ለውይይት መነሻ
ዶ/ር ዓቢይ ወደ ሥልጣን መድረክ ብቅ ያሉ ሰሞን፣ የይቅርታ ፖሊቲካ መመርያቸው መሆኑን በየሚድያው ሲታወጅ በነበረበት ወቅት፣ ይህ ነገር በጊዜው ተገቢው ትርጉም ተሠጥቶት፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ብሎም ሕገ መንግሥቱንና ሌሎችን ተጓዳኝ ብሔራዊ ሕጎችን የሚጥሱትን ዜጎች በደንቡ መሠረት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ፣ አገሪቷ ካፈራቻቸው ብዙ ሺህ የመስኩ ባለ ሙያዎች ጥቂቶቹ እንኳ ደፍረው አስተያየት ይሠጡበታል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። ግን አልሆነም። እንደ አብዛኛው አገራት ምሑራን፣ የኢትዮጵያ ምሑራንም፣ ትክክል ነው ብለው ለሚያምኑበት ሓቅና እውነት ደፍረው ከመጻፍም ከመናገርም ስለ ተቆጠቡ፣ ባለቤት አልባውን የባለ ሙያዎች የዕውቀት መድረክ፣ ሙያም ሆነ ልምዱ የሌላቸው ግለሰቦች የግል ይዞታቸው አድርገውት ለብቻቸው ሲፈነጩበት ከዳር ቆመን እየታዘብን ነው።
የባሰውኑ የሚያሳዝነው ደግሞ፣ በሕግ ምሑሮቻችን ዝምታ ምክንያት ያገራችን የፍትሕ ሥርዓት ከምን ጊዜም በላይ ተጨመላልቆ የዳኝነትና የመንግሥት ሚናም ተደበላልቆብን፣ የአንድ ማኅበረ ሰብ ዋልታና ማገር የሆነው የሕግ የበላይነት መከበር የሕልም እንጀራ ሲሆንብን ማየቱ ነው። ይህን ያህል የተማሩና የተመራመሩ የሕግ ባለ ሙያዎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ እንዴት መሠረታዊ የፍትሕ መሪህ አልባ አገር እንደ ሆነች ለማወቅ ራሱን የቻለ ምርምር ስለሚጠይቅ አሁን አንስቼው ጭንቅላቴን ማሳመም አልፈልግም። እሱን ለባለ ሙያዎቹ ልተወው! እንደው እንደ አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ትውልደ- ኢትዮጵያዊ ግን የሚሠማኝን በጽሁፍ መልክ ጉዳዩ ያሳስበናል ለሚሉ ወገኖቼ ባጋራ፣ በትንሹም ቢሆን ከኅሊና ጸጸት ለመዳን ይረዳ ይሆናል ከማለት፣ ይህንን የግል አስተያየቴን ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ላካፍላችሁ ወሰንኩ። እስቲ እናንተም ጉዳዩ ያሳሰባችሁ የመስኩ ባለ ሙያዎች፣ ሰከን ብላችሁ ሃሳባችሁን ግለጹና በሠለጠነ መንገድ በመወያየት ይህንን መረን የለቀቀውን የፍትሕ ሥርዓታችንን ወደ ሓዲዱ ለመመለስ የሚረዱ አስተያየቶቻችሁን አቅርቡና እንወያይ።
የችግሩ ይዘት
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ስለ ተፈጸሙ ወንጀሎች፣ አግባብ ባለው መልክና በባለ ሙያዎች የተጠናቀረ፣ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ሁለንተናዊ ዘገባ ለጊዜው ባይኖርም፣ ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በታዘብኳቸው ዓለም አቀፋዊም ሆነ የእርስ በርስ ጦርነቶች በተካሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሶሶቱ ዓለም አቀፋዊ (ከባድ) ወንጀሎች፣ ማለትም፣ (የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide)፣ ጸረ ሰው ልጆች ወንጀል (Crimes Against Humanity) እና የጦርነት ወንጀል ወይም (War Crimes) ሲፈጸሙ ስላየሁ፣ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜም፣ የእነዚህን መብቶች ጥሰት ውርድና ስፋት በትክክል አናውቀውም እንጂ ለመጣሳቸው አንዳችም ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም። ስለዚህ፣ መንግሥትም ሆነ ሕወሃት ወደዱም ጠሉም፣ እነዚህ ወንጀሎች ለመፈጸማቸው፣ በመስኩ በቂ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ልምድ ባላቸው ባለ ሙያዎች ተመርምረው ለፍትህ እንዲቀርቡ ሂደቱን የማስተባበርና በሂደቱ ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ፣ ለባለ ሙያዎቹ እንደ አስፈላጊነቱ በቂ የሎጅስቲክ፣ የቁሳቁስ እና የጸጥታ ድጋፍ ብቻ ሰጥተው አስፈላጊውን ረፖርት እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው። በጦርነቱ ወቅት፣ ሁለቱ ተፋላሚ አካላትና ሌሎችም በሕወሃት ወይም በአገር መከላከያ ሠራዊት ሥር ያልተቀናጁ ታጣቂ ኃይላት በሙሉ፣ የሰው ልጆችን መብት ጥበቃ በተመለከተ፣ በድርጊታቸውም (Action) ሆነ ባለማድረጋቸውም (Omission) ለመብት ጥሰቶቹ በቀጥታ ተጠያቂዎች ስለሆኑ አንዳቸውም ከፍትሕ አለንጋ ማምለጥ የለባቸውም። ከዚህ የፍትሕ ሂደት ራስን ወይም ሌላውን መብት ጣሽ ከተጠያቂነት ለማዳን መሞከር ደግሞ በራሱ ከባድ ወንጀል ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ ነው እንግዲህ መንግሥት፣ ሕወሃትና አንዳንድ ፖሊቲከኞች የወንጀሎቹን መከሰት ባይክዱም፣ ወንጀለኞቹን ከተጠያቂነት ለማዳን ከማለት፣ “የሽግግር ፍትሕ” የሚለውን፣ በአገራችን እምብዛም ያልተለመደውን የፍትሕ ሂደት “በተግባር ለመተርጎም” ዳር ዳር ሲሉ የሚታዩት። ለዚህም ይሆናል በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ሁሉን ዓቀፍ ስምምነት ሂደት ውስጥ፣ ለ“ሽግግር ፍትሕ” ተገቢው ትኩረት እንኳ ሳይሰጡ፣ በስምምነቱ አንቀጽ 10(3) ሥር እንደው በደፈናው “ተጠያቂነትና እውነትን ለማግኘት” “ተበዳዮችን መካስ” “እርቅ” “ቁስልን ማዳን” “በሕገ መንግሥቱና በአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ፍትሕ መሪህ መሠረት ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ምክክር እና ብሔራዊ የፖሊሲ ፈጠራ ሂደት” ወዘተ በሚሉ ቅርጸ ቢስና ተፈጻሚነቱ አጠራጣሪ የሆነውን “ኃላፊነት” ለመቀበል የተስማሙት።
በኔ አስተያየት፣ መንግሥትም ሆነ ሕወሃት የወንጀል ድርጊቶቹ ስለ መከሰታቸው ጥርጥሬ ባይኖራቸውም፣ በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ግን ቅን ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም። በዚሁ በፈረደበት ቅርጸ ቢሱ የብሔራዊ ምክክር ማዕቀፍ ውስጥ፣ በዳይና ተበዳይ ፊት ለፊት ተገናኝተው ይቅር ተባብለው ችግሩ መፍትሔ ያገኛል የሚል እሳቤ ያላቸውም ይመስለኛል። ለዚህም ነው ፖሊቲከኞቻችንም ሆኑ የመንግሥት አካላት፣ የሽግግር ፍትሕ በሚለው ሃሳብ ዙርያ አንዳች ዓይነት የተዛባ ግንዛቤ ያላቸው ይመስለኛል የምለው።
ለመሆኑ የሽግግር ፍትሕ ማለት ምንድነው? ከመደበኛው የፍትሕ ሂደትስ በምን ይለያል? የሽግግር ፍትሕ ማለት፣ በቀደመው ጨቋኝ ወይም አግላይ ሥርዓት ወይም በአንድ ረዘም ላለ ጊዜ በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት (ግጭት) ወቅት መሠረታዊ የሰው ልጆችን መብት የጣሱ ግለ ሰቦች ወይም ተቋማት፣ ከጦርነቱ በኋላ “በአሸናፊነት” በወጣው መንግሥት አቀነባባሪነት፣ በዳይና ተበዳይ፣ የተለያዩ የማኅበረሰቡ አካላትን በሚወክሉ ግለ ሰቦች በተዋቀረው የማሕበረሰብ “ዳኞች” ፊት ቀርበው ይቅር የሚባባሉበት ሂደት ማለት ነው። መለስተኛ ዓላማው፣ በዳይና ተበዳይን ፊት ለፊት አገናኝቶ፣ በዳዩ በድርጊቱ መጸጸቱን በሕዝብ ፊት ይቅርታ ሲጠይቅና፣ ተበዳዩም፣
የበዳዩን ከልብ የመነጨ ጸጸት ተረድቶ ከልብ ይቅርታ እንዲያደርግ ሲሆን የረጅም ጊዜ ዓላማው ግን፣ የፖሊቲካም ሆነ ማኅበረ ሰባዊ ሥልጣንን ተጠቅሞ ሰብዓዊ ፍጡርን መበደል፣ ወንጀል መሆኑ ታውቆ፣ ቀጣዩ ትውልድ ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጽምና፣ በዳይና ተበዳይም ከልብ ይቅር ተባብለው ለወደፊት ቂምና በቀልን በልብ ይዘው ለአገሪቷ ሰላምና ለማኅበረሰቡ ዕድገት ጠንቅ እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው። የሽግግር ፍትሕ ተፈጻሚነቱ በተለምዶ፣ በዝቅተኛ ደረጃ በደል በፈጸሙት ግለ ሰቦች ላይ እንጂ በዋነኞቹ (ባለ ሥልጣናት) መብት ጣሶች ላይ አይደለም። እነሱ በመደበኛው ወይም በልዩ ችሎት ይዳኛሉ። በመሠረቱ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደት፣ ከመደበኛው የፍትሕ ሂደት ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ እንጂ የሚተካው አይደሉም። በሌላ አነጋገር፣ የበዳይና ተበዳይ ፊት ለፊት ተገናኝቶ በማኅበረሰቡ ፊት ይቅርታ መጠየቅና መቀበል፣ በምንም መልኩ አንድን በዳይ፣ በተለይም “የወንጀል ድርጊቶቹን ያቀነባበሩትንና የመሩትን” ከመደበኛው ፍርድ ቤት ፍትኃዊ ብይን ነጻ አያደርጋቸውም።
ይህ ሂደት በተለምዶ፣ ማኅበረሰብ ከሚያስተናግዳቸው የፍትሕ ሂደቶች ለየት ያለና በጥቂት አገራት ብቻ በተግባር የተተረጎመ፣ ስኬቱ ግን ብዙም ያልተደነቀለት ነው። ለስኬቱ ዝቅተኛነት እንደ ምክንያት የተወሰደው፣ ሂደቱ ተበዳዩን ወገን በተፈለገው ደረጃ ለመካስ አለ መቻሉ ነው። ይህ የፍትህ ሂደት በአፍሪካ ውስጥ በሰፊው በተግባር የተተረጎመው በደቡብ አፍሪካና በሩዋንዳ ሲሆን፣ በመንግሥት ደረጃ የመሳካቱ ጉዳይ በአወንታዊ ሲወራ፣ በተበዳይ ግለ ሰቦችና ዘመዶች ዘንድ ግን ቅሬታው እንደ ቀጠለ ነው። ሰዎች በተፈጥሮ ተጨባጭ የሆነ ካሳ ፈላጊ ስለሆኑ፣ በዳይና ተበዳይን ፊት ለፊት አገናኝቶ ይቅርታ አጠያይቆና አስተቃቅፎ ማለያየቱ ብቻ የተበዳዩን ውስጣዊ ቁስል ለማጠገግ አልቻለም። በተረፈ ግን የደቡብ አፍሪካም ሆነ የሩዋንዳ የፍትሕ ሥርዓት ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት የጸዱ ናቸው ተብሎ ስለሚነገርላቸው፣ ለሽግግር ፍትሑ ዝቅተኛ ስኬት ብቸኛው ተጠያቂ ራሱ የሂደቱ መሪህ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።
ይህ የሽግግር ፍትሕ፣ ያላንዳች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሥራቸውን በሚያከናውኑ አገራት እንኳ እምብዛም ያልተሳካለት፣ መንግሥት ያለ ማቋረጥ ጣልቃ በሚገባበት ያገራችን የፍትሕ ሥርዓት ሥር እንዴት ስኬት ሊያስመዘግብ ይችላል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። በግሌ፣ በደቡብ አፍሪካው በተደረገው ስምምነት ውስጥ በግርድፉ በአንቀጽ 10(3) የተካተተው “የሽግግር ፍትሕ”፣ በአገራችን ተገቢ ትኩረት ተሠጥቶት የላንዳች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በተጠበቀው መልኩ ተፈጻሚ ይሆናል ብዬ ለመገመት ይከብደኛል። ለጥርጣሬዬ ምክንያት የሆኑትን አንዳንድ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እንደሚከተለው ላቅርብ።
የፍትሕ ሥርዓታችን
አብዛኞቻችን እያስተዋልን ያለውና አንዳንዶቻችን በአደባባይ፣ ሌሎቻችን ደግሞ በየቤታችን ሆነን የምንኮንነው፣ ዛሬ በአገራችን የሰፈነውን የተዛባ የፍትሕ ሥርዓት ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። አዎ! እኛ ምሑራን ደግሞ፣ የተዛባውን ሥርዓት ወደ ትክክለኛው መሥመር ለመመለስ አስፈላጊውን ሙያዊ አስተዋጽዎ ከማድረግ ተቆጥበን ዝም ብለን መንግሥት በቆፈረልን ቦይ እየፈሰስን እንገኛለን። ሰፊው ሕዝብ ደግሞ ጉዳዩን በጥልቅ ስለማይረዳው (የሕግ ጉዳይ ስለ ሆነ) ምንም እንኳ በማኅበረ ሰባዊ ሞራል ተመርቶ አልፎ አልፎ ድርጊቱን ቢኮንንም፣ ደፈር ብሎ ሰብዓዊ መብቱን ለማስከበር ለሚያደርገው ትግል የሚረዳ በቂ የዕውቀትና የንቃት ትጥቅ ያለው አይመስለኝም። ከዚያም በላይ፣ በዚህ በአገሪቷ የፍትሕ ሂደት ዙርያ የተወሳሰቡ እሳቤዎች ስላሉ፣ ጥያቄውን ራሱን በአግባቡ ለማስቀመጥ ብዥታ የሰፈነ ይመስላል። በርግጥም፣ በሰፊው ሕዝብ መካከል ውዥንበር የፈጠሩና የፍትሕ ሂደቱን ያዛቡ ብዙ አሳሳቢ የመንግሥት ድርጊቶች አሉ። ከነዚህ መሃል ሶስቱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣
ሀ) የሕግ የበላይነት መጥፋት፣
ለ) የመንግሥት በፍትሕ ሂደት ጣልቃ መግባት፣ እና፣
ሐ) ቅርጸ ቢስ የሆነው የመንግሥት “የይቅርታ ፖሊቲካ” የሚሉትን አንስቼ፣ ጠለቅ ባለ ሕጋዊ ትንተና ሳይሆን ለሰፊው አንባቢ እንዲያመች ከማለት፣ ቀለል ባለ መንገድ ባጭሩ ባብራራቸው አንዳች ዓይነት ግንዛቤ ይሠጣሉ ብዬ እገምታለሁ።
ሀ) የሕግ የበላይነት ማለት የአገሪቷ ሕጎች በዜጎች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ያለው፣ ሕጉን ጥሶ በሚገኘው ማንኛውም ዜጋ (ከርዕሰ ብሔሩ እስከ ጎዳና ተዳዳሪው ድረስ) ላይ የሚሠጠው ፍርድ፣ ግልጽና አድልዖ የሌለበት ነው ማለት ነው። በፖሊቲካ ሥልጣን ወይም በዝምድና ወይም በታዋቂነት ላይ ተመሥርቶ ፍርድን ማዳላት አይቻልም። ቅጣትን በተወሰነ ደረጃ ለማቅለል ወይም ለማክበድ ቢቻልም፣ የመጨረሻው ፍርድ የሚሠጠው፣ በተፈጸመው ወንጀል ቅርጽና ይዘት ልክ እንጂ በወንጀለኛው ማንነት ላይ የተመሠረተ አይሆንም። የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የመንግሥት መሠረታዊ ግዴታው፣
- የፍትሕ አካሉ (ዓቃቤ ሕጉ) በወንጀል የሚጠረጠሩትን ግለሰቦች ለፍርድ ያቀርብ ዘንድ ሁለንተናዊ እርዳታ ማድረግ፣
- የአገሪቷ ሕጎች በሙሉ ተከብረው የዜጎች መብት እንዳይጣሱ የተለያዩ የጥሰት ማስወገጃ እርምጃዎችን ለምሳሌ፣ የዜጎችን የመብት-ነክ ዕውቀትና ንቃት ከፍ ለማድረግ የሚረዳ ሁሉን-ዓቀፍ ትምሕርት የመስጠትና ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ነው።
ለ) የመንግሥት በፍትሕ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ አስፈጻሚው አካል (መንግሥት) እና የዳኝነቱ አካል አይነኬ አይጠጌ ናቸው። በተግባር ግን፣ መንግሥት በተደጋጋሚ በፍትሕ ሂደት ውስጥ ጣልቃ እየገባ “ለአገር ደኅንነትና ሰላም” በሚል ሰበብ የአንዳንድ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩትን ዜጎች የክስ ሂደት ሲያቋርጥ ይስተዋላል። በመሠረቱ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መንግሥት በፍርድ ሂደት ውስጥ ጣልቃ ያልገባበት ጊዜ ባይኖርም፣ የድሮውን ለታሪክ ብንተውና ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ብቻ ያስተዋልናቸውን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ብቻ ብናጤነው፣ የአገራችን የፍትሕ ሥርዓት ምንኛ እንደ ተዛባ ጥሩ አመላካች ሆኖ እናገኘዋለን። መንግሥት ከሚጠቀምባቸው የጣልቃ መግባት ስልቶች መካከል አንዱ፣ የክስ ሂደትን ማስማቆም (ክስን ለመሰረዝ) ሲሆን ሌላውና እጅግ በጣም አሳዛኙ ደግሞ፣ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው በጥልቅ ተመርምሮ በቂ ማስረጃ ስላልቀረበባቸው ዳኛው በነጻ ሲያሰናብታቸው፣ “ከመንግሥት ታዝዘን ነው” ነው የሚሉ ፖሊሶች ደግሞ፣ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ ላይ ቆመው እንደ ገና ወደ ማረሚያ ቤት ሲመልሷቸው ማየቱ ነው። በዚህ ምድር ላይ ፍርድን በተመለከተ ከዳኛ በላይ አንድም ምድራዊ አካል እንደሌለ እየታወቀ በኢትዮጵያችን ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአንድ ወቅት ንግግራቸው በቁጭት እንደ ተናገሩት፣ ፖሊስ ከዳኛ በላይ ሆኖ እያየን ነው። ይህንን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ብዙዎቻችን በተለያዩ ክልሎች እያስተዋልነው ሲሆን፣ በግሌ ደግሞ የማውቀውን አንድ ክስተት ባካፍላችሁ የላቀ ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
በአንድ ወቅት ላይ፣ የፖሊቲካ ወንጀል ፈጽማችኋል ተብለው ቁጥራቸው ከአሥር በላይ የሚሆኑ የኦነግ አባላት በፖሊስ ተይዘው ረዘም ላለ ጊዜ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎችና ጊዜያዊ በረቶች ታስረው ከዘመድ አዝማድ ርቀው የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕጉ፣ በቂ ማስረጃ ስላላገኘሁባቸው ክሱን አቁሜያለሁ ስላለ፣ ፍርድ ቤቱ ከሁለት ዓመት በፊት ተጠርጣሪዎቹን በሙሉ በነጻ ያሰናብታል። ተጠርጣሪዎቹም፣ ዘግይቶም ቢሆን፣ መጨረሻ ላይ ፍትሕ አገኘን ብለው በደስታ ፈንጥዘው ዳኛውን አመስግነው ሲወጡ፣ በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ላይ ቆመው ይጠብቋቸው በነበሩ ፖሊሶች ተይዘው ወደ ጣቢያ ይወሰዳሉ። ለምን እንደ ገና ለመታሠር እንደ በቁ ሳይነገራቸው፣ በክልሉ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ሲያዘዋውሯቸው ቆይተው መጨረሻ ላይ ወደ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ አምጥተው፣ ክስ እንደ ተመሠረተባቸው እስረኛ ሳይሆን እንደ ዕቃ በአደራ አስቀመጧቸው። ዜጎቹ ጉዳያቸውን አጠገባቸው ላለው የቡራዩ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ዳኛው፣ “ፍ/ቤቱ እስከሚያውቀው ድረስ በተጠረጠራችሁበት ወንጀል በቂ ማስረጃ ባለ መገኘቱ በነጻ ተለቅቃችኋል፣ ከተፈታችሁም በኋላ ደግሞ አንዳችም ዓይነት አዲስ ክስ ያቀረበባችሁ አካል ስለሌለ ፍርድ ቤቱን በተመለከተ፣ እናንተ ነጻ ዜጎች ናችሁ” ይላቸዋል። ግለ ሰቦቹን ለቡራዩ ፖሊስ በአደራ ያስረከበውን የክልሉን ፖሊስ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት ቀርበው ንጽሃን ዜጎችን ለምን እንደሚያንገላቱ እንዲያሳውቁ በተደጋጋሚ ማዘዣ ቢላክባቸውም፣ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። በመሆኑም፣ ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበታቸው ከሁለት ዓመት በኋላ፣ አሥራ አምስቱ ንጹሕ ዜጎች ዛሬም በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ፣ ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሠረትባቸው፣ ከፍ/ቤት ውሳኔ ውጭ በክልሉ ፖሊስ ውሳኔ ብቻ፣ ምድራዊ ፍትሕ ተነፍጓቸው እንደ ዕቃ ለቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ በአደራ ተሠጥተው፣ ፍዳቸውን እያዩ ነው። (እኔ በርግጠኝነት ስለማውቀው አንድ ነጠላ ክስተት ነገርኳችሁ እንጂ፣ በግል ሚዲያ ተቋማት መረጃዎች መሠረት በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳለ ይታመናል)።
መንግሥት በፍትሕ ሂደት ውስጥ ምን ያህል ጣልቃ እየገባ እንዳለና የሕግ የበላይነት በአገራችን እጅግ በጣም ውድ ሸቀጥ እንደ ሆነ ለማስረዳት ከዚህ የበለጠ ማስረጃ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በየዩኒቬርሲቲውም፣ በልምድ ደረጃም እንደ እግዚአብሔር ቃል፣ የሕግ አውጪው (ፓርላማው)፣ የፍትሕ ሥርዓቱና (ዳኝነትና ፍ/ቤት) አስፈጻሚው አካል (መንግሥት) በተለምዶ አባባል፣ (ሶስቱ ምድራዊ የዲሞክራሲ ሥላሴዎች) አንዳቸው በአንዳቸው ሥራ በጭራሽ ጣልቃ የማይገቡ፣ የአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ዕድገት መለኪያ መስፈርቶች ናቸው የሚባለው የፍትሕ መሪኅ፣ በአፍና በአፍንጫችን ሲንቆረቆርብን ላደግን የሕግ ባለ ሙያዎች፣ ከዚህ የከፋ ተስፋ አስቆራጭ መንግሥታዊ እርምጃ ያለ አይመስለኝም።
ሐ) የይቅርታ ፖሊቲካ፣ የይቅርታ ፖሊቲካ (መሆን ያለበት) ብቸኛ ዓላማ፣ ባለፈው የማኅበረ ሰባችን ታሪክ ዘመን፣ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲገፈፍ በቃልም በተግባርም ሲያራምድ የነበረውን ሥርዓት፣ የዛሬው መንግሥት፣ ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን አምኖ፣ በሕዝብ ስም በሥርዓቱ ሲጠቁ የነበሩ ሕዝቦችን ይቅርታ መጠየቅ ነው። ወንጀል በዘር ስለማይተላለፍ፣ ያኔ ሲፈጸም ለነበረው በደል የዛሬው ትውልድ ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት የለምና፣ የዛሬው መንግሥት በሕዝብ ስም፣ ተበዳዩን ወገን ይቅርታ ጠይቆና ካሳ ከፍሎ፣ ያንን ክፉ የታሪክ ምዕራፍ ዘግቶ፣ ቁርሾን ሳይይዙ በእኩልነትና በፍቅር ወደ ፊት እንጓዝ ከማለት መንግሥት የሚወስደው የ “ይቅር እንባባል” ፖሊቲካ ነው። የታሪካዊ በደል (historical injustice) ካሳ ደግሞ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ስለሆነ፣ ተገቢው ካሳ በመንግሥት ከተከፈለ በኋላ፣ አዲሱ ትውልድ በአዲስ መንፈስ የጋራ ጉዞን ይጀምራል ማለት ነው። ለምሳሌ ያሕል፣ በጥቁሮችና በነባሩ የኢንዲያን ሕዝብ (Native Americans) ላይ ሲፈጸም የነበረውን የወንጀል ድርጊት ኮንኖ የአሜሪካ መንግሥት በሕዝብ ስም ጥቁሮችንና ሕንዶችን ይቅርታ ጠይቆ ፖሊቲካዊ ካሳ ከፍሏል። የአውስትራሊያም መንግሥት በአቦሪጅኖች ላይ ሲፈጸም የነበረውን የመብት ጥሰት ኮንኖ ይቅርታ ጠይቋል። የካናዳም መንግሥት ነባር ኢንዲያንን ይቅርታ ጠይቆ የፖሊቲካ ካሳ ከፍሏል።
ወደ አገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ስንመለስ፣ በቀደምት መንግሥታትና ሥርዓት ሲበደሉ የነበሩትን ዜጎች (ለምሳሌ በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ለባርነት ተዳርገው እንደ ዕቃ ሲሸጡ የነበሩትን ብዙ የደቡብ ሕዝባችንን፣ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ወይም በሙያቸው ምክንያት በበታችነት ቆጥራቸው፣ በማኅበረ ሰቡም ሆነ በሕግ ፊት በእኩል በማይታዩበት ሥርዓት የተበደሉትን) የዛሬው መንግሥት በሕዝብ ስም ይቅርታ ጠይቆ የፖሊቲካ ካሳ መክፈል አለበት ማለት ነው። በዚህ ድርጊቱ፣ የመንግሥት ዋና ዓላማ፣ የተዛባውን ማሕበረ ሰባዊ ፍትሕ ለማስተካክላልና ያለፈውን በደል ሳንረሳ፣ ሆኖም ግን ስሕተቶቹን እንዳንደግማቸው፣ ለወደ ፊቱ የአገሪቷ ሰላምና የሕዝቦቿ አብሮነት የሚረዳ አዲስ ማኅበረ ሰባዊ ውል (Social Contract) ለመፈራረም ብቻ ይሆናል።
እንደሚገባኝ ከሆነ የአገራችንን የፍትሕ ሂደት ካራከሱትና ሕዝቡንም ግራ ካጋቡት ክስተቶች የሚከተሉት ሁለቱ ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ሀ) ወንጀለኛን በይቅርታ ነጻ ማድረግና፣
ለ) ከወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት ነጻ መሆን፣
ወንጀለኛን በይቅርታ ነጻ ማድረግ፣ ማለት ዳኛው በቀረበለት ማስረጃ ላይ ተደግፎ በወንጀል የተጠረጠረውን ዜጋ ሕጉ በደነገገው መሠረት ቅጣት በይኖበት ወደ ማረሚያ ቤት ከላከው በኋላ፣ የተፈረደበት ግለ ሰብም የተወሰነበትን ቅጣት ተቀብሎ ማረሚያ ቤት ከገባ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ በተለያዩ ምክንያቶች፣ የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ሥር በተደነገገው መሠረት ለወንጀለኛው ምሕረት (ይቅርታ) ተደርጎለት የእስር ዘመኑ ተቀንሶለት በነጻ ሲለቀቅ ማለት ነው።
ከወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት ነጻ መሆን፣ ማለት ደግሞ አንድን በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረን ግለሰብ፣ የተጠረጠረበትን ወንጀል ስለ መፈጸሙ መቶ በመቶ አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ ሳይገኝ ሲቀር፣ ፖሊሱ ወይም ዓቃቤ ሕጉ ተጠርጣሪውን ለዳኝነት ሳያቀርቡ፣ ከፖሊስ ቁጥጥር ሥር ፈትቶ በነጻ የሚለቅበት ሁኔታ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ፖሊስና ዓቃቤ ሕጉ ምርመራውን ጨርሰው ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከደረሰ በኋላ፣ ዳኛው በቀረበለት ማስረጃ መሠረት በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረውን ዜጋ ድርጊቱን ለመፈጸሙ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሳይሆን ሲቀር ተጠርጣሪውን ከወንጀል ድርጊቱ ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግበት ሂደት ማለት ነው።
ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች፣
ከላይ የጠቀስኳቸው ሶስቱ ከባድ የሰው ልጆች መብት ጥሰት ወንጀሎች፣ ዛሬ የዓለም አቀፋዊነት መልክ ይዘዋል። በመሆኑም፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ ተስማማቶ ኮንቬንሽኖችን ከመፈረምና ማጽደቅ ባሻገር በነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩትን ግለሰቦች የሚዳኝ ዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤትም አቋቁሟል። እነዚህን ሶስት ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎችን ከሌሎች ወንጀሎች ሁሉ የተለየ ክብደት እንዲያገኙ ካደረጓቸው ባሕርዮቻቸው መካከል አራቱን ብቻ መጥቀሱ አስፈላጊ ይመስለኛል።
ሀ) ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎቹ እንደ ሌሎቹ ወንጀሎች የይርጋ ዘመን (Statute of Limitations) የላቸውም። ይህም ማለት፣ አንድ ከነዚህ ሶሶቱ ወንጀሎች አንዱን ፈጽሟል ተብሎ የሚጠረጠር ግለ ሰብ፣ በዚች ምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ ከየትም ምድር ዳርቻና ከተደበቀበት ቦታ ተይዞ ለፍርድ ይቀርባል ማለት ነው። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ካበቃ ከሰባ አምስት በኋላ ያኔ በጦርነቱ ወቅት ለምሳሌ፣ በፋሺስቱ ጀርመን የእስረኞች ማጎርያ ጣቢያዎች (Concentration Camp) እንኳ በዘበኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ ግለ ሰቦች ዛሬ ከየትም የዓለም ዳርቻ ተይዘው ለፍርድ እየቀረቡ ነው። በእርጅና ወይም በበሽታ ምክንያት በሚጣልባቸው ቅጣት ክብደትና እርዝማኔ ላይ አስተያየት ይደረግላቸው እንደው እንጂ፣ በቂ ማስረጃ እስከ ተገኘባቸው ድረስ በምንም ተዓምር ከምድራዊ ፍርድ ሊያመልጡ አይችሉም።
ለ) ከነዚህ ወንጀሎች ቢያንስ በአንዱ የተጠረጠረውን ግለሰብ፣ በቂ ማስረጃ እስካቀረበ ድረስ ማንም ሰው (የውጪ ዜጋም ቢሆን) በተጠርጣሪው ላይ ክስ ሊመሠርት ይችላል። ይህም ማለት፣ ለምሳሌ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተደረገው ጦርነት ወቅት ከነዚህ ሶስት ወንጀሎች አንዱን ወንጀል መፈጸሙን ማስረጃ እስካሰበሰበ ድረስ፣ ማንም የውጭ አገር ዜጋ ወይም ተቋም በግል ሰቦቹ ላይ ሕጉን ተከትሎ ክስ ሊመሠርት ይችላል።
ሐ) በወንጀሉ(ሎቹ) ድርጊት የተጠረጠረውን ግለ ሰብ በቂ ማስረጃ እስከ ተገኘ ድረስ፣ የማንም አገር ፍርድ ቤት ሊዳኘው ይችላል። ለምሳሌ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከነዚህ ወንጀሎች አንዱን ፈጽሟል ብሎ ማስረጃ ከቀረበለት (ሌሎችም ተጓዳኝ መስፈርቶችን ጨምሮ) ከኢትዮጵያ ውጭ የማንም አገር የወንጀል ችሎት ኢትዮጵያዊውን ተጠርጣሪ ግለ ሰብ ክስ ሊመሠርትበትና ፈጽሟል የተባለውን ወንጀል ለመፈጸሙ መቶ በመቶ እርግጠኛ ከሆነ፣ በሕጉ መሠረት ተገቢውን ቅጣት ሊወስንበት ይችላል።
መ) በወንጀሉ(ሎቹ) ድርጊት የተጠረጠረን ግለ ሰብ፣ ከሳሹ አካል (ዓቃቤ ሕጉ) በቂ ማስረጃ ሰብስቦ ተጠርጣሪውን ለፍርድ ካቀረበ በኋላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) ወይም አስፈጻሚው አካል (መንግሥት) አንዳቸውም በፍትሕ ሂደቱ ጣልቃ ገብተው ጫና ሊያሳድሩ፣ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ እንዳይቀርቡ፣ ወይም የክሱን ሂደቱን ሊያቋርጡ አይችሉም። አንድን ተከሳሽ ከክስ ነጻ አድርጎ ሊያሰናብት ወይም ሊፈርድበት የሚችል አንድ ብቸኛ ምድራዊ አካል ዳኛ ብቻ ነው። ሆኖም ግን፣ በምድራዊው ፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን እየፈጸሙና በመታረም ላይ እያሉ፣ የሚያሳዩት ጸጸትና የመታረም ፍላጎት ታይቶ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ርዕሰ ብሄሩ ለወንጀለኞቹ ምህረት ሊያደርግላቸው ይችላል።
ከዚህ አጭር ማብራርያ እንደምንረዳው ከሆነ፣ እነዚህ ሶስት የሰው ልጅ መብት ጥሰት ወንጀሎች ከሌሎች ወንጀሎች ሁሉ ለየት ያሉና (የይርጋ ዘመን የማይመለከታቸው፣ አገራዊ ወሰን የማይገድባቸው) በምንም መልኩ በይቅርታ የማይታለፉ መሆናቸውን ነው። በዛሬው ዕለት፣ ከተራ ሌብነት ጀምሮ እስከ ነፍስ ግድያ የሚደርስ ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉት ግለ ሰቦች ላይ ፍርድ ቤቶቻችን ሕጉን ተከትለው ተገቢውን ቅጣት ሲበይኑባቸው እያየን፣ እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስት ከባድ ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩትን ግለሰቦች ግን፣ ለፍርድ ሳይቀርቡ በይቅርታ የሚታለፉበት ምክንያት ሊኖር አይገባም። የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ሥር በግልጽ እንዳስቀመጠው፣
“ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የአገሪቷ ሕጎች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን (ከላይ የጠቀስኳቸውን)፣ በፈጸሙት ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም። ይህ ወንጀል በሕግ አውጪው አካል ወይም በማንኛውም ሌላ የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፍም”።
መደምደሚያ
ማንኛውም መንግሥት በተፈጥሮው ጨቋኝ ነው። ለዚህም ነው ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዋናው ተጠያቂ መንግሥት ነው የሚባለው። የመንግሥት የመብት ጥሰት ቅርጽና ይዘት፣ ዜጎች ስለ መብታቸው ካላቸው የንቃት ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ ነው። ስለ ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በቂ ዕውቀት ያላቸው ሕዝቦች መብታቸውን በደንብ ያስከብራሉ። የሕዝቡን ንቃት በደንብ የተረዳ መንግሥት ደግሞ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን ከመጣስ እጁን ይሰበስባል። ዝቅተኛ ንቃት ያላቸው ሕዝቦች ደግሞ መብታቸው በመንግሥት የመጣሱ ዕድል ከፍ ያለ ነው። በኔ ግምት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ከሁለተኛ ወገን ይመደባል። ዛሬ አስፈጻሚው አካል የሕግ አውጪውን ሥራ ሲሻማ፣ ወይም በማያገባው የፍትሕ ሂደት ውስጥ ገብቶ ዜጎችን ሲያሳስርና ሲያስፈታ ማየቱ የሕዝባችንን የመብት-ነክ ንቃት ደረጃ እጅግ በጣም ዝቅ ያለ መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል። ስለ ሆነም፣ በዚህ መስክ በትምሕርታችንም ሆነ በሙያችን በቂ ልምድ ያለን ምሑራን ከፖሊቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ ሆነን “መሆን የነበረበትን እና ያለበትን” የሕግ የበላይነትን በአገራችን ለማስፈን የሚረዳ ሃሳብ ለማዋጣትና ብሎም የሕዝቡን የሰብዓዊ መብት ዕውቀት ደረጃና ንቃት ከፍ ለማድረግ ታሪካዊ ሚናችንን እንጫወት። ለዚህም፣ መጀመርያ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችንን ጠንቅቀን እንወቃቸው፣ አውቀንም እናስተምር። ዕውቀትን እናስፋፋ። የችግሩ መፍትሔ አንድና አንድ ብቻ ነው፣ የሕዝቡ የመብት-ነክ ንቃተ ኅሊና ከፍታ!
እስቲ የሚሰማችሁን አካፍሉንና እንወያይ! አገርን ከሚያጠፉት ድርጊቶች መካከል ዋነኛው የምሑራን ዝምታ ነውና በርግጥ በአገራችን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከልብ የምንመኝ ከሆነ ዝምታውን በመስበር ታሪካዊ ሚናችንን እንጫወት።
*****
ስቶክሆልም፣ ጥር 15 ቀን 2023 ዓ/ም