‘‘ፋሽዝም’’ በኢትዮጵያ!

በቅዱስ ዬሃንስ

ኢትዮጵያ በወያኔ ፈላጭ ቆራጭ ቡድናዊ አገዛዝ ስር ከወደቀችበት እነሆ ሁለት አስርተ ዓመታት ነጐዱ። ወያኔ ስልጣን ላይ ሲወጣ ካለፈው የተሻለ የዲሞክራሲ ለውጥ ይመጣል የሚል በብዙ ሰዎች ዘንድ የተስፋ ጭላንጭል ተጥሎለት ቢኖርም “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” እንዲሉ ስልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ ግን ተስፋ የተጣለለትን ዲሞክራሲ ደብዛውን በማጥፋት “ከፋፍለህ፣ በሆዱ ይዘህ፣ አሸብረህ፣ አደናግረህ፣ አናቁረህና አደንዝዘህ ግዛ” የሚለውን ሌሎች አምባገነን መንግስታት የሚከተሉትን የጡንቻ አገዛዝ ዘይቤ የዲሞክራሲ ሽፋን በመስጠት ዘላለማዊ ስልጣናቸውን ለማጠናክር ሲሉ በበለጠ ሲጠቀሙበት መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ቆይቷል።

በአገራችን ኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ አገዛዝ በዓለም ዙሪያ በተለያየ ዘመን ወደ ሥልጣን ከመጡት መሰል ፀረ-ሕዝብ መንግሥታት ቢብስ እንጂ በምንም መልኩ የተሻለ አይደለም። ፋሽዝምን እንቃወማለን፣ እናወግዛለን እያለ በጫካ ያናፋ የነበረው ወያኔ ዛሬ በዲሞክራሲ ድባብ ሥር እየተገበረው ያለ አገርና ሕዝብን ማዋረድና መዝረፍ፣ መቀጣጫ እያለ በግፍ ማሰርና መግደል ምን ተብሎ ሊጠራ ነው? በአዲስ አበባ ፣ በጋምቤላ ፣ በአዋሳ ፣ በወለጋ ፣ በሰሜን እና በአራቱም ማእዘን የኢትዮጵያ ክልሎች በየእለቱ በወያኔ ታጣቂዎች እየተካሄደ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ ምን ብለው ይጠሩታል?

ወያኔ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ተሸክሞት የመጣውን በቀል አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ አፋሩ፣ ኦጋዴኑ ወዘተ. ዘር የማጥፋት ተግባሩን ፈጽሞታል፤ አሁንም እያጠፋ፣ እየገደለ በየወህኒ ቤቶቹ እየማገደው ነው። ይዞት የመጣው ድህነትና በሽታን ብቻ ነው። ፖሊሲው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዓለም ሃገሮች በድህነት ከወለል በታች ያደረገ ስርዓት ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት በነበረበት ወቅት እራሱን እና ቤተሰቡን አብልቶ ቀሪውን ለገበያ በማቅረብ ሕዝቧ እንደ አቅሙ በልቶና ጠጥቶ ያድር ነበር። የወያኔ መንግስት መሬት የመንግሥት ነው ብሎ በማወጁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠሩም በከተማም መሬት አልባ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ ሃገሩ ሁለተኛ ዜጋ ከመሆኑ የተነሳ ሲሞት እንኳን የሚቀበርበት ቦታ ያጣ ሕዝብ ሆኗል። የዚህ ጽሁፌ ዋና አላማ የወያኔ መንግስት የፋሽስት አገዛዝ ስለመሆኑ ምሳሌዎችን አንድ ሁለት በማለት ነቅሸ በማሳየት ማስረገጥ ሲሆን ወያኔ ከምስረታው ጀምሮ ያካሂድ የነበረውን የንፁሃን ወገኖቻችንን ጭፍጨፋ ለማስረጃነት በማንሳት ለማሳየት እሞክራሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተቆለፈበት ቁልፍ ! ከዶ/ር ምህረት ደበበ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት፣ 438 ገጽ ትችት! -  በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

• ወያኔ በ1969 መጀመሪያ በትግራይ ሰላማዊ ዜጋ ላይ ግድያ በመፈፀም ፋሽስታዊ ጉዞውን ሀ ብሎ ጀመረ። ግድያው ሳያንሰው የንፁሃን ዜጐችን ሃብትና ንብረትም ወረሰ። ከደደቢት በረሃ የጀመረውን አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው በማለት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች አማራውን በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀልም ፈጽመዋል። ለሴቶች በግዳጅ የማምከኛ መድሃኒት በመስጠት የአማራው ቁጥር እንዳይጨመር አድርገዋል። ከኖረበት ቀየውና መሬቱ በግዳጅ እንዲፈናቀል አድርገዋል።
• ወያኔ ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ በ1984/5 መጀመሪያ ጀምሮ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ በመክፈት የግድያ፣ የቤት ማቃጠል፣ ንብረቱን መዝረፍና ከፍ ያለ ሰቆቃ አደረሰ። እንደ አማራው ሁሉ ከመኖሪያ ቦታውና ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሏል። የኦነግ አባል ናችሁ እየተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ ወደ ወህኒ ወርደዋል። በየቦታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የሚማሩት የኦሮም ልጆች ከትምህርታቸው ተባረዋል። የተባረሩትም፣ መባረራቸው አልበቃ ብሎ ለእስር ተዳርገዋል፤ የተገደሉትንም ቤት ይቁጠራቸው። ደጉና ሩህሩሁ የኦሮሞ ሕዝብ ከእርሻው ተፈናቅሎ የረሃብና የበሽታ ሰለባ በመሆን የፋሽስቱ ወያኔ የግፍ ፅዋ ገፈት ቀማሽ ከመሆን አላለፈም።
• ወያኔ በጋምቤላ አኝዋኮች ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማንም ይረሳልዋል ብየ አላስብም? ሕዝቡ ከመሬቱ ተፈናቅሎ አብዛኛው በጎረቤት ሃገሮች ስደተኛ ሆነው በየሃገሩ እየተንከራተተ በችግር ላይም ይገኛሉ።
• የኦጋዴን ሕዝብም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል። ቤት ንብረቱ በወያኔ ወታደሮች ተቃጥሎበታል፤ ሴት ልጆቹና ሚስቶቹ ተደፍረውበታል። በተጨማሪም ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሎ ለስደት ተዳርጓል።
• የአፋር ሕዝብም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ጎሳዎች የደረሰው ደርሶበታል፣ እየደረሰበትም ይገኛል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማሰቃየት ባለፈ ደግሞ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለሱዳን መንግሥት ሸጠዋል። ሃገሪቱን ካለባህር በር አስቀርተዋል። የሃገር ሃብትና ታሪካዊ ቅርሶችን አውደመዋል፣ ሸጠዋል።
እንደው በደፈናው በአገራችን ታሪክ ውስጥ በሕዝባችን ከቶም እንደ አሁኑ ሳንጃ በአንገቱ ላይ ተወድሮ ጦር ተሰብቆበት የሚገኝበት የፋሽስታዊ አገዛዝ ጊዜ የለም። ፋሽዝም ዛሬ በወያኔ/ህወሃት ጊዜ ነግሷል ሥርም ሰዷል። በሥልጣን ላይ ለመቆት፣ ሃብቷን በዝብዞና ሽጦ ለማፈራረስ በታቀደው የአገዛዝ ሽብር ተግባር፣ ፋሽዝም በዴሞክራሲ ታዛ ሥር ወያኔ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ እየፈጸመው ያለ ለመሆኑ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ይረዳውል ብየ አምናለሁ። ፋሽስት ሕዝብ ይጨፈጭፋል፣ ያስፈራራል፤ ፋሽስት የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳን ያስፋፋል፣ ውሽት ይዋሻል፤ ፋሽስት ትምክህተኛና ጦርነት ፈላጊ ነው። ፋሽስት ራስ ወዳዶችን፣ ሆዳሞችን፣ ግብዞችን፣ ዱርየዎችን መሳሪያ ያደርጋል፤ ፋሽስት ድርጅቶችን ያስፋፋል፣ ተለጣፊ ያበዛል ወዘተ። እንግዲህ የፋሽስት አገዛዝ ባህርያትን ማንሳቴ ወያኔን በነዚህ ባህሪያትም መዝነን ፍረጃችንን ለማጠናከር ይረዳን ዘንድ በማሰብ ነውና መዝኖ ፍርድ መስጠቱን ለእናንተው ትቻለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህወሃት/ብአዴን በጨለማ ጐንደርን በታንክ ምን ለማድረግ !!?

ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እጁን በንፁኃን ዜጎች ደም የታጠበው የወያኔ አገዛዝ ሕጋዊ የአምልኮት ነፃነታቸው ያለምንም የአገዛዙ ጣልቃገብነት እንዲከበር የጠየቁ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ በሃይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት ወንጅሎ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል። በክርስቲያን እምነት ተከታይ ወገኖቻችንም ተመሳሳይ ግፍ ሲፈፀምባቸው ተመልክተናል። ገዳማትን ማፍረስና መነኮሳትን ማሳደድና መግደል የወያኔ መለዮው ሆኗል። ወያኔ ንፁኃን ዜጎችን ከማሰቃየት፣ ከማሰርና ከመግደል የታቀበበት ወቅት ከቶውንም የለም፤ አልታየምም። ድብደባው፣ ማሰሩና ግድያው እየተፈጸመ ያለው በሁሉም የሃገሪቷ ክፍሎች በሚኖሩ ንፁሃን ዜጐች ሲሆን በግፍና በገፍ ወደ እሥር ቤት የማጎር እርምጃዎች ያልርኅራሄ ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በኢትዮጵያዊ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት በፋሽስቱ ወያኔ ወገን ሲደበደብ፣ ሲባረር፣ ሲገደል፣ ሃብት ንብረቱ ሲዘረፍ፣ ዳር ድንበሩ ሲወሰድ፣ በቋንቋ ልዩነት ሲመደብ፣ የተማረ ወገን ሲገደልና ሲሰደድ፣ አገር ለውጭ ባለሃብት ስትሽጥ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን እስከ አሁን በደልን ተሸክመህ በዝምታ ታግሰሃል። ዛሬ በፋሽስቱ ወያኔ ኢትዮጵያ ተደፍራለች፣ ሕዝቧ ተዋርዷል፣ የታሪክ ክብሯ ተንቋል። ለብዙ ሺህ አመታት የኛ ቀደምት ትውልዶች አጥንትና ደማቸውን በማፍስስ ታፍራና ተፈርታ የኖረች አገር ዛሬ በዚህ ወቅት የትውልድ መካን ሆና ጥቃቱና ጥፋቱ እጅግ ተነባብሯል። ኢትዮጵያዊ ወገኔ ሆይ! ፍርሃት ከአደጋ የመከላከያ ባህሪ እንጂ እየሸሹ ለመጥፋትና ለመሞት አይደለም። ይህ ጭቆናና ጥቃት ሊያበሳጭ፣ ሊያናድድህና ሊያስቆጣህ ይገባል። ሰው ነህና ለመብትና ለነፃነት መታግልና ለመጭውም ትውልድ ለልጆችህ አገር ማቆየት ይኖርብሃል። የኛ ቀደምት አባቶችና እናቶች እኛ ሞተን አገር ትኑር ብለው ለኢትዮጵያ ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ታሪክ ምስክርነትዋን መዝግባለች። ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ወኔና ጀብዱ፣ አትንኩኝ ባይነት ይደገም። ወያኔ ኢትዮጵያዊነት የሌለው አረመኔ ፋሽስት ነውና፤ መወገድ አለበት። ስለዚህ ለትዕግሥት ገደብ እንስጥ፣ አንዋረድ ፣ ትውልድ እንጠብቅ፣ አገርና ሕዝብ እናድን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እነ ሚሚ ስብሃቱ የሚያጨሱት ምኑን ነው?

ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!

ለአስተያየትዎ፡ kiduszethiopia@gmail.com አድራሻየ ነው።

1 Comment

Comments are closed.

Share