ባሕር ዳር ላይ የሚቀዝነው ኢህአዴግ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

በተረኝነት የሚፈራረቁት የጎሳ ድርጅቶች ራሳቸውን እንጂ የሚምሉበትን ሕዝብ አይወክሉም። ራሳቸው ተሰባስበው ወይም ሌላ ጌታ አሰባስቧቸው የቆሙ ጨቋኝና ጨፍላቂ ድርጅቶች እንጂ ዲሞክራሲያዊ አይደሉምና። አካሄዳቸውም እንወክለዋለን ያሉትን ሕዝብ የማስጠላት፣ የመነጠልና ጨቁኖ እና አስደንብሮ ሌላውን የመጨቆኛና የማጥቂያ መሣሪያ አድርጎ መገልገል ነው።

ከአሥር አመት በፊት ነው። አውሮፕላን ማረፊያው ደርሼ የመታሰቢያ ፎቶ ልነሳ ቀና ስል “ግንቦት ሃያ አውሮፕላን ማረፊያ” የሚል መፈክር ተጽፎበት አየሁ። እንደማቅለሽለሽ አደረገኝ። ባሕር ዳር ነው ቦታው። እውነት ባሕር ዳር ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። የአማራ ክልል ብላ ወያኔ በሰየመችውና በዋና ከተማው በባህር ዳር ኢትዮጵያ የፈረሰችበት፣ አማራ ከነነፍሱ የተቀበረበት፣ የሩዋንዳ ጂኖሳይድ፣ የዮጎዝላቪያ ፍርሻ ውጥኖች በኢትዮጵያ መሠረታቸው የተጣለበት ዘመን መባቻ በሆነው በግንቦት ሃያ መሰየሙ ያጥወለውላል።

ይሄንን አስቀያሚ ስሜት ባሕር ዳር ላገኘኋቸው የአካባቢው ተወላጆች ስገልጽላቸውና እነሱም በአማራ መሪነት የተሰየሙት ባእዳን ላይ ከፍተኛ ቁጣ ሲገልጹ ስሰማ ሰነበትኩ።  መልሱ ጉዞዬ ቀን በረከት ስምኦን ያለምንም አጀብና ጥበቃ እየተጎማለለ ባሕርዳር ኤርፖርት መጥቶ እኔው በምሄድበት አውሮፕላን ከፊት ተቀምጦ ሲሄድ አየሁ። “አይ አማራ ምስኪኑ!” ይላል ዘመድኩን።

የአውሮፕላን ማረፊያውን ስያሜ ስመለከት የተሰማኝ ስሜት ወያኔ ቁምጣውን ገልቦ ቅዘኑን በአማራው ላይ እንደተጸዳዳበት ዐይነት ስሜት ነው። ይቅርታ ለአገላለጹና ለቋንቋው።  እውነተኛውን ስሜት ለማሳየት በሚል ነው።   ዛሬም የአቢይ አህመድ  የአማራ  ማረጃ ቆንጨራ  የሆነው ሽመልስ  አብዲሳ አማራ ባረደ ቁጥር  ባሕር ዳር  እየሮጠ  ካባ  አልብሱኝ  ማለቱ  አልበቃው  ብሎ፣  ባሕር ዳር  ገብቶ  የብአዴን ስብሰባ ሲመራ  ውሏል።  የ ሽመልስ ጦር በዚያው ሰዐት በአንገር ጉተን እና ሌሎችም የወለጋ  ቀበሌዎች የተለመደውን የአማራ ጭፍጨፋ እያካሄደ በደም ጎርፍ እየዋኘ ያለበት ጊዜ ነው።  አማሮች በወለጋ የጅምላ መግደያ መጋዘኖች እየተዘጋጀላቸውና የጅምላ መቃብር እየተቆፈረላቸው ያለበት ወቅት ነው።  ከባሕር ዳር በመቶ ኪሎሜትር ርቀት በየጫካው የተበተኑ የወለጋ ተፈናቃዮች አባ ከና ያላቸው ሰው የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሠራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበርና አመራሮቹ ለደህንነታቸው በመስጋት ተሰደዱ

በአቢይ ሕወሃት ጦርነት በቢሊዮን ብር በወደመው የአማራ ክልል እና በሚሊዮን አሃዝ ባለቀው የአማራ ልጅና ገበሬ እልቂትና ውድመት የሽመልስ ቡድን “ድል ተመዘገበ” እያለ ቦላሌውን ገልቦ ሲቀዝንበት ውሏል። በብአዴን ላይ። ብአዴን ደግሞ በአማራ ስም ስለሚንቀሳቀስ የተዋረደው በእጅ አዙር ማን እንደሆነ ግልጽ ነው። አዎ ድል አስመዝግበዋል። ሀገር አፍራሾቹ ከፍርሻ አጀንዳቸው አኳያ። ያንን ውርደትና ውድመት ግን ተበዳዩን “ድሌ” ነው ብለህ ተቀበል ማለት በሰው ገበታ ላይ ከማስታወክ ይበልጥ ይቀፋል።

ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ይላሉ አበው። ጊዜ የሰጠው ድንጋይማ ምንኛ ይበረታ!

ታኅሣስ 27፣ 2015

አሁንገና ዓለማየሁ

 

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share