ዶ/ር ሙሉ ነጋ ያወጡት ጉድስለጀነራሎችና ስለመቶ ቢሊየን ብሩ ያልተሰማ ሚስጥር

‹‹ወደፊት በትግራይ እንዲህ ያለ ኃላፊነት የሚቀበል ሰው አለ ብዬ አላምንም›› ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ብሩክ አብዱ 

በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እነሆ አንድ ዓመት ከአራት ወራት ሊደፍን በቀናት የሚቆይ ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ላይ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት ኃይሎች ጥቃት በመሰንዘራቸው የመከላከያ ሠራዊት ራሱን እንዲከላከልና እንዲያጠቃ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ ካሉ በኋላ፣ የመከላከያ ሠራዊት መቀሌ ከተማን ለመያዝ የፈጀበት ሦስት ሳምንታት ብቻ ነበር፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መንግሥትነቱ የተሻረውን የሕወሓት አስተዳደር እንዲተካም ጊዜያዊ አስተዳደር ተዋቅሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከስምንት ወር በኋላ ትግራይን ለቆ እስከሚወጣ ድረስ 16 አባላት ባለው ካቢኔ ክልሉን ሲመራ ቆይቷል፡፡ በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከሚያበቃ ድረስ ለስድስት ወር ጊዜያዊ አስተዳደሩን የመጀመርያው ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)፣ ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ከኃላፊነታቸው ተነስተው የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንዲተኳቸው ተደርጓል፡፡ ሙሉ (ዶ/ር) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካበቃ በኋላ የተነሱ ቢሆንም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል የነበረው ቆይታ ከሁለት ወራት አልዘለለም፡፡ እሳቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳሉ የካቢኔ አባላትን ጨምሮ የወረዳና የዞን አመራሮች ተገድለዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በብቃት ክልሉን ያለ መምራት፣ የሀብት መባከን፣ በሕወሓት ደጋፊዎች ሰርጎ ገብነትና በተለያዩ ጉዳዮች የታማ ሲሆን፣ እነዚህንና የሰሜኑን ጦርነት በተመለከተ ሙሉ (ዶ/ር) ከብሩክ አብዱ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡-  ለመጀመር ያህል የሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ክልል ከመጀመሩ አስቀድሞ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት፣ እንዲሁም በብልፅግናና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የነበረው የቃላት ጦርነትና መካረር የተመለከቱ ሰዎች፣ ይኼ ውጥረት ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ወደ ትግራይ አንድ ጥይት ከምልክ በወቅቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ለነበረው የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ የሚሆን የፊት ጭንብል ብልክ ይሻለኛል ሲል ነበር፡፡ ለመሆኑ እርስዎ እንደ አንድ ታዛቢ በነበረው ሁኔታ ጦርነት ሊኖር ይችላል የሚል ግምት ወይም ሐሳብ ነበረዎት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ታስታውስ ከነበረ ብልፅግና ከመምጣቱ በፊት ረብሻዎችና የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥም ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ በአጋጣሚ እኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርጬ የኢሕአዴግን ውህደት ጥናት ካካሄዱት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ እዚያ ላይ የነበሩ ግኝቶች ኢሕአዴግ አጠቃላይ ችግር ላይ እንደወደቀ ነበር የሚያሳዩት፣ በተለይ በዴሞክራሲ፣ በፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ፣ በፍትሐዊነት፣ በግንባሩ ውስጥ የነበረው አለመተማመን፣ በአንድ ወገን የበላይነት፣ ወዘተ በግንባሩ ውስጥ በግልጽ ይታዩ ስለነበር አገሪቱን ወደ አላስፈላጊ መበታተን እያመራ ነው የሚል ሥጋት ነበር፡፡ ለዚህ መፍትሔ ሆኖ የተቀመጠው በብሔር፣ በተለይ በጎሳ የነበረው አደረጃጀት አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው የሚል ነው፡፡ በተለይ አገራዊ የሆኑ ዕይታዎችና አንድነት ተሸርሽረዋል፣ በብዛት የተሠራው በማንነት ላይ ነው፣ ሁሉም የራሱን ጎራ ለይቶ አንድነትን የሚያመጡ ዕድሎች ተሸርሽረው ቀጭጨው ነበር፡፡ እናም ያ የፈጠረው በየአካባቢው ‹‹ውጣልኝ የእኔ ነው›› የሚል፣ አንድ አገር ሆነን ልክ እንደ ተለያየ አገር መነካካትና ግጭት ነበር፡፡ ስለዚህ በዓለም ታሪክ ያን ያህል ጊዜ ግንባር ሆኖ የቆየ የለምና መዋሀድ አለበት የሚል መፍትሔ መጣ፡፡ እንደ አገር ወጥ የሆነ የፖለቲካ አመራር የሚሰጥ መሆን እንዳለበት፣ ያ ሲሆን ማንኛውም ዜጋ የትም ቦታ ተዘዋውሮ የሚኖርበት፣ የሕግ ከለላና ንብረቱን አፍርቶ ጥበቃ የሚያገኝበት ሥርዓት መዘርጋት ነበረበት፡፡ ከዚህ አኳያ ውህደቱ አስፈላጊ ነበር፡፡

በጥናቱ ላይ ኢሕአዴግ ሙሉ ለሙሉ የተሳተፈበት ቢሆንም፣ በመጨረሻ ሕወሓት አፈገፈገ፡፡ ሕወሓት ውህደቱ ከመጣ አጋር የነበሩ ፓርቲዎች ስለሚገቡ የነበረውን የበላይነት ያጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ርዕዮተ ዓለማዊ ችግር ይፈጠራል፡፡ እነሱ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጪ ሌላ መንገድ አይሆንም የሚል በጣም ድርቅ ያለ አቅጣጫ ይዘው ነበር፡፡ በጥናቱ ይኼም መታየት አለበት ብለናል፡፡ ከአገሪቱና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ኢሕአዴግ በሰዎች ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ ተቋማዊ የሆነና ጠንካራ ተቋማት የሚገነባ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት ካለና ሁሉም ለሕግ ተገዥ ከሆነ ግጭት አይኖርም፡፡ ይኼ ሁሉ ተስፋ የነበረው ለውጥ ነው እንግዲህ የመጣው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በተለይ ከሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ከኢትዮጵያዊነት አኳያ ብዙ ሰዎች የደገፉትን ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው ስለሆነ ደገፋቸው፡፡ ያ ሲሆን ግን የሕወሓት ኃይል ወደ ትግራይ ነው የሄደው፡፡ ሕወሓት አብሮ እንዲቆይና በጋራ እንዲሠራ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም አልተሳካም፡፡ ከዚያ አልፎ እኛ ገና ጥናቱን ሳንጨርስ ብዙ ትንኮሳዎችና አላስፈላጊ ንግግሮች ነበሩ፡፡ ለውህደቱም ያልሆነ ስም መስጠት ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ ሒደቱ እየቀጠለ ሲሄድ ሕወሓት ይዘጋጅ ነበር፡፡ ሥልጠናዎች ነበሩ፣ ጥርጣሬዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሄደው ሄደው መጨረሻ ከአሁኑ ካልተቋጨ የት ይደርሳል የሚል ሥጋት ነበር፡፡ በሰላም ካልተቋጨ አሊያም የፌዴራል መንግሥት አንድ ነገር ካላደረገ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ነበር፡፡ እንደምታስታውሰውም መሀል ላይ ምርጫ ሲራዘም ሕወሓት ግን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ አደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ሕግና ምርጫ ቦርድ አንድ ቢሆንም፣ ሕወሓት ግን የፌዴራል መንግሥቱን ሕገወጥ ነው ብሎ ምርጫ አከናወነ፡፡ ብዙም ተወዳዳሪ ሳይኖር ራሱን ነው የመረጠው፡፡ ከዚያ አልፎ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነት በሕወሓት ዘንድ ትልቅ ጥርጣሬ ፈጥሮ ነበር፡፡ ታሪካዊ የሆነ ቁርሾ ስለነበር ምንድነው ይኼ ነገር የሚል ጥርጣሬ ነበር፡፡ ሊመቱኝ ነው የሚል ሥጋት ነበር፡፡ ይኼንን እንሰማም ነበር፡፡ ይኼ ነገር ወደ አላስፈላጊ ጎዳና እንደሚሄድ ጥርጣሬ ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት እስከ መቼ ነው ዝም የሚለው የሚለውን ነገር እናስብ ነበር፡፡ ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ይመታል የሚል ባይሆንም፣ ከኤርትራ ጋር ነው የሚጋጨው ወይስ ከፌዴራል የሚል ጥርጣሬ ነበር፡፡ ግልጽ ግን አልነበረም፣ ስለዚህ ሥጋት ነበረን፡፡

ሪፖርተር፡- ሕወሓት እንደሚለው ምርጫውን ያደረገው በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የዜጎች የመምረጥና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለሕዝቤ አልነፍግም በሚል አመክንዮ ነው፡፡ ይኼ በሕገ መንግሥቱ የሠፈረ ነው በማለት ምርጫው ሕገወጥ አይደለም ብሎ መከራከሩ እንዴት ይታያል?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ትግራይን ሕወሓት ሲያስተዳድር ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ምርጫ ቦርድ ነው ያላትና ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት ነበረበት፡፡ ፈቃድ አላገኘም፣ ሕገ መንግሥታዊም ያላደረገው ይህ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሕወሓት በነበረው ቁርሾ ምክንያት የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔና የምርጫ ቦርድን ዕርምጃ አልጠብቅም ብሎ በራሱ አካሄደ፡፡ በአጠቃላይ ስታስበው እንደ አገር ልክ ነው፣ ሕዝቡ መምረጥ አለበት፡፡ ሁለተኛው በተግባር ያየነው ደግሞ፣ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ መሆን ነበረበት፡፡ ምን ያህል ፓርቲ ነው የተሳተፈው? ራሱ ተወዳድሮ ራሱን መምረጥ ማለት ምንድነው? ያም አንዱ መለኪያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ እንደ ትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ባይቶና ዓባይ ትግራይ፣ እንዲሁም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ተወዳድረው ነበር ተብሏል እኮ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔ ብዙም ተሳትፎ አደረጉ አልልም፡፡ ለምሳሌ አረና ነበር፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነበር፣ በዚያን ጊዜ ደግሞ ብልፅግና የሚባልም ተጀምሮ ነበር፡፡ ግን ምርጫው ክፍት አልነበረም፡፡ ተሳትፈዋል ብንል እንኳን ዋናው ጉዳይ እንዴት ነው የተካሄደው የሚል ይሆናል፡፡ በአካሄድ ሕገ መንግሥቱ በሰጠው ሥልጣን የምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ ነው የሚገባው፡፡ እርሱ ቢፈቅድለት ትክክል ነበር የሚሆነው፡፡ ይኼ ነው የሌለው እንጂ በመጨረሻ ያው ሕዝብ ነው የሚመርጠውና የፈለገውን መንግሥት የሚያደርገው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሕወሓትን ካለ ሊመርጠው ይችላል፣ ችግር የለውም፡፡ የተፈጠረው ችግር ግን፣ ያኔ ሲራዘም የትግራይን መንግሥት ለይቶ ሳይሆን ለሁሉም ነበር የተራዘመው፡፡ ለምን ቸኮለ? ያ የሚያሳየው በፌዴራልና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው መሳሳብ ውጥረት መፍጠሩን ነው፡፡ እንዲያውም ምንድነው የተባለው? እኛ ነን ሕጋዊ፣ የፌዴራል መንግሥት ከመስከረም ጀምሮ ሕገወጥ ነው ብሎ ነው ያወጀው፡፡ ይኼ ለራሱ ወደ ሰላምና መቻቻል የሚያመጣና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያግዝ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ሕግን ተከትሎ መሄድ ነበረበትና ሕወሓት ለራሱ የመንግሥት አካል ሳለ፣ ያፀደቀው አሠራርና የምርጫ ቦርድ መወሰን ነበረበት፡፡ ያራዘመው ምርጫ ቦርድ ነው፣ ከዚያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ወዘተ ተሳትፈውበታል፡፡ ይኼ ሁሉ የተለያየ አገር ሆኖ ቢሆን ግድ አይልም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ሁሉ ተደማምሮ እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀድመው እንዳስታወቁት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ተሰነዘረ፡፡ እርስዎ የት ነበሩ ያኔ? ዜናውን ሲሰሙስ እንዴት ነበር የተቀበሉት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔ አዲስ አበባ ነበርኩና በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ መከላከያ ማለት ዝም ብሎ ለሚያየው አገር ጠባቂ ብቻ ነው፡፡ ለትግራይ ደግሞ መከላከያ እዚያ የሆነው ከኤርትራ ጋር ከነበረው ቁርሾ በመነሳት ዳር ድንበር የሚጠብቅ ነው፡፡ እና እኔ የሰሜን ዕዝ ተመትቷል ሰባል በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ለምን የሚል ጥያቄም ነበረኝ፡፡ ደግሞ ሁላችንም እንዴት ይሆናል የሚል ጥርጣሬም ነበረን፣ አላመንኩም ነበር፡፡ ግን በተለይ ሴኮ (ሴኩ ቱሬ) ወጥቶ እንዲህ ያለ ኦፕሬሽን አካሂደናል ሲል በትክክል ሕወሓት ጥቃት እንዳደረሰ ራሱ አረጋግጧል፡፡ ይኼንን እኔ ትክክል ነው ብዬ አልወስደውም፡፡ ምክንያቱም መከላከያ ተመታ ማለት የትግራይን ሕዝብ እዚያ የሚጠብቀው ኃይል ከሌለ፣ ከኤርትራ ጋር ከነበረው ችግር አኳያ የሚፈጠረው ክፍተት ግልጽ ነው ማለት ነው፡፡ ከኤርትራ ወገን ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላልና እንደ ክልሉ ተወላጅ ሥጋት ነው የፈጠረብኝና በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የሴኩ ቱሬን ንግግር ካነሱ ላይቀር፣ እሱ በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲናገር የመከላከል ጥቃት ነው የፈጸምነው ብሎ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያት የሚያደርጉት ደግሞ የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለማጥቃት ዝግጅት እያደረገ ነውና ሥጋት ነበረብን የሚል ነው፡፡ ይኼ ለወሰዱት ዕርምጃ ውኃ የሚያነሳ ምክንያት ነው ይላሉ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ሥጋት ነው የነበረው፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነት ሁላችንም እንደምናውቀው ሥጋት ነበር፡፡ ምክንያቱም አብረው ይመቱናል የሚል ከፍተኛ ሥጋት እንደነበር ይታወቃልና፡፡ ሆኖም ባለው ሥጋት እዚያ ያለውን ኃይል መምታት ተገቢ ነው ብዬ አልወስደውም፡፡ መፍትሔው እሱ ስላልነበረ መፍትሔ አላመጣም፡፡ ስለዚህ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንዲያውም የሰሜን ዕዝ ኃይልና መሣሪያ እንዳይንቀሳቀስ፣ ወዘተ ሕወሓትም ሴራ ያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ ምክንያታዊ ነው አይደለም ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ያን ሥጋት ነው ወደ ጥቃት ያመራው፡፡ ሥጋቱ በፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳንቀደም በሚል ነው ያንን ዕርምጃ የወሰዱት፡፡

እኔ ግን ሳየው የነበረው የፌዴራል መንግሥት የአገር ሽማግሌዎችን፣ ነጋዴዎችንና ምሁራንን ወደ ትግራይ ይልክ ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር ባላውቅም፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ መጨረሻው ለሰላም ጥረት ነበራቸው፡፡ የሕወሓት የተወሰነ አካል ወደ ብልፅግና ገብቶ አብሮ እንዲሠራም ጥረት አድርገዋል፡፡ እነዚህን ስታይ ደግሞ የፌዴራል መንግሥትም የራሱ ሥጋት ይኖረዋል፡፡ ያ የቆየና ልምድ ያለው ኃይል ለመንግሥትም ሥጋት የሚፈጥር ነበር፡፡ ምክንያቱም ያሠለጥን ነበርና፡፡ በዚያ ወገን ምላሽ ባይኖርም ከፌዴራል መንግሥት የነበሩ ሙከራዎች ግን ጥሩ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሕወሓት ቢዋሀድና አብሮ ቢታገል ምን ነበር? ድሮ እኮ ሌሎቹ እንደዚህ ነበር የሚያደርጉት፡፡ እንዲህ ከማድረግ ውጪ ወደ ኃይል ማሰቡ ነው ጥፋቱ፡፡ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በውይይትና በሐሳብ ነበር መሆን የነበረበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ስለጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች የሚሰጧቸው ትርጎሞች የተለያዩ ናቸው፡፡ ሕወሓት በትግራይ ላይ የተቃጣን ሕዝብ የማጥፋት ጥቃት ለመመከት ወደ ጦርነት ገባሁ ሲል፣ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ የሥልጣን ሽሚያ ነው ሁለቱን ወገኖች ያጣላቸው የሚሉም አሉ፡፡ በእርስዎ ዕይታ ጦርነቱ የምን ውጤት ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አሁን ዝም ብለህ ስታየው ያን ጊዜ የመከላከያ የሰሜን ዕዝ ሲመታ ወዲያውኑ ለአገር ሥጋት ነው የሚሆነው፡፡ እንደሚባለውም በርካታ የኢትዮጵያ ኃይል በሰሜን ስለነበር፡፡ ዓላማውም ያንን መትተው ወደ መሀል አገር ለመምጣት ነው፡፡ እንዲያውም ወደ ኤርትራ አልነበረም ዕቅዳቸው፣ ኤርትራ ግምት ውስጥ አልነበረችም፡፡ ወደዚህ መጥተው መንግሥት አፍርሰው የራሳቸውን፣ ትክክል የሚሉትን ነገር ለማድረግ ነበር ያሰቡት፡፡ በተለይ የፌዴራል ሥርዓቱ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ወዘተ አደጋ ላይ ወድቋል ይላሉ፡፡ ይኼ እንግዲህ በኢሕአዴግ ጊዜ የነበረ ችግር ነው፡፡ ውህደቱ ደግሞ አሁንም አልተፈጸመም፡፡ እንደ ድሮው ኢሕአዴግ ነው ያለው፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው መዋቅርና አመራር ነው ያለው፣ ከሕወሓት ውጪ፡፡ ሥራ አስፈጻሚ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ወዘተ. ብታይ እንዳለ ቀጥሏል፡፡ የአመራር ለውጥ እንኳን አታይም፡፡ የአሠራር ለውጥ አታይም፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም የአስተሳሰብ ሳይቀር፡፡ ለምሳሌ በጥናታችን ያየናቸው የድሮዎቹ የጥቅም ትስስር፣ በጓደኛና በትውውቅ መሥራት አሁንም አለ፡፡ እነዚህ ነበር መጥፋት የነበረባቸው፡፡ ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነበር፡፡ ይህ አሁንም አልተሻሻለም፡፡ ሦስተኛው ሰላም ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች አሁን ላይ ሆኜ ሳያቸው አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ብልፅግና ስም ነው ይዞ የመጣው፡፡ ጥናታችን አንድ ወጥ የሆነ ሥራ አስፈጻሚ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ አገር አቀፋዊ ዕይታ ያለውና ሁሉም በግለሰብ ደረጃ አባል ሆኖ የሚቀጥልበት፣ ‹‹የዚህ ብሔር››፣ ‹‹የዚያ ብሔር›› የማይባልበት ነበር፡፡ ይኼንን ታሳቢ የተደረገ ሒደት እንዳለ ነው የቀጠለው፡፡ አሁን ቁልፍ ቦታ የያዙ ሰዎችን ብታይም ድሮውኑ ቁልፍ ቦታ የነበሩ ናቸው፡፡ ሆኖም ለሁሉም ነገር ሕወሓትን ብቻ የመውቀስ ልማድ ይታያል፡፡ አሁን ሳየው የሥልጣንም ጉዳይ አለው፣ ሥልጣን ነው፡፡ ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ አሁን ሥልጣን ጨመረ፡፡ ሕወሓትም ሥልጣኔን አጣሁ ነው የሚለው፡፡ ሌላው ደግሞ በተለያዩ መመዘኛዎች ተገፍቼ ነበር ነው፡፡ የሕወሓት ሰዎች ቁልፍ ቦታ ብቻቸውን ይዘው ነበር የሚሉ ትክክለኛ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ብልፅግና የአማራ፣ የኦሮሚያ እየተባለ ተመሳሳይ ሰዎች እየመሩት ነው ያለው፡፡ ይኼን ይኼን ስታይ እንዲህ የሚሉ ሰዎች እውነት አላቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን ዝም ብለህ ከጥቃቱ አኳያ ብቻ ስታየው ሕግ የማስከበር ሥራ ነው፡፡ እኛም የገባነው በዚያ ነው፡፡ ሕግ ተጥሷል፣ መከላከያ ተመትቷል፡፡ ይኼንን የጣሰ ኃይል ሥርዓት መያዝ አለበት፣ መወገድ አለበት በሚል ነው፡፡ ያ ትክክል ነው፡፡ ግን ሒደቱን ስታየው ደግሞ ውስብስብ ሆነ፡፡ ሌሎች ኃይሎች ገቡ፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ኃይል ገባ፡፡ ምን ማለት ነው? የኤርትራ ኃይል ገባ ማለት ትግራይ ውስጥ በሕወሓትና በኤርትራ መንግሥት ውጥረት ምን ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ግልጽ ነበር፡፡ የኤርትራ ኃይል ባይገባ ኖሮ ደግሞ ምን ይፈጠር ነበር? ባያግዝ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሩ ግንኙነት ባይፈጥርና ያ ኃይል ባይገባ ኖሮ፣ አዲስ አበባ ሌላ ችግር ይፈጠር ነበር፡፡ የራሱ የሆነ ጠቀሜታም አለው፡፡ ስለዚህ እነሱ ሲገቡ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጠረው የመጠቃት ስሜት ነው፡፡ ለእነሱ ትልቅ አጀንዳ ነው የሆነው፣ ሲናገሩ ነበር፡፡ ይኸው ከኤርትራ ጋር ሆኖ መንግሥት ሊያጠቃን ነው የሚሉትን ነገር በእነሱ መግባት ምክንያታዊነት አላበሱት፡፡ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ደግሞ ሲቆዩ፣ የፈጸሙዋቸው ትክክል ያልሆኑ ጥቃቶች፣ ንብረት ማውደም፣ ዝርፊያ፣ የሕይወት ማጥፋት እነዚህ ሁሉ በሕዝቡ ላይ አላስፈላጊ የመጠቃትና የመደፈር ስሜት ፈጥረዋል፡፡ ሕወሓት የሚለውን ፕሮፓጋንዳ እንዲቀበልና እንዲጠጋ አድርጎታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  4ኪሎ ዙሪያ በተኩስ ሲናጥ አደረ! | በመካነሰላም እንጅባራና ጎንደር/የመከላከያ እርስበርስ ውጊያ/የአገኜሁ ተሻገር ከሀገር የመኮብለል እቅድ

ሪፖርተር፡- ጦርነቱ በተጀመረ በሦስት ሳምንታት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት መቀሌን ሲቆጣጠር፣ የሕወሓት መንግሥትነት ተሽሮ የተመሠረተው ጊዜያዊ አስተዳደር ነበር ኃላፊነቱን እንዲረከብ የተደረገው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ እርስዎ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የመሩት ነበርና አስተዳደሩ ካስገኘው ጥቅም አንፃር ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ብለው ያምናሉ? በኋላ ከታየው የጦርነቱ መስፋፋትና የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ተቀባይነትን ከማጣት አንፃር ሲመዘን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥቅም አስገኝቷል ማለት ይቻላል? ወይስ የፌዴራል መንግሥት በሠራዊት ብቻ ማስተዳደር ነበረበት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔ እንዳየሁት ሐሳቡ ትክክል ነው፡፡ ሕዝቡ በራሱ በሲቪል እንዲተዳደር መወሰኑ በውሳኔ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ ችግሩ ግን አጠቃላይ ለተግባሩ (Operation) የተሰጠው ግምት አነስተኛ ነበር፡፡ በጣም ከሚገባው በታች (Underestimate) ነው ትኩረት ያገኘው ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት የማንተዋወቅ ሰዎች አምስትና ስድስት ሆነን እዚህ ተሰበሰብን፣ ከዚያ ውስጥ እኔ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆንኩ፡፡ ከዚያ በፊት ግን አንተዋወቅም፡፡ አንዱ አሜሪካ የነበረ፣ ሌላው ከሌላ ሥፍራ ነበር የመጣው፡፡ ሰው በራሱ ሲታይ ለዚያ ትልቅ ጉዳይ ይመጥናል ማለት ከባድ ነው፡፡ እኔ ያንን ኃላፊነት ስቀበል የተሰጡኝ ኃላፊነቶች ግልጽ ስለነበሩ ነው፡፡ አንዱ አገልግሎት ማስጀመር፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ እንዲሁም ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥና የምርጫ ዝግጅት ማድረግ ነበሩ፡፡ እነዚህ መሥራት የምንችላቸው ቀላል ሥራዎች ናቸው፡፡ ከባድ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቋቋም ግምት ውስጥ ያልገቡ ነገሮች ግን ነበሩ፣ የማናውቃቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ኃላፊነቱን ስቀበል የኤርትራን መግባት አላውቅም ነበር፡፡ አዕምሮዬ ውስጥ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ መንገዶች ሲነገር ነበር፡፡

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አዎን፣ ግን እኔ ወሬ ነው እንጂ በትክክል እዚያ ላይ ይሳተፋሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼንን የሚሉት ኦፊሴላዊ ሪፖርት ስላልደረሰዎት ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ልክ ነው፣ ስላልደረሰኝ ነው፡፡ መንግሥትም ለራሱ ልክ አይደለም ሲል ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ግምት ውስጥ አልነበረም እውነቱን ለመናገር፡፡ ሁለተኛው ከውስጣችን የነበረው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ከምዕራብና ከደቡብ ትግራይ ድንበሮች ጋር ያሉ ችግሮችም ግምት ውስጥ አልነበሩም፡፡ የነበረው ምንድነው? ይኼ ጊዜያዊ አስተዳደር ሄዶ ያስተዳድራል የሚል ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ ነው የሚመርጠው፣ ራሱ ነው የሚያደራጀው፡፡ እኛ አንሾምም ነበር፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ የፈለገውን እንዲያደርግ ነፃ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ አጀንዳዎች አልነበሩም፡፡ ትግራይ በሙሉ ነፃ ሳይወጣ ኅዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት ነው ሽረ የገባነው፡፡ ገና ዓድዋ ተይዞ ሌላው መቀሌን ጨምሮ ሙሉውን ትግራይ እነሱ ነበሩ የያዙት፡፡ እዚያ ጥሩ የሕዝብ አቀባበል ነበር፡፡ አልቋል፣ ተደምስሷል ቢባልም ያኔ በየቦታው ገና ጦርነት ነበር፡፡ ሽረን ጨምሮ ብዙውን ክፍል የኤርትራ ወታደሮች ይዘውታል፣ በብዙ ወረዳዎች፡፡ ስለዚህ ያኔ ብዙ ነገር ገና ነበር፡፡ ግን ሕዝቡ ትልቅ ፍላጎት ነበረውና ጥሩ አቀባበል ስላደረገልን በአጭር ጊዜ ነው አደራጅተን ሽረ ጥሩ ሥራ የሠራነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቀሌ ሄድን፣ በተያዘ በሦስተኛው ቀን ገደማ ይመስለኛል፡፡ እናም መቀሌ ስንገባ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ተደምስሰዋል ሲባል ጠፍተዋል ማለት አልነበረም፣ እኔ ባየሁት፡፡ የሞተ፣ የተማረከና የተበተነ ይኖራል፡፡ ስለዚህ በግልጽ ያየነው እኛ የተበተነ ኃይል እንደነበር ነው፡፡ ትጥቁን አስቀምጦ ተበትኖ በየቦታው የነበረ ኃይል እንደነበር ነው፡፡ ያ ጊዜ በሦስት ሳምንት ጠፍቷል የተባለው በየቦታው በጣም ትንንሽ ግጭቶች እንደነበሩና የእኛን እንቅስቃሴም ይገቱ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ስለዚህ እኛ መቀሌ እንደገባን ልክ እንደ ሽረ ሳይሆን ትንሽ ያለ መቀበል ችግር (Resistance) ነበር፡፡ ሕዝቡ ስንጠራው ያለ መውጣትን ጨምሮ፡፡ ከዚያ በቆይታ የአገር ሽማግሌዎች ከእኛ ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረው ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተቀብለውታል፡፡ እንዲያውም ሕዝቡ መንግሥት ነው ብሎ መቀበል ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ልክ እንደ ሽረ መቀሌም ጥሩ ሥራ ሠራን፡፡

በነገራችን ላይ ከሕወሓት በተለይ እኛ ስንሠራ የነበረው፣ በወረዳና በቀበሌ አመራሮችን ሕዝቡ ነው የሚመርጠው፣ እኛ አንሾምም ነበር፡፡ ይኼ ትልቅ ለውጥ ነበር፡፡ ሕወሓት እንዲህ አይሠራም፡፡ ሁለተኛ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፉ ነበር፡፡ ይኼ ለራሱ የትግራይ ሕዝብ ለመጀመርያ ጊዜ የዴሞክራሲ ልምምድ ያደረገበት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መቀሌን ስናደራጅ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ሰው ማግኘት ነው፡፡ የሰው ኃይል ስብስብ የለም፡፡ ሁሉም ትግራይ ማለት የመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ሁሉም የሕወሓት ደጋፊ ነው፡፡ ለዓመታት የተሠራበት ስለሆነ ምንም ታች ወርደህ ሰውን ቀምሰህ አታመጣም፡፡ የምታመጣው ሰው ምን እንደሆነ አታውቀውም፡፡ ከዚህም ከማዕከል የሚሄድ ሰው የለም፡፡ ሁሉም በየሚዲያው ይፎክራል እንጂ ሄዶ እዚያ ለመሥራት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ እዚያ የሄደው ጥቂት የሰው ኃይል፣ እዚያ ከነበረው እየመለመልን፣ እያሠለጠንን ነበር፡፡ የቢሮ ኃላፊ ለማድረግ እስከ አራት ወር ወስዶብናል፡፡ የማደራጀቱ ሥራ እስከ አራት ወር ነው የፈጀብን፡፡ አራት ወር ማለት ቀላል አይደለም፡፡ በአራት ወር የማደራጀት፣ ዕርዳታ የማድረስ፣ አገልግሎትና መሠረተ ልማት የመመለስ፣ ወዘተ. ነበር የሠራነው፡፡ ትልቅ ሥራ ነው፣ ይኼን እስከ ወረዳ ድረስ አሳክተነዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበሩት ሁለት ወራት ደግሞ ከግምገማ በኋላ ንቁ የሆነ ዕቅድ አዘጋጅተን ወደ ሥራ ነው የገባነው፡፡ እኔ በነበርኩበት ጊዜ፣ የነበረው እንቅስቃሴ ቀላል አልነበረም፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ የዘለቁ ብዙ ትርክቶችና አሉባልታዎች አሉ፡፡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነት ውጪ የሆነ ነገርም ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይመራ የነበረው በኮማንድ ፖስት ነበር፡፡ ኮማንድ ፖስቱን የሚመራው መከላከያ ነው፡፡ በመጀመርያዎቹ አራት ወር አካባቢ ጄኔራል አበባው ነበሩ የሚመሩት፡፡ እኔ አባል ነኝ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር የሚወሰነው በኮማንድ ፖስት ነው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩም ዕቅድ አብሮ ነው የሚታቀደው፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደር ቀርበው፣ በኮማንድ ፖስቱ ፀድቀው ያልተፈጸሙ ብዙ ናቸው፡፡ አንዱ ሕዝብን ማንቃትና ማደራጀት ነው፡፡ ከተሞችን ከሽረ ጀምሮ እስከ ማይጨው ድረስ ጨረስን፡፡ ለሕዝብና ለምርኮኛ የሚሆኑ የማሠልጠኛ ጽሑፎች እዚህ ሆነን አዘጋጅተን ጥሩ ሥራ ነው የሠራነው፡፡ ግን አብዛኛው ሕዝብ ገጠር ነው ያለው፡፡ የገጠር ወረዳዎች ለመሄድ ግን ምን ያስፈልጋል? የፀጥታው ሁኔታ መረጋጋት ያስፈልገዋል፡፡ ልክ በሦስተኛ ወይም በአራተኛ ወር ይመስለኛል ጥር አካባቢ የተወሰነው ውሳኔ ምንድነው? እኛ ከከተማ ወጥተን ለመሥራት በወረዳዎች የመከላከያ ቋሚ ኃይል ትንሽም ቢሆን ይደረግ ነው ያልነው፡፡

ከዚያ በወረዳ ደረጃ ኮማንድ ፖስት ይቋቋም ብለን ወሰንን፡፡ ይኼንን የወሰነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ኮማንድ ፖስቱም ተቀብሎታል፡፡ ያ አልተሳካም እኔ እስከምወጣ ድረስ፡፡ ለምን? ሳምንት ቀጠሮ ይሰጣል፣ ኮማንድ ፖስቱ እርስ በርሱ በየሳምንት ይሰበሰባል፡፡ ምክንያታቸው የተበታተነ ውጊያ ስላለ ቋሚ የምናደርገው ኃይል የለንም፣ መከላከያ ለአሰሳ ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት፡፡ የተበታተነ ኃይል ስላለ እሱን ለመምታትና ለመያዝ ዘመቻ ላይ ስለሆንን አንችልም ነው ምክንያቱ፡፡ ግን አንችልምም ሌላ ጉዳይ ነው፣ ቀጣይ ሳምንት እናደርገዋለን፣ አሥር ቀን ስጡን፣ ወዘተ እየተባለ ይኼ ቋሚ ኃይል አልተደረገም፡፡ እኔ እስከ ነበርኩበት ድረስ ለስድስት ወር ድረስ፡፡ ሦስተኛ ወር ጨርሰን ወደ አራተኛ ስንሄድ የቀረበ ምክረ ሐሳብ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ሁሉም ወረዳ አይደለም፡፡ በትግራይ 93 ገደማ ወረዳዎች አሉ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ 35 መርጠን እኛ ጨርሰን አስረክበን ምን እንደሚያስፈልግ አንድ ሻምበልም ይሁን ሻለቃ አድርጉ ነው ያልናቸው፡፡ ጄኔራል አበባው ታደሰ ናቸው የሚሰበስቡት እሺ ተባለ፡፡ ፀድቆ ግን ይኼ አልተፈጸመም፡፡ በ35 ወረዳዎች ብንሠራ ቀላል አልነበረም፡፡ ከዚያ ለማስፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ባለን ይሠራ ነበር ያልነው፣ ሌላውን ምዕራብን፣ ወዘተ ትተነው፡፡ ባለንባቸውን በምንቆጣጠራቸው ዞኖች ውስጥ እናድርግ ነው የተባለው፡፡ ይኼ ካልተፈጸመ ምንድነው የምንሠራው? ሄደን ስናደራጅ ሰውን አደጋ ላይ እንጥላለን፣ ሕወሓት ይገድላል እንደሰማኸው፡፡

ያም ሆኖ እኛ ሰዎችን መድበን ልክ መከላከያ ትንሽ በሚቆይበት ቦታ ሁሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያደራጃል፡፡ ሳምንትና ሁለት ሳምንታት ቆይቶ መከላከያ ሲለቅ እነሱ መጥተው ይገድላሉ፡፡ ከ38 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ የእኛ አመራር የሆኑ፡፡ መቀሌ ዓይተሃል የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ የነበረውን ዮናስ የሚባል ሰው ከተማ ላይ ነው የመቱት፡፡ እምብዛ የሚባለውንም እንዴት እንዳደረጉት ይታወቃል፡፡ የውቅሮ ከንቲባ፣ የግጀት ከንቲባ፣ ወዘተ፡፡ በሽረ የፀጥታ ኃላፊውን ሌሊት ገብተው ነው የገደሉት፡፡ ይኼ ምንድነው? ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቪል ነው፣ የራሱ ፖሊስ የለውም፡፡ የራሱ የፀጥታ ኃይል የለውም፡፡ ያንን ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም፡፡ ፍጠሩልን ነው፡፡ ስለዚህ ከ90 በላይ ወረዳዎች ጠፍተዋል፣ ደምስሰናቸዋል ካልክ የተወሰነ ቋሚ ኃይል አድርግ፡፡ እዚያ ኮማንድ ፖስት አቋቁመህ ካልሠራህ ምንም ዓይነት የሕዝብ ሥራ ማከናወን አይቻልም፡፡ ግን እነሱ በያዙልን ከተማና ወረዳ ግን ሠርተናል፡፡ ብዙዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩን ኦፕሬሽን እንደሚመራ ይወስዱታል፡፡ ሥልጣኑ የተወሰነ ነው፡፡ ለመገምገም ይኼ አንዱ ነጥብ ነው፡፡ ሁለተኛው የነበረው እውነት ምንድነው? የኤርትራና የምዕራብ ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ መጣ፡፡ እነዚህ ኮማንድ ፖስቱ እዚያ ያለውን ኃይል በሙሉ በሥሩ አድርጎ ይቆጣጠር፣ የኤርትራም የሚቆይ ከሆነ ይቆጣጠረው፣ በሕዝብ ላይ አደጋ እንዳይፈጥር፡፡ ያ ስሜት ስለሚፈጥር ሕዝቡ ወደ ሕወሓት ተጠግቶ ችግር እንዳይፈጥር በመከላከያ ሥር ሆኖ ቁጥጥር ይደረግ፡፡ የምዕራብ ትግራይም፣ የደቡብ ትግራይም አንድ ላይ መከላከያ ይቆጣጠረው አልን፡፡ እኛ ባንገባም ሌላው ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታል፣ ሕገ መንግሥቱ እስካልፈረሰ ድረስ፡፡ እኛም ሄደን እዚያ ችግር አንፈጥርም ሕዝቡ ከፈለገ፡፡ እኛ ሥራችን ማደራጀት ነው፡፡ ከፈለገ እንሄዳለን፡፡ ግን ከማንኛውም ገለልተኛ የሆነው መከላከያ ይቆጣጠረው፡፡ ምክንያቱም በአስቸኳይ ጊዜ መሠረት በኮማንድ ፖስት ሥር ነው መሆን ያለበት ብለን ተነጋግረናል፣ ግን አልተሳካም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያነሱትም የምዕራብም ሆነ ሌሎች ከአማራ ክልል ጋር ያለውን የወሰን ችግር እርስዎ ኃላፊነቱን ሲረከቡ ጀምሮ አንስተውት ነበር፡፡ አንደኛው ችግር ሊሆን እንደሚችል እኔ ለራሴ በውጭ ጉዳይ መግለጫ ላይ ጠይቄዎት አምነው ነበር፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ሰዎች፣ የአረና አመራር የሆኑት አቶ አብረሃ ደስታን ጨምሮ ቅሬታ ነበራቸው በዚህ ጉዳይ፡፡ ትግራይ ሙሉ ለሙሉ በነበራት ቅርፅ ካልሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚያስተዳድረውን ታጥቄ እታገላለሁ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ይኼንን ፈተና ብለውት የነበረውን ጉዳይ ለመፍታት ምን አደረጋችሁ? ከአማራ ክልል ጋርስ ውይይት ተደርጎበት ነበር?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ጉዳዩ መጀመርያ የሕግ ጥያቄ ነው የነበረው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተዋቀረው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው የመጣው፡፡ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት በሕጉ ላይ በግልጽ የተቀመጠውን እያዩ ነው እንደዚያ የሚሉት፡፡ እንደዚያ ከሆነ የምዕራብ ትግራይና የደቡብ ትግራይ ጉዳይ ጊዜው አይደለም አሁን፡፡ እውነት ለመናገር እኔ ብዙ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ ከፈለገ ሕዝቡ ይሂድ፡፡ አንድ አገር ነን፣ ስለአንድ አገር እያሰብን፣ ሕወሓትን ለመምታት እያሰብን ይኼንን አጀንዳ ከፈጠርን ለሕወሓት እንዲነሳ፣ አቅም እንዲሆን እያደረግን ነው ማለት ነው፡፡ ደግሞም ሆኗል እኔ ዓይቼዋለሁ፡፡ አንድ መቀስቀሻ የነበረው ይኼው አማራ ክልል ከዓብይና ከኤርትራ ጋር ሆነው ሊያፍኑን ነው የሚል አጀንዳ እኮ ቀርፀዋል፡፡ ያ እንዳይሆን ከእኛ የነበረው መፍትሔ፣ በተሰጠን ሥልጣን መሠረት፣ በፌዴራል መንግሥት ነው ሥልጣን የተሰጠን፣ የትግራይ ሳንሆን የፌዴራል መንግሥት አካል ነን፡፡ ተጠሪነታችንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነውና በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ይጨርስ ጥያቄም ካለ አልን፡፡ አሁን ግን ለሕዝቡ አጀንዳ እንዳይሆን ያንን መከላከያ ይያዘው፡፡ እኛ አስተዳደር አንመድብም፡፡ ሕዝቡ ነውና የሚመርጠው ራሱ ይምረጥ፡፡ ልክ ዓድዋ፣ መቀሌና ሽረ እንዳደረግነው እዚያም አንድ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ የሚፈልገው ራሱ መርጦ ወረዳና መሰል አደረጃጀቶችን ማድረግ ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ ከእነዚያ አካባቢ እንመድብ ብለን ነበር፡፡ እነሱም ከእኛ ጋር ለመሥራት ፍላጎት አሳይተው ከወልቃይት ራሱ መጥተው ነበር፡፡ የደቡብ ትግራይም ችግር ካለ ራሱ ሕዝቡ ይወስን፣ የራያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) የሚባል እኮ ከእኛ ጋር ተሳትፈው ነበር፡፡ ምክንያቱም ጥያቄ ስለነበራቸው፡፡ በዚህ ስምምነት ነው የመጡት፡፡ ሕዝቡ እንዲወስን መሆን አለበት፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ ካለው በሕግ መሠረት መመለስ አለበት፡፡ የግድ እዚህ ሁን መባል የለበትም፡፡ በወጣው ደንብ መሠረት ተፈጻሚ ለማድረግም ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ እና ይኼንን ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይኼንን ተቀብለው ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ አሁን ይኼ አጀንዳው አይደለም ብለው በሥራ አስፈጻሚ ሳይቀር ተነጋግረውበታል፡፡ መንግሥት አቋም ይዟል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ቀድሞ በትግራይ ሥር የነበሩና ከጦርነቱ በኋላ ወደ አማራ ክልል የተጠቃለሉ አካባቢዎችን ወደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለማምጣት ነበር ማለት ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ልክ ነው፡፡ እንደዚያ ነው ያሉት፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ መንግሥት አይደለም፡፡ የሚያደራጅ ነው እንጂ ልክ እንደ አማራ ክልል መንግሥታት ያለ ደረጃ የለንም፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካል የሆንንና ተጠሪነታችንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲያውም ድጋፍ ነው የሚያስፈልገን፡፡ የአማራ ክልል ያ እንዲሳካ፣ ሕወሓት አጀንዳ እንዳያደርገው መደገፍ ነበረበት ነው፡፡ ምክንያቱም የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ካለቀና ሕዝብ ወደ እኛ ከሳብን በኋላ በውይይት፣ በሕግና ሥርዓት ይፈታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 183 ሰዎች መሞታቸውን ተመድ አስታወቀ

ሪፖርተር፡- ከአማራ ክልል ያ እንዲሆን ፍላጎት ነበር?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አልነበረም፣ እኔ ባህር ዳር ድረስ ሄጄ ስብሰባ አድርጌያለሁ፡፡ የእኔ ትልቅ ህልም የነበረው፣ በአጋጣሚ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነበርና የተማርኩት ስለማውቀው፣ የአማራን ሕዝብ ከትግራይ ለይቼ አላየውም፡፡ እንዲያውም ሁለቱ ሕዝብ ከወሰን በላይ ነው፣ ከማንም በላይ ለማልማት አብሮ እንዲንቀሳቀስ መሥራት አለብን ነበር ያልኩት፡፡ በታሪክም፣ በባህልም፣ በብዙ ነገሮች ሁለቱ ሕዝብ ከማንም በላይ የተቀራረበ ነውና አሁን ለዚህ እንቅፋት ስለሌለ እንሥራ ብዬ ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ እዚያም የተወሰነ ሰው ደግፎታል፡፡ ግን በጣም ስሜቶች ነበሩ፡፡ የቆዩ ስሜቶች ነበሩ፡፡ ሕወሓት የፈጠራቸው ችግሮች፣ ኢመደበኛ የሆኑ ቡድኖችም በጣም ይከላከሉ ነበር፡፡ አይሆንም፣ እኛ በኃይል የተወሰደብንን በኃይል እናስመልሳለን የሚል አቅጣጫ ነበር፡፡ ያ ግን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነት መሆን አልነበረበትም፡፡ የእኛ ሥራ የትም ቢሆን ሰው አንመድብም፣ ራሱ ሕዝቡ ይምረጥ፡፡ ማንም ቢመጣ ያንን ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ ይኼንን እናድርግና ለሕወሓት አጀንዳ እንዳይሆን እናስቀር፡፡ አንድም አጀንዳ እንዳይቀር በሚል ተስማማን፡፡ ይኼንን በሦስተኛው ወር ሪፖርትም አቅርቤያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ አጀንዳዎች ካልተፈቱ ቅስቀሳ ነበርና ወጣቱ ሊሄድ ይችላል፡፡ ሕዝባዊ ጦርነት እንዳይሆን ብዬ በሪፖርት አስቀምጬ ተናግሬ ነበር፡፡ እንደ አመራር ስለገባኝ ወትውቻለሁ፣ ቶሎ እናስቀር፣ ሁላችንም ዓላማችን ሕወሓት እሱን ለመንቀል ይኼ የሕዝብ አጀንዳ መሆን የለበትም፡፡ እባካችሁ ካልሆነ ግን ይኼ ነገር አዝማሚያው ወደ ሕዝባዊ የእርስ በርስ ጦርነት ይኼዳል ብዬ በሦስት ወር ሪፖርት ላይ፣ በስድስተኛው ወር ሪፖርትም ላይ አስቀምጫለሁ፡፡ በዚህ መሠረት በአራተኛ ወር ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስብሰባ ስለነበረን ያኔ ምዕራብ ትግራይን መከላከያ እንዲይዘውና ተፈናቃይ እንዲመለስ፣ የኤርትራ ሠራዊት ወደ ድንበር እንዲመለስ ተወሰነ፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ጦርነት መሳተፉን ካመኑ በኋላ ማለት ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አዎን ካመኑ በኋላ ነው፡፡ በአራተኛው ወር መጨረሻ ላይ የሦስት ወር ግምገማ ተብለን መጥተን እዚህ ኮማንድ ፖስት ባለበት በትንሽ ቡድን ተነጋግረናል፡፡ እኔም ሪፖርት አቀረብኩ፡፡ የኤርትራ መቆየት ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ነገር ይስተካከል፡፡ ከሕዝቡም ምልክት ታይቶ ነበር፡፡ ወጣቱ መሄድ ጀመረ፡፡ ስለዚህ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር የሚል ሐሳብ ቀረበ፡፡ የምዕራብ ጉዳይም ጭምር፡፡ እንግዲህ የሥራ ክፍፍል አደረግን ማለት ነው፡፡ የምዕራብ ትግራይን ጉዳይ ከአማራ ክልል ጋር ተነጋግሮ ከትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደግሞ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ሆኖ የሎጂስቲክስ ሥራ አዘጋጅቶ እንዲመልስ፣ የኤርትራ ወታደሮች በሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ ድንበር እንዲወጡ፡፡ ይኼንን ኃላፊነት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ወሰዱ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደግሞ የአገልግሎት በማለት ትምህርት፣ ጤና፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ተገምግሞ በቶሎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተባለ፡፡ በደቡብና በምዕራብ ትግራይ መከላከያ ኃይል አስገብቶ እንዲቆጣጠር ተወሰነ፡፡ እዚያ ያሉ የአማራ ክልል ኃይሎችንም በእሱ ሥር እንዲያደርግ፣ ካልሆነም እንዲያስወጣቸው ተወሰነ፡፡ እንግዲህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አብረን ነው የወሰንነው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በተጨማሪ ሕዝብን የማንቃት ሥራና ብዙ ነገር ይወራ ስለነበር፣ አመራራችንን ፈትሸን እንድናስተካክል ኃላፊነት ወሰድን፡፡ ያንን ተከፋፍለን ሄድን፣ እኔ በካቢኔ አቀረብኩ፣ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ በወቅቱ የሰላም ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ሎጂስቲክስ እንዲያግዙን፣ ከአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ጋር ተነጋገርንና ተዘጋጀን፡፡ በኮሚቴያችን ከየት የተፈናቀሉ ሰዎች መቼ እንደሚመለሱ ሠራን፡፡ የመቶ ቀናት ግምገማ አደረግን፡፡ አመራር ለማስተካከልና ለማየት ፊልድ ሄደን፡፡ ስለዚህ ይኼ በአራተኛው ወር ነው የሆነው፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ሒደቱን ለመገምገም ቀጠሮ ያዝን፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን ጀመረና ጊዜው ሲደርስ የሰዎች ለውጥ አድርጎ ሥራውን ጨረሰ፡፡ መረጃ ስለነበር በግምገማ አስተካከልን፡፡ በወረዳም ጀመርን፡፡ ትምህርትም፣ ጤናም ለመጀመር ተንቀሳቀስን፣ ሌሎቹ ግን ገና ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ከእናንተ ውስጥ ከሕወሓት ጋር ይሠሩ የነበሩ አባላት እንደነበሩ፣ በትክክል ቁርጠኝነት ያልነበራቸው ሰዎች እንደነበሩና መሰል ችግሮች ይነሱ ስለነበር የግምገማችሁን ውጤት በዝርዝር ይንገሩን እስኪ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ነበሩ፣ ልክ ነው፡፡ ለምሳሌ ትክክለኛ መረጃ ሪፖርት እንዳይደረግ የሚሠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከታች ሕዝብ የመረጣቸው ቢሆንም፣ የሕወሓት ሰዎች ሆን ብለው ተደራጅተው የተመረጡባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ እኛ ውስጥም አንዳንዶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰርገው የገቡ ናቸው፡፡ እነዚህን ለይተን ነው ያስተካከልነው፡፡ ሌላው ደግሞ ስርቆት ነው፡፡ ለሕወሓት ማድላት ሳይሆን ወደ ገንዘብ፣ ወደ ጥቅም የሚያደሉ ሰዎች ነበሩና ይኼም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ካቢኔ ውስጥ የምናደርገው ስብሰባ ሾልኮ ይወጣ ነበር፡፡ እነዚህን ለይተን ዕርምጃ ወስደናል፡፡ በጣም ደግሞ ቁርጠኛ የሆኑ ሰዎች በብዛት ነበሩ፡፡ ከሁለቱም ወገን ያልሆኑ ግን ሕዝቡን ለማገዝ ሲሉ የገቡም ነበሩ፡፡ ችግሩ ምንድነው? አብዛኛው መዋቅር ላይ ግን ከዚያ የመለመልናቸው ሰዎች ያው ይታወቃል፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሳይቀር የእነሱ ነው፡፡ ለመቀየር ዓመትም ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይኼ ፈተና ነበር፡፡ እኛ ግን ፖለቲካውን ተውና ለሕዝብ አገልግሉ፣ በቀጣይም ትግራይ ውስጥ የምንፈልገው ሲቪል ሰርቪስ ነፃ እንዲሆን ነው በማለት አሳምነን ብዙ ነገር ቀይረናል፡፡ ያ የፈጠረው ለውጥ ነበር፡፡ ሆኖም የሚሄዱ ነበሩ፡፡ ደርሰው መጡ የሚባሉ ሰዎች ነበሩና እነሱን ለይተን አስለቅቀን ነበር፡፡ ግን ለመቀየር ሰው ስንፈልግ ደግሞ አስቸጋሪ ነው የሆነው፡፡ ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ ሰዎች አንፈልግም ነው ያሉት፡፡ ለማወያየት ሄጄ እኔን ፈትነውኛል፡፡ አጀንዳው ሕዝብን ማገልገል ከሆነ ሕዝቡ መቀሌ፣ አዲግራት፣ ማይጨው፣ ወዘተ. ነው ያለውና ለምንድነው እዚያ ያለውን ሕዝብ የማናግዘው? በቀጣይ ምርጫ እያሰብን ነውና ሕዝቡ የሚፈልገውን ይመርጣል፣ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ደግሞ በሕግ ይፈታል ብንል እንቢ አሉ፡፡ ከኤርትራ ጋር የነበረው ፈተና ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያው የኤርትራን ጉዳይ በተደጋጋሚ ካነሱ ላይቀር ከእናንተ ጋር ስብሰባ ይገቡ ነበር?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አይደለም፣ አይገቡም፣ መቀሌም አልገቡም፡፡ ዕዛቸው ውቅሮ ነበር፡፡ ሁሉም አዛዦችና ጄኔራሎች፣ ኤታ ማዦር ሹሙ ሳይቀር እዚያ ነበሩ፡፡ የእኛም ጄኔራሎች ውቅሮ ነበሩ፡፡ አብረው ነው የሚኖሩት፡፡ ከዚያ እኔ ሄጄ ተዋውቄ ተነጋግረናል፡፡ መቀሌ አልገቡም፣ እንዳይገቡ ነው የተደረገው፡፡ መንግሥትም ጥረት አድርጓል ከተሞች በጦርነት እንዳይጎዱ፡፡ ግን አልተሳካም ብዙ ከተሞች ገብተዋል፡፡ ከእኛ ጋር ስብሰባ አይገቡም፡፡ ከእኛ ጋርም ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ ችግሩም እሱ ነው፡፡ እኛ ልናዛቸው አንችልም፡፡ ኬላ ሠርተው እኔን ላያሳልፉኝ ይችላሉ፣ አዲግራት፣ ዓድዋ ስትሄድ ኬላዎች ሠርተዋል፣ እስከ ውቅሮና እዳጋ ሐሙስ ድረስ፡፡ እኔ የክልሉ አስተዳዳሪ ሆኜ ላያሳልፉኝ ይችላሉ፡፡ ይኼ ችግር ነበር፡፡ ግንኙነቱ ከወታደራዊ አዛዦች ጋር ነው የነበረው፡፡ በተለይ ከኤታ ማዦር ሹምና ከእነ ጄኔራል አበባው ጋር፡፡ በእነሱ በኩል አድርገን ነው እኛ ይኼ ነገር እንዲፈታ የምናደርገው እንጂ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በቀጥታ እዚህ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡ ስለዚህ ያ የራሱ የሆነ በእኛም ላይ ጫና ነበረው፡፡ ለምሳሌ ዕርዳታ ለማድረስ 12 እና 15 ቀናት ያስቆማሉ እነሱ ከልክለው፡፡ አይሄድም፣ አያልፍም ብለው ይከለክላሉ፡፡ በእነሱ ቁጥጥር ባለው ሥፍራ ዕርዳታ ለመስጠት አይፈቅዱም፡፡ ሰፊ ቦታ ይዘዋል፡፡ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ትግራይ፣ የምሥራቅ፣ በኋላም እስከ ደቡብ ድረስ ሰፊ ቦታ ሸፍነው ነበር፡፡ ዕርዳታ እዚያ ለማድረስ የግድ የመከላከያ አጃቢ ያስፈልገናል፡፡ ያ ደግሞ የቅንጅት ችግር ስለነበረው ዕርዳታ እንኳን በአግባቡ ለማድረስ፣ የጤና አቅርቦት ለማስተካከል ተቸግረን ነበር፡፡ የእኛ ሰዎች የጊዜያዊ አስተዳደር ደብዳቤ ይዘው ይመልሷቸዋል፡፡ ከእኛ ጋር በቀጥታ አይሳተፉም፡፡ ግንኙነትም አልነበረንም፡፡ ግን በኮማንድ ፖስቱ አማካይነት ችግራችንን እናቀርባለን፣ እንዲፈታ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ ወታደሮች የእናንተን ሥራ አዳጋች እያደረጉ፣ እናንተም ሪፖርት እያደረጋችሁ፣ የፌዴራል መንግሥቱም እንዲወጡ እየጠየቀ ለምንድነው ማስወጣት ያስቸገረው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እሱማ ግልጽ እኮ ነው፡፡ እነሱ ፍላጎት አላቸው፡፡ ውጊያ ስለነበር ሕወሓት ካልጠፋ አንወጣም ነው፡፡ ምክንያቱም ሕወሓት እንደገና ከተነሳ ለኤርትራም ሥጋት ይሆናል የሚል ነው ዋናው ነገር፡፡ በአራተኛው ወር ተወስኖ አልወጡም፡፡ ነገሮች እንዲያውም እየተባባሱ ነው የመጡት፡፡ ዕርዳታ ማድረስና መሰል ጉዳይ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ የምዕራብ ትግራይ ደግሞ እንኳን ሊስተካከል ቀርቶ ተጨማሪ ተፈናቃይ በተከዜ አድርጎ መጣ፣ ነገሩ ተወሳሰበ፡፡ በአምስተኛ ወር እናድርግ ያልነውንም ስብሰባ አልተሰበሰብንም፡፡ እኔ እዚህ መጥቼ ጥረት አደረግኩ፡፡ እዚህም አልተጠራም፣ ወደ ስድስት ወር ሄደ፡፡ በኮማንድ ፖስቱና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተወሰኑ ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ትግራይ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ጉዳዮች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሮች አይደሉም፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡ የራሱ የሆነ ድክመት ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን የሚችለውን ያህል እንዳይሄድ የፀጥታው ሁኔታ አልተስተካከለልንም፡፡ ሌላው ያልጠቀስኩልህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አንድ የነበረው ቅድመ ሁኔታ በትግራይ ፀጥታና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፣ ሰላም እንዲመጣ፡፡ ፖሊስ አልበረውምና፡፡ ፖሊስ ለማደራጀት መቀሌ እንደሄድን መጀመርያ ያስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ ይኼ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ይዘረፍ ነበር፡፡ መዓት ዘራፊ ነበረና ቶሎ ብለን ፖሊስ እናደራጅ አልን፡፡ በፌዴራል መንግሥት እሺ ተብሎ ገንዘብ ተመድቦ ነበር፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ትልቅ ድጋፍ ነበር፡፡ በኮማንድ ፖስቱ በኩል የነበረው ግን ደካማ ነው፡፡ መልምለን፣ የድሮ ፖሊሶችም እንዲመጡ አድርገን ለማደራጀት ጥረት አደረግን፡፡ ዴምሕት (ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ሕዝቢ ትግራይ/የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ) የሚባሉ በኤርትራ የሕወሓት ተቃዋሚ የነበሩ ኃይሎችንም አሰባስበን ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ጥገናዎች ይካሄዱ ነበር፡፡ የኩዊ የፖሊስ ማሠልጠኛ፣ የፖሊስ ጣቢያና የማረሚያ ቤቶች ጥገናም አከናወንን፡፡ ምክንያቱም ለሕግ ማስከበር ሥራ ፖሊስ ጣቢያ ያስፈልጋል፡፡ ብንለቅማቸው የት ነው የምናደርጋቸው? ይኼንን ሁሉ ሠርተናል፡፡ ነገር ግን ሥልጠና ሲባል፣ መሣሪያ ሲጠየቅ ያ ሁሉ ከትግራይ የተሰበሰበ መሣሪያ የት እንደደረሰ አይታወቅም፣ መሣሪያ የለም ተባለ፡፡ የተሰበሰቡና የሠለጠኑትን እንኳን ለማስታጠቅ መሣሪያ የለም፡፡ መቀሌ ይፈተሽ ቢባልም፣ እኔ እስከምወጣ አልተፈተሸም፡፡ እዚያ ምን እንዳለ አይታወቅም፡፡ ፖሊስ ዱላ ይዞ ያልተፈተሸና የታጠቀ ውስጥ ለውስጥ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መከላከያ መቀሌን እንደተቆጣጠረ ፈታሽ የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ተሠማርቶ አልነበረም እንዴ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አልተፈተሸም፣ እኛ መጀመርያ የነበረን ጥያቄም ይፈተሽ ነው፡፡ መቀሌ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ከተሞች ፍተሻ ይካሄድ ነበር ያልነው፡፡ እኔ እስከምወጣ አልተሳካም፡፡ ለፖሊስ የሚሆን መሣሪያ በጽሑፍና በእኔ ፊርማ ምን እንደሚያስፈልግ በእኛ ፖሊስ ኮሚሽነር ቀርቦ መልስ አላገኘም፡፡ እዚህም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ከዚያ በአራተኛው ወር የኮማንድ ፖስት ለውጥ አድርገናል፡፡ በፊት ጄኔራል አበባው ነበሩ፣ በኋላ ጄኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ሰብሳቢ ሆኑ፡፡ በእሳቸው ጊዜ እንዲያውም የባሰ ነው የሆነው፡፡ እሳቸው መከላከያውን ማዘዝ አልቻሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔራል ዮሐንስ ከትግራይ ስለሆኑ ተቀባይነት አልነበራቸውም እያሉ ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አይደለም፣ ግን ምን እንደሆነ እንጃ፡፡ በቀደመው ቡድናችን ዘመቻውን የሚመሩት እነ ጄኔራል ባጫ ደበሌን ጨምሮ ሁሉም ነበሩበት፡፡ በኋላ ግን ምን እንደሆነ ባይታወቅም ነገሮች የባሰ ነው ያሽቆለቆሉት፡፡ ግጭቱም እየጨመረና በየቦታው አልቀነሰም፡፡

ሪፖርተር፡- ስብሰባ ታደርጉ ስለነበር ጄኔራል ዮሐንስ ለምን አቃታቸው? አይታመኑም ነበር?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የተለያዩ ምልክቶች ነበሩ፡፡ በስብሰባዎቹ ሲጋበዙ የሚጠሩ አመራሮች አይመጡም፣ ተወካይ ይልካሉ፡፡ ይኼንን ስታይ ጄኔራል አበባው የክልሉን ዘመቻ በቀጥታ እየመራ ስንሠራ የነበረን አቅም ትልቅ ነበር፡፡ ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌም ነበሩ፡፡ ሲቀየር ግን እጅግ ተዳከመ፡፡ እጀባ ለማግኘት በራሱ ስንት ችግር ነበር፡፡ በትግራይ የዕርዳታና መሰል ነገሮችን የሚያስተባብር ኮሚቴ አቋቁመን ነበር፡፡ መከላከያ ያለበት፣ በእኔ ምክትል የሚመራ ትልቅ ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡ ግን እሱም አልተሳካም፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለው አቅም እንኳን ለመሥራት ፈታኝ የሆነ የፀጥታ ሁኔታዎች ነበሩ፣ ድጋፉም በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን በፌዴራል የነበረው እንቅስቃሴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ግን ብዙ ድጋፍ ነበር፡፡ ክልሎችም እንዲሁ ገንዘብም እንዲያግዙ የማነሳሳት፣ ወዘተ ሥራዎች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር ፡- በወቅቱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምን ያህል ገንዘብ ነበር ያገኘው? በበጀትም በድጋፍም? ገንዘቡስ የት ደረሰ? ገንዘቡ እንደባከነና በእርስዎ አስተዳደር ጊዜ ዘረፋ እንደነበረ ሁሉ ይነገራልና ገንዘቡን የት ነው ያደረጋችሁት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ውሸት ነው፣ ይኼንን ልንገርህ፡፡ በገንዘቡ ደመወዝ ብቻ ነበር የሚከፈለው፡፡ እስከ ሦስትና አራት ወር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የክልሎች ዕርዳታ እስከ 500 ወይም 600 ሚሊዮን ብር ገደማ የመጣው፡፡ እኔ እስከምወጣ ድረስ እሱ አልተነካም ነበር፡፡ አስረክቤ ነው የወጣሁት፡፡ ያልገባም ገንዘብ ነበር፡፡ ግን ግምቱ ወደ 600 ሚሊዮን ብር ይሆናል፡፡ የመጣልን የየክልሉ ደመወዝ 1.2 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው፡፡ እኛ ከደመወዝ በሚቆረጠው ግብር ነበር፣ ለአንዳንድ ነገር ስናውል የነበረው፡፡ ከክልሉ ትንሽ የተራረፉና ከአካውንት የተገኙ የተወሰኑትን ለመጠቀም ተሞክሯል፣ ግን ትንሽ ነው፡፡ እኛም ደግሞ በመጨረሻ አካባቢ ወደ 100 ሚሊዮን ብር አካባቢ ግብር ለመሰብሰብ ሞክረናል፡፡ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡ እና እንደሚባለው ይኼ 100 ቢሊዮን ብር ምናምን ልክ አይደለም፣ እኔ አላውቅም፡፡ እኔ የማውቀው ወደ እኛ የሚመደቡ በጀቶችን ለደመወዝ ነው የምናውለው፡፡ ለአራት ወር ደመወዝ ይከፈላል፣ ከዚህ ውጭ አልነበረም፡፡ ክልሎች የሰጡን ግን እንኳን ሊባክን፣ ሥራ ላይ እንዲውል ዕቅድ አውጥተን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የፌዴራል መንግሥቱ በስምንት ወር አወጣሁት የሚለው 100 ቢሊዮን ብር ትክክል አይደለም ነው የሚሉት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- ልክ አይደለም፣ በየት በኩል? እኛኮ ሥርዓት አለን፡፡ ምናልባት ይኼ ለዕርዳታና ለእህል መግዣ ከሆነ፣ ያ ደግሞ እኛ ውስጥ አይደለም፡፡ የፌዴራል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትም እኮ ለአስተዳደሩ ሰጠሁ አላለም፡፡ ለወደሙ መሠረተ ልማቶች ጥገናና ለሰብዓዊ ዕርዳታ ነው ወጣ ያለው፡፡

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እሱም ቢሆን 100 ቢሊዮን ብር ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም የክልሉ በጀት 18 ቢሊዮን ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ የሚልከው ደግሞ ስምንት ቢሊዮን ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን ስምንት ቢሊዮን ብር ነው እንግዲህ፣ እሱ ደግሞ ገቢ ስላልነበረን ለደመወዝም አይበቃንም፡፡ ስለዚህ መጨረሻ ላይ ጠይቀን ነበር ሁለት ቢሊዮን ብር አካባቢ ለአንዳንድ የሥራ ማስኬጃ ተብሎ እንዲጨመርልን፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያዝ ገንዘብ ነበረ እርሱ እንዲለቀቅልን የተወሰነ እንቅስቃሴ አድርገን ነበር እንጂ ገንዘብ አልነበረንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከመካነሰላም! "ሞርተር ተማረከ፣537 ወታደር ተደምስሷል"| ደብረ ዘቢጥ፣ ጋይንት፣ እስቴ! "ከነ ፓትሮሉ ወደሙ" | የአማራ ድምጽ ዜና

ሪፖርተር፡- እርስዎን ከጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነት ያስነሳዎት የመጨረሻው ግምገማችሁ ምን ነበረ? አንዱ ጉዳይ ይኼ አልነበረም?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አልነበረም፣ ይኼ አልተነሳም፡፡ ኮማንድ ፖስቱም አልተገመገመም፡፡ ትልቁ ነገር መገምገም ያለበት ኮማንድ ፖስቱ ነው፡፡ እኔም የምገመገም ከሆነ ኮማንድ ፖስቱ ቁጭ ብሎ እንገመገም ነበር፡፡ እኔም ይገምገም ብያለሁ፡፡ ተገምግሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግር ይኼ ነው፣ የኮማንድ ፖስቱ ችግር ይኼ ነው ተብሎ አልተለየም፡፡ ምንድነው የሆነው እኔ ስነሳ ግምገማ አልነበረም፣ ሪፖርት አቀረብኩ፡፡ ከዚያ የተነሳው ጉዳይ ምንድነው? ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ ስድስት ወር ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳደረገ፣ ግን ከዚህ በላይ ደግሞ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለበት ተቀምጦ በምሥጋና፣ እኔም ደስ ብሎኝ አመሥግኜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዲሁ፡፡ ከዚያም አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለሦስት ወር ተመደቡ፡፡ ያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚነሳ፣ ኮማንድ ፖስት እንደማይኖርና እኔም እዚህ ሆኜ እንዳግዝ ነው የተባለው፡፡ በዚህ ነው ያለቀው፡፡ እኔ ግን ለስም እንዲሆን ኮማንድ ፖስቱ ይገምገም ብያለሁ፡፡ ያ ሲባል በሰላም ሚኒስቴር ያልሆነ ቡድን ተሰብስቦ ይገምግም ተባለና ተጠራሁ፡፡ ልክ አይደለም፡፡ ኮማንድ ፖስቱን ያቋቋሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ እኔንም የሾሙኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ እሳቸው ባሉበት ትንሽ ቡድን ዘጠኝ አባላት ብንሆን ነው መገምገም ያለበት፡፡ በእኔ እምነት ያንን ሳንገመግም ስለዘመቻው ይኼንን ሁሉ ነገር መናገር ትክክል አይደለም፡፡ እውነት ከሆነ ያ ተገምግሞ ሚዛኑን በጠበቀ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይኼ ይኼ ድክመት ነበረው፣ መከላከያ እንዲህ ነበር የሚል ነው መሆን ያለበት፡፡ እንዲያውም በኋላ በአማራና በአፋር የደረሰው ውድመት እዚህ መድረስ ነበረበት ወይ? አልነበረበትም፡፡ ችግሩ መፈተሽ አለበት፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ አይደለም፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደነገርኩህ ነው፡፡ ስለዚህ 35 ወረዳ እንኳን ካልተያዘለት ሌላውን ተወው ምንድነው የሚሠራው? ይኼ መገምገም አለበት፡፡ እንዳልኩህ የተወሰኑ ውሳኔዎች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሕወሓት ኃይሉን ያሠለጥንበት የነበረው ቦታ፣ እንዲሁም ወጣቱ ከከተማ እየፈለሰ ሲሄድ ወደ ገጠር እየታወቀ ምንም ዕርምጃ አልተወሰደም ነው የሚሉት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- በነገራችን ላይ እኛ መረጃ ነበረን፡፡ ይኼንን ነገር አቀረብን፡፡ እንደማስታውሰው ብዙ ወጣት መሄድ የጀመረው በየካቲት ወር ውስጥ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሕወሓት የካቲትን ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀምበታል፡፡ ሕዝቡ ግን አይፈልግም ነበር፡፡ ግን አብዛኛው የሄደው የካቲት ወር አካባቢ ላይ ነው፡፡ እኛ እዚህ ሙሉ ካቢኔ ለግምገማ መጥተን ነበር፡፡ ልክ ሲፈልሱ መረጃ ነበረን፡፡ ያሠለጥኑ እንደነበር፣ ለኮማንድ ፖስት አንድ ነገር ይደረግ እያልን እናቀርባለን፡፡ ለመበተን ይሞከር ነበር፣ ዘመቻ ተካሂዶ ማሠልጠኛዎቹ ይበተናሉ፡፡ ግን ያው የእነሱ አካሄድ ምን እንደሆን አይታወቅም፡፡ እኔ ደግሞ በዘመቻው ውስጥ አልገባም፡፡ ግን የት ጋ ችግር እንደተከሰተ መገምገም ነበረበት፡፡ እንዲያውም 90 ወረዳዎች ይቅርና ለምንድነው በ35 ወረዳዎች ቋሚ ኃይል ተደርጎ መሥራት ያልቻልነው?

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የክልሉን አንድ ሦስተኛ እንኳን አልተቆጣጠራችሁም ነበር ማለት እኮ ነው?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- አልተቆጣጠርንም፣ አብዛኛው በኤርትራ ሥር ነው፡፡ የነበርነው ከተማውና ወረዳው ነው፡፡ መከላከያው ደግሞ እንቅስቃሴ ላይ ነበር፡፡ የእኛ 38 ሰዎች የሞቱበት ነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፡፡ የታፈኑም አሉ፡፡ እስከ 50 አካባቢ ናቸው የጠፉብን፡፡ ይህ ሁሉ ተሠርቶ ምሥጋና እንኳን አላገኘም፡፡ ዕውቅና እንኳን አልተሰጠንም በነገራችን ላይ፡፡ ይኼ በጣም ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ እኔ ያየሁት ምንድነው፣ ሕዝቡን ለማሳመን በአስተዳደሩ ላይ ማሳበብ ልክ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከሰኔ በኋላ ሕወሓት እስከ ዛሬ ድረስ ለምን ጥቃት ሊፈጽም ቻለ? ይኼ የአስተዳደር ችግር ነው ብለህ ታስባለህ? አማራ ክልል ከእነ ሙሉ ኃይል ነው ያለው፡፡ ልዩ ኃይልና ፋኖን ጨምሮ፡፡ አፋርም እንዲሁ፡፡ ምንድነው ሚስጥሩ? ችግሩ ምንድነው? በዕውን የአስተዳደር ችግር ነው?

ሪፖርተር፡- የትኛው ወቀሳ ነው ይበልጥ የቆረቆረዎት ግን?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔን ያሳሰበኝ፣ ይኼ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፖለቲካ ሥራ ስላልሠራ የሚለው ነገር ልክ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ሥራ አልተሠራም በሚለው ጉዳይ ግን ይስማማሉ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ልክ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥራ አልተሠራም፡፡ ይኼ ደግሞ ለሰው መንገር፣ መስበክ አይደለም እኮ፡፡ በተግባር ሕዝቡን የሚቆረቁሩና የሚያነሳሱ አጀንዳዎችን ማጥፋት አንዱ የፖለቲካ ሥራ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሕዝቡን ማስተማር ነው፡፡ ሕዝቡን ማስተማር ግን ከተሞች ላይ ሠርተናል፡፡ ገጠር ግን ሄደን እንድንሠራ ምቹ ሁኔታ ይፈጠር፡፡ ትግራይ ውስጥ ከ90 በላይ ወረዳዎች አሉ፣ እነሱ ይቅርና 30 ምናምን ወረዳዎች አሉ ብለን ያልተያዙም አሉ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ አሁን ግን እየተስተካከለ ነው፣ መከላከያም ሲናገር፡፡

ሪፖርተር፡- ከመከላከያም ሲባል የነበረው እኮ ወታደራዊ ዘመቻው ስኬታማ ሆኖ ሳለ፣ የፖለቲካ ሥራ ባለመሠራቱ የሕዝቡን ተቀባይነት ማግኘት አልተቻለም ነው የተባለው፡፡ የፖለቲካ ሥራ አልተሠራም በሚለው ሐሳብ ላይ ልዩነት አለዎት?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- በጉዳዩ ላይ ልዩነት የለም፡፡ የፖለቲካ ሥራ ማለት አንዱ ሕዝቡን ወርደህ ማስተማር ነው፡፡ ሁለተኛው ግን አጀንዳ ነው፡፡ ወደ ታች ወርደህ ስታስተምርም ያንኑ ነው የምታነሳው፡፡ እነሱ ያነሱት ዋናው አጀንዳ ግን መፈታት አልቻለም፡፡ ለምሳሌ በከተማ ያስተማርናቸው ለምንድነው ከእኛ ጋር ሊቀጥሉ ያልቻት? እነዚያ አጀንዳዎች ስላሉ ነው፡፡ እኔ ለራሴ የሥልጠና ሰነድ ይዤ ስሄድ፣ የመጀመርያው ጥያቄ የኤርትራና የወሰን ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም መግባት አትችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለፖለቲካ ሥራችን ይኼ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ እንፍታው ብዬ እኮ አቅርቤያለሁ፡፡ ሕወሓት ይኼንን አጀንዳ አግኝቶ ትጥቅ እየሰጠ ነው ብዬም ተናግሪያለሁ፡፡ አንደኛ የፖለቲካ ሥራ ማለት ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በነበረው የሰው ኃይልና በነበረው ተደራሽነት ሠርቷል፡፡ ሽረ፣ መቀሌ፣ ማይጨው፣ ደቡብና ምሥራቅም እንዲሁ የተወሰነ ሠርተናል እኮ፡፡ ዕድል አግኝተው እስከ ገጠር ሄደውም የሠሩ አሉ፡፡ ያ ግን በቂ አይደለም፡፡ ኮማንድ ፖስት በክልል ቢኖርም፣ በዞን አቋቋምን፡፡ በወረዳ ደግሞ ቀጣይ ዕቅዳችን ነበር፡፡ ሁሉንም ስለማንችል 35 ወረዳዎች ከሽረ እስከ ማይጨው ያሉ መርጠን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ እርስዎ እንደወጡ ወዲያው አብርሃም (ዶ/ር) ተተኩና እሳቸውም ለሁለት ወር ብቻ እንደቆዩ መከላከያ ትግራይን ለቅቆ ወጣ፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ሲገደሉ፣ ታፍነው ሲወሰዱና ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይተው፣ የፌዴራል መንግሥት ግን ትግራይ ክልልን ለቅቆ ሲወጣ የነበረው ወከባ እነዚያን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አብረው የሠሩትን ይዞ መውጣት አልተቻለም ነበር፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ቻለ? ችኮላውንስ ምን ያመጣው ይመስልዎታል?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔ እውነቱን ለመናገር ያንን ስሰማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበርና ተደንቄያለሁ፡፡ እዚህ ድረስ ይደርሳል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ የነበረውን ሁኔታ ስለማውቀው በአጭር ጊዜ እንዲህ ይገለበጣል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ከሆነ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ታች መዋቅር ያለው አልተነገረውም፡፡ መቀሌ ላለው ለራሱ ሚስጥር ነው የሆነው፡፡ የሰማ ብቻ ነው የወጣው፡፡ ሌላው ግን ሳይነገረው፣ እዚያው ቀርቶ አደጋ ላይ የወደቀ እንዳለ ሰምተናል፡፡ የታሰረም፣ የተገደለም አለ፡፡ በተለይ መቀሌ አካባቢ፡፡ ይኼ ልክ አይደለም፡፡ ታስቦበት በዕቅድ መሆን ነበረበት፡፡ መንግሥትን አምነው ነው አብረው የሠሩት፡፡ ይኼ አንድ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ ሁለተኛው ከተወጣ በኋላ ወደ እዚህ የመጣው የጊዜያዊ አስተዳደር አባል ለምን መጣህ ነው የተባለው፡፡ ይኼም ልክ አይደለም፡፡ መንግሥትን አምነው ሲሠሩ የነበሩ 70 የሚሆኑ የአስተዳደሩ አባላት አሁን በችግር ላይ ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ በትግራይ እንዲህ ያለ ኃላፊነት የሚቀበል ሰው አለ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያዊ አስተዳደሩ መጀመርያ ሲገጥመን የነበረው ችግር ነው የገጠመው፡፡ መጀመርያ መከላከያ የጊዜያዊ አስተዳደር ካለበት አንድ ቦታ  በድንገት ይወጣና እነዚያ ገብተው እየገደሏቸው አለቁ፡፡ ለምሳሌ ግጀትና አካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቋቁሞ እየሠራ ነበር፡፡ መከላከያም ነበር፡፡ አምነው ተኝተው ሌሊት ሳይነግሯቸው ወጥተው እነዚያ መጥተው የገደሏቸውና አፍነው የወሰዷቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከዚያ የጀመረ ነው፣ ትክክል አይደለም፡፡ ቅንጅትና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አልነበረም፡፡ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የነበረው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ በውሸት ትርክት እዚያ ውስጥ ያልነበሩ ሰዎች በጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ሠርተዋል፡፡ ለምንድነው? ያ ሁሉ ውድቀት የጊዜያዊ አስተዳደር ነው እንዲባል፡፡ ለመንግሥትም አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ተለይቶ ለመፍትሔ ነውና መሠራት ያለበት፡፡ የነበረውን የትግራይ ሁኔታ በአመራሩ ለራሱ እጅግ አናሳ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ በትግራይ የደረሰው ጉዳት በአማራና በአፋር ባልደረሰም ነበር፡፡ የወደመው ንብረት፣ የተጎዳውና የሞተው ሰው የእኛው ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ እንዳይሆን ግን ከመጀመርያው የቅንጅት ሥራው የተሰጠው ግምት አናሳ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ጦርነቱ በብዙ ሁኔታዎች መልኩን ሲቀያይር ተስተውሏል፡፡ የሕወሓት ኃይሎች እስከ ደብረ ሲና መጥተው ከባድ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ ከዚያም የፌዴራል መንግሥት መልሶ ትግራይ ያደረሳቸው ቢሆንም፣ በአማራና በአፋር ክልሎች አዳዲስ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ለድርድር ተቀምጠው ልዩነታቸውን ይፍቱ የሚል አስተያየት ይደመጣል፡፡ ድርድር ሊፈታው የሚችል ችግር ነው ብለው ያስባሉ? ለድርድርስ ምን ዓይነት እንቅፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- በአገራችን በደርግ ጊዜም ለ17 ዓመታት ጦርነት ነበር፡፡ ከኤርትራም ጋር ግጭት ነበር፡፡ በእኔ ዕይታ አሁን የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው፣ ከምንም በላይ፡፡ አገራችን ዓይታው የማታውቀው የሰው ሕይወት፣ የንብረት መውደም፣ የሕዝቡ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም ጉዳይ፣ ሰው እንደ ሰው ጥበቃ የማያገኝበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ወዘተ ስታይ ለውጡ አምጥቶት ከነበረው ተስፋ አኳያ በተለይ እኔ በጣም ያሳስበኛል፡፡ በአማራም፣ በትግራይም፣ በአፋርም ብዙ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ጉዳይ በድርድር እንዴት ነው የምትፈታው? የእነሱን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው የፍላጎት ጉዳይ ነው፡፡ የሕወሓት ፍላጎት ምንድነው? የፌዴራል መንግሥት ፍላጎት ምንድነው? ጥሩ ነው በመርህ ደረጃ ወደ ሰላምና ድርድር መምጣት ጥሩ ነው፡፡ ግን እንዴት ነው የሚሆነው? አሁን ያሉት ሰዎች የሚናገሯቸው ነገሮች ያሳስቡኛል፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት የሚነገረው ነገር፡፡ ምንድነው ይኼ ነገር በሕግና በማዕቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምንድነው እንደዚያ የምለው? ሕወሓትን ተወውና ሁሉም በራሱ የብሔር አጥር ገንብቶ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ከአንድ ብሔር ወጥቶ ማሰብ መቻል ይጠይቃል፡፡ የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ችግር የእኔ ችግር ነው ብለህ እንደ ዜጋ ማሰብ መቻል አለብህ፡፡ ሊሰማህም ይገባል፡፡ አሁንም በየክልሉ ያለው ከራሱ ብሔር ባለመውጣቱ የሚታሰበውን ሰላም ለማምጣት እንዴት ነው የምታጣጥመው የሚለው ፈታኝ ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ በየትም አገር ጦርነት ተጀምሮ በጦርነት አያልቅም፡፡ ወደ ድርድር ይመጣል፡፡ ግን ምን ለማምጣት ነው? ምን ለማግኘት ነው? መነሻው ምነድነው? የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ መነሻው ያው የሕግ ማስከበር አይደለም? ያንን ያሳካል ወይ? አሁን የሚታየኝ አንዱ ችግር ያለውን ሕግ ማክበር አልተቻለም፡፡ ስብሰባ አያስፈልግም ለዚህ፣ ማስፈጸም ነው፡፡ ድርድር መታሰቡ ጥሩ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከጦርነቱ በፊት መታሰብ ነበረበት፡፡ አሁን ጦርነቱ አልተቋጨም፣ የኤርትራ ጉዳይ አለ፡፡ ሁላችንም ስለሉዓላዊነት እናወራለን፡፡ ምን ማለት ነው? በአግባቡ መቋጨት አለበት፡፡ ምንድነው መርሁ? የኤርትራ ኃይል ትግራይም ሆነ ሌላ ቦታ ካለ እንዴት ነው ስለሉዓላዊነት የሚወራው? ጦርነቱ ደግሞ የእርስ በርስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጦርነት ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሰው ጥፋት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ በትግራይ ክልል ደረሱ በተባሉ በደሎች ሳቢያም በርካቶች ኢትዮጵያዊነትን አንፈልግም እያሉ ነው፡፡ የአማራና የአፋር ክልሎች ጥፋቶችም በትግራይ ላይ ያለውን አመለካከት አጠልሽተውታል፡፡ እንዲያው ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያና የትግራይ ክልል ዕጣ ፈንታ ምን የሚሆን ይመስልዎታል?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እንደ እኔ ጉዳዩ በብስለት ካልተፈታ ከባድ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ትግራይ ብቻ አይደለም ሌላውንም ሊነካ ይችላል፡፡ ይኼንን ችግር የመፍታትና ወደ አንድ የመምጣት ጉዳይ ለመላው ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነው፡፡ አቅልለን ማየት የለብንም፡፡ ለምሳሌ ትግራይ እገነጠላለሁ ብሎ ከተገነጠለ፣ ሊሆን አይችልም በብዙ ምክንያቶች ሊሆን የማይችል ነው፣ ነገር ግን በሩ ይከፈታል፡፡ ብዙ ፍላጎቶች አሉና፡፡ ይኼ ነገር በድርድር፣ በሰላም በእንቅስቃሴና በአጠቃላይ ባለው ነገር የተጎዳውን ኅብረተሰብ ግምት ውስጥ በማስገባት ሊፈታ ይገባል፡፡ ያንን ካልፈታህ ፓርቲዎች ተስማምተው ብቻ አይሠራም፡፡ ፓርቲ ሌላ ነው፡፡ ሕዝብ ሌላ ነው፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ ደም ተቃብቷል፡፡ አሁንም የዚህ አገር ሰላም የሚመጣ ከሆነ በጎረቤት ሕዝቦች መካከል ሰላም መምጣት አለበት፡፡ ካልመጣ አይሆንም፡፡ በተለይ በአማራና በትግራይ፣ በትግራይና በአፋር ያለው ችግር ቁልፍ ነው፡፡ ደግሞ ዓይተነዋል ይህ ችግር ነው እዚህ ድረስ ሰፍቶ ያስቸገረው፡፡ አለበለዚያ በሥልጣንና በመሳሰሉት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች ናቸው እነሱ፡፡ አንድ ፓርቲ ሕዝብን አይወክልም፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ስብስብ ነውና፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ድርድሩ ውጤት እንዲያመራን ኢትዮጵያዊነት ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ሰው አውቆም ሆነ ሳያውቅ በብሔር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከዚህ መውጣት አለበት፡፡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለው ተቃርኖ መፈታት አለበት፡፡ ሌላው በዚህ ለውጥ ቃል የተገቡ ነገሮች መተግበር አለባቸው፣ ተሸርሽረዋል፡፡ እኔ በጥናቱ ላይ ስለነበርኩ ኢሕአዴግን ያስወቀሰው የምታውቀውን ሰው መሰብሰብ፣ በጓደኛ መሳሳብ፣ ወዘተ ነው፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚመራ ድርጅት ወደዚህ ከገባ ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ልትገነጠል ትችላለች ብለው ያምናሉ?

ሙሉ (ዶ/ር)፡- እኔ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ሕዝቡም አያደርገውም፡፡ ለምንድነው? በጣም ከባድ ነው፡፡ አሁን እኮ እያየነው ነው፡፡ እህል እንዳይገባ መንገድ ከተዘጋ በሰላም ካልሆነ ከባድ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብም እንዲህ ያደርጋል ብዬ አላስብም፡፡ ሕወሓት ቢልም ሌሎች ኃይሎች አሉ፡፡ ይኼ ነገር ለሕዝብ አያዋጣም፡፡ የሚያዋጣው አብሮ መኖርና ሥርዓት ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሥርዓት አልፈጠረም ነበር፡፡ ይኼ ካለ አሁንም አይሆንም፣ ምክንያቱም የኢሕአዴግ አሠራር ነው የሚቀጥለው፣ በሕግ ላይ የጋራ መግባባት ፈጥሮ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡

 

https://youtu.be/o8qBFN2x3K0

ዶ/ር ሙሉ ነጋ ያወጡት ጉድስለጀነራሎችና ስለመቶ ቢሊየን ብሩ ያልተሰማ ሚስጥር

 

ሪፖርተር

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share