በሁሉም አከባቢዎች ያሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች ሃገር የቆመበትን ምሰሶ የሚቦረቡሩ ቅንቅኖች ናቸው!!!

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu@yahoo.com)

እንደኔ ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የምፈልገው ስርዓት በዜግነት ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ አስተዳደር ነው። ነገር ግን ቢያንስ አሁን ባለው የጦዘ የብሄርተኝነት ፖለቲካ የተነሳ ይህ ፍላጎቴ እውን የሚሆን አይመስልም። በዚህ ምክንያትም የብሄርተኝነት ፖለቲካው በምን መልኩ ጤነኛ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ ብንለዋወጥ፣ ብንነጋገር፣ ብንከራከር ይሻላል ባይ ነኝ።

ከዚህ ተነስቸ ቢዚህ ፅሁፍ ውስጥ ስለብሄርተኝነት ያለኝን ግንዛቤ ለመግለፅ እሞክራለሁ። ብሄርተኝነት በተለያየ መንገድ ሊገለፅ ይችላል። አንዱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ብሄርተኝነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ሌላ ጊዜ የምመለስበት ሆኖ እዚህ ፅሁፍ ላይ የማተኩረው ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነው ብሄርተኝነት ላይ ይሆናል።

ፀረ–ዴሞክራሲያዊ የሆነ ብሄርተኝነት በተፈጥሮው የስግብግብነት፣ የግለሰበኝነት፣ የአግላይነት፣ የአምባገነንነት፣ የጠቅላይነት፣ የጨፍላቂነት፣ የመርህ አልባነት ምንጭ ነው። ይህ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሃይሎች የምንጊዜም ትኩረታቸው የ’ኔ ነው የሚሉትን ቡድን ጥቅሞች ማስጠበቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች ካራሳቸው ቡድን አሻግሮ የማየት ፍላጎት የሌላቸውና ቢያዩም እንኳ ሌላውን ጥሎ በማለፍ የራሳችን ነው የሚሉትን ቡድን ለመጥቀም ብቻ ነው። በዚህ አስተሳሰብ የተለከፉ ሃይሎች በተለይ የመንግስትን ስልጣን ከተቆጣጠሩ በሃገርም ሆነ በህዝቦች አንድነት ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉት አደጋ በቀላሉ ሊገመት የሚችል አይሆንም። የፀረ- ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞችን አደጋ በሚገባ ለመረዳት በሚከተለው መንገድ ለማብራራት መሞከር ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ።

1.አስተዳደር፡ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ብሄርተኛ ሃይሎች የሚከተሉት የስተዳደር ዘይቤ ዝግ የሆነና በተቻለ መጠን ሌሎችን የሚያርቅ ነው። ስለዚህ ዋና ዋና ናቸው ተብለው የሚገመቱ ተቋሞችን የራሳችን ናቸው በሚሏቸው ሰዎች እንዲሞሉ ያደርጋሉ። ሌሎች እንዲሳተፉ ቢያደርጉ እንኳ ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ብቻ እየመዘኑና እየቃኙ ነው። በዚህ አይነት አስተዳደር ውስጥ ግልፅነት የሚባል አሰራር አይታሰብም። ሁሉም የሚፈፀመው በድብቅ ነው። ምክንያቱም ግልፅ የሆነ አሰራር ቢኖር የሚሰራው ሁሉ አደባባይ ይወጣና በቀላሉ ለትችትና ለጥላቻ ይዳርጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፋፋዮች አማራን የማዳን ኢትዮጵያን የመታደግ ትግል አታደናቅፉ

ለነዚህ ሃይሎች ተጠያቂነት የሚባል ነገርም ጉዳያቸው አይደለም። ተጠያቂነት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነም ከፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኛው ሃይል ውጭ ባሉ አካላት ላይ ያተኩራል። በእርግጥ እነዚህ ሃይሎች ስግብግብ ጥቅማቸውን ለማሳካት እንቅፋት ይሆኑናል ብለው ካሰቡ የራሳቸውን ብሄር አባላትም ቢሆን የተለያየ ሰበብ በመፍጠር ከማስወገድ ወደኋላ አይሉም። የሚሰሩት ስራ ትክክል እንዳልሆነ ስለሚያውቁም ፍፁም የሆነ አታላይነት፣ አጭበርባሪነት፣ ሸንጋይነትና በዋነኛነት ደግሞ አምባገነንነት የሚያጠቃቸው ሃይሎች ናቸው። ለዚህ እንዲያመቻቸው ዋና ዋና የፀጥታ ተቋማትን ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ። የሚታገላቸውና የሚተቻቸው ሃይል ካጋጠማቸውም የተለያየ ስም በመለጠፍ በዙሪያችው ባደራጁት የፀጥታ ሃይል ለመጨፍለቅ በሚችሉት መንገድ ሁሉ ይጥራሉ። በጥቅሉ መልካም አስተዳደር ማስፈን የሚባል ነገር በፀረ-ዴሞክራሲያዊ በብሄርተኞች ዘንድ አይታሰብም።

2.የህግ የበላይነት፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትና የህግ የበላይነት ሆድና ጀርባ ናቸው። የህግ የበላይነት በሚከበርበት ስርዓት ውስጥ ሁሉም ሰው እኩል ከመታየቱ በተጨማሪ እኩል ጥበቃም ይደርግለታል። ፀረ–ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ብሄርተኞች ግን ከነሱና ከቡድናቸው ውጭ ያለው ማህበረሰብ እኩል እንዲታይም ሆነ እኩል ጥበቃ እንዲደርገለት አይሹም። ለምሳሌ እነዚህ ሃይሎች የራሳችን ነው ከሚሉት ቡድን አንድ ተቀናቃኝ ቢኖራቸውና ከነሱ ቡድን ውጭ ካለው የማህበረሰብ ክፍል ደግሞ ሌላ ተቀናቃኝ ቢኖራቸው የተሻለ ጥበቃ የሚያደርጉለት እንኳ ከራሳቸው ብሄር ለወጣው ተቀናቃኛቸው መሆኑ አይቀርም።

3.ሰላም፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ብሄርተኞች ቅድሚያ የሚሰጡት የራሳችን ነው ለሚሉት ቡድን ሰላም ነው። የሌላው ሰላም የሚያሳስባቸው ከሆነም የራሳቸውን ሰላም የሚያደፈርስባቸው መስሎ ሲሰማቸው ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ባለው ሁኔታ ምናልባትም ከነሱ ቡድን ውጭ ያሉት የማህበረሰብ ክፍሎች ሰላማቸውን ቢያጡ ሊፈልጉት ይችላሉ። በራሳቸው ድብቅ ሴራም የሌሎች ሰላም እንዲረበሽ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። አንዳንዴም ራሳቸው የሚያስተዳድሩት አከባቢ በሰላም ማጣት እየተናጠ የሰላም አባት መስለው በመታየት ሌሎች ጋር ገብተን እንፈትፍት የሚሉበት ሁኔታ ይኖራል። ይህን የሚያደርጉት ሰላም እንዲመጣ ፈልገው ቢሆንም ጥሩ ነበር። መነሻቸው ግን የሌሎቹን ግጭቶች አባብሰው በሚፈሰው ደም ትርፍ ለማግኘት የሚጠቀሙበት እጅግ በጣም ርካሽ የሆነ ፖለቲካዊ ስሌት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለአቶ ገብረ መድህን አርአያ ሊላክ ያልተፈለገ ግልጽ ደብዳቤ

4.ልማት፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ሃይሎች ፍትሃዊ የሚባል የልማት ክፍፍል ጉዳያቸው አይደለም። በተቻላቸው መጠን ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጡት የራሳችን ነው ለሚሉት አከባቢ ነው። ሲጀመር ፍትሃዊና ሚዛናዊ የሆነ የልማት ቀመር እንዲኖር አይፈቅዱም። ከዚህ በመነሳትም በቻሉት መጠን የተለያዩ ምክንያቶችንና ሰበቦችን በመደርደር ቀመሮቹ ሁሉ የራሳቸውን አከባቢ በተለየ መንገድ ለመጥቀም በሚያስችል መልኩ እንዲቀረፁ የሚችሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ።

5.ሰብዓዊ መብቶች፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች የሁሉንም ዜጎች መብቶች እኩል የማስከበር ቁርጠኝነት የላቸውም። በተነፃፃሪነት ከታየ ግን የራሳችን ነው የሚሉት ቡድን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ። የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ መንገድ በተፈፀመ ድርጊት ሰዎች ቢጎዱ መርጠው የሚጮሁት የኛ ነው ለሚሉት ቡድን አባላት መሆኑ አይቀርም። በነሱ አከባቢ በሌሎች ላይ ጥቃት ቢፈፀም ግን የተለያየ ሰበብ በመደርደር አጥቂውን ለመከላከል የማይፈነቅሉት ደንጋይ አይኖርም። አስፈላጊ ከሆነም ተጠቂውን ጥፋተኛና ወንጀለኛ አድርገው በመቁጠር ተጠያቂ ሊያደርጉ ሁሉ ይችላሉ።ከአጥቂውና ከተጠቂው ውጭ ያሉ ሌሎች ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች ደግሞ እነሱን እስካልነካቸው ድረስ እንደነገሩ ሁኔታ ድርጊቱን ከማውገዝም ሆነ ከመደገፍ ይቆጠባሉ። ነገሮች ገፋ ብለው ከቀጠሉም ጡንቻ አለው ብለው ለሚያስቡት ሃይል ወግነው መጮህ ሊጀምሩ ይችላሉ።

6.ህዝባዊነት፡ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች ህዝባዊነት የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም። እነዚህ ሃይሎች ራሳቸው ለወጡበት ብሄር/ብሄረሰብ እንኳ አይጨነቁም። ብሄራችን ካሉም በስሙ ሊነግዱበት ካልሆነ በስተቀር ሊጠቅሙት አይደለም። ሲፈልጉ የወጡበትን ብሄር ከሌላው ጋር እያጋጩ የፖለቲካ ትርፍ ሊያገኙበት ይጥራሉ። ካልተመቻቸው ደግሞ ሌሎች ብሄሮችን በማጋጨትና በማባላት የራሳቸውን የበላይነት ለመጫን ይሞክራሉ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች የራሳችን ነው የሚሉትን ቡድን ለመጥቀም የሚንቀሳቀሱት ለራሳቸው የሚጠቅማቸው መሆኑን እርግጠኛ ሲሆኑ ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ግን ደንታ ቢሶች ናቸው። በተጨማሪም እነዚህ ሃይሎች ሌሎችን የሚፈልጉት ራሳቸው ብልጫ ይዘው ሌሎቹ እንዲያኗኑራቸው እንጅ በእኩልነት መርሆዎች ላይ ተመስርተው አብረው እንዲኖሩ አይደለም። ያ እንደማይሆን ባወቁ ጊዜ ግን ራሳቸውን ለመቻል ሲሉ አገር በጥብጠው ሊነጠሉ ምናልባትም ደግሞ በልተው ለበይ ሊሰጡ ይችላሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስኬት የሚገኘው ራዕይ ፣ ዕሴትና ተግባር ሲዋሃዱ ብቻ ነው - ማርእሸት መሸሻ

ከዚህ በመነሳት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ብሄርተኞች የሃገርን ቋሚ ምሰሶ የሚቦረቡሩ እና አዳክመው የሚጥሉ ቅንቅኖች ናቸው ቢባል ስህተት የሚሆን አይመስለኝም።
Note: ስለፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ይህን ያህል ካልን በቀጣይ ደግሞ አሁን ስልጣን ላይ ያለውን የኦሮሞ ብልፅግናን ቁመና ከላይ ከተቀመጡት ነጥቦች አንፃር ቃኝተን መፍትሄ ሊሆን ስለሚችለው ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት የተወሰነ ነገር እንላለን፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share