ታህሣስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 5, 2023)
- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ አቶ ለታገሠ ጫፎ
- ኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ አቶ አገኘሁ ተሻገር
- ኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር፣ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ
- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚንስትር፣ አቶ ደመቀ መኮንን
- አማራ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
ጉዳዩ፦ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ እና ራያ ጉዳይ የፍትህ እና የማንነት ጥያቄ ነው።
እኛ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ የአማራ ዓለምአቀፍ አንድነት ማህበር እና ስማችን ከዚህ በታች የተጠቀሰው የሲቪክ ድርጅቶች ታህሣሥ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. (December 31, 2022) አስቸኳይ ስብሰባ አድርገን በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን አቋም የወሰድን መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ እና የዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ እንፈልጋለን።
ጥናቶችና ምርምሮች፤ የኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ፤ በተለይ የአካባቢው የ1,600 ዓመታት ታሪክ እንደሚይሳዩት ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ እና ራያ የትግራይ አካል ሆነው አያውቁም። የትግራይ ድንበር ተከዜ መሆኑ በታሪካዊ መረጃ የተረጋገጠ ነው።
ይህንን የማይካድ ሃቅ የመሳሪያ ኃይል ተጠቅሞ፤ ነዋሪውን የአማራ ሕዝብ ጭፍጭፎ ገሎ፤ ከቀየው አስወግዶ፤ ያልሞተው እንዲሰደድ አስገድዶ፤ የቀረውን ማንነቱን፤ ባህሉን፣ ቋንቋውን፤ ወግና ማእረጉን፤ ስነ ልቦናውን ትግሬያዊ እንዲሆን ኢ-ሰብአዊ በሆነ ጭካኔ ያካሄደውና የነዋሪውን የሕዝብ ስርጭት (demographic change) በኃይል የቀየረው ህወሓት ነው። ይህ በረቀቀ ደረጃ የተካሄደ የአማራ ሕዝብ ጭፍፈጨፋና የዘር ማጽዳት (targeted indigenous Amhara genocide and ethnic cleansing) በራሱ የህወሓትን መሪዎች በሃላፊነት የሚያስጠይቅ መሆኑን ተቀብለናል።
ህወሓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ካርታ እውቅና የነበረውን የአማራውን አንጡራ መሬት ዳር ድንበር ጥሶና አፍርሶ በ 1984 በኃይል የነጠቀውን መሬት ወደ ታላቋ ትግራይ ሲያጠቃልል ነዋሪው ሕዝብ ድምጽ ሰጥቶበት አይደለም። ያጠቃለለው ሕግን ተከትሎና አክብሮም አይደለም። ሕግን አፍርሶና የነዋሪውን አማራ ህዝብ ማንነት ጥሶ ነው።
ይህንን ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ የቀየረው ባለፉት አርባ ዓመታት ብሶቱን፤ ጩኸቱንና አቤቱታውን ሲያሰማ የቆየው ነዋሪው ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተባብሮ ለነጻነትና ለፍትህ ባደረገው እምቢተኛነትና መስዋእትነት ነው። ጉዳዩ የፖለቲካ ነው የምንልበት መሰረታዊ ምክንያትም ይኼው ነው።
ይህን ወሳኝ የሆነ የፍትህ እና የማንነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሬፈረንደም ይካሄድ፤ የፌደራል መንግሥት አካባቢውን ይያዝ የሚባለው አማራጭ ተቀባይነት የለውም። እነዚህ አማራጮች “በግፍ ላይ ጀሮ ደግፍ” እንደሚባለው፣ ከግፍ ላይ ግፍ መጨመር እንጅ ፍትሃዊ መልስ ሊሆኑ አይችልም። እንዲያውም ይህን ማድረግ ህወሓት የሚመኘውንና የሚፈልገውን ስኬታማ ማድረግ ነው። ህወሓት አካባቢውን በመሳሪያ ኃይል ይዞ የነዋሪውን ህዝብ ማንነት ከማፈኑ በፊት 80 በመቶ የሚገመተው ነዋሪ ሕዝብ አማራ መሆኑ ይታመናል። የህዝብ ድምጽ አግባብ በሌለበት ሁኔታ ድምጽ ይሰጥበት የሚለው አማራጭ ኢ-ፍትሃዊና አጅግ በጣም አደገኛ ነው። አደጋው ለአካባቢው ሕዝብ፤ ለአማራው ህዝብ ብቻ አይደለም። ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና ደህነንነት ጭምር ነው።
ከዚህ በታች ስማችን የተጠቀሰው ድርጅቶች ስንገመግመው የኢትዮጵያ ፌደራልና የአማራው ክልል ባለሥልጣናት ሃላፊነት በህወሓት ትዕቢተኛነት እና ጭካኔ የተነጠቀውን የአማራ የማንነት ጥያቄ የሚመጥን ፍትሃዊ መፍትሄ ማስተጋባት፤ አካባቢውን መልሶ ማቋቋም፣ የተጎዱትን እንዲያገግሙ መርዳት፤ አስፈላጊውን የባጀት ድጋፍ መስጠት ነው።
ስለሆነም ይህ የፍትህና የአማራ የማንነት እና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ በፌደራል መንግሥት፤ በኢትዮጵያ የፌደራል ምክር ቤትና በአማራ ክልል መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጠው እና የሚከተሉት ውሳኔዎች በአስቸኳይ እንዲተገበሩ እናሳስባለን፦
- የነዋሪውን የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ያለ ምንም ገደብ ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ማድረግ፣
- የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በመሳሪያ ኃይል የተነጠቀውን የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ሰቲት ሁመራ፤ ጠለምት እና ራያ ካርታ እንዲስተካከል ማድረግ፤
- ለነዚህ አካባቢዎች ሊሰጥ የሚገባው የባጀት ፈሰስ ባስቸኳይ መመደብ፤
እኛ ለማሳሰብ እና ልናሰምርበት የምንፈልገው አስኳል ጉዳይ አገራችን ኢትዮጵያ ከአንድ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት እንድትሸጋገር የማንፈልግ መሆኑን ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት የሚያሰተናግዷቸው አማራጮች ችግሩን ያባብሱታል እንጅ መፍትሄ ሊሆኑ አይችልም።
ሀወሓት በኃይልና በጉልበት ከነዋሪው የአማራ ሕዝብ የነጠቀውን መሬት በህገ መንግሥቱ ደንብ ይስተናገድ የሚለው አማራጭ ኢትዮጵያን ወደ አላስፈላጊ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሚመራት በርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ይህ አማራጭ ተቀባይነት የለውም። ጉዳዩ የሕዝብ የማንነት ጥያቄ እና የፍትህ ጥያቄ ነው። መፍትሄው ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄ ማክበርና መተግበር ብቻ ነው።
ፍትሕ ለተበደሉ በሙሉ!
ፊርማ
- የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ የአማራ ዓለም አቀፍ አንድነት ማህበር
- Adwa Great African Victory Association (AGAVA)
- All Shewa Ethiopian People Multipurpose International Association
- The Amhara Association in Queensland, Australia
- Amhara Dimtse Serechit
- Amhara Well-being and Development Association
- Communities of Ethiopians in Finland
- Concerned Amharas in the Diaspora
- Ethio-Canadian Human Rights Association
- The Ethiopian Broadcast Group
- Ethiopian Civic Development Council (ECDC)
- Freedom and Justice for Telemt Amhara
- Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause
- Global Amhara Coalition
- Gonder Hibret for Ethiopian Unity
- Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation
- Network of Ethiopian Scholars (NES)
- Radio Yenesew Ethiopia
- Selassie Stand Up, Inc.
- Vision Ethiopia
- Worldwide Ethiopian Civic Associations Network (WE-CAN)