18.05.2022
ከ 200 አመት በፊት አንድ ጆን ሚሼልት የተባለ እንግሊዛዊ የጂኦሎጂ (Geology) ተመራማሪ ከከዋክብቶች የቁስ አካል ክብደት ጋር በተያያዘ ስለ ጠቋራው ጥልቀት ወይንም ደግሞ (ጥቁር ጉድጓድ) ተብሎ ስለሚጠራው እጅግ ግዙፋዊ አካል የራሱን መላ ምት ከገለፀ በርካታ አመታት ማስቆጠሩ ከታሪክ ድርሰቶች መመልከቱ የሚከብድ አይደለም። ይሁንናም ስለ ጥቁር ጉድጓድ የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች በተለያዩ ጊዜያት ቢንሸራሸሩም የማይጨበጥ፤ የማይታይ፤ የማይዳሰስ ስለ መሆኑ እስከ ጥቂት ወራት ድረስ ዘልቆ መቀጠሉ አልፎ ተርፎም ለመኖሩ ከፍተኛ ጥርጣሬ የነበሩ ለመኖራቸው ከነዚሁ የታሪክ ድርሰቶች ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ሆኖም ግን ሊቃውንቶቹ ጥቁር ጉድጓድን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት የተሰነዘሩና እየተሰነዘሩ ያሉ መላ ምቶችን በተግባር ፈትኖ ለማወቅና ለመረዳት ወቅቱ እያስገኘላቸው ያለውን የቴክኖሎጂ መሳሪያ በመጠቀም የምርምር ጥረታቸውን ብሩህ ተስፋን በመሰነቅ በከፍተኛ ትጋት መቀጠላቸው ለንባብ የቀረቡ በርካታ የምርምር ውጤቶቻቸው የሚያመላክቱት ናቸው። ይህ ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቶ የምርምር ውጤታቸውን ለሕዝብ እይታ የበቁት ውጤቶች ለሚያደርጉት የምርምር ጥረት ቀና አመለካከት ባላቸው ወገኖች በኩል ከፍተኛ አድናቆትን ቢያላብሳቸውም በዛው መጠንም ፈራ ተባን የሰነቀ አግራሞትን ማስተናገዳቸው የሚስተዋል ሆኗል።
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም፣ ከተማረበት የሙያ መስክ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው ተመራማሪዎቹ ላደረጉት ጥረትና ላስገኙት ውጤት በግል ደስተኛ ነበር አሁንም ነው። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የበለጠ ለማወቅና የግሉን የእውቀት ጥማት ለማርካት ሲል በአካባቢው የሚገኙ በመስኩ የተሰማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊቃውንቶች ሕዝባዊ ገለጻ በሚያዘጋጁበት ወቅት በመገኘት በርዕሱ ላይ ያተኮሩ መፃሃፍቶችን በመግዛትና በማንበብ፣ ጥያቄዎችን በማቅረብም ሆነ ሌሎችም ላነሷቸው የተሰጡትን መልሶችንም በጥሞና በማዳመጥ፣ ወደፊት ደግሞ ምናልባትም ለኖቬል ሽልማት ታጭተው በታላቅ ክብር ለሚቀበሉበት ቀን ያድርሰኝ በማለት የጉጉት ፍላጎቱን ራሱ ለራሱ የተመኘባቸው ቀናቶች ጥቂቶች አልነበሩም። እንደተመኘውም ፕሮፌሰር ራይንሃርድ ግሬንዘል የተባሉና የማክስ ፕላንክ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ጀርመናዊ የፊዚክስ ተመራማሪ ከሌሎች በተመሳሳይ መስክ ተመራማሪ ከሆኑት ከእንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ሮጀር ፔንሮዘ ና ከአሚሪካዊቷ ፕሮፌሰር ወይዘሮ አንድሪያ ጌዝ ጋር በ 2020 ዓ.ም. ለክብር ሽልማቱ ታጭተው ለመሸለም መብቃታቸው በዜና አውታራት ለማየትና ለማዳመጥ ቻለ። የረጅም ጊዜ ልፋታቸውና ያልታከተ ጥረታቸው ከንቱ እንዳልሆነ ተረጋገጠ።
እነዚህ ሶስት ሊቃውንት ለመሸለም የበቁት በየበኩላቸው የጥቁር ጉድጓድ ፍጥረትና ምንነት ለመረዳት የሚያስችለንን የምርምር ውጤት በማስገኘታቸው ነበር። በፕሮፌሰር ሮጀር ፔኖሮዘ አስተሳሰብ ጥቁር ጉድጓድ በእውቁ ሊቃውንት አልበርት አይንሽታይን ከቀረበው አንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብ የሚፅነስ መሰረታዊ ውጤት እንደሆነ ነው። ከዚህ ድምዳሜ ለመድረስ ያስቻለው የአልበት አይንሽታይን አጠቃላይ አንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብን ለመረዳትና ለመገንዘብ ይቻለው ዘንድ እጹብ ድንቅ የሆነ የሂሳብ ዘዴን ለመጠቀም በመቻሉ ነበር። ራሱ አይንሽታይን የአንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብ አባት የተባለ ሥም የተሰጠው እንኳ በወቅቱ ጥቁር ጉድጓድ በርግጥኝነት ይኖራል ለማለት ያልደፈረ እንደነበር ይነገራል። ሆኖም አይንሽታይን ከዚች አለም በሞት ከተለየ ከ 10 አመት በኋላ ሮጀር ፔንሮዘ ጥቁር ጉድጓድ በመሰረቱ እንደማንኛውም የአጽናፈ ሰማይ አካላት ሊፈጠር እንደሚችልና ምን አይነት ጠባዮች እንደሚያንፀባርቅም ባደረገው ጥናታዊ ምርምር ግልፅ ለማድረግ ከበቁት በርካታ ሊቃውንቶች መካከል በዋናነት ለመጠቀስ አብቅቶታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ይህ እጅግ ግዙፍ የሆነ አካል ሌላው ጠባዩ የተፈጥሮ ሕጎች ጨርሶ የማይሰሩበት ሲንጉላሪቲ ተብሎ የተሰየመ በውስጡ አቅፎ የመገኘቱ ሁናቴ ግልፅ መውጣቱ ነው። ይህ ሊቃውንት የአንፃራዊ የሂደት ፅንሰ ሃሳብን ለማጥናትና ለመረዳት ይቻል ዘንድ የሚያስፈልገውን የሂሳብ ፅንሰ ሃሳብ መጠቀምና ማዳበርም ነበረበት። ይህ በጃኑዋሪ 1965 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ያደረገው የምርምር ውጤቱ በመሰረታዊ ስነድነት የሚጠቀስ በመሆኑ የከፍተኛ የሂሳብ ትምህርት ችግር ለሌለባቸው አንባቢያን አፈላልገው እንዲያነቡትና እንዲገነዘቡት የዚህ መጣጥፍ ደራሲ የግል ምክሩን በትህትና ያቀርባል።
እይታችንን በፕሮፌሰር ወይዘሮ አንድሪያ ጌዝ ስናደርግ ደግሞ እኚህ ፕሮፌሰር በፊዚክስ መስክ የኖቬል ተሸላሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል አራተኛዋ ለመሆን የበቁ ሲሆኑ በደስታ ብስራታቸው ወቅት በአንድ የዜና ተቋም ተዘግቦ የዚህ መጣጥፍ ደራሲ ለማንበብ እንደተቻለው “ወጣት ሴቶችን ለመስኩ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው የኔ መሸለም እንደሚገፋፋቸው ተስፋ አለኝ“ በማለት የሰጡት ሃሳብ በአሜሪካ ለሚኖሩት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው አለም እንዲሁም የሀገሩን ወጣት ሴቶችንም የሚመለከት ነው የሚል ግምት ስላለው በበኩሉ የሰጡትን መልዕክት በደስታ የሚጋራቸው ነውና ለተሸላሚዎቹና ለመሰሎቻቸው የክብር ምስጋና ከእቅፍ አበባ ጋር ባሉበት በሃሳብ ደረጃ ይድረሳቸው ዝላል። ክብር ለሚገባው ክብር፣ ጥሪና ቅስቀሳ ለሚያስፈልገው ደግሞ የማይታክት ውትወታ ማቀበሉ መልካም ነውና። ከላይ የተገለፀው የምኞት ሃሳብ ስኬታማ ሆኖ ለማየትና ለመስማት መቻሉ በተለይም ከተሸላሚዎቹ አንደኛዋ ሴት በመሆኗ በልቡ ውስጥ ያሳደረብት ደስታ በርግጥም በአሁኑ ወቅት ከተመራማሪዎቹ ተርታ የተሰለፈ ባይሆንም በስሜት ደባላቸው እንዳደረገው ሆኖ ብቻ ሳይሆን በመስኩ ሊገኙ የሚችሉ አዳዲስ ውጤቶችን ለማወቅ ያለውን ጉጉት በይበልጥ እንዲቀጥልበት ውስጣዊ ግፊት አሳድሮበታል። እድሜና ጤንነቱን ይጠበቅ እንጂ።
ስለ ጠቋራው ጉድጓድ ውስጣው ይዘት የመጀሪያው የዳሰሳ ውጤት የሆነውና ስዕላዊ ገጽታውን የሚያሳይ ፎቶ በስነፈለክና በፊዚክስ ተመራማሪዎች አማካኝነት ሊቀርብ በመቻሉ በዋና ዜናነት በተለያዩ የሳይንስም ሆነ የዜና ጋዜጦችና መፅሄቶች፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በስፋትና በጥልቀት በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተዘገበ ይገኛል። በዚህ መለክ ስለ ጥቁር ጉድጓዱ በይበልጥ ጥረት የማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው ግን በ2017 ዓ.ም. እ. ኤ እ እንደሆነም በርካታዎቹ ተመራማሪዎች የሚስማሙበት ነው። የመጀመሪያው ትኩረት ተሰጥቶት ምርምር የተደረገበት፣ በ 53 ሚሊዮን አመታዊ የብርሃን አመት ርቀት በሚኘውና በ ቪርጎ አ (Virgo A) ሥም የሚጠራው ላይ ነው። ክብደቱም የጸሃያችንን 4 ሚሊዮን እጥፍ እንደሆነ ይታሰባል። የሚገኝበትም ቦታ ጋላክሲ M 87 (Messier-Object 87) ተብሎ በሚጠራው የከዋክብት ክምር መሃል እምብርት ውስጥ ነው። ተከታዩ ደግሞ በ27.000 የብርሃን አመታዊ ርቀት በሚሊኪዌይ የከዋክብቶች እምብርት በሚገኘው ላይና የመሃል ርዝመቱ 22 ሚሊዮን ኪሎሜትር በሆነው በ ሳጊተሪዩስ አ (Sagitarius „A“) ሥም የሚጠራው ላይ ነበር። በሁለቱም ጥቁር ጉድጓድ ላይ የተገኙት ውጤቶች ተመሳሳይነታቸው በጉልህ የሚታይ ሲሆን እጅግ ከፍተኛ ሙቀት እጅግ ያለው በከፍተኛ ፍጥነት በሚሽከረከር ጋዝ የተከበበ እንደሆነ ይታያል።
ይህን የመሰለ ውጤት ለማግኘት በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀናበሩ ስምንት የሬዲዮ ቴሌስኮፕ የምርምር ተቋማት በተጠቀሱት ጉድጓዶች ላይ በተመሳሳይ ጊዜና በጋራ አነጣጥረው ባደረጉት ምርምር እንደሆነም ተገልጿል። ጥቁር ጉድጓዱን በተለመደው አጉልቶና አቅርቦ በሚያሳይ ቴሌስኮፕ ለመመርመር ያልተቻለው በዚህ ግዙፍ አካል ዙሪያ የሚገኙት አቧራዎችና ጋዞች ስለሚሸፍኑት የሬዲዮ ሞገድን መጠቀሙ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ በመከሰቱ እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዚህ ሁናቴ የተነሱ ፎቶዎች የተለያዩ ቅርጾችን እጅግ በጣም ጉልህ አድርጎ የሚያሳይ ጉልበት ስላለው እንደሆነምና የተገኙት ውጤቶችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ነው። በዚህ መልክ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ነው እንግዲህ ሊቃውንቶቹ በተለያዩ የአለም አካባቢዎች የተገኙትን መረጃዎች አሰባስበውና አቀነባብረው የደረሱበትን ስዕላዊ ገፅታውን የሚያንፀባርቅ በፎቶ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ 2019 ዓ.ም. ኩራትና ደስታ በተሞላበት መልክ ለአለም ሕዝብ ለማቅረብ የቻሉት።
በርግጥም እስከዚያች ቀን ድረስ አድካሚ በሆነና በተዘዋዋሪ መንገድ መኖሩ ስለሚነገርለት ጠቋራው ጉድጓድ እንደሌሎቹ የአፅናፈ ሰማይ ከዋክብቶች ሁሉ ጨርሶ ሊካድ የማይቻል የሚታይና የሚዳሰስ አንዱ አካል ለመሆኑ ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ቀርቦ የአዲስ ምዕራፍ ብስራት ተበሰረ። ተምኔታውነቱ ለአንዴም ለመጨረሻም ከታሪክ ትቢያ እንዲጣል ተደረገ። በዚህም አዲስ የምርምር ታሪክ ሀ ብሎ ተጀመረ። የተጠቀሱት የጥቁር ጉድጓድ ስዕላዊ ገፅታዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች ለሕዝብ ይፋ እስከሆኑበት ግዜ ድረስ ይህ ግዙፍ አካል ለመኖሩ በተየዋዋሪ በማስረጃነት ይቀርቡ የነበሩት፣
ሀ. በ 2015 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. የስበት ሞገድን ለመለካት በተደረገው ጥረት የተገኘው ማስረጃ
ሁለት ጠቋራ ጉድጓዶች በሚዋሃዱበት ወቅት ጊዜንና ሕዋን አባጣና ጎባጣ አድርጎ በሁሉም አቅጣጫ በአፅናፈ አለም ውስጥ የሚከሰተው የመስፋፋትና ሂደት ጉዞን በመሬት ላይም በጣም ሴንሲቲቭ በሆነ መሳሪያ ለመለካት በመቻሉ፣
ለ. ከ 1990ኛ ዓ.ም. እ.ኤ.አ ጀምሮ በሳጊታሪዩስ አ ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ከዋክብቶች የሚሽከረከሩብትን ምህዋር(Orbit) የምርምር ትኩረት አድርጎ በመውሰድ ነጥብ በነጥብ ተከታትለው ያገኙት ሥዕላዊ ገፅታ እምብርቱ ከጥቁር ጉድጓድ ውጪ ሊሆን እንደማይችል ማረጋገጣቸው ነበር። እነዚህ ማስረጃዎች ከተጠቀሱት ፎቶዎች ጋር ተዳብለው ጥርጣሬ የነበራቸውን የተወሰኑ ክፍሎችን ሳይቀር አድናቆታቸውን እንዲቸሩ አድርጓቸዋል።
ይህ ውስጣዊ ይዘቱን ተፍተልትሎ ለማወቅ እንዳይቻል በተለያዩ እንከኖች ተጋርጦ ያለው ጠቋራው ጉድጓድ ግን በአጠገቡ ሊያልፉ የቻሉትን በቅድሚያ አስከ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮቻቸው ድረስ ብትንትናቸውን አውጥቶ በነፋሻ መልክ አዘጋጅቶ ለመሰልቀጥ ኃይለኛ ጉልበት ያለው አስፈሪ ግዙፍ አካል ነው። ይህን አይነት ድርጊቶችን ለማከናወን የሚያስችለው ኃይል ለማግኘት የሚያስችለው ደግሞ መጠነ ሰፊ የሆነ ወደር የለሽ ክብደት በአንድ ቦታ አቅፎና ጨምድዶ ለመያዝ የሚያስችለው ውስጣዊ ጉልበት ስላለው እንደሆነ ይነገርለታል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለመሆኑ ይህ ጉድጓድ ራሱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚለው ራሱን የቻለና የብዙዎችም ጥያቄ ሲሆን መልሱም የተለያዩ ክብደት ያላቸውን ከዋክብቶችና በውስጣቸው እየተከናወኑ ስላሉት የጥቃቅን ንጥረ አካላት ፍትጊያና በዚሁም አዳዲስ ንጥረ አካላት መፈጠር፣ በጊዜ ሂደትም ምን አይነት ክስተት እንደሚያጋጥማቸው ከማወቁና ከመገንዘቡ ላይ ሊታወቅ እንደሚችል መጥቆሙ አግባብነት ይኖረዋል።
እንደ ፀሃይ የመስሉ ከዋክብቶች በውስጣቸው በተቃራኒ ጎዳና ግፊት የሚያደርጉ ሁለት አይነት ኃይሎችን አቅፈው የሚገኙ ናቸው። አንደኛው የስበት ኃይል(Gravity Force) ንጥረ አካላትን አቅፎ ለመያዝ ወደ ውስጥ ግፊት የሚያደርግ ሲሆን ሌላኛው ድግሞ በጥቃቅን ንጥረ አካላት ፍትጊያና አዳዲስ ንጥረ አካላት በመፈጠር ሳቢያ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ተፈጥሮ የሙቀቱን ኃይል ወደ ውጭ ለማሰራጨት ግፊት የሚያደርግ ነው። በነዚህ ሁለት የተፈጥሮ ኃይላት መካከል የሚኖረው መሳሳብና መገፋፋት ሚዛኑን እስከጠበቀ ድረስ ከዋክብቶቹ የተረጋጋ ሁኔታን ለረጅም ጊዜያት የሚያንፀባርቁ ይሆናሉ። ይህ ሁናቴ ግን በከዋክብቶቹ ውስጥ አዳዲስ ንጥረ አካላት መፍጠሩ ሲገባደድና የቃጠሎው ሂደት በሚያከትምበት ወቅት የስበት ኃይሉ የበላይነቱን በመያዝ የከዋክብቶቹ በአንድ ቦታ መኮማተርነት ይከሰታል። ይህ የመኮማተር ክስተት የሚከናወነው ደግሞ እጅግ በጣም ፈጣን በሆነ ሁኔታ (10 ሚሊዮን ኪሎሜትር በሰከንድ) እንደሆነ የምርምር ውጤቶችና በአጋጣሚ የተገኙ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ናቸው። ይህ ክስተት ተሟልቶ ሲገኝ የጥቁር ጉድጓድ መፈጠሩን ሲያበስር የክብደቱ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆንና የንጥረ ነገሮቹ በአንድ ቦታ የመኮማተር ብዛት መጠነ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የስበቱን እጅግ ግዙፍ ኃያልነት መላበሱን ያመላክታል። ይህንን የቁስ አካለት እጅግ ከፍተኛና ብዛትነት ባለው ሁናቴ መከማቸትን ደግሞ ሊቃውንቶቹ (Singularity) በማለት ይገልፁታል:: ይህም የሚያመላክተው በጽንሰሃሳብ ደረጃ በሶስቱ የርዝማኔ እንዲሁም በአራተኛው የጊዜ መለኪያ እቅፍ ውስጥ ተግባራዊነት ያላቸው የተፈጥሮ ሕጎች ተፈፃሚነት የሌላቸው መሆናቸውን የሚጠቁም ሲሆን ለምን? እንዴትስ ? ለተሰኙ ጥያቄዎች ለወደፊቶቹ የማወቅና የመረዳት ጉጉት ለሚኖራቸው ተመራማሪ ሊቃውንቶች የአንጎል ጂምናስቲክ እንዲሰሩ የሚገደዱበት ሁናቴ ስለሆነ ለነሱ መተዉ አግባብነት ያለው ነው።
ከዚሁ ጋር በማያያዝም የእውቁ ሊቃውንት አልበርት አይንሽታይን አንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብ በዚህ እጅግ ጉልበተኛ የስበት ኃይል ባለበት አካባቢ የመፈተኛው ወቅት መድረሱን አመላካች ነውና ከዚህ አንፃር ቡርምሮች ምን ውጤት እንደሚያስገኙልን ወደፊት የምናየው ይሆናል። ስለ አፅናፈ ሰማይ የለንን የእውቀት ደረጃም የምናጎለብትበት ነውና ለማንኛውም እስከዚያው ገቱን ይስጠን።
አጭር ማስታወሻ
“የሀገራችን ምሁራን የምንባለው በተቻለ መጠን ነገሮችን ከስረ መሰረታቸው በማጥናት የሚያስከትሉትን አሉታዊ ውጤት ሳናጤን ፈረንጅ ያለው/ያደረገው ሁሉ ልክ ነው (ስርዝ የራሴ) በማለት በራሳችንና በሕዝባችን ላይ ቀንበር ከመጫን ወጣ ብለን እንድናስብና ነገሮችን በማስተዋልና በጥበብ ከአገራችን ዘለቄታ ጥቅም አኳያ መመርመር እንድንችል ለማበረታታት ነው” የጥቅሱ መጨረሻ
ይህ ጥቅስ የተወሰደው ጊዜ ሳገኝ በስፋት እዳስሰዋለሁ በሚል ወደ ጎን ካስቀመጥቁት ሰፋ ያለ ገፆችን የያዘ “የዘረኝነት ምንጭና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮች ለትውልድ ረፋኢ በተሰኘ ርዕስ በ April 23 2019 አ.ም. በድረ ገፆች ካገኘሁት ሰነድ ውስጥ ነው። ደራሲዎቹ ሽፈራው ሉሉ ና እንግዳሸት ቡናሬ በምን መለኪያ የምሁራን ካባ ለራሳቸው እንደደረቡ ባይታወቅም ሌላውን በጅምላ በነጭ አምላኪነት ሲወነጅሉ ለንባብ ያቀረቡት መጣጥፋቸው ግን በሁለቱ የክርስትና ኃይማኖት ተቋማት (ካቶሊክና ፕሮቴስታንት) ለሚያራምዱት የፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ አስተምሮት ክፉኛ በሚወቀሱት በነጮች ደራሲያን ከተደረሱት መጣጥፎች የተኮረጀ ብቻ ሳይሆን ከሳይንስ እውቀት ጋር ክፉኛ ከሚቃረኑት መሆኑን ለአፍታም የታሰባቸው አይደለም። እነዚህ ደራሲያን የሌላውን ከመኮረጅ ውጭ በራሳቸው ጥረት ሳይንሳዊ ምርምር አድርገው ውጤቶቹም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች ለእይታ ቀርበው የይለፍ ይሁንታ የተሰጣቸው ይኑራቸው አይኑራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ምንም ስለመሆናቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ አላቀረቡም።
“የኃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በተለይ ለሕዝብ የቀረቡና የሚሰሩ ናቸው። እነዚህን ሰዎች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራን አቀናጅተን ብንጠቀም ለሀገር ዘላቂ ሰላምና የአስተዳደር ሥርአት መፍጠር ይቻላል።
ፖለቲከኞች ሙሉ በሙሉ ተገልለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራን፣ የኃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎችን በማቀናጀት የኃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ሕዝቡን በማስማማትና በማቀራረብ የአስተዳደርና ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ሥርአት እንዲዘረጉ ቢደረግ በሁሉ ሕዝብ ተቀባይነት ስለሚኖረው ዘላቂ የሰላምና የአንድነት መሰረትን ለመጣል ያስችላል።” የጥቅሱ መጨረሻ ። የደራሲዎች የፅሁፋቸው ማሳረጊያው ይኸው ነው። ይህ አይነት ምክር የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ እንደሚባለው መዳረሻው ወዴት እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ምሳሌ ከተፈለገ በአለማችን በሽበሽ ነውና ለጊዜው እንተወው። አስፈላጊ ሲሆን ይቀርባልና። ለመሆኑ የሽማግሌ መንግስት ይመስረት ብሎ ያቀረበው ማን ነበር?
በበኩሌ ይህ አይነት ምክር ለሕዝብ የሚለገሰው በመስኩ ሙያተኛ ከሆኑትና በርካታ ተመክሮን ካካበቱ ሳይሆን በምሁርነት ካባ ተሸፋፍነው ግና የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሀ ሁ ምን እንደሆነ ጭራሱኑ ካልገባቸው ደናቁርት፣ አለበለዚያም በሥልጣን ላሉ የኃይማኖት እምነት አስተምሮሆትን ያለ ውዴታ በግዴታ በሕዝብ ላይ በመጫን የራሳቸውን አምባገነናዊ ሥርአት ለመግንባት ምኞት ካላቸውና የሥርአቱ ደጋፊ ለመሆን ከሚቃጣቸው ጥቂቶች ብቻ ነው። ነፃነትን የተላበሰ፣ በሕዝብ ለሕዝብ የሚገነባ ሥርአት መሰረቱ አቃፊ እንጂ አግላይ ሊሆን አይችልም።
ለማንኛውም በጅምላ የሚያዥጎደጉትን ስድባቸውን ወደ ጎን በማድረግና ከሳይንስ እውቀት ጋር የተጣሉበትን፣
ሀ). ስለ ዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሃሳብ፣
ለ). ሳይንስና ፍጥረት/ሕይወትና ትርጉሙ፣
ሐ). ስለ መሬት አፈጣጠርና እድሜ፣
መ). ነፃነትን ና ዴሞክራሲ፣
ረ). በኢትዮጵያ ተከስቶ ስለሚገኘው ችግሮችና መፍትሄ፣ በሁለቱ ደራሲዎች የተሰነዘሩት አስተያየቶችን ነቅሶ በማውጣት የሚኖሩንን ትችቶች በዝርዝር እንመለከታቸዋለን። ከኃይማኖት ጉያ ተሸጉጠው ባረጀ በፈጀ አስተሳሰብ 500 አመት ወደኋላ ሊመልሱን የሚቃጣቸውን የሚሸከም ትከሻ የለንም። ሰላም የመብት መከበር ውጤት ነውና የአፄውን፡ የደርግና የወያኔንም ጨቋኝ ሥርአት ለመደምሰስ ያለመታከት እልህ አስጨራሽ ትግል የምናደርገው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነፃነትን የተላበሰ ኑሮ በመኖር የራሱንም ሆነ የሀገሩን የወደፊት እጣ በጋራ እየወሰነ እንዲኖር ለማስቻል ነበር፣ አሁንም ነው። ይህ ነው የመኖራችን አልፋና ኦሜጋ። በዚሁም እንቀጥልበታለን። እስከዛው ሰላምና ጤናችን ይብዙልን!!