July 6, 2022
10 mins read

በምክር ቤቱ የዛሬ ውሳኔ ላይ የተቃውሞ ሀሳቤ – (ዶር ደሳለኝ ጫኔ የተወካዮች ም/ቤት አባል)

290911697 3240590282925440 1562147288998232031 nበቄለም ወለጋ የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ ላይ እንዲወያይ እና በአማራ ላይ በልዩ ሁኔታ የደረሰውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለይቶ ማውገዝ ሲገባው በአማራዎች ላይ የተፈፀመውን ተከታታይ ጅምላ ጭፍጨፋ ለማድበስበስና ለመሸፋፈን በሚመስል መልኩ «በአገራችን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ በኦሮምያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብ/ብ/ሕ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራ፣ በአፋር እና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በንጹኃን ዜጎቻችን እንዲሁም ፀጥታና ደህንነት ለማስከበር በተንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ላይ ለደረሰው የህይዎት መጥፋት አስመልክቶ የኢፌዴሪ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጊቱን እጅግ በጣም በመኮነን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኗል» ይላል።

የዚህ ውሳኔ ሀሳብ መግቢያ በመሰረቱ የውይይቱን መነሻ ጉዳይ ማለትም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአማራዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ጠርቶ ከማውገዝና ጉዳዩ ወደ ለየለት የዘር እልቂት እንዳይገባ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጉዳዩን አቃሎ ከሌሎች የንፁሀን ግድያዎች ጋር አዳብሎ ያቀረበ ነው። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የንጹሀን ሲቪሎች አሳዛኝ ግድያ አለ። ይሄም በጥብቅ ሊኮነንና ሊወገዝ የሚገባው ሲሆን መንግስትም ጥቃት ፈፃሚዎችን ተከታትሎ ወደ ህግ የማቅረብ ግዴታ አለበት።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈፀሙ ግድያዎች በአማራው እንደተፈፀሙት የብሔር ማንነትን ለይተው የተፈፀሙ ወይም ንጹሀን በብሄር ማንነታቸው ብቻ የተፈፀሙ አይደሉም። በኢትዮጵያ ውስጥ በማንነታቸው ተለይተው እየተገደሉና ጭፍጨፋ እየተፈፀመባቸው ያሉት የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው።

በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው በመንግስታዊ መዋቅሩ ድጋፍ አማራን ከወለጋ፣ ከ«ኦሮምያ» ማጽዳት ነው። አማራን በጅምላ መፍጀት ነው። በአጭሩ አይናችን እያየ እየተፈፀመ ያለው አለምአቀፍ ወንጀል የአማራ የዘር ፍጅት ነው።

የዚህ የዘር ፍጅት ዋነኛ ጠንሳሽ (master mind)፣ አዛዥና አስፈፃሚ ደግሞ በመንግስት መዋቅረወ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ብልጽግና አመራሮችን እንደሚጨምር ከበቂ በላይ መረጃም ይሁን ማስረጃ አለ። ምክር ቤቱ መሸፋፈን የፈለገውና ከሌሎች ግድያዎች ጋር አዳብሎ ለማሳነስ የሞከረው ይሄንን በመንግስት መዋቅር ጭምር የሚፈፀምን የዘር ጭፍጨፋ ነው። በአጭሩ በአማራ ላይ የተፈፀመውን በመንግስት መዋቅር ጭምር የሚደገፍ ጅምላ ፍጅትና የዘር ማጥፋት ለይቶ ከማውገዝና ወንጀሉን በስሙ ከመጥራትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ «ዜጎች» በሚል የወል ቃል እንዲሸፈን ነው የተደረገው። ይህ ደግሞ ምክር ቤቱን የዘር ፍጅትን በመካድ በታሪክ ተጠያቂ የሚያደርገው አካሄድ ነው።

2ኛ) የቀረቡት የውሳኔ ሀሳቦችን በተመለከተ ያለኝ ተቃውሞ

2.1. ውሳኔ ሀሳብ «ሀ» ላይ «በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ» ይላል። በምዕራብና በቄለም ወለጋ በሁለት ቀናት ጥቃቶች ብቻ ከ1500 እስከ 2000 የሚጠጉ አማራዎች በጅምላ ተጨፍጭፈው በማንነታቸው ብቻ የዘር ማጥፋት እንደተፈፀመባቸው እየታወቀ ይህ ጉዳይ አንድ ወይም ሁለት ሰው እንደተገደለ ሁሉ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት መታለፉ በምክር ቤቱ ታሪክ አሳዛኝና ትዝብት ውስጥ የሚጥለው ነው።

ለመናገር ዕድል የተሰጣቸው በርካታ የምክር ቤት አባላት እንደጠየቁት ቢያንስ 3 ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ታውጆ፣ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ምክር ቤቱ ሊወስን ይገባው ነበር። በሺዎች ሲቪሎች ተጨፍጭፈው የሀዘን ቀን ያላወጀ ፖርላማ መቼ ሊያውጅ ይችላል?

2.2. በዚህ አሰቃቂ ወንጀል ውስጥ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትን ተጠያቂ እንዲደረጉ የውሳኔ ሀሳብ ከማስተላለፍ ይልቅ እነዚህን አካላት ለመከላከል በሚመስል መንገድ «በሲቪል ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ያስከተሉ እና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ» በሚል አልፎታል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ይሄንን ጭፍጨፋ የሚመሩ፣ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ተባባሪ የሆኑ እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ ሀሳብ በውሳኔው ውስጥ አልተካተተም። ከዚያ ይልቅ በውሳኔ ሀሳቡ «3/ሐ» ላይ «በየደረጃው ያለው አመራር፣ የፀጽታና የፍትሕ አካል የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በጥብቅ እንዲያስከብር እና አጥፊዎቹ ለህግ ተጠያቂነት እንዲቀርቡ እንዲደረግ» በማለት አልፎታል።

2.3. በውሳኔ ሀሳብ «3/ረ» ላይ ደግሞ «በምክር ቤቱ የበላይ አመራር የሚሰየሙ፣ ስብጥሩ ሁሉንም ብዝህነቶች ታሳቢ ያደረገ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን በማጣራት ምክር ቤቱ እና ለህዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማስቻል፣ እንዲሁም ለቀጣይ ርምጃዎች የሚረዳ ምከረ ሀሳብ እንዲቀርብ ተወስኗል» ይላል።

በመሰረቱ የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። የዘር ማጥፋት ወንጀል ደግሞ በባህሪው አለማቀፋዊና ውስብስብ የምርመራ ሒደትን እንዲሁም የህግ እውቀትን የሚጠይቅ ወንጀል ነው። ከምክር ቤቱ በሚቋቋም ልዩ ኮሚቴ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊመረመር አይችልም። የተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ም/ቤቱ የሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎች በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55ም ይሁን በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 08/2006 ላይ ስልጣን አልተሰጠውም። ይህ አይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊመረመር የሚችለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወይም አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሚሰይማቸው በአለም አቀፍ ገለልተኛ የህግ ባለሙያዎች ወይም በፍትሕ ሚ/ር ስር ልዩ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ተቋቁሞ ነው።

በመጨረሻም ባለፈው በምክር ቤቱ ላይ ይህ ጉዳይ ውይይት እንዲደረግበት ጥያቄ ያነሳሁ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ቀን በዝግ ስብሰባ ሲደረግ አስተያየት ለመስጠት ተደጋጋሚ ጥያቄ ባቀርብም በእልክ እና በቀል በሚመስል መንገድ ተከልክያለሁ። ለሚጨፈጨፈው ወገናችን ድምጽ ለማሰማት የምናደርገው ትግላችን ግን በተገኘው መንገድ ሁሉ የሚቀጥል ይሆናል።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop