መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን እያሳሰብን ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑንም እናሳውቃለን፡፡
ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እስከአሁን ባደረጋችሁት ጽናትና ተጋድሎ ሃይማኖታችሁንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንችሁን እንዳላሳፈራችሁ ሁሉ አሁንም ከስሜታዊነት በወጣ ሁኔታ በከፍተኛ ጽናት እና ጥንካሬ የአባቶቻችሁን ድምጽ ብቻ እንድትሰሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን በየአጥቢያችሁ ተደራጅታችሁ እንድትጠብቁ፤ ለአባቶቻችሁ መንፈሳዊ ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንድትሰጡ፣ እየመጣው ላለ መከራና ስደት ለመንፈሳዊ ተጋድሎ እንድትዘጋጁና በፍፁም መንፈሳዊ ጨዋነት በአንድነት የመጣብንን ፈተና እንድትወጡ አደራ እያልን አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ የምንሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን::
የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከተሰጠው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ የተወሰደ
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት
የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን!