በአብዮቱ ማግሥት ደርግ ነጭ ሽብር ብሎ የሰየመው የኢህአፓ ሽብር እያየለ ሲመጣ በከተሞች እያንዳንዱ ሰው በቤቱ በር ላይ ፋኖስ (መብራት) እንዲያበራ ደርግ ሕግ አወጣ። የሚበራው የአምፖል ቢሆን ወይም የፍሎረሰንት መብራትም ቢሆን አዋጁን “የፋኖስ አዋጅ” ይለዋል ሰፈሬው በተለምዶ።
በኛ አጎራባች ገደላማ የከተማ ቀበሌ የብዙ ጎረምሶች አባት የሆኑ አንድ የአብዮት ጥበቃ ጓድ ኃላፊ ይህንን “የፋኖስ አዋጅ” ትእዛዝ በብርቱ ተቃወሙ። በዚህ ጊዜ አብረዋቸው የሚሰሩት የመኢሶን ካድሬዎች ጥርጣሬ አደረባቸው። ምናልባት የጥበቃ ጓዱ ኃላፊ ሌሊት በግድያ እና ሌላም ድርጅታዊ ተልእኮ የሚሠማሩ የኢህአፓ አባል የሆኑ ልጆች ይኖራቸው ይሆን? የሚል ጥርጣሬ። በኋላ ነገሩ ሲጣራ ልጆቻቸው ጨለማን ተገን አድርገው የመሸበትን መንገደኛ የሚቀሙ፣ አጥር ዘልለው ገብተው ቤት የሚዘርፉ አደገኛ ቀማኞች የነበሩ መሆኑ ተደረሰበት። አባትየው መብራቱን የፈሩት የልጆቼ ዝርፊያ ይደረስበታል፣ ጨለማውን ተገን አድርገው ለመዝረፍ ይቸገራሉ ብለው ነበር ማለት ነው። የፋኖሱ ነገር ያሸበራቸው ለዚህ ነበር። ይሄ ነገር ሲታወቅ የጥበቃ ጓድ ኃላፊው የፋኖስ አዋጁን መቃወሙን ትተው ልጆቻቸውን በጥበቃ ጓድ ምልመላ ውስጥ በማካተት በሌሊት እንደልባቸው ያለስጋት ጭራሽም መሣሪያ ታጥቀው እንዲንሸራሸሩ አደረጉ ተባለ።
ፋኖ ቀዬውን እና አካባቢውን ወሰኑን የሚጠብቅ ከሆነ የፋኖ መኖር የሚያሸብረው ይሄንን ቀዬ፣ አካባቢ ወይም ወሰን ጥሶ የሱ ያልሆነን ነገር ለመቀማት፣ ለመዝረፍ፣ ለመድፈር የፈለገን ኃይል ብቻ ነው። የፋኖ መኖር ልክ እንደ ፋኖሱ መኖር ዝርፊያና፣ ቅሚያውን የወንጀል ሥራውን የሚያጋልጥበት፣ የሚያስተጓጉልበት አካል ነው ፋኖን እንደ ፋኖሱ የሚጠላው። ፋኖሱን ካልሰበርኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁን ቢል ጨለማን ተገን አድርጎ ዝርፊያውን ሊቀጥልበት፣ ሊያጧጡፍና ሊያሳልጥ መሆኑ ግልጽ ነው።
በነገራችን ላይ monopoly of violence የመንግሥት ብቻ ነው የምትል ጥራዝ ነጠቅ ማጭበርበሪያና ማደናቆሪያ ከየጥራዝ ነጣቂው አፍ ስትወረወር ትደመጣለች። ፋኖ ድሮንና ክሩዝ ሚሳይል ይታጠቅ የተባለ ይመስል። ይሄ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ጦርነት በሌለበት ሰላማዊ የአሜሪካ ግዛቶች የፈለገ ገዝቶ የሚታጠቀው ሲሆን በአንዳንድ ግለሰብ ሲቪል አሜሪካውያን እጅ በአንድ ፋኖ ሳይሆን በአንድ የሕወሃት ጋንታ እጅ ካለው መሣሪያ የሚበልጥ ይገኛል። እንግዲህ በሰላም አገርና ምንም ስጋት በሌለበት ቦታ ነው ይሄ። ዙሪያውን በጠላት ተከብቦ፣ ሚስት እህት እናቱ እየተደፈሩ፣ እርሻና ቤቱ እየጋየ መሣሪያ አትታጠቅ የሚለው ወራሪው፣ ደፋሪው፣ ዘራፊው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ይህ ሕዝብ እኮ በሚበዛው ታሪኩ በሰላም ጊዜ ጭምር የነፍስ ወከፍ መሣሪያ የማይለየው ነው። መሣሪያ መያዝ ባሕሉ ሆኖ ሲኖር ዱላ መያዝ እንኳን ተከልክሎ ከነበረበት ዘመን የተለየ የወንጀል መስፋፋት የታየበት አልነበረም። ዛሬ ጦርነት ተከፍቶበት ወገኑ በወረራ ሥር እየማቀቀ ትጥቁን ለማስፈታትም ሆነ ፋኖን ለማሳደድ የሚፈልገው ኃይል በአማራው እልቂትና ጄኖሳይድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለው አካል ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው።
ኢመደበኛ የምትለዋም ነጠላ ዜማ ውሃ አትቋጥርም። ራሱ ልዩ ኃይል ኢመደበኛና ኤክስፓየር ያደረገው (ግን በጉልበት ሥራ ላይ የቀጠለው የኢህአዴግ ሕገ መንግሥት እንኳን የማያውቀው መዋቅር ነው። የኢመደበኛ ነገር ከተነሳ ብልጽግናስ በብርቱካን ሚደቅሳ ቸርነት ሥልጣን ላይ የተጎለተ ኢመደበኛ ፓርቲ አይደል እንዴ? ዝርዝሩ ሲባል ከርሟልና እዚህ ጊዜ አንወስድበትም። ይልቅ ፋኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ከውጭ ወራሪ ሲከላከልበት የኖረ በአማራው ክፍል ፋኖ በመባል የሚታወቅ አንድ የሀገር መከላከያ መደበኛ ተቋም ነው። ኢመደበኛ አይደለም።
በዚህም መሠረት ለሀገር እና ለወገን አስባለሁ የሚል መንግሥት ካለ ፋኖ ይህንን የሀገርና ወገን የመከላከል ሥራውን በብቃት እንዲወጣ ሁለገብ እገዛ ማድረግ ጉድለቶችም ካሉት እነዚህን በውስጡ በራሱ ሊያርምና ሊያስተካክል የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ነው የሚገባው። ይህም ሲባል ለሞት አሳልፎ ለመስጠት ይሁዳ ክርስቶስን እንደ ሳመው እናንተም ፋኖን ሳሙት ለማለት አይደለም (ሰሞኑን በባሕር ዳር እንደተደረገው)። ሐቀኛ ትብብር ይደረግለት ለማለት እንጂ።
ሳር እያሳዩ በሬን ገደል መስደድ የሀገር አስተዳደር ጥበብ ሳይሆን የተራ ብልጣ ብልጦች በውጤታቸውም ጅሎች ሊባሉ የሚገባቸው ባለ ትንሽ አእምሮ ሰዎች ፈሊጥ ነው። ገደል የገባው በሬ ሰኔ እያጉረመረመ የሐምሌና ነሐሴ ዶፍ ሲወርድ ለእርሻ ቢፈልጉት አይገኝምና።
ስለዚህ ጨለማና የጨለማ ኃይሎች ፋኖን ለቀቅ አድርጉ።