በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ላይ ያነጣጠረው የአገዛዙ የጥፋት ዘመቻ ኢትዮጵያን አፍርሶ ኦሮሙማን የማዋለድ ነው!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ቀኖናና ዶግማ ተጥሶ፤ መፈንቅለ ተዋህዶ በሚመስል በህገወጥ አሰራር ጳጳሳት መሾም ፍፁም ወንጀል እንደሆነ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ያምናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን በቅጡ ለመማር ከተፈለገ በጎሳ ፖለቲካ መራኮት ሳይሆን፣ እውቀቱ የሚፈልቀውና የሚመነጨው ከቤተክርስቲያኗ ቋንቋ ከግዕዝ ስለሆነ ትኩረታችን በግዕዝ ላይ ሊሆን ይገባል።

በኢትዮጵያ “አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው።” በሚል ብሂል ሕዝብ ሃይማኖት ሳይገድበው እንደአንድ ቤተሰብ በፍቅርና በመተሳሰብ ተስማምቶ እንደሚኖር ይታወቃል። ነገር ግን የቀድሞው ኢህአዴግ፤ የአሁኑ ብልፅግና/ኦሮሙማ መራሽ አገዛዝ አገራችንን በዘር ፓለቲካ ገዝግዘው ገዝግዘው ንፁሀንን እያረዱ፣ እያፈናቀሉ፣ ከተማ እያቃጠሉና እየዘረፉ ያለተጠያቂነት በወንጀል ተጨማልቀው በህዝብ ስቃይና መከራ እየተዝናኑ መኖር ብቻ አላረካቸውም።

ስለዚህ እንደኢትዮጵያ አይነት ጥንታዊት አገር ለማፍረስ የዘመኑን የጎሳ ፓለቲካ የምትጠየፈውንና የአብሮነታችን ማዕከል የሆነችውን፣ እስላም ክርስቲያኑን ፊደል ያስቆጠረችውንና በቱሪዝም የመንግሥት የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ የሆነችውን ቅድስት ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን መዳፈርን መረጡ። ለዚህም ፣

•|መንግሥት ለወንጀለኞቹና በህገወጥ መንገድ ሲኖዶሱን ለመፈንቀል ከሚጣደፉት ጋር በማበር፣ በመንከባከብና የጥበቃ ከለላ በማድረግ መንግሥት ረዥም እጁ እንዳለበት በተግባር እያሳየ ነው።

•ጠቅላይ ሚንስትሩ የአንድ ሰው ድምፅ ብቻ የሚሰማበትን ካቢኔ በመሰብሰብ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ፣በኦርቶዶክስ ላይ ያላቸውን ንቀት ጥላቻ አሳይተውበታል። የጠቅላይ ሚንስትሩ በማን አለብኝነት የተናገሩት ጠብ አጫሪ፣ ሐሰትና ማስፈራራት የተቀላቀለበት ንግግር ለሰማ መጪውን የጭካኔ እርምጃ አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል። በጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ሙሉ በሙሉ ይስማማል።

•ሌላው ማስረጃ ደግሞ የመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ይህን አደገኛና ትልቅ ችግር እንዳይዘገብ መከልከሉ ነው። የመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ለወትሮው የአገር ድምቀት የሆነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታላላቅ በዓላት፣ እንደ ጥምቀት፣ ልደትና ትንሳዔን ለመዘገብ እወቁን እወቁን ሲሉ ይታዩ ነበር። ታዲያ እነዚህ ጋዜጠኞች በአገዛዙ ማዕቀብ ተጥሎባቸው የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶን ወቅታዊ ችግር ባለመዘገብና የድርሻቸውን ባለመወጣት፣ በብዕራቸውና በካሜራቸው ሊቀመጥ የነበረ የታሪክ አጋጣሚ ስላመለጥቸው ሊታዘንላቸው ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቃል በተግባር ይገለጽ - ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን

•በኦሮምያ ክልል የሚገኘው የፀጥታ ጥበቃ ኃይል ከአፈንጋጩና ተፃራሪው ቡድን ጋር በመተባበር የቤተክርስቲያን በር እየሰበረ በመክፈት ለአፈንጋጩ ቡድን ቤተክርስቲያን መስጠት እንደጀመረ የአይን እማኞች መስክረዋል።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥር ፳፯፣ ፪ሺ ፲፭ ዓ.ም. (Feb. 4, 2023) ቅጽ ፲ ቁጥር ፩

•ምእመናንን እና ቤተክርስትያንን የመጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት መለኮታዊ ኃላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ያደረገውን ህዝባዊ ጥሪ ተከትሎ የአብይ/ብልጽግና/ኦሮሚማ አገዛዝ በሕዛብ ላይ ጦርነት አውጇል። የኦሮቶዶክስ ቤተክርስትያን በሮችን መስበር፣ ቤተ መቅደስን መድፈር፣ ምእመናንን መግደል በስፋት የጀመረ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በሻሸመኔ፣ ወለጋ ሌሎች አካባቢዎች በብዛት የኦርቶዶክስ አማኞች ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል።

የብልጽግና/ኦሮሙማ አገዛዝ ያልተገነዘበው ነገር ቢኖር ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በእያንዳንዱ ምዕመን ልብ ውስጥ ያለ እምነት መሆኑን ነው። ስለሆነም በትዕቢት የተወጠረው የኦሮሙማ አገዛዝ ኦርቶዶክስን ሲነካ በዘር የበታተነውን ሕዝብ በአንድ እየሰበሰበው እንደሆነ አልተረዳም። ስለዚህ ለኦሮሙማው አገዛዝ የጀመራችሁት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ማጥፋት አይቻላችሁምና የምትወዱት የሥልጣን ወንበራችሁ የሕዝብ የሚሆንበት ግዜ እሩቅ ባይሆንም፤ ፈጥኖ እንዲነቃነቅ ከሚያደርግ የጥፋት መንገዳችሁ ተቆጠቡ ሲል ይመክራል። በመጨረሻም ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የቅዱስ ሲኖዶስን አቋምና ውሳኔ በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆም ያሳውቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ብዙ ፈተና ያለፈና ዘመን የተሻገረ ሃይማኖት ስለሆነ ይኸንንም በፅናት ቆሞ በድል እንደሚወጣው ሙለ ዕምነት አለን!

ቅዱስ ሲኖዶሱን ሙሉ በሙሉ እንደገፋለን!

ኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትዋ ተከበራ ለዘላለም ትኑር!

www.moreshwegenie.org

InfoAndPR@moreshwegenie.org

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share