ያውቅ የሚናገር፤ ሳያነብ የሚጭር ጩኸት ብቻ ሶፍት ዌር እንዳልተጫነበት ኮምፒዩተር ነው!

በበላይነህ አባተ abatebelai@yahoo.com

 
የስብከት ሽውታ ሰውን የሚነዳው፣
ጭንቅላቱ እንደ ቅል ውስጡ ክፍት ሲሆን ነው፣
ሸወዱኝ ተሸወድኩ የዱባ ጠባይ ነው፣
እድሜ ልክ ቀቅሎት ቀቃዩን የሚያምነው፣
እንደገና ሰብኮ ተጓሮው ሲተክለው፡

braine wሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ አንድ አብሮኝ ይማር የነበረ ጎበዝ በተለምዶ “ልብ ወለድ” የሚባል መጽሐፍ ሳነብ አየኝና ተክተክ ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ምን እንደሚያስቀው ስጠይቀው “ይኸንን በማንበብ ጊዜህን የምታባክነውና ዓይንህን የምትጨምቀው ማትሪክ ለማለፍ እንዲረዳህ ነው ዝንቅል!” አለና ዳግም ስቆብኝ ሄደ፡፡ ዝንቅል የሚለውን ለማያውቅ ትርጉሙ ሞኝ ወይም ቂል ማለት ነው፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ሌላ የዶክትሬት ዲግሪ አለኝ እያለ ደረቱን እንደ ዓባይ ጋራ የሚነፋ ጎበዝ “ከትምህርት ቤት ከወጣሁ ጀምሮ አንዲት ገጽም አንብቤ አላውቅም፤ ምን ሊያደርግልኝ!” ሲል ሰማሁት ላለማንበብ በመወሰኑ እየተኩራራ፡፡ ይክ ጎበዝ የዶክትሬ ዲግሪውን ከተቀበለ 18 ዓመታት አልፈውታል፡፡

የሚገርመው ሰው ለማህበራዊ ጉዳዮች ሲገናኝና ውይይት ሲከፈት ያለማቋረጥ ተናጋሪዎችና ሁሉን ልፍጀው ባዮች እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ የአገርና የፖለቲካ ነገር ሲነሳማ ሌላውን ገፍትረው ወደ ዳር አሽቀንጥረው ተመሐል ገብተው ውይይቱን የቅቤ ገበያ የሚያስመስሉት እነሱ ናቸው፡፡ ሳያውቅ የሚናገርና በጥልቀት ሳያነብ የሚጥፍ ሰው “ጭጭጭጭጭጪ” እያለ ተሚንጣጣ ጥቅም ተሌለው ኮምፒዩተር የሚለየው በምንድን ነው?

ከብዙ አመታት በፊት ጎርደን ቴለር “ሰው ማሽን ወይንም ኮምፒዩተር ነውን?” ሲል ጠይቆ ነበር*፡፡ ኮምፒዩተር ሐሳብን ሰብስቦ  በፈርጅ በፈርጁ ያጠራቅማል፡፡ ኮምፒዪተር ያስባል፤ ያሰላል፡፡ እንዲያውም ሰው ማስላት የሚሳነውን ስሌት ይቀምራል፡፡ ስእል ይስላል፡፡ ወንጀለኛ ይለያል፡፡ ኮምፒዩተር አብዛኛው ሰው የማይሰራውን የተወሳሰበ ሥራ ሁሉ ይፈጥማል፡፡ ኮምፒዩተር እንደሰውም ይታመማል፤ ሲጨንቀውም ጭ…ጭ.. ብሎ ይጮሃል፡፡ ቫይረስም ያጠቃዋል፡፡ የቫይረስ መከላከያና መድኅኒትም ጤንነቱን ይጠብቅለታል፡፡ እንደ ሰውም ያረጃል፤ ተሰባብሮ ይወድቃል ወይም ይሞታል፡፡ ስለዚህ ኮምፕዩተር ሰው፣ ወይም ሰው ኮምፕዩተር ነውን? ሰው ኮምፒዩተር ከሆነ ሰውን ኮምፒዩተር የሚያደርገው አንጎሉ ይሆን? እውንን ኮምፒዩተርና አንጎል አንድ ናቸውን?

የሰው ልጅ አንጎል አራት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም ሰረብረም (ትልቁ አንጎል) ፣ ዴንሰፋለን (መካከለኛው አንጎል) ፣ ሴረብለም (ትንሹ አንጎል) ና የአንጎል ግንድ (ብሬን ስቴም) የሚባሉት ናቸው፡፡ የስእሉን መረጃ ከጎን ይመልከቱ፡፡

ስሙ እንደሚያመለክተው ትልቁ አንጎል ስራው መመራመር፣ መፈላሰፍ፣ ለምን፣ የት፤ መቼ፣ እንዴት፣ ማን? ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ መካከለኛው የአንጎል ክፍል  ከታላመስ(thalamus)፣ ሀይፖታላመስ(hypothalamus)፣ ኢፒታላመስና(epithalamus) ሌሎችንም ያልተጠቀሱ ጥቃቅን ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡  ታላመስ የስሜት ህዋሳት ወደ ትልቁ አንጎል ሊያስተላልፉ የፈልጉትን መልእክት ያጣራል፡፡ የምናየውን የምንሰማውን፣ የምናሸተውን፣ የምንቅምሰውንና የምንዳስሰውን ይነፋል፣ ያበጥራል ማለት ነው፡፡ የማበጠሩን ሥራ የሚሰራው መሐሉን እሳት እንደበላው ሰፌድ ወይም ቦርገድ ቦርገድ ተደርጎ እንደተሰራ ወንፊት ክፍት እስካልሆነ ድረስ ነው፡፡ ሃይፖታላመስ ደግሞ ርሃብን(ወይም ጥጋብን)፣ ጥማትን(ወይም ርካታን)፣ መብረድን(ወይም መወበቅን)፣ የግብረ-ስጋ ግንኙነት ፍላጎትን፣ ቁጣን ወዘተ የመሳሰሉትን ቅፅበታዊ ፍላጎቶችን (emotions) ያስተዳድራል፡፡ ኢፒታላመስ ደግሞ እንደ እንቅልፍ ያሉትን በዑደተ-ቀለበት የሚመጡትን ክንዋኔች(circadian rhythms) ላይ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡  ትንሹ የአንጎል ክፍል በፈንታው አረማመዳችንን፣ ሚዛን አጠባበቃችንን፣ አቋቋማችንን ወዘተ ይቆጣጠራል፡፡ የአንጎል ግንድ  የተባለው እንደዚሁ መሐለኛው አንጎል (mid brain)፣ ፓንስና(pons) ሜዱላ(medula) የሚባሉትን ነገሮች ያካተተ ሲሆን ስራውም ብዙ ነው፡፡ የልብ አመታት፣ የስተንፋስና ሌሎችም ለህይወት ቁልፍ የሆኑ ነገሮች መስሪያ  ቤቶች ሁሉ ከዚህ ስፍራ ናቸው፡፡

ከትልቁ አንጎል በስተቀር ሌሎቹን የአንጎል ክፍሎችን ከጅቡ፣ ካሳማው፣ ከአህያው፣ ከበሬው፣ ከቀበሮው ከፍየሉ ወዘተርፈ ጋር ሰው ይጋራል፡፡ እነዚህ ሁሉ የስሜት ህዋሳት አላቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ይርባቸዋል፣ ይጠማቸዋል፣ ይናደዳሉ፣ ይራባሉ፣ ይተኛሉ፣ የራሳቸው የሆነ የአቋቋምና አረማመድ አይነት አላቸው፡፡ የእስተንፋስና የልብ አመታት ተቆጣጣሪ ቢሮም አላቸው፡፡ ስለዚህ በሰውና፤ በእግዚአብሔር ፈቃድም ሆነ በአዝጋሚ-ለውጥ (evolution) ከርሱ ወረድ ብለው ባሉት እንሰሳት የአንጎል አይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ባብዛኛው ከትልቁ የአንጎል ክፍል የሚመነጭ ነው፡፡ በተቃራኒ መንገድ ግን አንጎል ከኮምፒዩተር ጋር የሚመሳሰለው በትልቁ የአንጎል ክፍል አማካኝነት ነው፡፡ ትልቁ አንጎላችሁ በምን አወክ ብሎ ወጥሮ እዚሁ አያዘኝ እንጅ ኮምፑተር አይርበውም፣ አይጠማውም፣ ጉቦ ሲበላም አይታይም፡፡ እነዚህ ከታናሽ የአንጎል ክፍሎች የሚመነጩ ባህርያት ስለሌሉት ኮምፒዩተር አንጎል አይደለም፡፡ አንጎል ካልሆነ ደግሞ ሌላው የሰውነት ክፍሉ ከሰው አያመሳስለውም፡፡ ስለዚህ ኮምፕዩተር ሰው አይደለም፡፡

ከዘፍጥረት አንጣርም ስናየው አንጎል የመለኮት እደ ጥበብ ሲሆን ኮምፒዩተር ደግሞ የሰው የእጅ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በአፈጣጠር፣ በተፈጥሮና በምግባር አንጎልና ኮምፒዩተር የተለያዩ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን አንጎልና ኮምፒዩተርን የሚያመሳስሏቸው ባህሪያት ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሶፍት ዌር ያልገባበት ኮምፒዩተር ሊናገር ሲሞክር የሚገኘው ውጤት እውቀት ሳይጎበኘው ተምላስ እንደተገናኘ አንጎል “እቡ…እቡቡ… “ እያለ ትርጉም የሌለው ፍሬከርስኪን መንጣጣት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎችን ተመሳሳይ አገሮች ተገጠሟቸው ችግሮች ሁሉ ቁንጮው ሶፍት ዌር እንዳልገባበት ኮምፒዩተር የሚንጣጣ እውቀት አልባ አንጎል ነው፡፡ እውቀት ሳይገባበት የሚንጫጫውን አገረ ገዥ፣ የፖለቲከኛ፣ ካድሬ፣ ጋዜጠኛ፣ ጠበቃ፣ ዳኛ፣ ሐኪም፣ ነርስ፣ ፋርማሲስት፣ መሀንዲስ፣ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ፣ የሰብአዊ መብት ተከላካይ፣ የጦር መኮነን፣ ተራ ዜጋ አንጎል መለኮት ይቁጥረው፡፡

ሞኝ ሕዝብ እውቀትን ከትምህርት ቤት ተሚገኝ የቢኤ፣ ማስተርስ፣ ኤም ዲና ፒ ኤች ዲ ጋር ያዛምደዋል፡፡ ይኸንን የሕዝብ ሞኝነት የተረዳው እውቀት እንደ ሰማይ የራቀው ባለዲግሪም “ምሁርን ነኝ” እያለ ጣቱን እያፍተለተለ ሲደሰኩር ይውላል፡፡ ለእንጀራ ሲሉ ብቻ ሲሸመድዱ ታልዋሉ ትምህርት ቤት ማዋልና እነዚህን ዲግሪዎች መጫን የእውቀት መገኛ መንገዶችን ሊጠቁም ይችላል፡፡ ዲግሪውን ተጫነበት ማግስት ጀምሮ  እንኳን ስለጠቅላላ እዉቀት ስለሙያውም መጻሕፍት ያላገላበጠ አንጎል የዘመኑን ሶፍት ዌሮች ማንበብ ተማይችል በስልሳዎቹ ከተሰራ ሳጥን ተሚያህል ኮምፒዩተር በምን ይለያል?

እድሜ ልኩን ስለምጣኔ ሐብት ምርምር ያላደረገ ሰው ስለ አገር ምጣኔ ሐብት ሊያስተምር የሚዳዳ አንጎል፣ ስለጤና ጭላጭ እውቀት ሳይኖረው ስለበሽታ መከላከያ ዘዴዎች ሊያስተምር የሚከጅል አንጎል፣ የምንድስና ትርጉም ሳይገባው ስለከተማ አመሰራረትና መንገድ አሰራር ሊያስረዳ የሚችል ከንቱ አንጎል የአማርኛ ሶፍት ዌር ሳይኖረው የአለቃ ደስታ ተክለወልድን መዝገበ ቃላት ሊያነብ ተሚጥር ኮምፑተር በምን ይለያል?

አብዛኛው የዚህ ዘመን አንጎል እንደ መጻሕፍት ታሉት የእውቅት ገበያዎች እንደ መንግስተ ሰማይት ርቆ እንደ ፌስ ቡክና ዩ ቱዩብ ታሉ የቡና ወሬ መንደሮች እንደ ሙጫ ተጣብቆ ይውላል፡፡ አንዳንዱ ዓይን አውጣ አንጎል እንዲያውም “መጻሕፍትንም ሆነ ረጅም ጽሑፍን ማንበብ ያስጠላኛል” ሲል ይደመጣል፡፡ መጽሐፍ ሳያነቡና ሳይመራመሩ በቡና ወሬ ብቻ እውቀት በምን ታምር ተአንጎል ማህደር ሊንቆረቆር ይችላል? ሶፍት ዌር እንደሌለው ኮምፒዩተር ጠቅላላ እውቀት ያልሰፈረበት አንጎልስ የሚሰማውን ነገር በምን ሰፌድ አበጥሮ ገለባውን ተግርዱ መለየት ይችላል? በጠቅላላ እውቀት ካስማነት ፀንቶ ያልቆመ አንጎል በሚሰማው የድስኩር ነፋስ ሁሉ እንደ ገለባ ተመነዳት በምን ታምር ሊድን ይችላል?

የድሮ አባቶች ለእውቀት ከነበራቸው ጥማት የተነሳ ተከብት ቆዳ ብራና ፍቀው፣ ከእፀዋት አበባዎች ቀለም በጥብጠው፣ ተአእዋፋት ክንፍ ብዕር ሰርተው ዛሬ የዓለም ቤተ መጻሕፍትን ያጥለቀለቁትን ትላልቅ የብራና መጻሕፍት ጽፈው አልፈዋል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት ለመጣፍም እጅግ ብዙ መጻሕፍትና ድርሳናት አንብበዋል፤ በእውቀት ተከራክረዋል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ሲያልቁና እኛ በምድጃ ዳር ተረት ተረትና በቡና ወሬ የተጠመድነው እውቀት አልባዎች ስንተካ አገራችን የተንሸራተተችበትን ገደል አይተናል፡፡ ተእውቀት እስተ ወዲያኛው በተጣላ አንጎል ቅስናን፣ ምንኩስናን፣ ፕትርክናን፣ ጵጵስናን፣ ሽምግልናን፣ ሼህነት፣ እውነትን፣ ምስክርነትን፣ ንስሃንና አብሮ የመኖርን ፀጋ ገለናል፡፡

ሕዝብ በገዥዎች የወሬ ነፋስ ተነድቶና ድምጥ ሰጥቶ ሶቅራጥስን እንደ ክርስቶስ ታስገደለው በኋላ ታላቁ ፕላቶ አገር በእውቀት በዳበሩ ፈላስፋዎች እንዲመራ ምክሩን ሰጥቷል፡፡ ፕላቶ ይኸንን የመከረው ለፈላስፋዎች አድልቶ ሳይሆን  በእውቀት ያልዳበረ ሕዝብ በወሬ ነፋስ እንደ አቧራ ተጠርጎ እንደሚነዳ በዓይኗ በብረቷ ስላየውና እውነተኛዋ እውቀት ሰውን ተግልብነት፣ ተስግብግብነት፣ ተሌብነት፣ ተቀጣፊነት፣ ተአድርባይነት፣ ተአድሎ፣ ተዘረኝነት፣ ተጠባብነት፣ ተጭራቅነት ወዘተርፈ ታጠዳዋለች ተሚል እምነት ነበር፡፡

ተመለኮት ቀጥሎ እውቀት የዓለም መድሀኒት ነው፡፡ እየከፋ የሄደው የዓለም ችግር መንስዔ ሥረ መሰረቱ ቢጠና መለኮትን ተካደና እውቀት ታልዞረበት አንጎል የሚመነጭ ነው፡፡ መለኮትና የካደና እውቀት ያልሰፈረበት አንጎል ሶፍት ዌር ታልተጫነበት ኮምፒተርም የባሰ ከንቱ ነው፡፡ እውቀት ያልሰፈነበት አንጎል ገዥ ሲሆን እንደ አበደ አውሬ የሚናከስ እርኩስ፣ ተገዥ ሲሆንም የወሬ ነፋስ እንደ ገለባ የሚነዳው እግዚአብሔር በአምሳሉ ያልሰራው ፍጡር ነው፡፡ እንደ አውሬ የሚናከስና የሚያናክስ እውቀት አልባ ገዥ እድሜው የሚረዝመው በወሬና በስብከት ነፋስ ተጠርጎ ተሚሄድ ተገዥ ሕዝብ ሲጫን ብቻ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሶቅራጦስም ሆነ ክርስቶስ የተሰውት እንደ አበደ አውሬ በሚናከስ የገዥዎች አንጎልና እንደ ገለባ በሚነዳ እውቀት አልባ የሕዝብ አንጎል “ስቀለው ስቀለው” ባይነት ነው፡፡ በሶቅራጥስና በክርስቶስ የደረሰው ግፍ ዛሬም በአገራችን እንደ ዶፍ እየወረደ ነው፡፡ እውቀትን፣እውነትንና ፍትህን እሚከተል ሁሉ “ስቀለው ስቀለው” እየተባለ እየጠፋ በክህደት፣ በስግብግብነት፣ በስርቆት፣ በዘረፋ፣ በቅጥፈት፣ በአድሎና በአረመኔነት ደቁኖ የቀሰሰ እውቀት አልባ ቁማርተኛ አንጎል እንደ ተባይ እየፈላ ነው፡፡ ይኸንን የተባይ መንጋ ሕዝብ የሚቋቋመው አንጎሉን የእውቀት ትጥቅ አስታጥቆ በስብከትና በቡና የወሬ ነፋስ እንደ ትቢያ አንዴ ወደ ምስራቅ ሌላ ጊዜ ወደ ምእራብ መብነኑን ታቆመ ብቻ ነው፡፡

የፍሬከርስኪ ስብከትንና የማዘናጊያ ወሬን ነፋስ የሚቋቋመው በእውቀት የታነፀ አንጎል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እውቀትን ስንፈልግ ሳይሆን ፍሬከርስኪ ስብከትና ማዘናጊያ ወሬ ስናነፈንፍ ውለን እያደርን አንጎላችንን ሶፍት ዌር ያልተጫነበት የኮምቢተር ሳጥን አናድርገው፡፡ እውቀት ያልሰፈረበት አንጎል ሶፍት ዌር ያልተጫነበት ኮምፒዩተር ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

* The natural History of the mind, Gordon Taylor, 1979

ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Abiy
Previous Story

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኔስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ

AEUP
Next Story

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop