አዲስ አበባም ሆነች ወልቃይት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት አካል መሆናቸውን ማንም መካድ አይችልም ። በእኩልነት በኢትዮጵያዊነታችን ሊያስተንግዱ የሚችሉ የሁላችንም ናቸው። ነገር ግን የጎሳ ፓለቲካው ባመጣው መዘዝ፤ ዛሬ አዲስ አበባና ወልቃይት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት የህልውና ጥያቄና ”የጦር ሜዳ ” ለመሆን በቅተውል።
ጎሰኝነት መሰረቱ ጥላቻና ጠባብነት ብሎም ድንቁርና ባይሆን ኖሮ፤ አዲስ አባባ ከወልቃይት በተማረች ነበር። ወልቃይት የሰው ልጅ የስቃይ፣ የጎሰኝነትና የዘር ማጽዳት በደቦ አስተናግዳ፤ ዛሬም ለሌላ እልቂት ”ተዘጋጅ” እየተባለች ከበሮ የተደለቀባት ነው። አዲስ አበባም አሁን በያዘቸው የዘር ማጽዳና የዘረኝነት ጉዞ ከቀጠለች፤ የወልቃይት ዕጣ እንደሚደርሳት ነብይ መሆን አያስፈልግም።
ታዲያ የጎሳ አቀንቃኞች፤ ”ይበለው ምግብ፣ ይለብሰው ልብስ” ለሌለው ህዝብ፤ ከፋፈለው፣ አራቁተውና በገዛ አገሩ ምጻተኛ ማደረጋቸው አልበቃ ብሎ፤ አገር አፍርሰው” የመሃል አገሮቹ ግብዞች ”ኦሮሚያ የምትባል፤ የሰሜኖቹ ደግሞ አገረ-የትግራይ ሪፑብሊክ ስንመሰረት ከሰማይ መና አውርደን እናበለሃለን ። ዛሬ ብትሞትም ብትገደልም፣ ብትራብም ለአገር ግንባታ የሚከፈል መስዋትነት ነው ። ” እያሉ የአገርን አንጡራ ሃብት ዘርፈውና አራቁተው ፤ ጥይት ብብድር ዶላር እየገዙና ከኢትዮጵያ ጠላቶች የተቸራቸውን አውዳሚ የጦር መሣሪያ ለመከረኛው ወጣት ትውልድ እያደሉ ያጋድላሉ። እነሱ በሞቀ ቤት-መንግሥታቸውና በምቾት፤ ልጆቻቸውን ውጭ እያስተማሩ በይቀኑ አገርና ህዝብ የሚያፈርስ አጅንዳ ”ይፈበርካሉ”።
በ’ርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አሁንም በጎሳ ፓለቲካ አራማጆች አስከ ተገዛን ድረስ፣ በጎሳ ሀግ-መንግሥት እስከተዳኘንና በጎሳ ክልል እስከ ተከለልን ድረስ፤ የአገራችን መጭው ዘመን ከድጡ -ወደ ማጡ እንድሚሆን ያለፈው ጉዙዋችን ምስክር ለመሆኑ፤ ከየት ተንስተን ፤ የት እንድደረስን ለዓለም ሁሉ ገሃድ ሆኗል።
ምጽአተ-እስራኤል በተሰኘው መጸሃፍ ውስጥ አንዲ ወጣት፤”—-እንኳን የሚኖሩበት ፣ የሚሞቱለት አገር ያላቸው ዜጎች የታደሉ ናቸው።—-” ትላለች። እኛም ዛሬ የምንኖርበት አገር እያጣን ነው፤ ግን ልንሞትላት የሚገባን አገር አለችን። አሁን ካልታደግናት ግን ‘ እሳራኤላዊቷ እንዳለችው ”እንኳን የምንኖርባት የምንሞትላትም አገር እናጣለን።” ይህ እንዲሆን ደግሞ እንዲት እንፈቅዳለን? ቅደመ ኢትዮጵያዊያን አልፈቅዱም፤ እኛም መፍቀድ የለብንም።
ኦነጋዊ-ብልጽግና አዲስ አበባ ፤ ”ፊንፉኔ ኬኛ” ብሎ በዘረኝነት ኗሪውን የምድርን ስቃይ ሁሉ ሲያሳይ፣ ቤት ንብረት ሲዘርፍና ሲያፈርስ፤ ታሪካዊ ቦታዎችን ሲያጠፋ፣ ብሎም ከክፍለ አገር የሚመጡ አማረኛ ተናጋሪ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይግቡ ሲከለክሉ፣ የኦሮሚያ መዝሙር ሲያዘምሩ፣ አርማው ካልተሰቀል ሲል፤ መዲነዋን ለማጠርና ለመቆጣጠር፡ ”ሸገር” በሚል አዲስ ከተማ ለመፍጠር ፤ ህዝብ በርሃብ እያለቀ ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለድግስ እየዋለ፣ ከተማ በመግንባት ስም መስጊድና ቤተ-ክርስቲያን እየፈረስ፣ ቀሳውስትን ሳይቀር በድንጋይ ወግረው ሲግሉ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲያፈናቅሉ፤ —–ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ወይም አጅንዳው ሆኖ አልነበረም። የኦሮሞ ህዝብስ ፍላጎትና ምኞት በድሙ ከተዋህደው ኢትዮጵያዊ ጋርና መሰዋአትነት በከፈለባት አገር በሰላም ተባብሮና ተከባብሮ መኖርን የሚመርጥ ነበር። ግን ኦነጋዊ -ብልጽግናዎች በየግዜው በጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት እያላዘኑ፣ አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ ፤በልቶ ማደር የተሳነውንና ወ’ቶ መግባት ያልቻለውን ህዝብ፤ ከወገኑ ጋር ካላናከሱና ካላጋደሉ ስልጣን ይዘው አገርንና ህዝብን እየዘረፋ መኖር አይችሉምና።
የእኩይነትና የተራነታቸውን አጀንዳ ለማስቀጠል ”ፊኒፊኔ” ወደፊት ለምትመሰረተው ”ኦሮሚያ” ዋና ከተማነት እየገነባን ስለሆነ፤ በከተማዋ ላይ የኦሮሞን ማንነትና የህዝብ ስብጥር በእኛ ቁጥጥር ሰር መሆን አለበት።” በሚል ፤ በመዲናቸን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ዘመቻው ተጧጡፏል። ”ኦሮሚያ ያለ ፊኒፊኔ፤ ፊኒፊኔ ያለ ኦሮሚያ” በሚል ግብዝነት ለዘመናት በክፋም በደጉም አብሮ የኖረውን ህዝብና ለዘመናት የኖረችውን አገር በማፍረስ አንደ ጡት አባታቸው ወያኔ እነሱም ተጠምደውል።
ከዚህ ላይ ሰሞኑን ጠ/ሚ አብይ አህመድ ”ለሰምቶ አድር ”ፓርላማቸው፤ ”—ከፈለግን ኢትዮጵያን ማፈረስ እቅቶን አይደልም።—” በማለት ‘ርሳቸው ኢትዮጵያን ጠፍጥፈው እንደስሯት አድርገው ሊነግሩን ፈልገዋል። ግን የካድሪነት ባህሪያቸው ስለማይፈቅድላቸው እንጅ፤ ከዚህ በፊት ” ኢትዮጵያ አትፈርስም፡ ሊያፈርሷት የሚፈልጉ ግን ይፈርሳሉ። ታሪክ የሚያስተምረን ይህን ሃቅ ነው። ” ሲሉ አድምጠናል። በርግጥም ኢትዮያን ለማፍረስ የሚፈልጉ፣ እነሱ ቀድመው ይፈርሳሉ። ይህን ደግሞ የግዜ ጉዳይ እንጅ በራሳቸውና በተባባሪዎቻቻው ላይ አንድ ቀን ያዩታል።
—-ይዘገያል እንጅ ግዜ ውል አይስትም
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም።—-
ሌላው ዱቄት” ሆኗል የተባለውና ” ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን።” ያለው ”ትግራይ ሪፑብሊክ ያለ ወልቃይት” የሚለው የወያኔ አጀንዳ ነው።
አሜሪካ በተለምዶ ወልቃይት አይተባለ የሚጠራውን ”አገር” —ገና ጦርነቱ እንደ ተጀመረ ”–የአማራ ልዩ ኃይል ከምዕራባዊ ትግራይ ይውጣ።” ስትል ፤ የሱዳን ጦር ከምዕራብ ኢትዮጵያ ይውጣ ግን አላለችም፤ አስከ አሁንም አልተነፈስችም። ቡዚህ ወርም አሚሪካ በወልቃይት ላይ ”ጥሩምባዋን” ነፍታለች።
አሜሪካን ተከትለው የአውሮፓ ህብረትም አስተጋቡ። ታዲያ አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት በአንድ ልዋአላዊት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸው ጠፍቷቸው አይደለም። ግን ምዕራባዊያን ደከማ ”የአገሩን ልዕልና ማስከበር የማይችልና ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ውጭ ጎሰኛ የሆነ መንግሥት” ሲያገኙ ቀጭን ትዛዝ መስጠታቸው የተለመደ ነው። ታዲያ በዚህ መልዕክታቸው ወልቃይት ለ’ነሱ ዓላማ የምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነችና ለወያኔ ያላቸውን ፍጹማዊ ድጋፍቸውን በገሃድ የሚገልጹበትና የሚያሳዩበት ነው።
ብዙ ኢትዮጵያዊ ልብ ያላልነው ግን፤ በመጀመሪያው ዙር ጦርነት ገና የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል መቀሌን ሲቆጣጠር፤ ኦነጋዊ -ብልጽግና ”በሰላም” ሚኒስተሩ በአቶ ደንዳ ታየ አማካኝነት ነበር ”—የአማራ ልዩ ኃይል ከወልቃይትና ከራያ ይውጣ።የእኛ ዓላማ ህግ ማሰከበር እንጅ ‘ርስት ማስመለስ አይደለም። ” በማለት፤ በወያኔ ማይካድራ ላይ በ ሺዎች የታረዱት ዜጎች ደም ገና ሳይደርቅ ነበር ለአሜሪካ ማመልከቻውን ያስገቡትና አፍቅሮ ወያኔነታቸውን ያሳዩት።
ታዲያ ዛሬ ከዚያ ሁሉ እልቂትና ውድመት በኋላ አባትና ልጁ ወያኔና ኦነጋዊ -ብልጽግና ”አንድ አምሳል አንድ አካል ሆነው” ” ወልቃይትና ራያ ለትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ይመለሳሉ፤ ልዩ ኃይልና ፋኖ የተባለው ኃይልም ትጥቅ ይፈታል፡” ሲሉ ባልገረመን ነበር፤ መገረም የነበረብንስ ይህን ባይሉና ወደፊታም የተናገሩትን በተግባር ባይፈጽሙ ነው። ”ልዮ ኃይል” ሆነ ሌላው ከመከላከያ ውጭ የሆነ ኢ-መደበኛ ጦር ሁሉ ትጥቅ እንዲፈታ የተጠየቀው ገና በወያኔ ዘመንና በብልጽግና ጦርነቱ እስኪጀመር ድረስ ነበር።
በጎሳ የታጠቀ ኃይል ዙሮ -ዙሮ ጥፋት እንጅ ልማት አያመጣም። ጥያቄው ግን ለምን ዛሬ? ይህ የሚያሳየው የኦነጋዊ -ብልጽግና መንግሥት በኢትዮጵያዊነት ስም አታሎ ከህዝብ ጋር ያጋመደውን ገመድ ቆርጦ ከወያኔ ጋር መጋመዱን ሳያንሰው ” አሁንም ላታላችሁ” የሚል ይመስላል።
የወልቃይት ጉዳይ የዓለም አቀፍ ጉዳይ ሲሆን ከጀርባው “ትግራይ” የምትባል አገር ለማዋለድ የታቀደ መሆኑን በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ትላንትም ሆነ ዛሬ እየነገሩን ነው።
ማንማ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ”የትግራይ ሪፑብሊክን እንመሰርታለን” ብለው የተንሱ ፤ አሁንም በሰላም ስምምነት ስም ” ችግራችን የምንፈተው በህግ-መንግሥቱ” አማካኝነት ነው።” በሚል፤ ከኦነጋዊ – ብልጽግና ከባለተረኞቹ ጋር የተቧደኑ ቡድኖች ያለ ወልቃይት አገረ – ትግራይ እንደማትፈጠር ፤ በተለይም የዘመናት ግፍና በደል ቀንበር ተሸክሞ የዘር ማጥፋት የትፈጸመበት ህዝብ በዚች ስዓት ሌላ የብቀላ እልቂት እንደ ተደገሰለት መረዳት እይደለም ለሞት-ሽረት ትግል መዘጋጀት አለበት። በ’ርግጥ ኢትያጵያዊ ለሆነ ሰው የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህልወና መሆኑን መገንዘብ አይሳነውም። የትግራይ ህዝብም ከወልቃይት ህዝብ ጋር በሰላም ለዘመናት ”ቤቴ-ቤትህ ነው ፤ በክፍለ አገር ደረጃም ተከዜ የጋራችን ።” እያለ የኖረና አሁንም መኖር የሚፈልግ ነው። ግን የገዛ ወገናቸውን በጦርንት ካልማገዱ፣ ኢትዮጵያን የሚያፈራርስ አጅንዳ ከሌላቸው ፤ ወያኔዎች በስልጣን ላይ መቆየት አይደለም ፤ ሌላው ቢቀር በትግራይ ህዝብ ላይ ለፈጸሙት ግፍና በደል ተጠያቂ ስለሚሆኑ፤ ወልቃይት ያለትግራይ እንደማትኖርና እንዳልነበረች በማላዘን፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ለመስራት ፤ ያለፈው ሳይበቃቸው አሁንም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከበኩር ልጃቸው ከኦነጋዊ -ብልጽግና ጋር እየተደገሱ ነው።
ታዲያ ካለፈው ጦርነትና የሰው ልጅ መከራ ያተረፋት የመቀሌው ወያኔና የአራት ኪሎው ኦነጋዊ -ብልጽግና ሲሆኑ ፤ ለፈጸሙት ወንጀል ሁሉ ተጥያቂነት እንዳይኖር በማደረግ፤ ኢትዮጵያን አዳክመው ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ከወደቀበት እንዳይነሳ፣ ተሸናፊነቱንና አቅመ-ቢስነቱን እንዲያምን ፤ የእነሱን ወሳኝነት እንዲቀበል በተለመደው የክህደት እንደበታቸው በቁስሉ ላይ ጨው ይጨምሩበታል።
አሁንም በተለመደ የክህደትና የውሸት አንደበታቸው፤ በተለይም ላለፋት ዓምስት ዓመታት በህዝብና በአገር ላይ የተፈጸመው ግፍ ሁሉ ”ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ሲባል ነው ”ሲሉን መጸሃፍ እንድሚለው ” —ኅሊናቸው በጋለ ብረት እንደ ተተኮሰ— ” ሆኖ፤ ኅሊና ወይም እምነት የሚባል ነገር እንዳልተፈጠረባቸው ምግባራቸው ምስክር ነው።
ከዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ትግራይና ኦሮሚያ እንደ አገር እንዲመሰረቱ አጥብቀው ከሚያግዙትና ትልቁን የቤት ሥራ የሰጡት ግብጽና ሱዳንም ይገኙበታል። የሚገርመውና የእኛን ደካማነት የሚያሳየው ግብጽና ሱዳን ሶስተኛ ቢንሻንጉል የሚባል አገር ይወለድ እያሉ አሜሪካን እየወተወቱ ነው። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት አባይን ለመቆጣጠር የ“ አገረ ትግራይ እና የአገረ ኦሮሚያ “ መወለድ ብቻ በቂ አይደለም፣ ኤሪትራን ስናስገነጥልና ኢትዮጵያ ወደብና የባህር ጠረፍ ስለማይኖራት ደካማ ሆና የአባይን ጉዳይ የማታነስ መስሎን ነበር። ስለዚህ ”ኢትዮጵያ መበታተን ” አለባት ብለው ስራቸውን እየሰሩና እያሰሩ ነው።
ታዲያ አሁንም ብዙ ኢትዮጵያኖች አፍጥጦ የመጠውን ሃቅ ተቀብሎ ምን እናድርግ? እንዲትስ እንደራጅና ህልውናችንስ እንዴት እንታደግ ? —ብሎ ለመፍትሄ ከመሻትና ለማይቀረው
ትግል ራስን ከማዘጋጀት ይልቅ ፤ እንደ ሰጎን ጭቅላታችን አሸዋ ውስጥ ከተን ፤ ምክንያትና ትርጉም ፍለጋ እንደፍቃለን። ሰበብ ፍለጋ እንኳትናለን። ራሳችን ለራሳችን አገርና ህልውናችን ተጠያቂ መሆናችን እና ሙሉ ኃላፊነቱ የእኛ መሆኑን ዘንግተን ”የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝን” እንደ መፍትሄ ቆጥረን በየቀን እንገደላለን።
ብዙ ሃተታ ሳናበዛ ”ዱቄት” ሆኗል የተባለው ወያኔ ዛሬ አራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ግብቷል። ታዲያ ለማስመሰል እንኳን በደቡብ አፍሪካ ተሰማማንበት ካሉት አንዱም ሳይተገበር ፤ ሚልዮኖች አልቀው፤ መርፌ እንኳን የጠፋ ያህል ሳይከብዳቸው፤ እነሱ አጥፍቶ ለመጥፋት ወደፊት እያሉ ነው። እነሱ ማንነታቸውንና ዓላማቸውን ለአለፍት ሃምሳ ዓመታት በተግባር አሳይተውናል። ምርጫው የኛ የኢትዮጵያዊያን ነው።
አንድ ጀርመናዊ ፈላስፋ፤ ”— መገደልም ሆነ መግደል አልፈልግም፤ ግን ከሁለቱ አንዱን እንደመርጥ ከተገደድኩ ያለ ጥርጥር እገላለሁ።–” ነበር ያለ።
እኛ ከተባበርን እና ከተናበብን ብሎም ከተደራጀን ኢትዮጵያችን መታደግ እንችላለን። እናት ኢትዮጵያ ግዛቷ እሳት ውስጥ እንደገባ ፕላስቲክ እየተሸበሸበሽ፤ ከዚህ ለመድረስ የበቃችው በእኛ ድክመትና ጠላቶቻችን ጠንቅቀን ያለመዋቅና ከማን ጋር ቅድሚያ መታገል እንዳለብን ያለመገንዘብ ፤ ትግሉ የሚያስፈልገውን መሰዋአትነት ለመክፈል ዝግጁ ባለመሆናችን ነው።
እነሱ ለእኩይ ዓላማቸውና ለገንዘብ ፍቅራቸው የመንግስትን መመበር እስከማያዝ ደርሰው የገዛ አገራቸውንና ወገናቸውን ብሎም ኢትዮጵያን የሚያክል አገር ማፍረስና መበታተን ሲችሉ፤ እኛ ለህልውናችንና ለአገራችን አንደነት እንዴት በአንድነት ቆመን ወገናችን መታደግ ተሳነን?? ”የጠላትህ ጥንካሬ የአንተ ድክመት ነው።” የሚባለው ብሂል ተምረን፤ ዛሬም ሌሎችን መወንጀሉንና ማሳበባችን ትተን በጋራ – ለጋራ አገራችን ከታገልንና ካታገልን፤ ከተዘጋጀልን የእልቂት ወጥመድ ወጥተን ኢትዮጵያን መታደግ እንችላለን።
ለሚጠይቀው መሰዋአትነት ራሳችን ማዘጋጅት የግድ ይላል። በአገር ላይ ምንም ምን ቢሆን ተስፋ አይቆረጥምና። ከተስፋ በላይ ያለችውን አገራችን እያሰብን፣ የሁላችንም መዳኛ ለሆነችው ኢትዮጵያዊነታችንና ለህልውናችን ዘብ እንቁም። ለመነታረክና ለመጠቋቆም አሁን ግዜ የለም፤ አዎ! ግዜ የለንም፤ ኢትዮጵያ —ለኢትዮጵያዊነት ለወገናቸው ሲሉ እንደ ቅጠል በረግፋት ልጆቿ፣ በፈሰሰው ደማቸውና በደቀቀው አጽማቸው እየተማጸነችን ነው። አረንጓዲ፣ ቀይ ፣ ቢጫ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርጎ በክብር የሚያውለበልብላት ጀግና ትናፍቃለች።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!
——–//—— ፊልጶስ
መጋቢት /2015
e-mail: philiposmw@gmail.com