(15/01/2015 ዓ.ም)
አቦይ ስብሃት ነጋን ለኢትዮጵያ ህዝብ አላስተዋውቅም፡፡የምን ምልክት እንደሆኑ ራሳችሁ መልሱት! በሌላው ብሔር ላይ የተፈጸመውን ለጊዜው እናቆየው፡፡በወያኔ ትግል ወቅት ወገኔ የሚሏቸውን ትግራዋይ ሰብስቦ በካምፕ ካጎረ በኋላ ምግብ ከልክሎ፤አጥንታቸው ብቻ ሲቀር ያንን በቪዲዮ ቀርጾ ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀምን ስብሃት ካልሆነ ማን ትዝ ሊለው ይችላል? እንታረቅ ብሎ ጠርቶ፤ በተኙበት መረሸንን ስብሃት ካልሆነ ማን ሊያስብ ይችላል? ግን አንድ ነገር ብቻ ላስታውስ፡፡ምናልባት የቀራቸው እንጥፍጣፊ ክፋ ምክር ካለ ተፈጥሮ ሳይቀድማቸው ያንን እንዲያስተላልፋ ምቹ ሁኔታን መፍጠር በሚመስል ሁናቴ ሲፈቱ የተፈጠረውን ስሜት እናስታውሳለን፡፡በወቅቱ በ No More ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርግ የከረመው ዲያስፖራ ስሜቱ ሳይቀዘቅዝ በተደረገለት የእናት ሃገር ጥሪ አገር ቤት የገባው ብዙ ነበር፡፡ግን የአቦይ ስብሃት መፈታት ውሃ ነበር የቸለሰበት፡፡ታዲያ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ ይህንን ማስተባበል ግድ ሆነባቸው፡፡ያሉትን ቃል በቃል አሁን ባላስታውስም ይዘቱን ግን አስታውሳለሁ፡፡ስድባቸውን ለፈጣሪ ልተወው! ያው እንደተለመደው እሳቸው አዛኝ፤ሩህሩህ በሌላ ወገን ለምን ተፈቱ ያልን ደግሞ ጨካኞች አንደሆንን አድርገው አቀረቡት፡፡አሁን “ጉድጓዳቸው የተማሰ፤ልጣቸው የተራሰ”፤ህመምና ዕድሜ የተጫናቸው አዛውንት ቢፈቱ ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው አሉን በተጠየቅ፡፡ እግረ-መንገዳችንን የነጻነት/የአርበኛ ወዳጅ የሆኑትን አዛውንቱን ኑሮም፤ዕድሜም የተጫናቸውን ጋዜጠኛ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በአሁኑ ሰዓት የት እንደሚገኙ በትይዩ አስታውሰን እንለፍ! ሁለተኛው ጠ/ሚ/ሩ ያነሱት ደግሞ ስለ ፍትህ የተናገሩት ነው፡፡ርዕሴ ያደረግሁት እሳቸው ስለተናገሩት ነው፡፡በወቅቱ ብዙወች ይቅርታና እርቅ ቢኖር እንኳን ፍትህና እውነት እንደ ደቡብ አፍሪካው ማለት ነው መጀመሪያ መረጋገጥ አለበት ባዮች ነበሩ፡፡የአገሪቱ ጠ/ሚ/ር ግን ስለ ምን ፍትህ ነው የምታወሩት? ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ አለ ወይ ብለውን አረፋት! በወቅቱ እርግማን ይሁን ምርቃት ያላወቅሁት ቃል ተጠቅመዋል፡፡ኡርቱፋ/ሁርቱፋ? በትክክል ማስታወሴን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡በእርግጥ ጠ/ሚ/ር ደ/ር አብይ አህመድ እኔ በተረደኋቸው መጠን ስለ Legal or Political Correctness ስለሚባለው ነገር ብዙ ተጨናቂ ሀነው አላያቸውም፡፡ከማስመሰል ይሸላል፡፡ ታዲያ አቦይ ስብሃትን ለመፍታት፤ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት ያልፈለገው መንግስት አርበኛ ዘመነ ካሴን ለማሳደድ ለምን እንቅልፍ አጣ? ነው ጥያቄው፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የልማትና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጥያቄወችን እናቆያቸው፡፡ህይወቱን፤ህልውናውን እንኳን ለአደጋ ስናጋልጥበት፤በመንግስት ላይ ህጋዊ ጥያቄ እንኳን የማያነሳውን ህዝብ ለምን ታነቃለህ ነው ወንጀሉ! ሌላው ትርፍ ነው፡፡
ከጦርነቱ በፊት ዘመነ የሚባል ስም አላውቅም፡፡ህወሃት እየገፋ ሲመጣ ያደረጋቸውን ንግግሮች ከዩ ቲዩብ አዳምጫለሁ፡፡ለብአዴን ያስተላለፈው መልክት፤ ከቻላችሁ ይህን ህዝብ ከጠላት ተከላከሉ፤ ካልቻላችሁ ደግሞ ራሳችንን አደራጅተን እንከላከላለን እንቅፋት አትሁኑን ነው ያለው፡፡ለአመታት በአማራ ህዝብ ላይ በተደረገው ክፋ ትርክት የአማራ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ለማስረዳት ሞክሯል፡፡መንግሰት ደመወዙን ከእኛ እየተከፈለው እኔም አልጠብቃችሁ፤ራሳችሁንም እንድትከላከሉ አልፈቅድም የሚል መንግስት በታሪክ ስለመኖሩ አልሰማሁምም፤አላነበብሁምም፡፡በሌላ አነጋገር ለምን ዝም ብላችሁ እንደ በግ አትታረዱም የሚል ነው፡፡በዕርግጥ ለምን በከፍተኛ የበቀል ስሜት ለመጣ ጠላት አሳልፎ እንደሰጠን ሰበቦችን ደርዳሪወች ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገር ቁስላችንን በእንጨት የሚወጉ አዘጋጅቶ ከሞት የተረፋትን ደግሞ ህሊናቸውን በመስበር ካሳ በመክፈል ላይ ይገኛል፡፡ይህንን የጻፍሁት በወለጋ አሁንም ወገን እያለቀ ባለበት ወቅት ነው፡፡መንግስት ሆይ ዘመነ የፖለቲከኛ እስረኛ ነው፡፡አመለካከትህን ለምን ገለጽህ ነው፡፡ስለሆነም ፍቱት እንላለን! ባይፈታም ጨው አይደለም አይሟሟም፡፡ህዝብን ለአደጋ ያጋለጡ ናቸው ህግ ካለ መጠየቅ ያለባቸው! ለመሆኑ የማንን ጎፈሬ እያበጠራችሁ ነው ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ፤በቁጥርም፤በሃብትም ጨርሶ ለንጽጽር የማይቀርብን ጠላት እንዲህ ያለ ግፍ እንዲፈጽም ዕድል የተሰጠው? ታሪክ የሚመልሰው ነው! መንግስቱ ሃ/ማርያም ሶማሊያን በ 3 ወር ውስጥ 3 መቶ ሺህ ጦር ታጠቅ አሰልጥኖ አዘጋጅቶ አገር አስከብሯል፡፡ግፍን ለምን ታገሳችሁ ነው?
ይቆየን!