እውነትን መወንጀል ዛሬ አልተጀመረም፣
ጥንት የነበረ ነው ሲፈጠር አዳምም፣
እግር አልባ ሳይሆን በእርግማን እባብም፡፡
እውነት የሚያሳድድ ከርሳም ስለበዛ፣
ለቅጣት ለትምህርት ጥፋት ውሀ መጣ፡፡
ጎርፉ ነጎድጓዱም ስላስተማረው፣
ከሀዲ ስግብግብ ምድሩን ስሞላው፣
ሰዶም ገሞራውን በእሳት አመደየው፡፡
በቃል በምልክት ሰው ስላልተማረ፣
በአካል ለማስተማር መለኮት ወረደ፡፡
መለኮት እውነትን መሆኑን የካዱ፣
ባንዳ ፈሪሳውያን ማርያምን የከዱ፣
ለሄድሮስ አቃጥረው ማሳደድ ጀመሩ፣
በሁለት ዓመቱ አንገት ሊያሳርዱ፡፡
ለኃጥአን የመጣ ደርሶ ለፃድቁ፣
በሄሮድስ ቢላዋ ሺዎቹ ታርዱ፡፡
በእናት ጀርባ ታዝሎ በርሃ ቢገባም፣
እውነትን ማሳደድ ባንዳው አላቆመም፡፡
የኦሪትን ሕጎች እያነበነቡ፣
አንዷንም በግብር ጭራሽ ሳያውሉ፣
ዘርፈው እየበሉ እያመነዘሩ፣
ሰው እያሳረዱ ሲቀጥፉ እየዋሉ፣
“የሙሴን ሕግ ጥሷል!” እያሉ ከሰሱ፡፡
ምስክር ዳኛዎች እራሳቸው ሆነው፣
ባንዳዎች ከሰሱት ወንጀልን ፈብርከው፡፡
ተከሳሽ ነፃ ነው ሲላቸው ገዣቸው፣
በጣም አስፈራሩት ባንዶች ዳግም ዋሽተው፣
“ንጉሥ ልሁን አለ” የሚልን አቃጥረው፡፡
ይህን ሁሉ ዋሽተው በሐሰት ክስ ከሰው፣
“ተደሙ ንጹሕ ነኝ!” ዳኛቸው ሲላቸው፣
ባንዶች ተሰብስበው ችሎትን አጣበው፣
አሉና ጮኹበት ስቀለው ስቀለው፡፡
እውነትን መለየት ዳኛውን ሲያቅተው፣
ሐዋርያው ከድቶ በመሳም ጠቆመው፡፡
ወንበዴዎች መሐል አጣብቆ ሲሰቅለው፣
አሁንም ባንዶቹ ተከትለው ሄደው፣
ሲሉ ተማጠኑ ሌቦቹን ፍታቸው፡፡
ተባንዶች ያበረው ፍርደ ገምድል ዳኛው፣
ሌባውን አውርዶ እውነትን ሰቀለው፡፡
ጥላም ስለሚፈራ ባንዳ በተፈጥሮው፣
ድንጋይ እረብርቦ እውነትን ቀበረው፡፡
ዳሩ እውነትና ጪስ ስለሚያገኝ መውጫ፣
ድንጋዩን ፈንቅሎ ሰማይ ምድርን ገዛ፡፡
በሐሰት ከሳሶች እውነት አሳዳቾች፣
ከአዳም እስከ ዛሬ የፈሉት ባንዳዎች፣
ለሆድ ለክርሳቸው ፍርድ አጣማሚዎች፣
በምድር ትቢያ ሆኑ አመድ በሰማይ ቤት፡፡
የዛሬ ባንዶች ሆይ እናንተም ግፍ ስሩ፣
እያሰደዳችሁ እውነትን ግደሉ፣
ሌባ እየፈታችሁ እውነትን ስቀሉ፣
እንደ ቀደምት ባንዶች ትቢያ እስክትሆኑ፡፡
ከይሁዳም አንስህ የማታውቅ ማፈር፣
ክህደት አሳፍሮህ አንገት የማትሰብር፣
በፀጸት ተጎድተህ ገመድ የማታስር፣
እንደ ፈሪሳውያን ተረግመህ እንድትኖር፣
ባንዳ ፋኖን እሰር እስክትሆን አፈር!
በላይነህ አባተ ([email protected])
መስከረም ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.