ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኔስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ

ከአልማዝ አሰፋ
imzzassefa5@gmail.com

ክቡር ጠቅላይ ሚኔስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ:-

እኔ የፓለቲካ ምሁር ወይም ተንታኝ ሳልሆን ስለተወለድኩባት አገርና ከትውልድ ወደ ትውልድ በሰው ሰራሽ መከራ ስለሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማስብ ለ50 ዓመታት ያህል በአሜሪካ የምኖርና ወደ ኢትዮጵያ የማልመለስ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተራ ሰው ነኝ:: የፖለቲካውን ትነተናና ግምገማ ለሱሰኛ ተራቢዎች በመተው: የሚሰማኝን በዘ-ሐበሻ ድረ ገፅ ላይ በማቅረብ በግልፅ ላካፍሎት መረጥኩኝ::

አገርን አገር የሚያደርገው ሕዝብ ነው:: ሕዝብ ተባብሮ በእንድነት አምኖ በሕብረት ያለበትንና የሚኖርበትን አካባቢ የጋራ አድርጎ ሲቀበል ከክልልነት ወጥቶ አገር ይመሰርታል:: ዛሬ ግን ኢትዮጵያ እንደአገር ከመታሰቧ ይልቅ : የክልሎች ጥርቅም ሆና ትታያለች:: ይህ በእርሶ አመራር የተጀመረ ሳይሆን ካለፈው የከፋፍለህ ግዛ አስተዳደር ስርዓት የወረሱት እንደሆነ : ሳይጠየቅ ያለፈቃዱ በግዴታ በክልል የተከፋፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል:: ሆኖም እርሶ የዛሬ ሶስት አመት ከአስራ አንድ ወሮች በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጡ : በአገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ ያለው እውነተኛ ኢትዮጵያውያን በአነጋገሮና በአቀራረቦ ተማርኮ : በእርግጥም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የአንድነትና የአገራዊነት ጎህ እንደበራላቸው ተሰምቷቸው የደስታ ጮቤ እረገጡ:: እርሶንም በዘመናቶች አልፎ አልፎ ለመልካም ለውጥ አምላክ መርቆ ከሚልካቸው መሪዎች አንዱ እንደሆኑ በመቁጠር ደሃውና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እልል ብሎ እንደተቀበሎት ይረዳሉ ብዬ አምናለሁ:: ከዚያም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃል የነበረውን መሻከር አስታርቀው በዓለም የሰላምን ኖብል ሽልማት ሲያገኙ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ ከጎኖ እንደቆመ እርሶም ይገነዘባሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርሶ አምኖ ካለበት ድህነት ለመውጣት ከፍ ሲል እንደሰው : ዝቅ ከተባለም በኢትዮጵያዊነቱ እከበራለሁ ብሎ ሲተማመን : ዛሬ ኢትዮጵያ የአንድነትና የህብረት አገር መሆኗ ቀርቶ : የኦሮሞ ተራኛነት መናኸሪያ እንደሆነች ሲሰማው : እርሶ እንደአገር መሪ ምን ይሰሞታል? ይህ የተረኛነት ስሜት የሚንፀባረቀው በሰፊው ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ላይ ሳይሆን : በጥቂት ኤሊቶችና በመንግስት አስተዳደር ላይ የተሰገሰጉ ሰባዊነት የተሳናቸው ራስ ወዳድ : በሕዝብ ስቃይና ርሃብ እየተሳለቁ : የአገኙትን ሥልጣን የግል ሃብት ማከማቻ ያደረጉ : የኦፒዶ ጁንታዎች ነው:: በእርግጥም ይህ ምግባረ ብልሹነት በሁሉም ክልሎች አስተዴደሮች ውስጥም ይታያል:: ሆኖም የዛሬ ኦዴድ የትላንትናው ሕወሓትን የተካ ይመስላል:: በተቻለው መጠን ኦዴዶች ዛሬ ሌላውን ኢትዮጵያውያን አፍነው : ተቆጣጥረው : ጨቁነውና በድለው : ኢትዮጵያዊነትን አጥፍተው ወይም በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠው ኦሮሞነትን የበላይ ለማድረግ የሚጥሩ ይመስላል:: እርሶም በዚህ ድርጅት ውስጥ አድገው የድርጅቱን ዓላማ ተቀብለው መርተዋል:: የኢሐደግን መሪነትም ያገኙት ይህንን ድርጅት ወክለው እንደሆነ ይታወቃል::

ቲፒለፍ አዲስ አበባ ገብቶ ሥልጣን ሲወስድ እርሶ ገና የ15 ዓመት ልጅ ነበሩ:: እድገቶም በዚህ ሰውበላ ስርዓት ውስጥ መሆኑን የማይገነዘብ የለም:: ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ እርሶን እንደ ግለሰብ ተጠያቂ ማድረግ : 120 ሚልዮን የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠያቂ ማድረግ ነው:: ግን የመሪነትን ቦታ ሲይዙ በአገሪቱ አስተዳደር ውስጥ ከላይ ሹማማምንት እስከ ተራ ዘበኛ የመንግስት ሰራተኛ ለሚያሳየው ብልግናና የስነምግባር ብልሹነት እርሶ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይገነዘቡታል:: እንደሚታወቀው የኢሐደግ ስም በብልፅግና ተቀየረ እንጂ : የድርጅቶች አቋምና የጎሳ ፖለቲካው እንደነበረ ነው ቢባል ከሃቅ የራቀ አይሆንም:: በፊትም በኢሐደግ ውስጥ ጠባብ ጎሰኝነትንና ፅንፈኝነትን ሲያራምዱ የነበሩ የኢሐደግ አባሎች : ዛሬ በብልፅግና ስም የሚያካሄዱት ጠባብ ጎሰኝነትና : ጎጠኝነትና ፅንፈኝነት እንደበፊቱ ነው:: እርሶ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ሲመረጡ ለመጀመሪያ ሁለት ዓመታት የጎሳው ፖለቲካ ትንሽ ገርበብ አለ እንጅ አልጠፋም ነበር:: አሁን ግን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል:: በቋንቋ ስም የተሰየሙ ክልሎች ለኢትዮጵያዊነት አደጋዎች ናቸው:: በተለይ የኦሮሞ ብልፅግና ፖርቲ (ኦዴድ) ለዚህ ለጠባብ ጎሰኝነት እሳት መባባስ ዘይት እያፈሰሰ ይገኛል::

የዛሬ ሶስት ዓመት ከአስራ አንድ ወሮች በፊት ሥልጣን ላይ ሲመጡ : በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን : እርሶ በተናገሩት ዲስኩር ተደንቆ : ኢትዮጵያን ካለችበት ጨለማ ያወጧታል ብሎ የተማመነው ሕዝብ : ዛሬ ተስፋው እየዳሸቀ : በእርሶ ላይ የጣለውን እምነት እያጣ ይገኛል:: ዛሬ ሕዝቡ ምንያህል እምነት በእርሶ አስተዳደር ላይ አለህ ብሎ ቢጠየቅ (opinion poll) የዛሬ ሁለት ዓመት ከነበረው እምነት ቀንሶ ይገኛል:: ይህ ለምን ሆነ? ብለን ብንጠይቅ ሕዝቡ የጠበቀው የብልፅግና ጎህ ወደ ጨለማ እየተቀየረበት ስለመጣ ነው:: ማስረጃዎች:-

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሃላፊነትና ተጠያቂነት - ጠገናው ጎሹ

1. የኑሮ ውድነት ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት እንጂ አልተሻለለትም:: የእርሶ አስተዳደር : ነጋዴዎች ተጠያቂነት ሳይሰማቸው ትርፋቸውን ለማሳደግ ሸቀጦችን በፈለጉት ዋጋ ሲሸጡ : መቆጣጠር የማይፈልግ ነው ብሎ ሕዝብ ያስባል:: እንዲያውም የእርሶ መንግስት ሹማምንቶች ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው በጉቦ ኪሳቸውን የሚሞሉ ሙሰኞች በመሆን ከሕወሓት ሹማምንቶች የባሱ እንጂ እንደማይሻሉ ሕዝብ ይገምታል::
2. የብልፅግና ፖርቲ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን ስትረከቡ : ሹማምንቶች ያላቸውን ንብረት ማሳወቅና ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል ተብሎ ነበር:: ካላስመዘገቡ ደመዎዝ እንዳይከፈላቸውም ተወስኖ ነበር:: እስከዛሬ ድረስ ይህ ፍፃሜ ላይ እንዳልደረሰና ወሬ ሆኖ እንደቀረ ይታወቃል:: ለምን? የተባለው ሕዝብን ለመደለል ይመስላል:: ያገሬ ሰው ሲተርት : “የተናገርኩት ከሚጠፋ : የወለድኩት ይጥፋ” ይላል:: ለምንስ እርሶ ይህንን የተናገሩትን ውሳኔ ስራ ላይ እንዲውል አልገፉበትም? በአሁን ጊዜ ስልጣንን ተገን ያደረጉ በዝባዦችና ሌቦች ተቀያየሩ እንጂ ለሕዝብ የሚበጅ ለውጥ እንዳልመጣ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰማው::
3. በኦሮሞ ክልል ውስጥ በተበላሸና በተዛባ የሗላቀርነት ምልክት በሆነ የጎሳ ፖለቲካዊ አስተዳደር : ኦሮምኛ የማይናገር ኢትዮጵያዊ በዚህ ክልል በመንግስት መስሪያ ቤቶች ለመቀጠርና ለመስራት እንደማይችል እየተነገረና ይህ የጎሳ ልዩነት በሰፊው እየታየ ነው:: በጣም የሚገርመው ሐኪሞች እንኳን ኦሮምኛ መቻል አለባቸው በመባል ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች እየተገለሉ ይገኛሉ:: ይህ ጠባብ ጎሰኝነት ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ያጠናክራል ብለው እርሶ ያያሉ? ድህነት የበዛበትም ቢሆን በደጉ ዘመን ማለትም በንጉሥ ኃይለሥላሴ ጊዜ ወጥቼ በዲያስፖራ ለብዙ ዓመታት ኖርአለሁ:: እየኖርኩም ነው:: በዚያ ዘመን ጎሰኝነት ብዙም አይታይም ነበር:: ሕወሓት እንኳን ሌሎች ኢትዮጵያውያን በትግራይ ውስጥ ለመስራት ትግርኛ እወቁ አላለም ነበር:: የዛሬው የኦሮሞ ክልል አስተዳደር ይህንን ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የማግለልና የመጨቆን እርምጃ ሲወስድ እንዴት ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ የሚል አስተዳደር ዝም ብሎ ያያል? ሕወሓት በኦሮሞ ብልፅግና (ኦዴድ) ፓርቲ እየተተካ ነው? ሌሎችም ጠባብ ጎሰኝነት ቢሰማቸው መደነቅ የለብንም:: ሁሉንም በእኩል ደረጃ አይተን ታዲያስ ለወላይታው : ለሀዲያው : ለከምባታ : ለጉራጌና ለተቀሩት ብሔሮችና ብሔረሰቦች በቋንቋቸው ክልሎች መሆን ለምን አይፈቀድላቸውም? የሚያሳዝነውና የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊነትን በአፍና በድለላ አጎላናት እንጄ በድርጊት ተቃራኒ ነው:: ማለትም ኢትዮጵያዊነትን በግራ በቀኝ እያዳከምን መሆኑ ነው:: እርሶ የሚመሩትን ፖርቲ አባላት ከጠባብ ጎሰኝነት : ወገናዊነትና ተረኛነት ካላወጡት የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅና ኢትዮጵያዊነትን ከጎሳ በላይ ማድረግ ያስቸግራል:: ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስር አንድ ቋንቋ አለን:: ይህም አማርኛ ነው:: መንግስት የአገር አስተዳደር ቋንቋ አማርኛ መሆኑን ክልሎች እንዲቀበሉ አቋም ካልወሰደ የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር አይቻልም:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ችሎታውና ዕውቀቱ እሰከፈቀደለት ድረስ የትኛውም ክልል ሄዶ ሰርቶ የመኖር መብቱ ካልተከበረና ካልተጠበቀ ኢትዮጵያን እንደ አገር ማቆየት የሚቻል አይመስለኝም::
4. ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተከፍተዋል:: በዓመት ወደ 150,000 ሰዎች በዲግሪ ይመረቃሉ:: ሆኖም ለዚህ ሁሉ የሚሆን ስራ መስክ እንዳልተከፈተና ኡብዛኛው ምሩቆች ስራ አጦች ናቸው:: ይህንንም ኢትዮጵያ ባሉት ቤተሰቦቼ ውስጥ ታዝቤአለሁ:: ተመርቀው ስራ የሚቀጠሩት በችሎታቸው ተመዝነው ሳይሆን : በዘመድ ወይም ለቀጣሪዎች ጉቦ በመስጠት እንደሆነ በሰፊው ይነገራል:: እንዲያውም የዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደሮች ዲግሪም ይሸጣሉ የሚልም ወሬ ይናፈሳል:: ይህ እውነት ከሆነ አሳፋሪና አገር ጎጂ ነው:: አዎን አገራችን በጥቂት ስግግቦች ስልጣን ጥማት ምክንያት የማያስፈልግ ጦርነት ውስጥ ተገዳ በመግባት ለልማትና ለብልፅግና መዋል ያለበት ገንዘብ ለጦርነት ማካሄጃ ውሎ እናያለን:: በዚህ እርሶን መወንጀል ተገቢም አይደለም:: ሆኖም ተመራቂዎች ለአገሪቱ ምርታማ የሚሆኑበትን እቅዶች መንደፍ አስፈላጊ ነው:: እንዲህ አይነት አግባብ ያልሆነ አሰራር ሲካሄድ ሰምቶና አዳምጦ ዝም ማለት ለስነምግባር ብልግና መዳበር አስተዋፅኦ ያደርጋል:: ለመንግስት መስርያ ቤቶች ቅጥርነት ከፖለቲካ : ከጎሰኝንትና ከወገናዊነት ነፃና ገለልተኛ የሆነ የተወዳዳሪዎችን እውቀት ; ችሎታና : ብቁነት የሚፈትን ደህናና ትክክለኛ የስራ ቅጥር ቦርድ ቢቋቋም ሰዎች ተወዳድረው በመቀጠር አድሎን ማስወገድ ይቻላል::
5. በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጥኩት ማስረጃ ኢትዮጵያውያን በኑሮ ውድነት መጎሳቀልን የእርሶ መንግስት ቅድሚያ አለመስጠቱን ስጠቅስ : ልማት ላይ መሰራት ያለበትን ስራ በአግባብ አለማየት እንደሆነ እታዘባለሁ:: ይህም በየሚኒስትሩ የተሾሙት ሹማምንት መስሪያ ቤቱ ለቆመበት የአስተዳደር መስክ ተልእኮ ለማሳካት በሙያና በእውቀት የተካኑ ሳይሆን በፖለቲካ እምነታችውና ታማኝነታቸው የተመለመሉ ናችው የሚል አመለካከት አለኝ:: ለምሳሌ የእርሻ ሚኒስቴርን የሚመራ በእርሻና በእርሻ ልማት እውቀትና ችሎታ ያለው ሰው መሆን ይኖርበታል:: ሕዝብን ለመመገብ የምግብ እህሎችን በበቂ ደረጃ ማልማት ተገቢ ነው:: ይህንን ለማሳካት በእርሻ ምርምርና ጥናት የዳበረና የበለፀገ እውቀት ያላቸውን ማሳተፍና መሪ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ለምሳሌ ሰሞኑን በሸገር ኤፍኤም 102.1 ሬድዮ በአንድ ወይዘሮ መዓዛ አስተናጋጂነት ስለኢትዮጵያ ግብርና አንድ ዶ/ር ፀደቀ አባተ የተባሉ ምሁር የስጡትን ቃለጥይይቅ ሰምቼ : እንዴት እንዲህ አይነት ምሁርና አዋቂዎችን የኢትዮጵያ መንግስት መልምሎ ለልማት የእኝን አይነት ሰው ጭንቅላት መጠቀም አልፈለገም? የሚል ጥያቄ አሰብኩኝ:: እኝን ምሁር ካዳመጥኩ በሗላ ጉግል ሳደርግ በኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርስቲ ኤንቲሞለጅስት የሆኑ አንድ ዶ/ር አሰፋ ገብረአምላክ የሚባሉ : በሚኔሶታ ስቴት ውስጥ አግሪካልቸራል ኤክስቴንሽንስት የሆኑ አንድ ዶ/ር ንጋቱ ታደሰን የመሳሰሉ ምሁራን በብዛት እንዳሉና ቢጋበዙ በእውቀታቸውና በሙያቸው አገራቸውን መርዳት እንደሚችሉ ታየኝ:: ለማንኛውም ከላይ የጠቀስኩትን ቃለጥይይቅ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ሁሉ ቢያዳምጠው እላለሁ:: እኝህን ጥልቅ ምርምር ያደረጉ አገር በቀልና በዲያስፖራ ያሉትን ሰፊ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያዊያንን በመጠቀም : ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን የምግብ እጥረት ወዲያውኑ ባያጠፋም : ለወደፊቱ በምግብ ራስ ቻይ እንድትሆን የሚረዳትን መንገዶች መቀየስ ይቻላል:: ከላይ የጠቀስኳቸውን አዋቂዎችንና መሰሎቻቸውን አሰባስቦ ማማከር ለአገር ይበጃል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  አብይ አህመድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ገደል ለመክተት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደረ ነው

ክቡርነትዎ:- የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ ናቸው:: የእነዚህ ችግሮች መነሻና ምንጩ የእርሶ አስተዳደር ብዬ ነው ብወነጅል እውነትን መራቅና ኢፍትሀዊ መሆን ይሆንብኛል:: ችግሮቹ ለዘምናት ከአመት ወደአመት : ከአንድ መንግስት ወደ ቀጣዬ መንግስትና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደ ውርስ ንብረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲቀባበላቸው የሰነበቱ ናቸው:: እነዚህን የማያቋርጡ ችግሮች እርሶና የእርሶ አስተዳደር ከሕዝቡ ጋር ወርሳችሗል:: አለመታደል ሆኖባት ኢትዮጵያ እንደ አገር : መንግስታት ሲቀያይሩ በጉልበትና በጦርነት : ያለፈው መንግስት ለቀጣዩ መንግስት የሚያወርሰው የበለጠ ችግርና ምስቅልቅል እንደሆነ ተደጋግሞ ታይቶባታል:: የእርሶም መንግስት እጣፋንታ የተሻለ አይደለም:: የተቀበሉት ችግር ወደር የለውም:: እንደዚያም ሆኖ ለማሻሻል የሚያደርጉት ታላቅ ጥረት ሊካድ አይቻልም::

አዎን በዚህ የለውጥ ሂደት የሚያደርጉትን ተቀብሎ ውጤታማ እንዲሆኑ በትግስት አብሮ ከእርሶ ጋር የሚጏዙ ብዙሃን አሉ:: በተቃራኒው በምንም አይነት መንገድና አቅጣጫ ጥረቶን ላለማየትና ላለመረዳት የተቻላቸውን ያህል ማንኛውንም የነቀፌታ ድንጋይ የሚያገላብጡ አሉታዊነት የወረራቸው ተቃዋሚዎችና ተሳዳቢዎች እንዳሉ ግልፅ ነው:: አሉታዊ መሆንና መቃወም ተገቢ ቢሆንም : ለሚቃወሙት ነገር አማራጭ መፍትሔዎች ማቅረብ ሲጠበቅ : የዘመናችን ተቀናቃኞችና ተቃዋሚዎች : ገንቢ ሃሳብ አቅርበው : ይህ ይሰራ : ይህ ይደረግ ማለት ሳይሆን : የስድብ ጋጋታ የሚያወርዱ : ፊታቸውን የማያሳዩ : ማንነታቸውን የሰወሩ : ጭንቅላተ አልባ የፌስቡክና የቲውተር አርበኞች ናቸው:: ከእነዚህ ጋር መከራከር ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ይሆናል:: ልንረዳቸውም ሊረዱም የማይቻሉ በጥላቻ የሚመሩ : ወገንተኞች : ጎሰኞች : ጎጠኞችና ፅንፈኞች ናችው:: ለዚህም ነው ለአንድነትና ለሰላም የማይጠቅሙ ትችቶች ሲያቀርቡ መልስ ሲሰጣችው እነዚህ ጠባቦች ለእድሜያችውና አለን ለሚሉት እውቀት የማይመጥን ውዳቂ ስድቦችን በፌስቡክና በቲዊተር ገፆቻቸው የሚለጥፉት:: በስድብ ሕዝብ አንድ አይሆንም:: የአቢይ ጫማ ላሺ በማለት የሃሳብ ልዩነት አይጣጣም:: በጠባብነት አገር አይገነባም:: ይህንን የማይረዱ ተቃዋሚዎች በበዛበት አገር እንዴት ልማት ሊሳካ ይችላል?

የተቃዋሚ ክፍል ይህንን የመሰለ ስነምግባር ብሉሹነት ቢያሳይም: ለማንኛውም ለአገሪቱ ውድቀት እንደ መሪ ተጠያቂነቶ ከጫንካዎ ሊውርድ አይችልም:: እንደ አንድ ሰው ማድረግ የሚችሉት እጅግ በጣም ትንሽ ቢሆንም እንደ መሪ አገሪቱ ሰላም ማጣት : የጠባብ ጎሰኞች ፅንፈኝነት : የሕዝብ ድህነትና የኑሮ ውድነት የሚያስወቅሰው አመራርን ስለሆነ እርሶም እንደ አገሪቱ መሪ ተወቃሽነቶን እንደሚቀበሉ ይታወቃል:: በአመራሮ ስርአት ውስጥ የሚጠበቅባችውን መልካም ስነምግባር የማያሳዩ : በተለይ በጠባብ ጎሰኝነት መርዝ የተመረዙ ፀረ-ኢትዮዽያን : በተረኝነት ስሜት የደነዙ ፅንፈኞች እስካሉ ድረስ : ዘረኝነትን ያልለበሱ ለአንድ ኢትዮጵያ የቆሙ ኢትዮጵያውያንና እርሶ የሚያስቧትና የሚመኟት አንድነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ማሳካት አንሸራታች ጭቃማ ተራራ መውጣት ያህል ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደወል 2 ዘኢትዮጵያ ደወል 2፡ ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ለኢትዮጵያ - ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ስለዚህ በተለይ በኦሮሞ ብልፅግና ፓሪቲ ውስጥ ያሉትን : የስልጣንና የመዝረፍ ተረኝነት በመሰማት : ደረታችውን ነፍተው ኢትዮጵያን የኦሮሞ ጠባብ ጎሰኞችና ፅንፈኞች መጨፈሪያ ማድረግ የሚያልሙት ፖለቲከኞች ከግብዝነታችው ተቆጥበው : ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን አያቶቻቸው በደማቸውና በአጥንታችው ልዑላዊነቷንና አንድነቷን ያስጠበቁላትን አገር : የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አገር መሆኗን እንዲገነዘቡ ካላደረጉ : ይህ በጠባብ ጎሰኝነት በኢትዮጵያ ላይ የሚያንዣብበው ችግር ለእርሶ አመራር ስኬታማነትና ለአገሪቱ ደህንነት እጅግ አደገኛ እንቅፋት ነው:: ይህንን ስሎት : ሌሎችም ጠባብ ጎሰኞችና ፅንፈኞች በአሁኑ ሰዓት የሉም ማለት አይደለም:: ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ጎሳ : ይህንን ውዳቂ ጠባብነት የሚያራምዱና የሚያቀነቅኑ እንዳሉ ሚስጥር አይደለም:: ግን አገርንና ሕዝብን የሚጎዳው : መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታግሎና መስዋእትነት ከፍሎ ያመጣውን ለውጥ : የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ውጤት መሆኑን ረስቶ : በእንድ ጎሳና በእንድ የፖለቲካ ቡድን የተገኘ የሚያስመስለው ዘረኛ ጥርቅም ነው:: ሕወሓት የሰራውን ስህተት : የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ሊደግመው ሲሞክር ማየት ኢትዮጵያ በልጆቿ አለመታደሏን ያሳያል:: አውሮፓውያን አገሮች የእንድነትንና የህብረትን ዋጋና ጠቄሜታ በመረዳት አንድ ሲሆኑ : ሕዝቡን ከልመና ስንዴ ያላወጣ ህብረተሰብ ስለጎሳ ነፃነት : ስለባንዲራና ስለክልል ሲያወራ : ይህን የሚያራምዱ መሪዎች ምን ያህል ደንቆሮና ደደቦች እንደሆኑ ያስጠይቃል::

ክቡርነትዎ : ጁላይ 2018 ከምኖርበት ስቴት 6 ሰዓት ነጅቼ ሚኔሶታ ስቴት በተደረገው የእርሶና የአቶ ለማ መገርሳ አቀባበል ላይ ስሳተፍ : በታርጌት ሴንተር ስታድየም ውስጥ በአንድ ጀዋር መሐመድ መሪነት የኦኔግ ደጋፊዎች አይና እውጣ ድርጊት ያሳየኝ : ከኢትዮጵያዊነትና ከኢትዮጲያ ባንዲራ ይልቅ : ኦሮሞንነትና የኦኔግ ባንዲራ የበላይነት ውዥንብር ነበር:: የኦሮሞ ጠባብ ጎሰኞች ማለትም የኦኔግ ደጋፊዎች በኢትዮጵያና በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንድራችን ላይ ያሳዩት ቁሻሻ ባህርይን ርሶም የታዘቡት ይመስለኛል:: እንደሰማሁትም : በምሽቱ በአሜሪካ ሞል ሆቴል ውስጥ በተደረገው ራት ግብዣ : ከክብር እንግዶች ጠረዼዛ ዙሪያ ከኦኔግ ደግፊዎችና ጠባብ የኦሮሞ ጎሰኞች በስተቀር : ከሌላ የኢትዮዽያ ጎሳዎች ከእርሶና ከአቶ ለማ መግርሳና ከተቀሩት አጃቢዎቻችሁ ጋር የተገናኘ የለም:: መረሳት የሌለበት የኢትዮጵያ መንግስት ወጭዋችሁን ሲከፍል : ገንዘቡ ከኦኔግ ደጋፊዎችና ከኦሮሞ ጠባብ ጎሰኞች ኪስ የወጣ ሳይሆን : የመላው ኢትዮጵያ ገንዘብ ነበር:: የአገሬ ሰው ሲተርት “የወጋ ቢረሳ : የተወጋ አይረሳም::” ይላል:: ያ በደል በልባችን ውስጥ ቢኖርም : ዛሬ የሚታየው ያንድ ጎሳ የበላይነት ጥረት በጣም ያስደነግጣል:: ያሳፍራል::

ሆኖም ላለፉት ሶስት አመታት ከአስራ አንድ ወር ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ : በለውጥ ሐዋሪያነቶ በመተማመን እየደገፍኮት እገኛለሁ:: በአንዳንድ የቲውተር መልእክቶች ላይ : ስለእርሶ ስከራከርና ስከላከል : የአቢይ ጫማ ላሽ ነሽ እየተባልኩ ተተቲቻለሁ:: ፍርፋሪ ለቃቃሚ ተብዬ ተሰድቢያለሁ:: የሚገርመው እነዚህ ተሳዳቢዎች የት እንደምኖር እንኳ ሳያውቁ ነው የስድብ ቃላት ለመፃፍ ጣታቸውን የፊደል ቁልፎች ላይ ያሳረፉት:: ኢትዮጵያንም ካየሗት ከ15 አመት በላይ ነው:: ታዲያ እንዴት አድርጌ ነው የእርሶን ጫማ የምስመው ወይም ፍርፋሪ የምለቅመው? ለአገር ግንባታ : ለሕዝብ አንድነት የሚጠቅም ሃሳቦችና አጥጋቢና አሳማኝ መከራከሪያ ነጥቦች የሌላቸው ምርጫቸው ስድብ መሆኑን በማሳየት ዶማነታቸውን ያስመሰክራሉ::

እነዚህን በጠራራ ፀሃይ ብርሃን ጨለማ የሚያዪትን አይናማ ስውሮችን ትቼ እርሶን የምጠይቀው : ስልጣን ሲረከቡ በኢትዮጵያዊነቶ እንጂ በኦሮሞነት ስላልሆነ : አደራም የሰጦት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ የኦሮሞ ክልል ኢትዮጵያውያን ባለመሆኑ : በአስተዳደሮ ዙሪያ ያለውን አደገኛ ጠባብ ጎሰኝነትና ፅንፈኝነትን : ዶማን ዶማ : አካፋን አካፋ ብለው በማስወገድ : ግራ የተጋባውንና እምነት እያጣ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እንዲሰማው እንዲያደርጉ ነው:: የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ የልብ ትርታ ካዳመጡ ሕዝቡ አቅፎት የምንመኛትን ሰላም የሰፈነባት : ሕዝብ ተደምሮ አንድ የሆነባት : ለምታ ሕዝቦቿ የሚጠግቡባትና የአፊሪካ ተምሳሌት የምትሆነውን ኢትዮጵያ መገንባት ይቻላል:: ይቻላል!!

ጠባብ ጎሰኝነትና ፅንፈኝነት ይወድማሉ:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያብባሉ::

23 Comments

  1. Almaz Asaaffaaaa,

    You said “በእርግጥም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የአንድነትና የአገራዊነት ጎህ እንደበራላቸው ተሰምቷቸው የደስታ ጮቤ እረገጡ:” as if you were NOT the one who danced with liar pastor until your bones break.

    We told you many times your love affair with liar and spy who was responsible for the suffering of millions of Ethiopians was immoral and inhuman.
    What did you learn from living in USA for 50 years? Falling in love with a spy pastor who participated in massacres, tortures, displacements and national treasons? Shame on you!

    • Are you?

      Do you have better and convincing argument besides spewing your insult, hatred and negativity? There is nothing worthy to learn from your comment. Come on, dude! Life isn’t black and white but grey. The thinking of one side to be always right and the other to be wrong manifests the political quagmire Ethiopia cannot get rid of. The difference between you and me is that I see things not as unidimensional but three dimensional. To assume whatever Abiy does to be wrong defies logic. Ethiopia would be better if our judgements and criticisms are balanced by recognizing the good too as we criticize the bad. The choice is not having carrots or sticks, but both because life is not perfect as we, human beings, are not always saints or devils but combination of these two antitheses. I wish that you could state couple of solutions to the current problem of Ethiopia rather than parroting the same anti-Abiy song being played in your camp since he became PM. To do that you should be fortunate enough to have thinking and creative rational mind which you are unfortunate of.

      If you are open to think humanly past your beast incarnate, I leave you with a quote from Martin Luther King, Jr.
      “Returning hate for hate multiplies hate, adding deeper darkness to a night already devoid of stars. Darkness cannot drive out darkness; only light can do that. Hate cannot drive out hate; only love can do that.” Amen!!

      • Almaz,
        You said “Life isn’t black and white but grey.” Not in this case!
        Whether to dance with the Nazi EPRDF spy was pure black and white. It was your choice to stand and dance with the Nazi spy. As you may know, it is not only Hitler who is cursed for ever, but also all his supporters including doctors and pastors.

        By the way your true color is coming out. You started to shout like a galvanized steel roof ( ye korkoro tara) in rain. No wonder the pastor’s hypocrite preaching rain made you dance and sing with him easily.

        • Are You?
          You are like porcupine shooting your quills of negativity in vain out of ignorance because you have nothing tangible & positive to give as solution to the political problem of Ethiopia. As Helen Keller once said, I keep my face to the sunshine not to see shadows of morons. By the way I don’t know what color you are talking about; but I am a black woman. You could have chosen a better descriptive word about my behavior to your nonsensical comment which is “ATTITUDE” instead of color. Anyways to think you need brain which you are devoid of. I am not insulting you; but I am stating fact, dear ቆርቆሮ ራስ! Just one thing, as septuagenarian person, I have seen, heard, and lived all the negativities of life and am not easily fazed. I can dish it out and can take it when others do the same thing. So, my boy, keep on exposing your stupidity by comparing Abiy to Hitler. Are you so ignorant? You are entitled to hate Abiy but comparing him to Hitler doesn’t hold water. Don’t disrespect the memories of Six million victims of the holocaust by citing the name of the DEVIL INCARNATE, HITLER, here.

          • Almaz, the Nazi EPRDF supporter

            The supporters of Hitler were like you. They never said Hitler did anything too bad. They wrote him supporting essays and poem like you do.

            As Kifle Wodajo was the servant of Hitler Meles, you are the servant of Meles’s hand picked son and believe you will be remember as such. Perhaps Kifle is better because he was serving him quiet.

            If counted properly, the number of people massacred in Ethiopia during the new EPRDF (otherwise known as PP) era is more than the number of people who died during the Jewish holocaust.

  2. Almaz,

    Here is how to change Abey and the Oromo.

    Amharas have no choice other than confederation simply because federation in the Ethiopian context does not work.
    Why?

    As a polirized multi-ethnic country, Ethiopia will not have a fair and free election without the opression of one or another ethnic group. Hence, democracy is an illusion that cannot be realized. The way Oromo rose to power and now control the entire country through proxy regional governments is the proof. Tigreans did it for the last thirty years and Oromos have stepped in Tigreans shoes to impose similar one ethnic group rule. With their number and size of their region, Oromo opressive rule will be much worse than Tigrean`s. Give another ten years to Oromo rule, Ethiopia will be the tail of the world by all standards of measure.

    So, it is time for Amharas to exercise their constitutional right to self-determnation and vote on confederation. If they adopt conederation, it will give them the opportunity to attract direct foreign investment since confederation will enable them to have economic diplomats and even have embasies abroad cutting the Oromo controlled foreign ministry diverting foreign investment to Oromia and other favoured regions. Amharas can also have a defense force which will protect them from foreign invaders including ethnic Oromo organizations.

    The Belgian model of confederation which appears to hep advance Amhara interests is something to explore.

    In any event, Ethiopia needs vast decentralization resembling confederation since the federalism the country has adopted is notheing other than unitarism in disguise. Controlled from the centre, it has miserably failed to develop the country let alone prosper and ensure safety and security of its citizens. The chaos we see in the country right now has much to do with lack of development (in all sectors) and security. Both have proven beyond the capacity of the federal government to provide.Change of government at federal level is not the answer for these problems.

    Tigreans have floated the idea of confederation, Amharas must follow. Tigreans know that they will not be fairly treated under Oromo rule; as a result, their choice of confederation appears just. Amharas must seize the opportunity to decide their destiny via self-determination as well without wasting another decade under incompetent Oromo rule. Despite all the atrocities they have committed, Tigreans are being heard and embraced by the Oromo rule since Oromos now feel tobe the savours of Ethiopia.

    Falks! Don’`t be fooled!. Oromos pretend to be “savours” only if they rule the entire country as one piece. Like any other ethnic group that aspire to oppress and dominate , they are after resources. If Amharas want to be heard and embraced as Tigreans, they have to go for confederation. If confederation does not work, they have to say good bye to the Ethiopian state.

    It is outdated for Amharas to hang on “mama ethiopia” cry since nobody in the country is interested in it any more. What Amharas got from this cry is atrocotoes, redicule and shame. All these on Amhara because they gave Oromos and other ethnic groups a country which they are not ready and willing to let go. If Amhara Insist on confederation, Oromos might call the army on it to protect the unity of the country! That will make them a laghing stock since they were in the forefront to weaken the unity of the country. Now they cannot be alllowed to reverse gear.

    Amhara! Wake up and smell the coffee. Tell Oromos that you want confederation – if not confederation then separation. Oromo crack down will soften even disappear as it did for Tigreans if Amara opt for confederation. But the idea is not to see Oromo softening on Amhara, it is to seek real confederation as a wayout from decades long quagmire. Oromo softeneing does not take Amharas anywhere.

    Try it! It will work and catapult Amhara development and growth to the sky and ensure their security. It will eventually liberate Oromos too from their bloody distructive path poised to takie everybody else down with them.

    For us, Oromos, conederation is also the answer.

  3. ወ/ ሮ አልማዝ መልካም ነው እንደ መሰለኝ አብይ አሜሪካ መጥቶ ያደረገው ዲስኩር ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ ጆሮዎ ላይ ያቃጭላል ሀቁ ግን ሌላ ነው። የዘረዘሩትን ሁሉ አብይ ያውቃቸዋል እርሶ እንደ ጥፋት የሚያዩት የአብይ ትክክለኛ አሰራር ነው። እርሶ አብይ አመለካከቱን እንዲለውጥ አይድከሙ ይልቅስ የእርሶን አመለካከት ይመርምሩ። ሽመልስ አብዲሳ፣ጁዋር መሀመድ፣ዳውድ ኢብሳ፣ቀጀላ መርዳሳ፣አረጋዊ በርሄ፣አዳነች አቤቤ፣ዶር ወርቅነህ፣ የመሳሰሉ እልፍ ነብስ ገዳዮችን ባካባቢው የኮለኮለ ከመሆኑም በላይ መፍትሄ ያመጣሉ ብለው የጠቀሷቸውን ምሁሮች ኢትዮጵያን ያስቀጥላሉ ብሎ ስለሚገምታቸው አጥብቆ ይጠላቸዋል። ከነሱ ይልቅ ኢትዮጵያን ትርምሷን ያወጡት ትግሬዎች በመንፈስ ስለሚቀርቡት ለነሱ ስስ ልብ አለው። በዲፕሎማሲም ደረጃ ታላላቅ ዲፕሎማቶችን ገለል በማድረግ እነ ሱሌማን ደደፎን ልምድና ዶላር እየከፈለ ኢትዮጵያን ያሰድብበታል። በአጣዬ፣በሻሸመኔ፣በማይካድራ በተደረገው ውድመት አብይ አሳምነው ላይ በወሰደው እርምጃ ፍጥነት እርምጃ ሊወስድ ቀርቶ ሲያወግዝም አልተሰማም። ለማንኛውም በጸሎት ይትጉ ኢትዮጵያ ክፉዎች እጅ ላይ ወድቃለች።

  4. ተራ ስድቡንና የዘር ቆጠራውን ወደ ኋላ በመተው ሰውን በሰውነቱ ማየት እስካልቻልን ድረስ ችግራችን ይቀጥላል። በታሪካችን ያልተጠላለፍንበት መንገድ አንድም የለም። ዞር ብሎ ማየትና የዛሬውን ካለፈው ጋር ለማመሳከር መሞከር ነው። ችግራችን እልፍ ነው። ኑሯችን ውድ ነው። አለቆቻችንም ብዙዎች ናቸው። የውጭ ጠላቶቻችን የቀጥታና የእጅ አዙሮቹ ሲደመሩ የትየለሌ ናቸው። በሃገር ውስጥ በሃይማኖት ሰበብ፤ በክልል ፓለቲካ፤ በቋንቋ ጦርነት እንፋለሳለን። ይህን ሁሉ ረጋ ብሎ ለተመለከተ ትሻልን ትቼ ትብስን እንደሚል እርግጠኛ ነኝ።
    በመሰረቱ ጠ/ሚ አብይ ከወያኔ የክፋት ኮሮጆ ያፈተለከና ከጊዜ ጋር መልኩን የቀየረ ሰው ነው። እልፍ ጊዜ የፈጣሪንና የኢትዮጵያን ስም በአደባባይ መጥራቱ ውስጡ ያለውን አያሳይም። ሞሶሎኒና ወታደሮቹም በጊዜው በሮማ ጳጳስ ተባርከው ነው በመርዝ ጋዝ የሃበሻውን ህዝብ የፈጅት። ከማያቋርጥ የቃል ጋጋታው ይልቅ ጠ/ሚሩ መመዘን ያለበት በሥራው ነው። አፍንጫው ላይ ቁጭ ብለው አይደል እንዴ ለኦሮሞ አንገት ቀንጣሶች ገንዘብና ትጥቅ እያፈላለጉ የሚሰድት። የኢትዮጵያ ፓለቲካ መኖሪያ ቤቱን እሳት ለኩሶ እሳት አደጋ እንደመጥራት ወይም ድረሱልኝ ብሎ ኡኡታ እንደማሰማት ይቆጠራል። ረሃብ ገባ፤ ኑሮ ተወደደ የሚሉን እኮ ያላቸውን ቀብረው ለከፍተኛ የገቢያ ዋጋ ቀን በሚጠባበቁ ስግብግቦች ነው። ለምርት የቀረበ እህልን የሚያቃጥል ወገን ተራብኩ ቢል ይሳቅበታል እንጂ አይታዘንለትም። እርግጥ ነው የሚጎድት ወላድ እናቶች፤ አዛውንቶችና ህጻናት እንደሚሆኑ። በቅርብ በተመለከትኩት የሃገሮች መፈራረክ መመዘኛ መሰረት አሁን ያለችው ኢትዪጵያ (Failed State) ተብለው ከሚመደቡት መሃል ትቆጠራለች። በገጠርና በከተማ ህግ የለም፤ የሰዎች መብት በየጊዜው ጠበንጃን ጉልበት ባደረጉ ሰዎች ይደፈራል፤ ጉቦውና ዘረፋው ቀጥሏል። ልክ በወያኔ ጊዜ እንደነበረው ከላይ እስከ ታች የሃገሪቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር በኦሮሞዎች ተጥለቅልቋል። ቋንቋ መግባቢያ ሆኖ እያለ፤ በቋንቋዬ ካልተናገርክ ጉዳይህ አይፈጸምም በማለት እልፎች ይጉላላሉ። ባጭሩ ግልጽ ደብዳቤ ተጻፈለት፤ ፊት ለፊት ተነገረው ጠ/ሚሩ አመንኳቸው በሚላቸው የቅርብ ባልደረቦቹ የተከዳ ነው። ጦርነት እያለ ጦርነት የለም። ህዝብ እየሞተ ምንም አልሆነም፤ ሰው እየተፈናቀለ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል የምንባልበት ሃገርና መንግስት ነው ያለን።
    ፓለቲካ የጉልበታሞች ታንቡር ነው። ቃናውን እንደፈለጉ እየደለቁ ለወደድት እስክስታ ያስመቱበታል፤ ለጠሉት ደግሞ መጣንብህ በማለት ነፋስ እንዳነሳው ድቄት ይበትኑበታል፤ ለመከራ ይዳርጉታል። አሁን እንሆ በዪክሬንና በራሽያ ያለው ፍትጊያ ምዕራባዊያኖች ከጅምሩ ባይገቡበት ኑሮ እዚህ ባልደረሰም ነበር። በነጮች የቀድሞዋ ሶቪየት ስትፍረከረክ ዪክሬን በመቶ የሚቆጠሩ ስትራቴጂክ ተዋጊ አውሮፕላኖች፤ የኑክሌር ባለቤት ነበረች። እድሜ ለአሜሪካ ውትወታና መላሾ ሁሉም ነገር ወደ ራሺያ እንዲመለስ ተደረገ። የሚገርመው የኑኩሌሮቹ ቅምቡላ እንኳን ሳይቀር ተተምኖ ዪክሬን ከራሽያ በምትገዛው ዘይት በልዋጭ ተሸጠ። ዪክሬን እንደታጠቀች ቢሆን ኑሮ ዛሬ እንዲህ ዓለም እያዪ አትንኮታኮትም ነበር። ረጅም ድላ ባይመቱበት ያስፈራሩበት ይሉሃል ይሄ ነው። አይናችን እያየ ራሽያ ዛሬ ምንም አላረኩም ሰላማዊ ሰውንም አልገደልኩም እያለች ስታናፋ መስማት ወደ ሃገራችን ጉዳይ ይወስደናል። ወያኔንም እንደዛ ነው። እየገደለ ሞተብኝ፤ ዘር እያጠፋ ዘሬ ጠፋ፤ እየሰረቀ ተሰረኩኝ። ፓለቲካና ፓለቲከኞች እውነትን አያውቁም። ሳይዋሽ በፓለቲካ ውስጥ መኖር አይቻልም። ዪጎዝላቪያን ለ 6 እንዲቆረስ ያደረገችው አሜሪካ ዛሬ ውጥንቅጧ ወጥቷል። በምድሯ የራሷ የሆኑ ሰማይ ጠቀስ ችግሮች አሏት። እንደ በፊቱ ከዚህም ከዚያም እየዘረፉ ሃገርን ማጎልበቱም እንደ ቻይናና ህንድ ሌሎችም በላተኛ ሃገሮች ስልታቸውን ተከትለው ስለተሰለፉ ለእኔ ብቻ የሚለው ነገር ቀርቷል። አሁን አሜሪካ የምትከተለው የውጭ ፓሊሲ የእኛንም ሃገር እንደ ዪጎዝላቪያ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው። በአንድ በኩል ስለ ሰላም እየተናገሩ በሌላ በኩል የመንግስት ግልበጣና ሴራ የሚያቅድ ናቸው። በአንድ አካል ሁለት ፊት ይሉሃል እንዲህ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያኔ እና አሁን በወያኔ፤ አሁን ደግሞ በቋንጨራ ታጣቂዎቹ ኦሮሞዎች በሰዎች ላይ የተደረገውና የሚደረገው ግፍ ለምዕራቡ ዓለም ቁልጭ ብሎ የታያቸዋል። ግን ደንታ አይሰጣቸውም። ቁጥራችን ሲቀንስ ደስ ይላቸዋል። በሊቢያ፤ በሶሪያ፤ በኢራቅና በሌሎችም ሃገሮች የሆነውና የሚሆነው ይህኑ የውጭ ፓሊሲ ተከትለው ነው። ሃበሻው ለራሱ ቢል እንደ ጨው ቢጣፍጥ ይሻለዋል። ያ ካልሆነ ግን ቀን የሰጠውም ሆነ ሌላው የሚከፍለው ዋጋ አሁን ከምናየው የከፋ ይሆናል። ጠ/ሚሩ ጨከን ብለው ስርዓትንና ደንብ በሃገሪቱ እንዲስተካከል እስካላደረጉ ድረስ የሚመጣው ዶፍ ለሁሉም ሰቆቃና ሞትን ያላብሳል። በዚያች ሰአት ተራፊና አትራፊ አይኖርም። ከሩዋንዳ መማር ይቻላል። የሊቢያው የፍርስራሽ ክምር፤ የሶሪያው የእሳት ገሃነም እንዲሁም ከታሪክ መጽሃፍትም አገላብጦ ዛሬ የምናየውን በማዛመድ ቀን እያለ ለማስተካከል መታገል ያስፈልጋል። ሞኝ አንሁን ሰው መርጦ አይወለድም። ቋንቋም የማንነት ማሳያ አይደለም።
    የጅሎች ፓለቲካ ማደናበሪያ እንጂ። መገዳደላችን ይቁም። በቃኝ!

  5. አልማዝ አሰፋ ጥሩ ብለሻል። እንደ ዜጋ ከሩቅ ሆነሽ ስለ አገር ማሰብሽ ተገቢ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ያለሽ መረዳት ግን ኦሮሞ ጠል አማራነት ይመስላል። ይኸ የአማራ ባህርይ አይደለም። ወያኔ አማራ ወገኑን በመጥላት ይታወቃል። አማራ ኦሮሞን በመጥላት እንዲታወቅ እያደረግሽ ነው። በልብ ሞልቶ በአፍ ይወጣላና፣ እስቲ “የኒህን ዓይነት ሰው ጭንቅላት” ብለሽ የጠቀስሻቸው ሁላቸውም አማሮች ናቸው፦ ዶ/ር ፀደቀ አባተ፣ ዶ/ር አሰፋ ገብረአምላክ፣ ዶ/ር ንጋቱ ታደሰን። ያስተዛዝባል፤ ቅን አለመሆን ያጋልጣል። ጥላቻን ያባብሳል። የዶ/ር ዐቢይ ደጋፊ ሆኜ አላውቅም። ሁሌ ጥያቄ የሚሆንብኝ፣ ወያኔ 30 ዓመት ያበላሸውን በአራት ዓመት ያቃና ማለታችን ነው። ወያኔ ያደራጀውን ፓርቲ ጥሎ ጫካ ገባ፤ ጦርነት ጀመረ። ወያኔ ያስቀመጣቸው ኦሮሞ አማራ ወላይታ ጉሙዝ እስከ አሁን በዐቢይ አስተዳደር ውስጥ በፀጥታ፣ በፋይናንስ፣ ወዘተ ተሰግስገው አድብተዋል። ወያኔ ወደ አዲሳባ አቀናሁ ባለ ጊዜ እነዚህ ቡድኖችን መተማመኛ አስቀምጦ ነው። የአገራችን መከራዋ ብዙ ነው፤ መደማመጥ ያለብን ለዚሁ ነው።

    • እባክሽን ወይም እባክህን (ስምሽ ወይም ስምህ ፆታሽን ወይም ፆታሽን ስለማይገልፅ) : እንዲህ አይነት መሰረታዊ ስህተት ከመስራትሽና ወይም ከመስራትህና ጠባብ ጎሰኝነትሽን ወይም ጎሰኝነትህን አደባባይ ከማውጣትሽ ወይም ከማውጣትህ በፊት የፃፍሽውን ወይም የፃፍከውን ከመለጠፍሽ ወይም ከመለጠፍህ በፊት ሁለቴ ገልመጥ ብለሽ ወይም ብለህ አንብቢው ወይም አንብበው:: አይ ዘንድሮ! ስም ደግሞ ጎሳ መግለጫ ሆነ? የተጠቀሱትን ምሁሮች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እንጂ : ሲወለዱ : የት እንደተወለዱ: ሆነ ማንነታቸውን በአካል ስለማላውቅ : የነገድና የጎሳ ዝርያቸውን እንዲህ ነው ለማለት :እንደ አንቺ ወይም አንተ የጥንቆላ ተሰጥኦ የለኝም:: 3 ምሁራን ስሞች በዘፈቃድ (RANDOMLY) ስለጠቀስኩ ከጎሰኝነት ጋር ማገናኘትሽ ወይም ማገናኘትህ ምን ያህል የተበላሸ ዘመን ላይ እንደደረስን ያሳያል:: ከ86 ጎሳዎችም ምሁራን አሉ: ያቀረብኩትን ነጥብ ለማጠናከር እንዲረዳኝ በአጋጣሚ ያገኘሗቸው ስሞች እንጂ ሆን ብዬ አንድን ጎሳ ለማሞገስ ያደረኩት አይደለም:: እማራስ ቢሆኑ ኢትዮጵያውያን አይደሉም? ስህተትሽን ወይም ስተትህን ለማጉላት ያህል እኔ በጎሳ ደረጃ ግማሽ ኦሮሞ ግማሽ ወላይታ ነኝ እንጂ እንዳሰብሺው ወይም እንዳሰብከው አማራ አይደለሁም:: ትውልዴ የእኔ ምርጫ ሳይሆን የተፈጥሮ ሂደት ውጤት ነው:: ዛሬ ያለኝ አቋም : በመጀመሪያ ደረጃ ሰው : በሁለተኛ ደረጃ ጥቁር : በሦስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነቴ : የምርጫዬ ውጤት ነው:: ጎሰኝነትን ለጠባብ አስተሳሰብ: ጎጠኝነትና ፅንፈኝነትን ለተከናነቡ ደደቦች ሰጥቻቼዋለሁና ይመቻቸው::

      የአቢይ አስተዳደርና አገራችን የተጋፈጡት ችግር በ10 አመት ውጥ ከተስተካከለም ጥሩ ነው:: መጀመሪያ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ሕዝቡ ማድረግ ይገበዋል:: ዋነኛው ለውጥ ጎሰኝነትንና ፅንፈኝነትን አስወግዶ : አንድ ኢትዮጵያ አንድ ባንዲራ አንድ ሕዝብ ላይ ማቶከር ነው::ይህም መጀመር ያለበት ከላይ ከአመራር ነው:: አቢይ ይህንን አቋም ከያዘና በኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ይህ የአንድ አገርነት አስተሳሰብ ከዳበረ : ሌላዎች ችግሮችን ለመፍታት ይቀላል:: እንዳልሽው ወይም እንዳልከው መናበብና መደማመጥ ያስፈልገናል:: የተረኝነት ስሜት አስወግደን ለሁላችንም የምትሆንና የምትበቃ አገር ማዳበር ይቻላል:: ያለውንም መንግስት ጥሩ ሲሰራ ካሮት (ማወደስ) እየሰጠን : ሲሳሳት እርጩሜ እያሳየን (መተቸት) የእድገትን መንገድ ይገነባል ብዬ አስባለሁ::

  6. አልማዜ!

    ተሳስቼ ነ ተንከርፍፌ አፍቅሬ ነበር ማለት ማለት ማንን ገደለ? አሁንም እኮ ሙዝዝ ያልሽ ነው የሚመስለው፡፡ ለነገሩ አንቺ ብቻ ሳትሆኝ እንዳንቺ ሳያይ ያመነውና ያጨበጨበው ሁሉ ተሳስቼ ነበርን አያውቃትም፡፡ ከስምንተኛ ክፍል ደርሶ ዶክተር ነኝ ያለን ሰላሳ አመት ሙሉ ነፍሰ በላ አገዛዝ ያገለገለን መናጢ ብልኮ እሚያካክል ጽሑፍ ጣፍሽለት፡፡ በፈጃቸው ዜጎች ድንጋይ ጪነሽ የፍቅር ግጥምም ገጠምሽለት፡፡ እግዚአብሄርንም እኮ የዚህን መናጢ ያህል ወደሽና አወድሰሽ የምታውቂ አይመስልም፡፡
    የፈጃቸውና ያስፈጃቸው ዜጎች አጽም ይፋረድሽ፡፡

    • የበሰበሰና ዛሬ ላለንበት የማይቋርጥ መከራ ምክንያት : እንዳንቺ ወይም እንዳንተ (ስምሽ ወይም ስምህ ፆታሽን ወይም ፆታህን ስለማይገልፅ) ለሕዝብ አሳቢ እየመሰሉ በጭፍን ጥላቻ የሚመሩ ዶማዎች ናቸው:: ችሎታሽ ወይም ችሎታህ ስድብ በመሆኑ : ቧዋቃ አፍነትሽን ወይም አፍነትህን እያስመሰከርሽ ወይም እያስመሰከርክ ነው:: የፃፍሽው ወይም የፃፍከው አንዲት አስተማሪ የሚሆን ነጥብ ስለሌለው : ጭንቅላትሽ ወይም ጭንቅላትህ የማሰብ ችሎታ የተሳነው መሆኑን ላረዳሽ ወይም ላረዳህ ወደድኩ:; ለጭንቅላትሽ ወይም ጭንቅላትህ ሞት ነፍስ ይማር!!

      • አልማዝ ምነው ምነው ልጄ እንደዛ ለስለስ ብለሽ ጀምረሽ ከግራ ቀኝ ሲቆነጥጡሽ እውነተኛው አልማዝ ወጣሽ? ባንች ልክ መች እነሱስ ጻፉ። አለም ነሽ ማለት ነው? አረ ተይ ሰው ስርአቱን ጠልቷል ሁሉን ተሳድበሽ አትችይም። እስራኤል ዳንሳ ዘንድ ሂደሽ ንስሀ ግቢ።

        • ነብዩ እስራኤል ዳንሳ ልጅ:-

          ምነው እንደዝርጎ ዝንብ ያለቦታህ ተንቀዥቅዠህ ተወዘፍክ? ያልበላው ቦታ የሚያክ እክካም ለምን ትሆናለህ? ሳትገራ አድገህ ስለቁንጥጫስ ምን ታውቃለህ? መረን ማደግህን ሳያዩ ያለፉት አያቶችህ እንዴት የታደሉ ናቸው? ዘለፋን ከቁንጥጫ ጋር ማመሳሰልህና : ግስንና ተውሳከ ግስን ለይቶ የማይረዳውን እስራኤል ዳንሳ አድንቀህ እሱጋ ሂጂ ስትል : ጣዖት አምላኪ መሆንህን ታዝቤ : ድንገት ኢትዮጵያ ከመጣሁ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ሄጅ ልፀልይልህ ቃል ገባሁልህ:: ስለዚህ ይህችን ሰባ ውስጥ ያለችውን አሮጊት እንደማታሳፍር ተስፋ ላድርግ? ለካስ! ስለቁንጥጫም አንስተህ ነበር:: ይብላኝ ላንተ ትውልድ : ለእኔና ለእድሜ መሰሎቼ ቁንጥጫ ፍንክች አያደርገንም:: አየስደነግጠንም:: አያስፈራንም:: በሰላም ያሳድግህ!!

          • አይ አልሚ የት ይደርሳል የተባለው ጥጃ ልኳንዳ ቤት ቀር ያሉት አቡነ ሃጎስ ወደው አይደለም። ጠ/ሚኒስቴር ካልመከረኩ ብለሽ ተነስተሽ እንዲህ ሁነሽ ትቀሪ? እኔ እኮ እንደ ፈለግሁ ነው የኖርኩት ተቆንጥጭ አላውቅም ስትይ የጻፍሽውን አንደ ባንድ መመርመር ያዝኩ ልክ ነሽ። ችግሩ ከኔ ነው ይህን እያወቅሁ ምናልባት ብዬ መጻፌ። አይዞሽ አንዳንደ የቀን ጎደሎ አለ ባይረዱሽ ይሆናል እንጂ እንዲህ ተጨንቀሽ ተጠበሽ የጻፍሽውን ባላራከሱብሽ ነበር። ወደ በራራ ስትሄጅ ላይደርስ ስለሚችል ኮፒውን በእጅ ስጫቸው። ተጨብጭቦልኝ ምስጋና አገኝበታለሁ ያልሽው ጽሁፍ እንዲህ ጉድ ይስራሽ? አይዞሽ ያልፋል ድንገት ብልጭ እንዳይልብሽ አንድ 3 ሳምንት ወደ ኮምፒተር አትጠጊ አንዱ በጊዜው ጉዳይ አንጀቱ የነደደ አንጀትሽን ጨምሮ እንዳያነደው። እኔ እርዳታ ነው የሰጠሁ አትስደቢኝ መልካም ጤና።

      • አልማዜዬ!!!

        አብደሻል! ለይቶልሻል! የንፁሐን ደም እንደዚህ ነው የሚያሳብደው፡፡ በወለጋና በሌሎችም ቦታዎች በፈሰሰው ደም ፍቅረኛሽ ብቻ ሳይሆን አንቺም በግጥምና ብልኮ በሚያካክል ፅሑፍ ፍቅርሽን ስትገልጪለት የኖርሽው አስገዳይ በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይ ቤትም ስትቃጠይ ነው የምትኖሪው፡፡ የንፁኸን ደም ይጮኻል!

        • መጀመሪያ እንደእኔው ሴት ነሽ ብዬ ልቀበልና : በአክብሮት ላናግርሽ:-

          ስለንፁሃን ዋጋ በሴት በወላጅ አንጀትሽ ትረጅያለሽ ብዬ አሰብኩና : ስለፍቅር የማታውቂ የጥላቻ ጆንያ ለሆንሽው ጎደሎነትሽን “ፀባይ ጥፉ : በስም ይደግፉ” እንደተባለው ተረት ሙሉ ተብለሽ የተጠራሽው የሰው ዲሪቶ መሆንሽ ትዝ ብሎኝ : ብነግርሽም የምናገረው ጉራማይሌ ስለሚሆንብሽ : በቃላት ጠረባ ልናገርሽና እኔ ቡልኮ (በነገራችን ብልኮ ሳይሆን ቡልኮ ነው የሚባለው) በሚያክል ፅሁፍ ፍቅሬን ለአቢይ ብገልፅለት ምነው ቆጨሽ? እኔስ የማሳየው የእናትነት ፍቅር ነው:: አስበሽው ነበር? አንዳንዴኮ ቅናትም ጥላቻን ያመጣል:: ኧሩ ስለሰው ከተቆጨሽ ምነው አማራን : ትግራይን : አፋርን ሳታነሽ ወለጋን አነሳሽ? እኔ በምድርም ሆነ በሰማይ የምቃጠልበት ምክንያት የለም:: አልማዝ አቢይን ወደደች ብለሽ እርር ድብን በማለት እንደአሻሮ እየተቃጠልሽ ያለሽው አንቺዋ የሰው ጎደሎ ነሽ:: ኬር ሰንብቺ ፈንዲሻ!!

          • አልማዜዬ!!!
            የፃፍሽውን እስቲ ደግመሽ አንብቤው! “በአክብሮት ላናግርሽ:-” በለሽ ጀመርሽና የስድቡና ናዳ እንደ እንትን ለቀቅሽው፡፡ ዞሮብሻል፣ አብደሻል ፣ በፍቅረኛሽ ዘመን የፈሰሰው ደም የንፁሐን ደም አንቀዥቅዦሻል ያልኩት እኮ ለዚህ ነው፡፡

            አልማዜ! አያቶቻችን በአንቺ እድሜ አለም በቃኝ ብለው ቆባቸውን ደፍተው ተእውነት በቀር ሌላ አይወጣቸም ነበር፡፡ አንቺ ግን ሰላሳ አመት ሙሉ የመለስ አሽከር ሆኖ ሕዝብ ሲያስገርፍና ሲያስፈጅ የኖረ አረመኔ አፍቅረሽ ዌብ ሳይት ላይ እንደ ምጣድ ተጥደሽ ስትዘፍኝለት ትውያለሽ፡፡ እግዜር ይማርሽ!

          • እህቴ አልማዝ አንድ አንድ ጊዜ ዝምታም መልስ ነው። በዘራቸው ሰከረው የሰው ልጅን ህልውና ክደው ደም ከሚያፈሱና ካፈሰሱ ጋር ስርግ ግብ አይበጅም። የኢትዮጵያው ፓለቲካ በክልልና በዘር የተዋቀረ በመሆኑ ሰው ነኝ ብሎ በሰውኛ ቋንቋና እይታ ነገርን ለመሞገት አይቻልም። እና አይዞሽ ብዙም በእነዚህ የተከፈሉና በበሉበት በሚጮሁ የክልልና የዘር ውሾች አትደናገጭ። ዝም ብሎ መንዘላዘል እንጂ የሃበሻው የፓለቲካ እሳት መርጦ አይበላም። ሁሉን በጊዜው ደርቦ ይልሰዋል። ዝና እንድትይ በእኔ ስም የዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ – አንድ አንድ ነገሮች ሙዚቃ ጋብዤሻለሁ።

  7. ብልጥ መሳይ ፍልጥ
    ሳር ጭድ አሳይተህ
    ቀንዳም ቀንዳም በሬ
    ገደል ከተህ ከተህ
    አፋፉ ላይ ቆመህ በሳቅ ትፈርሳለህ
    ሰኔ አጉረመረመ በምንህ ታርሳለህ?

    ግልጥ መሳይ ፍልጥ
    ጥርስህ ግልጥ ግልጥጥ
    ልቦች ቅልጥ ቅልጥጥ
    ጆሮን ድፍ….ን በጥጥ
    ጩቤህ ጀርባ ስምጥጥ
    ዐይን ወደ ውጭ ፍጥጥ
    ነፍስ እስትንፋስ ሙጥጥ

  8. አለም የአብይ ደጋፊ አይደለሁም ነው ያልሽው? ወደው አይስቁ አለ። አብይ ፕሮግራሙን ለጃፓን ሰጥቶ ለአብይ የተሰራሽ ሮቦት አይደለሽ? የሁሉም አስተሳሰብ ባንኮች ልክ ይመስልሻል? ቱሪስት ብይ።

  9. አልማዜ አይዞሽ ሃሳብ አይግባሽ ነገር ባሰቡት መሄድ ካቆመ ቆይቷል የተጻፈላቸው ሰውዬም መልእክትሽን ሰው ሹክ ሳይላቸው አይቀርም ድካምሽ እንዲህ በከንቱ አይቀርም። እነዚህ ከላይ የጻፉልሽ በስርአቱ በጣም የተጎዱ ወይም ያገራቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው ዜጎች ናቸው ለወደፊቱ እንዲህ ያለ ጽሁፍ በድፍረት ከመጻፍ ግራ ቀኙን ማየት ጥሩ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶቹ በወለጋ ስላለቀው ሰብአዊ ፍጡር፤ በማይካድራ በገጀራ በትግሬዎች ስላለቀው ህዝብ ፤አዲስ አበባ በየቀኑ እንደ ጥጃ ስለሚታሰሩ ዜጎች፤ በትግሬዎች ስላለቀው የመከላከያ ሰራዊት ጽፈውልሽ ነበር አንች ግን ቱግ ግንፍል እያልሽ ባልተገባ ቋንቋ አስተናገድሻቸውፍ። እንዳልሽው በስማቸው ላይጽፉ ይችላሉ በስማቸው ካልጻፉ ምክንያታቸውን ልትረጂላቸው በተገባ ነበር። እዚህ ጎረቤቴ ሃጎስ የሚባል ትግሬ ነበር እነሱ መሪ በነበሩበት ጌዜ አድዋ ነኝ ብሎ ተናግሮ አይጠግብም ነበር ዛሬ ብድግ ብሎ ስሙንም ብሄሩንም ቀይሮ እኔን ሲያይ መንገድ ያሳብራል። አንችም ከላይ በጻፍሻት ጽሁፍ እድሜ ከሰጠሽ ብዙ ትስተናገጅበታለሽ። አለም የተባለችው ግን ከአራጆች መሀል አንዷ ነች ተዘናግተሽ እግርሽን እንዳትቆርጥሽ። በተረፈ ከግራ ከቀኝ ልክ አይደለሽም ያሉትን በስድብ ባታስተጋጅ ጥሩ ነበር በዚህ ላይ የፈረንጅ እውቀትሽ ለጉድ ነው ሙሴ ሚናስን ነው የመሰልሽኝ። ተፈጥሮሽ እንደ ነብር ሳትሆኝ አትቀሪም ትግስት ጥሩ ነው በተለይ ቀይ ከሆንሽ ፊትሽ ቶሎ ካርታ ይሰራል ቀለሙንም በየ 3 ቀን እየተቀባሽ አትችይዉም። ወደ ካምፓላ ከመጣሽ ላስተናግድ ዝግጁ ነኝ።

  10. አልሚ ተሰላቸች ወይም ምክሬን ሰምታ ከሳይበሩ አለም በርራ ጠፋች። ልብ ገዛች ማለት ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share