መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም
አማራው ብሎም ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ባለችበት በአሁኑ ሰዓት ይህን ህዝብን አስተባብሮ ጠላትን ድባቅ ሊመታ የሚችል መሪ ማሰር ትልቅ ስህተት ነው:: አርበኛ ዘመነ አገራችንን ለማፈራረስ ቆርጦ የመጣውን ጠላት ወደመጣበት አፍሮ እንዲመለስ ብዙ ዋጋ የከፈለ የአገር ባለውለታ መሆኑ እየታወቀ ለእስርና ለእንግልት መዳረጉ አማራ ክልልም ሆነ ኢትዮጵያ ህዝብን ማስተዳደርና መምራት በማይችሉ ስብስቦች እንደተያዙ አንድ ማሳያ ነው::
የተፈጠረውን አለመግባባት በሽምግልና እና በእርቅ ለመጨረስ ከመግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ ክህደት በመፈፀም ተሸምጋዩን ለእስር መዳረግ ኢሞራላውና ከፍተኛ ነውርም ከመሆኑም በላይ ይህ በሴራ የተከናወነ እስር ብዙ መዘዝ የሚያመጣ አደገኛ አካሄድ ነው:: ሽምግልና ለአማራ ህዝብ ሺህ አመታት ያስቆጠረ የተከበረ የግጭትና አለመግባባት መፍቻ እሴቱ መሆኑ እየታወቀ አገዛዙ በተንኮል አርበኛ ዘመነ ካሴን ማሰሩ ከህዝቡ እሴትና ባህል ጋር መላተሙ መሆኑን ይረዳው ይሆን? ወጣቱስ አገዛዙ በወሰደው የክህደት እርምጃ ተደናግጦ ከጀመረው ሁለንተናዊ የህልውና ትግል ያፈገፍጋል ብሎ ገምቶ ይሆን? በእኛ እምነት የአርበኛ ዘመነ ካሴ መታሰር የተደራጀውን ብቻ ሳይሆን ተዘናግቶ የነበረውን ማህበረሰብ ወጣት አዛውንት ሳይል ወደ ትግሉ እንዲቀላቀል አዲስ ተነሳሽነት ያመጣል ብለን በፅኑ እናምናለን:: መሆን ያለበትም ይኸው ነው:: አገዛዙ ቀይ መስመር ያለፈ በመሆኑ መላው የአማራ ህዝብ ለህልውናው እምቢ ብሎ በመነሳት የሚደረገውን ኢፍትሃዊነትና እብሪት አሁኑኑ በቃህ ሊል ይገባል:: አማራውን ብሎም መላው ኢትዮጵያን ከትርምስ ለመታደግ ዓለም አቀፍ የአማራ ሕብረት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያቀርባል:
ለመንግስት አካላት፦
1ኛ/ አርበኛ እና ፋኖ ዘመነ ካሴ ያለምንም መዘግየት በአስቸኳይ እንዲፈታ፣
2ኛ/ ህግ ማስከበር በሚል ሽፋን ባለፉት አምስት ወራት ለእስር የተዳረጉ ፋኖዎች፣ የልዩ ኃይል አባላት: ሚሊሻዎች፣ የመከላከያ አባላትና የፓለቲካ ድርጅት እባላት ከእስር እንዲፈቱ፣
3ኛ/ እንደ ታዲዮስ ታንቱ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ መዓዛ መሐመድ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ አባይ ዘውዱ፣ ደራሲ አሳየ ደርቤ የመሳሰሉት አላግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ማህበራዊ አንቂዎች እንዲፈቱ፣
4ኛ/ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወለጋ የሚደረገውን የአማራው ጭፍጨፋ ለማስቆም ትርጉም ያለው ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲጀመር፣ 5ኛ/ በትህነግ የተወረሩ የአማራና አፋር አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
ለአማራ ህዝብ፦
1ኛ/ የወጣትነት ዘመኑን በሙሉ ለአማራ ህልውና፣ ለኢትዮጵያ አንድነት የሰዋውን ጀግናህን በፍጥነት ከእስር እንዲወጣ የማድረግ ግዴታ ያለብህ መሆኑን ተገንዝበህ እንደ አባቶችህ ትግልህን በጥበብ እንድታካሂድ ለማሳሰብ እንወዳለን::
2ኛ/ ለፍትህ የቆማችሁና የአማራውን የህልውና ትግል ለምትገነዘቡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ያለ አግባብ የታሰረውን አርበኛ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ሁሉም አገርን ከወረራ እና ከመፍረስ የታደጉ ፋኖወች፣ ጋዜጠኞች እና ማህበራዊ አንቂዎች እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት እንድታደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን::
አማራ የጀመረውን የህልውና ትግል በአሸናፊነት ይወጣል! ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ትግል ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!