የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ፣ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ‹‹በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ሳይረጋገጥ እንዳይነሳ›› በሚል ጠንካራ ክርክር ቢያደርጉም፣ አዋጁ በስብሰባው ከተገኙት 312 አባላት መካከል በ63 ተቃውሞና በ21 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንዲነሳ ተወሰነ፡፡
ምክር ቤቱ አዋጁን ያነሳው ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሲሆን፣ ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለ110 ቀናት ቆይቷል፡፡ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያካሂደው የነበረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በመግታት የመከላከያ ሠራዊቱ ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ በአሸባሪነት የተሰየመው ሕወሓት ታጣቂዎች ወደ አጎራባች አማራና አፋር ክልሎች በመግባት በርካታ የሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በማድረሳቸው፣ በአገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነ አደጋን በመደበኛው ሕግ መከላከል የማይቻል መሆኑን በመጥቀስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ማወጁ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የሕወሓት ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ የአማራና የአፋር ክልሎች አብዛኛዎቹ ቦታዎች ነፃ በመውጣታቸውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ፣ ሥጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመጥቀስ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሦስተኛው ወር እንዲነሳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያሳለፈው ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተመራ ከሦስት ሳምንታት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ፣ አሁን የፀጥታ ሁኔታው የተሻሻለ በመሆኑ አዋጁን በዚህ ሁኔታ ማስቀጠል ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ስለሆነ፣ ከየካቲት 8 ቀን ጀምሮ እንዲነሳ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው ጥያቄ ለፓርላማ አባላት አቅርበዋል፡፡
ፓርላማው እንዲያፀድቀው የቀረበውን የውሳኔ ሐሰብ ተከትሎ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ ምንም እንኳ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲታይ አንፃራዊ የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም፣ ‹‹ጁንታው አከርካሪው ተሰበረ እንጂ ገና ግብዓተ መሬቱ አልተፈጸመም፣ አዋጁን ማንሳት ለምን አስፈለገ?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
አክለውም ሕወሓት አሁንም የክልሉን ወጣት እያስገደደ፣ ‹‹በኢትዮጵያ አንድነት ፅኑ እምነት ያለውን ጀግናው የአፋር ሕዝብና አምስት ወረዳዎቹ ላይ ወረራ አካሂዶ በከባድ መሣሪያ እየጨፈጨፈና ንብረት እያወደመ በመሆኑ አሁንም ጦርነት ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡
በሕወሓት ምክንያት በአፋር ክልል ከ300,000 በላይ ወገኖች ተፈናቅለው የሰብዓዊ ቀውስ እያደረሰ እንደሆነ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል በራያና በማይፀብሪ ግንባሮች ለተጨማሪ ወረራ እየተዘጋጀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹የሕወሓት ጀሌና እሱ በአምሳሉ ጠፍጥፎ የሠራው ኦነግ ሸኔ የሚባል የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት፣ በኦሮሚያ ክልል ዘርና ብሔር እየለየ የፈረደበትን መከረኛ አማራ እየጨፈጨፈ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኦነግ ሸኔ በሙገር ሸለቆና በጎሃ ጽዮን ሕዝብ እየገደለና ንብረት እያወደመ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነፃ አወጣሃለሁ የሚለውን የኦሮሞ ሕዝብ ጭምር እየጨፈጨፈ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕዝብ በተመሳሳይ የጉምዝ ሽፍታ ችግር እየፈጠረ ባለበትና እዚህም እዚያም ችግር እያለ አዋጁን ለማንሳት ምን የሚያጣድፍ ነገር አለ? የበለጠ ማጠናከር አይሻልም ወይ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
‹‹በመደበኛ ሕግ ችግሮችን መወሰን የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሎ በመንግሥት ለቀረበው ጉዳይ ለእኔ ይኼ ቢሆን ጥሩ ነበር፣ ነገር ግን አይመስለኝም፤›› ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ በሁለተኛ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ፀረ ሕዝቦች እስኪጠፉ ድረስ አዋጁ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
ወ/ሮ አስቴር በሽር የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ምንም እንኳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ ተቃውሞ ባይኖረኝም፣ መንግሥት አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለውን የዜጎች ሞትና መፈናቀል በማስቆም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይችላል ወይ?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የአብን ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለአዋጁ መውጣት ጉልህ የነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተቀየሩ በመሆናቸው ተብሎ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የቀረበው ጉዳይ፣ አሁን ጉልህ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ሕወሓት ተቆጣጥሮዋቸው ከነበሩ ቦታዎች ማፈግፈጉ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን የሕወሓት የማድረግ አቅም (Military Capability) ሲታይ አሁንም ከ300,000 በላይ ወራሪ ጦር አዘጋጅቶ በአፋር ብዙ ወረዳዎችን መቆጣጠሩን፣ በሰቆጣ ሰዎች ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ መኖራቸውን፣ ሕወሓት አሁንም በዋጃና በማይፀብሪ ግንባሮች ለጦርነት እየተዘጋጀና የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሕወሓት ዕብሪትና ፀብ አጫሪነት አለመቀየሩን በመጥቀስ መንግሥት በመደበኛ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን መከላከል አለመቻሉን፣ ከሳምንት በፊት በአንድ ቀን አዳር ከ140 በላይ ንፁኃን ዜጎች ተጨፍጭፈው ማደራቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የዲፐሎማቲክ ማኅበረሰቡን ለማስደሰትና የተወሰነ የገጽታ መሻሻል ለማምጣት ተብሎ መንግሥት የዜጎቸን ደኅንነት፣ የሀብትና የንብረት ውደመት ዋስትና ባልሰጠበት ሁኔታ አዋጁን ለማንሳት መቸኮል ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ የነበረው ሁኔታ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ‹‹አሁን አዋጁ ይነሳ ሲባል የሚያሳስበኝ ነገር በአማራና በአፋር ክልሎች ወንደሞቻችን የጥይት እራት ከመሆን አልዳኑም፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋና ሸዋ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ይባባሳሉ ወይስ ይሻሻላሉ የሚለውን የህሊና ጥያቄ ራሳችን መጠየቅ አለብን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት የፓርላማ አባል አንጋሳ ኢብራሂም (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ላይ ያለው ሁኔታ ለክልሉ ብቻ ራሱን የቻለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያስፈልገው የገለጹት ተወካዩ፣ ‹‹ ከ395 በላይ የገጠር ከተሞች በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ፣ ሰው እየታፈነ ገንዘብ እየተከፈለ እየተለቀቀ መሆኑን፣ ኦነግ ሸኔ ግብር እየሰበሰበ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በአማራና በአፋር ክልል ዜጎች ጦርነት ውስጥ ባሉበት ወቅትና ኦነግ ሸኔ በርካታ ቦታዎች ተቆጣጥሮ ግብር እየሰበሰበ ባለበት በዚህ ሁኔታ፣ ‹‹እንደ ምክር ቤት አባል እኔ ለህሊናዬ፣ ለሕግና ለሕዝብ ነው ተገዥነቴ፣ በመሆኑም አዋጁ ይነሳ የሚለውን ሐሳብ በፅኑ እቃወማለሁ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዚህ ጊዜ መነሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን፣ በየአመራሩ ውስጥ ከአሸባሪዎች ጋር የጨረቃ ግንኙነት የሚያደርጉ አካላት ባሉበት፣ ተገምግመው ከሥልጣን ባልተነሱበት ወቅት አዋጁ ይነሳ የሚለውን ጉዳይ የምክር ቤት አባላቱ በብስለት ከፓርቲ ወጣ ብለው እንዲያዩትና ለህሊናቸው ለሕዝብ ሲሉ እንዳያፀድቁት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በርካታ የምክር ቤት አባላት ሐሳብ ለመስጠትና ጥያቄ ለማቅረብ እጅ አውጥተው ዕድል ያላገኙ ሲሆን፣ ዕድሉን ካገኙ አባላት ውስጥ ብዙዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አዋጁ ከወጣ ጀምሮ ሪፖርት ለምን እንዳላቀረበ ጠይቀዋል፡፡
ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስተሩ አቶ ተስፋዬ፣ ሁኔታው አሁን ጉልህ በሆነ ደረጃ መቀየሩን በመጥቀስ በጥቅምት ወር አዋጁ በተግባር ላይ ሲውል እንደ አገር የነበረው ሁኔታ አሁን መቀየሩን፣ በዚህ ጊዜም አዋጁን አለማንሳት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሥጋቶችን መንግሥት ዝቅ አድርጎ አያይም ብለዋል፡፡ በቀጣይ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ሥጋቶችንና ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠርና ለመከታተል በወጣው የሕግ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በክልሎች መግባት ሲያስፈልግ፣ በልዩ ትኩረት በመሥራት ከሥረ መሠረቱ ለኢትዮጵያዊያን ሥጋት የሚሆኑ ጉዳች ላይ በሚገባ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ከአዋጁ ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸውን ሥራዎች አጠናቆ በአንድ ወር ውስጥ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ የፍትሕ አካላትም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ የጀመሩትን ሥራ በመደበኛው የፍትሕ አሰጣጥ እንዲያከናውኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
ሪፖርተር