የሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ለዘመናት ሲነሳ ቆይቶ አሁን በደረስንበት ደረጃ ዝግጅት መጀመሩ ኢዜማ እንደ ትልቅ ቁምነገር የሚያየው ጉዳይ ነው፡፡ ኢዜማ ሀገራዊ ምክክርን እንደመፍትሄ ሲቀበል ወቅታዊና አንገብጋቢ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር ያሉብንን ውስብስብ መዋቅራዊ ማነቆዎች ለማሻሻል ዕድል እንደሚሰጠን በማመን ነው፡፡ለመፍታት ዘመን የተሻገሩ እርስ በእርስ እያጋጩን ያሉ አሁን ላለንበት ሁኔታ የዳረጉንን ቅራኔዎች በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትተን ሁላችን የምንመኛትን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መስማማት ወይም መተማመን ላይ እንድንደርስ ከረዳን ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም ይችላል ብለን እናምናለን፡፡
ይህን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት የሀገራዊ ምክክርን አስፈላጊነት አምኖ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የጥንሰሳ ምዕራፉን አስጀምሯል፤ በሂደቱም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁን አና አስራ አንድ ኮሚሸነሮችን በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስፀደቁን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የታዩ ግድፈቶች እርምት ተወስዶባቸው በሚቀጥሉት ሥራዎች እና ምዕራፎች ላይ የማይሻሻሉ ከሆነ ምክክሩ እንዲያሳካልን የምንፈልገውን ዘላቂ ሰላሟ የተጠበቀ ሉዓላዊነቷ እና አንድነቷ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ማየት ቀላል እንደማይሆን ስጋት አለን፡፡
አዋጁን ከማስፀደቅ ጀምሮ እስከ ኮሚሽን የማቋቋም ሂደት ውስጥ ካየነው ጥድፊያ እና ውክቢያ በተጨማሪ በተለያዩ ወገኖች የግልፅነት ችግር እየተነሳበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፤ እኛም እንደ ኢዜማ ከፍተኛ የሆነ የግልፅነት ችግር አስተውለናል፡፡ አዋጁ ላይ በቂ ውይይት ሳይደረግ የፀደቀበት ችኮላና የሚነሱት የግልፅነት ችግሮች እንዳሉ ሆነው ኮሚሽነሮች ጥቆማ ላይ የታዩ ያልጠሩ አሰራሮች፣ ጠቋሚዎችን ግራ ያገቡ ሕጎች፣ አንድ ጊዜ ያሻችሁን ያህል ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሰው ብቻ ነው መጠቆም የምትችሉት የሚሉ ወጥ የሆኑ መመሪያዎች አለመኖር፣ ኮሚሽነሮች ከተጠቆሙም በኋላ ሂደቱን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ በበቂ ሁኔታ አለመሰጠት፣ ምን ያህል ሰዎችና እነማን ተጠቆሙ? ምን ያህል ሰዎችስ በጥቆማው ተሳተፉ? የሚለውን ጨምሮ የተጠቆሙት ሰዎች ልየታ በምን መንገድ እንደተሠራ ግልፅ አለማድረግ የታዩ ጉልህ ችግሮች ናቸው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ከሚፈልጋቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ግልፅነት ሲሆን ይህ ደግሞ በዋነኝነት ሂደትን የሚመለከት ነው፡፡ ከውጤቱ እኩል ልንጨነቅበት የሚገባው የሂደቱን ግልፀኝነት መሆኑን ልናጤነው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ግልፅነትን ያላካተተ ሂደት የሚያመጣው ውጤት ምን መልካም ቢሆን ሂደቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ተአማኔነት እና ቅቡልነቱ ላይ ያላቸው ተፅእኖ ቀላል አይሆንም፡፡
በጥንሰሳው ምዕራፍ የመንግሥት ባለስልጣናት አጃቸውን በማስረዘም በተለያዩ ንግግሮች ላይ ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክተው የሰጧቸው የተዛቡ አስተያየቶች፣ ሚዲያዎቻችን ለጉዳዩ የሰጡት አናሳ ትኩረትና ቸልተኝነት መንግስት ሂደቱን ለጥድፊያና ለውክቢያ የዳገረበት መንገድ፣ ሕግ አውጪው አካል ሂደቱን በተመለከተ ያሳየው ግልፅ ያልሆነ አካሄድ በዚህኛው ምዕራፍ ሂደት ላይ የታዩ ግድፈቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መሰል ክስተቶች በመጨረሻ ለምናስበው ውጤታማ ምክክር የሚያሳድሩት ጫና ቀላል አይሆንም ሀገራዊ ምክክሩም ላይ የሚያጠሉት ጥላ ከባድ ነው፡፡
እንደ ኢዜማ ሀገራዊ ምክክሩ ያሉብንን ሁሉንም ዓይነት ችግሮች ፈትቶ ለሁሉም ሀገራዊ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች እልባት ይሰጣል ማለት እንዳልሆነ እንረዳለን፤ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ከዚህ ከጥንሰሳው ምዕራፍ በላይ ወሳኙ ምዕራፍ የዝግጅት ምዕራፍ ሲሆን ዋነኛው ኃላፊነትም የሚኖረው በዚህ ሂደት የተመረጡት ኮሚሽነሮች ላይ ይሆናል፡፡ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡት ኮሚሽነሮች የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ታማኝነታቸውን ለሕዝብና ለህሊናቸው ብቻ በማድረግ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከየትኛውም አካል የሚመጣባቸውን ጫና በመቋቋም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡና በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ማፅናት ሂደት ውስጥ ታሪካቸውን በጉልህ እንደሚፅፉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገራዊ ምክከሩን በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነት ወስደው ግልፅነት በተሞላበት መንገድ ቀሪዎቹን ምዕራፎች በንፅህናና በታማኝነት እንደሚሰሩም ተስፋ በማድረግ ኢዜማ መልካም የሥራ ጊዜ ይመኝላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
የካቲት 16/2014 ዓ.ም