ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ የት እንደቆየ እንደማያውቅ ተናገረ!!

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሣ እየበላ ከነበረበት በተለምዶ ፈረንሣይ ከሚባለው ሠፈር፣ ጊዮርጊስ ከተባለ ምግብ ቤት ለጥያቄ ትፈለጋለህ ብለው አፍነው የወሰዱት የፀጥታ ሰዎች በማይታወቅ ቦታ ለሳምንት አቆይተው እንደለቀቁት ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ለሪፖርተር ተናገረ፡፡ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ወደ አራት ሰዓት በተለምዶ ገላን እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎቹ እንደለቀቁት የገለጸው ገጣሚው፣ በቆይታው ወቅት የተለየ ማሰቃየትም ሆነ እንግልት እንዳልተፈጸመበት አስረድቷል፡፡

ስለታሰረበት ሁኔታ ለሪፖርተር ያስረዳው ገጣሚ በላይ፣ ባለሥልጣናት በሚሄዱበት ቪ8 እየተባለ በሚጠራ መኪና በመጡ ሰዎች ምሣ ከሚበላበት ቦታ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ መወሰዱን ገልጿል፡፡ መኪና ውስጥም ሆነ በወሰዱኝ እስር ቤት የፊት መከለያ ጭንብል አጥልቀው እንዳቆዩት ያስረዳው በላይ፣ ለመፀዳዳት ካልሆነ በስተቀር መውጣት ሳይፈቀድለት በጨለማ ክፍል ውስጥ መቆየቱን ተናግሯል፡፡ ‹‹ከቤተሰብም ሆነ ከማንም ጋር በስልክም እንድገናኝ አልፈቀዱልኝም፡፡ ሲወስዱኝ ያዩ ሰዎች በመጠቆማቸው ይመስለኛል መታሰሬም የታወቀው፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

ስለተጠረጠረበት ወንጀል ወይም ለእስራት ስላበቃው ምክንያት የፀጥታ ሰዎቹ ነግረውት እንደሆነ የተጠየቀው ገጣሚ በላይ፣ ስለምርመራው ብዙም ማውራት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ‹‹የራሳቸውን ጥያቄ ጠይቀውኛል፡፡ እኔም መልስ ነው የምለውን መልሼላቸዋለሁ፤›› ሲል የተናገረው ገጣሚው፣ በስተመጨረሻ በማያውቀው ሁኔታ ሰኞ ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ ፊቱን ጭንብል በማልበስ በመኪና ወስደው ገላን በሚባል አካባቢ በማውረድ፣ ‹‹ፊትህን ሳታዞር ቀጥ ብለህ ሂድ›› ከሚል ትዕዛዝ ጋር እንደለቀቁት አስረድቷል፡፡

‹‹ሕግና መንግሥት ባለበት አገር ሰውን አፍኖ ፊትን ሸፍኖ ባዶ ክፍል ውስጥ ለሳምንት ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም፤›› ሲል የተናገረው በላይ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ቢረጋጉም ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በከባድ ጭንቀትና ሐዘን ውስጥ መቆየታቸውንም አመልክቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ አውቶቡስ ተገልብጦ 6 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

ገጣሚ በላይ በተለይ መንግሥትን በሚሸነቁጡና ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ጠንካራ ትችት በሚያቀርቡ የግጥም መድብሎቹ ይታወቃል፡፡ በማኅበራዊ አንቂነቱና በህልውና ዘመቻው ወቅት በግንባር ለሚፋለሙ የኢትዮጵያ ኃይሎች ዕርዳታ በማስተባበር የሚታወቀው ገጣሚው፣ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተቺ ግጥሞችን ሲጽፍ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

ምንሊክ ሳልሳዊ

1 Comment

  1. የበላይ በቀለ ወያ ወንጀል አንድ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ መጽናቱ። ወላዋዪችና ፍርፋሪ ለቃሚዎች በሚያሽቃብጡባት ሃገር ላይ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የሆነ የተዋጣለት ገጣሚ ነው። ያው እርሱ በአንድ ግጥሙ ላይ እንደነገረን “ሽንኩርት የሚልጥና ሽንኩርቱን የገዛ በሚያለቅሱባት” ምድር ላይ እውነት ይኖራል ብሎ ማመን ራስን ማጃጃል ነው። ሰው ለምን ይታፈናል? እንዴት ያለ ዲሞክራሲ ነው እያፈነ ለቀናት ሰውሮ ሰውን የሚለቀው? ይህ ነው መደመር እንዴ? ሃሳብን እየቀነሱ፤ ሰውን ያለ ሥራው እየወነጀሉ? የ 70 ዓመት ሽማግሌ አስሮ አካኪ ዘራፍ ከሚል ሙት መንግስት ምን ይጠበቃል? መልሱ ምንም ነው። መታሰር የሚገባቸው፤ በህብረተሰብ መካከል መከራና ችጋርን ሞትን የሚዘሩ ስንት እንቅፋት ፈጣሪዎች እያሉ ይህን ለጋ የሃገር ፍሬ መሰወርና ቤተሰብን ማስጨነቅ ምን የሚሉት የመንግስት ዘይቤ ነው? ባለወረፋው የኦሮሞ ስብስብ መቼ ይሆን ካለፉት ገዥዎቻችን ውድቀት የሚማሩት? የሰው ልጅ በመጻፉ፤ በመግጠሙ፤ በብ ዕሩ በመታገሉ ሃሳብን በሃሳብ ሞገተ እንጂ ነፍጥ አልያዘ። መንግስትን ምን አስፈራው? ድፍረት ካለው መቀሌ ሂዶ አይፋለምም እንዴ?
    ግን እንረዳለን፤ ሰውን አንገት ለማስደፋት፤ የህዝባችን እይታ ለማዳከም ሆን ብሎ የተቀረጸ የኦሮሞዎች ወጥመድ ነው። ሌላ የለም። እውቁ ኢትዮጵያዊ ጄ/ሙሉጌታ ቡሊ ከረጅም ዘመን በፊት አሉ የተባሉትን ልጥቀስና ይብቃኝ። መወለድ ብቻውን ሰውን ሰው አያረግም። የትውልድ ሃረግም ቢቆጠር ብዙ ወደ ኋላ አያስኬድም። የሁላችንም ምንጭ አፈር ነው። ወደ አፈርም እንመለሳለን። አሁን ጊዜው ጠላት ሃገራችን የለቀቀበት እኛም በርትተን የምንሰራበት እንጂ በሆነ ባልሆነው አተካራ የምንገጥምበት ጊዜ አይደለም” ነበር ያሉት። ያ ጊዜ ረጅም ነው። ሃገሪቱ ግን አሁንም አረንቋ ውስጥ ናት። ምን ይሻለን ይሆን? መቼ ነው ጥይት ወደ ሰማይ እየተኮስን ማቅራራታችን የሚያቆመው? ያ ጊዜ ይመጣ ይሆን? አይመስለኝም። እንኳን ተፈታህ ወገኔ ደግመው እንዳይጠልፉህ ተጠንቀቅ። በርታ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share