February 22, 2022
13 mins read

የአሜሪካ ኤምባሲ በመቀሌ በከፈተው ጊዜያዊ ቢሮ የኮንሱላር አገልገሎት መስጠት ጀመረ

US EMBASSY Addis 768x391 1

US EMBASSY Addis 768x391 1ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በትግራይ ክልል መቀሌ በከፈተው አዲስ ጊዜያዊ የመስክ ቢሮ የኮንሱላር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ዋዜማ ስምታለች።

ኤምባሲው አዲስ አገልገሎት የጀመረውና የመስክ ቢሮም የከፈተው በክልሉ የሚኖሩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና አሜሪካውያንን ከነቤተሰቦቻቸው ለመድረስ ታስቦ መሆኑን የኤምባሲው ምንጮቻችን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ኤምባሲው የመስክ ቢሮውን እንዲከፍት ያስገደደው በትግራይና በማዕከላዊ መንግስት መካከል የትራንስፖርትም ሆነ የመገናኛ አውታር በመቋረጡ ከአዲስ አበባ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ነው።

ባለፈው ዓመት በትግራይ ጦርነቱ ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹን ከክልሉ ለማስወጣት ጥያቄ ቢያቀርብም ከሁለቱም ተፋላሚዎ ይሁንታ ባለማግኘቱ በርካታ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት እንዲቆዩ ተገደዋል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈና የተሰወሩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ግለሰቦች ከመመዝገብ አንስቶ ማንነታቸውን የሚገልፅ ስነድ ለጠፋባቸው ዜጎች ጊዜያዊ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ መኖሪያ ሀገራቸው አሜሪካ እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሞከረ ነው።

በተለይም ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው የጉዞ ሂደት ለማመቻቸት የሚፈልጉ እና አዲስ አበባ ወደሚገኘው ኤምባሲ ቀርቦ ሂደቱን ለማስፈፀም ለተቸገሩ የክልሉ ነዋሪዎችን አገልግሎት ለመስጠት እንደታሰበም ተነግሯል።

አንዳንድ ባለጉዳዮች ጊዜያዊ ሰነድ ካገኙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከነቤተሰቦቻቸው አልያም በተናጠል ከሀገር መውጣት የሚያስችላቸው የተሟላ ሰነድ ያገኛሉ ተብሏል።

እነዚህን ዜጎችና ቤተሰቦቻቸውን በልዩ በረራ ከትግራይ በቀጥታ ወደ ውጪ ሀገር ለመውሰድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ዋዜማ አላገኘችም። [ዋዜማ ራዲዮ]


ለቸኮለ! ሰኞ የካቲት 14/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች
1፤ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው 11 የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። ምክር ቤቱ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር እና ኂሩት ገ/ሥላሴን የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሹሟል። ምክር ቤቱ የሾማቸው ኮሚሽነሮች፣ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ ኂሩት ገ/ሥላሴ፣ አይሮሪት ሞሐመድ (ዶ/ር)፣ ተገኝ ወርቅ ጌቱ (ዶ/ር)፣ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ሞሐመድ ድሪር፣ ዘገየ አሥፋው፣ መላኩ ወ/መርያም፣ ሙሉጌታ አጎ፣ ብሌን ገ/መድኅን እና አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) ናቸው። ለኮሚሽነርነት ከተጠቆሙት 632 ግለሰቦች መካከል 100 የሚሆኑት ሌሎች ተጠቋሚዎች ወደፊት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚደረጉ የአገራዊ ምክክር መድረኮች አወያይ ይሆናሉ ተብሏል።
2. ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት እየሄደበት ያለውን የአገራዊ ምክክር አካሄድ እንዲቃወም ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል። ባልደራስ በመግለጫው፣ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን እና የሐይማኖት ተቋማትን በማግለል የአገራዊ ምክክር ሂደቱን በማናለብኝነት ለብቻው ጠቅልሎ ይዞታል፤ ግልጽ የመምረጫ መስፈርቶችን ሳያስቀምጥ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ሹመት ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አድርጓል በማለትም ከሷል። ገዥው ፓርቲ ወይም መንግሥት የአገራዊ ምክክሩን ተስፋ ገና ከመነሻው ያመከነው መሆኑን ሕዝቡ እንዲረዳ የጠየቀው ባልደራስ፣ መንግሥት በአገራዊ ምክክሩ ላይ የመረጠው አካሄድ ሀገሪቱን ለተጨማሪ ውስብስብ ችግሮች ይዳርጋታል ሲል አስጠንቅቋል።
3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ ማክሰኞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ። ዕቢይ በቀጥታ በቴሌቪዥን ለሕዝብ እንደሚተላለፍ የሚጠበቀውን ምላሽ እና ማብራሪያ የሚሰጡት፣ በዋናነት በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች በተለይም በሰሜኑ ጦርነት፣ እየተባባሰ በሄደው የኑሮ ውድነት፣ በውጭ ግንኙነት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች እንደሆነ ታውቋል።
4፤ መንግሥት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስር ያቋቋመው የሚንስትሮች ግብረ ኃይል ወደ አማራ፣ አፋር እና አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው የምዕራባዊ ትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪ ቡድኖችን በቀጣዩ ሳምንት ሊያሰማራ እንደሆነ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል። ግብረ ኃይሉ ለአዲሱ የመርማሪነት ተልዕኮው 9 መርማሪ ቡድኖችን እንዳቋቋመ እና ቡድኖቹ በሦስቱ ክልሎች በ9 የተመረጡ አካባቢዎች ምርመራ እንደሚያደርጉ የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ታደሠ ካሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል። መንግሥት ከሚንስትሮች የተውጣጣውን ግብረ ኃይል ያቋቋመው ግን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራዩ ጦርነት በተፈጸሙ ወንጀሎች ዙሪያ ባደረጉት ጥምር ምርመራ ባገኟቸው ግኝቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና በጥፋተኞች ላይ ክስ ለመመስረት ሲሆን፣ ለዚህም ንዑስ ኮሚቴዎችን ማቋቋሙ ይታወሳል።
5፤ ምርጫ ቦርድ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑትን ዘላለም ሙላቱን ከምክር ቤቱ አባልነታቸው ለማስነሳት ድጋፍ እንዲያደርግ ከባልደራስ ፓርቲ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን በድረገጹ ባሰራጨው ደብዳቤ አስታውቋል። ቦርዱ በሕዝብ ተመራጭን ከምክር ቤት አባልነት ለማስነሳት ድጋፍ የሚያደርግበት አንዳችም ሕጋዊ አሠራር እንደሌለ የጠቀሰው ቦርዱ፣ የቦርዱ ሥልጣን መራጩ ሕዝብ በተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ ማሟያ ምርጫ ማድረግ ብቻ እንደሆነ አብራርቷል። ባልደራስ ጥያቄውን ያቀረበው፣ ተወካዩ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና አዲስ አበባ ከተማን አስመልክተው በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል የዘለፋ ንግግር አድርገዋል በማለት ነው።
6፤ በግዙፉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ፌስቡክ የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች በኢትዮጵያ ሁከት እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ኦብዘርቨር ጋዜጣ እና የምርመራ ጋዜጠኞች ቢሮ በጋራ ባደረጉት ምርመራ ገልጸዋል። የምርመራ ቡድኑ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያዊያን የመረጃ አጣሪዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፌስቡክ በሀገሪቱ ግጭቶችን በማባባስ እና በማንነት ተኮር ለሆኑ ግድያዎች ሚና እንዳለው እያወቀ ርምጃ አልወሰደም በማለት ወቅሰዋል። ኢትዮጵያዊያን መረጃ አጣሪዎች ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ከፌስቡክ ድጋፍ ጠይቀው ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ፌስቡክ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መረጃ አጣሪ ድርጅቶች ጋር የሥራ ትብብር አልፈጠረም። ሜታ ኩባንያ በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ደኅንነት የሚያረጋግጡ ርምጃዎችን ወስጃለሁ ይላል።
7፤ የኬንያ ፖሊስ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በሕገወጥ መንገድ የገቡ 108 ኢትዮጵያዊያንን ኪያምቡ በተባለ የሀገሪቱ አውራጃ ውስጥ ባለፈው ዓርብ እንደያዘ የሀገሪቱ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ፓሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ኢትዮጵያዊያኑን ያገኛቸው አንድ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪነት በሚጠረጠር ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው ሲሆን፣ ወደ ኬንያ የገቡት በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ሳይሆን እንደማይቀር ፖሊስ ተናግሯል። ኢትዮጵያዊያኑ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 35 እንደሚገመት ተገልጧል። ፓሊስ በዕለቱ 4 ኬንያዊያን ተጠርጣሪ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን ጭምር በቁጥጥር ስር አውሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]

3 Comments

  1. አሜሪካ መቀለ ላይ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፈተች የሚለው ዜና ምንጩ ለምን አልተገለጸም? እንደ ቆንስላ ቢሮነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ አሻጥር ማቀናበሪያ ማእከል እንዳይደረግ ምን ዋስትና አለው? አሜሪካ ትህነግ ን ነው የምደግፈው ማለቷ እየታወቀ! አዋዜ ዜና ብሎ ያቀረበው ከመንደር ወሬ አላለፈም!

  2. አሜሪካ የሽብር ስራዋን ለማጠናከር እና በቅርበት በመደገፍ የተለየ ሴራ ለመስራት ጭራሽ የኮንሱላር ጽ/ቤት ጉዳ ሳይሰማ…. ይባል የሌ ይህ መረጃ እውነት ከሆነ በጣም ገራሚ ነው፡፡ ይህ የሴጣን መልዕክተኛ የሆነ የአሜሪካ አመራር በአገራችን ላይ በጣም እየቀለደ ነው፡፡
    አሁን ደግሞ HR የተባለ በሴነት የተዘጋጀ Bill ለማፀደቅ የሚራራጡ የትህነግ ተላለኪ የኮንግረስ አባለትን መንግስት ለማክሸፍ በምንያህል ፍጥነት እየተሯሯጠ እንደሆነ አይገባንም እነሱ እዚህ ደረጃ ሲያደርሱት፡፡ መንግስት በውስጡ ያሉ ነቀርሳዎችን በደንብ ነቅሶ ስላላሰወገደ ገና ከባድ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ በአሜሪካ ያለው ኤምባሲ አምባሰዳር እና ቆውንሲላ ምን ያህል ስራ እየሰሩ እንደሆነ በደንብ እየተፈተሸ አይደለም፡፡ አምባሳደሩ የትህነግ አባል የነበሩ ስለሆነ ላይ ላዩን እያስመሰሉ የሚሰሩት ሴራ አልታወቀም፡፡ ሊፈተሸ ይገባል፡፡ ይህቺ አገር በባንዳ እየደማች እስከመቼ?????
    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

  3. የአሜሪካ መንግስት የሽብር ስራዋን ለማጠናከር እና በቅርበት በመደገፍ የተለየ ሴራ ለመስራት ጭራሽ የኮንሱላር ጽ/ቤት ጉዳ ሳይሰማ…. ይባል የሌ ይህ መረጃ እውነት ከሆነ በጣም ገራሚ ነው፡፡ ይህ የሴጣን መልዕክተኛ የሆነ የአሜሪካ አመራር በአገራችን ላይ በጣም እየቀለደ ነው፡፡
    አሁን ደግሞ HR የተባለ በሴነት የተዘጋጀ Bill ለማፀደቅ የሚራራጡ የትህነግ ተላለኪ የኮንግረስ አባለትን መንግስት ለማክሸፍ በምንያህል ፍጥነት እየተሯሯጠ እንደሆነ አይገባንም እነሱ እዚህ ደረጃ ሲያደርሱት፡፡ መንግስት በውስጡ ያሉ ነቀርሳዎችን በደንብ ነቅሶ ስላላሰወገደ ገና ከባድ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ በአሜሪካ ያለው ኤምባሲ አምባሰዳር እና ቆውንሲላ ምን ያህል ስራ እየሰሩ እንደሆነ በደንብ እየተፈተሸ አይደለም፡፡ አምባሳደሩ የትህነግ አባል የነበሩ ስለሆነ ላይ ላዩን እያስመሰሉ የሚሰሩት ሴራ አልታወቀም፡፡ ሊፈተሸ ይገባል፡፡ ይህቺ አገር በባንዳ እየደማች እስከመቼ?????
    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

127612
Previous Story

ዶ/ር ሙሉ ነጋ ያወጡት ጉድስለጀነራሎችና ስለመቶ ቢሊየን ብሩ ያልተሰማ ሚስጥር

127607
Next Story

የአቶ ክርስቲያን ታደለ ጥያቄ እና የዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ.. |Christian Tadele | PM Abiy Ahmed

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop