ምክንያት አልባው ፅንፈኝነት – በያሬድ ኃይለ መስቀል

 

‹‹በፅንፈኝነት መሀል ወርቃማ አማካይነት ፍለጋ›› በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚዘጋጀው ‹‹የአዲስ ወግ›› ሦስተኛ ውይይት ላይ በአድማጭነት ተካፍዬ ነበር። በውይቱ ላይ መጋበዜን ሳውቅ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ ጽሑፎች አነበብኩ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መጽሐፍ ፅንፈኝነት ምንድነው? መገለጫዎቹስ ምንድናቸው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ዓይኔን የከፈተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዘር ማጥፋት ምክያቶችና ዓይነቶች ምንድናቸው የሚሉ አራት ቁም ነገሮችን አስጨብጦኛል።

የመጀመርያው መጽሐፍ ‹ፅንፈኝነት፣ የፍልስፍና ትንተና› የሚል በፕሮፌሰር ቃሲም ካሳም (Extremism:- A Philosophical Analysis, Quassim Cassam, 2022) ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹ለምን ሁሉንም አንገላቸውም?›› (Why Not Kill Them All, Daniel Chirot & Clark Mc Cauley, 2006) ነው።

ከእነዚህ ጽሑፎች ያገኘሁትን ቁምነገሮች በተከታታይ ጽሑፍ ለአንባቢያን ለማካፈል ወስኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ምንም የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ሕፃናትና ወልደው የተኙ አራሶች ሳይቀሩ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚታረዱበት አገር ሆናለች፡፡ አንዳንዴ የተራ ጉዳይ ነው እንጂ በርካታውን ማኅበረሰብ ለማረድ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ፅንፈኛ ያለበት አገር ሆናለች፡፡ ስለዚህ በፅንፈኝነት ላይ መወያየትና መፍትሔውን ማፈላለግ ግድ ይላል።

የኒውዮርክ (New York) መንታ ሕንፃዎችን ለመምታት የአልቃይዳ አጥፍቶ ጠፊዎች አውሮፕላን ማብረሪያ ትምህርት ቤት ገብተው ማብረር ተምረው፣ ከዚያም አውሮፕላኖቹን ወደ ሚሳይልነት ቀይረው ራሳቸውንና ሦስት ሺሕ ሰዎችም ይዘው ከጠፉ በኋላ የዓለም ተመራማሪዎች ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ብዙ የጥናት ጽሑፎች አሳትመዋል። እኔም መጻሕፍቱ ካነበብኩ በኋላ ፅንፈኝነት በየቀኑ የምናየው፣ በቅርባችን ያለ፣ በመንግሥት ፖሊሲዎች፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራም፣ በታጣቂዎች ጭካኔና በአክቲቪስቶች ቅስቀሳ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ አየሁ።

በውይይቱ ላይ የቀረበው መደምደሚያ ፅንፈኝነት ‹‹ለእኔ ብቻ፣ ለእኛ ብቻና የእኔን ሐሳብ ካልተቀበልክ አጠፋሃለሁ›› የሚለው ዕሳቤ እንደሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሳይተዋል። በእርግጥ እነዚህ ባህሪዎች የፅንፈኝነት መገለጫ ከሆኑ ለ50 ዓመታት የገዙት የኢትዮጵያ መንግሥትና የተቃዋሚዎችም መገለጫዎች ናቸው።

ኮሎኔል መንግሥቱ የእኔን መሪነት ያልተቀበለ ‹‹ፀረ አብዮተኛ›› ነበር የሚሉት። ጠላቶቻችንን አስተምረንና አርመን አብረን እንኖራለን ሳይሆን መፈክራቸው፣ ‹‹በጠላቶቻችን መቃብር ላይ አዲሲቷን ሶሻሊስት ኢትዮጵያ  እንገነባለን›› ነበር። ከመደምሰስ በታች ያለ ምርጫ ለማንም አያቀርቡም ነበር።

ከዚያም ቀጥሎ የመጣው ኢሕአዴግ ከእሱ ሐሳብ የተለየ ነገር ከመጣ ‹‹በእኛ መቃብር ላይ›› ይል ነበር። ዛሬም መንግሥትነት ተቀምቶ ወደ አማፂነት ተርታ ከቆመ በኋላም ደምስሰው ብቻ ነው የሚለው። የኢሕአዴግም መንግሥት አንድ እጁ ወደ አማፂነት ከተቧደነ ወዲህ ይኼኛውስ የሰውም የአስተሳሰብ ለውጥም ማድረጉን በተግባር አላሰየም፡፡

ይህንን ያህል ስለውይይቱ ካልኩኝ ይብቃና እንደ ፕሮፌሰር ቃሲም ያሉ አጥኚዎች የጻፏቸውን ጭብጦች ላካፍል።

‹‹አክራሪነትን የፍልስፍና ትንታኔ›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ፅንፈኛነትን ሦስት ዓይነት ነው ይላል። አንደኛው የርዕዮተ ዓለም ፅንፈኝነት ነው። ሁለተኛው የተግባር ወይም የጭካኔ/የአረመኔ ፅንፈኝነት ነው ሲል፣ ሦስተኛው ደግሞ የሥነ ልቦና ፅንፈኝነት ነው ይላል። ሦስቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ግድያን እንደ መፍትሔ መውሰዳቸውና ምንም ያህል መረጃ ቢቀርብላቸው የአቋም ለውጥ የማያደርጉ መሆናቸውን ነው። አንዳንድ ፅንፈኞች ሦስቱን ወይም ሁለቱን ባህሪያት ያሳያሉ።

የርዕዮተ ዓለም ፅንፈኝነት

በርዕዮት ላይ የተመሠረተ ፅንፈኝነት በሁለት ይከፈላል። አንዱ የቀኝ ፅንፈኝነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የግራ ፅንፈኝነት ነው። ለምሳሌ የሒትለር ፅንፈኝነት ቀኝ አክራሪ ፅንፈኝነት ነበር። የካንቦዲያው (Cambodia) ፖልፖትና የኮሎኔል መንግሥቱ ደግሞ የግራ ፅንፈኛ ነበር።

የቀኝ አክራሪዎች የተሻለ ዓለም ለመፍጠር ሁሉም ሰው ሰጥ ለጥ ብሎ በአንድ ዓይነት ዕርምጃ እንዲተም በማድረግ ዓለምን መግዛት እንችላለን የሚል ፍልስፍና ነው። ይህን ማሰብ በራሱ ፅንፈኛ አያስብልም። ይሁንና ይህ የገዥ ዘር የሚፈጠረው የማይፈለጉ ዘሮችን በማፅዳት ነው ብለው በማመናቸውና ይህም በጉልበት ነው የሚፈጸመው ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ለምሳሌ ሒትለር አይሁዳውያን፣ ጂፕሲ የሚባሉትን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አካል ጉዳተኛ ሆነው የተወለዱትንና ሕፃናትን ሳይቀር በማጥፋት የአርዓያን ብሔር ደም ከማይፈለጉ ዝርያዎች ደም መቀላቀልን ለመከላከል ነበር።  ስለዚህ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ውጪ ምንም ዓላማ አልነበረውም።

በናዚዎች ዕይታ የጀርመን አርዓያን ብሔር ማለት ሰማያዊ ዓይን፣ ወርቃማ ፀጉርና ረዣዥም ቆንጆና ከሁሉም ዘሮች በላይ የማሰብ አቅም ያጎለበተ ብሔር ነው ብለው ያምኑ ነበር። ይህም የበላይ ብሔር በአናሳ ደም ተበርዞ እንዳይጠፋ ይሠጉ ነበር። ስለዚህ ይህ ብሔር እንዳይጠፋ የናዚዎችን ርዕዮት ቀምረው ተገበሩ። ሌላው የርዕዮተ ዓለም ፅንፈኝነት የግራ ፅንፈኝነት ነው።

በግራው በኩል ደግሞ ያሉት ፅንፈኞች እነ ስታሊን፣ ማኦ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ፣ የካምቦድያው ፖልፖት ግልባጩን የመፍጠር ምኞት ነበር። የገዥ መደብ የሚባለውን፣ ንጉሣው ቤተሰቡን፣ ባላባቱን፣ ከበርቴውን፣ ፊውዳሊዝምንና ካፒታሊዝም የተባለውን ሁሉ በማጥፋት በጣም የምታምር፣ ሁሉም ጠግቦ የሚያድርባት፣ ጭቆናና ምዝበራ የጠፋባትና ሁሉም በነፃነትና በደስታ የሚኖርበት ኮሙዩኒዝም የሚባል ዓለም መፍጠር ነበር። በኢትዮጵያውያን መሀል ያለው የማይታረቅ ቅራኔ ነው። በአድኃሪያን መቃብር ላይ ነው አዲሲቷ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ የምንገነባው የሚል ፅንፈኝነት ነበር።

ይህም እምነት የኮሎኔል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የግራ ክንፍ ፓርቲዎችም ውስጥ ነበር። በምንም ዓይነት ፊውዳሎች፣ ፀረ አብዮተኞች፣ ባላባቶች በዚህ ምድር ላይ እንዲኖሩ ርዕዮተ ዓለማቸው አይፈቅድም ነበር። አብዮቱ ትልቅ ጣኦትና የአድኃሪያንን ደም ካልጠጣ የማይፋፋ ነው ብለው ያመኑ ይመስላሉ፡፡

በአጭሩ ሁለቱም የርዕዮት ጽንፎች የሌሎችን ሰዎች በሕይወት የመኖር መብት አይቀበሉም። ቦታ ሳይጠብ ‹‹አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ እንገነባለን›› ይሉ ነበር። በመቃብር ቦታ የሚገነባ አገር ምኑ እንደሚያምር የጠየቀ ምሁር አብዮተኛም አልነበረም፡፡ ጠላትን መግደል ሕጋዊ ሆነ። አገር የጠበቁ አርበኞች ተረሸኑ፡፡ ከዚያ አረም ነቀላው ቀጠለ። ወጣቱ ‹‹ፀረ አብዮተኛ››፣ ማርክሲስት ነኝ ያለው ‹‹ቀኝ መንገደኛ››፣ ‹‹የሲአይኤ ሰርጎ ገብ›› እየተባለ ተጨፈጨፈ።

ተማርን ያሉ ተራማጅ አብዮተኞችም ሻዕቢያ፣ ወያኔ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሰደድ፣ ኦነግ፣ ወዝ ሊግ፣ ኢጭአት፣ ወዘተ የሚሉ ቡድኖች የቡድንና የቡድን አባቶች እያሉ ተቧድነው አደኃሪያንን፣ ፊውዳሎችን፣ ፀረ አብዮተኞችን፣ መሀል ሰፋሪዎችን፣ ነፍጠኛና የሲአኤ ሰርጎ ገቦች ያሏቸውን መነጠሩ። ‹‹የእኔ ብቻ፣ የእኛ መንገድ ብቻ›› ይህንን ያልተቀበለ ደግሞ ተደመሰሰ።

ስለዚህ በውይይቱ ላይ በቀረቡት መመዘኛዎች ‹‹የእኔ ብቻ፣ የእኛ ብቻ›› ብሎ ኃይል መጠቀም የኢትዮጵያ የሃምሳ ዓመት ሥርዓተ መንግሥት መገለጫ ነበር። መቻቻልና መደማመጥ ሳይሆን አሁንም ፋሽስት፣ ጁንታ፣ ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ ያሉትን በሕይወት የመኖርና ፍትሕ የማግኘት መብትን አያከብሩም። ለመግደል የፍርድ ማዘዣ የማይጠበቅበት ማኅበረሰብ አለ።

አንድ ሰው የርዕዮተ ዓለም ጽንፈኛ ከሆነ በኋላ በሰፊው የሰሃራ በረሃ ላይ እንኳን ቢተው ጠላቴ የሚለው ካለ ዓለም አትበቃውም፡፡ ጠላቱን ከመደምሰስ ውጪ አማራጭ አያስብም። ስለዚህ መደምሰስ፣ ደምስሰው ይሆናል ጨዋታው ሁሉ።

ይህ ፅንፈኝነት በተማሪዎቹ ንቅናቄ፣ አብዮታዊ ነን በሚሉ ፓርቲዎችና በተገንጣይ ቡድኖች ውስጥ የተያዘና በተግባር የተተረጎመ ነበር። አሁንም ሕወሓት፣ ብአዴንና ኦፒዲኦ የመደምሰስ አማራጭ ብቻ እንደሌለ ነው የሚያውቁት፣ ለመጤ ለነፍጠኛ ነፍስም፣ ፍርድም፣ ዕንባም ጠብ አያደርጉም።

የተባር ንፈኝነት ወይም አረመኔነት (Methods Extremism)

ካሲም ሁለተኛው የፅንፍ መገለጫ የጭካኔ የተግባር ወይም አረመኔያዊ ፅንፈኝነት የሚለው ነው። ይህም ፅንፍ የረገጠ ምንም ርዕዮት የሌለውና የፖለቲካ ጠቀሜታ የማይመዝን የጭካኔ ፅንፍ ነው። ካሲም በመጽሐፍ ውስጥ የአይሲስ (ISIS) የሚባለውን በኢራቅ የተነሳውን ኃይል እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል። በጦርነቱ ጊዜ አንድ የዮርዳኖስ አብራሪ ይወድቅና በአይሲስ እጅ ይገባል። ይህንን የዓረብ አብራሪ በፍግርግር ብረት አስገብተው፣ በላዩ ላይ ነዳጅ አፍሰው፣ በክብሪት ለኩሰው በቪዲዮ እየቀረፁ ለዓለም ያስተላለፉትን ዓይነት ማለት ነው። ፓይለቱን መግደል ሲቻል በመጨረሻው ጥግ በረገጠ ሰቆቃ መደሰት ነው፡፡ እኛም አገር በወለጋ እየተካሄደ ያለው የንፁኃንን ሕፃናት፣ እናቶችንና አራሶች፣ ክርስቲያንኖችንና ሙስሊሞች የመግደል ልክፍት ከአረመኔያዊ ፅንፈኝነት ይመደባል።

የርዕዮት ፅንፈኝነት ከጭካኔ ፅንፈኝነት የሚለየው የርዕዮት ፅንፈኝነት ግድያን፣ ኃይልንና አመፅን እንደ መንገድ እንጂ እንደ ግብ አይደለም (Violence as a means not as an end)። ለርዕዮት ፅንፈኛ ግድያ በራሱ ግብ አይደለም። ለጭካኔ ተግባር ፅንፈኝነት ግድያንና ሰቆቃን በራሱ ግብ ነው ብሎ ይሠራል። አንድን ሰው በጥይት ከመግደል ሆዱን ቀዶ እሳት አንድዶበት ሥቃዩን አብዝቶ የጭካኔ ድርጊት መፍጠሩ በራሱ የሚያኮራው ግብ ይሆናል። በኩራት ሰው ዘቅዝቆ ሰቅሎ አብሮ ፎቶ ይነሳል። የሚገድለው ኃይል ደግሞ ዋጋ ይኑረው አይኖርም ብሎ አይመዝንም። ግድያው ጅምላ ነው።

የርዕዮት ፅንፈኝነት ጄኔራሉን ከገደለ በኋላ ወታደሩን ይማርክና ሐሳብ አስቀይሮ የራሱ ተዋጊ ኃይል ያደርገዋል። የጭካኔ ፅንፈኝነት ግን ‹ተቀበል፣ አትቀበል› የሚል ክርክር ውስጥ የማይገባ፣ የርዕዮት ግብና የሚፈጥረው ዓለም የለውም። የኢራቁ አይሲስ ፅንፈኝነት ጭካኔ ቢሆንም፣ ከአህዛብ የፀዳ የመካከለኛው እስላማዊ ዓለም መፍጠር ነበር። ስለዚህ እስልምናን ተቀበል፣ አለዚያም እገድልሃለሁ ነበር የሚለው። የኦነግ ሸኔ  ጦር ግን ተቀበል፣ አትቀበል ጥያቄ አያቀርብም። ለዚህ ነው ፅንፈኝነቱ በምክናታዊ ከርክር ሊፊታ የማይችለው።

ኮሎኔል መንግሥቱ አብዮቱን ተቀብሎ ‹‹ከጓድ መንግሥቱ ጋር ወደፊት!›› ካለና ኮቱን ቀይሮ ካሽቃበጠ ከኢሕአፓም ከሻዕቢያም ይምጣ ሥልጣን ሳይቀር ይሰጠው ነበር። ከኢሕአፓ ከድተው ለጓድ መንግሥቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ የደረሱ አሉ።

ሕወሓትም ኢሕአፓ ሆነው ተዋግተውት ወይም የኢትዮጵያ ጦር ሆነው የወጉትን ሳይቀር ወዶ ገባ በመሆን የብሔር ጥያቄ ርዕዮት ተቀበልን ሲሉ ‹‹ብአዴን›› እና ‹‹ኦፒዲኦ›› ብሎ አደራጅቶ ሥልጣን አካፍሏል። የራሱን የሥልጣንና የርዕዮት ተቀባይነት እንጂ ግድያን በራሱ ግብ ያደረገ አይደለም። ኦነግ ሸኔ ግድያዎቹን የፈጸመው በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ብሎ እያመኻኘ እንጂ፣ ተግባሩ ማንም የሚፈጽመው ግድያ የጭካኔ ተግባር ፅንፈኝነት በሚለው ነው የሚመደበው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የተስፋፋው ይህ ዓይነቱ ፅንፈኝነት ነው። ምንም ያላደረጉ ሰዎች በጎጇቸው ተከተው እየነደዱ፣ ተዘቅዝቀው እየተሰቀሉ፣ ነዳጅ ተርከፍክፎባቸው ጭራሮና ግንድ ተጭኖባቸው ሲነዱ በቪዲዮ መልቀቅ ተለምዷል፡፡ ይህ ፅንፍ  የርዕዮት መሠረት ሳይሆን የጥላቻ መገለጫ ነው ይላል ፕሮፌሰር ካሲም፡፡ ከዚህ ዓይነት ፅንፍ የቅደም ተከተል እንጂ ማንም ከመቃጠልና ከመታረድ አይድንም፡፡ መፍትሔው የመግደል አቅሙን ማሳጣት ብቻ ነው፡፡

ነ ልቦና ንፈኝነት

እንደ ካሲም ሦስተኛው ፅንፍ የሥነ ልቦና ፅንፍ ነው። ይህም ንፁህ ብሔር፣ ንፁህ ሃይማኖት፣ ማለትም ከምንም ያልተነካካ ብሔር ወይም ሃይማኖት መፍጠር ነው። ለመቻቻል ምንም ቦታ የለውም።

ለምሳሌ ናዚዎች ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል ከይሁዳውያን ጋር የሚኖሩበት ዓለም አይፈልጉም ነበር። ምክንያቱም የይሁዳውያን ደም በዚህም በዚያም ብሎ ከአርያን ብሔር ደም ጋር ሊቀላቀል ይችላል የሚል ፅኑ ፍራቻ ስለነበራቸው ነው። ስለዚህ ከዚህ ሥጋት መዳን የሚቻለው ‹‹የመጨረሻው መፍትሔ›› ያሉት ‹‹እኛና እነሱ›› ብለው መስመር ሠርተው እነሱን እንደ ተባይ ማጥፋት ብቻ ነበር። ይህ የኛና የእነሱ አባዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፅንፈኝነት መገለጫ ነው። እነሱ ከመጥፋት ውጪ ብዙም አማራጭ የላቸውም፡፡ አንድ ሰው በአይሲስ ቁጥጥር ውስጥ ቢወድቅ እስልምናን ከተቀበለ አይሞትም። ከእነሱ ወደ እኛ መዛወር ይፈቀድለታል። አንድ ይሁዲ ግን የአርያን ብሔር መሆን በምንም ዓይነት አይቻለውም። የኢትዮጵያን ፅንፈኝነት አንድ አማራ ተብሎ የተፈረጀ ሰው ምን ሰማይ ቢቧጥጥ ኦሮሞ ሆኖ ተቀባይነት አያገኝም፣ ምሕረትም አያገኝም፡፡ በኦሮሚያ ፅንፈኝነትን አስፈሪ የሚያደርገው ይህ ነው።

ለምን ሰዎች የሥነ ልቦና ንፈኝነት ውስጥ ይወድቃሉ?

ይህንን ካሲም የበላይነት ወይም የበታችነት ላይ የተመሠረተ የተበቃይነት ሥነ ልቦና ነው ይላል።  አሁን በእኛ አገር ያለው ፅንፈኝነት የዚህ ዓይነት ፅንፈኝነት ነው፡፡  ‹‹እኛና እነሱ›› የሚለው በመንግሥትና በሕገ መንግሥት የታገዘና በደንብ ተቀምሞ ለወጣቱ የተሰጠ የበታችነት ስሜት ውጤት ነው።  ለዚህ ነው አንድ ነገር ኮሽ ያለ ቀን ጎረቤት ጎረቤቱን ለማረድ ካራውን ይዞ እሳት ጭሮ ገድሎ ንብረቱን የሚያቃጥለው። እነሱ መጥፎ እኛ ጥሩ የሚል የሥነ ልቦና ቀውስ ነው፣ ሌላውም ሲታረድ ቆሞ ቪዲዮ የሚቀርፀው።

 

የሥነ ልቦና ፅንፈኝነት የዘር መቀላቀልን መፍራት፣ ‹‹ዲቃላ ነው›› በማለት እንደ ስድብ በመፈክርነት ቦሌ መንገድ ላይ የዛሬ ሁለት ዓመት የሰማነው ነው።  የሃይማኖት መበረዝ፣ ከሌላ እምነትና ጎሳ የፀዳ ዓለም መፍጠር መፈለግ ይታይበታል፡፡  ለምሳሌ ጀርመኖች ይሁዳውያንን ከአገራቸው ማባረር ይችሉ ነበር። የስፔን ካቶሊኮች እኮ የአይሁዳውያንን ብሔር በመካከለኛው ዘመን ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ፣ ወይም ስፔንን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል። ናዚዎች ግን የይሁዳውያንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ወደ ጋዝ ማፈኛ ከተው ስድስት ሚሊዮኖችን ፈጁ።

አሁን እኛ አገር አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ሰዎች የሚኖሩባት አገር ብትፈጠር፣ ጭቆና የሚጠፋና እኩልነት የሚሰፍን የሚመስላቸው ብዙ ናቸው። ትግርኛ ብቻ የምትናገር አገር፣  ኦሮሚኛ ብቻ የምትናገር አገር፣ ሲዳሚኛ ብቻ የምትናገር አገር ብንፈጥር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ይፈጠራል ብሎ ማሰብ ነው።

ክልልን ከጉራማይሌ ለማፅዳት የተሻለ ዓለም ይፈጥራል የሚል የሥነ ልቦና ቀውስ ነው።  ጃዋር ተከበብኩ ያለ ጊዜ ጠቅላዩ እሱ ዲቃላ ነው የሚባል መፈክር በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተሰምቷል። ይሁንና ሶማሊያ፣ የመን፣ ሰሜን ኮሪያና የዓረቡ ዓለም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። ሶማሌ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ስላላት ከኢትዮጵያ፣ ከህንድና ከአሜሪካ አልበለጠችም። ይሁንና ኦሮሚያን ነፃ አወጣለሁ የሚለው አካል በሶማሊያ የሚቀና ይመስላል፡፡ አማራን፣ ጉራጌን፣ ጌዲዮን፣ ወላይታን፣ ከንባታን፣ ትግሬን  ካፀዳ በኋላ ኦርቶዶክስን ወይም እስልምናን ባፀዳ ደግሞ በምድር ላይ ገነት እፈጥራለሁ ብሎ ማሰብ የሥነ ልቦና ፅንፈኝነት ነው።

በተቃራኒው አሜሪካ አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሲዳሚኛ፣ ጃፓንኛ፣ ቻይንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽኛና የመላው ዓለም ቋንቋ ያለባት ገናና አገር ናት፡፡ ቋንቋዋ  የሰላምና የብልፅግና መገለጫ ቢሆን ኖሮ የኦሮሞም፣ የሲዳማም፣ የትግራይም ነፃ አውጪ መሪዎች ወደ ሶማሊያ እንጂ ወደ ጉራማይሌ አሜሪካ  ባልተሰደዱ ነበር።  ስለዚህ የዘር፣ የቋንቋና የሃይማኖት መበረዝ ሥጋት ሥነ ልቦናዊ ቀውስና ፅንፈኝነት ነው፡፡

የፅንፈኝነት መገለጫዎች

የሦስቱ ፅንፈኝነት መገለጫቸው በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ካልሆነ የትም ቦታ ቤት አንሠራም ማለታቸው ነው፡፡ አንድ ሰው ፅንፈኛ ሆነ ማለት ምክናታዊነቱን አስወገደ ማለት ነው። ምንም ዓይነት መረጃና ምንም ዓይነት ምክንያታዊነት፣ ምንም ዓይነት ለቅሶ፣ ምንም ዓይነት መማፀን ሐሳባቸውን አያስቀይረውም። ፅንፈኝነትን በመታገልና በኃይል ፍላጎቱን ማስፈጸሚያውን  ከማሳጣት ውጪ በምንም ዓይነት ምክንያታዊ ክርክር ማስቀየር አይቻልም፡፡ የናዚዎችን ፅንፈኝነት ማስቆምና ከይሁዳውያን ጋር በሰላም የሚኖሩበት ዓለም መፍጠር የማይቻል ነበር፡፡  ሒትለር ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፋችሁ አቃጥሉኝ እስካለባት ደቂቃ ድረስ ስለይሁዳውያን ያለውን አመለካከት አልቀየረም።

ለናዚዎች የፅንፈኝነታቸው ምክንያታዊ አለመሆን የሚያሳይ አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ለናዚ ፓርቲ አባላት አሁን ዘራችሁ ወደ ላይ ቢቆጠርና በዘራችሁ ውስጥ ይሁዳዊ ቢገኝ ምን ትላላችሁ ብለው ተጠይቀው ነበር።  መልሳቸው በዘር ማንዘራችን ይሁዳዊ ካለ ‹‹እኛም ወደ ጋዝ ማፈኛው ወርውሩን›› ነበር ያሉት። ይህ እውነተኛውና ጥግ የደረሰው ፅንፈኝነትና ከምክንያታዊነት መፅዳት ምልክት ነው። የሃይማኖትም የርዕዮትም ፅንፈኞች ልጆቻቸው ወይም ሚስታቸው የሃይማኖት ወይም የርዕዮት ለውጥ አድርገው ቢያገኟቸው ራሳቸው ነው የሚገድሏቸው።

ፅንፈኝነት በአጭሩ ቢተረጎም ምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ፣ በስሜታዊ አዕምሮ ብቻ መመራትና የራስን ስሜት እንደ መጨረሻው እውነትና መንገድ መውሰድ ነው፡፡ ይህንን በሁሉም ላይ ለመጫን ኃይልን መጠቀም ነው። ስለዚህ አገራችን የፅንፈኞች ከተማ ከሆነች ምን አደከመን ትሉ ይሆናል። ፅንፈኛን ማሳመን አይቻልም፡፡ ይሁንና ኤሪክ ሆፈር የሚባል ጸሐፊ አንዱን ዓይነት ፅንፈኝነት ወደ ሌላ ዓይነት ፅንፍ ማሸጋገር ይቻላል ይላል። ምክንያቱም ፅንፈኝነት ምክንያታዊነት ሳይሆን እምነት ነው። ስለዚህ አንድ ፅንፈኛ አማኝን ምክንያታዊ ማድረግ ሳይሆን፣ ወደ ሌላ ፅንፍና እምነት መቀየር ይቀላል ይላል ኤሪክ ሆፈር።

አንድ ፅንፈኛ የኮሙዩኒስት በአጭር ቀን ውስጥ የፋሺዝም ፅንፈኛ ለመሆን ብዙ ቀን አይወስድበትም። ዛሬ ፖለቲካ የነበረ አክራሪ ሃይማኖተኛ ፅንፈኛ ለመሆን ጊዜ አይወስድበትም። ለምሳሌ አቶ ታምራት ላይኔን እንደ ምሳሌ ማቅረብ ይሻላል። ፅንፈኛ የማይችለው ራሱን መሆንና ምክንያታዊ መሆን ብቻ ነው። በእኛ አገር በ1970ዎቹ ብዙ ፅንፈኛ አብዮተኞች እግዚአብሔር የለም፣ ሃይማኖት የሕዝብን ማደንዘዣ ሀሺሽ ነው ይሉ ነበር፡፡ ከአብዮተኞች መሁል ሲገለሉ ሌለ ቡድን ፈልገው የዚያ ቡድን ፅንፈኛ ነው የሆኑት።

ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች ብለው ያስተማሩና ዓለም አቀፍ እውነትን በግድ በጅራፍ ሁሉም እንዲዘምር ያስገደዱ አንዱ ቡድን ሲፈርስ በማግሥቱ የብሔር መሪ ሆነው፣ ዓለም አቀፋዊነት ይቅርና ከአገርም ወርደው የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝ ሆኑ። በሚቀጥለው ጽሑፍ ፅንፈኝነት እንዴት ይፈጠራል የሚለውን እናያለን። የፅንፈኝነት ማርከሻዎችን ከመጻሕፍቱ ለቅሜ አቀርባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም የማማከርና የኮሙዩኒኬሽን ኤጀንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው yaredhm.yhm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

173707
Previous Story

ሕዝብ ቁጣውን ቀጥሏል፤ የአዲስ ድምጽ ቃለ ምልልስ

Cry Ethiopia 1
Next Story

‘‘እናቴ ሀገሬ በጠና ታመሻል፤ እግዚአብሔር ይማርሽ!!’’

Go toTop