እያመመን መጣ! – በቦቆቅሳ ሉባክ

ታህሣሥ 2015


ቂምን ሻረውና ፣ ወይ ፍቅርን አንግሠው
ሁለት ሆኖ አያውቅም፣ አንድ ነው አንድ ሰው፡፡

ቴዲ አፍሮ 2014 ዓ.ም. (እያመመው መጣ ቁ. 2)

‹‹በብልህ ላይ ያለ ድንቁርና ተራራ ያህላል›› ይላሉ አበው በምሳሌ ከአንዳንድ በአክብሮት ከሚታዩ የማሕበረስብ አባላት የማይጠበቁ ግዙፍ ስህተቶች መፈፀማቸውን ሲ ስተውሉ፡፡  በሕብረተሰቡ ዘንድ የተከበሩ የሚባሉ ወይንም ሥልጣን የያዙ ሰዎች የሚሰጧቸው የተዛቡ የአስተዳደር ውሳኔዎች፣ የፍትህ አሰጣጥ ግድፈቶች፣ አድሎአዊና ወገንተኛ አካሄዶች፣ እንዲሁም የሚከተሏቸው የሕይወት አቋሞ ሕፀፆችና ሌሎች የማይጠበቁ ውሳኔዎች መላ ቢስነት ወይንም ጉዳት አስከታይነት በዚህ መልክ ይገለፃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ እያሳዩ የመጡት ያልተጠበቀ ፀባይ ለዚህ ምሳሌ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መጀመሪያ ላይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ባሳዩት ብስለትና ብልህ አመራር እንዲሁም ለሕዝብ በገለፁት ራዕይ የተነሳ የሰጣቸው ድጋፍ፣ ፍቅርና ማበረታታት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡  በሰከነ የአመራር ስልታቸው፣ በቅንነታቸው፣ እውቀትን በተላበሰው አነጋገራቸው፣ በትህትናቸውና በገቡት ቃል ኪዳን ከፍተኛ ተስፋ ጥሎባቸው ነበር፡፡  አጀማመራቸው እንከን የሚወጣለት አልነበረም፡፡   በቅን መንፈስ አገሩን ለሚወድና የአገሪቱን በጎ ለሚመኝ ሁሉ ታላቅ ተስፋ የሰጠ ጅምር ነበር፡፡  ይህቺን ከውስጥም ከውጭም ጠላቶች እንደአሸን የፈሉባትን ጥንታዊት አገር ከከፍተኛ የመከፋፈል ጭንቀት ውስጥ አውጥተው ለሁሉም ሕዝብ ወደሚመች ሰላማዊና ሚዛናዊ አስተዳደር እንደሚመሯት ብዙዎቻችን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡

በእርግጥ ይህ ቀላል አንደማይሆን አለመገንዘብ የዋህነት ይሆናል፡፡  የውስጥ የፓለቲካ ሽኩቻ፣ አለም አቀፍ ጫናዎች፣ እንዲሁም ያልተገቡ፣ እውነታን ያላገናዘቡና በሃሰተኛ ትርክት ላለፉት 30 ዓመታት ሲቀነቀኑ የቆዩ ከየአቅጣጫው የሚመጡ ፍላጎቶች ነገሮችን ሊያወሳስቡ እንደሚችሉ ግልፅ ነበር፡፡

በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክፋትን/የጎሰኝነትን መንገድ ይከተላሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡  በቅን መንፈስ አገራቸው ኢትዮጵያን እንደሚወዱና ባጠቃላይ ለሁሉም ሕዝብ የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ቀን ከሌት የሚባዝኑ ቅን ግለሰብ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ሆኖም፣ ከየአቅጣጫው ጫና እየበዛባቸው ሲመጣ ለሥልጣናቸው አስተማማኝ የሚሆነውና ለክፉ እንዳይጋለጡ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ የሚሰጣቸው፣ እንዲሁም የያዙትን ወንበር የሚያስጠብቅላቸው የመጡበት ዘውግ መሆኑን በመገንዘብ ባሁኑ ሰዓት ልክ እንደ ት.ሕ.ነ.ግ ሥልጣንን ያንድ ቡድን የግል ንብረት በማድረግ የለውጡ ሁኔታ ያመቻቸለትን የተረኛነት ዕድል ለማሳለጥ ጥረት እያደረገ በሚገኝ ምስጢራዊ፣ ፅንፈኛና ዘረኛ ጎራ ተፅእኖ ሥር ሆነው አገር ለመምራት እየሞከሩ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይህ ሁኔታ ትክክል እንዳልሆነና እንደማያዋጣ ቢገባቸውም አማራጫቸው ጠባብ እየሆነ ስለመጣ ከዚህ አክራሪ ጎራ ጋር ያሏቸውን የአመለካከት ልዩነቶች እያቻቻሉ ለመቀጠል መሞከራቸው ከሚታየው ሂደት መረዳት ይቻላል፡፡  ባጠገባቸው የተሰባሰበው ይህ አስመሳይ ፅንፈኛ ኃይል ፍላጎቱ ከሳቸው ሕልም ጋር ሙሉ በሙሉ ባይጣጣምም በሃገሪቱ ላይ ካላቸው ተቀባይነት አንፃር ሊጠቀምባቸው እየሞከረ እንደሆነ ሁኔታዎች ያሳብቃሉ፡፡ እሳቸውን ከፊት አስቀድሞ ሕዝብን በማዘናጋት የሚያልማትን የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ለመመስረት ይታትራል፡፡ ውስጥ ለውስጥ ራሱን ያደራጃል፣ ወጣቶችን ይመለምላል፣ አላማውን ለማሳካት የሚያስችለውን ሁኔታ በያቅጣጫው ያመቻቻል፡፡  ሲመቸውም ልክ እንደነገር አባቱ ት.ሕ.ነ.ግ ችግር እየፈለፈለ ሕዝብ ከሕዝብ የሚጋጭበትን ሁኔታ በመፍጠር በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ ሁኔታ እንዳይኖር በማድረግ የአንድነት ጎራው እንዲዳከምና እንዲፈረካከስ የተቻለውን ያደርጋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒሰትሩ በኩልም በኦሮሞ የበላይነት የተገነባች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ይቻላል ብለው ለማሳመን የሚሞክሩ  ይመስላል፡  ይህን ሃይል ሳያስከፉና ሳያስበረግጉ በዓላማቸው ፀንተው ሊሄዱ የሚችሉበት ድረስ ለማስኬድ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ የሚታየው ሁኔታ ይመሰክራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የአቅም ሚዛኑ ወደጽንፈኞቹ እያደላ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡  በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየአቅጣጫው በሚመጣባቸው ጫና የተነሳ ወዲያና ወዲህ እያሉ ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው ለማስተናገድ የሚሞክሩ ይመስላል፡፡  ሁለት ተክለ ሰውነት ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሊመስለን የቻለበት ምክንያት በዚህ የተነሳ ይመስለኛል፡፡

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ባጠገባቸው፣ እንዲሁም በየድርጅቱና በየመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተሰግስገው አገርበሚያተራምሱት ፅንፈኞች መካከል የሚካሄደው እርስ በርስ የመፈታተን ውዝዋዜ ተብላልቶ የመጨረሻው ሁኔታ ላይ ሲደርስ ግን ሁለቱ ወገኖች አብረው መጓዝ ስማይችሉ በውድም ሆነ በግድ አንዳቸው ላንዳቸው አላማ ማጎብደዳቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ ሁለቱ ሃይሎች ባይነ ቁራኛ እየተያዩ እስከተወሰነ ደረጃ ይጓዛሉ፡፡  በመጨረሻም ጉልበቱ ያየለው ክፍል አንደኛውን አስወግዶ ወይንም አንገት አስደፍቶ የበላይነቱን ይይዛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው አማራጭ ይህ ሃይል እንዳያስወግዳቸው ተመሳስሎ መዝለቅ፣ አንዳንዴም እንደ አክራሪዎቹ ከረር በማለት ላንገራገረው ፅንፈኛ ጎራ መተማመኛ በ ስጠት ለዘብ እንዲልላቸው ማድረግን ሳይወዱ በግድ የሚመርጡት ለመኖር ሲባል የሚደረግ ትንንቅ ይሆናል፡፡  የፅንፈኛው ቡድን ጉልበት አሁን እንደሚታየው እየፈረጠመ ሲመጣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቡድን ጋር ተመሳስሎ በመኖር አላማውን ለማስፈፀም የሚያስችለውን ሁኔታ በማንገራገር እየተቀበሉ በአምባገነንነት ከመቀጠል ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡  ይህ አይነት ሁኔታ ብዙ ጊዜ በቅን መንፈስ የሚነሳሱ መሪዎች በሥልጣን ለመቆየት የሚያስችል አማራጭ ሲጠብባቸው ሳይወዱ በግድ ለመኖር ሲሉ የሚመርጡት አካሄድ ነው፡፡ ፅንፈኛው ጎራም የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሥልጣን በተለየዩ ሁኔታዎች ሲቦረቡር ይቆይና ጊዜው ሲያመቸውና ሁኔታዎች ሲስተካከሉለትሊያስወግዳቸው እንደሚሞክር ከተያዘው አካሄድ መረዳት ይቻላል፡፡

በተለይ አፍሪካ ወስጥ በተለያየ ግፊት በየአቅጣጫው ተወጥረው አምባገነንነት ውስጥ የሚዘፈቁ መሪዎች በዚህ መንገድ ሲጓዙ ብበዛት አይተናል፡፡ ሁኔታው የተመቻቸለትና ጉልበቱን ያፈረጠመ ቡድን ጋር ጥምረት በመፍጠር ቀድሞ ለሃገር የሚጠቅም ይዘት የነበራቸው አላማዎች እየተረሱ የፈረጠመው የፅንፍ ቡድን የሚፈልገው ድብቅ አላማና እንዲሁም የምዝበራና የበላይነት ጥማት አየሰመረ እንዲሄድ የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ በመግባት ሥልጣንን ለማራዘም የሚደረግ የመኖር ጥያቄ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡  አሁን አየተከሰተ ባለው አምባ ገነናዊ ሁኔታ መዝለቅም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊወገዱ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ለአገራችን ትልቅ እዳ ይዞ እንደሚመጣ ግልፅ ነው፡፡  በተለይም የሥልጣን ዝውውርን ለማሳለጥና በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን እንዲቻል የሚረዳ የተቋሞች ግንባታ በሚፈለገው መጠን ሊካሄድ ስላልቻለ/ስላልተፈለገ ማንኛውም አይነት ለውጥ ለሃገሪቱ አስጊ ሁኔታ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማገናዘብ ተገቢ ነው፡፡

አምባ ገነንነት በተለያየ የስነ ልቦና፣ የአስተዳደግና የኑሮ ልምድ ምክንያቶች የሚከሰት ጠባይ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል የአምባ ገነንነት ምልክት ያልታየባቸው መሪዎች ወደ አምባ ገነንነት የሚገፉበት ዋናው ምክንያት በሚደርስባቸው የውስጥ ጫና የተነሳ ህልማቸውን ዳር ሳያደርሱና ያለሙትን ሳያሳኩ እንዳይወገዱና አላማቸው እንዳይደናቀፍባቸው የሚፈጥሩት የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡  ይህ ጫና እያደረ የተነሱበትን ዓላማ እያስረሳ ሥልጣንን ለማንበር የሚያደርጉት ጥረት አብዛኛውን ችሎታቸውንና እውቀታቸውን እንዲያተኩሩበት በማድረግ የተነሱበት ዓላማ ቀስ በቀስ እየከሰመና እየተረሳ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡  በተለይ እንደኛ ባለ የወደደውን ግለሰብ የአምላክ ያህል በመካብ ለሚያገን፣ የጠላውን ደግሞ ለነገ ሳይል በማዋረድ ማጣጣል የሚቀናው ሕብረተሰብ ውሰጥ የአምባ ገነንነትን ጠባይ ለማዳበር ብዙ ጊዜ አይፈጅም፡፡  ለዚህም ባለፉት መሪዎቻችን የታዩት ሁኔታዎች ምስክር ናቸው፡፡ .

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሳንሆዜ ከተማ ለወራት የታቀደው የወያኔ የማጭበርበር ሴራ በሚያሳፍር መልኩ ተጠናቀቀ

ዶ ር አብይም አምስት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአምባገነንነት ስነ ልቦና እየተላበሱ ምመጣታቸውን ለማረጋገጥ በቅርቡ እያሳዩ የመጡትን ለምን አስተያየትም ሆነ ገንቢ ትችት ተሰነዘረብኝ በማለት የሚያሰሙትን የእልህ፣ የቁጣና እብሪት የተሞላባቸው አፀፋዎች ማድመጥ ይበቃል፡፡ ለሚጠየቁ ጥያቄዎችና ለሚሰነዘሩ ማሳሰቢያዎች ቀጥተኛ አሳማኝና በእውነታው ላይ የተመረኮዘ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፅንፈኞቹን ላለማስከፋት ሲሉ የሚሄዱበት የተወሳሰበ መንገድ እሳቸውንም ሆነ አገሪቱን ከማትወጣበት ማጥ ውስጥ እየከተታት እንደሆነ ለማመን የደፈሩ አይመስልም፡፡  ስህተትን በተደጋጋሚ ስህተት ማረም እንደማይቻል፣ እውነትን አፍኖ ማቆየት እንደማያዋጣ፣ የሕዝብን ትዕግሥት በንቀት መመልከት በእጅጉ እንደሚያስከፍል በራሳቸው አንደበት ገልፀውልን ሲያበቁ አሁን ባወገዙት መንገድ ለምን እንደሚጓዙ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሊጠፋን አይገባም፡፡   የችግሩ አሳሳቢነት በቁጣና በኃይለ ቃል እንደማይስተካከል ቢረዱትና ሁኔታዎችን ወደ ሕዝባዊነትና ዲሞክራሲያዊነት ለመመለስ ቢሰሩ አገሪቱን ከብዙ መከራ ሊታደጓት ይችሉ ነበር፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲህ አይነቱን ግለሰባዊ ወይንም ቡድናዊ ገደብ የለሽ ፈላጭ ቆራጭነትና ሁሉን እኔ አውቃለሁ ባይነት ከመስመሩ እንዳይወጣ ለመቆጣጠር ሆነ ተብሎ የሚዋቀር የአስተዳደር ስልት ነው፡፡  የሰው ልጅ በተፈጥሮው ገደብ የሌለው ሥልጣን ከተሰጠው ቅጥ ያጣ ጉልበተኛ ሊሆን እንደሚችልና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሥልጣኔን ሠይፍ በፈለግሁት መንገድ እጠቀምበታለሁ ሊል እንደሚችል በመገንዘብ ነው የሥልጣን ክፍፍልና ቁጥጥርን ያካተተ ሥርዓት እያስፈለገ የመጣው፡፡  ‹‹ገደብ የለሽ ስልጣን ገደብ በሌለው ሁኔታ ያበላሻል›› የሚባለውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡   በሀገራችን ከዚህ አይነቱ ሥርዓት ለመላቀቅ በተከታታይ ጥረት ቢደረግም በየጊዜው እየጨነገፈ አሁንም አስተማማኝ ባልሆነ የአስተዳደር ቀንበር ውስጥ እንገኛለን፡፡

የተረገጠ እውነት

አሁን እያየን ያለነው በተለያየ የፈጠራ ትርክትና በዝቅተኝነት ስሜት በተወጠሩ አክራሪዎች ቀመር መሠረት፤ የነበረቸውን፣ያለችውንና በማእከላዊ አስተዳደር ረዥም ታሪክ ያ መዘገበችውን ጥንታዊት ኢትዮጵያን አጥፍቶ፣ ያልነበረቸውንና በታሪክ የተደራጀ ማእከላዊ አስተዳደር ኖሯት የማታውቀውን የኦሮሚያን ሪፐብሊክ ለመመስረት የሚደረግ የቁም ቅዠት ነው፡፡ ት.ሕ.ነ.ግ በመሰሪ እቅዱ መሠረት የራሱን ነፃ መንግሥት ሲመሰርት፣ በቀጣይነት ያስቀመጠው ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችም እሱን ተከትለው ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ነው፡፡  እኛና እነሱ የሚለው ከፋፋይ አስተሳሰብ በሕብረተሰቡ፣ በተለይም በወጣቱ ዘንድ እየሰረፀ መሄድ ከጀመረ ቆይቶ በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡  አያት ቅድም አያቶቻቸው ከተለያዩት የአገሪቱ ሕብረተሰቦች ጋር ሆነው አብረው ተዋድቀው ያቆዩትን አገረ መንግሥት ለእንድ ዘውግ አስረክበው ራሳቸውን በባይተዋርነትና በተጠቂነት አያዮ በምቀኝነትና በቂም በቀል ስሜት እንዲያድጉ ተደርጓል፡፡ (የኦሮሞ ክልል በማለት ፋንታ፣ ኦሮሚያ ክልል የተባለበት ምክንያት የነፃ አገር ምስረታ ቅድመ ዝግጅት እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡  በዚህ አይነት ስያሜ መሰረት ከተሄደ፣ አማራ ክልል – አማርያ፣ ደቡብ ክልል – ደቡቢያ፣ ሶማሌ ክልል- ሶማሊያ ወዘተ. መባል ነበረባቸው)

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አቀማመጥ ለዚህ ቅዠት መሳካት ትልቅ መሰናክል መሆኑ ታምኖበት ከተማዋን በተለያየ ዘዴ በኦሮሚያ ክልል ተፅእኖ ሥር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የምናየው ነው፡፡  የእግር ውስጥ እሳት የሆነችባቸውን አዲሰ አበባን እንዴት አድርገው ኦሮሞ ለማድረግ እንደሚችሉ የያዙት አሳዛኝና አገር አጥፊ ጥረት በአውነት እነዚህ ሰዎች የሚመሩት በደመ ነፍስ፣ በቂም በቀልና በእልህ እንጂ በማስተዋል እንዳልሆነ ግልፅ  ያደርገዋል፡፡  እውነታንና መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ለማገናዘብ እንደቸገራቸውም ማየት ይቻላል፡፡ የሚሰሩት፣ የሚወስኑትና ሕዝብ በግድ እንዲቀበል የሚያደርጉት የማስገደድ ሁኔታ በእውነት እነዚህ ሰዎች የማሰብ ችሎታ አላቸው ይሆን ብለን ለመጠየቅ ያስገድደናል፡፡ በአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ላይ የእኔን ፍላጎት ልጫንብህ ማለት እነሱ ተጫነብን ከሚሉት የበላይነት ስሜት በምን መልኩ ይለያል ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ ያልቻሉት በእልህ፣ በቅናት፣ በበታችነትና በቂም በቀል ስሜት ስለሚነዱ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

ታዲያ ዶ/ር አብይ በዚህ አይነቱ ሰንካላ አላማ በተለከፉ ከጎናቸው ተሰልፈናል በሚሉ አስመሳይ መሰሪዎች ተፅእኖ የተነሳ ባሰቡት መንገድ ኦሮሞነትን ሳይጥሉ ኢትዮጵያዊነትን አግንነው ለመምራት እንደቸገራቸው መገንዘብ አያዳግትም፡፡  በአካሄድ፣ በአላማና በግብ ልዩነት የተነሳ የውስጥ ሽኩቻ እንዳለ ግልፅ ነው፡፡  ት.ሕ.ነ.ግ በቀየሰው መንገድ አገር መከፋፈል አለባት ብለው የሚያምኑ በርካታ ሥልጣን የያዙ ጎሰኛ ግለሰቦች እንዳሉ አለመገንዘብ ራስን ማታለል ይሆናል፡፡  በእብሪትና በዝቅተኝነት ስሜት ተገፋፍተው እኛና እነሱ እያሉ ሕብረተሰቡን በመከፋፈል ያለሙትን እኩይ አላማ ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው ብለው ይህን አላማ ለማሳካት የሚታትሩ ብዙ መሆናቸው በግልፅ እየታየና ውጤቱም ትርምስ፣ ሥርዐት-አልበኝነትና የድሃ ሕዝቦች ጭፍጨፋ እየሆነ እንደመጣ የምናየው ነው፡፡

የዘር ጉንፋን

ት.ሕ.ነ.ግ የጀመረው ጦርነት ያሰናከለው የለውጥ ሂደት መኖሩን ሳንዘነጋ የለውጥ ኃይል ነኝ በሚለው ቡድን ቃል የተገቡት ነገሮች ሁሉ ባልታሰበና በማይጠበቅ መንገድ ሲጨናገፉ ማየት የዘወትር ሰቀቀናችን ሆኗል፡፡  ዜጎች በግፍ እየተጨፈጨፉ ነው፡፡  የተረኝነት ስሜት ተንሰራፍቶ ህዝብ በሚደርስበት ቅጥ ያጣ በደል እየተማረረ ነው፡፡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው የህልውናና የሰላም ጥያቄዎች ወደጎን ችላ ተብለው የማስመሰልና የአስረሽ ምቺው ግርግር በዝቷል፡፡

በተለይም የፍትህ መዋቅሩ ከወያኔ በባሰ ሁኔታ ‹‹ያይናችሁ ቀለም አላማረኝም›› አያለ ንፁኃንን እንደፈለገ የሚያስረውንና የሚያንገላታውን  ምስጢራዊ ቡድን መቆጣጠር አልቻለም ወይንም አልፈለገም፡፡  በሰላማዊ መንገድ ተፃራሪ አስተሳሰብ ማቀንቀን ሃጢአት ሆኖ ሥልጣን የተቆጣጠሩት አካላት የማይፈልጉት ሃሳብ ያለው ግለሰብ ወይንም ቡድን እንኳን ራሱን መግለፅ ቀርቶ ሃሳቡን በነፃነት እንዳያንሸራሽር የሚፈታተን ሥርዓት ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ ነው፡፡

‹‹ሳናጣራ አናስርም›› ተብሎ ቃል በተገባበት አገር ዜጎች የሚሰማቸውን ስለተናገሩና ስለፃፉ በመንግስት እውቅና ባላቸው ምስጢራዊ አፋኝ ቡድኖች እየታገቱ ሲጉላሉ ማየት አሁን መሪ ነን የሚሉትን ግለሰቦች አለማሳፈሩ የሚያሳዝንና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡   ያለፉትን አገዛዞች በተመሳሳይ ድርጊታቸው ሲነቅፉ የነበሩ ሰዎች እነሱ ተራቸው ደርሶ ሥልጣኑን ሲይዙ ለምን ተነካን? ለምን ተተቸን? ለምን ተደፈርን? ማለታቸው እንደሀገር ልናዝንበትና ልናፍርበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡  እነዚህ ሰዎች ካለፈው ስህትት ምን ተማሩ? ይህን አይነት አይን ያወጣ የመብት ጥሰት እየፈፀሙ ያለፉትንስ ለመውቀስ የሚያስችል ምን የሥነ ምግባር ልእልና ሊኖራቸው ይችላል?  መነቀፍን፣ መገሰፅን፣ አያያዛችሁ ትክክል አይደለም አስተካክሉ መባልን እንደውርደት የሚቆጥሩ ሰዎች እንዴት ነው ዲሞክራሲን ሊገነቡ የሚችሉት?  ወይንስ ከበፊቱም ቢሆን የት.ሕ.ነ.ግን አላማ ይዘው ነው የመጡት?

አገር ያለችበትን አስቸጋሪና አሳሳቢ ሁኔታ እንገነዘባለን፡፡  ይህን አስጊ ሁኔታ በማጤን ሕዝቡ ከፍተኛ ትእግሥትና መተባበር አሳይቷል፡፡  በመንግሥት በኩል ቅንነት የጎደለውአካሄድ፣ የአስተዳደር በደል፣ ንቀትና ቸልተኝነት እያየ ሁኔታው ስላላመቻቸው ነውና እስቲ እንታገሳቸው እያለ በትብብር መንፈስ እሰካሁን ዘልቋል፡፡  አመራሩን የተቆጣጠሩት የጊዜው ሰዎች ግን ይሉኝታ ቢስና ውለታ ቢስ ሆነውበታል፡፡  ወደ ሥልጣን ያወጣቸውን ሕዝብ በንቀት፣ በእብሪትና በእልህ ለመምራት ቆርጠው የተነሱ ይመስላል፡፡  ት.ሕ.ነ.ግ የሕዝብ ብዛት ሳይኖረው መላ ኢትዮጵያን ረግጦ ለሃያ ሰባት አመታት መግዛት ከቻለ፣ እኛ ይህን አይነት አቅምና ቁጥር ይዘን ከዳር አስከዳር ረግጠን ለመግዛትና ለመተራመስ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም የሚል የትእቢት መንፈስ ውስጥ የተዘፈቁ ይመስላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የግብፅና ኢትዮጵያ መጪው ዘመን ምን ሊመስል ይችል ይሆን?

ይህ አስተሳሰብ ትክክል ስላልሆነና አገሪቱ ከአስከፊ ጥፋት እንድትወጣ ችግሮች ሲኖሩ እንዲስተካከሉ መወትወት የዜግነት ግዴታችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡መሪ ነን ባዮችም እንደፈለግን እኛ በተመቸን መንገድ እንግራችሁ ሲሉን አይሆንም፣ ይበቃል ልንላቸው ይገባል፡፡  የእኔ አውቅልሀለሁ ዘመን አልፏል፡፡  አብረን ተባብረን የአገራችንን ቀጣይ እጣ መወሰን መብታችንም ግዴታችንም ነው፡፡  ገና ለገና መሪዎቻችንን ያሳጣል ብለን በይሉኝታ ዝም ብለን የምናሳልፋቸው ነገሮች እየተጠላላፉ በመሄድ ለመፍታት የሚከብዱ የተቆላለፉ እዳዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አሁን የምናየው የተወሳሰበና የተርመጠመጠ ሁኔታ ግልፅ ማስረጃ ነው፡፡

ተስሰተባበለም አልተስተባበለም ተረኝነት በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የዛሬ ባለጉልበቶች ተረኝነት አልተንሰራፋም በማለት ራሳችሁን ቅሌትና ትዝብት ውስጥ ከመክተት ይልቅ ሕዝቡን ብትሰሙት ከከፍተኛ ውድቀት ትድኑ ነበር፡፡ ህዝቡ በተረኝነት ስሌት የሚንቀሳቀሱ ሌቦች አስቸገሩን ሲላችሁ፣ ያየህውና የሰማህው ውሸት ነው ማለት የሚያኗኑር አይደለም፡፡  ህዝቡ ተረኝነትን በት.ሕ.ነ.ግ ሥርዓት ለ 27 አመታት በደንብ አይቶታል፣ ኖሮበታል፣ ተበድሎበታል፣ ተሰቃይቶበታል፣ የበይ ተመልካች ሆኖ ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ልጆቹንና የራሱን ሕይወት ሰውቶበታል፡፡  ይህን ሕመም ከሀ አስከ ፐ ከት.ሕ.ነ.ግ የፅንፍ መፅሃፍ ቀድታችሁ በእብሪትና በጉልበት ስትግቱት ተረኝነት ሳይሆን ወተት ነው የምናጠጣህ በማለት ለማታለል መሞከራችሁ የናንተን ዝቅጠት ገደብ አልባነት ከመመስከር ሌላ ምንም አያመጣላችሁ፡፡  ቀኑ ሲደርስ የሚገባችሁን ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል ሕዝብ አየፈጠራችሁ እንደሆነ ቢገባችሁ ጥሩ ነበር፡፡  ሆኖም ለ27 ረጅም ዓመታት ያየውን የውድቀት ጎዳና በቀጥታ በመቅዳት እንደገና ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለመጫን ከሚሞከር ቡድን ብዙ መጠበቅ ራስን ማታለል ይሆናል፡፡

በድህነት የሚማቅቁ፣ ኑሮ ያጎሳቆላቸው ሰላማዊ ድሃ ዜጎች በማንነታቸው እንደዋዛ ማንም በዘረኝነት የተለከፈ ጊዜ የሰጠው ጉልበተኛ እየተነሳ ሲያፈናቅላቸው፣ ሲጉላሉና ሲገደሉ መፈናቀላቸውና መገደላቸው ማሳዘኑና ይህ አይነት ሁኔታ እንዳይደገም መፍትሄማፈላለግ ቀርቶ ከኛም ወገን ሰዎች ሞተዋል፣ ተፈናቅለዋል እየተባለ ሞትን ውድድር ለማስመሰልና የችግሩን አሳሳቢነት ለማጣጣል ሲሞከር አየታዘብን ነው፡፡  ሌላው ቀርቶ የህሊና ፀሎት ይደረግላቸው ሲባል ከሰው ልጅ አሰቃቂ ሞት በላይ ሁኔታው ሊኖረው የሚችለው ፖለቲካዊ እንድምታ የሚያሳስበው ሥራ አስፈፃሚና ሕግ አውጪ አካል ገና አምስት ዓመት ሳይሞላው የቱን ያህል በእብሪትና በንቀት የተሞላ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

በኦሮሚያና በቤኒ ሻንጉል (በሌሎችም ክልሎች) እየተፈናቀሉና እየሞቱ ያሉ ዜጎች (በብዛት አማራዎች) ግፉ፣ መፈናቀሉናግድያው የሚደርስባቸው ዘራቸው ተመርጦ፣ መጤ ናቸሁ፣ ተብለው መሆኑ በሌሎች ሳይሆን በራሳቸው በገዳዮቹ ተመስክሯል፡፡  በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከተጠቂዎቹ ጋር በጋብቻ፣ በሥራ ወይንም በሰው ልጅነታቸው በቅን መንፈስ የተሳሰሩ የአካባቢው ሰዎች መጠቃታቸው ግልጽና የሚጠበቅ ነው፡፡ ከነዚህ ሰዎች ጋር ባይተባበሩ ግን ለጥቃት እንደማይጋለጡ እየታወቀ የእኛም ሰዎች ተጠቅተዋል እየተባለ የነገሩን አሳሳቢነት ለማድበስበስና የብሄር ተዋፅኦውን ለማመጣጠን መሞከር አላማው ምንድነው ብለው ዜጎች በመጠየቃችው ተገቢው መልስ ሊሰጣቸው ይገባል እንጂ ለምን ጠየቃችሁን ተብለው የሚብጠለጠሉበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ እንዲህ አይነቱ ጥያቄ የዜግነት መብት መሆኑን ምነው ዘነጋችሁት?  ት.ሕ.ነ.ግን ከሥልጣን ያባረረው ተመሳሳይ እብሪት መሆኑ ይገባችሁ ይሆን ወይንስ እውነታውን ለማየት የሥልጣን ስካርና ዘረኝነት ህሊናችሁን ጋርዶታል?

በመጀመሪያ ነገሩን (ግድያውንና ማፈናቀሉን) በማጣጣል ጥቃቱ የደረሰበትን የሕብረተሰብ ክፍል እልህ ውስጥ ማስገባት እንደሚፈለግ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡  ይህ ለምን ይጠቅማል ብለን ብንጠይቅ መልሱ፣ ይህ ጥቃት የሚደርስበት የህብረተሰብ ክፍል በተለይም አማራው ኢትዮጵያዊነትን ከላዩ ላይ አውልቆ በአማራነቱ እንዲከርና ራሱን ከኢትዮጵያዊነትና ከአገራዊ አንድነት ፍላጎቱ እንዲያርቅ ይፈለጋል፡፡  ይህ የሚፈለገው ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ ብሄሮችን ለማግነንና አገርን አፍርሶ፣ ገነጣጥሎና አሳንሶ የራስን ጥቃቅን መንግሥታት ለመፍጠር ነው፡፡

አማራው ላይ ተደጋጋሚና አሰቃቂ ጥቃት በመፈፀም ያለውን አገራዊ አቋም አስትቶ ወደ ራሱ ዘውግ መብት አስከባሪነት አንዲሸጎጥ የሚገፋው ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀምበትና በደል ሲሰማው ነው ተብሎ ይታመናል፡፡  በዚህም ጥቃት የተነሳ እኛና አነሱ በማለት ክፍፍል ይፈጠራል፡፡ ይህ ሁኔታ ለጎሰኞች ነፃ አገር ለመመስረት ለምናራምደው አላማ ከፍተኛ መሰናክል ይሆንብናል ብለው ያሰቡት የሕብረተሰብ ክፍል ማግለያ መሳሪያ ይሆናል፡፡  የሚፈጠረው ልዩነትም እየከረረ የመለያየት አጀንዳን በሁሉም ወገን እንዲቀነቀን ለማድረግ ይረዳል፡፡  በመጨረሻም ክፍፍሉ እየከረረ ሄዶ የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡  ይህም ሁኔታ እንደገና አብሮ ለመኖር ወደማያስችል መቃቃር እንዲሸጋገር ሁኔታዎችን ይገፋል፡፡ በዚህም የተነሳ ተለያይተን የየራሳችንን አገር እንመስርት ወደሚለው መደምደሚያ እንዲደረስ ምክንያት ይሆናል፡፡  በሕዝብ መካከል ልዩነትን ፈጥሮ የራሱን ነፃ አገር ለመመስረት እንደ ት.ሕ.ነ.ግ አሁንም የተደበቀ አጀንዳ ይዞ ለመጣው ተረኛ ጎራ ይህን ልዩነት በተቻለ መንገድ ማስፋት የታለመውን የቁርስራሽ አገሮች ምስረታ ያፋጥነዋል፡፡

ይህ ፅንፈኛ እቅድ ወረቀት ላይ ሲነበብ በቀላሉ ሊሳካ የሚችል ቢመስልም መሬት ላይ ሲወርድ ግን ሊኖረው የሚችለውን ውስብስብ ችግርና ትርምስ አቀንቃኞቹ ማጤን የቻሉ አይመስሉም፡፡   እነሱ ጊዜ በሰጣቸው ጉልበት ተማምነው ሊያፍኑት የሚጥሩት ድምፅ ባልጠበቁት መንገድ እቅዳቸውን ሊያወሳስብባቸው እንደሚችል ቢገነዘቡ ከውድቀት ሊድኑ ይችሉ ነበር፡፡  ጎሰኝነቱ፣ ግትርነቱና ቂመኛነቱ ግን መልካሙን መንገድና የፍቅርን/የወንድማማችነትን/የእህትማማችነትን ውበት ሊያሳያቸው ባለመቻሉ እየተደናበሩ አገሪቱንም በማይሆን ሁኔታ እያደናበሯት ይገኛሉ፡፡

የትግራይን ትርምስ በሚመለከት የት.ሕ.ነ.ግ መሰሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጦርነቱ የተካሄደበት ሁኔታ፣ ከክልሉ የተወጣበት መንገድና የት.ሕ.ነ.ግ ጦር አዲስ አበባ ለመድረስ ትንሽ አስኪቀረው ድረስ የገሰገሰበት ሁኔታ ብዙ አጠያያቂ ሁኔታዎች ያሉበትና ምስጢሩ አስካሁን ያልተገለጠበት ሁኔታ አገራችን በአሳሳቢ ጎዳና እየሄደች እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡  መሪዎቻችን አትጠይቁን እኛ እናውቅላችኋለን እያሉን ብዙ መስዋእትነት ከፈልን፣ አሁንም እየከፈልን ነው፡፡  ሁኔታው ግን አሁንም አልተቋጨም፡፡  አነጋጋሪ፣ ከፋፋይና ለጥቃት የሚያጋልጡ ውሳኔዎች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ተቋሞች እንዲጠነክሩና የዲሞክራሲ አሰተሳሰብም አየሰረፀ እንዲሄድ በማድረግ ፋንታ ውሳኔዎች በግብታዊነት፣ በማን አለብኝነትና በእኔ አውቅልሃለሁ ባይነት ሲካሄዱ ስናይ የምንሄድበት መንገድ የዲሞክራሲ ነው ወይስ ፀረ-ዲሞክራሲ ነው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡  አገርን በጠላትነት የቦጠቦጡ፣ ያዋረዱ፣ የገደሉና ተስፋ ያሳጡ ግለሰቦች ያለምንም የፍርድ ሂደት ለሰላም ስንል ፈተናል ማለት ትልቅ ክህደት፣ ኢዲሞክራሲያዊና ኢፍትሃዊ አካሄድ መሆኑንና ሕዝብን ግራ እንዳጋባ መሪ ነን ባዮቹን የተረዱት አይመስሉም ወይንም ሕዝቡን በሚያስተዛዝብ ሁኔታ ንቀውታል፡፡  ዶሮ ሰርቀሃል ተብሎ ለረጅም ጊዜ ለእስር የሚዳረግ ዜጋ ከእነኝህ ሰዎች የባሰ ምን መጥፎ ነገር ስለሠራ ነው እርሱ ለእስር ሲዳረግ እነሱ የሚፈቱት?

በየጊዜው አየተፈራረቀ በድህነት እንዲማቅቅ የሚገፋው የጨቋኞች ሥርአት ኑሮውን ስላተራመሰበትና ስላስራበው ሰርቆ ሕይወቱን ለማቆየት የጣረ ሰው ወንጀለኛ፣ ሆነ ብለው አቅደውና ከጠላት ጋር ተመሳጥረው አገር ለማጥፋትና ሕዝብን እርስ በእርስ ለማፋጨት ቀን ከሌት በምቀኝነትና በዝቅተኝነት ስሜት አየተነዱ አገር የዘረፉ ወንበዴዎች ነፃ የሚሆኑበትን ምክንያትስ በምን አይነት ሁኔታ ፍትሃዊነቱን አሳማኝ ማድረግ ይቻላል? ለአገር ሲባል ድሃው ሕዝብ እሰካሁን የከፈለው አሰቃቂ መስዋእትነት አልበቃ ብሎ መሰሪዎች እንደመዥገር ደሙን ሲመጡት ወንጀላቸውን ችላ ማለት አዳዲሶቹን ተረኞች በምታዩት መንገድ ደም መምጠጡን ቀጥሉበት ማለት አይሆንም? የፍርድ ሂደቱ እንዲፋጠን ተደርጎ ለጥፋታቸው የሚገባው ፍርድ እንዲሰጥበት ያልተፈለገበትስ ምክንያት ምንድነው?  ይሄ አካሄድ የአገሪቱን የፍትሕ መዋቅር አላዋረደም ወይ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ምን እያስተማሩን ነው?

በእኔ እምነት እነዚህ ሰዎች ክሳቸው ሳይቋረጥ ወንጀላቸው ፍርድ ሊሰጥበት ይገባ ነበር፡፡  የፍርዱን ሂደት አጠናቆ ለሰላም ስንል ምሕረት አድርገናል ማለት ይቻል ነበር፡፡  ፍትሕም፣ አቅም፣ ጉልበትና ደጋፊ ወገን ያላቸው እንደፈለጉ የሚያዳፍኗት፣ አቅም የሌላቸው ምስኪን ድሆች ደግሞ በትንሽ ስህተት የሚማቅቁባት፣ ሚዛኗ የተዛባ የተረኞችና የፅንፈኞች መጫወቻ አትሆንም ነበር፡፡  ታዲያ ይህን ስናይ በዚህ ሥርዐት ውሰጥ ከሰዎቹ በቀር ምኑ ነው የተቀየረው ብለን ብንጠይቅ ይፈረድብናል?  ያሁኖቹስ ባለስልጣኖች ቢሰርቁ ቢዘርፉ ሃላፊነታቸውን ቢያጓድሉ ምን ይፈረድባቸዋል? መስረቅ አዋራጅ መሆኑ ቀርቶ ሲያስከብርና ሲያስፈራ እያዩ የማይሰርቁበት ምክንያትስ ምን ሊሆን ይችላል?

ዲሞክራሲያዊ ተቋሞችን በመገንባት ፋንታና የሀገሪቱ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ በሥርአት እንዲመራ የሚያስችሉ የአስተዳደር፣ የፍትህና የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር ፋንታ ተቋሞች ባጠቃላይ በግብታዊነትና በሹማምንት የግል ፍላጎትና የእብሪት አካሄድ የሚነዱበት ምክንያትስ ምንድነው?

ፊውዳሊዝም በድሎኝ ነበር፣ ወታደራዊ አገዛዝ መብቴን አላከበረልኝም፣ የት.ሕ.ነ.ግ ሥርዓት እውነተኛውን እኩልነት አላመጣልኝም እያለ የሚናጥ ጎራ ተጨባጭ የተቋም ግንባታ ሂደት ላይ ቸልተኝነት ያበዛው በሕግ መገዛትን ስለማይፈልግና የተደበቀ አጀንዳ ስላለው እንደሆነ ብንጠረጥር ይፈረድብናል?  ለራሱ አላማ እንዲመቸው ሕግን፣ አስተዳደርን፣ ማሕበራዊ ትስስርን ወዘተ. የሚያቀጭጩና የሚያዋርዱ ውሳኔዎች ያለገደብ ከማስተላለፍና በጉልበት ከመጫን ሌላ ምን ተስፋ የሚሰጥና ሰላምን የሚያሰፍን ሥራ ተሠራ? አገሪቱ አሁን ባለው ሁኔታ በግለሰቦችና በስውር ቡድኖች ፍላጎት ላይ በተመረኮዙና በጉልበት የሚጫኑ ውሳኔዎች አይደለም እንዴ የምትንቀሳቀሰው?

ሚዛናዊ ለመሆን፣ በርካታ ተጨባጭ ሥራዎች አልተሠሩም ለማለት እንዳልሆነ ግልፅ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡  የተሠሩት ሥራዎችና የተከናወኑ ገንቢ እንቅስቃሴዎች ግን በቅን አስተዳደርና በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አስተዳደርና በህግ በሚመሩ ጠንካራ ተቋሞች ካልተደገፉ ለሕዝብ የሚሰጡት ጥቅም ውሱን እንደሚሆንና አገሪቱን ለከፋ ችግር ሊዳርጉ እንደሚችሉ ባይዘነጋ ጥሩ ነው፡፡  ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውና በምንም አይነት ሁኔታ ችላ ሊባል የማይገባው የዜጎች በሰላም የመኖር፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት ነው፡፡  መንግሥትም ይህንን መብት ከምንም ነገር በፊት በቅድሚያ የማስጠበቅ ሃላፊነትም ግዴታም አለበት፡፡  የልማት ሥራዎችን በጎንዮሽ ማካሄድ አያስወቅስም፡፡  የዜጎችን ደህንነት ችላ እያሉ የተወሰኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ ብቻ አገር አስተዳድራለሁ ማለት ግን ከማስወቀስም አልፎ በአስተዳደር ቸልተኝነት ወንጀል ያስጠይቃል፡፡

አትተቹኝ/አትተቹን ባይነት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በቅርቡ የሚታዩት ያልተጠበቁ ጠባዮች የእልህና ለምን ተደፈርኩ/ተደፈርን አይነት ይዘት ያላቸው ምላሾችና ወቀሳዎች በሳቸው ደረጃ ለሚገኝ ሰው የሚመጥኑ አይደሉም፡፡  እውነተኛ ዲሞክራሲን ለመገንባት ትችት አስፈላጊ መሆኑን ባይዘነጉት ጥሩ ነው፡፡  ሥነ ሥርዐትን በጠበቀ ሁኔታ የሚሰነዘር ትችት ላወቀበት በገፍ ከሚዥጎደጎድ የአድር ባይነት፣ እሺ-እሺ ባይነትና አጎብዳጅነት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ብልህነት አለመሳሳት ሳይሆን ስህተትን አምኖ ችግሩን ለማሰተካከል ሊኖር የሚችለውን የግል ጥንካሬ መጠቀም ነው፡፡

እንደምናየው ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አጠገብ ያሉ ሰዎችም አበሻ ቆንጠጥ ካላደረጉት አይቻልምና ኮምጨጭ በሉ የሚል ምክር የለገሷቸው ይመስላል፡፡ ሲጀምሩ ያሳዩት ቅንነት፣ ታጋሽነት፣ ተግባቢነትና አርቆ አስተዋይነት ጥሏቸው ከጠፋ ከረመ፡፡  ጫና ስለበዛባቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡  ሆኖም የተሸከሙት ሃላፊነት፣ የገቡት ቃልና ያለባቸው በአርኣያነት የመታየት የስልጣን ግዴታ አደብ እንዲገዙ ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡  ትችት ሊያጠነክር ይገባል እንጂ አልህ ውስጥ ሊያስገባ አይገባውም፡፡  ለትችት ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንጂ ሌሎችን ማሸማቀቅ፣ ማንጓጠጥ፣ ማስፈራራትና ማናናቅ ዲሞክራሲን እገነባለሁ ከሚል መሪ አይጠበቅም፡፡

አጠገባቸው የተሰገሰጉት ደግሞ ተረኝነት እየተባለ ለምን እንወቀሳለን እያሉ ነው፡፡ ለምን ወቀሳችሁን ብለው ከመርገፍገፍ ለምን ለተባለው ነገርና ለሚጠየቀው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አይሰጡም?  በእውነት በት.ህሕ.ነ.ግ መንገድ አየተሄደ አይደለም? አይንን በጨው አጥቦ የምታዩትን አላያችሁም ማለት ት.ሕ.ነ.ግን የት እንዳደረሳት ከናንተ ወዲያ ማን ጥሩ ምስክር ሊሆን ይችላል?

ከላይ እንደጠቀስኩት መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጋችሁ ፅንፈኞች ትርምስ እንዲፈጠር እንደምትፈልጉ ግልፅ ነው፡  ሕዝብ አባልተን የምናልማትን ኦሮሚያ እንገንባ ብላችሁ የማትፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ አያየነው ነው፡፡  ለእናንተ ባይታያችሁም ሁሉም የአምላክ ፍጡር ነው፡፡  ለስቃይ የምትዳርጉት ነፍስ፣ ፈቅዳችሁ ወይንም ችላ ብላችሁ የምታስጠፉት ሕይወት፣ ሕይወታቸውን እስኪጠሉ ድረስ የምታስለቅሷቸው ዜጋዎች አልገባችሁም እንጂ በተለያየ መንገድ ወንድሞቻችሁ/እህቶቻችሁ/አባቶቻችሁ እናቶቻችሁና  ልጆቻችሁ ናቸው፡፡  ምድሪቱም ነገ ለቃችሁ ለተተኪው ትውልድ የምታስረክቧት በመሆኗ የሁላችንም ናት፡፡  ወንድም ከወንድሙ አባልታችሁ የምትመሠርቱት አገር የሚኖር ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡  መብቱ እንዲከበር የሚጠይቅ ግለሰብ የሌሎችን መብት መዳፈር አያዋጣውም፡፡  አብሮ ተግባብቶ ተሳስቦ መኖር ለሁሉም ይጠቅማል፡፡

የአገራችን ልሂቃን ግልፅና ቅን ሆኖ መነጋገር ስለማይደፍሩ፣ መሰሪነት፣ አስመሳይነት፣ ምቀኝነትና እብሪት ሰለወጠሯቸው ነገሮች ከጊዜ ጊዜ እየተወሳሰቡ እዚህ ደርሰናል፡፡ ለዚህ  ሁሉ  ተጠያቂዎች የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ ልሂቃን ቢሆኑም ሁኔታው ወደ እማይሆን አቅጣጫ ሲያዘግም እያዩ ዝምታን የመረጡት ሌሎች ልሂቃንም ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ሁኔታውን ብናድበሰብሰው የትም አንደርስም፡፡  በግልፅ እንነጋገርና ችግራችንን እንፍታ፡፡ መሠሪነት ለማንም ሲጠቅም አላየንም፡፡

ማሳሰቢያ ለተቺዎች

በሁለቱም አቅጣጫ ለምን ከላይ ያለው ትችት ተሰነዘረ ወይንም በቂ አይደለም ብላቸሁ በእልህና በጥላቻ ለምትገፉ ሰዎች፡፡ ሚዛናዊነትን፣  እውነትን፣  ቅንነትን  ብታራምዱ ራሳችሁንም ወገኖቻችሁንም አገራችሁንም ከአስከፊ ሁኔታ ማራቅ  የምትችሉ ይመስለኛል፡፡  

ግለሰቡን ወይንም ድርጅቱን እኔ ስለምወደው ፣ የእኔ ወገን ስለሆነ ወይንም ለኔ ስለተመቸኝ አይተችም ወይንም የሚሰራው ሁሉ እንከን አይወጣለትም ካላችሁ  የግለሰቡን/ድርጅቱን  ውድቀት የምታፋጥኑት እናንተ ናችሁ፡፡  ‹‹ከሰው ስህተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋምና!››  ለጥሩው ማበረታቻ እየሰጣችሁ፣ ለጉድለቱ ደግሞ ማሰተካከያ እየለገሳችሁ ሂዱ እንጂ ጭፍን አምልኮት ለናንተም፣ ለወገኖቻችሁም ለአገርም አይጠቅምም፡፡  

በጥላቻ ጎራ ያላችሁትም የሚሠራውን ሁሉ በክፉ አይን እያያችሁ በቅናትና በጥላቻ መንፈስ ለማውደምና ለማባላት ጊዜያችሁን ከምታባክኑ፣ጥሩውን እያበረታታችሁ መጥፎውን ደግሞ በቅን መንፈስ እየነቀፋችሁ ብትሄዱ ለሁሉም የምትሆን አገር መገንባት ይቻላል፡፡  ቂም በቀልና ጥላቻ የትም አያደርስ፡፡  ይልቅ እርስ በርስ አየተባላችሁ አገራችሁን በባእዳን ከምታስመዘብሩ ተባብራችሁ መንግሥታችሁን በበጎው መንገድ እንዲሄድ እያበረታታችሁም ሆነ እየወቀሳችሁ ብታጠነክሩ ለሁሉም ሕዝብ የሚተርፍ ሃብት ያላት አገር በመሆኗ ሁሉም ተመችቶት የሚኖርባት አገር በህብረት መፍጠር ትችላላችሁና አትስገብበገቡ፣ አትጥሉ፣ ወገንተኛና ዘረኛ አትሁኑ፣ የሌላውን ውድመት አትመኙ፡፡

 

 

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share