ሻጥር ፤ ሴራ ፅንሰ ሃሳብና የኢትዮጵያ ፖለቲካ – አልማዝ አሰፋ

ከአልማዝ አሰፋ
imzzassefa5@gmail.com

የሴራ ፅንሰ ሃሳብ (conspiracy theory) በአለም ላይ ባላፉት 100 ዓመታት ብዙ የተባለበት ሃሳብ ነው፡  በመሰረቱ ይህ ፅንሰ ሃሳብ የመንግስትን የፖለቲካ ስልጣን ለመጨበጥና ከዛ ባስም ሲል በያዙት ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረግ ውስብስብ ሻጥርን የሚገልፅ ስያሜ (term) ነው፡፡ ቅጥልጥል ምስሎችን በማያያዝና በማገናኘት ለታሰበው አላማ በትንተና የማገኛኘት ስራ ነው፡፡

የሴራ ሰዎች : ፖለቲካን እንደ ህዝብ ህይወት መቀየርያ መሳርያ ሳይሆን እንደ ብልጣ ብልጥ የአሸናፊ ተሸናፊ ጨዋታ ብቻ ይቆጥሩታል፡  የሴራ ፅንሰኞችና አራማጂዎች ሁሉንም አይነት አጋጣሚዎች ለሃሳባቸው ማሳከያ ሲያውሉት ይታያል፡: አንድ ጊዜ የያዙት አቋም ጊዜው ቢያልፍና ሃሳቡ ቢያረጅ እንኳን ላለመሸነፍ ብዬ ነበር እኮ የሚል መልእክት እንዳይወሰድበት የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም፡፡ ለምሳሌ አሁን ባለው ሃገራዊ ሁኔታ የተከፉ አካላት ይህች ሃገር ያለኛ ሰላም ልትሆነ አትችልም፤ የሚል መሰረታዊ የሃሳብ ግንባታና ድምዳሜ አድርገዋል:: ይህ ሳያንስ ደግሞ ሃገር ተሸጣለች፤ አመራሩ ህዳሴ ግድቡን ሽጦታል የሚሉ የተለያዩ ትንተናዎች ጨማምረው ያሉት ከሚጠፋ በሚል እሳቤ የሚገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ፤ ይኽው አላልንም!! ሰላም እኮ የለም! ለማለት ሰላም የመደፍረስ ምልክት ሲያዩ ጮቤ ሲረግጡ ይታያል፡፡ ግድቡ ውሃ ሞልቶ እንኳን ምንተእፍረታቸውን ሃቁን ላለመዋጥ ሲላላጡ መስማት በእጅጉ ያሳራል፡፡ ከዛም ላቅ ሲል ይህንን ቅዠት እውን ለማድረግ በጀት መድቦም እስከመንቀሳቀስ ተደርሷል፡፡

ሴራና ሻጥር በፖለቲካ የነበረ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ64 አካባቢ በሮም የተከሰተው ታላቁ የእሳት አደጋ በቤቶቹ የእንጨት ስሪትና በንፋሱ ግፊት ምክንያት ለሳምንት ያህል ሳይጠፋ ሮምን እንዳልነበረች እንዳደረገ የታሪክ መዛግብት ያሰፈሩ ሲሆን በዚያ ወቅት እሳቱ ሲነሳ ገዥው ኔሮ ከከተማዋ ውጪ ነበረ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በስፋት የተሰራጩት የሴራ ትንተናዎች ውስጥ አንዱ ኔሮ ይህንን ያደረገው ሆነ ብሎ ሮምን ድጋሚ ለመገንባት በነበረው ድብቅ እቅድ ምክንያት ነው ይባል እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ታዲያ ኔሮ ይህንን ሲሰማ ለዚህ ክስ ምላሽ በተቃራኒው ሌላ የሴራ ትንተና አዘጋጀ ፡፡ ይጠላቸው የነበሩትን ክርስቲያኖችን (በወቅቱ የእየሱስ ተከታዮች የሚባሉት) እነሱ ናቸው እሳቱን ያስነሱት በማለት መፅሃፍ ቅዱሳቸውን በአንገታቸው እያንጠለጠለ በታሪክ እጅግ ዘግናኙን ጭፍጨፋ አካሄደ፡፡ ሴራ ሴራን እየወለደ በታሪክ ውስጥ ለብዙ እልቂቶች ሰበብ ሆኗል፡፡

የአይሁድ ሴራ ፅንፀ ሃሳብ የሚባለውና ለብዙ አይሁዳውያን እልቂት እንደ ሰበብ ሆኖ ያገለገለው በአለም ላይ የአይሁድን ታላቅነት ለማምጣት እየሰሩ ነው የሚለው ሃሳብ (ሴራ ትንተና) ለብዙ ዘመናት የፀረ አሁዳዊያን እንቅስቃሴ መሰረት ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1930 እና 1940ዎቹ የናዚው መሪ ሂትለር ንግግሮች ሁሉ በዚህ ቴዎሪ ያጠነጠኑ ነበሩ:: ሂትለር በንግግሮቹ በ1ኛው የአለም ጦርነት ለጀርመን ሽንፈት እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚያነሳው አይሁዳዊ ቦልሼቪዝም በሚል መጠርያ የሚታወቀውን የአይሁዳን ሻጥር የሚለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ በማራመድ ነበር፡፡ በዚህ ሴራ ትንተና የተነሳ ከ5 ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያን አልቀዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ጆሴፍ ስታሊን የሚባለው የሩስያ መሪ የሴራ ፅንፀ ሃሳብን ገልብጦ አይሁዶች ለናዚዝም መነሳትና መስፋፋት ሰበብ ናቸው በማለት ይከሳቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባክኖ የቀረ  አየር ኃይል - ክንዴ ዳምጤ - ሲያትል

የሴራ ትንተና የዲሞክራሲ ባህል በዳበረባቸው ሃገራት የሆነ የተዛባ አመለካከት ቢፈጥርም ጠንካራ ተቋማት በመኖራቸው ምክንያት ስርዓቱን የማናጋት አቅም ባይኖረውም፡ የራሱ የሆነ ጉዳት ግን ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ 60 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን አሁንም ድረስ ሲአይኤ ፕሬዚደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲን እንደገደለ ያምናሉ፡  በተለይ በጎርጎራዊያን አቆጣጠር  የመስከረም አስራ አንዱ 2001 ዓ.ም ጥቃትን አስመልክቶ አንዳንዶች : የቡሽ አስተዳደር መከላከል እየቻለ ሆን ብሎ በመተው ነው ብለው ሲከሱ : አንዳንዶች ደግሞ የሳውዲ መንግስትንና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን በተለያየ ትንተና ይከሳሉ፡፡ በ2020 የአሜሪካ ፕሬዝደንት የተደረገውን ሕጋዊና ዲሞክራሳዊ ምርጫ ብንመለከት የሴራን :: ምርጫው ተሰርቋል በማለት በተሸነፈው ፕሬዝደንት ትራምፕ አጫፋሪነት የተቀጣጠለው የውሸት ሴራ ነበልባል በሪፓብሊካን ፓሪቲ ደጋፊዎች ላይ የፈጠረውን ተፅእኖ በአኳያው በጃንዋሪ 6, 2021 በአሜሪካን ምክር ቤት ላይ የደረሰውን ሁከት ስንመለከት የምንደርስበት ግምገማ ሻጥርና ሴራ የሚያራምዱ ሰዎች ትኩረታቸው የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ ብቻ ነው::

በጎርጎራዊያን አቆጣጠር የ2007-2008 የፋይናንሽያል ቀውስ ኦባማ እንዲመረጥ ለማድረግ ሆነ ተብሎ የታቀደ የዲሞክራት ባንክ ባለቤቶች የሻጥር ተግባር ነው በማለት ብዙዎች ይከሳሉ፡፡ ኦባማ የተወለደበትም ቦታ ከምርጫው ጋር በማያያዝ በነጭ አክራሪ ሃይሎች የሴራ ትንተናው አካልም ነበር፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በመሳፍንት ዘመን የነበረውን አንድ ጠንካራ ሴንትራል ሃይል በሃገሪቱ እንዳይኖር የሆነበትን በተለይ በኢትዮጵያ የንጉሶችና የቤተመንግስት ህይወት ለብዙ የሴራ ትንተና የተጋለጠ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ የአጼ ምኒሊክ ህልፈትን ተከትሎ ህዝቡ ምናልባትም ለአመታት ምንም መረጃ ሳይኖረው እንደቆየ ይነገራል፡፡ ይህንን ተከትሎ የተለያዩ መላምቶችና የሴራ ትንተና እየተሰነዘሩ ብዙ ውዥንብር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ነበር፡  በተመሳሳይም የአፄ ምኒሊክ የልጅ ልጅ ከሆነው ከልጅ እያሱ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ ራስ ተፈሪ የሚመራው ሃይል ልጅ እያሱን አንድ ጊዜ ሙስሊም ሆኗል የኢትዮጵያ ንጉስ መሆን የለበትም ብሎ ሲከስ በሌላ በኩል ለእንግሊዞችና ፈረንሳውያን ደግሞ ይኽው ልጅ እያሱ በወቅቱ ከነበረው የአለም ፖለቲካ ጋር በማያያዝ ማዕከላዊ ኃይል /Central power/ (ከቱርኮች) ጋር በጅጅጋ ስምምነት ላይ ደርሷል በማለት ከፍተኛ ጫና አድርሰውበት በዛም ሳያበቃ ጦር አዝምተው የስልጣኑ ማብቂያ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዐይነ ስውር ድንጋይ ወርውሮ፣ ጠላቱን ስቶ ወዳጁን መታ!

ከዚያ ወዲህም በተመሳሳይ ብዙ የተለያየ ትርጉም የሚሰጣቸው ክስተቶች አልፈዋል፡  በደርግ የመጀመርያ አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የታየው መልካም የፖለቲካ ድባብ የከሸፈው በሴራና ሻጥር ፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡ በእርግጥ የግራ ፖለቲካ ባህርይ የድሃ ወገን ነን ቢሉም ቅሉ የመደብ ጠላት ብሎ የፈረጀውን ካላጠፋ እንቅልፍ የማይተኛ መሆኑ በራሱ ተፅእኖ የነበረው ነው::

የሆኖ ሆኖ በታሪካችን በፖለቲካዊ ንቃት በሃገራዊ ፍቅር ወርቃማ የነበረው የፖለቲካ ትውልድ ተደጋግፎና ተናቦ ሃገርን ከማዳን ይልቅ በእኔ ልብለጥ ፉክክር ትውልድ በዱር በገደል እንዲያልቅና አገሩን ለቆ እንዲሰደድ ምክንያት ሆኗል፡  ይህ ትውልድ የወለደውና ያሳደገው ፖለቲካ ደግሞ በእርግጥ የ60ዎቹ ትውልድ እስካሁን እግሩን ነቅሎ ባያወጣም ከቅንነት ይልቅ ጥርጣሬ : ከመተማመን ይልቅ ሴራና ደባ ልቆ የሚታይበት መጥፎ ዘር ተዘርቷል፡፡ መንግሰትም ሌላውም ከሴራ ሳይላቀቁ ዘመናትን ተሻግረን እዚህ ደርሰናል፡፡

ባለፉት ዓመታት ደግሞ ስርዓቱ የዲሞክራሲና የሃሳብ ነፃነት ድህነት የፈጠረው በመሆኑ ውድድርን ስለሚፈራ የተዳከሙ ተወዳዳሪዎችን በመፍጠር በሚፈራሩ ሃይሎች መሃከል ተደላድሎ የመኖር ሃልዬት ገንብቶ ኖሯል፡፡ በቅራኔዎች መሃከል መከራ ማለፉን እንደ እድል የቆጠረ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ በህዝቦች መሃከል ለዘመናት የማይታረቁ ቅራኔዎችን መፍጠር ብሎም ግለሰብ ከግለሰብ እንኳን እንዳይተማመን እስከማድረስ የሚደርስ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ለመቆየት እንደ ዋነኛ ስልት ይወሰዳል፡፡

በተለምዶ የአሻጥርና የሴራ ትንተና ፖለቲካ በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፋ ብሎ የሚደመጥ ከሆነ ያ ማህበረሰብ ያልተረጋጋና ለብዙ ግጭቶች የተጋለጠ መሆኑን መገንዘብ ለአስተዋይ አይሳነውም፡፡ የሴራ ትንተና ጨርሶ የፀረ ዲሞክራሲ መሰረት ያለውና የሃሳብ ልዩነትን የማይቀበል አስተሳሰብ ነው፡፡ ልክ ነኝ ብሎ የሚነሳ ሲሆን አብዛኛው መነሻው ጥላቻና ተቀናቃኙን እንደ ጠላት የሚመለከት : ወገን ለይቶ የሚያጠቃ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም በሴራ ፖለቲከኞች በጭራሽ ዴሞክራሲ ሊገነባ አይችልም፡፡

 

ዛሬ ያለውን የአቢይን መንግስት በስራውና በሚትገብረው ከመፈረጅ ይልቅ በግለሰቡ የትውልድ አመጣጥ : የእምነት አሰላለፍ : የስልጣን ምኞት ላይ የተመሰረተ: ለኦሮሞ ያደላል : ፔንተኮስታሎችን ያቀርባል : ዲክቴተር ሊሆን ይፈልጋል በሚል የጥርጣሬ ሴራ ዘመቻ በማድረግ ሕዝቡ እምነት እንዳያድርበት የሚደረገው ሻጥር ለሕዝቡ ሰላምና እድገት የሚሰጠው ጥቅም አይታይም:: ይህ ሻጥራዊ ሴራ የሴራው ፅንሰኞችና አራማጂዎች የሚያስቡትን አገርን ሰላም ማናጋትና ሕዝብን ማጋጨት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጠቀሜታ የለውም:: በተለይ ለአራት አስር ዓመታት በስብሶ የነበረውን መንግስታዊ አስተዳደርን ለመለወጥና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት: ለስልጣን መቀመጫ የሚራሯጡ ፀረ-አንድነትና የአገር ፍቅር የሌላቸው ግለሰቦች በስመ-ሕዝብና በስመ-ዲሞክራሲ የጎሳ ጦርነት በማስክፈት መረጋጋት በጠፋበት ወቅት : ጨቅላውን መንግስት በእውነት ላይ የተሞረከዘ ገንቢ ሂስ እያቀረቡ ከማገዝና ከማበረታት ይልቅ በሻጥርና በሴራ እንቅፋት መሆን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የበለጠ ሰቀቀን ውስጥ ይከታታል:: ለምሳሌ  ብንወስድ የአጫሉ ሁንዴሳን አሳዛኝ ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው አስከፊ የሕይወት መጥፋት የሻጥርና የሴራ ትንተና ውጤት ነው:: በዚያን ወቅት የጠፋው ንብረት ያመጣው የኢኮኖሚ ውድቀት የጎዳውና እየጎዳው ያለው በኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን ደሃውን ሕዝብ ነው:: የሻጥራዊ ሴራ አራማጂዎች የጀመሩት ጦርነት የትግራይ የአማራ የአፋር ህዝብንም የአሻጥርና የሴራ ትንተና ፖለቲካ ሰለባ አድርጎአል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   በኢትዮጵያውያን ምሁራን ፎረም ላይ ስሜን በመጥቀስና ካለአግባብ በመክሰስ ለዶ/ር ኤሌኒ ገብረመድህን ጠበቃ በመሆን ለወነጀለኝ ለዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ የተሰጠ መልስ!

ሴራና ሻጥር የትም ሃገር : አንድነት ያለው ጠንካራ ሃገር ገንብቶ አያውቅም:: አንድ ኢትዮጵያ እንጂ ሌላ ሃገር እንደሌለን ተረድተን በትውልድ እድሜና በህዝብ እጣ ፋንታ ላይ ባንቀልድ ይመረጣል፡፡ ለሻጥርና ሴራ አራማጆች ሕዝቦች የስልጣን ገበጣ ጨዋታቸው ጠጠሮች ናቸው:: ሴራ እና የጥላቻ ፖለቲካ የትም እንደማያደርሰን የመጣንበት መንገድ በቂ ትምህርት የሰጠን ይመስላል፡፡ ጥያቄው ግን ምን ያህል ተምረናል? ምን ያህል ተገንዝበናል? ያለን እድል ሴራውን ትተን በቅን ልቦና በሆደ ሰፊነት ለሕዝብ አንድነትና ደህንነት አገር በጋራ መገንባት ብቻ ነው፡፡

ስንጠቀልለው የሴራ ትንተና አላማው አገር መገንባት ወይም ለአገር መቆርቆር አይደለም፡፡ ከስልጣን ጋር የተያያዘ ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እያየነው ያለው  አስከፊ የጎሳ ጦርነት ባልተጀመረ ነበር፡፡ አንዱን የአገር ህዝብ ክፍል እወድሃለሁ እያሉት ማስፈጀትና ከሌላው የአገር ህዝብ ክፍል ጋር ማቃቃር ማጣላትና ማጋደል የሚያመጣው ጥቅም ለህዝብ ሳይሆን ለሴራ ፖለቲከኞች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም የህዝብ ግጭት ለሴራ ፖለቲከኞች የገንዘብ መስሪያ መንገድ ነው:: መታወቅ ያለበት በኢትዮጵያ አንዱ የህዝብ ክፍል ያለሌለው ሊኖር አይችልም፡፡

የዛሬ የጎሳና የክፍፍል ፖለቲካ : የጥቂት ለህዝብ አሳቢ አስመሳዮች ሻጥርና ሴራ : ለጊዜው ውዥንብር ከመፍጠር ውጭ : ኤኢሶፕ (AESOP) ከተወለደበት በአነስተኛው ከ640 የክርስቶስ ልደት በፊት ዓመት ጀምሮ ለዘመናት ከትውልድ እስከ ትውልድ ያለችውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አያፈርስም አይበትንም:: ምክንያቲም ኢትዮጵያዊነት ላይፈታ የተሳሰረና የተቆላለፈ ረቂቅ ሚስጥራዊ የክር ድር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቢፈቱት ቢፈቱት ተበትኖ ያልተላቀቀው፡:

ኢትዮጵያና  ኢትዮጵያዊነት ለዘለአለም ይኖራሉ!!!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share