ኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ አድቮከሲ ኔትወርክ እንዲሁም አንድነት ለኢትዮጵያ በአማራ ወገኖቻቸን ላይ፣ በድጋሜ አማራ በመሆናቸው ብቻ የደረሰባቸውን አሰቃቂ የጅምላ ግድያ በይፋ ይቃወማል፣ ይወቅሳልም።
ትናንት ልንገላገለው ሲገባ ዛሬም ያልተገላገልነው በሃይል የተጫነብን ቀንበር ዘረኝነት እና ባለተራነት እዳ የአማራው፣ የኦሮሞው፣ የሶማሌው፣ የአፋሩ፣ የትግሬውም እዳ ነው። ይህ ቀንበር የጉራጌ፣የሱርማው፣ የሲዳማው ነው። ይህ ሸክም የጋምቤላው የደራሼው የከፋው የከንባታው፣ የሃዲያው ሸክም ነው። ትናንት ከትናንት ወዲያ ልናራግፈው ልንገላገለው ሲገባን ለዛሬ ያደረ ሸክም፣ ቀንበርና እዳ። ትናንት እና ከዚያ በፊት መስራት ሲገባን ሳይሰራ ለዛሬ ያደረ የቤት ሥራ!!! ዘረኝነት! ያውም በህገ መንግስት የተደገፈ!! ሁለት ሳምንት ባልሞላው ግዚያት ሌላ ሰቆቃ ሌላ ግድያ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በወለጋ ተፈፅሞ ማየት እጅግ ይከብዳል።
በአማራ ወገኖቻቸን ላይ አማራ ስለሆኑ ብቻ ሰቆቃ መፈፀም ይቅር የማንለው ወንጀል ነው። ነገ ተጠያቂነትን ማስከተሉ ፈጽሞ አይቀርም። በአማራም ብሄር ሆነ ይህንን የወንድሞቻቸውን ሞት ለመከላከል በሞከሩ የኦሮሞ ብሄር ወገኖቻቸን ላይ እየደረሰ ባለው ሰቆቃ እጃችሁን ያስገባችሁ ሁሉ ተገቢውን ቅጣት የምታገኙበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ዜጎች እንኮን በሀገራቸው ምድር ቀርቶ በባእዳን ሀገራት ተንቀሳቅሰው ሲኖሩ የሰውነት ክብራቸው ይጠበቅላቸዋል፤ በሀገራችን ግን ትናንት በህወሃት ተዘጋጅቶ በተሰጠን ህገ መንግስት ምክንያት በዘር ተቦድነን አማራ ትግሬ ኦሮሞ ክልሌ እየተባባልን ይሄው ስንፋጅና ስንገዳደል ይታያል።
የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ ካወንስል ዘረኛነት መቃወም እና ህገ መንግስት እንዲቀየር መጣር ለራሱ ክብር ከሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው ና የሚመለከተውን አካል ግንባር ቀደም አድርጎ ለችግሮቹ መፍትሄ እንዲሰጥ እንጠይቃለን!!!
ዘረኝነት አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ኋላቀር አስተሳሰብ አንድ ቡድን በሃብትና ሥልጣን የበላይነትን የሚይዝበት አድሎዓዊ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ እ.ኤ.አ 1965 ወጥቶ ከ1969 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የተባበሩት መንግሥታት የሁሉም ዓይነት የዘር-መድሎዎች ማስወገጃ ኮንቬንሽን የዘር- መድሎን በሚከተለው አኳኋን ይተረጉመዋል፡፡ የዘር-መድልዎ ‹‹…ዓላማው ወይም ውጤቱ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን በፓለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ ወይም በሌላ ማናቸውም የማኅበራዊ ሕይወት ዘርፍ ውስጥ በእኩል መጠቀምን የሚያጠፋ ወይም የሚያሰናከል በዘር፣ በቀለም፣ በአስተሳሰብ፣ በብሄር ወይም በጎሳ መነሻነት የሚደረግ አድልዖ፣ ማግለል፣ መከልከል ወይም የተለየ አሰራርን መጠቀም ነው፡፡›› ከላይ እንደተገለፀው የተባበሩት መንግሥታት ባስቀመጠው ትርጓሜ መሠረት የዘር መድልዎ የሚፈፀመው ዘርን ወይም አስተሳሰብን መሠረት አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ በአገራችን ሁለቱንም መሠረት ያደረገ የዘር መድልዎ እየተደረገ ነው፡፡ የአማራ እናቶች፣ አባቶች፣ በእድሚያቸው ምንም የማያውቁ ህፃናት ቦርቀው ሳይጨርሱ በዚሁ በሽታ የዘር ሰለባ እየሆኑ ነው። ይህ አለም አቀፋዊ ወንጀልና የዘር ጭፍጨፋ ነው!
ይህም በሀገራችን ኢትዮጵያ ሆነ በውጪ ሃገራት በዘረኛነት ምክንያት በደረሰው በአማራ ብሄር ተወላጆች ጭፍጨፋ ላይ ለሀገሩ የሚቆረቆርና ለሰው ልጆች ክብር ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አስቆጥቷል። ከኢትዮጵያዊያንም አልፎ ለራሳቸው ጠባብ ጥቅም የህወሃትን ወንጀሎች በቸልታ የሚመለከቱትን የውጭ መንግሥታትንም አስደንግጧል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ቀርበው የሰጡት ምላሽ የችግሩ መፍትሄ ከመሆን ይልቅ የሚያባብስ እና የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ቡድኖች የሚያስቆጣ ፍትሃዊ ያልሆነ መልስ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመናገር እንወዳለን። በህዝብ የተመረጠ መንግስት የመረጠውን ህዝብ ቁጣና ብሶት አልሰማም ያለ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በውስጥም በውጪም የህዝብ አመኔታን ያሳጣዋል።
መንግስት የህዝብን ጩኸት ጀሮ ዳባ በማለት የሚያድበሰብሰው እና መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚሄድበት አካሄድም የወንጀሉ ተባባሪ ያደርገዋል። ስለሆነም የዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብትን የነፈገውን አካል በአስቸኮይ ለፍትህ ማቅረብ ግድ ይለዋል። ለዛም ነው ካውንስላችን ዜጎችና ሃገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ፈውሱ ህዝብ የተሳተፈበት ህገመንግስትን ማሻሻል የተሻለ ነው የምንለው።
በመጨረሻም መንግስት የጀመረው ለውጥ ግብ እንዲመታለት የህዝብ ደህንነት ዋስትና ቁልፍ በመሆኑና ህዝብ ከሌለ ሀገርም ስለማይኖር ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች የአስቸኮይ ጊዜ አዋጅ በማሳለፍ መስዋእት በመክፈል ከዘረኝነት አደጋ ኢትዮጵያን መከላከል አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመውም የምንወዳት፣ ተከባብሮ እና ተጋምዶ የነበረውን ህዝባችን ለመከፋፈል እንደጥሩ አጋጣሚ ለሚጠቀሙ አክራሪ ዘረኞችም መመቻቸት የለብንም። ይህ ጊዜ ያልፋል፤ የትላልንት የህወሃት ጊዜ ምስክር ነውና እባካችሁ አንድ እንሁን በጋራ ተያይዘን ዘረኝነት በህገ መንግስት እንዲታገድ እንስራ እናለልን።
የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶችም ይህ እያባላን ያለውን ህገ መንግስት እንዲቀየር እንደምትሰሩ ቃል ግቡ። መንግስት የመንግስትነት ቁመነዋን የሚያስተካክለው የህዝብ ድምፅ፣ እሮሮ መስማት የቻለ ጊዜ ነውና ለሀገር ግንባታ፣ለዜጎች እኩልነት፣ ለሀገር ሉአላዊነት አብረን በመከራም በችግርም እንድንዘልቅ፣ የዜጎችን የመኖር መብት አለም አቀፋዊ ዋስትና በኢትዮጵያ ምድር ማረጋገጥ አለበት። ወንጀለኞችን ለፍትህ በማቅረብ እና ሽብርተኞችን በማደን ሌላ አደጋ እንዳይመጣ ቀን ከሌት መስራት አለበት። ካውንስላችን በኢትዮጵያ ምድር በተፈፀመው ድርጊት ማዘን ብቻ ሳይሆን ከማዘን ባሻገር በውጪ ሀገር የድርጊቱ ተሳታፊዎች እንዲጠየቁ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።
በመሆኑም መንግስት የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ኮሚሽን ጨምሮ በተቋቋመ ገለልተኛ አካል የደረሰውን ወንጀል አጣርቶ: ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን። በመንግስት መዋቅር ያሉ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ በማናቸውም ደረጃ ስልጣን ላይ ያሉ አመራሮቹን አጣርቶ ተጠያቂ እንዲያድረግ እና ይህንንም ለህዝብ ግልፅ እንዲያደርግ በአፅኖት እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ
ኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣
የኢትዮጵያ አድቮከሲ ኔትወርክ ፣
አንድነት ለኢትዮጵያ ፣ ግሎባል ክርስቲያን ኢትዮጵያን ሲስተር ሁድ- አውስትራሊያ