋል።

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን የኦነጉ መሪ አብይ አህመድ የሕዝቡን ትኩረት ለማስለወጥ የአሰብ ወደብን ላስመልስልህ ነው የሚል ላሙኛችሁ ተረት ተረት ይዞ ብቅ ብሏል፤አሰብን ለማግኘት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባለቤትነቷ  በቂ መከራከሪያ ነው።ይህንን ባለቤትነቷን ያስነጠቁት የውጭ ሃይሎችና ደርግ ወድቆ  በወያኔ ፣ኦነግና ሻእብያ ይመራ የነበረው የሽግግር መንግሥቱ ነው። ኤርትራ ተወደደም አልተወደደም አንድ ልዑላዊት አገር ተብላ እውቅና ካገኘች 30 ዓመታት አልፏል።አሁን ያለው የሁለት አገሮች ግንኙነት ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብና የኤርትራ ሕዝብ ከሚለያያቸው ይልቅ የሚያገናኛቸው ብዙ ነገር አለ።ለጊዜው አንድ መሆኑ ቢያቅት እንኳን በመልካም ጉርብትና ለመኖር የሚችሉ ሕዝቦች ናቸው።የወደፊቱ ግንኙነታቸው ከሕዝቡ መቀራረብና ከሁለቱም አገራት የእድገት ደረጃ ተከትሎ የሚከሰት መፈቃቀድ ሊኖር ይችላል።ለኢትዮጵያ ከጅቡቲ የተሻለ ዋስትና ያለው ከቅርበትም አንጻር በአሰብ ወደብ መጠቀሙ ነው።ለኤርትራውያኑም የሚሻለው ባዶውን ጥቅም ያልሰጠ ወደብ ይዞ ከመቀመጥ ይልቅ የገቢ ምንጫቸው ቢያደርጉት የተሻለ ይሆናል።ከገንዘቡ በላይ የሁለቱም አገሮች እጣፈንታ የተሳሰረ ስለሆነ ለወደፊቱ ህልውናቸው መሠረት ይሆናል።ለጊዜው ግን በሰላምና በመግባባት ኢትዮጵያም የምትጠቀምበትን መንገድ ለማምጣት የኤርትራውያን ፍላጎት መታዬት ይኖርበታል።የአሜሪካኖችንና የአውሮፓውያኑን ድጋፍ ይዤ በጉልበት እነጥቃለሁ ማለት ለተጨማሪ ድቀትና ዘለቄታዊ ጠላትነት ይዳርጋል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖርበትን መሬትና የመሰረታትን ከተማ አዲስ አበባን እነጥቃለሁ ብሎ ከሚያፈናቅለው፣ከሚገለውና ከሚዘርፈው የኦሮሙማ ቡድን አሰብን አስመልስልሃለሁ የሚል ቃል መስማቱ ከኦሮሙማው ቡድን ጅልነት በላይ ሕዝቡን ጅል አድርጎ መቁጠር ይሆናል።እኛም “ ፊት አባት ይኑርሽ በዃላ ማይበት” የሚለውን ያገራችንን ተረት ተርተን ከወደብ በፊት ኢትዮጵያ አገራችን በነጻነት፣ባንድነትና በእኩልነት የመኖሯ ዕድሏ ይረጋገጥ እንላለን።ሕዝቡ በረጋው መሬቱ ላይ የመኖር መብቱን ተገፎ በወደብ የሚያገኘው ጥቅም አይኖረውም።ዝንጀሮም መጀመሪያ የመቀመጫዬን ብላለች፤እኛም መጀመሪያ አገር ይኑረን እንላለን።

የኢትዮጵያ መሬት በሰሜንና በደቡብ ሱዳኖች ተይዞ ለማስለቀቅ ያልደፈረ ቡድን ከኤርትራ አሰብን አስለቅቃለሁ ሲል መስማቱ ባለቤቷን የተማመነች ፍዬል ላቷን ከውጭ ታሳድራለች እንደሚባለው በአሜሪካኖችና በአውሮፕያውያኖች የተማመነ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።የነሱን የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ሲል  በድንበር ከማይዋሰናት ደቡብ አፍሪካም ጋር ተዋጋ ቢሉት ከማድረግ አይመለስም።

አማራውን ከቆረቆራት ከተማ ከአዲስ አበባና ከኖረበት የኢትዮጵያ መሬት እያፈናቀለ  መድረሻ ያሳጣ የወንበዴ ቡድን የአሰብን ወደብ ላስመልስልህ ነው ተከተለኝ ቢለው ስቆበት በትግሉ ይቀጥላል እንጂ መሳሪያውን አውርዶ ክብሩን አያስነካም።

አብይ አህመድ አሁን ላይ የአሰብን ነገር ጎትቶ ያመጣው በሁለት ምክንያቶች ነው፤እነሱም

1 ከላይ እንደገለጽነው ኢሳያስን ለማሶገድና በእሱ ምትክ ለአሜሪካኖችና ለምዕራባውያን ያጎበደደ ባርያ መንግሥት እንዲመሰረት ለማድረግ በምትኩ የፖለቲካና የገንዘብ እርዳታ ለማግኘት፣

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለትልቁ ሰው፤ መድኃኔዓለም አቤት ብያለሁና፣ መልሴን እጠብቃለሁ!! - በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

2 እንመሰርታታለን ላሏት የኦሮሚያ የቅዠት አገር የወደብ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ በሰሜን ሸዋና በአዋሽ በኩል አፋርን ሰልቅጦ የጅቡቲን የመገናኛ መስመር ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱና አዳጋችም ስለሆነ  ፊቱን ወደ አሰብ በማዞር የወደቡ ባለቤት ለመሆን ፣

አሰብን ምክንያት አድርጎ የሚሰማው የኦነግና የወያኔ የጦር ጉሰማ ይበልጥ ከባቢውን የሚያምስ ስለሆነ ሁሉም ሰላም ወዳድ ሊቃወመው ይገባል።

ወያኔም በምጽዋ ወደብ ላይ ዓይኑን ከጣለ ቆይቷል፤ሃሳቡማ የኤርትራን መሬት ተቆጣጥሮ  ታላቋን ትግራይ በመመስረት የከባቢው ሲንጋፖር ለመሆን ነበር።አሁንም ያው ምኞቱ አልከሰመም።ከኦሮሙማ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን ጋር ተባብሮ የጋራ ፍላጎታቸውን ለማረጋገጥ አማራውን ለማጥፋት ግንባር ፈጥረዋል።

በጣም የሚገርመው ነገር የአሰብን ወደብ ተከትሎ የባሕር ሃይል መቋቋሙን  በብርሃኑ ጁላ በተባለው ገልቱ የተሰጠው መግለጫ  ነው።ለመሆኑ የትኛው ወደብ ላይ ስልጠና ተካሄደ?ቤዝና እዙ መቀመጫው ፣የጦር መርከቦቹስ ማረፊያና ጥገና የት ይደረግላቸዋል?ወይስ የፈረደበት ናዝሬት/አዳማ ደረቅ ወደብ ላይ ነው?ወይስ በኪሳቸው አሻንጉሊት ወደብና  መርከብ ይዘው ይሆን? የባሕር ሃይል ቢኖር እንኳን ከአረቦቹ ወይም ከምዕራባውያን ባለቤትነት የራቀ ሊሆን አይችልም።ኤርትራን ከባሕርና ከአዬር እንዲሁም ከምድር የመምታት እቅድ ተከትሎ የመጣ  ሊሆን ይችላል።ስለሆነም ኤርትራውያን  ከአማራውና ከአፋሩ ጋር ተባብረው  ለህልውናቸው ቢቆሙ ይሻላቸዋል።

እርግጥ ነው ወደብ ለአንድ አገር እድገት የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ አይካድም፣ይህ ማለት ግን ወደብ ያለው አገር ሁሉ አድጓል ወይም ሰላሙ ተጠብቆለታልማለት አይደለም።በአንድ በኩል ሶማሊያን፣ማዳጋስካርንና የመሳሰሉትን በውሃ የተከበቡ አካባቢዎችን  በሌላ በኩል ወደብ ሳይኖራቸው ለከፍተኛ እድገትና ሰላም የበቁትን የአውሮፓ አገራት መመልከት ከወደብ በላይ ውስጣዊ ሁኔታው ፣የሥርዓቱ አይነት ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን።

የኤርትራ ሕዝብም በበኩሉ ካለፉት ስህተቶች ተምሮ በታሪኩና በብዙ እሴቶቹ ከሚመሳሰለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ከሚያዋስነው ሕዝብ  ከአማራው ጋር ግንኙነቱን ቢያጠብቅ ለሰላሙና ለእድገቱ ዋስትና ይሆናል።የትግራይም ሕዝብ ለጥቂት የወያኔ አረመኔዎች  ስልጣንና ጥቅም ብሎ ልጆቹን ለጦር ሜዳ መዳረጉን አቁሞ ከቀረው ወገኑ ጋር የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነቱንና ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ቢመርጥ ይበልጥ ይጠቅመዋል።የአሜሪካኖችንና የአውሮፓውያኑን መርዘኛ ሴራ ተቀብሎ የገነባትን አገር ከማፍረስ ቢታቀብ ለዘላቂ ህይወቱ ዋስትና ይሆናል።ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆኖ ዘላለም ከማልቀስ ይሻለዋል።

አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ ንቀት እንዳለው በግልጽ አሳይቷል። በሰሞኑ በጋና ዋና ከተማ በአክራ ከጁን 18-21 2023 ድረስ በተደረገው የአፍሪካና የካሪቢያን የንግድ ልውውጥ( Import-Export) ና የባንኮችን ሚና በተመለከተ አፍሬክሲምባንክ(Afreximbank)ስብሰባ ላይ እንደሚገኝ ተናግሮ ሲጠበቅ ካለምንም ማብራሪያ ቀርቶ በምትኩ የሱ ውታፍ ነቃይ የሆኑትን እንደ ሃይለማርያም ደሳለኝ የመሳሰሉትን ድኩማኖች እንዲገኙ አድርጓል።እሱ ግን ምዕራባውያን በፈረንሳይ ከተማ ፓሪስ ላይ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የተለመደ ልመናውን አቅርቧል።ምዕራብያውያኑ ገንዘባቸውን እሱ ስላለቀሰ የሚሰጡት ሳይሆን የሚፈልጉትን ለማድረግ ቃል ከገባና በተግባር ካሳያቸው ብቻ ነው።ለዚያም ነው ያገሪቱን  ቅርሶችና ተቋማት እዬቸበቸበ ታማኝነቱን በመግለጽ ላይ የሚገኘው።ኢሳያስ አፈወርቂንም ለማሶገድ በታሰበው እቅድ ውስጥ ገብቶ አሰብን ምክንያት ለማድረግ የሚሞክረው።ያም ብቻ አይደለም የግብረሰዶምን ቁሻሻ ተግባር እንዲስፋፋ በማድረግ በሰብአዊ መብት ሰበብ በሕግ ለማጽደቅ ዳር ዳር እያለ ይገኛል።ይህንን ቁሻሻ ጸረ ትውልድ ድርጊት የቀሩት ያፍሪካ መሪዎች ሲቃወሙና በሚፈጽመው ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት ሲጥሉ ታይተዋል።አንዳንዶቹም በምዕራቡ ላይ የከረረ ተቃውሞ በመሰንዘር ላይ ናቸው።ምዕራባውያንም ጥርሳቸውን ቢነክሱባቸውም ሕዝቡ ከነሱ ጋር በመቆሙ ለጊዜው የሚገቡበት ቀዳዳ አላገኙም። እንደልማዳቸው የጎሳ ፖለቲካ መርዝ እረጭተው አገሮቹን እንደኛ ላለማመሳቸው ዋስትና የለም፤አፍሪካን ለመበታተን ቀላሉ ዘዴ ጎሰኝነት ስለሆነ የሕዝቡን ድክመት ተጠቅመው እርስ በራሱ ተባልቶ አገሩን ሰላም አልባ ከማድረግ አይመለሱም።

በአጠቃላይ አፍሪካ ለምዕራባውያን የምታጎበድድበት ዘመኑ ያለፈ ይመስላል።ይህ ግን የሚረጋገጠው ሁሉም አፍሪካዊ በአንድነት ሲቆም ብቻ ነው።እንደ ወያኔና ኦነጋውያን  ያሉ ባርነትን እንደ ዕድልና ስልጣኔ የሚቆጥሩ ባሉበት ክፍለ አህጉር ውስጥ ዘላቂ ሰላም መምጣቱ አጠራጣሪ ነው። ለአፍሪካ አገራት ዘላቂ ሰላም፣አንድነትና ነጻነት የነሱና መሰሎቻቸው መጥፋት አስፈላጊ ነው።

ሕዝባዊ ትግሉ ይጠንክር!ሁሉም የድርሻውን ያበርክት!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ትግል በነጻነትና በአንድነት ለዘለዓለም ትኑር!!

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share