June 26, 2022
21 mins read

የመንግሥት ዋና ተግባርና ሃላፊነት የሕዝብን ጸጥታና ደህንነት መጠበቅ ነው! “ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ እለበለዚያ ግን ድንጋይ ነዉ ብለዉ ይጥሉሀል”

ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም.

የአንድ ሀገር መንግስት ተቀዳሚ እና ዋነኛ ሃላፊነቱ የሚያስተዳድረዉን ሕዝብ ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ ሲሆን፡ በአንጻሩ ደግሞ ሕዝብ መንግስት ያወጣውን ሕግ፣ ደንብ እና ስርአት ተከትሎ የመኖር መብትና ግዴታ አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ መንግስት የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ ከተሳነዉ፡ መንግስት በሕዝብ ዘንድ የተቸረዉን ቅቡልነት እና አመኔታ ስለሚያጣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀረ በመንግስትነቱ እንደማይቀጥል እሙን ነዉ።

ከዚህ በመነሳት ከ አራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ በተከሰተዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ አጥቢያ ወደ ስልጣን የመጣዉ በ ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራዉ የብልጽግና ድርጅት ተቀዳሚ ተግባሩን መወጣት እንደተሳነዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ባለፉት አራት አመታት በሀገራችን ከተከሰቱት ዘግናኝ የዜጎች እልቂት፣ መፈናቀል እና ስደት በጥቂቱ ዋና ዋና ያልናቸዉን በመዘርዘር ለማሳየት እንሞክራለን። እንዲሁም በነዚህ አራት ዓመታት መንግስት የፈጸማቸዉን ስኬታማ ከሚባሉ ስራዎቸ ከብዙ በጥቂቱ በተጓዳኝ በመዘርዘር ለንጽጽር እንዲረዳ ለማሳየት እንሞክራለን።

ለዉጡን ተከትሎ መንግስት በሀገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ያሉን ማናቸዉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሀገራቸዉ ዉስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሰላም ዘንባባ የያዙ እጆቹን ከዘረጋበት ቅጽበት አንስቶ ብሔር እና ዘዉግ ተኮር ግጭቶች ወደ ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ ተሸጋግረዉ ይሄዉ ዛሬ ከስድት መቶ (600) በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎቻችን በአማራነታቸዉ ብቻ እንደ ዶሮ በወለጋ ታርደዋል።

•ከለዉጡ በፊት የነበረዉን የኢህአድግ መንግስት ከሀገር ዉጭ ሆነዉ በትጥቅ ትግል ሲታገሉ የነበሩት የግንቦት 7 እና የኦሮሞ ነጻ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት በሳምንታት ልዩነት ሲመለሱ ለአቀባበላቸዉ በተዘጋጀዉ ትእይንት ላይ የተገኙት ደጋፊዎቻቸዉ በያዙት ሰንደቅ ዓላማ ላይ በተነሱ አለመግባባቶች በሰዉ አካል እና በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር ሊመጣ ላለዉ የብሔር እና የዘር ተኮር እልቂት ማሟሻ እና እርሾ ሆኗል።

•ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ በምትገኘዉ በቡራዩ ከተማ የኦነግ ደጋፊ ናቸዉ በተባሉ ዘረኛ አጉራ ዘለሎቸ በንጹሃን የጋሞ፣ የወላይታ እንዲሁም የጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ በፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ ዜጎች ሲገደሉ አብዛኞቹም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

•ብዙም ሳይቆይ በአዋሳ ከተማ ኢጄቶ በመባል በሚታወቅ ስም የተደራጁ የሲዳማ ብሔር ተወላጅ ወጣቶቸ የሲዳማ ብሔር አይደሉም ባሏቸዉ ዜጎች ላይ የፈጸሙት እሳፋሪ እና ዘግናኝ ጭፍጨፋ አይረሳም።

•በፖለቲከኛዉ ጃዋር መሀመድ የተከብቤአለሁ የቲዉተር/ፌስቡክ ተማጽኖ በአዲስ አበባ እና በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተቀሰቀስ ረብሻ የብዙ ሰዎች ህይወት ሲጠፋ ከፍተኛ የንብረት ዉድመት ደርሷል።

•የአርቲሲት ሃጫሉን አሳዛኝ ግድያ ተከትሎ በመላዉ ኦሮሚያ በሚባል መልኩ በተለይም በሻሸመኔ ከተማ በቃል ለመግለጽ የሚያዳግት በበዙ መቶዎች የተገደሉበት እና የቆሰሉበት ዘር እና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። በበዙ ሚሊዎን ብር የሚቆጠር ንብረት እና ሀብት ወድሟል። ከጭፍጨፋዉ በኪነ ጥበቡ የተረፉት እዛዉ አድገዉ፣ከብደዉ እና ወልደዉ የኖሩበትን እገር ጥለዉ ላይመለሱ ተሰደዋል።

•በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ አጣዬ እና ከሚሴ ኗሪዎች ላይ በጽንፈኛ የኦሮሞ ታጣቂዉች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተዋላጆች ላይ የተፈጸመዉ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና የደረሰዉ ዉድመት ይሄ ነዉ አይባልም። ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አጣዬ ከተማ ወድማለች።

•ላለፉት ሶስት አመታት ያለ ማቋረጥ በ ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በተለይም በመተከል አዉራጃ ዘር ላይ ያተኮረ በይበልጥም በአማራ ተዋላጆች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሲገደሉ እና ሲቆስሉ፡ ለመቁጠር እስኪያስቸግር ድረስ በብዙ ሺዎች ተፈናቅለዉ ለስደት ተዳርገዋል።

•ባለፉት አራት አመታት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወለጋ በቃላት ለመግለጽ በሚያዳግት መልኩ በ 1970 ዎቹ አካባቢ በሰሜኑ የሀገራቸን ክፍል በተከሰተዉ ድርቅ ሳብያ መንግስት በወሰደዉ የነፍስ አድን ዘመቻ ወደ ወለጋ በሰፈራ ከወሎ የሄዱ ዜጎቻችን ላይ በአማራነታቸዉ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በጽንፈኛ የኦሮሞ ሃይሎች በተደጋጋሚ ተጨፍጭፈዋል ታርደዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰደዋል ተፈናቅለዋል። ይሄዉ ዛሬም ዘር ተኮር ጭፍጨፋዉ ቀጥሎ ጠ/ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ ከወጡ ከ አራት አመት በኋላ ከ 600 መቶ በላይ ሲታረዱ ብዙ ሺዎች ምድር ቁና ሆናባቸዉ በስቃይ ማጥ ዉስጥ ይዋልላሉ።
•ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ከፍል ስናቀና ደግሞ፡ ለተከሰተዉ ዘግናኝ እና አዉዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት መንስኤ የተጠያቂነቱን ድርሻ ትህነግ ቢወስድም ጦርነቱ በትህነግ ከመጀመሩ በፊት የነበረዉን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም መንግስት ይህን እይነት ድንገተኛ ጥቃት ሊመጣ እንደሚችል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊገነዘብ እና ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ ይገባ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ፤

1. ጥቃቱ ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ በነበሩት ወራት መንግስት የሰሜን እዝን ከትግራይ አዉጥቶ ወደ መሐል እገር ለማንቀሳቀስ ባደረገዉ ሙከራ ትህነግ የአካባቢዉን ህጻናት እና እናቶች አሰልፎ መሬት ላይ በማስተኛት ሰራዊቱ ከትግራይ እንዳይወጣ በማር የተለወስ ተንኮል ተጠቅሞ ስራዊቱን እዘናግቶ እዛዉ ለማረድ እንዲቀር ማድረጉ።

2. ጥቃቱ ከመፈጸሙ ጥቂት ሳምንታት በፊት የሰሜን እዝ እዛዥ በትህነግ ተመርዘዉ አዲስ አበባ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል በህክምና ላይ መሆናቸዉ።

3. በእርሳቸዉ ምትክ የተላከዉ የጦር ጀነራል ትግራይ እንዳይገባ ከመቀሌ አዉሮፕላን ማረፊያ በትግራይ ልዩ ሃይል ታግዶ መመለሱ።

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸዉን ጥቂት ተጨባጭ ነገሮች በተገቢዉ መንገድ ካለማጤን እና ካለመገምገም የተነሳ ሰራዊቱ ምንም አይነት ጥርጣሬ እና ስጋት ሳይኖረዉ እራሱን ሳያዘጋጅ ሀገር ሰላም ብሎ በተኛበት ለመጨፍጨፍ በቅቷል። አዎ በወቅቱ በሰራዊቱ ዉስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ከፍተኛ መኮንኖች የትህነግ ደጋፊዎች ስለነበሩ ሁኔታዎችን በተገቢዉ መንገድ ለመገምገም እና መፍትሄ ለማግኝት እዳጋች ነበር የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ መልስ የሚሆነዉ በወቅቱ የሠራዊቱ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት የዛሬዉ አምባሳደር ጀነራል አደም ሲሆኑ በተጨማሪም የያኔዉ ም/ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት የዛሬዉ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ነበሩ። የሚገርመዉ እና ያሚያሳዝነዉ በሀገራችን ላይ በተለይም በሠራዊታችን ላይ ለደረሰዉ ጥፋት የሠራዊቱ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምም ሆነ የደህንነት እካላት ተጠያቂ እልሆኑም። እንዲያዉም ጥፋታቸዉን እና ድክመታቸዉን ለመሸፈን በሚመስል መልኩ በአምባሳደርነት ተሹመዉ ከሀገር ወጡ።

ከጦርነቱም በኋላ ለደረሰዉ ከፍተኛ የሰዉ ህይወት እና የንብረት ጥፋት የፌደራል መንግስቱ በከፊልም ቢሆን ተጠያቂ ነዉ። ምክንያቱም ሰራዊቱ በአሽናፊነት መቀሌ ገብቶ ለስምንት ወራት ያህል በተቀመጠበት ወቅት የትህነግ ሠራዊት ከትብያ ተነስቶ ለመደራጀት እና መልሶ ሠራዊታችንን ለማጥቃት እስኪደርስ ድርስ በመንግስት ደህንነት በኩል ያለዉን ስፊ የመረጃ እጥረት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ለዚህም ይመስላል ጠ/ሚንስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር ትህነግ (ጁንታዉ ባሳቸዉ አጠራር) ዱቄት ሆኗል ተበትኗል ያሉት። ይህ አባባላቸዉ አቅደዉትም ባይሆን ህዝብን እንዲዘናጋ አድርጓል። በተለይም የአማራ ክልል አመራሮች የጠ/ሚንስትሩን ዱቄት ሆኗል ቧልት ተከትለዉ ይመስላል ሌት ተቅን ትህነግ ከአማራ ጋር የማወራርደዉ ሂሳብ አለኝ ይል የነበረዉን ዛቻ ዘንግትዉ ሕዝቡን በስነ ልቦና እና በትጥቅ ሳያዘጋጁት ለስምንት ወር ተጎልተዉ ይሄ ነዉ የማይባል ዋጋ አስከፍለዉታል።

የዚህ አይነት ተጠያቂነት የሌለበት፣ ነገሮቸን ቀድሞ በመገምገም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ካለማጤን እና ተገቢዉን ጥንቃቄ ካለማድረግ የተነሳ በሰራዊታቸን ላይ የደረሰዉ አሳዛኝ ክስተት በወለጋ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ የአማራ ተወላጅ ዜጎቻችን ላይ በተደጋጋሚ ላለፉት አራት አመታት እንዲጨፋጨፉ ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጓል።

መንግስት ህግን ከማስከበር ባሻገር የሐገሪቱ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማሕባራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫዋታል። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በዶ/ር አብይ የሚመራዉ መንግስት በሀገሪቱ የተጀመሩ እና አዳዲስ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያሳየዉ ትጋት እና ብቃት ሊደነቅ ይገባል። እንደ ምሳሌ፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፤ የኩታ ገጠም እርሻ ፤ የበጋ ወር የስንዴ እርሻ ልማት እና አረንጓዴ አሻራ በመባል የሚታወቀዉ በመላዉ ሀገሪቱ በተከታታይ አመታት የተደረገዉ እና በመደረግ ላይ ያለዉ የችግኝ ተከላ በኢኮኖሚዉ ረገድ ከፍተኛ ዉጤት የሚያስገኙ ናቸዉ። በዲፕሎማሲዉ ረገድ ደግሞ ምንም ተቋማዊ ሂደትን የተከተለ ባይሆንም ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ የሰላም ድርድር እንደ ታላቅ ስኬት ይቆጠራል። እንዲሁም፡ የመንግስት እና የሲቪክ ተቋማትን ለማዘመን እና መዋቅራዊ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረዉ ስራ እንደተጠበቀዉ ዉጤት ባያመጣም ሀገሪቱ ካለባት ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጫና፣ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እና ተቋማትን ለማስተካከል ከሚጠይቀዉ ረዘም ያለ ጊዜ እኳያ የሚያበረታታ መጠነኛ ለዉጥ ታይቷል። ለዚህም የመከላከያ ሠራዊት፣ የምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ሰባዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ቱሪዝም እና ማሕበራዊ ሕይወትን በተመለከተ የብልጽግና መንግስት በተለይም ዶ/ር አብይ አመርቂ ስራን ሰርተዋል። ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ የተሰሩት የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ ያብሮነት ቤተ መጽሐፍት፣ የአንድነት ፓርክ እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ ያሳይንስ እና የአድዋ ሙዚየሞች፣ በየክልሉ ያስጀመሯቸዉ ሆቴሎች እና መዝናኛ ቦታዎች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸዉ። በማሕበራዊዉ ረገድ ጠ/ሚንስትሩ እና ባለቤታቸዉ ተቀዳሚ እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ የአዛዉንቶችን ቤት በመስራት እና በመጠገን፡ ትምህርት ቤቶችን በማሰራት፣ የተቸገሩትን እና የታመሙትን በመጠየቅ የሚያሳዩት ግላዊ እርዳታ ለማሕበረሰባችን ታላቅ ምሳሌነት አለዉ።

ይህ ሁሉ ጠቃሚ እና ጥሩ ተግባር ሆኖ እያለ ከላይ እንደገለጽነዉ የአንድ አገር መንግስት ተቀዳሚ እና ዋነኛ ሃላፊነቱ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነትን ማስጠበቅ ሲሆን የብልጽግና መንግስት ይህን ማሳካት ፈጽሞ ተስኖታል። የአንድ መንግስት ብቃት መገለጫዎች ናቸዉ ከሚባሉት ባሕርያት መካከል በተቀዳሚነት የሚነሳዉ፡ በሀገር ላይ ችግር በተፈጠረ ወቅት መሪዉ ሙሉ ሃላፊነትን በመዉስድ ሕዝብ ፊት ቀርቦ ሰለጉዳዪ አስፈላጊዉን ማብራርያ ስጥቶ ዜጎችን አጽናንቶ እና አረጋግቶ ተገቢዉን እርምጃ በአፋጣኝ ሲወስድ ነዉ። በዚህ ረገድ ጠ/ሚንስትሩም ሆነ የሚመሩት የብልጽግና ድርጅት በተደጋጋሚ የብቃት ጉድለት አሳይተዋል። ይህም በመሆኑ መንግስት እስካሁን የመጣበትን መንገድ በግልጽ እና በጥንቃቄ መርምሮ እና ገምግሞ እንዳለፉት አራት አመታት በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ ጭፍጨፋ በደረሰ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ አስቀምጠናል ከሚል ትርጉም የለሽ ሽንገላ ተላቆ አስቸኳይ እና ፈጣን እርማት ሊያደርግ ይገባል።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን አስከፊ የንፁሀንን እልቂት ለማስቆም የሚችለውን ሁሉ በማድረግ የዜግነት ግዴታዉን መወጣት ይኖርበታል:: ስለሆነም ፤ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለስቦች፣ ልሂቃን፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ተቋማት፣ መንግሥት የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት እንዲያስጠብቅ ጫና ማድርግ ይጠበቅባቸዋል:: እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት በተለይም የብሔር ፖለቲካን የሚያስተጋቡ፡ ጽንፈኛ ሃይሎች፡ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስቆም ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። በብሔር የተደራጁ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም የሀዘን መግለጫ ከማዉጣት እና ገለልተኛ አጣሪ እንዲቋቋም ከመጠየቅ በተጨማሪ፡ የዘር ተኮር ግድያ፣ ዘረፋ እና ማፈናቀልን በፅኑ ማውገዝና በትጋት መከላከል አለባቸው::

መንግስታት ከነሱ በፊት ከነበሩ እና ካለፉት መማር አለባቸው። አንዱን አካባቢ እና ሕዝብ አኬልዳማ በማድረግ የሚግኝ ትርፍም ሆነ ዘለቄታዊ ድል የለም። እንደውም በሁሉም ዘንድ መጠላትን አስከትሎ መንግስት የሥልጣን ዘመኑ ባልጠበቀዉ ሰአት እና መንገድ ያለጊዜዉ በዉርደት እንዲያበቃ ይዳርጋል። ”ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ግን ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል ሳይሆን ይወረውሩሃል” የሚለው በመንግሥት ላይ ይደርሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop