ጨው ለራስህ ስትል አትጣፍጥ! – በላይነህ አባተ

ጨው ሆይ!

ድልህ አዋዜን ባሳማርክ፣ ቀይ አልጫውን ባጣፈጥክ፣
በጥርስ መንጋጋ ታኝከህ፣ በምላስ ጪልፋ ተላውሰህ፣
በማንቁርት ክርን ተገፍተህ፣ የጉረሮን ቦይ ተሻግረህ፣
በከርስ ወፍጮ ተፈጨህ፣ በእባብ አንጀትም ተበላህ፡፡

ምግቡን በአሻቦ ጣዕም አርገህ፣ ውሀንም በአንካር አጣፍጠህ፣
የተራበውን በመገብክ፣ የተጠማውን ባጠጣህ፣
የኮሰመነ ባፋፋህ፣ የመነመነ ባወፈርክ፣
ደም ግፊት አምጪ እያሉ፣ ይሉኝታ ቢሶች ኮነኑህ፡፡

ሙያ የለሹን ሰው ባረክ፣ የመብል ጣዕምን ባስተማርክ፣
ውሻ እማይነካውን ምግብ፣ ጣት አስቆርጣሚ ባደረክ፣
ሕዝብን ተንሰሳ በለየህ፣ ተሳር ጋጪነት ባወጣህ፣
እጅህ እንደ አማራ ሕዝብ፣ አመድ የሚያፍስ ሆኖብህ፣
“ለራስህ ስትል ጣፋጭ ሁን፣ አለዚያ ድንጋይ ነህ” አሉህ፡፡

እንግዲህ ተልድምህ ተማር፣ መጣፈጥ መጣም ይቅርብህ፣
ዓለም ከንቱ እንደሆነች፣ እናት ደግ እንደማትወድ ይግባህ፡፡

በልተው እንዳያጠፉህ፣ ጠጥተው እንዳይጨርሱህ፣
አትብሉኝ አትጠጡኝ በል፣ እንደ እንቆቆ እሬት አምርረህ፡፡

እንኳንስ ተእሬት ተእንቆቆ፣ ተአሸዋ ድንጋይም ተማር፣
ሲፈጩህ ወፍጮውን አንክት፣ ሲያኝኩህ ጥርስንም ስበር፡፡

ሲውጡህ እነቅ ጉርንቦን፣ ወርደህም ከርስ ሆድን ተርትር፣
በደም ተሻግረህ ኩላሊት ቀትል፣ ጣራ እስቲነካ ደም ግፊት ጨምር፣
ልብ ሥራ በዝቶባት እስክትደክም፣ በመጨረሻም ሲው እስክትል፡፡

ጨው ሆይ እባክህ ንቃ፣ የሳመ መስሎ ሱሳም አይላስህ፣
መላእክት ተእግር ብረት ውስጥ፣ ሳጥናኤል ተዙፋኑ ላይ ይታይህ፣
ሰባራው ሚዛን አይጣልህ፣ ዓለም ፍርደ ገምድሏ አታጥፋህ፡፡

ምድሪቱ ለሥጋ ለአካል ላትበጅህ፣ ሰማዩም ለፀድቅ ለምቾት ላይሆንህ፣
አንተ ተምድር ስጠፋ፣ እንደ ወንጅ ስኳር ተልሰህ፣
ህሊና ይሉኝታ ቢሱን፣ ጨው ላሹን ማፋፋት ይብቃህ፡፡

እነ ማተብ የለሾች፣ በልተው ጠጥተው የሚያሙህ፣
ገንፎ ጨምረው ሊበሉህ፣ ለከብቶቻቸው ሊያጠጡህ፣
በባልጩት ብትር ሰባብረው፣ አራት አንካሮች ሊያደርጉህ፣
እንደ ውቃቢ ሲጠጉህ፣ እንደ እርኩስ መንፈስ ሊወሩህ፣
እንደ ቀጋ እሾህ ተዋጋ፣ ዝናሮችህን አጥብቀህ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአቢይ ኑዛዜ!!! - በአየለ ታደሰ

በጅል በከብቱ ተጎርሰህ፣ በሽግናሞችም ታኝከህ ተመዋጥ፣
በፈርሳም ጨጓራ ተፈጭተህ፣ ተአንጀት ቱቦ ውስጥ ተመስመጥ፣
ሲመክሩህ ስማ ድፍን ጨው፣ ለራስህ ስትል አትጣፍጥ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መስከረም ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share