April 12, 2022
5 mins read

የጥፋት እሣትና ኢትዮጵያዊነት (በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ)

እሣት ፣ እሣት ፣ እሣት ነው ፤ ዘመኑ
የሚጋረፍ ፣ የሚለበልብ ፤ ወላፈኑ
የሚቀቅል ፣ የሚጠብሥ  ፤ ሙቀቱ
የሚያከሥል ፣ የሚያሣርር  ፤ ቁጭቱ ፡፡

………………………………………..
ጉልቻ  እየተቀያየረ  ከተረሳ  ድስቱ
አይቀርም  በእሳት  መጎርናቱ  ፡፡
ገብስ እንኳ  ፣ በወግ ካልሆነ አቆላሉ
በእሳት ፣ አራሪው ይበዛል ከብሥሉ ፡፡

…………………………………
ለዚህ ነው እናቶች ገብሥ ሲቆሉ
የአሻሮ እና የቆሎ ጉልቻን የሚያሥተካክሉ ፡፡
ለቆሎ ጥቂት አሸዋ ምጣዱ ላይ የሚበትኑ
ገብሱን ከማረር ፣ ከአሻሮነት ሊያድኑ ፡፡

………………………………………..
አገር ተገንዘብ  ወግኛውን የእሣት ጫወታ
በገዛ አገርህ ሳያደርግህ ከርታታ ና አውታታ
ዛሬ እጅግ ረቋልና  የእሣት ጫወታ

እንዳይመስልህ ሥካር ፤ የፖለቲካ ሞቅታ  ፡፡

አእምሮ ቢሱ ፣ ሲጫወት እያየህ ፣ የሞት ጫወታ ፡፡

………………………………………………
ሰው ሆይ ፣ አስተውል ፤ አትሆን አጉል ተቺ
እወቅ ፣ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ እንዳለ ፣ ለሰው ሟቺ ፡፡
ለአምሳየው ተጨናቂ ፣ ተሟጋቺ ።
ከእሣት ጋራ ተናናቂ
እሣትን ጣይ አስወዳቂ
አለ እጅግ ብዙ ፣ ጀግና ወጣት  በአገሬ
መሰዋት ሆኖ የሚያኖረኝ በየመንደሬ  ።

(በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )
ሚያዚያ 3/ 2014

 

ማሳረጊያ
( ሚያዚያ 1/2014 ዓ/ም በመኖርዬ ጊቢዬ ውሥጥ የተከሰተው ይኽ ፣ እሣት ፣ ብዙ ንብረት እንዳያወድምና ከእኔ ቤት አልፎ በአካባቢው መኖሪያ ቤቶች ላይ እንዳይዛመት ሲሉ ፤ ልብሳቸውን አውልቀው ፣ በቁምጣ ፣ ከሚጋረፈው እሣት ጋራ ተናንቀው ፣ አንድ ነፍስ ሳትጠፋ ፣ ድል ለነሱ ፣ የናዝሬት ነዋሪዎች ( ወርቅ ሰዎች ) ፣ ከቅርብና ከሩቅ መጥተው አካባቢውን ላጥለቀለቁት ና ላዘኑልኝ በሺ ለሚቆጠሩ ሰው መሆናቸውን ብቻ ለሚያውቁ የፈጣሪ ፍጡራን ሸዎች ፣ በሙሉ ፣ ይኽ ግጥም መታሰቢያ ይሁንልኝ ። በዚህ አጋጣሚ እሣቱን የናዝሬት ወጣትና ጎልማሣ በአፈር ና በውሃ ከተቆጣጠረው ከአንድ ሠዓት በኋላ የመጣው ፣ የአዳማ እሣት አደጋ መሥሪያ ቤት የሥልክ መሥመር ዕዳ አለው ተብሎ ተቋርጧል መባሉን መንግሥት አጣርቶ አሥቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወሥድና በየቀበሌው ቋሚ የለሊት የየመንደር ጉብኝት በፀጥታ አካላት እንዲደረግ አሣሥባለሁ ። የመብራት ኃይል አሠራር እጅግ እየተበላሸ እንደመጣና ( እሥከዛሬ መብራቱ አልተቀጠለልንም ) ለሥራ ዳተኛ መሆኑ እየባሰ ብቻ ሣይሆን ፣ የእሣት አደጋ ሲፈጠር መሥመሩን ለማቋረጥ ፈጥኖ ባለመድረሱ ፣ የሚያሥከትለው እልቂት ወደፊት ሊኖር ሥለሚችል ፣ ከወዲሁ ቢታረም መልካም ነው ። እንደመብራት ኃይል ና እንደ እሣት አደጋ የመንግሥት ተቋም ዳተኝነት ቢሆን ኗሮ በዚህ እሣት አልቀን ነበር ። ሆኖም ለፈጣሪ እየፀለየ ባለው በፆሚው ክርስቲያን እና ሙሥሊም የናዝሬት ህዝብ ከእልቂት ተርፈናል ። ክብር ለፈጣሪያችን ። አሜን ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop