የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍን ለማዳበር በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ከተደረጉ የማኅበረሰብ ምክክሮች ፈልቀው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተሰጡ የጋራ ምክረ ሐሳቦችን እና ቁልፍ ግኝቶችን ያካተተ መሪ ሰነድ
ስምምነቱ “የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በሕዝባዊ ምክክር የሚገኙ ግብአቶችን መሠረት አድርጎ እና መደበኛ ሀገራዊ የፖሊሲ አወጣጥ ሂደቶችን ተከትሎ ሊዘጋጅ እንደሚገባ” ያስቀምጣል
መግቢያ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR / የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት) በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.) መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህዋሓት) መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈረመው እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲፀድቅ የሚደነግገውን የዘላቂ ሰላም እና ግጭት ማቆም ስምምነት (የሰላም ስምምነት) በድጋሚ በመልካም የሚቀበሉት ሲሆን የሰላም ስምምነቱ በተለይም በአንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ (African Union Transitional Justice Policy Framework) ጋር በተጣጣመ መልኩ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ እውነትን ለማውጣት፣ ማኅበረሰባዊ እርቅ እና ፈውስ ለማምጣት እንዲሁም የተጎጂዎችን መፍትሔ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርግ” ይገልፃል። ስምምነቱ አክሎም “የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በሕዝባዊ ምክክር የሚገኙ ግብአቶችን መሠረት አድርጎ እና መደበኛ ሀገራዊ የፖሊሲ አወጣጥ ሂደቶችን ተከትሎ ሊዘጋጅ እንደሚገባ” ያስቀምጣል።
እውነተኛ፣ አሳታፊ፣ አካታች፣ ሀገራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ እና የዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆችን እና ድንጋጌዎችን ያከበረ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ማኅበረሰባዊ ዕርቅ እና ፈውስ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ኢሰመኮ ከተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. ድረስ ባካሄዷቸው የማኅበረሰብ ምክክሮች የለዩዋቸውን ቀዳሚ ዋና ዋና ግኝቶች እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ እና የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ የተ.መ.ድ.ን አካሄድ ለመግለጽ በተ.መ.ድ. ዋና ጸሐፊ የወጣው የመመሪያ ማስታወሻ (Guidance note of the United Nations (UN) Secretary General: United Nations Approach to TJ) ላይ የሰፈሩ፤ ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን በሚነድፉበትም ሆነ በሚተገብሩበት ወቅት ሊመሩባቸው የሚገቡ ቁልፍ መርሆችን እንደሚከተለው ያቀርባሉ። በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ሊደረግ ታቅዶ የነበረው የማኅበረሰብ ምክክር በዚሁ ወር ባገረሸው ጦርነት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡ ሆኖም በአማራ እና አፋር ክልሎች በተደረጉ ምክክሮች ላይ ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን የጸጥታ ሁኔታው በሚሻሻልበት ወቅት የትግራይ ክልልን ጨምሮ ምክክሩ ባልተደረገባቸው ሌሎች ክልሎችም የማኅበረሰብ ምክክሩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ዳራ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት[1] እና በአፍሪካ ህብረት[2] በተሰጡ ትርጓሜዎች መሠረት የሽግግር ፍትሕ ማሕበረሰቦች የተለያዩ (መደበኛ እና ባህላዊ/መደበኛ ያልሆኑ) የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ እና ተቋማዊ አሠራሮችን በመጠቀም ማኅበረሰቡ ያለፉ መጠነሰፊ ጥሰቶችን ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ፣ ፍትሕን ለማስፈን እና እርቅን ለማውረድ፣ ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል። ሁሉን-አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት አራት እርስ በርስ የተያያዙ እና የሚደጋገፉ መሠረታዊ አካሎችን/ስልቶችን ያካተተ ሲሆን እነዚህም እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት፣ ተጠያቂነትን ማስፈን (መደበኛው የፍትሕ አስተዳደር መደበኛ ባልሆነው ወይም በባህላዊ ሥርዓቶች እየታገዘ)፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ መስጠት፣ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግን ጨምሮ በማኅበረሰባዊ እና ባህላዊ ዘርፎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን በመተግበር ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ዋስትና መስጠት ናቸው (ለምሳሌ የሲቪል ማኅበራትን ማጠናከርን፣ የመታሰብያ/የማስታወሻ (memorialization) ተግባሮችን ማከናዎንን፣ ትምህርት እና የስነ-ልቦና ድጋፎችን ማቅረብ።)
ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ
በተሰጣቸው ስልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት (OHCHR) እና ኢሰመኮ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መሥፈርቶች እና ደረጃዎች የተቃኘ ሁሉን-አቀፍ የሽግግር ፍትሕ መዋቅርን በመጠቀም ለተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግጋት ጥሰቶች የተጠያቂነት እርምጃዎች እንዲወሰዱ መወትወትን ጨምሮ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት እና መከበር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡የኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የጋራ ምርመራ ቡድን በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉትን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች፣ የሰብአዊነት እና የስደተኞች ሕግጋት ጥሰቶችን በተመለከተ በጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት ካስቀመጣቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል፣ “ሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች መርሆችን የሚያሟላ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተጎጂዎቸን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት እንድታቋቁም” የሚል ይገኝበታል።[3] በተጨማሪም የጋራ ምርመራ ቡድኑ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ መሥፈርቶች ላይ የተመሠረተ የሽግግር ፍትህ ሥርዓት በማቋቋም ረገድ የኢትዮጵያ መንሥስትን እንዲደግፍ/እንዲያጠናክር ” ጥሪ አቅርቧል።
ከሽግግር ፍትሕ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምክረ ሐሳቦች ትግበራን ለማገዝ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተወካዮችን፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የተ.መ.ድ. ኤጀንሲዎችን፣ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ አዘጋጅተው የነበረ ሲሆን፤ ተሳታፊዎቹ ወደፊት የሚደረጉ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን አቅጣጫ ለማስያዝ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ሰፊ ምክክር የሚጎለብት ፍኖተ ካርታን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ተወያይተው ያሏቸውን ሐሳቦች አጋርተዋል። ከዚህ አንጻር ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ በመጡ ስመጥር ባለሙያዎች በመታገዝ ከመጋቢት 15 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የሽግግር ፍትሕ አካል የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ስብሰባ የተደረገ ሲሆን ባለሙያዎቹ የተሳታፊዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ቀጣይ እርምጃዎችን ለማገዝ እንዲያስችል ያላቸውን መልካም ተሞክሮዎች አጋርተዋል። በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጡ ውስብስብ ችግሮችን ከመፍታት፣ ዘላቂ ሰላም እና ዕርቅን ከማስፈን፣ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ተገቢውን መፍትሔ ከመስጠት አንፃር ሀገራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ ያስገባ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ማስጀመር ተገቢነት እና ወቅታዊነት ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል። በሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮሩ ምክክሮችን በማጠናከር በዚህ ሥርዓት ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን ሊያግዙ የሚችሉ ልዩ ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶችን፣ አካሄዶችን እና ጥሩ ልምዶችን
መለየት እና መሰነድ የሚሉት ከስብሰባው ከመነጩ ቁልፍ ምክረ ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል።
በሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ በኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የተካሄዱ የማኅበረሰብ ምክክሮች
በመጋቢት ወር በተደረገው ስብሰባ ላይ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች እና በግጭቶች ሳቢያ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ድምጽ ለማጉላት፣ ሥጋታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ለማቅረብ እና ይፋ ለማውጣት ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ለማሳካት ከሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር አስራ ሶስት የመስክ ምክክሮችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ተጠያቂነትን ለማምጣት፣ እርቅን ለማስፈን፣ እውነትን ለማውጣት እንዲሁም የተጎጂዎችን የማካካሻ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚረዱ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የተሳታፊዎችን አስተያየት ለመሰብሰብ ተችሏል። በዚህ መሠረት የኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የጋራ ቡድን እስካሁን በአፋር፣ በአማራ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝቷል። ከላይ እንደተገለጸው በአማራ እና አፋር ክልሎች በተደረጉት ምክክሮች ላይ በርካታ ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቢሳተፉም በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ሁለት ምክክሮች በአካባቢው የነበረው ግጭት በድጋሚ በመቀስቀሱ ምክንያት ለቀጣይ ዙር እንዲተላለፉ ተደርጓል።
የማኅበረሰብ ምክክሮቹ አሁንም በመካሄድ ላይ የሚገኙ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚያካትቱ ሲሆን ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት እስካሁን በተደረጉት እና ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ተፈናቃዮች፣ የሃይማኖት እና የባህል መሪዎችን እና በሰብአዊ መብት እና በሰላም ግንባታ ጉዳዮች ላይ ከሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ 282 ሴቶችን ጨምሮ በድምሩ 717 ግለሰቦችን ባሳተፉት የመስክ ምክክሮች ወቅት የተገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን ይፋ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እነዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች በተመጠኑ የአተኩሮ ቡድን ውይይቶች፣ ከዋና መድረክ በተንፀባረቁ ምልከታዎች እና በግል ቃለመጠይቆች አማካኝነት ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከማኅበረሰቡ የተገኙ አስተያየቶችን ያካትታሉ።
የማኅበረሰብ ምክክሮቹ ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሕዝብን አስተያየት ለይቶ ለማውጣት እና በሌሎች ተቋማት አማካኝነት ከሽግግር ፍትሕ የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ለማገዝ የሚያደርጓቸው ሰፊ ጥረቶች አካል ናቸው። ባለመብቶችን በተለይም የግጭት ቀጥተኛ ተጎጂ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ ላይ ያተኮረው ይህ የተቋማቱ አካሄድ፣ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ለሚደረጉ ውይይቶች እንዲሁም ተገቢ ፣ ሁሉን አቀፍ ፣ እውነተኛ እና አካታች የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለማዳበር እንደ ግብአት እንደሚያገለግል የኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት እምነት ነው። በተጨማሪም ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ተጠያቂነትን፣ እውነትን መፈለግን፣ ማካካሻን፣ ተቋማዊ ማሻሻያን፣ እርቅን እና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጎለብቱ የለውጥ ማሻሻያዎችን ያበረታታል።
የማኅበረሰብ ምክክሮቹ ዋና ዋና ግኝቶች
- ሰላም እና ደኅንነት[4]
በሁሉም የመስክ ምክክሮች ወቅት ተጎጂዎች ግጭቶች እና ከዚህ ቀደም ያጋጠሟቸው ጥሰቶች ያገረሻሉ በሚል የማያቋርጥ ሥጋት ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ስለዚህም ሰላምና ደኅንነት ማግኘት ቀዳሚ ፍላጎታቸው እንደሆነ እና ሌላው ሁሉ ነገር ቀጥሎ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም ተሳታፊዎች ሰላም ግንባታን ለማጎልበት እና እርቅን ለማስፈን ሲባል ሁሉንም ወገኖች እና ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ እውነተኛ ህዝባዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በሽግግር ፍትሕ አማራጮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን ጨምሮ ሌሎች ጥረቶችን ለማድረግ፣ ሰላምን እና ደኅንነትን ወደነበረበት መመለስን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማየት እንደሚገባ በአንዳንድ የምክክር መድረኮች ላይ ከተሳታፊዎች ተጠቁሟል። እንዲሁም በመስክ ምክክሮች የተሳተፉ ተፈናቃዮች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ እና የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንን እኩል ጥበቃ ለማረጋገጥ ሕግን የማስከበር ሥራ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል። የሰላም እና ጸጥታ መስፈን እንዲሁም የሕግ የበላይነት ወደነበረበት እንዲመለስ መደረጉ ያለፈውን ጊዜ በምን መልኩ መሻገር እንደሚቻል እና በግጭቶች ምክንያት ለመጡ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ተጎጂዎች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሳተፉ እና የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ያስችላል። ስለሆነም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉ ግጭቶች መነሻ ምክንያት ላይ ትኩረት በማድረግ መፍትሔ ለመቀየስ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላም እና እርቅ እንዲሰፍን እና ተገቢ ካሳ እንዲከፈል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆን ይገባዋል።
2. ማካካሻ[5]
በሕዝባዊ ምክክሮቹ ወቅት ተጎጂዎች እንደገለጹት በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ለደረሰባቸው ጉዳት ማካካሻ ማግኘትን ሲሆን ይህም ከግጭቱ በፊት ወደነበሩበት ሁኔታ መመለስን፣ ካሳን፣ መልሶ ማቋቋምን እና ጥሰቶቹ ወደፊት ላለመደገማቸው ዋስትና መስጠትን ያካትታል። ከውይይቶቹ ለመረዳት እንደተቻለው ምንም እንኳን ተሳታፊዎች በግጭቱ ወቅት ያጡትን ሁሉ መልሶ ማግኘት እንደማይቻል የሚገነዘቡ ቢሆንም፣ የተጎጂዎችን የአጭር ጊዜ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ ንጽህና መጠበቂያ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እኩል ተደራሽ ሊደረጉ እንደሚገባ በአንድ ድምጽ ጠይቀዋል። ይህንንም በማድረጉ ሂደት ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ፣ በተፈናቃይ ጣቢያዎች እና ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። የመፍትሄውን አይነት በተመለከተ እንደተሳታፊዎቹ የግል እና የማኅበረሰብ የጋራ ልምድ የተለያዩ ፍላጎቶች የተስተዋሉ ሲሆን በአጠቃላይ ተሳታፊዎች መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የማኅበረሰቡን መጠነ ሰፊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችል ስትራቴጂ እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል። እንደ ተሳታፊዎቹ እምነት ከግጭቱ በፊት ወደነበሩበት ሁኔታ ከመመለስ አኳያ ተጎጂዎችን ወደ ቀድሞ መኖሪያ ስፍራቸው መመለስን፣ ከፍርሃት ነጻ ሆነው መኖር እንዲችሉ ማድረግን እና መተዳደሪያቸውን መልሰው እንዲያገኙ ማስቻልን እንደሚያካትት እና እነዚህ የማካካሻ ማእቀፎች ተጎጂዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንጻር አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ንብረቶቻቸውና ከብቶቻቸው የተዘረፉ ተጎጂዎች መደበኛ ሕይወታቸውን ለመቀጠልንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸው እና እውነተኛ ይቅርታ ሊጠየቁ እንደሚገባ ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ አክለውም እንደ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት ያሉ ጉዳት የደረሰባቸው የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ መገንባት እንደሚገባ እንዲሁም የግጭት ጉዳቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስነ-ልቦናዊ ድጋፎችን ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
3. እውነት፣ እውቅና፣ እና ይቅርታ መጠየቅ[6]
ተሳታፊዎች በግጭት ወቅት የተከሰተውን እና እውነት ነው ብለው የሚያምኑትን ሁሉ ለማካፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን ያመላከቱ ሲሆን ተጎጂዎች ስለደረሰባቸው ጉዳት በጉዳት አድራሾች እና ተቋማት እውነቱ ወጥቶ እውቅና ካገኘ፣ ተገቢው መፍትሔ ከተሰጠ፣ እንዲሁም እንደ ሀገር መሪ፣ የክልል ፕሬዝዳንት እና የመከላከያ ሠራዊት ሚኒስትር/አዛዦች ከመሳሰሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች አዛዦች እውነተኛ ይቅርታ ከተጠየቁ ይቅር ለማለትም ሆነ ዕርቅ ለማውረድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ተሳታፊዎች ነጻ፣ ገለልተኛ፣ እምነት የሚጣልበት እና ራሱን የቻለ እውነትን የማፈላለግ፣ የመምራት እና ይፋ የማውጣት ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ተቋም በሀገራችን እንዲቋቋም ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን ሙሉ በሙሉ መንግሥት-መር በሚሆኑ ሂደቶች እና ተቋማት ያላቸውን ተቃርኖም አንፀባርቀዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ እና ሀቀኛ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያቀፈ፣ ሴቶችን ያካተተ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ እና የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችን የሚወክሉ ሰዎችን የያዘ፤ በሚከተላቸው ሂደቶች እና መስፈርቶች ዙሪያ የነጻ እና ገለልተኛ ባለሙያዎችን ምክር ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ሥርዓት እንዲቋቋም ሐሳብ ሰጥተዋል። ተሳታፊዎቹ አክለውም ከላይ የተጠቀሱት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መሪዎች በኅብረተሰቡ መመረጥ እንዳለባቸው፣ ተአማኒነትን እና ተቀባይነትን እንዲያተርፉ የአመራረጥ ሂደቱ ግልጽ፣ አካታች እንዲሁም አቅም እና ችሎታ ላይ በተመሠረተ መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል።
4. ተጠያቂነት[7]
ተሳታፊዎች ፍትሕ ከወንጀል ተጠያቂነት በላይ መሆኑን እንደሚረዱ እና ላለፉ ግፎች እና የግጭት ታሪኮች መፍትሔ ማበጀት፤ ግጭት እና ብጥብጦች እንዲቆሙ እና ዳግመኛ እንዳይከሰቱ መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በግጭት ወይም በሌሎች አውዶች ውስጥ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ላይ ሁሉ በመደበኛው የፍርድ ቤት ሥርዓት ክስ መመስረት እንደማይቻል ይገነዘባሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥላቻን ያሰራጩ ግጭቶችን በሕዝቦች መካከል እንዲፈጠር ያደረጉ ናቸው ያሏቸውን በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን የመሩ/የጠነሰሱ ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ አፅንኦት ሰጥተው የተናሩ ሲሆን እንደ አስገድዶ መድፈር እና ሲቪሊያኖችን መግደል ዓይነት ከባድ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎችም ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ጨምረው አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም እንደ ተሳታፊዎቹ አስተያየት ትዕዛዝ ለሰጡ አመራሮች እና ከባድ ወንጀል ለፈጸሙ ሰዎች ምህረት መሰጠት የለበትም፡፡ በአጠቃላይ ተሳታፊዎች በአሁኑ ወቅት ዳግመኛ ጥፋት እንዳይደገም የሚከላከል አይደለም፣ ሰላምን እና ማኅበረሰባዊ ተሃድሶን አያመጣም ብለው ከሚያስቡት የመደበኛው ፍትሕ ሥርዓት ይልቅ እርቅን በማበረታታትም ሆነ ጥሰቶች እንዳይደገሙ በመከላከል ረገድ የተሻሉ ናቸው ብለው በሚያምኗቸው መደበኛ ባልሆኑት (ባህላዊ/ሃይማኖታዊ) የፍትሕ ሥርዓቶች ላይ የበለጠ እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል። ነገር ግን ባህላዊ ሥርዓቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ከተፈለገ ማስተካከያዎች ሊደረጉባቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል። ለምሳሌ በባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ፈጽሞ አለመኖር ወይም ውስን መሆን፣ በተለይም ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ሴቶችን እኩል የማያዩ አካሄዶች መኖራቸው በተሳታፊዎች ከተነሱ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እውነተኛ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ነጻ እና ገለልተኛ መርማሪ እና ከሳሽ አካላት፣ ነጻ የሆነ ልዩ ፍርድ ቤት (ወይም በሀገራዊ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚሰየሙ ነጻ የሆኑ ልዩ ችሎቶች) ሊቋቋሙ እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና መስጠት[8]
ተሳታፊዎች በአጠቃላይ በመንግሥት ተቋማት በተለይም በሕግ አስከባሪ እና የዳኝነት አካላት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸው በማኅበረሰቦች መካከል መከፋፈልን እና መድሎን የሚያባብሱ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ጨምሮ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ተጎጂዎች ሕዝብን መጠበቅ እና ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ማረጋገጥ የመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተሳታፊዎቹ ለተከሰቱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አንዳንድ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን በተወሰነ ደረጃ ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ስር ያሉ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እና ሰላም እና ደኅንነትን ማረጋገጥ ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ለመከላከል የሚያስችሉ ቀዳሚ መንገዶቸ እንደሆኑ ተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች መንግሥት ግጭትን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማስወገድ የግጭት መንስኤዎችን ከስር መሠረታቸው ለመፍታት እንዲሁም ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ለመከላከል የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻል እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ መልካም እሴቶችን በማስተማር እና ተግባራዊ በማድረግ ወላጆች ለልጆቻቸው አርዓያ በመሆን የሃይማኖት እና የማኅበረሰብ መሪዎች ወጣቶችን ሥነ-ምግባር በማስተማር፣ የመገናኛ ብዙኃን የተዛቡ መረጃዎች እና ጥላቻን ወይም ስሜትን የሚቀሰቅሱ ንግግሮችን ከማመንጨት በመቆጠብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተጠያቂ በማድረግ እና ወ.ዘ.ተ ተመሳሳይ ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ በመከላከል ረገድ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጫወቱት ሚና እንዳለ ተሳታፊዎች በአጽንኦት ተናግረዋል።
ትርጉም ያለው ተሳትፎ
እውነተኛ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖር በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ከማኅበረሰቡ ጋር (grass-root/community level) ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሕዝብ ምክክር ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ግጭት ባለባቸው አካባቢ ያሉ ሕዝቦች በተለይም ተጎጂዎች ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ድምጽ ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። እንደ ተሳታፊዎቹ እምነት፣ በግጭት እጅጉን ለተጎዱት ድምፅ መስጠት እና ማዳመጥ በኢትዮጵያ ያለውን የሽግግር ፍትሕ ሂደት ስኬታማነት የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ ነው። ያቀረቧቸው ግብዐቶች የመንግት ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን ለመቅረጽ እንዲያግዙ እና መልዕክቶቻቸው ፖሊሲ አውጪዎች ጋር መድረሱን እንዲያረጋግጡ ተሳታፊዎቹ ኢሰመኮን እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤትን አሳስበዋል። ፍትሕን ማረጋገጥ ፈውስን እና እርቅን ለማምጣት ያለውን ፋይዳ በመረዳት እንደ እውነት መናገር ባሉ ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዙ ሂደቶች ውስጥ ለመሳተፍ ያላቸውን ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ወደፊትም በማንኛውም የሽግግር ፍትሕ ሂደት መሳተፍን ጨምሮ በመናገራቸው ምክንያት ጉዳት ይደርስብናል ብለው ሳይሰጉ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት አስተማማኝ ምህዳር መፍጠር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። ነጻ እና ገለልተኛ ከሆኑ ተቋማት ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች መሆናቸውን የገለጹት ተሳታፊዎቹ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተዓማኒነት ሊኖረው የሚችለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን የሚወክል ከሆነ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እና ሃይማኖት መሪዎች መደበኛ ያልሆኑ (ወይም ባህላዊ) ሂደቶችን በመጠቀም በተሳካ ሁኔታ አለመግባባቶችን የመፍታት እንዲሁም ተጠያቂነትን፣ ማካካሻን እና እርቅን የማበረታታት የካበተ ልምድ ስላላቸው በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች እና ስልቶች ውስጥ መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከተጎጂዎች እና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና ምክክር በማድረግ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን መንደፍ እና መተግበር፣ ተጎጂዎች ብሎም ሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል ተሃድሶን፣ ሰላምን ፣ ዲሞክራሲን እና እርቅን በማስፈን ሂደት ውስጥ እንደሂደቱ ተጠቃሚ እና እንደ ዋና የለውጥ ኃይል ስለሚኖራቸው ቦታ እና ስለሚጫወቱት ሚና ያላቸውን አመለካከቶች እና መረዳቶች እንዲቀይሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከሀገራዊ እና አካባቢያዊ ባለቤትነት መርህ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን የመንደፍ እና የመተግበር ሂደት ሁሉንም የግጭት ተሳታፊዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ባካተቱ ሀገራዊ ባለድርሻዎች ሊንቀሳቀስ እና ሊመራ ይገባል። ተጎጂዎች[9] እና ሌሎች በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን እና አካሄዶችን በመንደፍ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው። የአካታችነት፣ ርትዕ እና አድልዎ ያለማድረግ መርህ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች እንደ ሴቶች እና ልጃገረዶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ታዳጊዎች እና ሕፃናት ወታደሮች ያሉ የተጨቆኑ እና ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖችን ተሳትፎ የሚያበረታታ እና ፍላጎቶቻቸውንም የሚያሟላ እንዲሆን ያስገድዳል።
የሽግግር ፍትሕ ትግበራ፣ ክትትል እና ግምገማ[10]
የማኅበረሰብ ምክክሩ ተሳታፊዎች የሽግግር ፍትሕን ሂደት ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ድረስ በገለልተኛ አካላት በየጊዜው መከታተል እንደሚያስፈልግ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ እና ምክረ ሐሳቦቻቸውም በአግባቡ እንዲታዩ እንዲሁም አጠቃላይ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የተዓማኒነት፣ ግልጽነት እና ሕጋዊነት/ተቀባይነት መስፈርቶችን ያከበሩ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል። አንዳንድ ተሳታፊዎች ያቀረቧቸውን ሐሳቦች የፖሊሲ አውጪዎች በምን መልኩ እንደተቀበሏቸው እና እንዳካተቷቸው ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት በየመንፈቅ ዓመቱ የሚካሄድ የምክክር ጊዜ እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል። በተጨማሪም የሽግግር ፍትሕ ተቋማቱ በተሰጣቸው ተልዕኮ ላይ ምንም ዓይነት ጣልቃገብነት እንዳይኖር ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።
መደምደሚያ፡- ተጨማሪ ቁልፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆች
በማኅበረሰብ ምክክሮቹ ወቅት ያገኟቸውን በግጭት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሐሳብ እና አስተያየት ከማቅረብ በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ መዋቅርን የማጎልበት እና ትግበራ ሥራ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ባገኙ መሠረታዊ እሴቶች እና መስፈርቶች ላይ የተመሠረተ፣ ተፈጻሚነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት የተቃኘ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዓውዶች ከተተገበሩ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓቶች መልካም ተሞክሮዎች የሚወስድ መሆን እንዳለበት ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. ሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የሚመለከታቸው ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ አካላትን ለማሳሰብ ይሻሉ። በተለይም የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የሚከተሉትን መርሆች ያከበሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል[11]፡-
- ዐውድ–ተኮር፡ በኢትዮጵያ ዐውድ ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊ እና ሕጋዊ አደረጃጀት፣ ታሪክ፣ ባህል እና በተለይም ተጎጂዎች በገለጿቸው ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ላይ በመመሥረት በየአካባቢው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን በመለየት እና ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ደንቦችን ያከበረ ሊሆን ይገባል።
- ሥርዓተ–ጾታን ያማከለ፡ በሁሉም የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ውስጥ እና በየትኛውም ደረጃ ባለ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሴቶችን በማካተት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት ጾታዊ እኩልነትን ማስፈን፣ በጾታዊ ጥቃቶች እና በሥርዓተ-ጾታ ላይ የተመሠረቱ ጥሰቶች እና ዋና መንስኤዎቻቸው ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል።
- ሁሉንም ኅብረተሰብ የሚለውጥ፡ የሽግግር ፍትሕ ሂደት በታሪክ ወደኋላ ለመጓዝ ብቻ የሚደረግ ሙከራ ሳይሆን የተጎጂዎችን ፍላጎቶች በማሟላት እና አለመመጣጠኖችን ጨምሮ ፍትሐዊ ያልሆነ የሥልጣን መዋቅሮችን፣ሥር የሰደዱ አድልዎ እና አግላይ አሠራሮችን፣ የተቋማዊ ጉድለቶችን እና ለሌሎች መሰል የመብቶች ጥሰት ዋና መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነትን አደጋ ላይ ለሚጥሉ ሁኔታዎች መፍትሔ በማበጀት ጉልህ ማኅበረሰባዊ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል እድል ተደርጎም ሊወሰድ ይገባል።
- የሽግግር ፍትሕን የማስፈጸም ኃላፊነት፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተደገፈ ከአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት።
- የሽግግር ፍትሕ አካሎች ማቀናጀት፣ ቅደም ተከተል ማስያዝ እና ማመጣጠን፡ የሽግግር ፍትሕ ተግባራትን የማቀናጀት ምርጫ፤ በአንድ በኩል የሰላም እና የዕርቅ ዓላማዎችን በሌላ በኩል ደግሞ የፍትሕ እና የተጠያቂነት ዓላማዎችን ተደጋጋፊነት እንዲሁም አካታች ልማትን ለማረጋገጥ መጣር አለበት።
- ትብብር እና ቅንጅት፡ ሰላም ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያለው ግፊት እንዲሁም የበርካታ ተዋናዮች መገኘት ትብብር እና ሁሉም አካላት እና ሂደቶች የሀገሪቷን እና ጉዳት የደረሰባቸው ሕዝቦች ቅድሚያ ለሚሰጣቸውን ጉዳዮች እና ፍላጎቶች ምላሽ እንዲሰጡ ለማድረግ ትብብር እና ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሀገራዊ ባለቤትነትን፣ የአፍሪካዊ አመራርን፣ ሕጋዊነትን እና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ሚናዎችን እና ኃላፊነቶችን ማብራራት እና መግለጽ ያስፈልጋል።
- የአቅም ግንባታ ለዘላቂነት፡ ኅብረተሰቡ ሀገራዊ ሂደቶች እና ተቋማትን የሚደግፍበት እና የሚያሳድግበትን አቅም ከማጠናክር አኳያ፣ ሁሉም የሽግግር ፍትሕህ ሂደቶች የአቅም ግንባታ አካል ሊኖራቸው ይገባል።
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም.
[1] የሚከተለውን ሊንክ በመጫን የተ.መ.ድን የሽግግር ፍትህ መምሪያ ማስታወሻ ይመልከቱ https://www.un.org/ruleoflaw/blog/document/guidance-note-of-the-secretary-general-united-nations-approach-to-transitional-justice/
[2] ለምሳሌ በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማእቀፍ ክፍል 19 የተጠቀሰው ሊንኩን በመጫን ይመልከቱ https://au.int/sites/default/files/documents/36541-doc-au_tj_policy_eng_web.pdf
[3] የጣምራ ምርመራ ሪፖርቱን ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ https://www.ohchr.org/sites/default/files/2021-11/OHCHR-EHRC-Tigray-Report.pdf
[4] የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ “የሰላም ሂደት” ማንኛውንም ቀጣይ ሁከት ለማስቆም፣ በተጎዱ ህዝቦች ላይ ያሉ ተጨማሪ የጥቃት ስጋቶችን ለማስወገድ እና በግጭቱ ወይም በአመጽ በተጎዱ አካባቢዎች ለሲቪሎች የጥበቃ እና የደህንነት ዋስትና መስጠትን የሚያካትት መሆኑን ያመለክታል።
[5] የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የማካካሻ ፍትህ ለተፈጸሙት ጥሰቶች እና ጉዳቶች ውጤታማ እና በቂ የሆነ የገንዘብ እና ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ካሳዎችን ያቀፈ መሆኑን ይደነግጋል።
[6] የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እውነት፣ ፍትሕ እና ዕርቅ የተሰኙ የሽግግር ፍትህ አካላት የአስከፊ ግጭቶች እና የሥርዓታዊ ወይም ከባድ የሰብአዊ እና የሕዝቦች መብቶች ጥሰት ታሪክ ያላቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ምርምራዎች የሚደረጉባቸውን ሕዝባዊ ሂደቶች ማዘጋጀትን እንደሚያካትቱ ይደነግጋል። የማኅበረሰብ ምክክሩ ተሳታፊዎች እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን በአንድ ድምጽ ተስማምተው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥትዊ ባልሆኑ ጥቃት አድራሾች ለፈጸሙት ጥፋቶች እውቅና መስጠት እና ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
[7] በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መሠረት ፍትህ እና ተጠያቂነት የሚባሉት የሽግግር ፍትህ አካላት ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም ለተጠቂዎች የፍርድ መፍትሔን ለመስጠት እና ለደረሰባቸው ጉዳት ዕውቅና ለመስጠት ሲባል የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመመርመርና ክስ ለመመሥረት እንዲቻል ሥራ ላይ መዋል ስላለባቸው (መደበኛና ባህላዊ) የሕግ እርምጃዎች የሚያወሱ መሆኑን ይገልጸል።
[8] በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሽግግር ፍትሕ ዐውድ ውስጥ የሚደረጉ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ ወሳኝ የመንግሥት ተቋማትን ለማሻሻል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ፣ ማኅበራዊ እና እኮኖሚያዊ ለውጦችን የሚያረጋግጡ እንዲሁም የወደፊት ጥሰቶችን የሚከላከሉ ተቋማትን ለመገንባት ያለሙ እንደሆነ ይገልጻል። እነዚህ ሂደቶች ሕጋዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ጨምሮ አዳዲስ ሕግጋትን ማጽደቅን፣ ትጥቅ የማስፈታትን፣ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም እና መልሶ የመቀላቀል ሂደቶችን፣ የፍትሕ እና ደኅንነት ተቋማትን ማሻሻልን፣ በመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይ የማጣራት(vetting) ተግባራትን መከወንን እና መሰል እርምጃዎችን ሊያካትት የሚችል ነው።
[9] የሽግግር የፍትሕ ሥርዓትን በመንደፍ እና በመተግበር ሂደት የተጎጂዎችን ማእከላዊነት እና በሂደቱ ውስጥ የሚይዙትን ልዩ ስፍራ በመገንዘብ ክብራቸው ሊጠበቅ፣ አመለካከቶቻቸው ሊከበሩ ፣ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች እና ሥጋቶቻቸው ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
[10] የሽግግር ፍትሕ ምዕራፎችን ማቀድ፣ መተግበር፣ መከታተል፣ መገምገም እና ሪፖርት ማድረግ የሀገር ውስጥ እና አካባቢያዊ ተዋናዮች ተቀዳሚ ድርሻ እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ይደነግጋል። ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ከማበረታታት፣ በሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍዊ ባለድርሻ አካላት የጋራ አላማ እንዲኖራቸው ከማድረግ እና እምነትን ከመጨመር አንጻር በሁሉም ተዋናዮች እና ሂደቶች መካከል የሚኖር ቅንጅት እና መናበብ አስፈላጊ ነው።
[11] ስለሽግግር ፍትሕ እና ሰብአዊ መብቶች የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ተጨማሪ ያንብቡ- https://www.ohchr.org/en/transitional-justice/about-transitional-justice-and-human-rights
የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍን ለማዳበር በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ከተደረጉ የማኅበረሰብ ምክክሮች ፈልቀው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተሰጡ የጋራ ምክረ ሐሳቦችን እና ቁልፍ ግኝቶችን ያካተተ መሪ ሰነድ (እዚህ ያውርዱ)