February 24, 2022
2 mins read

አይ ስኳር!- በላይነህ አባተ

sugarrr

እንደ በለስ ፍሬ አዳም እንደጋጠው፣
ተልሰህ ተቅመህ ስንቱን አስከዳሃው!

አይ ስኳር!

ተበለሱ ኃጥያት ሔዋንን ያወጣው፣
ታንተ ሊያድን ደሞ መቼ ይሆን መምጫው?

አይ ስኳር!

አንተ እንደምትሟሟው ሙቅ ውሀ ሲያስገቡህ፣
የላሰህን ሁሉ እንደ እምቧይ አፈረጥክ!

አይ ስኳር!

ሲልሱህ ሲቅሙህ ምላስ እየጣፈጥክ፣
በጉረሮ ወርደህ ክርስንም ተሻግረህ፣
ተአንጀት በደም ሥር ውስጥ ወደ ልብ ተጉዘህ፣
ስንቱን ልብ አፍርሰህ ስንት እግር አስቆረጥክ?

አይ ስኳር!

ስንቱ ምላሰኛ አንተን የቀመሰ፣
እሬብ እያሰፋ ተአይምሮው አነሰ!

ስንቱ ስኳር ቃሚ የዘነጋ ሞትን፣
ገላን እያፋፋ አቃጠላት ነፍሱን!

ስንት ስኳር ፈላጊ ተጉንዳን ያነሰ፣
በሕዝብ ተረማምዶ ወንበር ቁጢጥ አለ!

አይ ስኳር!

እንደ ጨው እንደ አንኳር ላም እንዳስጎመጀው፣
ስንቱን ምሁርን ነኝ ባይ እም…ቡዋ አሰኘኸው፡፡

አይ ስኳር!

የበቃው ባህታይ ማር ይስሐቅ እንዳለው፣
አንተን ቅሞ ቅሞ ዓለምን አፍቃሪው፣
ስንቱ ጳጳስ አቡን ቆቡን ወረወረው!

አይ ስኳር!

አንተን በሚቅመው በከርሳም ምክንያት፣
ስንት ሕዝብ አለቅ በሰላሳ ዓመት ውስጥ?

አንተን እየላሰ እየቃመ ሊኖር፣
ስንቱ ገረድ ሎሌ የገዥ እግር ያጥባል?

አይ ስኳር!

ታጋዩ ጎመራ ነፃ ወጣ ሲባል፣
አንተን ይልስና ባርያ ሆኖ ያድራል፡፡

ብረት መዝጊያ አገኘን ብሎ ሲያስብ አእላፍ፣
ነድፈህና አሳስተህ ጥጥ አርገኸው እርፍ!

አይ ስኳር!

ሕዝብን አስጨርግዶ አድር ባይ ሲቅምህ፣
ምነዋ በቁጪት መርዝ መሆን አቃተህ?

አይ ስኳር!

ተበለሱ ፍሬም ብሰህ በማማለል፣
ለሰይጣን ሰጠኸው ስንቱን ነጥቀህ ተእግዜር!

አይ ስኳር!

በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
የካቲት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop