July 13, 2022
48 mins read

ጠቅላይ ሚኒስትሩና አወዛጋቢው የፓርላማ ውሏቸው – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

abiy leba
  1. መግቢያ

ያለፈው ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮምያ ክልል በምእራብ ዎለጋ ዞን፣ በግንቢ ዎረዳ፣ በቶሌ ቀበሌ፣ በተለያዩ መንደሮች፣ የአማራ ተወላጆች ብሔራዊ ማንነታቸው ብቻ እንደሀጢኣት ተቆጥሮ የተጨፈጨፉበት እለት ነበር፡፡ ነጻና ገለልተኛ ምርመራ ባለመካሄዱ የዚያ አስከፊና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሰለባዎች ቁጥር እስካሁን ድረስ በትክክል አይታወቅም፡፡

ለነገሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ዘግየት ባለ ጋዜጣዊ መግለጫቸው 338 ሰዎች እንደታረዱ አርድተዉናል፡፡ ሆኖም ከአንድ ወገን የተገኘ መረጃ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አንዳች ቅሸባ ሳይፈጸምበት እንዳልቀረ ተጠራጥረው ብዙዎች ለዚህ አሃዝ ጀሮ የሰጡት መስለው አልታዩም፡፡

በርግጥ አለም-አቀፉ የመገናኛ-ብዙኀን እየተቀባበሉ እንዳስተጋቡት ከሆነ ከ1500 እስከ3000 የሚደርሱ ንጹሃን የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው እየተመረጡ ተጨፍጭፈዋል፣ አልቀዋል፡፡ የቆሰለውን፣ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሀብትና ንብረት ሜዳ ላይ በመበተን እግሬ አውጪኝ ብሎ ከየመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሎ የተሰደደውንማ ቤቱ ይቁጠረው፡፡

አቶ መሀመድ ዮሱፍ የተባሉትና እንደንፍሮ ውስጥ የጥሬ ቅንጣት ከዚያ አስከፊ የጅምላ ጭፍጨፋ በተአምር አምልጠው በህይወት የተረፉትአንድ የ64 ዓመት አዛውንት ብቻ በጠቅላላው እስከ22 የሚደርሱ ልጅና የልጅ ልጆቻቸውበዚያ የግፍ እርምጃ በበላኤ-ሰቦቹ ሰይፍ ያለርህራሄ እንደታረዱባቸውና አስከሬኖቻቸውን በጭካኔ ተቆራርጠው ከየወደቁበት እየለቃቀሙ ብቻቸውን ለመቅበር እንደተገደዱ ለBBC የአማርኛው ክፍል እንባ እየተናነቃቸው በሲቃ ሲገልጹ አድምጠናቸዋል፡፡

አበው‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’ ይላሉ፡፡

ዎለጋም የደም ምድርነቷን ባልተቋረጠ ሁኔታ ቀጥላሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም) ደግሞ ትኩስ በተሰማውመረጃ መሰረት አብዛኞቹ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን የሆኑባቸውና ከአምስት መቶ የሚበልጡ አማሮች በሌላው የዎለጋ ክፍል፣ ማለትም በቄለም-ዎለጋ ዞን፣ በሃዋ-ገላን ዎረዳ፣ በለምለም ቀበሌ በተለይ በመንደር 20ና 21 መጨፍጨፋቸው ታውቋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሰዎች ደግሞበታጣቂሀይላቱታፍነው ወደጫካ ስለተወሰዱናደብዛቸው ስለጠፋ ምን እንዳጋጠማቸው አይታወቅም፡፡

ለነገሩ እኮ የኦሮምያ አጎራባች በሆነው በቤኒ-ሻንጉል ክልል መተከልን ጨምሮ በተለያዩ ዞኖች፣ ዎረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ ያለአንዳች ከልካይ የተካሄዱትን ዘር-ተኮር ግድያዎችና የንብረት ዘረፋዎች ሳንጨምር በምስራቅ ወለጋ ዞን በጉሊሶና በሆሮጉድሩ ዞን አቢ-ደንጎር አካባቢዎች ቀደም ሲል ከየካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በመከረኛው ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈጸሙትን መሰል ጭፍጨፋዎችና የደረሱትን እልቂቶች አንዘነጋቸውም ብቻ ሳይሆን ቆጥረንም አንዘልቃቸውም፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ በወርሃ-ሚያዚያ 2010 ዓ.ም በህዝባዊ አመጽ ታጅቦ የተደረገውን ላእላይ የመንግሥት አመራር ለውጥ ተከትሎ ላለፉት አራት ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ወገኖቻችንንየተነጠቅንባቸውን በርካታ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች በየጊዜው ያስተናገድን መሆኑ አይካድም፡፡በሳምንታት ልዩነት ብቻ የተፈጸሙት ሁለቱ ሰሞነኛ ብሔር-ተኮር ፍጅቶች ግን ፍጹም አሳዛኝና ልብ የሚሰብሩአድራጎቶችሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑጨፌ ኦሮምያን ጨምሮ የሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አሁንም ገና በማላገጥ ላይ ናቸው፡፡

አማራው በየስፍራው እየተለቀመ በመታረድና ገሚሱም ወደጫካ እየተጣለ የአውሬ ሲሳይ በመሆን ያልቃል፣ ከየመኖሪያ ቀየው በገፍ ይፈናቀላል፣ ፓርላማው ግን አዝኛለሁ ለማለት እንኳ እየከበደው አብዝቶ ይጨነቃል፡፡

የወቅቱ የሥልጣን አካላት አከታትለው እንደሚያሰሟቸው ረብ-የለሽ የፈነጅራ መግለጫዎች ከሆነ ኦ.ነ.ግ-ሸኔ በየደረሰበት አማሮችን የሚጨፈጭፈው እኛ የሰነዘርንበትን ጥቃት ተከትሎ ሲሸሽ ተሸናፊነቱን ለመበቀል ሲል ነው ይሉናል፡፡ እንግዲህ በየባለሥልጣናቱ የእንቶ-ፈንቶ መግለጫ መሰረት ታጣቂው ቡድን እርምጃውን የወሰደው በመንግሥት የጸጥታ ሀይሎች ድባቅ ተመትቶ በሽሽት ላይ እንዳለ ሳይሆን አይቀርም፡፡

  1. ዘር ማጥፋት፣ በሰብእና ላይ የተፈጸመ ፍጅት ወይስ የጦር ወንጀል?

እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር December9 ቀን 1948 ዓ.ም የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ በውሳኔ ቁጥር 260 (A)III ባጸደቀው የጄኔቫ ስምምነት መሰረት ‘የዘር ማጥፋት ወንጀል’ ማለት አንድን ብሔር-ብሔረ-ሰብ፣ ጎሳ ወይም ዘውግ፣ ዘር ወይም ሀይማኖታዊ ቡድን በከፊል ወይም በሙሉ ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት ታስቦና በሚገባ ታቅዶ የሚፈጸም አለም-አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ ይህ የወንጀል አድራጎት በሠላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ ቢፈጸም አድራጊውን በኀላፊነት ከማስከሰስና በጥፋተኝነት ከማስቀጣት አያድነውም፡፡

ከJanuary  12 ቀን 1951 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው የዚህ አለም-አቀፍ ስምምነት አንቀጽ (2) በማያሻማ ሁኔታ እንደሚተረጉመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በጥቃቱ ኢላማ የተደረገውን ቡድን አባላት በመግደል፣ ከባድ የአካልም ሆነ የአእምሮ ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግ፣ ግዙፋዊ ህልውናውን በከፊልም ሆነ በሙሉ በማጥፋት ላይ የተነጣጠሩ የኑሮ ሁኔታዎችን በቡድኑ ላይ ሆነ ብሎ በማክበድ፣ በቡድኑ ውስጥ መራባትን እንዲያግዱ ወይም እንዲከለክሉ ታስበው ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችን በመጫን ወይም በቡድኑ ውስጥ የተወለዱትን ህጻናት በአስገዳጅ ሁኔታ እያፈናቀሉ ወደሌላ ባእድ ቡድን ወይም ስብስብ በማዛወር ሊገለጽ ይችላል፡፡

ከወንጀል ስነ-ሕግ የጥናት ዘርፍ እንደምንረዳው ታስቦ የሚፈጸም የትኛውም አይነት የወንጀል ድርጊት በመርሕ ደረጃ አያሌ የአፈጻጸም እርከኖች እንዳሉት በተለይ በሕግ ማሕበረ-ሰቡ ዘንድ በሚገባ ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ ወንጀሎች ታዲያ በፍጻሜና በሙከራ ደረጃ በኀላፊነት የሚያስጠይቁ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ብቻ የከባድነታቸውና በጠቅላላው ህዝብ ዘንድ የሚያስከትሉት አደጋ ከወዲሁ እየታየ ገና በመሰናዶ ደረጃ ሳይቀር እንደሚያስከስሱና እንደሚያስቀጡ የሚደነገግላቸው ናቸው፡፡

ከነዚህ አንደኛው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሆን በስምምነቱ አንቀጽ 3. ስር እንደተደነገገው ይህ አለም-አቀፍ ወንጀል በፍጻሜው ብቻ ሳይሆን በሴራ፣ ቀጥተኛና ይፋዊ በሆነ ማነሳሳት፣ በሙከራም ሆነ በተባባሪነት ደረጃ ሳይቀር የተካፈለውን ሁሉ በተሳትፎው ልክ የሚያስከስስና የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ተደርጎ እናገኘዋለን፡፡የድንጋጌው አቀራረጽና ይዘት መንግሥታት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ይህንን አስነዋሪና አስከፊ ወንጀል እስከመጨረሻው ጥግ ድረስ አምርረው ለመከላከልና ለመዋጋት በጊዜው ያደረባቸውን የተባበረ ቁርጠኝነት ያሳየናል፡፡

እንዲያውም በተጠቀሰው አለም-አቀፍ ውል አንቀጽ 6. ስር በግልጽ ሰፍሮ እንደምንመለከተው በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው እንደተገቢነቱ ድርጊቱን በፈጸመበት አገር የዳኝነት አካል ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ለመዳኘት ሥልጣን በተሰጠው አለም-አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ችሎት ፊት በአማራጭ ተከሶ ሊቀርብና የቅጣት ውሳኔ ሊተላለፍበትይችላል፡፡

  1. የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ

ሀገራችን ኢትዮጵያከበርካታ የአለም አገሮች ቀድማ ዘር ማጥፋትን በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕጓ ውስጥ በንቃት ያካተተች፣ ያንኑ በከባዱ የሚያስቀጣ ወንጀል ያደረገችና በዚህ ረገድ አብነት የሆነች አገር ናት፡፡ እርሱን ተክቶና በወርሃ-ግንቦት 1997 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢ.ፌ.ደ.ሪ የወንጀል ሕግም በቁጥር 269 ስር በወራሲነት ተቀብሎ በተጠናከረ ሁኔታ ወንጀል አድርጎታል፡፡

ዘግይቶ የወጣውና በአሁኑ ወቅት ጸንቶ የሚሰራበት የዚህ ፌደራላዊ ሕግ ቁጥር 269 ‘ዘርን ስለማጥፋት’ Genocide በሚለው ርእስ ስር እንደሚከተለው ደንግጎ እናገኘዋለን፡-

ማንም ሰው በሠላምም ይሁን በጦርነት ጊዜ በብሔር-ብሔረ-ሰብ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በሐይማኖት ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የጥፋቱን ድርጊት በማደራጀት፣ ትእዛዝ በመስጠት ወይም ድርጊቱን በመፈጸም፡-

ሀ.በማናቸውም ሁኔታ የማሕበረ-ሰቡን አባሎች የገደለ ወይም አካላዊ ወይም ህሊናዊ ጤንነታቸውን የጎዳ ወይም የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም ያጠፋ እንደሆነ ወይም፤

ለ. የማሕበረ-ሰቡ አባላት በዘር እንዳይራቡ ወይም በህይወት እንዳይኖሩ ለማድረግ ማናቸውንም ዘዴ በስራ ላይ ያዋለ እንደሆነ ወይም፤

ሐ. የማሕበረ-ሰቡን አባላት ወይም ህጻናት በግዴታ ከስፍራ ወደስፍራ ያዛወረ ወይም የበተነ ወይም ሊሞቱ ወይም ሊጠፉ በሚችሉበት ሁኔታ እንዲኖሩ ያደረገ እንደሆነ፤

ከአምስት ዓመት እስከ25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑእ ስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ-ልክ ጽኑእ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል”፡፡

በስራ ላይ ያለው የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት በበኩሉ በሰብእና ላይ የሚፈጸሙ ናቸው ያላቸውን ወንጀሎችበሚዘረዝረው አንቀጹ ስር የዘር ማጥፋት ወንጀልን ከሌሎች አለም-አቀፍ ወንጀሎች ጋር አጃምሎናበጥቅሉ ደንግጎት ነው የምንመለከተው፡፡

ከዚህም የተነሳ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 28 በንኡስ አንቀጽ (1) ስር “ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው አለም-አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የሀገሪቱ ሕጎች መሰረት በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ናቸው ተብለው የተወሰኑትንናእንደየሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር ወይም ኢሰብኣዊ የድብደባ ድርጊቶችያሉ ወንጀሎችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ እንደማይታገድና በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በየትኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔበምህረት ወይም በይቅርታ እንደማይታለፍ”በአጽንኦት የሚያሳስብ ስነ-ስርአታዊ ድንጋጌ ሰፍሯል፡፡

እዚህ ላይ ተጃምሏል ያልኩበት አይነተኛ ምክንያት ዘር ማጥፋት የተሰኘው ወንጀል በሰብእና ላይ ከሚፈጸሙ ሌሎች ተዛማጅ ወንጀሎች ጋር በአንድነት ተቀላቅሎና በመጠኑም ቢሆን ያለአግባብ ተወሳስቦበመደንገጉ ብቻ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ በሁለት ተከታታይ ዙሮች በጠበበ የጊዜ ልዩነት በምድረ-ዎለጋ ሰኔ 11ና ሰኔ 27 ቀናት 2014 ዓ.ም የተካሄደው የአማራ ተወላጆችዘግናኝና  አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የመንግሥት አካላትም ሆኑ ግብዝ ደጋፊዎቻቸው በሰብእና ላይ የተፈጸመ እንጂ አንድን ብሔር፣ ዘውግ ወይም ሀይማኖት ለይቶ የተካሄደ የዘር ማጥፋት ወንጀል አይደለም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ሲሟገቱ ይደመጣሉ፡፡ ፡፡

ለመሆኑ የዎለጋው ሰሞነኛ ፍጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ወይስ በሰብእና ላይ የተፈጸመ ወንጀል?

የጦር ወንጀል የሚለው እንኳ በጭራሽ አይመለከተውም፡፡

ዎለጋ ውስጥ በትላንቱም ሆነ በዛሬው የጅምላ ፍጅት በሚናገሩት የአፍ መፍቻ ልሳን ተመርጠው የተጨፈጨፉት በሰፊው የኦሮሞ ማሕበረ-ሰብ መሃል አፈር እየገፉ የሚኖሩና ከፖለቲካ ጋር ይህ ነው የሚባል ግንኙነት ጨርሶ ያልነበራቸው ህዳጣን አማሮች ናቸው፡፡ በርግጥ አለቅጥ አፍጥጦ የወጣውን ይህንኑ ደረቅ ሀቅ እስካሁን ድረስ ወደፊት ወጥቶ በቀጥታ ለማስተባበል የደፈረ አካል የለም፡፡

ሆኖም አንድን ህዝብ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት አስቀድሞ በታቀደና በተደራጀ መንገድ በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥራት/ማጥፋት ወንጀል በስሙ ለመጥራት ሁሉም አይን-አፋርነት ሲሰማውና አብዝቶ ሲጨናነቅ ታዝበናል፡፡ ከዚያ ይልቅ ጭፍጨፋው ያለርህራሄ የበላቸውን የአንድ ብሔር ሰለባዎች ንጹሃን ዜጎች በሚል መጠቅለያ በሰብእና ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው እየተባለ ሲድበሰበስና ሲስተጋባ ነው በአንክሮ የምንከታተለው፡፡

እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር July 17 ቀን 1998 ዓ.ም በጸደቀውና አለም-አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ባቋቋመው የሮሙ ሰነድ አንቀጽ 7. ንኡስ አንቀጽ (1) ስር ተተርጉሞ እንደምናገኘው በሰብእና ላይ የተፈጸመ ወንጀል “crime against humanity” ማለት በተቀነባበረ መንገድ በማናቸውም ሠላማዊ ህዝብ ላይ በቀጥታ የተነጣጠረና ሆነ ተብሎ የሚሰነዘር የማናቸውም መጠነ-ሰፊ ጥቃት ክፍልና አካል ነው፡፡

ሁለቱም ወንጀሎች ተጠርጣሪው በአለም-አቀፍ ደረጃ የሚሳደድባቸውና በተገኘበት ስፍራ ተይዞ የሚጠየቅባቸው ከባድ ወንጀሎች መሆናቸውን እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡ አያሌ ጠባያትን እንደሚጋሩ ቢታወቅም ታዲያ እንደሕጉ አቀራረብ በሰብእና ላይ የሚፈጸምን ወንጀል ከዘር ማጥፋት ወንጀል በዋነኝነት የሚለየው ከመነሻው አንድን ብሔር፣ ዘውግ፣ ማሕበረ-ሰብ ወይም ቡድን ኢላማ አድርጎ የሚፈጸም አለመሆኑ ብቻ ነው፡፡

  1. በቁጣ የታጀበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትርአቢይ አህመድ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ያሰሙት ዲስኩር ቀደም ሲል ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ካሰሙትም የባሰና ፉከራ፣ ቅሌት፣ ንቀት፣ ውሸትና ክህደት በስፋት የታየበትና የተደመጠበት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ ዜጎች በግፍ እየተጨፈጨፉችግኝ አትትከሉ የሚሉትን ወገኖች አትስሟቸው፤  እኛ ሰው እየሞተም ቢሆን ዛፍ መትከላችንን እንቀጥልበታለን፤ ይህ ነውር የለውም፤ ቢያንስ አስከሬኑ ጥላ ያገኛልሲሉ አሳቀዉናል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ዛፍ መትከልማ ነውር የለውም እኮ፡፡ መላው አለም በአማራ ተወላጆች ላይ የተካሄደውን አስደንጋጭ የዘር ጭፍጨፋና የደረሰውን እልቂት እየተቀባበለ ሰፊ የዜና ሽፋን ከመስጠት ባሻገር አምርሮ በሚያወግዝበትና ስለመንግሥታቸው ቀዳሚ ኀላፊነት አብዝቶ በሚጮህበት ወቅት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማሳወጁና የሀገሪቱን ባንዲራ ዝቅ ማድረጉ ቢሳናቸው እንኳ አንዳች የተለየ ነገር እንዳልተፈጠረ ቆጥረው አረንጓዴ በማልበሱ ፕሮጀክታቸው ያለሀፍረት መቀጠላቸውና ይህንኑም ለአስከሬን ጥላ ይሆናል በማለት ጭፍጨፋውን በዚያ ደረጃ ማስተሀቀራቸው ነበር እንደመዘባበት የተቆጠረባቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሃኑ በጅምላ መጨፍጨፋቸው ያን ያህል ተጋኖ መታየት የለበትም፤ ይህ እኮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰት ጉዳይ አይደለም፤ እንደአሜሪካ ባሉት አገሮችም ዘወትር ያጋጥማልማለታቸው ሲበዛ አስተችቷቸዋል፡፡

በርግጥ እንዲህ ያለው ከንቱ ማነጻጸሪያ ውሉ የጠፋበት ነው፡፡ ጠቅላዩ ለማወዳደር እንደተዳፈሩት ስነ-አእምሮው ክፉኛ የታወከ፣ አመክንዮ የጎደለው ወይም በጥላቻ ያበደ ማንኛውም ግለሰብ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚፈጽመው ድንገተኛ የጥይት ተኩስና በጅምላ የሚያደርሰው ሰብአዊ ጉዳት ወይም እልቂትና በደንብ ታቅዶ በተደራጀ መንገድ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወንጀል አንድና ተመሳሳይ አይደሉም፣ ሆነውም አያውቁም፡፡

እውነቴን ነው የምላችሁ፤ ምን አይነት መንበዛበዝ እንደሆነ ፈጽሞ ለሰው አይገባም፡፡

የሐገሪቱ መሪ በተፈጥሯዊ ተሰጥዎ አንደበተ-ርቱእ ሲሆኑ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሳይጽፉ የመናገር ችግር የለባቸውም፡፡ አሁን-አሁን ግን ራሳቸውን መምራትም ሆነ አንደበታቸውን መግራት እየተሳናቸው የመጣ ይመስለኛል፡፡

አፈሩ ይቅለላቸውና ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ራሳቸውን ብልህና ታላቅ መሪ አሰኝተው ነበር እስከወዲያኛው አለም የተሸኙት፡፡

በርሳቸው መንፈስና ተክለ-ሰውነት ስር ይንቀሳቀሱ የነበሩት መካከለኛ መሪ አቶ ሀይለ-ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የመለስን ያህል የተባ አንደበትና መሰሪ ስነ-ተፈጥሮባይኖራቸውም እንደአንድ ቁንጮ የሀገር መሪ የተረጋጋ ስነ-አእምሮና ማለፊያ ሰብእና ነበራቸው፣ አላቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡

አቢያችንም እኮ አነሳሳቸውን ለተመለከተና ላስተዋለ እንደመጠሪያ ስማቸው ሁሉ አቢይ መሆን ቢያቅታቸው እንኳ ንኡስ መሪ የመሆን እድል ነበራቸው፣ አሁንም አላቸው፡፡

ሆኖም ይህንን እምቅና ወርቃማ ተሰጥዎ በወጉና በኀላፊነት ስሜት እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ ነጋ-ጠባ አደገኛ የልሳን እንሽርት ባጋጠማቸው ቁጥር እኛ ምንዝሮቹ ተሳቀን መሞታችን ነው፡፡

በርሳቸው ደረጃ ያሉ አቻ የመንግሥታት መሪዎች በልማድ እንደሚያደርጉት ጭፍጨፋው የተፈጸመበትን የትኛውንም ስፍራ ለአንዳፍታ ጎራ ብለው ለመጎብኘትና የተጎዱትን ሰለባዎች በአካል ተገኝተው ለማጽናናት ባይደፍሩም የዜጎቻቸውን ህይወት ለመታደግ ባለመቻላቸው ግን ልባዊ ሀዘን እንደተሰማቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነግረዉናል፡፡

ያም ሆኖ አንዳንድ ወገኖች ያለአግባብ ሊያሳጧቸው እንደሚሞክሩት የቶሌውም ሆነ የሃዋ-ገላኑ ፍጅት በመንግሥታቸው ቸልተኝነት ወይም ዳተኝነት የተፈጸመነው ብለው አያምኑም፡፡

እንደሰውየው አነጋገር ከሆነ ከዚያ ይልቅ ሲቪል ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ እነርሱን ከጭፍጨፋው ለማዳን በግዳጅ ላይ የተሰማሩ የፖሊስ፣ የጸጥታና የመከላከያ ሀይል አባላት ሳይቀሩ ውድ ህይወታቸውን እንደገበሩ በሚያታክት ስሜት ያደረጉት ተጨማሪ ገለጻ ፍየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያ ሲሆንባቸው ታዝበናል፡፡

የሚሉት እውነት ቢሆን እንኳ ታዲያ በቀጥታ እንዲመልሱት ከፓርላማ አባላቱ የቀረበላቸው ጥያቄ እርሱ ስላይደለ ያሰቡትን ያህል ትኩረት ስቦ በውል ሳይደመጥላቸው ቀርቷል፡፡ በርግጥ እንዲህ ያለው ዲስኩር ቀዳሚ ኀላፊነቱን በቅጡ መወጣት ለተሳነው መንግሥት በጭፍጨፋዎቹ ሰለባዎች አንጻር የሂሳብ ማወራረጃ ሆኖ ሊያገለግል እንደማይችልአቢይ አስቀድመው መረዳት የነበረባቸው ይመስለኛል፡፡

የሽብር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የሀገሪቱ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም አንቀጽ 18. ንኡስ አንቀጽ (1)ና (2) ድንጋጌዎች መሰረት ራሱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀደም ሲል በሁለት-ሶስተኛ ድምጽ በቀንደኛ አሸባሪነት ከሰየመው ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሀ.ት)) ጋር ሊካሄድ ስለታሰበውና በመንግሥታቸው በኩል ከወዲሁ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት ስለሚደረግበት ድርድር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማው በኩል ሌላ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበርም ተከታትለናል፡፡

ለሠላም ስንል የማንከፍለው ዋጋ የለም፡፡ ከአሸባሪው ት.ህ.ነ.ግ ጋርም ቢሆን ትርፍ እስካገኘንበት ድረስ ለሠላም እንደራደራለን፡፡ ይህንንም ቢሆን የብልጽግና ፓርቲ በህዝብ የተመረጠ ገዢ የፖለቲካ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ብቻውን መወሰኑ ነውር አይደለም፡፡ እናንተም ብትሆኑ ቀደም ሲል የተወያያችሁበት በመሆኑ ለነገሩ እንግዶች አይደላችሁም፤ በአንድ በኩል ህዝባችን ተፈናቀለ፣ ተጎዳ ትላላችሁ፤ ተደራድረን ችግሩን እንቀንስ ስንላችሁ ደግሞ ካልፈቀዳችሁ ራሱ ችግር ይሆናል፡፡ ከአሸባሪ ጋር መወያየትና መደራደር እኮ በኛ አልተጀመረም፤ ሌሎች አገሮችና መንግሥታትም ያደርጉታል፡፡ ደርግም ቢሆን ከሻቢኣናህ.ወ.ሀ.ት ጋር ሲያካሂደው ነበር፡፡ ቢነገርም ባይነገርም ይህ አይነቱ ድርድር ይካሄዳል፤ የትም ያለ ነገር ነው ሲሉ ሰፋ ያለናድፍረት የተመላበት የመከላከያ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ግን ህ.ወ.ሀ.ትን ቀድሞ ነገር አሸባሪ ያላችሁት እናንተ አልነበራችሁም፤ ሲሉ የህዝብ እንደራሴዎቹንእስከማንጓጠጥና በቀረበው ጥያቄብዙ እንዳይገፉበት ለማሸማቀቅ እስከመሞከር ድረስ የሄዱበት ረዥም ርቀት ነው፡፡ በዚህ ያልተገባ አቀራረባቸው ታዲያ ከፍተኛውን የመንግሥት ሥልጣን አካል እንደአንድ ተራ የግለሰቦች ስብስብ እንጂ እርሳቸውን ጭምር እስከመገሰጽና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለመስተዳድራቸው የመተማመኛ ድምጽ እስከመንፈግ የሚዘልቅ ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው ተቋም ሊመለከቱት አለመፍቀዳቸውን ታዝበናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዎለጋ የተጨፈጨፉትን ንጹሃን ዜጎች ከእልቂቱ ባለማዳናችን እናዝናለን፤ እንዲያም ሆኖ ጠላቶቻችን ግድያና ማፈናቀሉን በመደጋገም ኢትዮጵያን ያጎሳቁሏት እንደሆነ ነው እንጂ ሊያፈርሷት ከቶ አይችሉም፡፡ ሲሉ በተለመደው አሰልቺ የግብዝነት ማጽናኛቸው ሊያረጋጉን መሞከራቸው አልቀረም፡፡ በርግጥ ይህ ምጸት ይመስላል፡፡ ሰውየው የአገር መፍረስ ምን ማለት እንደሆነ እንኳ ፈጽሞ የተገነዘቡ አይመስሉም፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ሸኔ የሽብር እንጂ የፖለቲካም ሆነ የርእዮተ-አለም አላማ የለውም፣ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ጠላት ነው ብለውናል፡፡ዘንግተዉት መሆን አለበት እንጂ በሌላ የቀደመ ንግግራቸው ግን ይኸው ቡድን በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሀይል እንደመሆኑ መጠን የብዙኀኑ ድጋፍ ሳይኖረው አይቀርም በማለት ሽብርተኛውን ቡድን በተመለከተ ከማሕበረ-ሰቡ ጋር መወያየት እንደሚገባ ተቃራኒውን በመናገር አስደንግጠዉን ነበር፡፡

ከሁሉም በላይ የዎልቃሂት-ጠገዴን በጀት በተመለከተ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የተባሉ የህዝብ እንደራሴ ላቀረቡላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መልስ ንቀት የተመላበት፣ ማን አህሎኝነት የተጠናወተውና ማምታታት የታከለበት መስሎ ታይቶባቸዋል፡፡ አጠቃላይ ይዘቱም የዎልቃሂትን በጀት በትግራይ ክልል በኩል መድበናል፤ ከዚህ አልፎ ጥያቄው የበጀት አስተዳደር ከሆነ ደግሞ ራሱን ችሎ ይታይና ወደፊት የሚፈታ ይሆናል ሲሉ ነበር በመጀመሪያ ሊያድበሰብሱ የሞከሩት፡፡

ከዚያም አከል አድርገው በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ችግሩ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ እርሳቸው ከመቸውም ጊዜ ባልተለመደ ሁኔታ ‘ምእራብ ትግራይ’ ብለው የጠሩት የዎልቃሂት ጠገዴ አካባቢ አስቀድሞ ሲተዳደር የነበረው በትግራይ ክልል ውስጥ እንደመሆኑ መጠን በጀቱ በዚያ በኩል የተመደበለት ስለመሆኑ ያለይሉኝታ አርድተዉናል፡፡ሆኖም እርሳቸው ቢረሱትም ዎልቃሂት የቤጌ-ምድር ግዛት ነው በማለት ከጥቂት ወራት በፊት ሲቀፍሉን እንደነበር አይዘነጋም፡፡

እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ብርቱ ቁምነገር ቢኖር በርሳቸው ደረጃ የሚገኝ የአንድ አገር መሪ አንድ ዓመት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአንድናተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ሁለት እርስበርሳቸው የሚቃረኑ አስተያየቶችን ቢሰጥ በቅድሚያ የሚያጣው የራሱን ኅዝባዊ ተቀባይነት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ የተገነዘቡ አለመሆናቸውን ነው፡፡

ለማናቸውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምስጋና ይግባቸውና ከመቸውም ጊዜ ይልቅ በሰኔ ሰላሳው የፓርላማ ዲስኩራቸው ህ.ወ.ሀ.ት ወደትግራይ በጉልበት አጠቃሏቸው የቆዩትን የአማራ አካባቢዎችና ነዋሪዎች በተመለከተ አንድ ነገር ግልጽ አድርገዉልናል፡፡ በተለይ ወልቃሂት-ጠገዴ በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በክልሉ ልዩና የሚሊሻ ሀይሎች፣ እንዲሁም በህዝቡ መሪር ተጋድሎ ከህ.ወ.ሀ.ት የተጽእኖ አገዛዝ ተላቃ በአማራ ክልል ስር መተዳደር ከጀመረች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ እንደሆናት ቢታወቅም በጀት ይገባኛል የምትል ከሆነ ይህንኑ ልትጠይቅ የምትችለው ከጓድ ደብረ-ጽዮን ገብረ-ሚካኤል እንጂ ከጓድ አቢይ አህመድ በጅሮንድ ጽህፈት ቤት ሊሆን አይችልም፡፡

ሰውየው በዚህ ሳይወሰኑ የዎልቃሂት ጉዳይ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ተጣርቶ በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል የመጨረሻ እልባት እንዲሰጠው በተለይ ለአማራ ክልላዊ መንግሥት ተደጋጋሚ ተልእኮ ሰጥተናል ሲሉ ራሳቸውን ከኀላፊነት ነጻ በማውጣት ለጉዳዩ ዳተኛ ሆኖ የሚታየው ሌላው ክፍል እንደሆነ ለማሳጣት ሲሞክሩ ተደምጠዋል፡፡እኔ በበኩሌ ይህንን አይነቱን አባባላቸውን ፈጽሞ እንደማላገጥ ነው የምቆጥረው፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ እርሳቸው በየአደባባዩ የሚረገረጉለት ህ.ወ.ሀ.ት-ወለዱ የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት ራሱ ዋናው ችግር ፈጣሪ ስለሆነ ያንኑ የበለጠ ከማወሳሰብ በስተቀር ሌላ ችግር የመፍታት አቅም የለውም፡፡የፌደሬሽን ምክር ቤትም ቢሆን ጥያቄው በአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በኩል ተደራጅቶ ከቀረበለት እድሜ ያስቆጠረ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ለዚህን ያህል የተራዘመ ጊዜ አንዳች አይነት እልባት መስጠት ተስኖት ያለአግባብ ሲያንከባልለው እንደቆየ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዲስኩራቸው ሕግ መተርጎም እኮ የናንተ የስራ ድርሻ አይደለም፤ የሕግ አንቀጽ ከመጥቀስም ብትቆጠቡ ይሻላችኋል፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት ስራ ጣልቃ የምትገቡትስ ምን ቆርጧችሁ ነው፤ መሬት ወርዳችሁ ባላረጋገጣችሁት ጉዳይ እኔን እዚህ ለምን ትነዘንዙኛላችሁ በሚል አደገኛና አንባገነናዊ ድምጸት የተከበሩትን የምክር ቤት አባላት ክፉኛ ሲወርፏቸው እየተሳቀቅንም ቢሆን አስተውለናል፡፡

እርሳቸውስ ቢሆኑ በየደረሱበት ስፍራና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ‘በሕገ-መንግሥቱ መሰረት’ እያሉ የሚያስደምሙን “ሕገ-መንግሥታዊ ሕግ’ የተሰኘውን የእውቀት ዘርፍ በተመለከተ ምን የተለየ ተጠባቢነት ኖሯቸው ይሆን?  ?? “ ‘’

በመሰረቱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በቁንጽሉ እንደገመቱት ሕግ መተርጎም የፍርድ ቤቶች ብቸኛ ኀላፊነት አይደለም፡፡ በሌላ ገጹ ቢመለከቱት ኖሮ ‘ሕጎችን ከወጡበት መንፈስና አውድ ጋር በተገናዘበ መንገድ መተርጎም‘ (LEGISLATIVE INTERPRETATION)የሚባል የስራ ዘርፍ እንዳለ የመረዳት እድልና አጋጣሚ ይኖራቸው ነበር፡፡

እንዲሕ ያለው ተግባር ታዲያ ለዳኝነት አካሉ ሳይሆን በልዩ ጠባዩ ምክንያት ለሕግ አውጪው የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በተፈጥሮ የተሰጠ የስራ ድርሻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አይነተኛ አላማውም ሕግ አውጪው አካል ሕጉን ባወጣበት ወቅት ምን ሃሳብ ወይም ፍላጎት እንደነበረው በይፋ ጠይቆ ተፈላጊውን ምላሽና ማብራሪያ ማግኘት ነው፡፡

ለማናቸውም ሰውየው ከሙያቸው አድማስ ውጭ በሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ያን ያህል አብዝተው ባይጨነቁ መልካም ነበር እላለሁ፡፡

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጉንቱ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪ ይመስሉኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ስሜታዊነትን በተላበሰው በዚያ ዲስኩራቸው መንግሥቴ በስእል፣ በጽሁፍና በዘፈን ጋጋታ አይሸበርም፣ዙፋኔም አይነቃነቅም ሲሉ የሰነዘሩት የአሽሙር አይነት አነጋገር የቀደመውን አቋሜን እንድመረምር አስገድዶኛል፡፡ እንዲያውም ይህ አስተያየታቸው ራሱ በስም ባልጠቀሷቸው ጸሀፍት፣ ካርቱኒስቶችና አዝማሪዎች ወቅታዊ የጥበብ ስራ ውጤቶች መሸበራቸውን በቀላሉ እንደሚያሳብቅባቸው እንኳ ስለመገንዘባቸው ተጠራጥሬያለሁ፡፡

  1. መደምደሚያና ምክረ-ሃሳብ

መሪነት አርኣያነት ነው፡፡ የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ በየትኛውም እርከን የሚገኙ የህዝብ አገልጋዮች ሁሉ ስራቸውን በምሳሌነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በግል ኑሯቸውና በቤተሰብ አመራራቸው ሳይቀር ከተራው ሰው የተሻለ ወይም ላቅ ያለ የስነ-ምግባር ደረጃ እንዲያሳዩንም ይጠበቅባቸዋል፡፡

በርግጥ መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተከታዮቻቸው ጋር የሚገናኙት በንግግር እንጂ በአካል ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ከጥቂቶች በስተቀር መሪዎች ሁሉ የተዋጣለት የንግግር ክህሎት ላይኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም በተሰጥዎ ያላገኙትን ችሎታ ክፍተት ከጀርባ በሚያሰማሯቸው ብቁና ንቁ አማካሪ ሙያተኞች ድጋፍ ይሸፍኑት ዘንድ ሰፊ እድል አላቸው፡፡

በተለይ እንደአፍሪካ ባሉ ክፍለ-አለማት ቁንጮ የፖለቲካ መሪዎች በአደባባይ የሚያስደምጡት የትኛውም አይነት ንግግር ራሱ ሕግ በመሆኑ በውል ታስቦበት ሊለቀቅ ይገባል፡፡ ትላንትና ከትላንት ወዲያ ከተሰሙት ሌሎች ቀደምት ንግግሮቻቸው ጋር በሚገባ ተገናዝቦ ካልተለቀቀ ግን ለጎላ ስህተትና ለከፍተኛ ትዝብት ይዳርጋል፣ በተደራስያኑዜጎችና ማሕበረ-ሰቦች ዘንድም ጭራሽ ተቀባይነትን ሊያሳጣ ይችላል፡፡

አበው “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት’ እንዲሉ መሪዎች ቀድሞውኑ ወደሥልጣኑ ማማ በቀላሉ ተረማምደው መንበሩን የሚቆናጠጡት ከሰዎች መካከል መሆኑን በሚገባ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ የተነሳ ማእከላዊ አመክንዮን እንጂ ፍጹምነትን ከርሳቸው የምንጠብቅ የዋሃን አይደለንም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ግን የሀገሪቱ ራስ መሆናቸውን ብዙ ጊዜ ይረሳሉ፡፡ ሌላው ይቅርና ውድ ባለቤታቸው ስንት የሚበልጧቸው ወይዛዝርት እያሉ እነርሱን ሁሉ ልቀው ቀዳማዊት እመቤት እየተባሉ በተለየ ክብርና ሞገስ በመንቆለጳጰስ የሚጠሩት ከርሳቸው ቁጥር አንድ ኀላፊነት በመነጨ አመክንዮ መሆኑን ጨምሬ ላስታውሳቸው እገደዳለሁ፡፡

እነሆ ለጊዜውም ቢሆን ታዲያ ሀገር በጃቸው ላይ የወደቀችባቸው ሰውና ኀላፊነታቸውም ከመነሻው የከበደ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበ የመጣም ጭምር እንደመሆኑ መጠን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደቀደመ ቀልባቸው እንዲመለሱና ተከታዮቻቸው አምነን እናግዛቸው ዘንድ ተረጋግተውናምራቃቸውን ዋጥ አድርገው እንዲመሩን እንፈልጋለን፡፡

ማን ከሁላችንም ቀድሞ እንደተናገረው ያን ያህል አጣርቼ መጥቀስ ባያስፈልገኝም ሥልጣን ግለሰብኣዊ ማንነትን ያስረሳል፡፡

ያልተገደበና ፍፁማዊ ሥልጣን ደግሞ በዚያው ልክ ሰውን ያበላሻል፡፡

አበቃሁ፡፡

 

1 Comment

  1. ጌታዬ ጠሚንስተሩ በጎመን አማካሪዋች (አባዱላ ገመዳ፣ሌንጮዎች፣ዲማ ነጋዎ ፣አዳነች አቤቤ፣ታየ ደንዳና፣አረጋዊ በርሄ ተከበው እንዲህ ነገር ጠፍትቷቸው እሳቸውም ጠፍተው አገር ከሚያጠፉ እንደ ልጅ እያሱ ልብ እስኪገዙ አጠገባቸው ብትሆን ዛሬ የተናገሩትን ነገ እራሳቸውን እንዳይቃረኑ ይመከሩ ነበር። እንዲህ እንዳንተ ረጋ ብለው ያስተውሉ ሲባሉ አማሮች ተቹኝ ይላሉ። በመሰረቱ በየእለቱ ጥምብ እርኩሳቸውን የሚያወጡት ኦነግና ህወአት ሲሆኑ እሳቸው ግን አማራው ላይ ተንጠልጥለው ቀርተዋል። አንዳንዴ እሳቸውም ላይ አልፈርድም የከበባቸው የጴንጤ መንጋ ጨርቅ አስጥሎ ያስመንናል። ለማንኛውም ብዙ ረዳኻቸው ካወቁበት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

292152913 3243883475854109 8748215462428530622 n
Previous Story

“ኤልሻዳይ” ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ጋር በመመሳጠር የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀሎች ፖሊስ ይፋ አደረገ

skynews sri lanka protest presidential 5828881 1
Next Story

ነፃነት እና ህልዉና ዕዉን ለማድረግ ከማንም አንጠብቅ!  

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop