መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ከተሳነው ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ፈጥሮ እንደሚታገል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ። በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ” ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣን ድረስ “የሰርጎ ገብ አደረጃጀት አለው” ሲል የወነጀለው ፓርቲው፤ መንግስት የህዝብ ደህንነት እንዲያስጠብቅ እና መዋቅሩን “በጥልቀት” እንዲፈትሽ አሳስቧል።
ኢዜማ ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ አርብ የካቲት 25፤ 2014 በአዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የዛሬው የኢዜማ መግለጫው ትኩረት ካደረገባቸው አምስት ነጥቦች አራቱ በጸጥታ እና ግጭት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ የዳሰሰው የኢዜማ መግለጫ አንዱ ክፍል፤ በክልሉ በተደጋጋሚ “ጥፋት” እየፈጸመ ይገኛል ያለውን “የኦነግ ሸኔን” ቡድን የተመለከተ ነው። በኢዜማ መግለጫ “የሽብር ቡድን” በሚል የተጠራው “ኦነግ ሸኔ”፤ በመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ድጋፍ በማግኘት አላማውን በማስፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኦነግ ሸኔ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የኢኮኖሚ እና ቁሳቁስ ድጋፍ የሚያመቻች “ምስጢራዊ ቡድን አዋቅሯል” ሲል ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ወንጅሏል። “የሽብር ቡድኑ” ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ድረስ “የሰርጎ ገብ አደረጃጀት” አለው ሲል የሚከስሰው ኢዜማ፤ ቡድኑ ባደራጀው ምስጢራዊ ቡድን መረጃዎችን ያገኛል ባይ ነው።
ኢዜማ በመግለጫው ያነሳው ሌላኛው ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ጉዳይ፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮችን ናቸው። በአማራ ክልል ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ልዑክ መላኩን ያስታወሰው ፓርቲው፤ በደቡብ እና እና ሰሜን ወሎ ዞን ደረሱ ያላቸውን ችግሮች በመግለጫው ዘርዝሯል። በአማራ ክልል “ሕገ ወጥ የመሳሪያ ንግድ እና ዝውውር እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያለው ኢዜማ፤ “አንዳንድ ከተሞች ከፍተኛ የጦር መሳሪያ መሸጫ ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል” ብሏል።
የህወሓት ኃይሎች ከአማራ ክልል መውጣትን ተከትሎ፤ “ሸሽተው የነበሩ የብልጽግና አመራሮች” ወደ ክልሉ ተመልሰው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ “በርካታ አዳዲስ የታጠቁ ቡድኖች፣ ሃይማኖት ተኮር የወጣት ሊጎች የመሳሰሉ አደረጃጀቶች” መፈጠራቸውን ኢዜማ ገልጿል። ኢዜማ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አሉ ያላቸውን “ችግሮች ለማስወገድ እና በጋራ ለመስራት” የሁለቱን ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች ለማነጋገር በደብዳቤ ቢጠይቅም ፍቃደኛ አለመሆናቸውን አስታውቋል።
ኢዜማ በመግለጫው ያነሳው ሶስተኛው ነጥብ በአፋር ክልል በህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉትን አካባቢዎች የሚመለከት ጉዳይ ነው። ፓርቲው “የህወሓት ጦር ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ እስኪወጣ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ስራው የሆነው መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ” ሲል አሳስቧል።
“የህወሓት ጦር ሙሉ በሙሉ ከአፋር እና አማራ ክልል ባልወጣበት ሁኔታ” መንግስት “የህልውና ዘመቻውን አንደኛውን ምዕራፍ አጠናቅቄያለሁ” ማለቱን፤ ኢዜማ “ግብታዊ ውሳኔ” ሲል ነቅፎታል። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉም “ጦርነቱ ሳያልቅ፤ ጦሱን አማራ እና አፋር ክልል ላይ ጥለን፤ አልቋል ብለን መሄድ ተገቢ አይደለም። ገና እኮ ነው፤ ዋጋ እየተከፈለ ነው ያለው” ሲሉ የፓርቲያቸውን ሃሳብ አንጸባርቀዋል።
አዜማ በመግለጫው ያካተተው ሌላኛው ነጥብ “በመንግስታዊ መዋቅር የታገዙ” ያላቸውን የደቡብ ክልል ግጭቶች ነው። “በደቡብ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች መንግስት ከዚህ ቀደም የወሰደው ልል የህግ ማስከበር ሂደት ቀጠናውን የስጋት ውጥረት እንዲያጠላበት አድርጎታል” ያለው ኢዜማ፤ በክልሉ አለ ላለው “ግጭት” መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ መቀመጫ ያለው ኢዜማ፤ በዛሬው መግለጫው ለጠቀሳቸው የጸጥታ ችግሮች “የመንግስት መዋቅር በተለያየ ስውር አላማ ባላቸው አካላት መጠለፍ፣ ቀሪውም መዋቅር የህዝብን ጥቅም ለማስከበር አቅሙን አጠናክሮ መስራት አለመቻሉን” በምክንያትነት አንስቷል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም ችግሩ ያለው አሰራር ላይ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የአሰራር፣ የፖሊሲ፣ የእዝንላልነት፣ የቸልተኝነት ወይም ስልጣንን የማስቀደም ካልሆነ በስተቀር፤ ሀገሪቷ ውስጥ የመንግስትን የጸጥታ ኃይል ሊገዳደር የሚችል ምንም አይነት ኃይል የለም። እዚህ ሀገር በጣም በርካታ የፌደራል ፖሊስ፤ መከላከያ ነው ያለው። በጣም ብዙ የጸጥታ ኃይል ነው ያለው። የአደረጃጀት እና ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠት ችግር ነው ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ አቶ የሺዋስ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አንኳር ነጥቦች፡-
- ከሕወሓት ወረራና ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮች፤
- የኦነግ ሸኔን ጥቃት የሚያስቆመው አካል ሊገኝ አለመቻሉ፤
- በሱማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖችና ቦረና ዞን በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ፤
- የአፋር ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች አሁንም በሕወሃት ወራሪ ሃይል ስር ስለመሆናቸው፤
- የደቡብ ክልል ግጭት መነሻዎች በመንግሥታዊ መዋቅር የታገዙ ስለመሆኑ
መንግሥት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የሕዝብን ደኅንነት ሊያስጠብበቅ፣ መዋቅሩንም በጥልቀት ሊፈትሽ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በመንግሥት ትኩረት ማነስ፣ የመንግሥት መዋቅር በተለያየ ስውር አላማ ባላቸው አካላት መጠለፍ፣ የቀረውም መዋቅር የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር አቅሙን አጠንክሮ መሥራት ባለመቻሉ ምክንያት በአገራችን የሚከሰቱ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት መጠናቸው እየበዛ አፈጻጸማቸውም እየረቀቀ መጥቷል ብሎ ያምናል፡፡
በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች መዋቅራዊ ድጋፍ እንዳላቸው መታየቱ፣ ሕዝቡም ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ድረስ ጠንቅቆ እያወቃቸው ከመኾኑም ባሻገር የመንግሥት አመራሮች በሚሰጡት ግብረ ገብነት የጎደለው ምላሽ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ የራሱን አዋጭ መንገድ መከተል ከመጀመሩ በፊት ለሕዝብ ደኅንነትና በቀጣይ ለአገራችን ሕልውና ሲባል አፋጣኝ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ አገራችን ወደማትወጣው የከፋ አደጋ ውስጥ ትገባለች ብለን እንሰጋለን፡፡
ኢዜማ ከዚህ በታች የዘረዘራቸውን እና ለጊዜው በመግለጫው ያላካተታቸውን ችግሮች በማጠናቀር፤ ድጋሚ እንዳይፈጠር፣ ተረዳድቶ ችግሮችን ለማስወገድ እና በጋራ ለመሥራት ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፈለ (ዶ/ር) ጋር ለመነጋገር የቀጠሮ መጠየቂያ ደብዳቤ በመፃፍ ጭምር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ሁለቱም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡
- ከሕወሓት ወረራና ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮች፣
ኢዜማ ከጦርነት በኋላ ልዑካን በመላክ ቅኝት ካደረገባቸው ክልሎች መሀከል አንዱ የአማራ ክልል ነው፡፡ አማራ ክልል በተለይም በሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሕወሓት ወራሪ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው በሌሎች ቦታዎች ላይ ያሉ ወገኖች ከእነሱ ያልተናነሰ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ቦታው ድረስ ሄዶ በማየት አረጋግጧል፡፡
በቅኝቱ የተገኙ መረጃዎች፤
- የሕወሓት ወራሪ ኃይል ወደ ትግራይ ማፈግፈግን ተከትሎ በጦርነቱ ወቅት በሕልውና ዘመቻው ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው፣ ቀድመው የሸሹ የብልፅግና አመራሮች ወደ ክልሉ ተመልሰው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ በርካታ አዳዲስ የታጠቁ ቡድኖች፣ ሃይማኖት ተኮር ወጣት ሊጎች የመሳሰሉ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፤
- በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ንግድ ዝውውር እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ አንዳንድ ከተማዎች ከፍተኛ የመሳሪያ መሸጫ ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል፤
- ከዚህ በፊት በኅብረተሰቡ ዘንድ ፍጹም የተጠሉና በሕወሓት የአገዛዝ ወቅቶች ለሕወሓት አጎብዳጅ የነበሩ ካድሬዎች ዛሬም የስልጣን ማማው ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ከዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች የተገፉ የብልጽግና አመራሮች ከሕወሓት ጎን ተሰልፈው ሕዝቡን ሲወጉ እንደነበር፣ አሁንም ልባቸው ከሕወሓት ጋር እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፤
- ባለሥልጣናቱ ከሸሹበት ከተመለሱ በኋላ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ከተማዋን ለቆ ያልወጣ፣ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን ሕዝብ “ለሕወሓት መንገድ ጠቋሚ ናቸሁ!” በማለት አላግባብ ፍረጃ እና ውንጀላ ውስጥ ገብተው ሰላማዊ የሆነውን ነዋሪ እያሰቃዩት ይገኛሉ፤
- ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ አንዳንድ የወረዳ አመራሮች የሕግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻላቸው፤ የተወሰኑ ከተማዎች ሌሊት ሌሊት በመሳሪያ ተኩስ ሲናጡ ያድራሉ፡፡ ሕዝቡም “የሕወሓት ወራሪ ኃይል ተመልሶ መጥቷል” በሚል የስጋት ኑሮ እንዲገፋ ተገዷል፡፡
- ወደ ሕዝቡ ወርዶ የሚያናግር የመንግሥት አመራር እስካሁን ባለመኖሩ በክልሉ ከት/ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ በስተቀር (እርሱም ከፍተኛ ጉድለት አለበት) ሌሎቹ የመንግሥት መሥስሪያ ቤቶች በተገቢው መንገድ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም።
- ለምግብ እርዳታ ስርጭት በሕዝቡ የተወከሉ ኮሚቴዎች ቢኖሩም ባለሥልጣኖቹ ኮሚቴዎቹን በራሳቸው ጊዜ ሸኝተው እርዳታውን በአግባቡ እንዳይደርስ አድርገው ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ የኢዜማና የሌሎች ፓርቲዎች አባላት እና አንዳንድ ግለሰቦች የሚደረገውን ዝርፊያ የማጋለጥ ሥራ ሲሠሩ ባለሥልጣኖቹ እኩይ ተግባሩን ከማስቆም ይልቅ የራሳቸውን የፌስቡክ ሠራዊት በማደራጀት በማኅበራዊ ሚዲያም፣ በአካልም ማስፈራራቱን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል፤
የሰሜን ወሎ የኢዜማ አመራሮችና አባላት በሕልውና ትግሉ ወቅት ስንቅና ትጥቅ ወደ ግንባር በማድረስ፣ መሳሪያ አንግበው በመዋጋት። አገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፤ አቡበከር ያሲን የተባለ የኢዜማ አባል ወልዲያ ላይ የነበረውን ሰቆቃ ለሚድያ በማሳወቁ ወራሪው ኃይል ደሴ በገባበት ወቅት አባላችንን በጥቆማ አፍኖ በመውሰድ እስካሁን ድረስ የት እንዳደረሰው አልታወቀም፡፡ የኢዜማ አባላት ይሄን መሰል ብዙ ሁነቶችን ያሳለፉ ሲሆን በተለያዩ ግንባሮች ተሰልፈው እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የከፈሉ አባላት እንዳሉትም ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር የክልሉ መንግሥት በህልውና ዘመቻው ወቅት ግንባር ድረስ በመሰለፍ አስተዋጽዖ ላደረጉና የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢዜማ አባላትና አመራሮች እንደ ዜጋ እውቅና መስጠት እንዳለበት ማሳወቅ እንሻለን። አባላቶቻችን ላይ ከሚያደርሰው ጫና እና እንግልትም እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡
- የኦነግ ሸኔን ጥቃት የሚያስቆመው አካል ሊገኝ አለመቻሉ ፤
በተለምዶ ‘ሸኔ’ የሚባለው ራሱን ‘የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት’ ብሎ የሚጠራ ቡድን በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ኢሊባቦር፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ባሌ እና ቦረና ዞኖች በሚገኙት ጫካዎችና ቆላማ መሬቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ ይዞታውን እያሰፋና እየቀያየረ የሚንቀሳቀስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ አጥፊ ቡድን ነው፡፡
ኦነግ ሸኔ በዋናነት በጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ በተባለ ስፍራ ውስጥ ዋና ማዘዣውን በማድረግ ከልካይ ሳይኖረው የሽብር ተግባር ለመፈጸም ራሱን በየቀኑ እያደረጀ ይገኛል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምዕራብ 250 ኪ.ሜ ገደማ ላይ የምትገኘዋ የዳኖ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ‹‹ሰዮ›› ከተማ ዙሪያ ያሉት በርካታ ቦታዎች እስካሁን ለመንቀሳቀስ ስጋት የሆኑ ሥፍራዎች ሆነዋል፡፡
ታጣቂዎች በርካታ የወረዳ ገጠር ቀበሌዎችን በመቆጣጠራቸውም ወደ ከተማዋ ምንም ዓይነት ምርት ባለመግባቱ ንጹሃን ዜጎች ለረሃብ የሚጋለጡበት እድል ሰፊ ሆኖ ይገኛል፡፡
ኦነግ ሸኔ አደረጃጀቱ ውስብስብ ሲሆን ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ድረስ የሚደርስ የሰርጎ ገብ አደረጃጀት ያለው ሲሆን በአንድ ዙር ከ4 እስከ 6 ወር በሚፈጅ ስልጠና ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሽምቅ ተዋጊዎችን በየጊዜው በማስመረቅ ላይ ይገኛል፡፡ ኬንያ ያለው ትልቁ እና ግዙፉ የሽብርተኛ መፈልፈያ ማሰልጠኛ ከሆነው ‹‹ሶሎሎ›› ከሚባለው ማሰልጠኛ የሰለጠኑ ብዛት ያላቸው የወለጋ እና የሐረርጌ አከባቢ ወጣቶች ሰልጥነው ለሽብር እንደተሰማሩ ይነገራል፡፡በአገር ውስጥም ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እንዳላቸውም ይነገራል።
በ2014 ዓ.ም በመንግሥት ጥሪ የገናን በዓል ለማክበር በሚል ሰበብ ወደ አገር ቤት ከኖርዌይና ከአሜሪካ የመጡ ጥቂት ዲያስፖራዎች የኦነግ ሸኔን ታጣቂዎች ምሥራቅ ወለጋ ድረስ ሄደው መጎብኘታቸውና ቁሳቁሶችን መርዳታቸው ይታወሳል፡፡ ኦነግ ሸኔ እጅ የገባው ቁሳቁስ በየት በኩል እና እንዴት ለቡድኑ እንደደረሰ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የመንግሥት አካላትም በጉዳዩ ላይ ለሕዝቡ ማብራሪያም ሆነ ማስተባበያ ለመስጠት አልደፈሩም፡፡ በሌላ በኩል የሸኔ ጦር ሠራዊት ማሰልጠኛ ካምፖች በቢቢሲ ጋዜጠኞችም ተጎብኝተዋል፡፡
ካደረሳቸው ጥፋቶች ጥቂቶቹን ለማሳያ ያህል፡-
- የሽብር ቡድኑ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በ1ለ5 አደረጃጀት ጭምር በመግባት በከተማ ውስጥ ቡድኑን በኢኮኖሚ እና በቁሳቁስ ድጋፍ የሚያመቻች፣ መረጃን በመሰብሰብ ጫካ ላለው ተዋጊ ኃይል አሳልፎ የሚሰጥ ምሥጢራዊ ቡድን አዋቅሯል፡፡ የሽብር ቡድኑ ሃብት የሚያሰባስበው ከባለሃብቶች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከመደበኛ ነዋሪዎች ሲሆን በትብብር እና በመግባባት ድጋፍ እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ ለመተባበር እና ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑትን ከቤተሰቦቻቸው አባላት አንዱን በማገት ወይም በማስገደድ ተፈጻሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
- ኦነግ ሸኔ በተደጋጋሚ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የአፈና፣ ጅምላ ግድያ፣ ዝርፊያ እና የበርካታ ንጹሃንን ቤት እና ንብረት የማውደም ተግባራትን እየፈጸመ ከመሆኑ ባሻገር የታገቱ ግለሰቦችን ለመልቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል። እንዲሁም በዞን እና በወረዳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚላቸው ግለሰቦች ላይም የአፈና እና የግድያ እርምጃዎችን ያለ ርህራሄ ይወስዳል፡፡
- የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም የዕለት ተግባሩ ሲሆን ዘግናኝ የሆኑ የሽብር ጥቃቶችን በአካባቢው በሚኖረው ማኅበረሰብ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ አድርሷል።
- እስር ቤት በመስበር በደረቅ ወንጀል የታሰሩ እስረኞችን አስመልጧል፤
- የመንግሥት ኃላፊዎችን ከቤት በማውጣት በቤተሰቦቻቸው ፊት ረሽኗል፤
- የበርካታ ንጹሃንን ቤትና ንብረት አውድሟል፤
- በኦነግ ሸኔ ወታደሮች ሴቶች ተደፍረዋል፡፡ ሕጻናት ተገድለዋል፤
- በምዕራብ ሸዋ ዞን የጮቢ ወረዳ ከ146 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ጥንታዊውን የጮቢ ደብረ መድኃኒዓለም ገዳምን አውድሟል፤
- በየጊዜው ከሚፈጽመው ዝርፊያ በተጨማሪ በአንድ ጊዜ ብቻ ከ10 በላይ ባንኮች ዘርፏል፤
- ከመንግሥት ግምጃ ቤት ጦር መሳሪያ ዘርፏል፤
- የኢንቨስተሮችን፣ የመንግሥት ተቋማት ንብረቶችንና መኪናዎችን፤ የሰብዓዊ ድርጅት ተቋማት ፒካፕና አምቡላንሶችን ያለከልካይ ለመውረስም ችሏል፤
- በተለይ የንጹሀን ዜጎችን ንብረትና መኪናዎችን እየወረሰ ይገኛል፡፡
የመፍትሔ ሀሳቦች፡-
- የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በርካታ ወረዳዎችና ቀበሌዎችን በመቆጣጠር መጠነ ሰፊ የሽብር እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ መንግሥት ይህን የኦነግ ሸኔን እንቅስቃሴ በሚመጥን መልኩ የተቀናጀ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝብን ደኅንነት የማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን በአፋጣኝ መወጣት ይኖርበታል።
- ኦነግ ሸኔ ከሕወሓት ጋር በመቀናጀት አገር የማፍረስ ተግባር ላይ በመሰማራትና የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ከሕወሓት ጋር በአንደኛ ደረጃ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። መንግሥትም ይህንን በአንደኛ ደረጃ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሆነውን የሽብር ቡድን የሚመጥን እና ጨርሶውንም ስጋት እንዳይሆን የሚያደርገውን ሁለንተናዊና የተቀናጀ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል። ኦነግ ሸኔ የሚንቀሳቀስባቸውና አደጋ የተጋረጠባቸው አካባቢዎችን ራሳቸውን መከላከል በሚችሉበት ሁኔታ ማደራጀት እና በጥብቅ ወታደራዊ ክትትል ስር እንዲገቡ በማድረግ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የመጠበቅ ኃላፊነትን መንግሥት በአግባቡ እንዲወጣ እናሳስባለን።
- በሱማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ፤
ባለፉት ወራቶች በሶማሌ ክልል ውስጥ የተከሰተው ድርቅ በክልሉ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ቢነገርም በሕዝብም በመንግሥትም ትኩረት አግኝቷል ማለት አያስደፍርም፡፡ ድርቁ ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያም የእንስሳት መኖ እጥረት በመፈጠሩ በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በርካታ አርብቶ አደሮችም የምግብ እጥረት ስላጋጠማቸው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የውኃ፣ የጤናና የትምህርት አቅርቦት ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል፡፡ የተከሰተው ድርቅ በሱማሌ ክልል ከአንድ ዞን ውጭ 10ሩም ዞኖች እና ከ78 በላይ ወረዳዎችን በማዳረሱ በሚሊዮን የሚቆጠር የክልሉ ሕዝብ የድርቁ ሰለባ ሆኗል፡፡
የሶማሌ ክልል ወሳኝ የኢኮኖሚ መሠረት ተደርጎ የሚወሰደው የእንስሳት ሀብት በመሆኑ ድርቁ በክልሉ አርብቶ አደር የእንስሳት ሞት ተወስኖ ሊቆም ባለመቻሉ የክልሉን ኢኮኖሚ እያሽመደመደው ይገኛል፡፡ በርካታ እንስሳት በመሞታቸውም ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ የጤና ቀውስ ይፈጠራል የሚል ሥጋት ደቅኗል፡፡ በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ጉዳቱ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፤ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ለጋሾች አጣዳፊ ዕገዛ እንዲያደርጉ እየጠየቅን ኢዜማ በሱማሌ ክልል እና ቦረና አካባቢዎች የተፈጠረውን ድርቅ ተረባርቦ ለመመከት በሚደረገው ጥረት ከክልሎቹ እና ከፌዴራል መንግሥት የሚቀርብለትን የትብብር ጥሪ ተቀብሎ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፡፡
- የአፋር ክልል የተወሰኑ ቦታዎች አሁንም በሕወሓት ወራሪ ኃይል ቁጥጥር ስር ስለመሆናቸው፤
የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር በተግባር ያሳየ ጠንካራ ሕዝብ ነው። በሀገር ሕልውና ላይ የመጣን ጠላት በሙሉ አቅም እንደሚታገል፣ ለሀገር ነጻነት ውድ ሕይወቱን እንደሚሰጥ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ያረጋገጠ ፣ በጦር ሜዳ ውሎ ደማቅ አሻራ ያኖረ ሕዝብ መሆኑ አሁንም እያደረገ ያለው ተጋድሎ ብቻ እማኝ ምስክር መሆን ይችላል፡፡
የሕግ ማስከበር ዘመቻው በተሳካ ኦፕሬሽን መከላከያ ሠራዊት በሦስት ሳምንት ጊዜ መቀሌን በመቆጣጠሩ፣ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ለሰባት ወራት የማስተዳደር ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደር ጠያቂነት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም አድርጌያለሁ በማለት ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የአፋር ሕዝብ ልክ እንደ አማራ ሕዝብ በሕወሓት ወራሪ ኃይል ከፍተኛው የችግር ገፈት ቀማሽ ለመሆን ተገድዷል፡፡
መንግሥት በየጊዜው ግብታዊ የሆኑ ውሳኔዎችን እንደ ልማዱ በመወሰን የሕወሓት ጦር ሙሉ ለሙሉ ከአፋር እና ከአማራ ክልል ባልወጣበት ሁኔታ የህልውና ዘመቻውን አንደኛውን ምዕራፍ አጠናቅቄያለሁ ብሎ ይፋ ቢያደርግም ሕወሓት በአፋር ማኅበረሰብ ላይ ጥቃት በመክፈት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፤ ይህን ድርጊት መንግሥትም የአፋርን ሕዝብ ጩኽት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍን መርጧል፡፡
መንግሥት ግልጽ የሆኑ መረጃዎችን ካለመስጠቱም በተጨማሪ በአፋር እና በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በአግባቡ መመከት አቅቶት ጦርነቱ የአማራ እና የትግራይ፤ የአፋርና የትግራይ ግጭት ለማስመሰል የሚያደርገው አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ልናስገነዝብ እንፈልጋለን፡፡
የሕወሓት ጦር ከአፋር ክልል ሙሉ ለመሉ ጠቅልሎ እስኪወጣ ድረስ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ስራው የሆነው መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡ በተጨማሪም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ትኩረት ሰጥቶ ከአፋር ሕዝብና ከክልሉ መንግሥት ጎን እንዲቆም መንግሥትም ከዳተኝነቱ በመላቀቅ ከሚዲያ ፕሮፖጋንዳ በዘለለ የአፋርና የአማራን ክልል ቦታዎች ከሕወሓት ወራሪ ኃይል የማስለቀቅ ሥራ እንዲሰራ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
- የደቡብ ክልል ግጭት መነሻዎች በመንግሥትዊ መዋቅር የታገዙ መሆናቸው።
በሀገራችን የሰሜኑ ጦርነትን እንደከለላ እየተጠቀሙ በምዕራብ፣ በምስራቅ፣ በመሀል እና በደቡብ የታጠቁ ሸማቂ ኃይሎች የኢትዮጵያዊያንን ኑሮ የመከራ ቋፍ ላይ አድርሰውታል። ዜጎች በአስተሳሰባቸው፣ በሃይማኖታቸውና በማንነታቸው ምክንያት ባላሰቡት ሸማቂ ኃይል ውድ ሕይወታቸውን እያጡ፣ አካላቸው እየጎደለ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። ‹‹ከለውጡ›› በኋላ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የመብት ረገጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እየመጣ ይገኛል፡፡
- በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ መንግሥት በአማሮ ልዩ ወረዳ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ባለመቻሉ በአካባቢው የሸመቁ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በየጊዜው ዜጎችን መግደል፣ መዝረፍ እና ማሰቃየቱን የዕለት ተዕለት ተግባር አድርገውታል፡፡ ከጥር 25 እስከ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም የ11 ንጹሃን ዜጎችን ህይወት ሲቀጠፍ፤ ጥቂት የማይባሉ ቆስለዋል፤ በርካቶችም ተዘርፈዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤
- በአማሮ ኬሌ የኮሬ ሕዝብ ላይ የተቃጣው የሽብር ተልዕኮ ከ300 የማያንሱ ዜጎችን ህይወት አሳጥቷል። የሟቾችን አስከሬን ተቀብሎ ለመቅበር እንኳን ታጣቂው ኃይል ከአቅም በላይ የሆነ ክፍያ እየተጠየቀ ይገኛል፡፡
- በጊዴኦ ዞን ከዲላ ከተማ ተነስቶ ወደ አማሮ የሚሄደው መንገድ ከተዘጋ አራት አመታት ያለፉት ሲሆን የሕግ የበላይነትን በማስከበር መንገዱን ማስከፈት አልተቻለም።
- በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳና በቤና ፀማይ ወረዳዎች አዋሳኝ በበነታ ሚሮና በጫሊት ቀበሌ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ በተነሳ አለመግባባት ከ10 ያላነሱ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የክልሉ መንግሥት ግጭቱን ለመቆጣጠር ባሳየው ዳተኝነት ግጭቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ አድርጎታል፡፡
ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች መንግሥት የወሰደው ልል የሕግ ማስከበር ሂደት ቀጠናውን የስጋት ውጥረት እንዲያጠላበት አድርጎታል። በድጋሚ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት በመሥራት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ እንዳለበት እናሳስባለን።
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሀገራችን ውስጥ ከተከሰቱት ችግሮች መሀከል የተወሰኑትን ብቻ ሲሆን የክልሎቹ መንግሥታት ተቀራርቦ ለመሥራት እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ካላቸው ኢዜማ የሰበሰባቸውን መረጃዎች አቅርቦ ፊት ለፊት ለመወያየት እና በጋራ አገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለመሥራትም ዝግጁ መሆኑን ያሳውቃል፡፡
መንግሥት አሁን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሙሉ አቅሙን በመጠቀም፣ የሕዝብ ደኅንነት ሊያስጠበቅ፣ የራሱን መዋቅርም ከላይ እስከ ታችኛው በጥልቀት ሊፈትሽ ይገባል፡፡ የዜጎችን የሰቆቃ ድምጽና ዋይታ ችላ በማለት የሥልጣን መንበሩን ለማስጠበቅ ብቻ የሚተጋ ከሆነና ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ከተሳነው ኢዜማ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሕጋዊ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር የሕዝቡ ወጥቶ መግባት፣ የሁሉም ዜጋ በየትኛውም ስፍራ የመንቀሳቀስ መብቱ እንዲከበር ከፍተኛ ትግል የሚያደርግ መሆኑን ያሳውቃል፡፡
የካቲት 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)