በላይነህ አባተ ([email protected])
በባለጊዜዎች የስልጣን ጦርነት ምክንያት ሕዝብ በወሎ፣ በሸዋና በጎንደር በሚታጨድበትና በሚሰደድበት ሰሞን ምእመናን በማረጋጋት በጎ ተግባር የተሰማሩ የአንድ መነኩሴ አባት ሥም ብቻ ተደጋግሞ መነሳቱ ለኢትዮጵያ መንፈሳዊና ምንኩስና ታሪክ “የዓባይን እናት ውሀ ጠማት” አስኝቶ የሚያስተክዝ ነው፡፡
እንደሚታወቀው መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ እሴት ኢትዮጵያን በአለት ላይ የገነባ ፀጋ ነው፡፡ ይኸንን ፀጋ እየተመገቡ በሰላም ጊዜ በነፍስ አባትነት፣ በሽምግልና፣ በመምህርነትና በፈላስፋነት የሚያገለግሉ፤ ሰላምን የሚነሳ ሰይጣን የላከው ወራሪ ሲመጣም ጦር ሜዳ ሄደው እስከ መዋጋት የሚደርሱ የሃይማኖት አባቶች ቁጥር እልቆ መሳፍርት አልነበረውም፡፡ ለምሳሌ በአምስቱ ዘመን ፊልክስዩን(ከመጻሕፍተ መነኮሳት አንዱ) “የዋህ ሁን ለክፉ ግን የዋህ አትሁን” [1] የሚለውን መልዕክት ተከትለው መነኮሳት በእንቁላል ቀቃይ ባንዳዎች እየተመራ ሕዝብ የፈጀውን ፋሽሽት መሳሪያ ታጥቀው እንደተዋጉ የሚታወቅ ነው፡፡ የበቁ መነኮሳት በደብረ ሊባኖስና በሌሎች ገዳማትም እንደተረሸኑ አፍ ቢኖራቸው ስጋቸውን የበሉት ሜዳዎችና ተራሮች እንደዚሁም ደማቸውን የጠጡት ወንዞች የሚመሰክሩት ነው፡፡
ዛሬ የዓባይ እናት ኢትዮጵያ ውሃ ጠምቷት የአንድ መነኩሴ ሥም ብቻ ጠርታ ለሁለተኛ ጊዜ የምትጠራው ተጠምታ የብቁ መነኩሴ ያለህ እያለች ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ጥማትም የመነኩሳት መተዳደሪያ ወይም መለኮታዊ መመሪያ የሆነውን መጻሕፍተ መነኮሳት እንድንፈትሽ እየገፋፋን ነው፡፡
መጻሕፍተ መነኮሳት የመነኮሳትን ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ ታሪክ፣ ተጋድሎና ተመከራም የሚያገኙትን ትሩፋት የሚያስተምር ተአዋልድ መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ የአዋልድ መጻሕፍት ትርጉም የመጻሕፍት ልጆች ማለት ሲሆን ወላጆችም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፡፡
ተብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን የተወለዱት መጻሕፍተ መነኮሳትም ሶስት ናቸው፡፡
ልጅ አንድ፡- ማር ይስሐቅ ስለመነኮሳት ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ጾምና ተጋድሎ ያስትምራል፡፡
ልጅ ሁለት፡- ፊልክስዩስ ስለ መነኮሳት የገዳም ታሪክና ተጋድሎ ያስረዳል
ልጅ ሶስት፡- አረጋዊ መንፈሳዊ መነኮሳት መከራን ተቀብለው ስለሚያገኙት ፀጋ ወይ ትሩፋት ያስተምራል፡፡
አረጋዊ መንፈሳዊ ሥርዓተ ብሕትውናን ጳውሎስ፤ ሥርዓተ ምንኩስናን ደሞ እንጦስ እንደ ጀመረው ያስተምራል፡፡ [2] የናጠጠ ባለጠጋ ልጅ የነበረው እንጦስ ሥርዓተ መንኩስናን የጀመረው ቤሳ ሳያስቀር ሐብቱን ሁሉ ለዓለማውያን ትቶ ነው፡፡ የእርሱን ፈለግ በመከተል ቁጥር ስፍር የሌላቸው የኢትዮጵያ መነኮሳት ይህችን ዓለም ንቀው ገዳም ገብተው ቃል ኪዳንን እንደጠበቁ፣ በጾም አካላቸውን አድቀው በፀሎት ደግሞ መንፈሳቸውን አጠንክረው ሰይጣን የላከውን በፀሎት ብቻ ሳይሆን በመሳሪያም ታግለው እንዳለፉ ታሪክና ብቻ ሳይሆን ብዙ ቋሚም በዓይኗ በብረቷ ያየው ነው፡፡
ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ግን ምንኩስና እንደ እንጦስና የቀድሞ ኢትዮጵያውያን አባቶች ከባለጠጋነት ወደ ድህነት የሚሸጋገሩበት መንፈሳዊ ድልድይ ሳይሆን ከድህነት ወደ ባለጠጋነት የሚሸጋገሩበት አካላዊ መሰላል እንደሆነ ሁሉም በየሰፈሩ የሚያየው ነው፡፡
በፓትርያሪክነት፣ በጵጵስናና በተለያዩ የክህነት መንበሮች የተቀመጡ መነኮሳት የመጻሕፍተ መነኮሳትን መለኮታዊ መመሪያ እረግጠው ለመመረጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ ለጥቅም በካድሬነት ነፈሰ ገዳይ ገዥዎችን ሲያገለግሉ፣ ገንዘብ ሲመዘብሩ፣ በደመወዝ ከምእመናን ጋርና እርስ በርሳቸው ሲጨቃጨቁ መታየታቸው ወዘተርፈ እንኳን መለኮትን ሰይጣንንም የሚያስገርም ነው፡፡
ማር ይስሐቅ መነኮሳት እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲያስተምር “ለሰውነትህ እረፍትን ኅድዓትን ታገኝ ዘንድ ዘወርትር መጽሐፍትን መመልከት ውደድ፤ ከንዑሳን ሕጣውእ ተከልከል” ይላል፡፡ ንዑሳን ሕጣውእንም “ማየት፣ መስማት፣ ያለመጠን መብላትና መጠጣት ናቸው” ይላል፡፡[3] ማር ይስሐቅ ማስተማሩን ሲቀጥልም “የእንጨት ብዛት እሳቱን እንደሚያበዛው የምግብ ብዛትም ዝሙትን ያበዛል፡፡ በልቼ ጠጥቼ፤ አይቼ ሰምቼ፣ ንጽሕናየን ጠብቄ ከሴት ርቄ መኖር ይቻላል አትበል” ይላል፡፡ [4]
ማር ይስሐቅ መነኮሳትን ስለገንዘብ ማሳደድ ሲያስጠነቅቅም “ድሀ ትሆን ዘንድ ውደድ፣ ተርታ ልብስ መልበስን ውደድ” ይላል፡፡ [5]
መለኮት ምስጋና ይግባውና ኢትዮጵያ የማር ይስሃቅንም ሆነ የሌሎቹን መጻሕፍት መነኮሳት ትዕዛዛት በትክክል የፈፀሙ ባህታውያን ገዳም ነበረች፡፡ ዛሬ ግን የእውነተኛ መነኩሴ ድርቅ መቷት “በሽልማት” የሚንበሸበሹ አንድ መነኩሴ ብቻ ጠርታ ሁለተኛውን ለመጥራት ክፉኛ ተጠምታለች፡፡ ድንበር ተሻግሮ የስንቱን ሕይወት እንደሚታደገው የዓለም ረጅሙ ወንዝ ዓባይ ስንቱን ውቂያኖስ ተሻግራ የዓለም ቤተመጻሕፍትን በመንፈሳዊ ሐብት የምትመግበው ኢትዮጵያ ዛሬ ቀን ጥሏት ውሀ እንደ ጠማት የዓባይ እናት በመነኩሴ ጥማት እየተሰቃየች ትገኛለች፡፡ ጥማቷ እንዲረካም እጆቿን ወደ ሰማይ ትዘረጋለች!
ዋቢ፡-መጻሕፍተ መነኮሳት 1928 ዓ.ም ብርሃንና ሰላም እትም
- ፊልክስዩስ ገጽ 252-253
- አረጋዊ መንፈሳዊ፡ መቅድም ገጽ 3
- ማር ይስሐቅ ገጽ 10
- ማር ይስሐቅ ገጽ 57
- ማር ይስሐቅ ገጽ 14
ይቆይን!
የካቲት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.