አትሰቀል ይቅር! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

/

በገባለት ቃሉ – አባትህ ለ’ኛ አባት፤
አንተ ለኛ ሞተህ – ልንድን ከሃጢያት፤
እኛን አድናለሁ – ብለህ ከመከራ፤
መስቀል ተሸክመህ አትውጣ ተራራ::

በጨካኞች ጅራፍ – አይገረፍ ጀርባህ፤
ምስማር አይቸንከር – በጅና በግሮችህ፤
በጦር አይወጋ – አይበሳ ጎንህ፤
አትጠጣ ፍጹም – የሃሞት መራራ፤
አድናለሁ ብለህ – እኛን ከመከራ፤
መከራህ አይብዛ መከራችን ላይቀር፤
ተንገላተህ አትሙት አትሰቀል! ይቅር::

ተከባብሮ መኖር – አብሮ መብላት ቀርቶ፤
ጥላቻ፤ ጭካኔ – መከራ በርክቶ፤
ወንድማማችነት – ፍቅር መተባበር፤
አንድነት፤ ነፃነት – ፍጹም ጠፍተው ካገር፤
መቻቻል፤ ደግነት – ከሃገር ተሰደው፤
ግፍ በደል በርክቶ – ሞልቶ ፈሶ ጽዋው፤
ሰው ሆነን ሰው ካልሆን – ተፈጥረን ባምሳልህ፤
ከሰማየ ሰማይ – ወርደህ ከዙፋንህ ፤
አፈር ለባሽ ገላ : ከንቱ ሥጋ ለብሰህ፤
አትሰቀል በቃ! እኛን ላድን ብለህ ::

ይልቅስ ከሰሙህ እንዲህ ምከራቸው………!
እንደዚህ በላቸው – ስልጣን ላዋስካቸው……!

ስልጣን ተገን አርጎ – ቀምቶ የበላ፤
ለሥጋው አድልቶ – ወገኑን ያጉላላ፤
ዘረኝነት አርሶ – ቂም በቀል የዘራ፤
የሚያበዛ ት’ቢት – ሰው የሚያስፈራራ፤
ውሸት ያመረተ – በደል የከመረ፤
በግፍ የገደለ – ወህኒ ቤት ያጎረ፤
ጥላቻን አንግሶ – ፍቅርን ያኮሰሰ፤
ወንድሙን የገፋ – በደል ያነገሰ፤
ቁጣዬን አብዝቶ: መከራውን ያጭዳል፤
ሕዝቤን አታጉላሉ: ከንግዲህ ይበቃል !
ብለህ ንገራቸው………!
ልቦና ቢገዙ…. ድንገት ቢመለሱ.… ወደ ሕሊናቸው ::

ግን፤
የሕዝብህን ጩኸት – እየሰማ ጆሮህ፤
ስቃይ መከራውን – እያየኸው ባ’ይንህ
ሲካድ ሰብዕናው – ፈጥረኸው ባምሳልህ፤
ዝምታህ ከበዛ – ከዘገየ ፍርድህ፤
ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ: ላ’ባትህ ልናገር፤
ቁም ስቅልህ ይብቃ! እኛ አልዳንምና: አትሰቀል ይቅር!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ትርፍ ማግኘት አይቻልም- ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መግለጫ

አንድ ቀን

በፍትህ እጦት በወህኒ ቤት፤ በኑሮ ውድነት፤ በሥራ አጥነት፤ በስደት ለሚጉላው፤ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ማስታወሻ ትሁንልኝ::

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share