እውነተኛ ማንነት ሲገለጥ (በይበቃል ያረጋል ረታ)

የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም.

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ዶ/ር ዐብይ አህመድ በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት ቀርበው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ሲሾሙ ካደረጉት እስደማሚ ንግግር ጀምሮ፡ በተከታታይ ወራት በሀገር ውስጥ እና በውጭ በመዘዋወር እንዲመሩት በጉጉት ለሚጠብቀው ሕዝባቸው ባሳዩት ትህትና፥ እክብሮት እና ፍቅር በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያገኙት ተቀባይነት እና የተቸራቸው መልካም ምኞት በኢትዮጵያ ስነ መንግስት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ለዚህ አይነት ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ያበቋቸው የተለያዩ አበይት ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ከነዚህ ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛ ነው በሚባል ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት አስተዋጽዎ ነው። በቀድሞው የኢህአዲግ አገዛዝ ጣልቃ ገብነት እና ቀጥተኛ ትዕዛዝ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ፓትርያርክ የነበሩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ከስልጣናቸው ተገፍተው እንዲወርዱ ብሎም እንዲሰደዱ ተደርጎ ነበር። የቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ቀኖና ተጥሶ በህይወት እያሉ ባላያቸው ላይ ፓትርያርክ በመሰየሙ ቤተክርስቲያኗ ለተወሰኑ ዓመታት የቅዱስ ሲኖዶስ መከፈል ገጥሟት ችግር ላይ ወድቃ ነበር። ይህንንም ችግር ለመፍታት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባሉ ካህናት እና ታዋቂ ግለስቦች አስተባባሪነት በተደጋጋሚ በተደረገው የማስታረቅ ጥረት፣ የነበሩት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀረፉ ጥሩ ደረጃ ደርስው ነበር እና በወቅቱም ዶ/ር ዐብይ ወደ ስልጣን በመምጣታቸው እና ለጉዳዩም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በሂደት ላይ የነበረው እርቅ ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ በማድረጋቸውና በስደት ላይ የነበሩትን ቅዱስ ፓትርያርክ ይዘዋቸው ወደ አገራቸው በመግባት ላደረጉት አስተዋጾ ከፍተኛ አድናቆት እና ተቀባይነትን በሕዝቡ ዘንድ አስገኝቶላቸዋል።

 

ሆኖም ግን ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በይበልጥም በኦሮሚያ ክልል የማያባራ የንፁሐን እልቂት እና ፍጅት በመቀጠሉ እና እንዲሁም ይበርዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የዘር ፖለቲካ በከፋ መልኩ እየተባባሰ መሄዱ የዶ/ር ዐብይን ደካማ አመራር ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል። ከሁለት አመት ባላይ በፈጀው በስሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው የሕዝብ እልቂት፤ የአካል ጉዳት፤ የንብረት ውድመት እና የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ዶ/ር ዐብይ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ በተለይም የኦሮሞ ብልጽግና የሚወስዳቸው ዘርን ያማከለ አንዳንድ ውሳኔዎች እና በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያደርጓቸው ንግግሮች ላይ የሚሰነዝሯቸው ዘር ተኮር ቃላቶችና ሐሳቦች፤ የሚያሳዩት ወገናዊነት እና ብልጣብልጥነት በሕዝብ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ጥያቄ ላይ ጥሎታል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሞከረውን መፈንቅለ ሲኖዶስን አስመልክቶ፣ መንግስታቸው ሊያደርግ የሚገባውን የሕግ ማስከበር ሕገ መንግስታዊ ሀላፊነት እና ግዴታ ባለመወጣት አብያተ ክርስቲያናት ሲደፈሩ፤ ሃይማኖታቸውን እና ቤተ ክርስቲያናቸውን አናስደፍርም ያሉ ሰላማዊ ምዕመናን በመንግስት ሃይሎች በአደባባይ ሲገደሉ እና ሲቆስሉ ስለጉዳዩ ለተወስኑ ቀናት መንግስት ምንም ሳይናገር ሰንብቶ ነበር። ነገሩ ተካርሮ ወደ አስከፊ ደረጃ ሊደርስ ሲል ግን ጠቅላዩ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ስለተከሰተው ጉዳይ እግረ መንገዳቸውን በሚመስል መልኩ ለግማሽ ሰዓት ገደማ በሰጡት የተዛባ አስተያየት አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ በተለይም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ቁጣን አስነስቶባቸዋል።

 

ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት በሕግ የምትታወቅ፤ ከ 60 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የእምነቱ ተከታይ ያላት፤ እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ወቅቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሀገር ናት ያሏትን ቅድስት ቤ/ክ ዝቅ በሚያደርግ መልኩ ከቤ/ክ አፈንግጠው በወጡ ሶስት ጳጳሳት፤ የቤ/ክ ሥርአት፤ ሕግ እና ቀኖና በመጣስ ላቋቋሙት ሲኖዶስ እና በነርሱም የተካሄደውን ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት እውቅና በመስጠት ከሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር አቻ በማድረግ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ነው ሲሉ እንዲስማሙ ያስተላለፉት መልእክት ቤ/ክርስቲያኗን አዋርዷል፤ መዕመኗንም አሳዝኗል። ይህም ብቻ ሳይሆን ባለፉት 30 አመታት የተዘራው አጸያፊ የዘር ፖለቲካ እና ለዚህም መንስኤ የሆነው የዘር ፌደራል አወቃቀር ያስከተለው ሀገራዊ ቀውስ ያነስ ይመስል፣ ሃይማኖቱንም ፊደራላዊ ይዘት እንዲይዝ በሚመስል መልኩ ዘርን እና ቋንቋን አንስተው ያሳዩት ወገናዊነት እጅጉን አሳፋሪ እና በአንድ ወቅት እኔ አሻግራችኋለሁ ሲሉ ከነበረ መሪ የማይጠበቅ ብዙዎችን አንገት ያስደፋ ክስተት ነበር። ከላይ እንደጠቀስነው የዘውግ ፖለቲካና የዘር ፌደራሊዝም ለሀገራችን ምንም እንዳልበጀ እየታወቀ፣ ወደዚያ መውረዳቸው አሳዛኝ ነው።

 

ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ባደረጉት ንግግር ላይ የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያንን አስመልከተው ለስነዘሯቸው አስተያየቶች እና የተዛቡ ማስረጃዎች፡ በቤ/ክርስቲያኗ በኩል መስመር በመስመር በማስረጃ የተደገፈ ሰፋ ያለ ማብራሪያና እጥጋቢ መልስ ስለተሰጠበት በዚህ ጽሑፍ አናካትተውም፤ ሆኖም ግን፡ ቤተ ክርስቲያኗ በስጠቸው መልስ ማጠቃለያ ላይ የሰፈረው፤

 

በመጨረሻም መንግሥታችን በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና፣ በሕግ የተሰጣትን መብትና ጥቅም በማስከበር ሕገወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በደላችንን ለዓለም ሕዝብ ችግሩ ተፈቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕትን ድረስ በመክፈል የምናሳውቅ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ ይገልጻል፡፡የሚለውን ተከትሎ ስለተከሰቱት ኩነቶች ጥቂት እንላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጎብላንድ ፣ አጭበርባሪው ጦጣ - አገሬ አዲስ

 

መንግስት ከቅዱስ ሲኖዶሱ የተላለፈውን የሕግ ይከበርልኝ ተማጽኖና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከመጤፍ ባለመቁጠር ሕግ የማስከበር ሕግ መንግስታዊ ግዴታውን ከመወጣት ይልቅ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶሱ የተወገዙትን ሕገ ወጡን አካላት በማጀብ አብያተ ክርስቲያናትን በመድፈር፥ ቤተ ክርስትያናቸውን አናስደፍርም ያሉ ምዕመናንን በመደብደብ፥ በመግደል የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት እና ሀብት በማስወስድ እና በማዘረፍ አሳፋሪ ሰራውን ቀጠለበት። ከዚህ የተነሳ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጾመ ነነዌን አንተርሶ በመላው ሀገሪቱ ላሉት የእምነቱ ተካታዮች የሐዘን ልብስ ምልክት የሆነውን ጥቁር ልብስ በመልበስ ጾሙን በሐዘን፥ በጸሎት፥ በምህላ እና በአርምሞ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲማጸኑ በታዘዘው መሰረት ሀገር ጉድ ባስባለ መልኩ ሕዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ በመውጣት ለእምነቱ ያለውን ጽናት፥ ለአባቶቹ ያለውን ታዛዥነት እና ሙሉ ድጋፍ እንዲሁም መንግስት የያዘውን አቋም እንደሚቃውም በዘር ሳይወሰን በግልጽ አሳይቷል።

 

ይህንን አስፈሪ በዝምታ የተዳፈነ የእምነቱን ተከታዮች ቁጣ፥ እንዲሁም በሌላ እምነት ተከታዮች በኩል በመንግስት ላይ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ድምጽ እና ለቤተ ክርስቲያኗ የሚስጡትን ድጋፎች ያየ መንግስት ለየካቲት 5ቀን 2015 ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያኗ የተጠራውን ሰላማዊ ስልፍ ለማስቆም በተደጋጋሚ ያወጣው ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ ውጤት አልባ እንደሆነ ሲረዳ ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያኗ ለመንግስት የተላለፈውን የእንነጋገር ጥሪ በፍጥነት ተቀብሎ ዓርብ የካቲት 3 ቀን 2015 ንግግሩ ተጀመረ። ከዚህ የተነሳ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ለተወሰነ ጊዜ በሚል ለጊዜው ተሰረዘ።

 

ይህ ጽሑፍ እስከ ተጻፈበት እስከ አሁኗ ሰአት ድረስ ባለን መረጃ ሙሉ በሙሉ መቋጫ ያልተገኘለት ይህ መፈንቅለ ሲኖዶሱን ለማካሄድ ባቀዱት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ በተወገዙት ጳጳሳት ተጀምሮ፣ በመንግስት መዋቅር ታግዞ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ ቡራኬ ጸድቆ በሀጋሪቱ ላይ የተለኮሰው ዘርን ያማከለ ሀገር የሚያጠፋ የሃይማኖት ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል እኩይ ተግባር ምን እስተማረን ብሎ እንደ ሚጠይቅ ሀላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ የሚከተለውን እንላለን፤

 

ሕገ ወጡ ቡድን፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የራሷ ሥርዓተ ሕግ እና ቀኖና ያላት፣ በመንፈስ ቅዱሰ መሪነት በቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራ ሐዋርያዊ ትስስሯን የጠበቀች ቀደምት ከሚባሉ የክርስትና እምነቶች እንዷ መሆኗ ይታወቃል። ይህ ሆኖ ሳለ፣ ቤተ ክርስቲያኗ አስተምራ፥ አሳድጋ ለጵጵስና ማእረግ ያበቃቻቸው የመንፈስ ልጆቿ፣ ሥርዓተ ቤተ ከርሰቲያንን እና ቀኖናን በመጣስ እራሳቸውን ሲኖዶስ ብለው፣ በጫካ ውስጥ ተደብቀው ለ 25 መነኮሳት የሊቀ ጵጵስና ሲመት አካሂደናል ብሎ ማለታቸው በመንፈሳዊው ረገድ ብቻ ሳይሆን በብዙ መልኩ ፈጽሞ ስህተት ነው። ቤተ ክርስቲያን ብሔር እና ዘውግ የሌላት መሆኗ እየታወቀ ሆኖም ግን በውስጧ ሊከሰቱ በሚችሉ አስተዳደርዊ ጉድለቶች የተነሳ ሊደርሱ የሚችሉን ስህተቶችን በተገቢው የአስተዳደር መዋቅር ለመፍታት እና ለማረም እንደ መጣር ፈንታ፣ ሀገሪቱ ለገባችበት ምስቅልቅል ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የቋንቋ እና የብሔር ፌደራሊዝምን የመሰለ ክልላዊ የሃይማኖት ሲኖዶሶች ለማቋቋም መሞከር የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም ነው። አላማቸው በሰፊው የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ዘንድ ድጋፍ አለማግኘቱ ምን ያህል ስህተተኞች እንደሆኑ የሚያሳይም ነው።

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ፤

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከዚህ ቀደም ከውስጧ ባሉም ሆነ ከውጭ ጣልቃ ገቦች የተነሳ ብዙ የተለያዩ ችግሮች የገጠሟት ቢሆንም አሁን እንደተከሰተው ችግር ቤተ ክርስቲያንን ገጥሟት አያውቅም። ይህን ለየት ያለና አደገኛ የሚያደርገው፣ ችግሩ ሀገሪቱ የተዘፈቀችበትን የዘር ፖለቲካ መሰረት ያደረገና ውጥኑም የምድራዊ ሥልጣን ፍለጋ ብቻ ሳይሆን የተፈለገውን ሥልጣን ለማግኝት ብሔር የለሽ ቤተክርስቲያኗን የብሔር ማዕከል በማድረግ እንዳትጠገን አድርጎ ለማዳከም፥ ለመበታተን ብሎም ለማጥፋት መሆኑ ነው። ይህንን እኩይ ተግባር ቤተክርስቲያኗ ተረድታ ዘመን ጠገብ የአስተዳደር ልምዷን፥ ለዘመናት ከቤተ ክህነት እስክ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በጥበብ ያዋቀረቻቸውን የእዝ ሰንሰለቶችን አቀናጅታ፣ የመጣውን መከራ በቆራጥ መንፈሳዊነት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቅዱስ ሲኖዶሱ የወሰደው እርምጃ፥ በአባቶች መካከል የነበረው መናበብ፥ የአመራር ብስለት እና ጥበብ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ሊወሰደበት የሚገባም ነው።

 

ይህ ዛሬ የተከሰተው ችግር እንደ ደራሽ ጎርፍ ዛሬ በድንገት የተከሰተ ሳይሆን፣ ቤተ ከርስቲያኗ ያላትን አስተዳደራዊ መዋቅር ከጊዜው ጋር አብሮ እንዲዘምን ያለማድረጓ እንዱ ችግር ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን፡ በመንፋሳዊውም ሆነ በአስተዳደር ላይ አንዳንድ የሚመደቡ ግለስቦች ስነ ምግባር፥ ብቃት እና ልምድ በአግባቡ የተፈተሽ እና የተጠና ባለመሆናቸው አስተዳደራዊ ጉድለቶችን እና መንፋሳዊ ስብራቶችን በመፍጠር ለሚነሱት ችግሮች መንስኤ ሆነዋል። በተጨማሪም ቤተክርሰቲያኗ ካሏት ተከታዮች ብዛት እና ከምታገኘው የገቢ ምንጭ አኳያ ያላት የፋይናንስ አያያዝ ድክመት ለከፍተኛ ምዝበራ እና ብክነት አጋልጧታል። በዚህ አይነት አጸያፊ ተግባር የሚሳተፉት ግለስቦች ስራቸውን ለመሸፈን ሲሉ በሚያደርጉት ኢፍትሐዊ አሰራር የተነሳ ቤተ ከርስትያኗን ለከፋ ችግር ዳርገዋታል።

 

በሌላ ረገድ አመርቂ እና በቂም ባይሆን ቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገለግሎቷን በተለያዩ ቋንቋዎች ማስፋፋቷ የሚመሰገን እና የሚበረታታ ሲሆን፣ ካላት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሕዝብ ቁጥር አኳያ ገና ብዙ ስራ ይጠበቅባታል። ይህንን ክፉ አጋጣሚ እንደ እድል በመጠቀም በቁርጠኝነት በመነሳት በስፊው ወደ ሰራ በመግባት ያሏትን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን የሄዱባትን ልጆቿን ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው ለመመለስ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ቆጥራ፣ በቁርጠኝነት እና በፍጥነት ወደ ሰራ ልትገባ ይገባል።

 

ምዕመናን፤

ይህ የተከሰተው ችግር ያለምንም ማወላወል ያሳየን ሀቅ ቢኖር፤ በብዙዎች ዘንድ የጥንትና አሮጌ እንደሆነች፣ እንደደከመች እና የነበራት ተቀባይነት ብሎም ተሰሚነት እያሽቆለቆለ ነው ብለው ያሰቧት ቢኖሩ፤ ለመማን በሚቸግር መልኩ እንደ ጠዋት ፀሐይ የፈነጠቀች፣ እንደተዳፈነ ፍም ቦግ ያለች፥ ሊቆሙላት ሳይሆን ሞተው ያቆሟት፥ መንፈሰ ጠንካራ፥ ጽኑ ሃይማኖተኛ ከልጅ እስከ ደቂቅ፥ ካዋቂ እስከ አረጋዊ ወንድ የለ ሴት፣ ምሁር ሆነ ገበሬ፥ ኦሮሞ ሆነ ትግሬ፥ ውራጌ ሆነ ሐረሬ፥ ጋሞ ሆነ ወላይቴ፥ አማራ ሆነ ወዘተ… በአንድነት እንደ እንድ ተናጋሪ እንደ እንድ ልብ መካሪ በመሆን በነቂስ በመውጣት የአባቶቹን ድምጽ እና ትእዛዝ በመስማት ዓለምን አስደምመዋል። ይህ ለወዳጅ ኩራት ለጠላቷ ደግሞ ፍርሃትን የለቀቀ የማስጠንቀቂያ ደውል ሆኖ ሊወሰድ ይገባዋል። የሕግና የሚድያ አባላት የሆኑት ምዕመኖችዋ ያለክፍያ ቤተክርስትያንዋ በፍርድ ቤትና በመገናኛ ብዙኀን በመወከል እያደረጉት ያለው አስተዋጸኦ የሚያኮራ ነው። በሀገራችን ኢትዮጵያም ሕግና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አቋምን መግለጽና ለመብትም መከራከር እውን ይቻል እንደሆነ የፍትሕ ሥራዓቱንም እየሞገቱ ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሽግግር ፍትህን ለማሰብ የሚቻለው ከትናንቱ ዛሬ የተሻለ በጎነት ሲኖር ነው (ገለታው ዘለቀ)

 

መንግስት፤

በቅዱስ መጽሐፍ “ሁሉም ነገር ለበጎ ሆነ” የሚለው ኃይለ ቃል በግልጥ የተተረጎመበት አጋጣሚ ቢኖር ይህ የተከሰተው ችግር ነው። ይህን ለማለት ያስደፈረን ከላይ እንደጠቀስነው የተከሰተው ችግር ክፉ ጠባሳ በሁሉም ላይ ቢጥልም፥ ጠባሳውን ለወደፊት እንደ ማስታወሻ መጠቀሚያ፣ በሌላ ጎን ደግሞ የመጣውን ችግር እንደ እድል በመጠቀም ሁላቸንም እንድንማርበት ይጠቅማል። ከዚህ በመነሳት መንግስት በዚህ ጉዳይ በይበልጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑትን ተግባር ስንመለከት፣ ላለፉት አምስት አመታት በይበልጥም በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት በሚያማልሉ ቃላት ታጅበው ለሕዝብ ያቀርቡት የነበረው የተስፋ እንጀራ ዛሬ ስናየው ባዶ መሆኑን በአደባባይ ተገልጦ ብዙዎች የተረዱበት ወቅት ነው። ትላንት ሀገር ናት ያሏትን ቅድስት ቤተክርስቲያን እራሱን የብሔር ብሔረስቦች ሲኖዶስ ብሎ ከሚጠራ ሕገ ወጥ ቡድን ጋር አቻ አድርገው ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በመላው ሀገሪቱ ከ60 ሚሊዎን በላይ ተከታይ ያላትን ቅድስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በአደባባይ ሲያንጓጥጡና ሲፈርጁ ማየት፤ እውነተኛ ማንነታቸውን ማየታቸን የመንፈስ ቅዱስ ስራ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መግደል መሽነፍ ነው ሲሉን ከርመው በጠራራ ፅሐይ ከ30 በላይ ንጹሐን በመንግስት በአደባባይ ሲጨፈጨፉ፤ አብያት ክርስቲያናት በሕገ ወጥ ቡድኑ በኦሮሞያ ልዩ ሃይል ታጅቦ ሲስበሩና ሲዘረፉ ደንታ ሳይስጣቸው፤ በብዙ ትግል ሕገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን በቋንቋቸው መጠቀምን ሊከለከሉ አይገባም ብለው መንፈሳዊውን ነገር ጥርሳቸውን ወደነቀሉበት የዘር ፖለቲካ በመወተፍ በሕዝብ ላይ የተሳለቁት በጣም ያሳዝናል፣ ብሎም ያሳፍራል።

 

ይህም ብቻ አይደለም እራሰን እግዝፎ ሁሉንም አውቃለሁ ከሚል ተልካሻ አስተሳሰብ በመነሳት ለብዙ ዘመናት ስነ መንግስትን ያስተማረች፥ ቀለም በጥብጣ፣ ቆዳ ፍቃ ፊደል ቀርጻ ዓለም ላይ ካሉ ቋንቋዎች በብቃቱ እና በረቂቅነቱ የተወደሰውን ዛሬ ጠቅላዩ እርሳቸው በኩራት የሚራቀቁበትን ቋንቋ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሽጋገረች፥ ሕዝብን ለዘመናት ግብረገብ ያስተማረች፥ ኢትዮጵያዊነትን ከእግር እስከ እራሷ የተላበስች ያለበስች ቤተክርስቲያንን ወደታች እያዩ ለማንጓጠጥ መድፈራቸው፣ እውነተኛ ማንነታቸውን አሳብቆባቸዋል። ይህም የማይደፈረውን፥ ሊነካ የማይገባውን የሃይማኖት ጉዳይ በመንካት የሴራው ተቋዳሽ ሆነው በአብዛኛው የእምነቱ ተካታይ በመታየታቸው ሊያንሰራሩበት ከማይችሉት የሕዝብ ተቃውሞ ተዘፍቀዋል።

 

ከላይ እንዳልነው ይህ ክስተት ላወቀበት፣ በይበልጥም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆም ብለው እንዲያስቡ እና እራሳቸውን እንዲመረምሩ ጥሩ እጋጣሚ ፈጥሮላቸው ነበር። ይሄውም ከአስመሳይነት እና ከብልጣብልጥነት ተላቀው መንግስታቸው በተደጋጋሚ ያወጣውን የማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ መሰል ትዕዛዝ ሳይበግረው ለሦስት ቀናት በየአጥቢያው ቤተክርስቲያን በመላው ሀገሪቱ ወገቡን አስሮ፣ ቁጭቱን አምቆ፣ እንባውን እያፈሰሰ በአደባባይ በእርስዎ እና በመንግስትዎ የተስማውን ሀዘን እና ብሶት ለፈጣሪው ሲያሰማ የዋለውን የሕዝብ ማዕበል ተረድተው እና ተገንዝበው እርምት ቢወስዱና ይቅርታ ቢጠይቁ ምንኛ ባወቁ ነበር። ሆኖም ግን እንደው አለመታደል ሆኖ አጀማመሩን እና አጨራረሱን ቀድሞ ሳይታይ በሚታወቀውና የግልዎ ባደረጉት የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን (ETV) ሰሞኑን ካስለቀቁት የተለመደው ተውኔትዎ እንዳየነው ብዙም እንዳልተማሩ እና እንዳልተረዱ ማረጋገጥ ተችሏል። ይህ ሀገራችን ያለቸበትን ከፍተኛ ችግር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፤ ለዚህም ከልብ አዝነናል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተረዱት እና ያልተገነዘቡት ነገር ሕዝብ ሁል ጊዜ ትክክል መሆኑን ነው። ለዚህም ትልቁ ምስክር እራሳቸው በአደባባይ የተፈጠረውን ችግር ለሕገ ወጦቹ ወግነው፣ ወደ ዘር ጎትተው ቢከቱትም እራሳቸው የተገኙበት የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም የተዋሕዶ እምነት ተከታዩ ሃይማኖቱን ላለማስነካት የአባቶቹን የቅዱስ ሲኖዶሱን ትዕዛዝ አክብሮ እንደሌላው ወንድሞቹ “አንዲት ሃይማኖት፥ አንድ ሲኖዶስ፥ አንድ ፓትርያርክ ሲል መስዋትነትን ተቀብሏል። ይህን አይነት ትእግስት እና ቁርጠኝነት ያሳየ፥ ገዳይ ሠይፉን ይዞ ሲመጣበት እጁን ሳያነሳ ሰመዓትነትን የተቀበለ ሕዝብ፤ ትዕግስቱ ተሟጦ ያለቀ ዕለት እንኳን ምድራዊ ሃይል ማንም አያቆመውም። ይህን አለማስተዋል እና አለመገንዘብ ሕዝብን መናቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን ከትዕቢት እና ከመታበይ አላቀው ጆሯቸውን ከፍተው ይህን እንዲሰሙ ከልብ እንመክራለን።

 

ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል። ደምን ለማፍሰስ ከእኛ ጋር ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት ቢሉ፤ በሕይወታቸው ሳሉ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ በሙሉም ወደ ጕድጓድ እንደሚወድቁ ይሁኑ፤ መልካሙን ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፤ ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ፤ ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤ እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። (ምሳ. 17፥ 10-16)

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና የፖሊቲካ ድርጅቶች (የግል አስተያየት) - ባይሳ ዋቅ-ወያ

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሻገር የመላው ሀገሪቱን ህዝቦች ወክለዋል የተባሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሀገሪቱ በሚያስፈራ ሁኔታ ወደ ሃይማኖት ጦርነት ልትገባ ይሆን ወይ ተብሎ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ሲረበሽ፤ ምንም እንዳልተፈጠረ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጣቸው እጅግ ያሳዝናል ብሎም ያሰጋል። ዳሩ ግን ይህ የሚያመለክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ሚኒስትሮቻቸው አንድም እንዳይተነፍሱ ያስጠነቀቁት ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለፓርላማው አባላትም ጭምር ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።

 

ማጠቃለያ፤

ከላይ በስፊው ለተነሳው ውዝግብ መንሥዔውን፥ በጉዳዩም ላይ ዋነኛ ተሳታፊዎችን እንዲሁሞ የተከሰተው ችግር ያስከተለውን ጉዳት እና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን በተወሰነ ደረጃ ለመዳሰስ ሞክረናል። ሆኖም ግን ጉዳዩን ብቻ ዘርዝሮ ያለ መፍትሔ ሃሳብ መተው የተነሳንበትን አላማ እና ማስተላለፍ የተፈለገውን ሃሳብ ጎደሎ ስለሚያደርገው ለሁሉም የባለ ድርሻ አባላት የሚከተለውን ምክረ ሃሳብ በትሕትና እናቀርባለን።

 

  • ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሶስቱ የተወገዙት ጳጳሳት ሥርዓተ ቤ/ክ እና ቀኖናን በመጣስ በሕገ ወጥ መንገድ ያቋቋሙት ሲኖዶስ እና ያከናወኑት ሲመተ ጵጵስና ስለሆነ፤ እኒህ አባቶች ይህን ለማድረግ  ምከንያት አድርገው ያነሱት የቋንቋ ጉዳይ ውኃ የማይቋጥር ቢሆንም፣ በተወሰነ መልኩ ቤተ ክርስቲያኗ ልታስብበት እና አጥብቃ ልትሰራበት የሚገባ ጥያቄ ነው። ስለሆነም እኒህ አባቶች የፈጸሙት ስህተት ሕገ ቤ/ክ መጣስ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንን የሚከፍል፥ ሕዝብን የሚያጣላ ብሎም ሀገርን የሚያፈርስ በመሆኑ መለስ ቀለሱን ትተው ከልብ ተጸጽተው ቤተ ክርስቲያንን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ እንመክራለን
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ይህ የገጠማት ችግር አስከፊና ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍላትም፤ በተጓዳኝ ደግሞ እራሷን እንድትመረምር፥ ውስጧን እንድታጸዳ እና ከቀደመ ስህተቷ የምትማርበት ከፍተኛ እድል ፈጥሮላታል። ይህም በመሆኑ ከላይ እንደጠቀስነው አስተዳደራዊ እና ስብከተ ወንጌልን የምታሳልጥበት መንገድን እና ለሁሉም እምነት ተከታዮች ተደራሽ በሚሆን መልኩ ዘመኑን የዋጀ ሁሉንም ቋንቋን ያካተተ አሰራር ብትከተል ተገቢ ነው እንላለን። በተጨማሪም በአባትነት ተመርጠው የሚሾሙትን ብፁዐን አባቶች በሚገባ ትምህርተ ሃይማኖቷን ጠንቅቀው የተማሩ የተረዱ፤ በምግባራቸው እና በቀናይነታቸው የተመስገኑ እንዲሁም በሚመድቡባቸው ሐገር ስብከቶች ምዕመናን ዘንድ ቅቡልነት ያላቸው ቢሆኑ ጠቃሚ ይመስለናል። የቤተ ከርስቲያኗን ሥርዓተ ሕግ እና ቀኖና ጥስው የታገዱ እና የተወገዙ እካላትን በንስሐ እጇን ዘርግታ ስትቀበል፣ የቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እና ቀኖና በሚያዘው መሰረት ከማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ (የመንግስት) ጫና ተላቃ ተገቢውን እርምት እና ቀኖናዊ ቅጣት በመስጠት ቢሆን ተገቢ እና አስተማሪም ነው ብለን እናስባለን። ይህን ያልንበት ምክንያት የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ዛሬ በተከሰተው መጠንና ልክ ባይሆንም በይዘቱ ተመሳሳይ የሆነ ችግር ተከስቶ ነበር። ይህም ችግር ዛሬ ከተወገዙትና ይቅርታ ከጠየቁት አካላት ውስጥ የነበሩበት ሲሆን በወቅቱ ጉዳዩን በመሪነት ሲያራምድ የነበረው ቀሲስ በላይ በቅዱስ ሲኖዶሱ ክህነቱ ተይዞበት ጉዳዩ ከመንፈሳዊንት ይልቅ ዘር ተኮር ፖለቲካዊ መልክ በመያዙ ጉዳዩን ለማርገብ እና ለመደባበስ በሚመስል መልኩ ተመልሶ በፊት ከነበረበት ኃላፊነት የበለጠ ስልጣን ተስጥቶት ጉዳዩ ለጊዜውም ቢሆን ተዘጋ። “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዲል በወቅቱ ነገሮችን በቅጡ እና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና ቀኖናን ተከትሎ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ ለደረሰው ችግር አትጋለጥም ነበር ብለን እናስባለን።
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ምዕመናን ያሳዩት ጽናት እና የከፈሉት መስዋትነት እጅግ የሚደንቅ እና ይበል የሚያስብል ነው። ድካማቸው እና ጸሎታቸው ከንቱ እንዳልቀረ ፈጣሪ እንደመለስ በግልጽ ታይቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን አባቶች ያሳዩት ጠንካራ ድጋፍ እንዲሁም ለቅዱስ ሲኖዶስ ታዛዥነተቸውን ለዓለም አስመስክረዋል። ይህን ያሳዩትን ድጋፍ በመቀጠል አሁንም ሆነ ወደፊት ቤተ ክርስቲያኗ በቀጣይ የምትወስዳቸውን አርምጃዎች እና ማስተካከያዎች ተገቢነታቸውን እና መተግባራቸውን በቅርብ በመከታተል ገንቢ ሃሳቦቸን እና ተገቢ ትችቶችን በመሰንዘር አባቶችን መርዳት እና ማገዝ ይጠበቅባቸዋል እንላለን። ቤተክርስትያንዋ ለወደፊቱም ፈተናና ችግር ሊገጥማት ስለሚችል፣ የሕግና የሚድያ ባለሙያዎች ያደረጉትን እስተዋጽዎ እና ጥብቅና እንዳያቋርጡ ልናበረታታ እንፈልጋለን።
  • መንግስት ተቀዳሚ ስራው እና ሀላፊነቱ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ነው። በተቃራኒው ግን እራሱ ያወጣውን እና ሁሌ የሚጠቅሰውን ሕገ መንግስት በናደ መልኩ ሕግን በመጣስ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ማጥፋት ፈጽሞ አይገባውም። ይህም ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግስቱ ላይ ተደንግጎ ያለውን መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ፈጽሞ ጣልቃ መግባት የለበትምየሚለውን ማክበር በቻ ሳይሆን ማስከበር ይጠበቅበታል። በተለይም ለተነሳው ቸግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንግስት የራሱ ድርሻ እንዳለው በገሀድ እየታየ “አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ እንደታየው በሃይማኖት ተቋማት ላይ እራሱ ችግር ፈጥሮ ተመልሶ አስታራቂ ሆኖ በመቅረብ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከመሞከር ፈጽሞ ሊታቀብ ይገባዋል እንላለን። በተጭማሪም በራሱ በመንግስት ኃይሎች ለተገደሉ፥ ለቆሰሉ፥ ለተጎዱ እና ለጠፋው ንብረት እራሱን ተጠያቂ አድርጎ ወንጀለኛ ግለሰቦችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ለተፈጸመውም ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል፤ ይቅርታ እንዲጠይቅ እና ዳግመኛ እንዲህ ካለ እኩይ ተግባር እንዲቆጠብ በጥሞና እንጠይቃለን።

 

በመጨረሻም ለሃይማኖታቸው እና ለእውነት ሲሉ በመንግስት ሃይሎች ስመዓትነትን ለተቀበሉ፣ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ያኑርልን፤ ቤተስቦቻቸውንም እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጣቸው። እንዲሁም የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፤ ለቆስሉ እና ለተጎዱም እግዚአብሔር መድኃኒት ይሁናቸው።

 

የኢትዮጵያን ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናቸንን እግዚአብሔር ይጠብቅ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

አሜን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share