June 26, 2022
ጠገናው ጎሹ
እንደ እኛ አይነት አብዛኛው ታሪኩ የውስጥ (የእርስ በርስ) ጦርነት እና ከውጭ ወራሪ ሃይል ጋር የተደረገ ጦርነት ታሪክ እንጅ የውስጣዊ ነፃነት ፣ፍትህና እኩልነት ታሪክ በእጅጉ የሚጎለው አገር ሰላም የሚለውን ቃል የሚያየው ወይም የሚተረጉመው ከጦርነት መኖር ወይም አለመኖር ጋር ብቻ አያይዞ ቢሆን አይገርምም ። ጦርነት የሰላም ቀጥተኛ ተቃራኒ የሆነና ጉዳቱም ከፍተኛና በግልፅ የሚታይ ሰው ሠራሽ ክስተት በመሆኑ የሰላም ጉዳይ ሲነሳ በአእምሯችን ቀድሞ የሚመጣውም እረሱ ጦርነት ነው።
ከጦርነት ባሻገር ያለውን የሰላም ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት ለመረዳት አለመፈለግ ወይም አለመቻል ግን የሰላምን ትርጉም ጎደሎ ያደርገዋል። ሰላም ማለት የጥይት ድምፅ አለመስማት ማለት ብቻ አይደለምና።
እኛ ግን የሁሉም አይነት ሰላም ማጣት ሰለባዎች ከሆን አያሌ ዓመታት ተቆጠሩ። ከህወሃት የበላይነት መዳፍ ወጥቶ በተረኛ የኢህአዴግ አንጃ ቡድኖች (ኦህዴዳዊያንና አሽከሮቻቸው ብአዴናዊያን) ቁጥጥር ሥር የዋለው ወንጀለኛ የፖለቲካ ሥርዓት የመከራውንና የውርደቱን አስከፊነት እጅግ ከፍ በማድረግ የሰላምን ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በአፍ ጢሙ ደፍቶት አረፈ። ይህንን እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ድርጊት አልባ የሃዘን እንባ በማንባት፣ የፅዕናቱን ይስጠን ቃለ “ቡራኬ” በማነብነብ እና የሰመዓትነት ትርክትን በመተረክ ለማለፍ (ለመወጣት) መሞከር ጨርሶ የትም አያደርስም።
የሰላምን ምንነት፣ለምንነትና እንዴትነት ከጦርነት ባልተናነሰ ለመከራና ለውርደት ከሚዳርገው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ አእምሯዊ፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ጎስቁልና ነፃ ከመሆን ወይም ካለመሆን ጋር አያይዘን ካላየነው በስተቀር እጅግ ጎደሎ ስለሚሆን የሰላም አለመኖር ከፍተኛ መገለጫ ከሆነው የጦርነትና የትርምስ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ከቶ የሚቻለን አይሆነም።
በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ ምክንያት በርሃብ ቸነፈር እየተመቱ፣ የእለት ጉርስን ሳይቀር ከሌሎች እጆች (ከመፅዋቾች) እየተጠባበቁ ፣ ታክሞ ሊድን በሚችል ቀላል ህመም እየተሰቃዩና እየሞቱ፣ በመሠረታዊ እውቀት እጥረት (በፍፁም ድንቁርና) ምክንያት የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥዎችና ሸሪኮቻቸው ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እየሆኑ፣ አቤት የሚሉበት የፍትህ ሥርዓት ባለመኖሩ የኢፍታዊነትን መሪር ፅዋ እየተጋቱ፣ የባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የካድሬ ስበስብ የሆነውን ህግ አውጭ አካል ወይም ፓርላማ ተብየ እንደ ትክክለኛ የህዝብ ወኪል እየቆጠሩ፣ እንደ አብይ አይነቱን ፈጣሪን ሳይቀር የግፍ አገዛዙ ባልደረባ እስከማድረግ ባደረሰ እጅግ ሸፍጠኛና ሴረኛ የፖለቲካ ሰብእና እና የሞራል ጉስቁልና የተለከፈ ሰው “እርሱ ከሌለ አገር ፈረሰ” በሚል የውርደትና የድንቁርና ሥነ ልቦና ውስጥ እየተርመጠመጡ ስለ ሰላም መስበክ ወይም መተረክ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።
እጅግ አያሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ የተገኙበትን ማህበረሰብ ማንነት በመለየት አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ የሚፈፅሙትን ጭራቃዊ ብድኖች (ኦነግና መሰሎቹን) ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ ከሚቸራቸው የአብይ አህመድ አገዛዝ ለይቶ ባለማየት ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ጠንክሮ ከመሥራት (ከመታገል) ይልቅ የምድሩ አንሶ ሰማያዊ ግፍ የሚፈፅም እውነተኛ አምላክ ያለ ይመስል “የሰመዓታትን ነፍስ ይማር” በሚል እግዚኦታ ብቻ እንኳን ሰላምን ያህል እጅግ ገዙፍና ጥልቅ ጉዳይ እውን ለማድረግ በገፍና በግፍ የሚጨፈጨፉትን ንፁሃን ወገኖች ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመታደግ አይቻልም።
ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ለረጅም ጊዜና በተከታታይ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፅሙትንና የሚያስፈፅሙትን እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ድርጊት አልባ ውግዘት፣ መግለጫ፣ ጉባኤ፣ ምህላ/እግዚኦታ በማዤጎድጎድ እና የሰመዕትነት ትርክት በመተረክ ለማስቆም ፈፀፅሞ አይቻልም። ዛሬ በአገር ላይ የሚወርደው የመከራና ውርደት ዶፍ ለዓመታት የዘለቀው የፖለቲካና የሞራል ውድቀታችን ውጤት መሆኑን በአግባቡ መረዳት የችግሩ መፍትሄ ፍለጋ መንገድ አጋማሽ ነው። ቀሪውና ወሳኙ ክፍል በቂ ዝግጀት የማድረግና ወደ ተግባርየመሠማራት ጉዳይ ነው።
ከዚህ ውጭ ያለውን ስሜት የለሽ ትርክት እኮ አገር ለአራት ዓመታት ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ፖለቲካ ወለድ ሰደድ እሳት ስትለበለብ ለአንድ ደቂቃ እንኳ በይፋ ወጥቶ “ለሆነው ሁሉ ሃዘኔን ስገልፅ ይህንን አይነት ጨርሶ ስሜት የሌለው ሰቆቃ ለማስቆምና ፈፃሚዎችንም ወደ ፍትህ ዓለም ለማቅረብ የሚቻለውን ሁሉ እንደማደርግ ቃል እየገባሁ” ለማለት ጨርሶ ያልደፈረው አብይ አህመድም ደጋግሞ ተርኮልናል። አሁንም እየተረከልን ነው።
በማንነታቸው ተለይተው የተጨፈጨፉ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች አስከሬኖች በየጫካውና በየሰፈሩ ገና ተስበስብው ባላለቁበት በዚህ እጅግ አስጨናቂ ወቅት“ኢትዮጵያ ከችግሯ እንድትላቀቅ በተስፋ እንታገል፣ እንፀልይ ፣ ጥላቻን እንፀየፈው፣ ዛፎችን እንትከል” የከተማውን ቤቶች (ህንፃዎች) አንድ አይነት ቀለም እንቀባ ፣ ቅጠል በጨው እንመገብ፣ ዳቦ በሙዝም ሸጋ ነው፣ወዘተ የሚልና ከምንገኝበት የመከራ ዶፍ አንፃር በእጅጉ ህሊናን የሚያቆስል ዲስኩር ከሚደሰኩር እና የለየለት ጨካኝ ፖለቲከኛ (አብይ አህመድ) ሰላምን እየጠበቅን ከሆነ ወደ አፈር አልተመለስንም እንጅ በቁማችን ሞተናል ማለት ነው።
አዎ! ከተዘፈቅንበት እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ አዙሪት ሰብረን መውጣት ካለብን በዚህ ልክ ነው መነጋገር ያለብን።
ጎደሎ የሆነ ወይም በእጅጉ የተንሸዋረረ የሰላም አተረጓጎማችንና አረዳዳችን ለዘመናት የመጣንበት የመከራና የሁለንተናዊ ውድቀት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓትን አስወግደን እውነተኛ ሰላም የሚሰፍንበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግን በሚመጥን አኳኋን ለመታገል አላስቻለንም።
አሁንም ይህንን እጅግ አስቀያሚና አደገኛ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን በማረም እና ከክስተቶች ትኩሳት ጋር በስሜት ከመጋለብ በመውጣት ምክንያታዊና ውጤታማ በሆነ የጋራ ትግል ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን እውን ለማድረግ በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ የመሆናችን ጉዳይ ከጥያቄ ምልክት ውጭ አለመሆኑን አምነን በመቀበል ትግሉን በነቃ፣ በተደራጀ፣ በፅዕኑ መርህ ላይ በተመሠረተ እና ዘላቂነት ባለው የአንገዛም ባይነት አርበኝነት መቃኘትና ማስኬድ ይኖርብናል።
የገጠመንና እየገጠመን ያለውን እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሁለንተናዊ ቀውስ ስሜታዊነት በሚያጠቃው፣ የክስተቶች ትኩሳት በሚመራው እና እዚያና እዚህ በሚደረግ የአደባባይና የመንገድ ላይ ቁጭትና እሪታ እንኳን ልንለውጠው አደብ ልናስገዛውም አንችልም። በግፍ ግድያ ከአፈር ጋር የተቀላቀሉ አያሌ ንፁሃን ዜጎችን መሪር ሃዘን በቅጡ ባልተወጣንበት ሁኔታ አሁን ከሰሞኑ ደግሞ የሰማነው በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች የመከላከያ ሃይል በቅርብ ርቀት በሚገኝባቸው ቀበሌዎች በአንድ ጀምበር ተጨፍጭፈው በየጥሻው ወድቀው የማየት በእጅጉ መሪር እውነታ ለቁርጠኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የማያነሳሳን ከሆነ በግፍ ከተገደሉት ንፁሃን ወገኖች በከፋ ሁኔታ በቁም የሞትነው እኛው ራሳችን ነን ማለት ነው።
እናም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወርቃማ መገለጫ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው ሰላም እውን ይሆን ዘንድ ብልጭና ድርግም ከሚልና በተናጠል ከሚያስመታ ህዝባዊ የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴ ክፉ አዙሪት መውጣት ይኖርብናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዘመን ጠገቡን ልክ የሌለው የመከራና የውርደት ሥርዓት አስወግዶ የእውነተኛ ሰላምና የጋራ እድገት ዋስትና የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እውን ሊያስደርገን የሚችል ፅዕኑና ዘላቂ የጋራ ትግል ማድረግን ይጠይቃል።
ለዚህም ነው ከሰሞኑ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምሬትን ወይም ብሶትን በማስተንፈስ ተመልሰን ለዘመናት ወደ ነበርንበት ድርጊት አልባ እሮሮና እግዚኦታ የመዘፈቅ ክፉ አባዜ የተጠናወታቸው እንዳይሆኑ ብስለት የተሞላበትና ወደ ኋላ የማይታጠፍ የጋራ ጥረት ማድረግ ፍፁም አስፈላጊ የሚሆነው። ይህ ሲሆን ነው ለአያሌ ዓመታት የዘለቀውን የእኩያን ፖለቲከኞች ሥርዓት ከሥረ መሠረቱ ነቅሎ በማስወገድ የእውነተኛ ሰላምና የጋራ እድገት ዋስትና የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አምጦ መውለድ የሚቻለው። ከዚህ ያነሰው መንገድ ሁሉ ተጨማሪ እና ምናልባትም ሲያስቡት የሚከብድ መከራና ሰቆቃ የሚያስከትል ነው የሚሆነው።
ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ተዘፍቀን የኖርንበትን እጅግ አስከፊና አሳፋሪ የፖለቲካ እኛነት አሁንም የሙጥኝ እያልን በሌላ በኩል ግን ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊት አገርን የመናፈቅ ከባድ እንቆቅልሽ ከምር የማያሳስበን ከሆነ እና ይህንኑ እንቆቅልሽ ለመፍታት አሁንኑ በቁርጠኝነት የማያነሳሳን ከሆነ አሁንም የቁም ሙቶች ነን።
ለዚህም ነው ከሰሞኑ የምናያቸው “የበቃን አንገዛም” እንቅስቃሴዎች በስሜት የሚነጉዱ ሳይሆኑ የጭንቅ ጊዜ ተወልደው ከጭንቅ የሚያወጡ የዴሞክራሲ አርበኛ መሪዎችን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ከትግሉ ሜዳ ፈልጎና መልምሎ ማውጣት ግድ ይላቸዋል ማለት ከትክክልም ትክክል የሚሆነው።
እናም “የዜግነትና የሰብአዊ መብቴ ባልተከበረበት ሁኔታ ውስጥ የሚኖረው ሰላም ጎደሎ በመሆኑ እውነተኛ ጣእሙን ለማጣጣም የሚያስችለኝን ሥርዓተ ፖለቲካ ለመፍጠር የማደርገውን ጥረት ወይም ትግል ሲሆን አግዙኝ ቢያንስ ግን ፀረ ሰላምና ፀረ የአገር ደህንነት በሚል የምታዘምቱብኝን የግፍ አገዛዝ ሰይፋችሁን ሰብስቡልኝ ወይም ወደ ሰገባው መልሱልኝ” በማለት ትግልን ከመቀጠል ውጭ ሌላ ተመራጭ መንገድ ጨርሶ የለም።
ፍፁም ባለጌና ጨካኝ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የሚገድሉትን፣ የሚያስገድሉትን ፣ የሚያገዳድሉትን እና እያሳደዱ የሰቆቃ አይነት የሚያስቆጥሩትን መከረኛ ህዝብ ቁጥር መብዛትና መቀነስ እያሰሉ “አንፃራዊ ወይም ፍፁማዊ ሰላም ሰፍኖል ወይም እየሰፈነ ነውና ደስ ይበለን” ሲሉን ይበልጥ ካላስቆጣንና አሁንስ በቃ! ካላሰኘን ምን ያህል ተጨማሪ መከራና ግፍ እንደሚያስፈልገን አላውቅም ።ባለጌና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች በሚዘውሩት መሪር የፖለቲካ እውነታ ውስጥ እውነተኛ ሰላም ይወለዳል ብሎ መጠበቅ የለየለት ባርነትን የመቀበል ክፉ የፖለቲካ ደዌ ካልሆነ ከቶ ሌላ ሊሆን አይችልም።
በሰላም ስም ግፍ ሲፈፅምና ሲያስፈፅም የኖረውንና አሁንም በእጅጉ በሚያሰቅቅ ሁኔታ የቀጠለውን ሥርዓተ ኦህዴድ/ብልፅግና “ሁሉንም ባለድርሻ አካል የሚያሳትፍ የሽግግር ጊዜ መንግሥት እንዲመሠረት የድርሻህን ተወጣ ፤ ካልሆነ ደግሞ ለዘመናት ክፉኛ ከቆሰለው የከመከረኛ ህዝብ ጀርባ ላይ ውረድ” ብሎ መጠየቅ ለምንና እንዴት አገር እንደሚያፈርስ እንኳን ለማመን ለማሰብም በእጅጉ ይከብዳል።ታዲያ ዴሞክራሲና ሰላም እንዴትና በየት በኩል ነው እውን የሚሆኑት?
ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ በማይድን የፖለቲካ ካንሰር የተለከፈን ሥርዓተ ፖለቲካ አሁንም “እባክህን ሰላምና መረጋጋትን አምጠህ ውለድልን” ከሚልና ፈፅሞ ስሜት ከማይሰጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ አረንቋ ውስጥ የመገኘታችን መሪር እውነታ ነው።
ከሰሞኑ በምድረ ኦሮሚያ (ወለጋ) ውስጥ የምንሰማውና የምናየው ነገር ሁሉ ለአራት ዓመታት በእየለቱ በሚያሰኝ አኳኋን ሲሆን የነበረው ትዕይንተ ሰቆቃ ወደ ለየለት የሲኦልነት ታሪክ እየተለወጠ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ማሰብንና መመራመርን አይጠይቅም።
ለዚህ አይነት እጅግ አሰቃቂ ደጋግሞ የመውደቅ አባዜ ዋነኛ ተጠያቂዎች ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥዎች የመሆንናቸው እውነታ የማያጠያይቅ አለመሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እኛስ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ጎረቤት፣ በሙያ እና በልዩ ልዩ ማህበራት (ስብስብ) ሥር እንደ ታቀፈ ዜጋ፣ እንደ ተማረ የህብረተሰብ አካል ፣ እንደ ሃይማኖት ተቋም ( መሪና አስተማሪ) ፣ እንደ የሃገር ሽማግሌ ፣ እና በአጠቃላይ እንደ ማህበረሰብ ለምን ይህን ያህል ተንሻረትን ሳይሆን ተምዘግዝገን ቁልቁል ወረድንና ተዋረድን ? ብለን ካልጠየቅንና ተገቢውን መልስ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ጥረትካላደረግን ሰላምን መናፈቃችን ጨርሶ ትርጉም የለውም።
በተለይ ከሰሞኑ እየሰማንና እያየን ያለነውን እንኳን ለመግለፅ ለማሰብም የሚከብድ ፖለቲካ ወለድ ሰቆቃና ወንጀል አሁንኑ ለመስቆም ከስሜታዊነት ይልቅ በማይናወፅ ዓላማና መርህ ፣ አቋምና ቁመና (አደረጃጀት) ፣ በሞራልና በሥነ ምግባር ልእልና ላይ በተመሠረተ የአንገዛም ባይነት መንፈስ ማስኬድ እስካልቻልን ድረስ “እውነት ፣ ትእግሥት ፣ ሰላምና ፍቅር ያሸንፋል!” የሚል አጠቃላይ (ደምሳሳ) ትርክትና መፈክር ከቶ የትም አያደርስንም።
እናም እውን እውነተኛ ሰላምን እየፈለግን ከሆነ ሰላምን መፈለግ ያለብን እጆቻቸው ለዘመናት በንፃሃን መከራና ደም ከተዘፈቁ ሴረኛ ና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እና ከአድርባዮች (ከልክስክሶች) ሰፈር ሳይሆን ለእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ (ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ) ከሚደረግ የጋራ ተጋድሎ አደባባይ መሆን አለበት ።
እርግጥ ነው በሰው ልጅ ውስብስብና አስቸጋሪ ባህሪ (በተለይ ከልክ ባለፈ የበላይነት አባዜ/ደዌ) እና የዚሁ ነፀብራቅ በሆነው መስተጋብራዊ ሂደት ምክንያት እንከን የለሽ ወይም ፍፁም የሆነ ሰላም መጠበቅ የገሃዱ ዓለም እውነታ አይደለም።
ይህ ሲባል ግን በረጅሙ የፖለቲካ ታሪክ ሂደት ውስጥ ብልጭ ድርግም የሚል እና ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አንፃራዊ የሆነ ሰላም ኖሮ አያውቅም ማለት አይደለም።
እውነተኛ የብዙሃኑን ፍላጎትንና ጥቅምን በሚያረጋግጥ መሠረት ላይ የቆመ ሥርዓተ ፖለቲካ (ዴሞክራሲ) ባልነበረበት ዘመንና ሁኔታ የሰላምን የተሟላ ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት መጠበቅ አይቻልም ወይም ከምናባዊነት አያልፍም።
አዎ! የመሰልጠን (civility) መገለጫዎች አንዱ ሰላም እና ሰላም ነው። እጅግ ፈታኝ የሆኑ እንከኖች የመኖራቸው እውነት እንዳለ ሆኖ በአንፃራዊነት ሥልጣኔን ከዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር አጣጥመው የሄዱና እየሄዱ ያሉ አገሮች በቁጥር እጅግ ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኛውን የዓለም ክፍል (አገራት) የተቆጣጠረው ግን የፀረ ሰላም ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ወይም ቤተሰባዊ (ዘውዳዊ) አገዛዝ ነው ።
እኛም ባአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከማጉረምረም ፣ አንዳንዴሞ አደባባይ ወጥተን ተደብድበን እና ነቅተው ያነቃሉና ታግለው ያታግላሉ የሚባሉ ሰዎቻችንን አስረክበን ከመመለስ የዘለለ የፖለቲካ ሥራ ሳንሰራ ሩብ ምእተ ዓመት አስቆጠርን። ገዥዎቻችንም ሲያሻቸው “ዴሞክራሲና ልማት አይነጣጠሉም” ይሉንና ይህን የማድረግ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ፍላጎትና ወኔ እንደሌላቸው ትዝ ሲላቸው ደግሞ “የለም የቅድሚያ ትኩረት ልማት ስለሆን ለተለመዱ መንግሥታዊ አካላት ብቻ ሳይሆን ለመገናኛ ብዙሃንም ልማታዊ የሚል ስያሜ ሰጥተናልና ይህንን ተላልፎ የሚገኝ ሁሉ ፀረ ልማትና ፀረ ሰላም ስለሚሆን ወዮለት” በሚል መሠረታዊ የሆነውን የሰብአዊ መብት በር ጨርሰው ጠረቀሙት ።ይህ ግን ቢዘገይም ተፈረካክሶ ከመውደቅ አላዳናቸውም ።
ከሃያ ሰባት ዓመታት መሪር ተሞክሮ በመማር አስቀድሞ ከምር የተደራጀና የተዘጋጀ ዴሞክራሲያዊ ሃይል (ድርጅት) ባለመኖሩ ከአራት ዓመታት በፊት በልጭ ብሎ የነበረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ የበላይ አዛዣቸውን ህወሃትን ገፍትረው ሥርዓቱን ግን በባሰ አኳኋን ባስቀጠሉት ተረኞች እጅ ወደቀ። የተለመደው የግፍና የአፈና ዘመቻም እጅግ በከፋ ሁኔታ ቀጠለ።
አብዛኛው ተቀዋሚ ነኝ ባይም ፖለቲካውን ከህወሃት ከቤተ መንግሥት መወገድ ጋር ብቻ በማያያዝ የድል ባለቤት ነን ላሉት ተረኛ የኢህአዴግ አንጃዎች ሁለመናውን አስረክቦ ባለሟል ሆነ። አንዳንዱም የመግለጫ ፖለቲካን እንደ ሥራ ቆጥሮ ለአገር ሲል መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሆነ ራሱን የማሳመንና የማታለል ክፉ አዙሪት ውስጥ መሽከርከሩን ቀጠለ። በጣም ጥቂቶችና በአንፃራዊነት መልካም አገራዊ ራዕይና ዓላማ አላቸው የሚባሉት ደግሞ በሚግባቡባቸው ትልልቅ ጉዳዮች አማካኝነት ተመካክሮና ተባብሮ እና ከተቻለም ግንባር ወይም ውህደት ፈጥሮ ለመታገል ባለመቻላቸው አገራችን ከምትገኝበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ለመሥራት አልተሳካላችውም።
እናም ይህ እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ በአስቸኳይ እርምት ተደርጎበት የሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችን በአመርቂ ሁኔታ የሚገዳደርና በህዝባዊ አልገዛም ባይነት ትግል የሚታገዝ የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) እስካልተፈጠረ ድረስ የዴሞክራሲና የሰላም ጉዳይ ምናባዊ ፍላጎት ብቻ ሆኖ ይቀራል።
ይህን አይነት እጅግ አስቀያሚ የሆነ የተግባር አልባነት እግዚኦታ ተቀብሎ የሚያስተናግድ አምላክ የለም። እውነተኛው አምላክ የክፉዎችን መንገድ አሸንፈን የሰላምን መገኛ መንገድ እውን ለማድረግ በምናደርገው የጋራ ጥረት ወይም ተጋድሎ ሁሉ እየተገኘ ለድል እንድንበቃ የሚያደርግ (የሚያግዝ) እንጅ በየእምነት ቤቱ ወይም በየአዳራሹ ወይም በየአደባባዩ ወይም በየመንደሩ ወይም በያለንበት ተቸክለን (ሰባኪና ታዳሚ ሆነን) እግዚኦ ካልወረድክ እያለን ስለ ጠራነው በመካከላችን የሚገኝ አይደለም። የፈጠረበትን ዓላማ በቅጡ ተረድቶ ሃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን የማይወጣ ሰብአዊ ፍጡር እራሱን አይቀጡ ቅጣት የሚቀጣው እራሱ እንጅ በተሟላ ሁኔታ የፈጠረው ፈጣሪ ከቶ አይደለም።
በሚጠበቁ ወይም ጨርሶ ሊወገዱ በማይችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ አስፈላጊውንና ተገቢውን ክትትል የማድረጉ ጉዳይ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እስካሁን ባለው የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ ታሪክ ሂደት እውነተኛ ሰላምን ለማረጋገጥና ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ አማራጭ ያልተገኘለት መፍትሄ (መንገድ) ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ፀረ-ሰላምና ፀረ- ሰብእዊ መበት በሆነ ክፉ የፖለቲካ ልክፍት በተለከፉ ገዥዎች መሪነት እውን ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሽንፈትንና የሚያስከትለውን ማለቂያ የሌለው መከራና ውርደት ከመቀበል ፈፅሞ አይሻልም።