ክፍል-2
በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
መግቢያ
ባለፈው ጽሁፌ (በክፍል-1) በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተከፈተዉን ዘመቻ፤ ቀደም ብሎ ከነበሩት የተለየ እንደሆነና፤ በአገራችን ህልዉና ላይ ያንዣበበውንና “በብሄር ፖለቲካ” ተመርኩዞ የቆመዉን “የዘረኝነት ስርአት” አደገኛነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት፤ የእዚህ አስከፊ ስርአት መርዝ፤ በሀይማኖት ተቋሞች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች በሚባል ደረጃ ማለትም፤ በፖለቲካዉ፤ በኤኮኖሚው፤ በማህበራዊ ኑሮ፤ በመንግሥት መዋቅር፤ በፍትህ፤ በትምህርት፤ በፋይናንስና በባንክ፤ በሌሎችም እንደተሰራጨ ግልጽ ነው፡፡ አገራችን ከድህነት ተላቃ እንዳታድግና እንዳትገነባ፤ ወደፊትም እንዳትራመድ ሰቅዞ እንደያዛት ምንም አያጠራጥርም፡፡ በዉስጧ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ፤ ለህልዉናዋም ጸር እንደሆነ፤ በቅርቡ በትግራዩ ጦርነት በደረሰባት አደገኛ ፈተና እንኳን ለመረዳት ይቻላል፡፡
ባለፈው ለእዚህ ሁሉ ዉስብስብ የአገራችን ችግር መፍትሄው ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ ለአንባብያን አቅርቤ ነበር ጽሁፌን ያቆምኩት፤ ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ቢያግዝ በሚልም የአቅሜን አስተያየት ለመስጠት በክፍል 2 እመለስበታለሁ ብየ ቃል ገብቸ ነበር፤ ይኸዉና ዛሬ ይህችን አጭር ጽሁፍ በትህትና አቀርባለሁ፡፡ የጽሁፌ ዋና ዓላማ በተለይም በእዚህ ከባድና ዉስብስብ በሆነው የአገራችን አንገብጋቢ የፖለቲካ ጥያቄ፤ “በብሄር ፖለቲካ” ላይ የቆመዉን “የዘረኝነት ስርአት” መዘዙን እንዴት እናስወግደው በሚለው፤ ከተቻለ ሰፊና ጠለቅ ያለ አገር አቀፍ ዉይይት “በብሄራዊ ምክክሩ” አማካይነት እንዲከፈት በትህትና ለማሳሰብም ነው፡፡ በተጨማሪ ሀገራቸዉን አፍቃሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ በሚችሉት ሁሉ አቅም ሀሳባቸዉን እንዲያበረክቱ ለማበረታታትና፤ በጋራ መፍትሄ እንድናፈላልግ በትህትና ለማሳሰብና ድርሻየን ለማበርከት በሚል ነው ይችን አጭር ጽሁፍ የማቀርበው፡፡
የብሄር ፖለቲካ መነሾው ከየት ነው?
በቅድሚያ ይህን የመሰለ በጣም አስቸጋሪና አወዛጋቢ አስተሳሰብ ያዘለ “የብሄር ፖለቲካ” ወይም “ርዕዮተዓለም” ሊባል የሚችል ዘይቤ ወደ አገራችን እንዴት ሊገባ ቻለ የሚል ጥያቄ በብዙ ኢትዮጵያውያን ስለሚነሳና፤ ያለፈውን ትዉልድ “እሱ የተከለው መርዝ” ነው በሚል ብዙ ትችትም ስለሚቀርብ፤ ታሪኩን አጠር አድርጌ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ “የብሄሮች እኩልነት በኢትዮጵያ” የሚለዉንና ሌሎችንም ዴሞክራሲያዊ ጥያቄወች፤ በዋነኝነት “መሬት ለአራሹን” እና “ሕዝባዊ መንግሥት” የሚሉትን አንግቦ፤ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከድህነት፤ ኋላቀርነትና የባላባታዊ (ፊዉዳል) የግፍ አገዛዝ፤ እንዲሁም ከኢምፔሪያሊዝም የእጅ አዙር ተጽእኖ ነጻ ለማዉጣትና፤ ፍትሕ፤ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ዓላማ በመከተል፤ ከፍተኛ ትግል ካደረገዉና፤ ከባድ መስዋእትነትም በህይወቱ ሳይቀር ከከፈለው ትዉልድ የወጣሁ፤ በዕድልና በታምር ሊባል በሚችል አጋጣሚም ከተረፉት ጥቂቶቹ አንዱ መሆኔን አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ይህንም የምገልጽበት ዋናዉ ምክንያት፤ ከሌሎች በተለይም በመስዋእትነት ከወደቁት በሽ የሚቆጠሩ፤ ሀገራቸዉን አፍቃሪ ጀግኖች ወጣቶች፤ የእራሴን ኢምንት ታሪክ አጉልቸ ለማሳየት ሳይሆን፤ ዛሬ አገራችን ለገባችበትና መዉጫዉ ለጠፋበት “የብሄር ፖለቲካ አዙሪት” የአሁኑ ትዉልድ በደፈናዉ፤ እኔ ያለፍኩበትን ትዉልድ ዋነኛ ተጠያቂ ስለሚያደርግ፤ ያንን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ቢረዳ በሚል ነው፡፡ በመሠረቱ ማናቸዉም ትዉልድ ሀገሩን በየጊዜው ለሚያጋጥሟት ዉስብስብ ችግሮች፤ በስሜት ሳይሆን በዕዉቀት፤ በስማ በለው ሳይሆን፤ በጥናትና በምርምር ላይ የተመሠረተ መፍትሄ በማፈላለግ፤ በበኩሉ የእራሱን ድርሻ ማበርከትና፤ የአገሩንና የታሪክን አደራ ለመወጣት መጣር ይኖርበታል፡፡ ሁልጊዜ ያለፈዉን ትዉልድ በጭፍኑ ማዉገዝ ለአገራችን ችግሮች መፍትሄ አያመጣም፤ ለአገራቸው ሲሉ በህይወታቸው መስዋእትነትን እየከፈሉ፤ አገራችንን ተንከባክበው አቆይተው ያወረሱንን ወላጆቻችንና አያት ቅድመ አያቶቻችንን በደፈናዉ እያማረሩ መኖሩም ትክክል አይደለም፡፡ ጥፋትም ፈጽመው ከሆነ ከስህተታቸው በመማር፤ ጥሩም ከሰሩ፤ በእነሱ ስኬትና ተሞክሮ ላይ እየገነቡ፤ አገራችንን ለማሳደግ በመጣር ፋንታ፤ በቂም በቀል ባለፈው ትዉልድ፤ በአያት ቅድመ አያቶቻችን፤ ጥርስን እየነከሱ መኖሩ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ስንፍናን፤ የአስተሳሰብ ድህነትንና አቅም ማጣትንም ያዳብራል፡፡ ዕድል ብሎላት ታዲያ አገራችን በተደጋጋሚ በትዉልዶቿ እየደረሰባት ያለውና፤ እስከዛሬም መዉጫ ያላገኘችለት የቀዉስ አዙሪት፤ በድህነትም ወደኋላ ያስቀራትና ብዙ ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ያለው፤ አንዱም ይህ ጎጅና መጥፎ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡
የሆነው ሆኖ እኔ ያለፍኩበት ትዉልድ፤ “በብሄር ጥያቄ ላይ” የነበረው አመለካከት በጥቅሉ በሁለት ሊከፈል የሚችል ይመስለኛል፤ እርግጥ የሁለቱም ምንጭ በ60 ወቹ ካደገውና በአገራችን የፖለቲካ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን ካሳደረው የተማሪወች ንቅናቄ ነው፡፡ አንደኛዉ አመለካከት፤ አገራችን ኢትዮጵያ ብሄሮቿ ወይም ብሄረሰቦቿ በእኲልነት የሚኖሩባት አይደለችም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝባችን በብሄር፤ በቋንቋ፤ በጾታ፤ በባህልና በሀይማኖት ቢለያይም፤ ሁሉንም እኲል የሚያይና የሚያስተናግድ ዴምክራሲያዊና ሰብአዊ ስርአት ባለመኖሩ ነው ይልና፤ ለዚህም መነሾው በህብረተሰባችን የመደብ ልዩነት ስላለ፤ የመንግሥት አዉታሩን የሚቆጣጠረው፤ ኋላ ቀሩና በሕዝብ ላይ ግፍ የሚያደርሰው የባላባታዊው (የፊዉዳል) ገዥ መደብ ስለተንሰራፋ ነው የሚል እምነት ነበረው፡፡
በእዚህ ገዥ መደብም ከአንድ ብሄር፤ ሀይማኖት፤ ወይም አካባቢ ብቻ ሳይሆን፤ ይብዛም ይነስም ከተለያዩ ብሄሮች የመጡ አባላት አሉበት ይልና፤ በአጭሩ በህብረተሰባችን የሰፈነው ዋነኛ ቅራኔም በመደቦች መሀከል ያለው እንጅ በብሄሮች መሀል ያለው አይደለም ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህን ኋላ ቀርና ፍትሕ የለሽ የባላባታዊ (ፊዉዳል) ስርአትም አስወግዶ፤ ለሁሉም ዜጎች፤ የብሄር፤ የቋንቋ፤ የጾታ፤ የሀይማኖትና የባህል እኩልነትን የምታስተናግድና፤ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በነጻ በሚመርጡት መንግሥት የምትተዳደር፤ ህብረ ብሄርና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በምትኩ መገንባት አለብን የሚል ዓላማ አንግቦ ነበር ትግሉን ያካሄደው፡፡ እርግጥ ይህ አስተሳሰብ የአጭር ጊዜ ግቡ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በአገራችን ለመገንባት ይሁን እንጅ፤ ለረዥም ጊዜ ግቡ መዳረሻ ግን፤ የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለምን ዋና መመሪያው አድርጎና በዉስጡም ይዞ ነበር የሚጓዘው፤ በእዚህ አመለካከት ዙሪያ፤ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቁት ኢሕአፓና ሜኤሶን የነበሩ ሲሆን፤ ሌሎችም የህብረ ብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩበት፤ እኔም የኢህአሰ (የአሲምባ ሠራዊት) መሥራች አባል እንደመሆኔ መጠን፤ የኢሕአፓም አባል ነበርኩ፡፡
በአንጻሩ የእዚህ ትዉልድ ሌላዉ ካምፕ፤ ዘግየት ብሎ ከተማሪወች ንቅናቄ የተወለደውና፤ በዋነኝነት በህወሐት የሚመራዉ፤ በአገራችን ዋናዉ ትግል በመደቦች ሳይሆን በብሄሮች መሀከል ያለው ነው የሚል እምነት ይዞ ነው ትግሉን የጀመረው፤ እንደዚህ አመለካከት፤ በህብረተሰባችን የሰፈነው ዋናዉ ቅራኔ በመደቦች ሳይሆን በብሄሮች መሀከል ያለው ነው፤ ትግላችንም የብሄር ጭቆናን ለማጥፋት መሆን አለበት የሚል ነው፤ በዚህ አስተሳሰብ፤ ህወሐት “ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሄር” ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጥቅሉ በሁለት በመክፈል ነበር የሚያየውና የትጥቅ ትግሉንም የቀጠለው፤ በኋላም የመንግሥት ስልጣን ላይ የተቆናጠጠው ይህን የተዛባ አመለካከት እንደያዘ ነው፡፡ ጨቋኝ ብሄር የሚለዉም በተናጠል አማራን ሲሆን፤ በተጨቋኝ ወገን ግን ሌሎችን በሙሉ (ትግራይንና ኦሮሞንም ጨምሮ) ያካትታል፤ በአማራ ብሄር ዉስጥ ያለው አብዛኛዉ ዳሀ ገበሬ ሕዝብም “ከጨቋኙ የአማራ ብሄር” ከሚለው ጋር ይጠቃለላል፤ ለህወሐት የመደብ ትግል የሚለው በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ሲሆን ለትግሉም ወሳኝ አልነበረም፤ እየቆየ ሲሄድ ግን እንዴት የአማራን ብሄር ወይም ደሀዉንና ሰፊዉን ሕዝብ በሙሉ ጨቋኝ ትላላችሁ? ሲባል፤ ሌላ ቃል መወርወር ጀመረ፤ “የአማራ ጨቋኝ ገዥ መደብ” የሚል፡፡ በእዚህ አባባል እኛ መጥተን እስክናድናችሁ ድረስ፤ የሀገሪቱን የመንግሥት ስልጣን የያዘው አማራ ብቻ ነው (እኛ ትግሬወች ወይም ሌሎች እንደኦሮሞ ያሉት) አልነበረንበትም ማለቱ ነው፡፡ በዚህም አለ በዚያ እስከዛሬ አገራችንን በእሳት ዉስጥ የከተታትና እያመሳት ያለው ይህ ከጅምሩ የተዛባ፤ በጥላቻና “በጠባብ የብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ” ላይ የቆመ መርዘኛና ከፋፋይ ርእዮተ ዓለም እንደሆነ፤ ባለፉት 30 አመታት የነገሰው የህወሐት “የዘረኝነት አገዛዝ” እራሱ በቂ ምስክር ነው፡፡
ምናልባት “የብሄር ጭቆና” የሚባል ካለም፤ ከኃ/ሥላሴና ደርግ ዘመነ መንግሥት ይልቅ፤ በበለጠ በህወሐት አገዛዝ ነው ስር የሰደደው ቢባል ከእዉነት የራቀ የሚሆን አይመስለኝም፤ ለምን ቢሉ ህወሐት ብሄርን ተገን አድርጎ ሁሉንም ዘርፎች፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ፤ ኤኮኖሚ፤ ማህበራዊ ኑሮ፤ የሚሊታሪና ደህንነት፤ የክልል፤ የእምነት ተቋሞችንም ሳይቀር ከእራሱ ብሄር በወጡ ሹመኞችና ካድሬወች ይቆጣጠር ነበርና፤ ለእዚህ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ካላፉት መንግሥታት ግን ሌላዉ ቢቀር በአጭሩ ለማሳየት፤ የንጉሱን ባላባታዊ ስርአትና የደርግን መንግሥት ቁንጮ የያዙት፤ ኃ/ሥላሴና መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንኳን ሙሉ በሙሉ አማራ አልነበሩም፡፡
የሚያሳዝነው፤ ህወሐት ለጊዜው ቢነቀልም፤ መርዘኛዉና ለአመታት ስር የሰደደው “የብሄር ፖለቲካ ስርአት” ግን ከአገራችን እስካሁን ሊነቀል አልቻለም፡፡ ልክ እንደህወሐት ሌላ ብሄርን ተገን አድርጎ በተራዉ፤ የአገሪቱን የፖለቲካና የኤኮኖሚ፤ የማህበራዊ ኑሮ፤ የመንግሥት መዋቅርና ተቋሞችን በሙሉ ለመቆጣጠር እየታተረ ያለ “የገዥ መደብ” ተተክቶአል፡፡ ለእዚህ ሁሉ መንስኤ፤ “ለብሄር ፖለቲካዉና ዘረኛው ስርአት” ስረ መሰረቱና ግንዱ ደግሞ ህወሐት የተከለው ህገ መንግሥት እንደሆነ ምንም አያሻማም፡፡ በነገራችን ላይ፤ ደርግ እንደወደቀ ሥልጣን ለመያዝ ህገመንግሥቱን ሲያረቅ፤ በተቻለው መጠን ሌሎችን ተቀናቃኝ ድርጅቶች አግልሎ ወይም በስሩ አድርጎ “የትግራይ ልሂቃንን” ወደ ሥልጣን እንዲያወጣ አመቻችቶ ነበር ያነጸው፤ ይህ እንዲሳካለት፤ ከመጥፋት በታምር የዳኑትን፤ የህብረ ብሄር ድርጅቶች ኢሕአፓንና ሜኤሶንን፤ የመንግሥት ስልጣን መጋራቱስ ይቅርና፤ ህገ መንግሥት በሚያረቀው ጉባኤ ላይ እንኳን እንዲሳተፉ አልፈቀደላቸውም፡፡ ሕዝቡም በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፋና ጠለቅ አድርጎ አልተወያየበትም፡፡
ህወሐት የመንግሥት ስልጣን ላይ ከወጣም በኋላ፤ በተለይም በአማራ ብሄር ላይ ያለዉን የከረረ ጥላቻ በአገር ደረጃ የፖሊሲ መመሪያ በማድረግ ነው የቀጠለው፤ በሌሎች ብሄሮች፤ በተለይም በኦሮሚያ የተለያየ ስም፤ ለምሳሌ “ነፍጠኛ” “ወራሪ” የሚል ቅጽል እየተለጠፈበት፤ ምስኪኑ የአማራ ሕዝብ እንዲሸማቀቅ፤ በሕዝብ እንዲጠላና እንዲወገዝ፤ “መጤ” እየተባለም ወልዶና ተዋልዶ ተዛምዶ በሰላም ለአመታት ከኖረበት አካባቢው ዘሩ እየተቆጠረ ሳይቀር ተለይቶ እንዲፈናቀል፤ በግፍ እንዲጨፈጨፍ ነው የተፈረደበት፡፡ ዛሬ “ሸኔ” በሚል ስም የሚጠራዉ የኦነግ ክንፍም የአስተሳሰብ ምንጩ ከዚያ ሰይጣን አመለካከት ነው፤ ባጠቃላይ፤ ባለፉት 30 ዓመታት፤ ህወሐት በአገራችን በዘራዉ መርዘኛ “የብሄር ፖለቲካና” ባንሰራፋዉ “የዘረኝነት ስርአት” የተነሳ በብሄር፤ በመሬትና በሕዝብ ለሕዝብ ግጭትና መፈናቀል በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ንጹሀን ኢትዮጵያዉያን፤ ከሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች አልቀዋል፤ ቀያቸዉን እየለቀቁ በበረሀ ተሰደዋል፤ ለእረሀብና በሽታ ለሞትም ተዳርገዋል፡፡
በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለብዙ አመታት የኖሩት አማሮች በመጨፍጨፍና በመፈናቀል ብዙ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፤ የሚያሳዝነው ዛሬም በሁለቱ ክልሎች በተለይ በኦሮምያና በትግራይ “ጠባብ ብሄረተኞች” እና ጠባቂወቻቸው በተሰገስጉባቸው የክልል መንግሥታት፤ ይህ የዘረኛና ኋላ ቀር አስተሳሰብ መርዝ ሊገታ አልተቻለም፡፡ የአገራችንን ህልዉና እየተፈታተነ ይገኛል፤ የትግራይና የኦሮሞያ “ጠባብ ብሄረተኞችና ጽንፈኞች” በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ያላቸዉን ጥላቻ ከህሊናቸው ጨርሰው ሊፍቁት አልቻሉም፤ ጭራሽ ባሰባቸው፡፡ የሚያሳዝነው አልሆንላቸው ብሎ ነው እንጅ፤ ለዘመናት ተስማምተውና ተግባብተው በሰላም የኖሩትን፤ ሶስት ታላላቅ ሕዝቦች (ኦሮሞ፤ አማራና ትግራይ) ለመነጣጠልና፤ በመሀላቸው አንድነት እንዳይኖር ለማድረግ፤ ብሎም አገራችን ኢትዮጵያን ለመሰነጣጠቅና ለማፈራረስ እስከዛሬ ያልሸረቡት ሴራና ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም፡፡ ህወሐት በቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነት በአፋርና አማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ እራሱ ታሪክ አይረሳዉም፡፡ በአጋሩ “ሸኔ” በኦሮሚያ በተለይም በወለጋ እስካሁን የሚካሄደው የአማራ ድሆችን ጭፍጨፋና ማፈናቀልም፤ ታሪክ ምንጊዜም ይቅር አይለዉም፡፡ ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብም አልቀረለትም፤ ለእዚህ መርዘኛ “የብሄር ፖለቲካ” ሰለባ በመሆን በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ልጆቹን በጦርነቱ ገብሮአል፡፡ እንግዲህ የትኛዉን “ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” ነው “የብሄር ፖለቲካዉና ዘረኛ ስርአቱ” የጠቀመው? ከገዥወቹና የስርአቱ ጥቅም ተካፋዮች፤ ከሌቦችና ዘራፊወች በስተቀር!
ህወሐት በዘረጋዉ “የብሄር ፖለቲካ” መርዝና “የዘረኝነት ስርአት” ሳቢያ፤ ባለፉት 30 አመታት (በተለይም በቅርቡ 5 አመታት) በኦሮሚያና አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩትም ዜጎች፤ በደቡብ፤ በሶማሌ፤ በአፋር፤ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል፤ በክልል፤ በመሬትና በድንበር፤ በዘር ግጭት የተነሳ፤ በእርስበርስ ጦርነት፤ በጭፍጨፋና በመፈናቀል ምክንያት በብዙ ሽ የሚቆጠሩ አልቀዋል፤ ቀያቸዉን እየለቀቁ ተሰደዋል፤ በዚያ ሰቆቃ ላይ ድህነቱ፤ ሙስናና ዝርፊያዉ፤ የኑሮ ዉድነቱ ተደራርቦ ሕዝቡ ይሰቃያል፤ ይህ መጥፎ “የብሄር ፖለቲካና ዘረኛ ስርአት” ካልተቀየረ ወይም ካልተወገደ፤ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና እድገት መቸም አይመጣም! ህወሐት በሕዝብ አመጽ ተነቅሎ በ“ብልጽግና” ተተክቶም እንደሚታየው መሰረታዊ ለዉጥ እስከዛሬ ድረስ አልመጣም፤ የሚያሳዝነው፤ “የብሄር ፖለቲካን” ያስቆማሉ በሚል ሕዝቡ ትልቅ ተስፋ የጣለባቸው የብልጽግና መሪወችም፤ ታሪክ ሊሰሩ ሲችሉ ዕድሉን እስከዛሬ አልተጠቀሙበትም፡፡ ፓርቲያቸው ለእራሱ “በብሄር ፖለቲካ” ወገቡን ተተብትቦ፤ ያንን መፍታት አቅቷቸው፤ ወደፊት ለመራመድም አቅቶት መሀል መንገድ ላይ ቆሞ፤ ግራና ቀኝ እየተንገዳገደ፤ አገሪቱንም ይዟት እንዳይወድቅ እያሰጋ ነው፡፡ ከህወሐት ስህተት ተምሮ፤ አቅጣጫዉን ቶሎ እንደማስተካከል፤ እሱም በ”ኢህአደግ የቁልቁለት ጉዞ” በፍጥነት እየተንደረደረ ነው!
በኢትዮጵያ የ“ብሄር ፖለቲካውና የዘረኝነት ስርአቱ” የማያባራው መዘዝ፤
በ60 ወቹ መጀመሪያ ላይ በኃ/ሥላሴ ዩኒበርሲቲ ስማር፤ ተማሮች በተለያዩ ጊዜአት የደቡብ አፍሪካን የነጮች ዘረኝነት ስርአት ተቃዉመው በስብሰባና በሰላማዊ ሰልፍ ሲያወግዙ፤ እኔም አብሬ ለመሳተፍ ዕድል አግኝቸ ነበር፤ በወቅቱ እናት አገራችን ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን የነጮች ዘረኛ ሥርአትና የምእራባዉያንን በአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ በመቃወም አህጉሩን በመምራት ግንባር ቀደም ነበረች፡፡ በቅርቡ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ስንቱን በረሀና ዱር አቋርጠው መጥተው፤ ኦሮሚያ ድንበር ሲደርሱ፤ መታወቂያቸው እየታየ፤ ኦሮሞ የሆኑት እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው፤ የአማራ መታወቂያ የያዙት ግን በክልሉ ፖሊሶች አትገቡም እየተባሉ ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲገደዱ ሳይ ያ የረሳሁት ከ50 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ በዘረኝነት ስርአቱ ይደርስባቸው የነበረው ግፍ በህሊናየ ድቅን እያለብኝ ዉስጤን ህመም ይሰማኝ ነበር፡፡ ከእዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ፤ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ያዉም በኢትዮጵያ የነጭ ሳይሆን የጥቁር በጥቁር ዘረኝነት አያለሁ ብየ በህልሜም ሆነ በዉኔ አስቤው አላዉቅም ነበር፡፡ እነዚያ ለሀገራቸው ነጻነትና ለሕዝባቸው ሰብአዊ መብት ሲታገሉ ህይወታቸዉን ለመስዋእትነት አሳልፈው የሰጡት በሽ የሚቆጠሩ ወጣቶች (የሁሉም ብሄር ልጆች) በታምር ከመቃብራቸው ተነስተው፤ ሀገራቸውን ዛሬ ምን እንደምትመስል ቢያዩአት ምን ይሉ ይሆን ነው ያልኩት፡፡
በደቡብ አፍሪካ በ1950 ዓም (በፈረንጅ አቆጣጠር) ዘረኛዉ የነጮች መንግሥት ባወጣዉ ህግ (Group Areas Act) መሠረት፤ በሁሉም የለሙ ከተሞች አካባቢወች የሚኖሩት ጥቁሮችና ህንዶች፤ በዘራቸው እየተለዩ ተነቅለው፤ ልክ እንደዛሬይቱ “አዲሲቱ ሸገር ከተማና አዲስ አበባ” እንዲሁም በ”ብሄርና በቋንቋ” የታጠሩት የኢትዮጵያ ክልሎች፤ ከነጮች እርቀው፤ እርስበርስ እንዳይገናኙም ተደርገው እንዲሰፍሩ ነበር የተገደዱት፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር “ሸገር” የሚል ስም በተሰጠውና፤ አዲስ አበባን እንደቀለበት ዙሪያዋን ባጠራት አዲሱ ከተማ፤ ኦሮሞ ያልሆኑት በዘራቸው እየተለዩ፤ ቤታቸው በሌሊት በግሬደር በላያቸው ላይ እየፈረሰ ወደሌላ ቦታ እንዲሰደዱና እንዲሰፍሩ እንደተደረጉት፤ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮቹም ተመሳሳይ እጣ ነበር የገጠማቸው፡፡ በተግባር ሲዉል የነበረው ጭካኔና፤ በንጹሀን የሰው ልጆች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ግን የኢትዮጵያው ይብሳል፡፡ ሌሎችንም በርካታ ምሳሌወችን የደቡብ አፍሪካዉን የዘረኝነት ሥርአትና በኢትዮጵያ አሁን የተንሰራፋዉን “በብሄር ፖለቲካ” ስም የቆመዉን “የዘረኝነት ስርአት” የሚያመሳስሉትን መጥቀስ ይቻላል፤ ለጊዜው ግን እዚህ ላይ ላቁምና ወደእኛዉ የጉድ ታሪክ ላተኩር፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ “የብሄር ፖለቲካውና የዘረኝነት ስርአቱ” በፖለቲካዉ መስክ ላይ ብቻ እንኳን ያደረሰዉን ጉዳት ብንወስድ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ለምሳሌ በክልሎች የእዚያው ብሄር “ተወላጅ” ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች ዘራቸው እየታየ መሪ መሆን አይፈቀድላቸዉም፤ በሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶችም ከተመደቡ ዕድለኞች ናቸው፤ በመንግስት መዋቅሮች በተለይ ዜጎች በችሎታቸዉ፤ ተሞክሮአቸውና ዕዉቀታቸው ሳይሆን በአብዛኛዉ ዘራቸው (ብሄራቸው)ና ዘዉጋቸው እየታየ ነዉ ኃላፊነት የሚሰጣቸው፤ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ቢበዛም፤ በተለይ የአማራ ተወላጆች በከፍተኛ አስተዳደር እርከን እንዲመደቡ አይፈቀድላቸዉም፤ ለምሳሌ በትንሹ እንኳን የድሬዳዋን ከተማ ብንወስድ፤ አማራ የሚባሉት ቁጥራቸው የኗሪዉን አንድ ሶስተኛ ያክል ሆኖም እንኳን ከተማዋን ማስተዳደር አይፈቀድላቸዉም፤ የኦሮሞና ሶማሌ ብሄር ተወላጆች ናቸው በየአራት አመቱ እየተፈራረቁ ከተማዋን የሚመሯት፤ ሌሎችንም በርካታ የዘረኛ ስርአቱ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ያስከተለውን መጥፎ ክስተቶች፤ በህግ ተደግፈው የሰፈኑትን መጥቀስ ይቻላል፤ ቦታ ስለማይበቃን እዚህ ላይ ልተወዉና ለእዚህ ሁሉ ምክንያት “የብሄር ፖለቲካዉ”ና “የዘረኝነቱ ስርአት” መሠረት ወደሆነው በህገ መንግሥቱ ላይ ላተኩር፤ ከእዚያ ቀጥየም የመፍትሄ ሀሳቦች የሚመስሉኝን ጠቁሜ ጽሁፌን ለጊዜው አቆማለሁ፡፡
ህወሐት የተከለው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥትና፤ እሱ የወለደው “የብሄር ፖለቲካና የዘረኝነት ስርአት” መዘዝ፤
ገና ከጅምሩ፤ የህገ መንግሥቱ አንዱ ዋነኛ ችግር፤ “ብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝብ” ማለት ምን ማለት ነው? አንድነታቸዉና ልዩነታቸዉስ ምንድን ነው? ለምንስ የህገ መንግሥቱ አዉታር ሊሆኑ ቻሉ? ለሚሉት ጥያቄወች መልስ በግልጽ አለማስቀመጡ ነው፤ ይህን በታዋቂው አንቀጽ በ39 (ቁ፡5) ስር ለማብራራት ቢሞክርም በቂ አይደለም፤ “ብሄር ብሄረሰብ ሕዝብ ማለት፤ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶችና፤ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፤ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልዉና አለን ብለው የሚያምኑ፤ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸዉና በአብዛኛዉ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ይላል ህገ መንግሥቱ፡፡
እስኪ እግዚአብሔር ያሳያችሁ! እያንዳንዱን ቃል ወይም ሀሳብ አተኩራችሁ እዩትና፤ ከላይ በተጠቀሰው መስፈርት፤ በኢትዮጵያ ከ80 በላይ አሉ የሚባሉትን “ብሄር ብሄረሰቦች” ወስዳችሁ፤ ይህ ብሄር ነው ወይም አይደለም፤ ብሄረሰብ ነው ወይም አይደለም፤ ሕዝብ ነው ወይም አይደለም ብላችሁ በጥቂቶቹ ከቻላችሁ ብታስረዱኝ እንዴት ደስ ባለኝ! ለምሳሌ እዚህና እዚያ ተቆርጠዉና ተቀጥለው ብሄር ናቸው ተብለው የተካለሉትን የኦሮሚያንና የአማራን ክልል እንኳን ብንወስድ በዉስጣቸው የሚኖሩት ዜጎች በሙሉ ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ አያሟሉም፡፡ አንዱን መስፈርት “ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው” የሚለውን ብንወስድ፤ በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ቋንቋወች አማርኛንና ኦሮምኛን ጨምሮ ሕዝቡ ለመግባቢያ ይጠቀማል፤ ከእዚያ በላይ ቀደም ብሎ፤ በሁለቱም ክልሎች፤ በተለያዩና አንዳንዶቹ ጨርሶ በማይዋሰኑ ወይም በማይገናኙ አካባቢወች፤ አዉራጃወችና “ክፍለ ሀገሮች” ነው ሕዝቡ የኖረው፤ ስለዚህ እንዴት ብሎ ነው በህገ መንግሥቱ (አንቀጽ 39 ቁ 5) በተሰጠው መስፈርት (ለምሳሌ በቋንቋ)፤ አንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ አንተ የኦሮሞ፤ የአማራ ወይም የቤኒሻንጉል ብሄር አባል ስለሆንክ የእዚህ ክልል አባል ነህ ብለን ልንለየውና ልንመድበው የምንችለው? የዘሩንስ እንተወው! “የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸዉና” “የጋራ ወይም የተዛመደ ህልዉና አለን ብለው የሚያምኑ” የሚለዉንም እንዴት ነው ለማወቅና መለየት የሚቻለው? አንደድሬዳዋ፤ ሐረርና አዲስ አበባ ባሉ የብዙሀን ከተሞች በተለይ፤ ከተለያየ ብሄር ተጋብተው፤ ወልደዉና ተዋልደው የሚኖሩትን እንዴት ብለን ነው ብሄራቸዉን የምንለየው? ባጠቃላይ ህወሐት ባስቀመጠው መስፈርት እንኳን ብንሄድ፤ መጀመሪያ የተካለሉት ዘጠኙ ክልሎች በቂ ጥናት ተካሂዶባቸው “ራስን በራስ ለማስተዳደር” ወይም “ለፌደራል አስተዳደር” አመች ብሄሮች እንዲሆኑ ታስቦ ሳይሆን ለሌላ አጀንዳ ነበር የተዋቀሩት፡፡ እሱን ከታች በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
በተጨማሪ ህገ መንግሥቱ “በብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ” ተወካዮቻቸው ነው የጸደቀው የሚለውም ፍጹም ስህተትና ከታሪክ ጋር የማይገናኝ ሀሰት ነው፤ ብሄርን ብሄረሰብንና ሕዝብን እንወክላለን የሚሉ “የብሄር ፖለቲከኞች” ያጸደቁትና ቀስ በቀስ “የዘረኝነት ሥርአት” በአገራችን የተከሉብን መዘዝ እንደሆነ ያለፉት 30 ዓመታት ምስክር ናቸው፡፡ ከሁሉም የከፋ ደግሞ፤ ህገ መንግሥቱ በተለይም አንዳንድ አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾቹን (ለምሳሌ አንቀጽ 39) በቀላሉ እንዳይሻሻሉ ተብትቦ ማሰሩ ነው፡፡ ህገ መንግሥት የሚደነገግበት አንዱ ዋና ምክንያት፤ በዜጎች መሀል ብሄራዊ ስሜትንና መግባባትን እያዳበረ፤ የህግ የበላይነትን እያስከበረ፤ አገርን በጋራ ለመገንባትና ለማሳደግ መሰረት እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህገመንግሥት ግን ብሄራዊ መግባባት ሊፈጥርና፤ አገር ለመገንባት ሊያግዝ ቀርቶ፤ ሆነ ተብሎ ዜጎችን ለማራራቅና ለመከፋፈል ብሎም ካስፈለገ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የታቀደ ሴራ እንደሆነ በተግባር፤ ባለፉት 30 ዓመታትና፤ በቅርቡም በትግራይ ጦርነት በግልጽ ታይቶአል፡፡
የሚገርመው፤ ታዋቂው አንቀጽ 39 እራሱ “የብሄሮችን የእራስን በእራስ የማስተዳደርና የመገንጠልን መብት ጨምሮ” የሚለው፤ መብት በህገ መንግሥቱ የተካተተው፤ በቀላሉ ከማይቀየሩት በምእራፍ 3 (“መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች”) ከገቡት አንቀጾች ጋር ተሰንቅሮ ነው፤ ይህን አንቀጽ ለማሻሻል ለዚያዉም ከተቻለ፤ ብዙ ዉጣ ዉረድ አለው፡፡ በአሁኑ ህገ መንግሥትና በብሄር (ዘር) ላይ በቆመው “የፌደራል አወቃቀር” እሱን ለመንካትና ለማሻሻል በጣም አዳጋች ነው፡፡ (አንቀጽ 104 እና አንቀጽ 105 ን ይመልከቱ)፤ በአጠቃላይ ከህገ መንግሥቱ በርካታ መሻሻል የሚገባቸው አንቀጾችን መጥቀስ ይቻላል፤ እሱን ለማድረግ ግን የእዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ሙያየም አይፈቅድልኝም፤ ከተሳካልኝ “ለብሄራዊ ምክክሩ” እንደኢትዮጵያዊነቴ ሀሳቤን አቀርባለሁ፡፡ አሁን የሚያስጨንቀኝ “የብሄራዊ ምክክሩስ” ቢሆን እራሱ ይካሄዳል ወይ የሚለው ነው! አንድ ለአገራችን ሰላምና ህልዉና የቀረን መፍትሄ እሱ ብቻ ነበር፤ ይሁን እንጅ፤ እሱም አደጋ ላይ እየወደቀ ነው! በሀገሪቱ በሞላ ሰላምና መረጋጋት በጊዜአዊ መልክ እንኳን ካልሰፈነ፤ እንዴት ብሎ “ብሄራዊ ምክክር” እና ሕዝባዊ ዉይይት ማድረግ እንደሚቻል አንዱ ፈጣሪ ነው የሚያዉቀው!
የ”ፌደራል” አወቃቀሩ፤
የ”ብሄር ፖለቲካዉ ህገ መንግሥት” አንዱ ዋና በአገራችን ላይ የፈጠረው ጦስ፤ የብሄር ጥያቄን ጭራሽ በአገራችን ለዘመናት ገና ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት “ከመሬት ጥያቄ” ጋር ማወሳሰቡና መተብተቡ ነው፡፡ ለዚያም ነው አንዱም መፍትሄ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው፡፡ ህወሐት ሀገሪቱን በብሄር (ዘር) ከከፋፈለ በኋላ፤ ክልል በሚል ስም መሬቷን በመሸንሸን አድሎ፤ “ይኸዉላችሁ እንደፈለጋችሁ አስተዳድሩ” ሲላቸው፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ እነዚህ የ“ክልሎች፤ ብሄሮችና ብሄረሰቦች” ፖለቲከኞች አንዳንዶቹ ወሰናቸዉን ለማስፋፋት፤ ሌሎቹ በድንበርና በግዛት በመጣላት ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨታቸዉን ቀጠሉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ የሀገሪቱን ዋና ከተማ ምናልባትም ከ80 ወቹ “ብሄሮችና ብሄረሰቦች” የመጡ ዜጎች ያለስጋት በሰላምና በፍቅር ተዋህደው የሚኖሩባትን አዲስ አበባን “ፊንፊኔ የእኛ ክልል ሀብት” ናት የሚሉ ተነሱ! ገና ከጅምሩ፤ የህወሐት መሪወች ኢትዮጵያን ማስተዳደሩ አንሷቸው፤ ለመጠባበቂያ የእራሴ የሚሉትን የትግራይን ክልል አስፋፍተው፤ ተከዜን ተሻግረው፤ ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን፤ እንዲሁም ከላይ ራያን በጉልበት ነጥቀው “ህገ መንግሥቱ የሰጠን” የእኛ ሀብት ነው ሲሉ ነው ነገር የተበላሸው፤ ለዘመናት በሰላም አብረው ጎን ለጎን የኖሩትን ሁለቱን ሕዝቦች፤ አማራንና ትግራይን ደም አቃብተው ለመለያየትና አገራችንም ለማፍረስ ስንት ወጣት አስጨረሱ፡፡
ስለዚህ የኋላ ቀር ስርአት መቆሚያ የሆነውና ፍትሕ የጎደለው ህገ መንግሥትና “የፌደራል ክልል አወቃቀር” የተተከሉት በዋነኝነት በአገራችን ዴሞክራሲ ለማስፈን፤ ወይም “ብሄሮች እራሳቸዉን በእራሳቸው እንዲያስተዳድሩ” ታስቦ ሳይሆን፤ አገሪቱን በዘርና በብሄር በክልል ከፋፍሎ፤ በስልጣን እስካሉ ድረስ መሬትና ሀብት ያለገደብ እየዘረፉ ለመግዛት፤ አለዚያም ካልተቻለ የእራስን ሰፊ ክልል ወይም ብሄር ይዞ ለመገንጠል ነው ቢባል ከእዉነት የራቀ ሚሆን አይመስለኝም፤ ለእዚህ ነው በብሄር ፖለቲካና በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተው “የፌደራል ሥርአት” ተብየዉ የክልል አስተዳደር መዋቅርም፤ ዛሬ ጭራሽ የአገሪቱን ህልዉና እየተፈታተናት ያለው፡፡
ህወሐት (ኢሕአደግ) ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት በገዛበት ወቅት “ብሄሮችና ብሄረሰቦች” የተባሉት እራሳቸዉን በእራሳቸው ሊያስተዳድሩ ቀርቶ፤ በላያቸው ላይ የአንድ ብሄር የገዥ መደብ (የህወሐት) ወኪሎች በፓርቲ ስም እየተመደቡላቸው፤ የእራሱን ስልጣን ለማስጠበቅ በአምባገነንነት የሚገዙና፤ የክልሉንና የሕዝቡን መሬትና ሀብት የሚዘርፉ ነበሩ የሚያስተዳድሯቸው፡፡ የሚያሳዝነው ባለፉት አምስት አመታት ህወሐት ከማእከላዊ ስልጣኑ ተወግዶም ስርቆቱ፤ የሀገሪቱን ሀብትና መሬት መዝረፉና፤ በሕዝቡ ላይ ግፍ መሥራቱ ሊቆም ቀርቶ ጭራሽ ባሰበት፡፡ የህወሐት ተማሪወች ተተኩበት! አዲሱ የብልጽግና ፓርቲም “ከብሄር ፖለቲካዉ” (“ዘረኝነት ስርአቱ”) ሊላቀቅ አልቻለም፤ ሕዝቡ እንደዚያ የጓጓላትን፤ ነጻነት፤ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት፤ ትክክለኛዉን አቅጣጫ መያዝ አልቻለም፤ ዛሬ ሕዝቡ በእሱም ተስፋ እየቆረጠ ነው፤ እንደህወሐት ጊዜው ሳይመሽበት፤ በቆራጥነት ተነሳስቶ አቅጣጫዉን ያስተካክላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አለዚያ እሱም የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል!
“የብሄር ፖለቲካዉንና ዘረኝነቱን” አስወግደን፤ ኢትዮጵያ አገራችንን፤ በሀገር ፍቅር ስሜት በጋራ ለመገንባት፤ መፍትሄው ምንድን ነው? ምን ማድረግ ይሻለናል?
በሚቀጥለው ጽሁፌ (ክፍል 3) ይህን ትልቅ አርእስት በተለይም በህገ መንግሥቱና “የፌደራል ስርአቱ” ዙሪያ ላይ በማተኮር በምችለው አቅም ለማብራራት እሞክራለሁ፤ እስከዚያ ግን አጠር አድርጌ፤ የሚከተሉትን መንደርደሪያ ሀሳቦች በትህትና አቀርባለሁ፤
1ኛ የ”ብሄራዊ ምክክሩ” ስኬታማ እንዲሆን በሚገባ መምራትና ሕዝቡን በሰፊው ማሳተፍ፤ በተለይም መንግሥት በቆራጥነት፤ በቅንነትና በግልጽነት ምክክሩ እንዲሳካ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ከልቡ መሥራት ይኖርበታል፤
2ኛ በህገ መንግሥቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ፤ ካለፈው ስህተት በመማር፤ ሕዝቡ ያለፍርሀት በነጻ እንዲወያይበት ማድረግ፤
3ኛ በክልሎች መሀል አወዛጋቢ የሆኑትን የማንነትና የመሬት ጥያቄወች፤ በሰላምና በዉይይት፤ በሕዝቡ በእራሱ ፍቃድ እንዲፈቱ ሁኔታወችን ማመቻቸት፤ ብሄራዊ ምክክሩን “የብሄር ፖለቲከኞች” ከሕዝቡ ጠልፈው እንዳያመክኑት መጠበቅ!
4ኛ በ”ፌደራል” (ክልል) አወቃቀሩ ሕዝቡ በሰፊው እንዲወያይበትና ሀሳቡን እንዲሰጥበት ማድረግ፤ የሀገሪቱን መሬት “በብሄር ብሄረሰብ መከፋፈሉ” ተሻሽሎ፤ ለሀገር ሰላም፤ መረጋጋት፤ ለጋራ እድገትና አንድነት፤ “ህብረ ብሄርና ፌደራል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ”ን ለመገንባት አመች የሆነ ፍትሐዊ የክልል አስተዳደር እንዲመሠረት ተግቶ መሥራት፤
5ኛ “ህገ መንግሥቱ አይነካም! ወይም ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት! የሚሉትን ሁለት ጫፍ ይዘው “ገመድ የሚጎትቱትን” ማዳመጥ ትተን “ህገ መንግሥቱ ይሻሻል” በሚለው አቋም እንጽና! በ230 ዓመት እድሜው የአሜሪካን ህገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ሳይቀየር 27 ጊዜ ተሻሽሏል፤ ከማሻሻያወቹ አንዱ (Amendment 13) ባርነትን በአሜሪካ ያስቀረው አንቀጽ ነው፤ ሕዝባችን ከተስማማ በኢትዮጵያም ህገ መንግሥቱ “ፖለቲካ በብሄር ሀይማኖትና ዘር ጣልቃ እንዳይገባ” ወስኖ፤ በአገር ላይ ብቻ ያተኮሩ፤ ሀገር አቀፍና ህብረ ብሄር የሆኑ ፓርቲወች እንዲመራ ማድረግ ይቻላል፤ ይህ መሻሻል (Amendment) እራሱ ትልቅ እፎይታና ሰላምን በአገራችን ያሰፍናል!
እነዚህን ሀሳቦች በክፍል 3 ለማብራራት እሞክራለሁ፤ በደህና ቆዩኝ! እስከዚያ ለአገራችን ቸር ወሬ ያሰማን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ! ሰላም ያዉርድልን!
ዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
በሀገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ ደራሲ
የካቲት 23 ቀን 2015 ዓም (March 2nd, 2023)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የገጠማት አንዱ ፈተና ጦስ መውጫ የታጣለት ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› አዙሪት ነው!
(ክፍል አንድ)
በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ዝናን ካተረፉላት ታላላቅ የባህልና የታሪክ ቅርሶች አንዱና ዋነኛው፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የዘርና የብሔር አጥር ሳይከልላቸው ሕዝቦቿ፣ ለዘመናት ተከባብረው፣ ተቻችለው፣ ተፋቅረው፣ ተሳስበውና ተዛዝነው፣ ተጋብተውና ተዋልደው፣ ያገኟትን አብረው ተካፍለው እየበሉ መኖር መቻላቸው ነው፡፡ ይህን ግሩም የሆነ የአገራችን ቅርስ ህልውናና ቀጣይነት፣ በየጊዜው ፈተና ውስጥ የሚያስገቡት መንግሥታትና መሪዎች እንጂ ሕዝቡ ራሱ አይደለም፡፡ ለዚህም መልካም ባህል መገንባትና ዘመን ተሻጋሪ መሆን፣ የአገራችን ቤተ እምነቶች፣ በተለይም ታላላቆቹ የጥንት ሃይማኖቶቿ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና እስልምና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እነሱ እርስ በርስ ተከባብረውና ተቻችለው፣ ኅብረተሰቡንም እንደ ድርና ማግ አዋህደው፣ ሕዝባችንን በአገር ፍቅርና የአንድነት ስሜት አስተሳስረው ለአገራችን ዋልታና ማገር በመሆን፣ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሠረት ላይ አቁመው ለዘመናት ካዘለቋት መልካም ቅርሶች ዋነኞቹ እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡
በተለይም ዕድሜ ጠገቧና ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገራችን ለምትታወቅባቸው መልካም ቅርሶች፣ የመቻቻል፣ የትዕግሥት፣ የሰላምና የእርቅ እሴቶች ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ለእነዚህ በገንዘብ የማይተመኑ የኅብረተሰብ ፀጋዎች ፅኑ መሠረትና ጠንካራ ምሰሶ ሆና ለዘመናት እንደዘለቀች ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከአንድ ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት በ7ኛው ክፍለ ዘመን፣ ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸው በእምነታቸው ምክንያት ሲሳደዱባቸው፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይቷ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ሲያደርጉ፣ ያለ ምንም ማመንታት እጆቿን ዘርግታ በፍቅር አቅፋ በመቀበል፣ እምነታቸው ተከብሮ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ተዋህደው፣ ያለ ምንም ሰቀቀን በሰላም እንዲኖሩ በመፍቀድ፣ የሃይማኖት ነፃነትንና የመቻቻልን ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ፈር የቀደደች፣ የምታኮራዋና እንቁዋ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ለመሆኗ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት፣ መብትና ሕግ የሚባል በየትም ቦታ፣ በአውሮፓም ሆነ በእስያና በአሜሪካ አኅጉር በማይታወቅበት የጥንት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ያንን አስደናቂ ታሪክ ለመሥራትና ለዓለም ኅብረተሰብ ለማስተማር የቻለች፣ እስከ ዛሬም እያስተማረች ያለች፡፡ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሌሎች አገሮች የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት መብት የሚባል በሕግ መደንገግ የተጀመረው፣ በኢትዮጵያ ከተባረከ ቢያንስ ከአንድ ሺሕ ዓመት በኋላ ነበር፡፡ እስከዛሬ ይህን ሰብዓዊ መብት ማስከበር አቅቷቸው ሰላም ያጡና የፈረሱ አገሮችም በርካታ ናቸው፡፡
የሚያሳዝነው ግን ይህን የመሰለ የሚያኮራ ሀብት በያዘችና የመቻቻልና የፍቅር ታሪክ ባለፀጋ በሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት፣ ‹‹የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት›› ከተተከለባት ጊዜ አንስቶ፣ የመሪ ዕጦትና የአስተሳሰብ ድህነት ልክፍት ተጠናውቷት፣ በሕመም እየተሰቃየች ትገኛለች፡፡ ባለፉት ዓመታት፣ በተለይም በሁለቱ ታላላቅ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በእስልምና የውስጥ ጉዳይ፣ ፖለቲከኞች ጣልቃ እየገቡ መርዝ በመርጨትና እርስ በርስ በማናቆር፣ ከዚያም አልፎ በዘር፣ በቋንቋና በብሔር እየከፋፈሉ ለማጋጨት ብዙ ጥረዋል፡፡ ቢችሉም እነዚህን ተቋማት በካድሬዎቻቸው ለመቆጣጠርና በተዘዋዋሪ መንገድ የእነሱ ወይም የመንግሥት ቅርንጫፍና ተገዥ ለማድረግ፣ አለዚያም ከባሰ በውስጣቸው ገብቶ ምዕመናኑንና መሪዎችን በማፈላለስ፣ አገራችንን ለመሰነጣጠቅ ሌትና ቀን ሴራ ሲሸርቡ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ እነዚህን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ታላላቅ የአገራችን ቅርሶች፣ በውስጥና በውጭ ጠላቶቻችን ጥቃት እንዲፈጸምባቸውና የአገራችንም ህልውና በተደጋጋሚ ለአደጋ እንዲጋለጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተው አደገኛ ዘመቻም የዚያ ሴራ አንዱ ዘርፍና ተቀጽላ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡
ያም ሆኖ ግን የአገራችን ጠላቶች እስከ ዛሬ በሃይማኖት ሳቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ አልተሳካላቸውም፡፡ በርካታ ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶች በተደጋጋሚ ሲቃጠልባቸው፣ የሁለቱ ሃይማኖቶች ምዕመናንና መሪዎቻቸው በመደጋገፍ በሚያስደንቅና ሌሎች አገሮችን በሚያስቀና ኅብረት እየተጋገዙ መልሶ በመገንባት፣ እንኳን እርስ በርሳቸው ሊጋጩ ቀርቶ አንድነታቸውን በማጠናከር፣ ጠላቶቻቸውን በጋራ በመመከት ለመቋቋምና እስከዛሬ ድረስ በስኬት ለማለፍ ችለዋል፣ ለወደፊቱም ይችላሉ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምናልባትም በታሪኳ አይታው የማታውቀውን አደገኛና ከባድ ፈተና ሲያጋጥማትም በርካታ የአገራችን የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ ከሌሎች እምነቶችና ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ማኅበራት ሸንጎ ጋር በመሆን ፈጥነው ድጋፋቸውን ሰጥተዋታል፡፡ በዚያም በክፉ ቀን ከጎኗ ስለቆሙላትና በጭንቋ ስለደረሱላት ለሁሉም የሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን ምሥጋናዋን ለግሳቸዋለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለያዩዋቸው ለአገራቸው አንድነትና ሰላም ምን ያህል በጋራ እንደሚቆሙ እንደገና አስመስክሯል፡፡
የዚህ ዓይነት የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ኅብረት በተለይ የቤተ ክርስቲያኗና የአገራችን አንድነት ጠላቶችን፣ ‹‹የጠባብ ብሔርተኛ ፖለቲካን›› አቀንቃኞችንና ጽንፈኞችን ቅስም ነው የሚሰብረው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሁሉንም ዘዴያቸውን ሞክረው ሞክረው፣ በቋንቋ በዘርና በብሔር የእርስ በርስ ግጭት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቢያቅታቸው፣ ተስፋ በመቁረጥ ከሌላ አቅጣጫ ነው የመጡት፡፡ ለአገር ፍቅርና አንድነት፣ ለሕዝቦቿ መቻቻልም ዋና መሠረት ሆና ለዘመናት የዘለቀችውን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ ከሥሯ በመቦርቦር ገፍቶ ለመጣልና ለመበታተን ነው አደገኛና አዲስ ጥቃት የከፈቱት፡፡ በተለመደው እኩይ ዘዴያቸው ሕዝቡን ከፋፍለው አገራችንን ማፍረስ ቢሳናቸው፣ አንድ የቀረውንና የሚያገናኘውን ጠንካራ ክሩን ሃይማኖቱን በጣጥሰው በመጣልና እርስ በርስ በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው ጥረታቸው፣ አይሳካላቸውም እንጂ፡፡ ሳያስቡት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደተለመደው በአንድነት፣ ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ እንዲነሳ ነው የቀሰቀሱት፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች በተለመደው ጥበባቸው ምዕመናኑንና በአጠቃላይ በውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለውን አገር ወዳድ ሕዝብ በጥንቃቄ በመምራት ሕዝቡ ብሶቱንና ግፉን በትዕግሥት፣ በፆምና በፀሎት፣ በተስፋና በዕንባ ለፈጣሪው አቤቱታውን በማሰማት እንዲታገል ለምነው አበረዱት እንጂ፣ ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል እንደ ሕዝቡ ሐዘንና ከፍተኛ ቁጣ፣ አገራችን እንዴት ያለ መአት ሊወርድባት ይችል እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ የአገሪቱ መሪዎች፣ የሕዝቡን ጩኸትና የቤተ ክርስቲያኗን ስሞታ በጥሞና አዳምጠው፣ በቅንነትና በብልኃት በጋራ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ካላገኙለት አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ላይ አደጋው እንዳንዣበበ ነው፣ ጉሙ ገና አልገለጠም፡፡
ደግነቱ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል፣ የአገር ፍቅር ስሜትና፣ ፅኑ የሆነ እምነት ስላላቸው ጠላቶቿ ብዙ ሞክረው አገራችንን እስከ ዛሬ ለማፍረስ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ እምነታቸውንና አገራቸውን የሚፈታተን ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያያቸው፣ በጩኸት ተጠራርተው ይሰባሰቡና፣ ጠላቶቻቸውን በጋራ ይመክታሉ፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለዘመናት በዘለቀው፣ እንደ ብረት በጠነከረውና በማይበገረው መሣሪያቸው፣ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በፆምና በፀሎት፣ ሲብስም በቆራጥነት እየተዋጉና በሕይወታቸው መስዋዕትነትን እየከፈሉ፣ ጠላቶቻቸውን በመቋቋም አገራቸውን አስቀጥለዋል፡፡ እስከ ዛሬ አገራችን ቀጥ ብላ በኩራት ቆማ ልትሄድና ለዘመናት በወዳጆቿም ሆነ በጠላቶቿ ተከብራ፣ ተፈርታና ታፍራ ልትቀጥል የቻለቸው በእዚህ ተዓምራዊ ሊባል በሚችል ውስጠ ሚስጥሯ ነው፣ በቅርቡ እንኳን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ጦርነት የደረሱባትንና በውስጥና ውጭ ጠላቶች የተቀነባበሩ ከባድ ፈተናዎች ተቋቁማ ያለፈችውም ለዚያ ነው፡፡
በአገራችን ዙሪያ ያሉ ንፁኃን ዜጎች በየጊዜው የሚፈጸምባቸውን ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ ረሃብ፣ ስደትና ግጭት ችለው፣ ከዚያም አልፎ በኃያላን ምዕራባውያን መንግሥታትና በዓባይ ግድባችን ዓይናቸው የቀላ ነባር ጠላቶቻችን በመታገዝ የዘር (‹‹የብሔር ፖለቲካን››) መግቢያ ቀዳዳ አድርገው አገራችንን ከብዙ አቅጣጫ የዘመቱባትን ከሀዲዎችን ተቋቁማ ለመግታት የቻለችው፣ ለዘመናት በዘለቀው የሕዝቧ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና የእምነት ጥንካሬዋ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህን ታላላቅ የአገር እሴቶች የመንከባከብና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲዘልቁ የማድረግ ኃላፊነት ከማንም በበለጠ የመንግሥት መሪዎች ነው፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ዕድል ብሎላት ይችን የመሰለች ዕንቁ የታሪክና የባህል፣ የልዩ ሕዝብ ባለፀጋ የሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በመሪ አልታደለችም፡፡ ጠንካራ ሕዝቦቿ ሌላውን ችግር፣ ረሃቡን፣ ድርቁን በሽታውንና የኑሮ ውድነቱን መስዋዕትነት እየተቀበሉም ቢሆን በፆምና በፀሎት፣ በዕንባና በትዕግሥት ብርታት በፅናት ያልፉታል፡፡ የመሪ ዕጦት ግን ከባድ ነው፡፡ ለዓመታት የሚዘልቅ በትውልድ ላይ የሚደራረብ ብዙ መዘዝና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በደረሰባት ጉዳትም፣ አገራችን እስከ ዛሬ ከተደራራቢና የማይሽር ቁስል ለመዳንና ከዚህ መጥፎ ባህልና የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት ለመውጣት አልቻለችም፡፡ ወጣሁት ብላ የንጋቱን ጎህ ልታይ ተስፋ ስታደርግ ተመልሶ ይጨልምባታል፡፡
ደግነቱ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ሕዝባችን ‹‹በጠባብ ብሔር ፖለቲከኞች›› ቢመረዝም፣ ጠንካራ የአገር ፍቅርና የሃይማኖት ስሜቱ ግን ጨርሶ አልጠፋም፡፡ ኢትዮጵያም ልትጠፋ ነው ተብሎ ሲፈራ ከወደቀችበት ተንገዳግዳ እንደገና እየተነሳችና ከአደጋ እየወጣች እንደተለመደው ከድህነቷና ከመከራዋ ጋር ወደፊት እየቀጠለች ነው፡፡ ሁሉንም ፈተና በጥበብ፣ በፅናትና በአንድነት ኃይል እየተቋቋመች በማሳለፍ እስከ ዛሬ ይኸውና ሳትፈርስ ቀጥላለች፣ ለወደፊትም ትቅጥላለች፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ለምንድነው ነው አገራችንን ሁልጊዜ ትልልቅ ፈተና የሚያጋጥማት የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተውን አዲስ ዘመቻ ማየቱ ራሱ በቂ ነው፡፡ ይህን አደጋ የተለየ የሚያደርገው በአገራችን ህልውና ላይ ያንዣበበውን ‹‹በብሔር ፖለቲካ›› የቆመውን የዘረኝነት ሥርዓት ከፍተኛ አደገኛነት አጉልቶ በማሳየቱ ነው፡፡
ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ተከታይ ምዕመናን ያላትንና ለዘመናት የዘለቀቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክልልን፣ ቋንቋን፣ ብሔርንና ዘርን ተመርኩዞ ‹‹የብሔር ፖለቲካው›› እሷንም አገራችንንም ለማጥፋት ነው በአደገኛ ሁኔታ የዘመተባት፡፡ ‹‹ለብሔር ፖለቲከኞች›› ዛሬ አገራችንን እንደ ድንገተኛ ጎርፍ ካጥለቀለቀው ‹‹የክልልነት ጥያቄ›› ጋር አቀላቅሎ፣ ቤተ ክርስቲያኗንም ከፋፍሎ ለማጥፋት መሞከር ዕብደት ብቻ ሳይሆን በትውልድ፣ በታሪክና በአገር ላይ ትልቅ ደባ እንደ መፈጸም ይቆጠራል፡፡ በምንም መንገድ ቢታይ የሚደገፍ አይደለም፡፡ በተለይም የአገር መሪዎች እውነት ይህን እንዴት መረዳት እንዳቃታቸው ይገርማል፡፡ ዘመን ተሻጋሪው ትልቁ የአገሪቱ ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ የሚመሯት አገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ እንዴት አይታያቸውም? ይህ እኮ ለረዥም ጊዜ የታቀደውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ‹‹የጠባብ ብሔርተኞች›› አንዱን ሴራ በተግባር የማዋልና ምናልባትም የመጨረሻው ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህን በሚገባ ይረዳል፣ መሪዎች ግን ለምን መረዳት እንዳቃታቸው ይገርማል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይ በአገራችን ዙሪያ በተከሰቱት ቀውሶች የተነሳ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ከባድ ፈተናዎችን አሳልፋለች፡፡ ቤተ እምነቶቿ ሲቃጠሉ፣ በርካታ ምዕመናቶቿና ካህናቶቿ በግፍ ሲገደሉ፣ ለአገር አንድነት ስትል፣ ክፉውን ቀን ቶሎ እንዲያሳልፍልንና ለኢትዮጵያም ሰላም እንዲያወርድላት፣ ፆምና ፀሎቷን ሳታቋርጥ በተስፋ ለፈጣሪዋ ስሞታ እያሰማች፣ በተለመደው ባህሪዋ በትዕግሥት እያሳለፈች ነው የዘለቀችው፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገር አንድነትና ፍቅር ምልክት የሆነውን ስንት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ ብሔርና ቋንቋ ሳይለያያቸው መስዋዕት የከፈሉለትን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ለምን አነገብሽ እየተባለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምዕመናኖቿን ሕይወት ገብራለች፡፡ መንግሥት ይህን ሁሉ እያየ እንዳላየ ያልፈዋል፣ ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱንም አይወጣም፡፡ ይህች የሺሕ ዓመት የአገር ፍቅርና አንድነት ታላቅ አለኝታ የሆነችው ትልቅ ተቋም ልትፈርስ ስትል ዝም ብሎ ያያታል፡፡ ጭራሽ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከአፍራሾቿ ጎን መቆም ጀመረ፡፡
ዕድል ብሎላት ነው መሰል አገራችን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ምንጊዜም አይተኙላትም፡፡ ቢያንስ የውስጥ ሰላሟንና የሕዝቦቿን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ፣ ጠንካራና አስተዋይ መንግሥት ደግሞ ለዓመታት አላገኘችም፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ የመጣው ሁሉ መሪ ያጠቃታል፡፡ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ‹‹በብሔር እኩልነትና ፌደራል ስም›› የተተከለው የዘረኝነት ሥርዓት ሕዝባችንን በቋንቋ፣ በዘርና በክልል ከፋፍሎ በጥላቻና በጥርጣሬ እርስ በርስ በማጋጨት አገራችንን ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍላት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ድርሻዋን አግኝታለች፡፡ በዘር (የብሔር ፖለቲካ) መንገድ ማፍረስ ሲሳናቸው አሁን ደግሞ በረቀቀ ዘዴ በሃይማኖት ለማጥቃት በአገራችን ላይ ጽንፈኞቹ አደገኛ የሆነ ዘመቻ በእሷ ላይ ከፈቱባት፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጥቂት አፈንጋጭ ሊቃነ ጳጳሳት በሚባሉ የተቀሰቀሰው ጦስ፣ ከቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ጉድለት ወይም የቋንቋንና የብሔርን እኩልነትን መብት ለማስከበር ታስቦ ሳይሆን፣ በዋነኝነት በአገራችን ሥር የሰደደውና ‹‹በብሔር ፖለቲካ ላይ›› የቆመው መርዘኛው ዘረኛ ሥርዓት አገር የማፍረስ ዘመቻ አንዱ የፖለቲካ ዘርፍ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
እርግጥ ‹‹የብሔር ፖለቲካው›› በአገራችን ባሰፈነው ጦስ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗም እንደ ማናቸውም ተቋማት የአስተዳደር ሳንካ ሊኖርባት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት የቋንቋ፣ የክልል፣ የዘር ወይም የብሔር አጥር ሳያግዳት ሁሉንም እኩል የምታገለግል ተቋም ዛሬ ያለችው ምናልባት እሷ ብቻ ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀብታም ደሀ ሳትል፣ ፆታ፣ ዘር፣ ቋንቋና ክልል ሳትለይ፣ ደካማውንም ጠንካራውንም፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል በማየት በቅንነት ስታገለግል ለዘመናት የኖረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ድክመት ቢኖርባትም፣ እንድታሻሽል በጥሞና በመምከር ፋንታ እንደ ምስጥ ውስጧን ቦርቡሮና ሰነጣጥቆ ገንድሶ ለመጣልና አገራችንን ለማፍረስ ለምን አስፈለገ?
ደግነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን አደገኛ ፈተና በጥሞና በማጤን፣ በተለመደውና ለዘመናት በዘለቀው ተሞክሮዋና ባህሏ በመመከት በስሜት ሳይሆን በማስተዋል፣ በቁጣ ሳይሆን በትዕግሥት በጥንቃቄ እያመዛዘነች በመራመድ ቀውሱን ለማርገብ ቻለች እንጂ፣ እንዳካሄዱ የአገራችንን ህልውና የሚፈታተን በጣም አደገኛ ዘመቻ ነበር፡፡ ቀውሱን ያወሳሰበውና ያባባሰው እንደ ተለመደው ‹‹ከብሔር ፖለቲካ›› ጋር መገናኘቱ ሲሆን፣ በዋነኝነት ግን የመንግሥት ጣልቃ መግባት ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉትን አገራቸውን አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ያሳሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው፣ ያስቆጣቸውና በመንግሥት ላይ ጨርሶ እምነት ያሳጣቸውም ዋናው ለእሱ ነው፡፡ የዜጎችን ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት፣ የመንግሥትንና የሃይማኖትን ድንበር በማስከበር፣ ቤተ ክርስቲያኗ ለሺሕ ዓመት በዘለቀ ሕጓ፣ ደንቧና ሥርዓቷ ለችግሩ መፍትሔ እንድታፈላልግ በመደገፍ ፋንታ፣ ያላግባብ ጣልቃ በመግባት፣ ጭራሽ ወገንተኛ ሆኖ ሕግ የጣሱትን የልብ ልብ እንዲያገኙ በማደፋፈር ቤተ ክርስቲያኗን በማስጠቃቱ ሁሉንም አሳዝኗል፣ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር የሕዝብ ማዕበል በቁጣ ገንፍሎ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲነሳ ያደረገውና አገራችንን እንደ አዲስ አደገኛ የሆነ የቋያ እሳት እንዲቀጣጠልባት ያጋለጣትም በዋነኝነት የመንግሥት ጣልቃ መግባት ነው፡፡
በቀላሉ ሊገታና ሊቆም የሚችል ችግር በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተነሳ እንደተለመደው ያላግባብ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ፣ በርካታ ንፁኃን ዜጎችም ያለ ምንም ጥፋታቸው በከንቱ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ ደግነቱ ቤተ ክርስቲያኒቷ ምዕመናኖቿን ከጫፍ እስከ ጫፍ ቀስቅሳ በማስነሳት በፆምና በፀሎት እየመራች፣ በጠንካራ እምነታቸው ፀንተው በጋራ ቆመው እንዲከተሏት በማድረግ፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ በኅብረትና በአንድነት ኃይል በመቋቋም የቀውሱን እሳት ለማብረድ መቻሏ እንጂ፣ በአገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመገመት ያዳግት ነበር፡፡ እርግጥ ነው ምንም እንኳን ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ መንግሥትም የሕዝቡን ጩኽትና ምናልባትም የሽማግሌዎችን ልመናና፣ በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ የሃይማኖት ተቋማትን ስሞታ ሰምቶ አቋሙን ቶሎ ማስተካከሉ የሚበረታታና የሚያስመሠግነው ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ በእልህ ቢቀጥል ኖሮ ግን ጉዳቱ ከፍተኛ በሆነ ነበር፡፡ የአገራችን ህልውናም ሳይቀር አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር፡፡ አሁንም መንግሥት በሰከነ መንገድ፣ በቅን ልቦና ችግሩን በጋራ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር በመወያየት ፈትቶ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ኃላፊነቱን ይወጣል በሚል ሁሉም አገሩን አፍቃሪና ሰላም ወዳዱ ኢትዮጵያዊ፣ በውስጥም በውጭም ያለው በተስፋና በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ ከስህተት መማርና ሕዝብን ማዳመጥ የመሪነት ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ በጉልበት መተማመን ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ለአገራችን ሲባል ካለፈው የአገራችን ታሪክ፣ ከመንግሥታት መሪዎች ስህተት መማሩ ጥሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገራችን ጠላቶች ዋና ዒላማ ልትሆን የቻለችበት ዋና ምክንያት፣ ለሕዝብ ፍቅርና የአገር አንድነት ጠንካራ ምሰሶ በመሆኗ ነው፡፡ እሷን ገፍተን ከጣልናት ኢትዮጵያንም ለመጣልና ለማፍረስ ምንም አያዳግተንም በሚል ጠላቶቻችን አምርረው በሴራ ስለተነሱባት ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የተተከለውና ሥር የሰደደው በ‹‹ብሔሮች እኩልነት›› ስም የሚሞካሸው የዘረኝነት ሥርዓት፣ አንዱ ሥራዬ ብሎ የያዘው ለዘመናት ጠንካራ ሆኖ የኖረውን የአገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ስሜት በረቀቀ ዘዴ ሥሩን እየቦረቦሩ አገራችንን ቀስ በቀስ ለማፈራረስና ጨርሶ ለመናድ ነው፡፡ ለዘመናት ተቻችሎ በሰላም የኖረውን ሕዝባችን፣ በጎሳ በሃይማኖት በቋንቋና በድንበር ከፋፍሎ እርስ በርስ በማጋጨት ኢትዮጵያን አፈራርሶ ቢቻል በፍርስራሿ ላይ እርስ በርስ የሚባሉ ደካማና ትንንሽ ‹‹ብሔሮችን ወይም አገሮችን›› ለመትከል ታስቦ ነው፡፡
ይህን እርኩስ ዓላማ ለማሳካት ‹‹ጽንፈኞቹ የብሔር ፖለቲከኞች›› ከሚጠቀሙባቸው ዋና ዋና ዘዴዎች ደግሞ፣ ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት በከፍተኛ አገር ፍቅር ስሜት አስተሳስረው በሰላም በማኖር ያዘለቁትን፣ የጋራ ታሪካቸውንና የአንድነት ምልክት ተቋሞቻቸውንና ቅርሶቻቸውን ለምሳሌ እንደ ዓድዋ ድል፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የአማርኛንና የግዕዝ ቋንቋን የመሳሰሉትን እያጠለሹ በማስጠላት ጨርሶ መግደል ነው፡፡ ያ አልሳካ ሲላቸው በብሔር፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በክልል ድንበር ልዩነት ስም እየከፋፈሉ ጥርጣሬን፣ ጥላቻንና መጥፎ ትርክትን በሕዝቡ መሀል በማስፋፋት እርስ በርስ በማጋጨት፣ የአንድነት ስሜትንና አገራዊ ፍቅርን ለማጥፋት መጣር ነው፡፡ ሌላው የሌለ ጠላት በመፍጠር በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የጥላቻ መርዝ በመንዛት፣ በሌሎች ብሔሮች እንዲጠላና ቂምና በቀል እንዲፈጸምበት ማድረጉ ባለፉት 30 ዓመታት በሰፊው ሲሠሩበት የቆዩት ዘዴ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለዘመናት ተከባብረውና ተሳስረው የኖሩትን የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ ለማለያየትና ለማጋጨት ለብዙ ዓመታት የዘለቀው ሴራና በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም የአማራ ተወላጆችን በወለጋና በሌሎችም ቦታዎች ያስጨረሰውና ያፈናቀለው እስከ ዛሬም ያልተገታው የዚህ እኩይ ዘመቻ ሌላው ዘዴ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ አልሳካ ሲላቸው በመጨረሻ በሃይማኖት መጡ፡፡ የአገር ፍቅርና የሕዝብ አንድነት ዋልታ በሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ኃይላቸውን አሰባስበው ዘመቱባት፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የአገራችን ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ ምን ሊሆን ይችላል? ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ቢያግዝ በሚል፣ የአቅሜን አስተያየት ለመስጠት በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን!
ዘላቂ ሰላምም ያውርድልን!
መሪዎችንም ልባቸውንና ህሊናቸውን ክፍት አድርጎ፣ ብልኃቱንና ቀናውን መንገድ ያመላክታቸው!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹በአገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ›› ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡