“ በስመአብ ! በስመአብ! … በ3000 ብር በዲግሪ የተመረቀ ተማሪን መቅጠር ? ማለት ምን ማለት ነው ?” አማተቡ አንጋፋው ኢኮኖሚሥት ፣ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ። በሸገር 102 ኤፍ ኤም ቢዝነስ ዜና ላይ ፣በወቅቱ የኑሮ ውድነት ጉዳይ አሥተያየት እንዲሰጡ በአዘጋጁ የዲግሪ ምሩቅ ደሞዝ በአንዳንድ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች 3000 በመሆኑ በዚህ ኑሮ ውድነት እንዴት ኑሮን መግፋት ይችላል ? በማለት ሲጠየቁ ። መልሳቸውን በመገረም ድምፀት ቀጠሉ ። ” … መኖሪያ ቦታ እንዴት ያገኛል ? …በ3000 ብር …ምን አላት 3000 ብር ? …ገበያ ወጥተኽስ ምን ትገዛለች ? … በቢዝነሱ ዓለም በእኔ ሴክተር የጠቀስከውን እጥፍ ብር ነው የሚከፈለው ፣ ለዲግሪ ተመራቂ ። ( በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ። ) …” አሉ ። የ3000 ብር ደሞዝተኛ ባለ ዲግሪ በኢትዮጵያ መኖሩን ያለማወቃቸው አያሥገርምም።
የሸገሩ 102 ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ያነሳው ጉዳይ ግን ወቅታዊ እና በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው ። የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለዲግሪ ተመራቂ በዜሮ ዓመት ልምድ ሲቀጥሩ ከአራት ሺ ከፍ አይሉም ። አራት ሺ ምናምን ላይ ይቆማሉ ። በየመሥሪያ ቤቱ እና በየኢንዱስትሪ ፖርኩም ያለው ክፋያ ለዲግሪ ምሩቃን 6000 አይሞላም ። ( የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአንፃራዊነት ቢሻልም ፣ 2000 ብር ተከፋይ የለም ማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ ከሚያመርቱት ምርት ፋይዳ አንፃር ፋብሪካዎቻቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመገንባት የበለጠ ምርታማ በማድረግ የሠራተኞችን ደሞዝ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል ።)
ወዳጄ እርግጥ የኑሮ ውድነቱ በራሱ በሥመአብ ! ብለህ እንድታማትብ ያሥገድድሃል ። ለምን ብትል በየቀኑ የምትሰማው የምግብ ሸቀጦች ላይ እና እህሎች ላይ ጭማሬ ነውና ! ያውም የተጋነነ ። እና በ3000 ብር ደሞዝ አዲስ አበባ ውስጥ ቤት ከሌለህ ተቀጥረህ ለመሥራት እንዴት ትችላለህ ? የተሻለች ቅልብጭ ያለች አንድ አልጋ የምታዘረጋ ቤት ከ3000 ብር በታች አታገኝም ። ያውም በደላላ ጥረት ኮሚሽን ከፍለህ ነው ቤቷን የምታገኘው ። በዚህ ወጪ ላይ የምግብ ፣ የታክሲን ፣ የንፅህና መጠበቂያን ወጪ ጨምርበት ። ታዲየስ ? ይሄ “ በሥመ አብ ! “ አያሰኝም ትላለህ ?????
ለምሳሌ ያህል በዚህ ደሞዝ የመምህርንን ድካም በጥልቀት አሥበው እስቲ ? ቁልጭ ፣ ቁልጭ የሚሉ አሣዛኝ የነገ ተሥፋዎችን ዓይን ማየቱ በራሱ የህሊና ፈተና ውሥጥ የሚጥል ትውልድን የመቅረፅ ሥራ ነው የሚሰሩት ። እነዚህ ታደጊ ወጣቶች እና ወጣቶች ወደ ቀድሞ ፊደል ቆጠራህ ዞር ብለህ እንድትመለከት የሚያሥገድዱህ ናቸው ። እናም እነዚህን አሣዛኝ ፣ ልበ ንፁሆች ዕውቀት ለመመገብ ሣትሰለች ደጋግመህ ማሥረዳት ይጠበቅብሃል ። በዚህ የተነሳ ጉሮሮህ ይደርቃል ። ይኽንን ግን ማንም አይገነዘብልህም ። በዛ ላይ የጠመኔው ብናኝ ፣ ወይም የቀለሙ ሽታ አለ ። የግል ተምህርት ቤት ባለቤቶች ቢያንሥ ምሣና አንድ ሌትር ውሃ ቢችሉህ መልካም ነበር ፣ እንደ መንግሥት ትምህርት ቤት አይከፍሉህምና በዚህ ቢክሱህ ትወድ ነበር ። ሲያምርህ ይቀራል ። እናም የጠዋቱን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ጨርሰህ ምሣህን ከተማሪዎችህ እጅግ ያነሰ ዝቅተኛ ምግብ ( ዳቦ በሻይ ) ምሳህን በልተህ የከሰዓቱን ፔሬድ እንደምንም ትደመድማለህ ። ከዛም በእግርህ የቤትህን መንገድ ትያያዘዋለህ ። …
የደሞዝ አነሥተኝነት ፣ አሥተማሪውን እንዴት ምሥኪን እንዳደረገው አሥተዋልክ ? እንደርሱ ሁሉ ፣ በካምፕ የማይኖረውን ወታደር ፣ ፖሊስ፣ዳኛ እና ጠበቃ የሚከፈለው ደሞዝ ከወቅቱከመሠረታዊ ፍላጎት ወጪው ጋር ባለመሄዱ እጅግ እንደጎዳው አሥተውል ። የዚህ ህግ አሥከባሪ አካል መጎዳት ደግሞ እጅግ መጥፎ ሁኔታን ይከስታል ። … ። በዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት አልፈልግም ። ይሁን እንጂ በእነዚህ ተቋማት የሚሰሩ ዝቅተኛ ደሞዝ ብቻ የሚከፈላቸው ፣ ቤትና ጥቅማጥቅም የሌላቸውን በማሥተዋል የዋጋ ውድነቱን በመንተራስ፣ አሥቸኳይ የደሞዝ ማሥተካከያ ማድረግ አሥፈላጊ እንደሆነ መንግሥት የሚገነዘብ ይመሥለኛል ። …
እሺ ተራው ህዝብስ ምን ይሁን ? ዘይት ፣ በርበሬ፣ ስኳር ፣ዛሬ ደግሞ ሽንኩርት እና ቲማቲም እየናፈቀው ይኑር ? ከተሜው ፣ ሽሮ እየበጠበጠ በውድ ዋጋ እንጀራ እየገዛ በቀን አንድ ጊዜ እየተመገበ አንጀቱ እያረረ ወደ ፈጣሪው ያንጋጥ ? በገጠር ከተሞች አካባቢ ደግሞ ከዚህ የባሰ ጎሥቋላ ኑሮ አለ ና የበቆሎ ቆሎ ቆርጥሞ እሥከመቼ ይኖራል ? …ወደ ጎደናስ ልጆቹ እሥከመቼ ይወጣሉ ?
ይህን እውነት ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካላወቃችሁ እወቁ ። የምትበሉትን በምግብ ጠረጴዛችሁ ላይ የተቆለለውን ቡፌ ከእሱ አንድ እፍኝ የበቆሎ ቆሎ ጋር እሥቲ ለአፍታ አሥተያዩ ? በዕዝን ልቦናችሁ ሥትመለከቱ ምን ተሰማችሁ ? … የምትመገቡትን ምግብ ትታቸው ፣ ወደ ውጪ በመውጣት ሥውር ቦታ ፈልጋችሁ አለቀሳችሁ ? ወይስ “ የ40 ቀን እድሉ ነው :: ” በማለት ተሳለቃችሁበት ? …
ይኽ የ40 ቀን ዕድል ጉዳይ አይደለም ። የተቀበላችሁት የማሥተዳደር ጉዳይ እንጂ ! በዚህ ደሃ ህዝብ ሥም ነው ከፍታ ላይ የተገኛችሁት ። ቢያንስ ለራሳችሁ ፡፡ … ልታሥቡለት ፣ ህይወቱ እንዲቀየር ልትረዱት የሚገባው ነበረ ይኽ ምስኪን ሆኖም አስተዋይ በለአገር ። ዜጋን የማገልገል ግዴታችሁ ነው ።
በእውነቱ ይኽንን ግዴታውን የሚያውቅ ሹመኛ የበዛ ቢሆን ኖሮ ፣ ይኽቺ አገር በአጭር ጊዜ ሀብታም ትሆን ነበር ። ( ሰማህ እዛ ማዶ ያለኸው ? ጭቁንን ፣ ደሃውን ፣ ባለአገሩን እየገደልክና እየዘረፍክ እንዴት ለህዝብ ቋሜያለሁ ፤ በማለት አፍህን ሞልተህ ትናገራለህ ? በባርነት ያልኖረውን የትግራይ ህዝብ አንተ በሐሰት ትርክት ከማነው ነፃ የምታወጣው ? ) ህዝብን አገለግላለው የሚል ሁሉ ህዝብን በተጨባጭ ካላገለገለ እና ሥልጣንን መክበሪያና መንደላቀቅያ ካደረገ አጠቃላይ ህዝቡን መጥቀም እንዴት ይቻለዋል ?????????
የትም ክልል ብትሄዱ ያለው ችግር ይኽ እኮ ነው ። “ በሥልጣን መገልገል እንጂ ማገልገል የለም ። “ ባመዛኙ ። ከቀበሌ ጀምሮ በየምክንያቱ ፣ በሰበብ አሥባቡ ፣ በመታወቂያ ሽያጭ ሣይቀር ኪሱን የሚያሣብጥ ባለሥልጣንን ነው የምታስተውሉት ።
ዛሬም ሥልጣን የባለሥልጣናት መበልፀጊያ ሆኗል ። የሰፊው ህዝብ መበልፀጊያ “ ፀረ _ ሌብነት ፖሊስ “ የብልፅግና ፖርታ መቼ ይሆን የሚያወጣው ? ይኽ ቆራጥ የሆነ እርምጃን የያዘ የፀረ ሌብነት ፖሊስ በአሥቸኳይ ወጥቶ ካልተተገበረ በስተቀር የኑሮ ውድነቱ እጅግ እየባሰ ይሄዳል ። ሌቦቹ አንድ ኪሎ ሥጋ 2000 ቢገባ ጉዳያቸው አይደለም ። የሥርቆት ብር ሥላላቸው ለምን ለነሱ ሲል 5000 አይገባም ? ሥለ ጥራጥሬ እና አትክልት ውድነትም መስሚያ ጊዜ የላቸውም ። እነሱ ሁሌም በፊሽታ እና ሀብት በማከማቸት ተጠምደዋልና …
ደሞዝተኛው ግን ኑሮ ክበበው ገዳ ከዓመታት በፊት እንደ ቀለደው ቀልድ ሆኖበታል ።
ክበበው በበላተኛው ብዛት ሥለጠፋው በሬ ነበር የቀለደው ።
” …ወደፊት ለልጆቻችን ስናወራ ፤ አንድ በሬ የሚባል እንስሳ ነበረ ፤ እርሱን ተቃርጠን ሥጋውን በቢላዋ እየመተርን በማጥሚጣ እያጠቀስን እንዲህ እያደረግን እንበላ ነበር ። ” ብለን እናወራለን ። በማለት ። የሚገርመው በሬው ሳይጠፋ ፣ አሁን እና ዛሬ ፣ ትንቢቱ መፈፀሙ ነው ።ዛሬ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ብዙ አሥፈላጊ ዕለታዊ ምግቦች እጅግ ተወደውበት ፣ በአይኑ ከመመገብ በዘለለ መላ ቅዱሱ እንደጠፋበት ይታወቃል ።
ደሞዝተኛው ሁሉ ፤ ባንክን እና አየር መንገድን ሳይጨምር ፤ ደሞዙ እዛው ነው ። ጡረተኛው ደሞዙ በአንድ ብር ከፍ አላለም ። ። ገበያው ግን በየቀኑ እሳት እየሆነ ነው ። ከተሜው ትላንት እንደልብ የሚበለው ዳቦ በሻይ እንኳን በሥኳሩ ውድነት ሳቢያ ህልም ሆኖበታል ።
ይኽ እውነት ነው ። ተረት ተረት አይደለም ። መንግሥት ለሚያሥተዳድረው ህዝብ በመጨነቅ ፈጥኖ ካልደረሰ እና ገብያውን ለማረጋጋት ካልሰራ ፤ የኑሮ ውድነቱ የማይቀለበሥ አደጋ ያመጣል የሚል ሥጋት ይኽ ፀሐፊ አለው ።