እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ መታሰቢያ ቀን አደረሳችሁ ። ኢየሱስ ክርስቶስ ህገ አራዊትን አሶግዶ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ያሳየን ዘንድ ተግተን እንፀልይ ። በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነፃነት አወጣን እንግዲህ ፀንታችሁ ቁሙ ። እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ ።
( ገላትያ ምዕራፍ 5 ፤ 1 )
ሲና ዘ ሙሴ
ሰው ፣ ሰውን እንዲጠላ የሚያደርግ አንቀፅ ያለው ህገ መንግሥት ሉሲ ፈራዊ ነው ። አንቀፅ 39 ከህብረት ይልቅ መለየትን ፤ ከአንድነት ይልቅ መበታተንን ፤ ከፍቅር ይልቅ ፀብን የሚያበረታታ ነው ። ምንም እንኳ የሰው ሥብሥብ የሆነው ህዝብ አጭር ህይወቱን በተቻለው አቅም ህብረትን፣አንድነትን ፍቅርን እጅግ ቢፈልግም በእኛ አገር ህገ መንግሥት አልተፈቀደለትም ።
ሰው ከፍጥረቱ ጀምሮ እየተባበረ ፣ እየተፋቀረ ፤ እየተጋባ እና እየተዋለደ ከእንሥሣ የተጠጋ ኑሮ ከመኖር ቀስ፣በቀሰ ወደ ሥልጡን እና በጥበብ የተሞላ ኑሮ መኖር መጀመሩን ከታሪክ እንረዳለን ። ሰው ፣ በጥረቱ እጅግ የሠለጠነ ኑሮ ላይ በጥበቡ ቢደርስም ፣ በእኛ አገር አሁናዊ ሁኔታ የሰው የእግዚአብሔር ፍጡርነቱ በገዢዎች የተካደ ሆኗል ። በጥቂት እናውቃለን በሚሉ ሆኖም ሁሉንም ነገር ከዘር ጥቅማቸው አንፃር በሚመለከቱ ፣ ጠመንጃን እንደ ሥልጣን ምንጭ በሚቆጥሩ ግለሰቦች በምትመራው አገራችን ሰዎች የሚታዩት እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ቋንቋ ነው ። ሰው ሲፈጠር አንድ ሆኖ ሣለ ፣ በእኛ አገር ግን ሰው በዘሩ እንዲተያይ በመንግሥት እየተገደደ ይኸው ለ33 ዓመት በቅቷል ።
በዛሬዋ የትብብር ዓለም ውሥጥ ተጠቃሚ እንዳይሆን በድንቁርና ዘራዊ ሥርዓት አደንዝዘው በህገ አራዊት ሥርዓት ለመግዛት የዛሬዎቹ ባለተራዎቹም ከትላንትናዎቹ ብሰው ህዝብን እርስ በእርሱ ለማጫረስ ያለማቋረጥ የጥፋት ቢላዋ በመሣል ለገዳዮች እያቀበሊ ነው ። ኢትዮጵያዊው በራሱ መንግሥታዊ የዘር ሥርዓት እጅ እና እግሩ ታሥሯል ። እናም በጠመንጃ እየተነዳ የግዱን ሰው በሰውነቱ ሳይሆን ፈቅዶና ወድዶ ባልተወለደበት ዘሩ እየተፈረጀ እየተፈጀ ነው ። …
ለመሆኑ ፣ እኔ የተለያየ ነገድ ደም ቢኖረኝ ማነው በአማራ፣በትግሬ፣በሱማሌ፣በኦሮሞ፣በአፋርነት ወዘተ ። ሊመድበኝ የሚችለው ። አባቴ ከአፋርና ሱማሌ ፤ እናቴ ከኦሮሞ ፣ ከትግሬና አማራ ቢዛመዱ ፤ እኔን ይኽ የቋንቋ ፣ የነገድ ና የዘር መንግሥት ማን ብሎ ይጠራኛል ?
ከቶ ወዴት እየሄድን ነው ?
በለው ! ምታው ! ጣለው ! አሠቃየው ! ግደለው ! በማለት ሥልጣንን በምርጫ ሰጥቶ በህግ የበላይነት አሥተዳድረኝ ያለውን የአንድ አገር ህዝብ ፣ በነገድ ና ቋንቋ ፈርጆ ማሰር፣ማንገላታት ፣ መግደል ፣ ማሰቃየት ሉሲፈራዊ ድርጊት አይደለም እንዴ ?
መንግሥት ህዝብ በሰጠው ሥልጣና ተጠቅሞ መልሶ እንዴት ህዝብን ያሰቃያል ? ይሄ ድርጊቱ ፕሮፌሰር መሥፍን እንዳሉት “ህገ አራዊትነት “ አይደለም እንዴ ? ህገ አራዊትነት ደግሞ በጠብመንጃ አሥገዳጅነት አገርን የሚመሩ አምባገነን መንግሥታት ባህሪ ነው ።
አምባገነኖች በህገ አራዊት ሥርዓተ መንግሥት ፤ ትላንት ለጥቅማቸው ቀጣይነት በመጨነቅ ብቻ ንፁሐንን ያለርህራሄ ሲፈጁ ሲያስሩና ሲያሰቃዩ እንደነበር በታሪካችን በጥቁር መዝገብ መመዝገቡን እንዴት እንረሳለን ?
በህገ አራዊት የፖለቲካ ሥርዓት ከምንመራ ይልቅ ፣ “በህገ ሰው የሚመራ መንግሥታዊ ሥርዓት “ ቢኖረን ኖሮ በምንም ዓይነት መልኩ ዜጎችን በኢትዮጵያ ከሚኖሩበት ቀዬ ቤተሰቦቻቸው ተገለውና ተዘርፈው እነሱ በሽሽት ተርፈው ተፈናቅለው ቤት ተመፅዋች ምንዱባን አይሆኑም ነበር ?
በጥይት ዜጎችን ያለርህራሄ በዘረኝነት የተደራጀ ሽፍታ ዜጎችን በተዝናኖት የሚፈጅበት አንድ አገር ኢትዮጵያ መሆኑ ዛሬ በዓለም ተረጋግጧል ።
በእኛ አገር “ የክልሌ ልዩ ኃይል ከሌሎች ልዩ ኃይሎች ቀድሞ ወደ ህጋዊ አደረጃጀት አይዛወርም ። ከተዛወረም ወቅቱ አሁን አይደለም ። በኃይል ተወሥዶብኝ የነበረ መሬቴን በመሰዋትነቴ የራሴ አድርጌያለሁ ። ታሪክ የሚያረጋግጥልኝን ፣ መረጃና ማሥረጃ ያለውን “ የወልቃይቴ ና የራያን “ ህዝብ መኗሪያ ፣ ሥልጣንን መከታ በማድረግ ለትግራይ ክልል መንግሥት መልሶ መሥጠት ህጋዊነት የለውም ። የወልቃይቴ ና የራያ ህዝብ መብት መጠበቅ አለበት ። በህገ መንግሥቱ መሠረት ። ሥለሆነም ራሱን ችሎ እንደ ሐረሪ ክልል ይሆናል እንጂ ተመልሶ ወደ ትግራይ ክልል አይገባም ። “ የሚለውን የአማራ ክልል ህዝብ በኃይል ጥያቄውን ለማዳፈን መግደልና መሰርን እንደመፍትሄ የሚቆጥር ህገ አራዊት መንግሥት ነው ያለው ።
“ በህዝብ ብዛቴ መጠን ታይቶ የክልሌ ፖሊሥ ቁጥርም ከትግራይ ክልል በ3 እጥፍ መብለጥ አለበት ። “ በማለት ህዝብ ጥያቄ ይዞ አደባባይ ሥለወጣ ምላሹ ጥይት እና አሥር ሲሆን እያየን ነው ።
ገዢው ፓርቲ ብልፅግና በህገ አራዊትነት አገርን እየመራ እንደሆነ ፣ በራሱ ና በየክልሉ ያሉ ህግ አሥፈፃሚዎች በየቀኑ የሚፈፅሙት ህገ ወጥ ተግባር ይመሠክራል ። ጠ/ሚ አብይም “ እኛ ነን ፤ አሸባሪ ። “ ብለው ገና ሥልጣን እንደያዙ ፣ ከ5 ዓመት በፊት የተናገሩትን ዛሬ ሳያሥቡት ዘው ብለው በተግባር እየኖሩበት በመሆኑ ሥለ ህገ አራዊት አገዛዛቸው ዋቢ መጥራት አይጠበቅብኝም ።
ዛሬ በኢህአዴግ ሰውነት ላይ ብልፅግና የሚል የህገ አራዊት ቆዳ አገዛዙ ለብሶል ፤ “ እበላ ባይ ካዲሬዎቸን ከቀበሌ ጀምሮ በማደራጅትም የሚቀጥለውን 13 ወይም 43 ዓመት ምርጫን በኮሮጆ ግልበጣ በማሸነፍ መንግሥት ሆኜ አገሪቱን እየበዘበዝኩ እቀጥላለው ብሎ ያሥብ ይሆናል ። “
እንዲህ አይነቱ የቀቢፀ ተሥፋ ህልመኝነት ምነጩ ፣ የነቃ እና የተደራጀ ህዝብ እንዳይኖር በማድረግ ፣ እሥርቤትን በማሥፋፋት ኢትዮጵያን የዜጎቿ እሥር ቤት በማድረግ የሚሳካ ነው ። ለዚህም ይመሥላል ለሥርዓት መከበር ፣ ለህግ የበላይነት ደንታ ቢስ የሆነው ጥቂቶችን በማበልፀግ ላይ በህቡ የሚሰራው መንግሥት ፣ ህዝብ ንቃተ ህሊናው የማያድግ ግዑዝ ፍጥረት እንደሆነ በማሰብ እሥር ቤትን እሥከ አዋሽ አርባ ያሥፋፋው ።
አበልፃጊ ነኝ የሚለው በተግባር ግን እያደኸየን ያለው መንግሥት ያልተረዳው የዛሬ 50 ዓመት በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ የነበረው የዛን ጊዜው ወጣት ዛሬ በአብዛኛው ያለመኖሩን ነው ። ያለውም አርጅቷል ። ከፖለቲካው ጫዎታ ውጪ ሆኗል ። በእርሱ ምትክ እጅግ ምጡቅ ጭንቅላት ያለው ወጣት ትውልድ ተፈጥሯል ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥር እጅ የሚበልጥ የአእምሮ ግዝፈት ያላቸው ሚሊዮን ወጣቶች ዛሬ በአገራችን አሉ ። ይኽንን በቅንነት ተገንዝቦ ለእውነተኛ ለውጥ መነሳት ከብልፅግና ፓርቲ ይጠበቃል ።
አንዳችም ለውጥ ሳያመጡ ፣ ከቀድሞው ኢህአዴግ በባሰ መልኩ ፣ በአምባገነንነት ፣ በህገ አራዊት ሥርዓት አገርን መምራት የብልፅግና ዘይቤ እየሆነ የመጣው ይምጣ ብሎ ብልፅግና ከኢህአዴግ ሰውነት ላይ ልብሱን ሳያወልቅ መጓዙን ከቀጠለ ግን ጉዞው እጅግ አጭር እንደሚሆን የታወቀ ነው ።
የብልፅግናንን ቆዳ የለበሰው የቀድሞው የኢህአዴግ መንግሥት በህገ አራዊት ሥለሚመራ ነው ፣ በአገሪቱ ህገ መንግሥት መሠረት ክልሎች ፖሊሥ ብቻ እንዲኖራቸው ያላደረገው ። በህገ አራዊት በሚመሩት ፣ የዛሬዎቹ ብልፅግናውች ናቸው የትላንትናዎቹ ኢህአዴጋዊያን ። በሥልጣን ላይ በነበሩበት አገዛዝ ወቅት በህገ መንግሥት የሌለ ልዩ ኃይል ተዋቅሯል ። ዛሬም ፣ አገሪቱ ከዚህ “ ህገ አራዊት የአገዛዝ መንገድ “ ወጥታ “ በህገ ሰው “ መንገድ በሥርዓት እየተጓዘች እንዳልሆነ ከቤተመንግሥት ብዙም ሳይርቁ የሚፈፀሙ አፈናዎች ግድያዎች ና ዘረፋዎች ያሳብቃሉ ።
ዛሬ አብይ መራሹ አበልፃጊው መንግሥት ጥቂቶችን ለማበልፀግ ቆርጦ የተነሳው መንግሥቱ ህገ አራዊትነቱን ሥለተጠናወተው ነው ። የ 27 ዓመቱ ህገ አራዊትነት እጅግ በገዘፈ ጭካኔ “ በልፅጎ “ ዳግም መከሰቱ ይኸንኑ ይመሰክርልናል ። ( ነገሮችን ሁሉ ከባለሥልጣናቱ ጥቅምና ምቾት አንፃር በማየት በከፋ ጨቋኝነት እና ሰልቃጭነት ሀገን በአውሬነት “ ብልፅግና ተብየው “ እየገዛት ነው ። )
በተለይም በኦሮሚያ ክልል ሥርዓተ አልበኝነት በእንስሳዊ መልኩ ነግሶ አንገት እየቀላ ፤ ዜጎችን እንደ እንሥሣ በማየት አውሬው እየሰለቀጣቸው ነው ። አማራ እንደ ታዳኝ እንሥሣ ተብይ ሆኗል ። ሰው ላልሆኑት አራዊት ባለሥልጣናት ። ከዚህ አንፃር አማራው አሁን ካሳየው የትግል አንድነት እጅግ የጠነከረ ትግልና ተጋድሎ ይጠበቅበታል ። የሰው ባህሪ ያልተፈጠረባቸው ፣ በህገ አራዊት አገራችንን የደም ምድር እያደረጓት ያሉትን ሉሲፈራዊያንን ለማሶገድ ግን የአማራው ክልል ህዝብ ትግል ብቻ በቂ አይደለም ። …
ማንኛውም ዜጋ የቋንቋ መጠሪያውን ይዞ ይጠራ፣ አማራ ይሁን ኦሮሞ ፤ ትግሬ ይሁን አፋር ፤ ደቡብ ይሁን ሱማሌ ፤ ቤንሻጉል ይሁን ጋምቤላ ፤ ሲዳማ ይሁን ሐረሬ …። በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ታፍሮና ተከብሮ ለመኖር ከፈለገ እነዚህን ጥቂት እጃቸው በደም የጨቀየ ሉሳፈራዊያን ከጫንቃው ላይ ማሶገድ ይጠበቅበታል ።
በዚች አገር ህገ አራዊት በከፍተኛ ሁኔታ በመንሰራፋቱ ዜጎች የመብላት ሳይሆን የመበላት እጣ ፈንታ ወድቆባቸዋል ። በየጊዜው እንደከብት እየተነዱ ዛሬወደ አምባገነኖች ማጎሪያ ካምፕ ይጓዛሉ ። ዛሬ በኢትዮጵያ ገደብ በሌለው ቸበር ቻቻ “ አለም በጎኔ አሐፈች “ እያሉ በየቀኑ የሚደሰቱት በፊደራልም ሆነ በክልል በሥልጣን ላይ ያሉት እና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ብቻ ናቸው ።
ከገበሬው እሥከ ወታደሩ የተጎሳቆለ ኑሮ ነው የሚኖረው ። ከላብ አደሩ እሥከ የመንግሥት ሲቪል ሠራተኛው ኑሮን መቋቋም አቅቶት ለእንዲህ ዓይነቱ የኑሮ ውድነት ያበቃውን ህገ አራዊቱን አገዛዝ ሌት ተቀን እየረገመ ኑሮን በተአምር እየኖሩ ነው ።
በህገ አራዊትነት ተመርተው ፣ በማንአህሎኝነት ና በእብሪት ግለሰቦች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ የሚፈፅሙት ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ነገ በወንጀል ያስጠይቃል ። … ። አገርን በህገ አራዊት ሥርዓት ማሥተዳደር ትርፉ የከፋ ውድቀት ነው ።
“ ምን ታመጣለህ ? ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ ! “ ማለትም የህገ አራዊቶች የእብሪት መንገድ ነው ። በመንግሥትነትም የሚያሰነብት የተደላደለ መንገድ አይሆንም ። ከጉዞ አሰናካይ ሥውር መቀበሪያ ጉድጓድ ያለበት ዘግናኝ መንገድ ነው ።
በህገ አራዊት መንገድ በመጓዝ በአማራ ክልል ውሥጥ የፌደራሉ መንግሥት ታላቅ ነውጥ ፣ አመፅ ፣ የንፁሐን መገደለን እና ሠላም ማጣትን መንግሥት እንዲከሰት በማድረግ “ ገገማ የሆነ ሉሲፈርነቱን “ አሥመሥክሯል ። በዚህ ግጭት ፣ ሁከትና ሠላም ማጣት የምትጎዳው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን እንኳን እንዴት አያውቅም ? ወይሥ እያወቀ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ተልኮ ተሰጥቶት በህቡ የሚንቀሳቀስ በዘረኝነት ያበደ መንግሥት ነው ያለን ? የሠከረ ህሊና ያለው ህገ አራዊትን የሚያራምድ መንግሥት እንዳለን ተግባሩ እያረጋገጠልን አይደለም እንዴ ? …
ዛሬ ወደ አማራ ክልል የተሸጋገረው የህገ አራዊት ድርጊት ትላንት በትግራይ እብሪተኞች የተፈፀመ ነበር ። ዘረኝነትን ፤ ጠባብነትን ፤ ትምክህትን እና ሥግብግብነትን በህሊናቸው ያነገሱ የሕወሓት ሰዎች በአምባገነንነት ያንን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጥቃት በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በመፈፀም ግልፅ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ላይ በመክፈታቸው አይደለም እንዴ መቶ ሺዎች ፣ ኢትዮጵያን እንዴት ትደፍራላችሁ በማለት ያንን ታሪክ በልዩ ሁኔታ የሚያወሳውን መስዋዕትነት የከፈሉት ።
ዛሬም በግራና በቀኝ ያሉ ፣ የፊደራልና የክልል ሹመኞች ፤ ይኽንን ህገ አራዊትነት ከህሊናቸው ካላሶገዱ ወይም እነሱ ካልተወገዱ እና እውነተኛ ፣ አሥተዋይ ፣ በተግባር ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚታትሩ የተግባር የፖለቲካ መሪዎች ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ ወደሥልጣን እሥካልመጡ ጊዜ ድረሥ በዚች ምድር የህግ የበላይነት ይሰፍናል ብለው ዜጎች አያስቡም ። አንዳንዶችም “ የህ መንግሥት ጀዝቧል ። በየክልሉ አገሪቱን በእንደዚህ አይነት የምንግዴ አሥተዳደራዊ መንገድ የሚመሯት ጀዝባ ጅላጅል ና ጅላፎዎች ናቸው ። እናም ለህዝብ የሚበጅ በተግባር የሚታይ ሥራ በመሥራት ፣ የዳቦ ና የፖለቲካ ጥያቄውን በአጭር ጊዜ ውሥጥ በተግባር የሚመልሱ ፣ የነቁ ና የበቁ የፖለተካ ሰዎች በቅጡ በመደራጀት ወደ ፖለቲካ ትግሉ በመምጣት አገራችንን ከውድቀት ሊያድኗት ይገባል ። “ በማለት አምርረው ሲናገሩ ይደመጣሉ ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ለ 21 ኛው ክ/ዘ የሚመጥን የፖለቲካ ሥርዓት በአገራችን ማንበር የምንችለው ፣ እንደበለፀጉት አገራት የሰው ፖለቲካን ምርጫቸው ያደረጉ ፣ በህገ ሰው የሚመሩ አርቀው የሚያሥቡ ፣ ከሥግብግብነት የፀዱ ፣ በዕውቀትና በጥበብ የበለፀጉ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርታዎች ሲኖሩን መሆኑንን እናውቃለን ።
ህገ አራዊት የሆነው አገዛዝ በሥግብግብነቱና በአይጠረቄነቱ ባይገባውም ከበለፀጉት አገራት ጋር ይሚመሣሠል ፣ ህገመንግሥት አፅድቀን በህግ የበላይነት ዜጎች እንዲተዳደሩ በብርቱ እንፈልጋለን ። ( በተባበረችው አሜሪካ እንኳ የሌለ የዓለም ጎሣና ነገድ የለም ። ነገር ግን ዜጎች እንደ ዜጋ እንጂ እንደ ነገድ ና ጎሣ አይታዩም ። የሚተዳደሩት በህግ የበላይነት ብቻ ነው ። ዜጎች ናቸው እኩል የዜግነት መብት አላቸው ።
አሜሪካ ፣ በጠንካራ ህግ አውጫዎች ፣ህግ ተርጓሚዎች ፣ህግ አሥፈፃሚዎች ና በአራተኛው ጠንካራ ተቋም በፕሬሥ ጣምራ ተቋማት ትመራለች ። በተለይም ነፃ ፕሬሥ በበለፀጉት አገራት ህግ እንዲከበርና ዜጎች ፍትህ እንዳይነፈጉ ነገርን ከሥሩ እየመረመረ የላቀ ህጋዊ እገዛ ሥለሚያደርግ ከሦሥቱ የታወቁ የመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ “ አራተኛው መንግሥት “ እንደሆነ ታውቆ ይከበራል ። በዚህ ነፃ እና እውነትን ይዞ የሚሟገት ፕሬሥ እየታገዘም መንግሥት በትክክለኛው የሰው የፖለታካ አመራር መንገድ በመጓዝ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ።
ዜጎች የግል አሥተያየታቸውን ያለ መሸማቀቅ በተለያዩ የፕሬሥ ውጤቶች ላይ በየቀኑ ይሰጣሉ ። አፈና፣ወከባ፣እንግልት ቶርቸር የለባቸውም ። በህገ መንግሥታቸው ጥበቃ ይደረግላቸዋል ( እንደ እኛ አገር በወረቀት ላይ ብቻ የቀረ ህግ የላቸውም ! የእኛ መንግስት ግን ለምን ተናገራቸሁ እና ፃፋችሁ እንደ ታዲዮስ ታንቱ እና እንደ መስከረም አበራ ወዘተ ። የመሳሰሉትን ″ አሳብያን ″ በከንቱ ዛሬም አሥሮ እያሰቃየ ይገኛል ። እንደ ታዬ ቦጋለ አይነቱን ደግሞ ክፉኛ በማሰቃየት ፣ ጨካኝነቱ እንደ ጀብድ እንዲወራለት ያደርጋል ። እንዴት ሰው በተፈጥሮ የታደለውን አንደበት ዘግተህ ቁጭ በል ተብሎ በህዝብ ተመርጫለሁ በሚል መንግሥት ይታዘዛል ። ?
አዎ በአገራችን የህገ አራዊትነት ሥርዓት የወለደው ችግር አለ ። ጠቅላይ ሚኒሥቴር አብይ አህመድ ብቻቸውን አይፈቱትም ። የክልል ፕሬዝደንቶችም ለብቻቸው የሚፈቱትም አይደለም ። ሆኖም የመፍትሔው አካል ካልሆኑ የችግሩ አካል አለመሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ። በሰላማዊ መንገድ የሽግግር መንግሥት የሚቋቋምበትን እና ይኼየህገ አራዊት ሥርዓት የሚቀየርበትን መንገድ ተባብረው ይጥረጉ።
በበኩሌ አመፅ፣ ሁከት ፣ግጭት ና ትርምሥ በዚህ ወቅት እንደማያሥፈልግ አምናለሁ ። የአብይ የመደመር መንገድም መክሸፉን ተገንዝቤለሁ ። በመደመር ብቻ የሚሆን ምንም አይነት የፖለቲካ ሥርዓት የለም ። የመደመር ትውልድ ብሎ ነገርም የለም ። የጠቅላዩን የጭፍለቃና የጎሣ ፖለቲካ አካሄድም የመደመር መንገድ ብዬ ልወስድላቸው እችላለሁ ።
በአናቱም ፣ የእሳቸው ቲዎሪ እንደ ደመራ የሚያነድ እንጂ የሚያበለፅግ ከቶም አይደለም ። በዘረኞች መንገድ ተጉዞ የበለፀገ አገር በዓለም ላይ የለምና !
ኢትዮጵያን ዛሬ በመሥታወት ቤት ውሥጥ ያሥቀመጣት ይህ በህገ አራዊት መንገድ የሚጎዝ እጅ እግር የሌለው የመደመር መንገድ ነው ። ተደምሬለሁ ሥትለው አማራ ሥለሆንክ ቅንሼሃለሁ ይልሃል ።
ይኽንን የምለው ዛሬ የኦሮሞ ጦር ፣ የሱማሌ ጦር ፣ የደቡብ ጦር ፣ የትግሬ ጦር ፣ የአማራ ጦር ና የአፋር ጦር እየተባለ ፣ ዘራዊ ግጭትን በህገ አራዊትነት ተገፋፍቶ ፣ በመከላከያ ውሥጥ ለመዝራት የሚጥሩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን እያስተዋልኩ በመሆኑ ጭምር ነው ። ይኽ በግልፅ የመቀነስን መንገድ አጉልቶ ያሣያል ። ይኽ በመደመር ሥም የሚካሄድ የህገ ጨራዊቶች የመቀነሥ መንገድ እጅግ አደገኛ ነው ። በዜጎች እርብርብም በአፋጣኝ የውድቀታችን ጉዞ መክሸፍ አለበት ።
ዛሬ መንግሥት እየተጎዘበት ያለው መንገድ ፣ የግብዝነት መንገድ ነው ። የእብሪት እና የትዕቢት መንገድ ነው ። እናም እኛ ኢትዮጵያዊያን በዚህ አውዳሚ መንገድ መመራት አንሻም ። በቋንቋችን ፣ በባህላችን ሥም የሉሲፈርን መንግሥት ለማንበር እየተፈፀመ ያለውን ግልፅ የሆነ አገር አጥፊ ሤራንም አጥብቀን እንቃወማለን ።