በሀገሩ ተወለደ፤ ሀገሩን በላቡ ዓለም አደባባይ ወለደ፡፡ ዛሬ የማይቀደመው-ኢትዮጵያዊ ጀግና ልደት ነው!! (በሄኖክ ስዩም )

ኃይሌ የማይቀደም ሰው ነው፤ ከስሙ ፊት ብዙ ስሞች አሉ፤ ሰዎች ሁሌም የሚመርጡትና ቅድሚያ የሚሰጡት ግን “ጀግናው” የሚለውን መጠሪያ ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያዊው ጀግና ልደት ነው፡፡

አትሌቱ፣ የሀገር ሽማግሌው፣ አርበኛው፣ ሥራ ፈጣሪው፣ ኢንቨስተሩ፣ ሻለቃው፣ የዓለም ክብረ ወሰኖች ጌታ ተደምረው ጀግንነቱን ሊገልጡ ጀግናው የሚለው ቃል የእሱ ሆኖ ከስሙ ቀደመ፤ በሀገሩ የተወለደው የዓለም ሰው፣ ሀገሩን በላቡ ዓለም አደባባይ ላይ በመልካም ስም ወለዳት፡፡

የሀገሩን ክብር ከፍ አድርጓል፡፡ ስሟን አስጠርቷል፡፡ ደግሞ ሀገር ኾኗል፤ እሱን እንጂ ሀገሩን በስሟ የማያውቅ የሀገሩን ሰንደቅ ዓይቶ ስሙን ይጠራል፡፡ ስሙ ሲጠራ የኢትዮጵያ ስምም አብሮ ይጠራል፡፡ ሀገሩን ያስጠራው ለሀገሩ ስም የሆነው አትሌት እንኳን ተወለደ የምንለው በምክንያት ነው፡፡

ኃይሌ አይቀደምም፤ ከፊት ይሆናል፡፡

በተሰማራባቸው ኢንቨስትመንቶች ሁሉ ሀገር በምሳሌ የምታነሳቸውን ስራዎች ሰርቷል፡፡ ሮጦ መቀደምን ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ልማት ላይ የደገመ ሥራ ፈጣሪ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ በላቀ አገልግሎት አጠጣጥ ምልክት የሆነን መለዮ ስያሜና ተቋም ገንብቷል፡፡ ኃይሌ ሪዞርትና ሆቴሎች የሥራ እድል፣ ልማትና ሀብት ብቻ አይደሉም፡፡ የላቀ አገልግሎት አሰጣጥ ማሳያ ትምህርት ቤቶችም እንጂ፡፡

ለዚህ ነው እንደ ኃይሌ ዓይነት ጀግና ብቻውን አልተወለደም የምንለው፤ ኢትዮጵያ ተወልደው የወለዷት ጀግኖች ድንቅ ሰርተው ያጸኗት ሀገር ናት፡፡ እናም የጀግናው ሰው ልደት የሀገር ልደት ነው እላለሁ፡፡ ሀገርም መልካም ልደት የምትባልበት፤ አንዳንዱ ከእናት ከአባቱ ብቻ ሳይሆን ከሀገሩም ይወለዳል፡፡ ሀገሩንም ይወልዳል፤ ለሀገሩ ምልክት ይሆናል፡፡

ስለ ኃይሌ ዘፍነናል፡፡ እንደ ስሙ ከገጠመው ድሉ ጋር አብደናል፡፡ ስኬቶቹ ሀገር ማኩራት ብቻ ሳይሆን ሀገር የሚማርበት ሆኖ በምልክነት ደጋግመን አንስተነዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ልደቱ ነው፤ መልካም ልደት እንለዋለን፤ ኃይሌ ስለተወለደ፤ ብዙ ሜዲያሌያዎችን ሲያጠልቅ አብረን አጥልቀናል፤ ድል ሲያደርግ ድል አድርገናል፤ ደግሞ ሲያለማ ወገን የዕለት ጉርስ አድርጓል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያነበዉ የሚገባ ከሕወሓት ጓዳ የወጣ ወሳኝ መረጃ - "አማራን ለመነጣጠል የተዛቡ ታሪኮችን መጻፍ"

በትልልቅ ሀሳቦች እንደ ታላቁ ሩጫ ዓይነት ሀገር ያተረፈችበትን ቅርስና ውርስ አስረክቦናል፡፡ ሀገሩን ያመከነ ሳይሆን ሀገሩን በብዙ የወለደው ሰው ደጋግመን እንላለን፤ እንኳን ተወለደ፡፡ መልካም ልደት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share