የግላስ ጌጧን አውልቃ ቅርቀብ ተጪና ስለአዩአት፣
በቅሎን አባትሽ ምንድነው በሚል ጥያቄ ሲያፈጧት፣
ፈረስ አጎቴ ብላ እርፍ የብልጠት ዲግሪ ስላላት፡፡
እንደ ፈረሱ የእህት ልጅ የብልጠት ዲግሪ የጫኑ፣
መሀል ሰፋሪው ምሁሩ ፕሮፌሰሩ ዶክተሩ፣
በጣር ያሉትን ተማሮች በቶሎ አስፈቱ ሲባሉ፣
የቦንዱን ግድብ አክስቴ አድዋ አጎቴ ይላሉ፡፡
ሕዝብን ተእልቂት ለማዳን ተደራጅተናል እያሉ፣
ይፎክሩና እንደ ወንድ ነፃነት ወይ ሞት እያሉ፣
በሕዝብ ጫንቃ ተሻግረው ምኒስቴር የፓርላማ አባል ሲባሉ፣
በሕዝብ ደም የተለወሰ ጉርሻ በደመወዝ መልክ ሲጎርሱ፣
እንደ ጅብ አሞት አፍሰው ማነከስ ይጀምራሉ፡፡
በመለስ ጆሮ ጠቢዎች ጆሮዎን ተላጉ ሲባሉ፣
መደመር የወንድሜ ልጅ ሱስም አጎቴ ይላሉ፡፡
ህግ አስከባሪ ጠበቃ አቃቤ ህግ ነን ባዮቹ፣
ለጭራቅ ታዛዥ ወስላቶች ጀግና ያስበሉት ዳኞቹ፣
ቃለ መሐላን ቦጨቁ አምላክን ከዱ ሲባሉ፣
አስቸኳይ አዋጅ አክስቴ የሽብሩ ህግ አጎቴ ይላሉ፡፡
ፓትርያሪኩ ጳጳሱ መነኩሴው አስራት ዘራፊው፣
ምእመን እንደ ጨፈቃ ተቃጥለው እነሱ እሳት ሲሞቁ፣
ታቦት እንደ ደመራ ሲያያዝ ሞዝቦልድ ተጋድመው ሲተኙ፣
እንደ ጴጥሮስ ሚካኤል ደፍራችሁ መሪዎች ሁኑ ሲባሉ፣
ተአቃጣይዎቹ ፊት ቀርበው እንደ አሽከር ደጅ ይጠናሉ፡፡
የቀለም አባት ነኝ ባዩ ጣት አፍተልታዩ ምሁሩ፣
ለአኝዋክ ሰዎች ዘር ማጥራት ፍትህን አምጡ ሲባሉ፣
በኦጋዴኑ የእሬሳ ጎታች ብይን በይኑ ሲባሉ፣
ለበደኖውም ዘር ፍጅት ፍርድን አውርዱ ሲባሉ፣
ተአስከሬን ክምር ቁጪ ብለው በሙታን ይቆምራሉ፣
ይቅርታ የወንድሜ ልጅ ፍቅር የእህቴ ልጅ ነው ይላሉ፡፡
ለወልቃይቱ ዘር ማጥዳት ልጓም አብጁ ሲባሉ፣
ለራያውም ዘር ማጥራት ገደብ ስሩለት ሲባሉ፣
ሰላም ምንስቴር እህቴ የእርቅ ኮሚቴ ወንድሜ ይላሉ፡፡
እነ ፈረስ አጎቴ ተደምረናል እያሉ ለኮር አባሎች ሲሰግዱ፣
ተባንዳ ጀርባ ተጣብቀው በላይ ምንሊክ ቴዎድሮስ ሲዘፍኑ፣
እንደ አርበኛ ልጅ አይነዱ ህሊና እንዳለው አያፍሩ፡፡
ተመቃብር እሬሳ እንደ ምስጥ ሲመጠምጡ የሚያድሩ፣
ዲግሪና ቆብን ኮፍሰው ፈረስ አጎቴ የሚሉ፣
ባንዶች የተከሏቸው አረም ምሁራን እያሉ፣
ፍትህና እውነት በጦቢያ እንዴት ተዘርተው ይብቀሉ?
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.