የጦቢያ ሰው ጣጣ…ያሬድ መኩሪያ

ይሻሻላል ያልነው፣ተስፋ ያረግንበት
በነነ እንደ ጭስ፣ተነነ እንደ እንፋሎት
ተሰወረ እንደ ጉም፣ሸሸ እንደ ሌሊት ወፍ
ሁሉም ተተራምሶ፣ጠፋ ቅጥ አንባሩ
አፈሩ አንገት ደፉ፣በለውጡ የኮሩ::
በቃ የጦቢያ ሕዝብ፣ሆነ እጓለ ማውታ
እረኛም የሌለው፣ሚጠብቀው ያጣ
እንደዚህ ተምታቶ፣ተናክሶ ተባልቶ
ፊቱ ቆሞ ያለ፣ይሄን የዓለም ፍዳ
በየቱ ጥበብ ነው፣ደርሶ የሚወጣ::
ምጣኔ ሀብት የለም፣በዕቅድ የሚመራ
ምድሩን የሞላው፣አገር አልበቃ ያለው
ቅርሻት ፓለቲካ፣ንጥቂያ ዝርፊያ ብቻ
ፍጥረተ ዓለም በዛ፣ቁጥሩ ገደብ አጣ
ምድርን አጣበበ፣ተበተነ እንደ ጨው
ተነዛ እንደ ጅብጥላ፣ፈላ እንደ ፌንጣ
ሚበላ ሚጠጣው፣መጠለያም ጠፋ::
የእምቦጭ እንዘጭ ኑሮ፣ደርሶ ማይቀየር
ማን ሄደ ማን መጣ፣ተጨማልቆ ማዝገም
ሞትን እንደ ውልደት፣ተላምዶ ዞር ማለት
ዘንድሮ ላይ ቆሞ፣ያለፈን መናፈቅ
አዙሪት እርግማን፣የጦቢያ ሰው ጣጣ…
ደስታው ተንቦግቡጎ፣ወዲያው የሚጠፋ::
        ~***•° **** °•***~
ጥፋቱ ውድመቱ እያደር ለሚብስ
የሰብእን ዓለማዊ ቆይታ ላከበደ ላከፋ
ሲኦልና ጨላማ ላረገ የሐበሻ ምድር
መዘከርያ
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ግንቦት ፲፬/፳፻፲፫ ዓ.ም
May 22/2021
ቅዳሜ)05:18(ሚኪ.ላ/አ.አ
©ያመጌዕ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስልኝ ላንተ በቁምህ ለሞትከው በደም ተጨማልቀህ ገምተህ ለሸተትከው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share