ስለ ብአዴን ማውራት በመቃብር ስፍራ በሌሊት እንደመገኘት የሚቀፈኝ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅት እና ስራው ላለማውራት ለራሴ ቃል ከገባሁ ዓመት አልፎኛል፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ በዚህ የከረፋ ፓርቲ ሰፈር አንድ የተለየ ነገር መገኘቱ ቀልቤን እንደሳበው መደበቅ አልችልም፡፡ይህ ለውጥ መጣ ከተባለ ጊዜ በኋላ (ከዚህ በኋላ ፈጥነን እንሰማችኋለን ሲባል እውነት መስሎኝ የነበረ ሰሞን)ስለ ብአዴን ሰዎች አቅሜ በፈቀደ መጠን (ቀረቤታ ካላቸው አካላት) አንዳንድ ማጣራቶችን አደርግ ነበር፡፡
በውስን ጥረቴ የተረዳሁት ነገር በዚህ ፓርቲ ውስጥ አማራ የሚባል የሚፈጅ፣የሚጠቃ፣ሚሳደድ ህዝብ መኖሩ ትዝ ከሚላቸው ከአራት የማይዘሉ የብአዴን አባላት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠሩት አቶ ፀጋ አራጌ እንደሆኑ ነው፡፡ይህን ከሰማሁ ሁለት አመት ተኩል ያህል ጊዜ ቢሆነኝም እሳቸውም ቢሆኑ ከቪ8 ወርደው ለዚህ ህዝብ በተግባር ምንም ስላላደረጉለት እሳት ካየው ምን ለየው በሚል የያዝኳቸው ሰው ነበሩ፡፡ በተግባር ወጥተው ምንም ሲያደርጉ ባናይም በየስብሰባው ማንንም ሳይፈሩ ዱላ ቀረሽ የልባም ሰው ክርክር እንደሚያደርጉ ግን በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ፡፡
ሰውየው ይህን የስብሰባ ላይ ትግላቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የተቸገሩት ብአዴን የተባለው ፓርቲያቸው ውስጥ ያለው አማራ ነኝ ባይ ከሞላ ጎደል ሁሉም እንደ ወደል ውሻ በበላበት፣በጠጣበት የሚያውደለድል፣ እልፍ ሲልም የገዛ ወንድሙን አሳልፎ ሰጥቶ በተረኛ ጌታ ፊት ፊት ሞገስ ለማግኘት እግዜርን እንኳን የማይፈራው ስለበዛ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ አቶ ፀጋ በስተመጨረሻው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሰማሁትን ማንነታቸውን የሚገልፅ እርምጃ ወስደዋል፡፡ የአቶ ፀጋ እርምጃ ፓርቲ ውስጥ አባል የሚኮነው የብድር ማግኛ የድጋፍ ደብዳቤ ለማፃፍ የሚመስለውን ከርሳም የብአዴን ካድሬ ነርቭ ነክቶ አረፋ እያሰደፈቀ እንደሚገኝ ብአዴን ትናንት ባወጣው እንኩቶ መግለጫ ያስታውቃል፡፡
የዚህን ፓርቲ መግለጫ ለመተንተን ጊዜ መድቦ መቀመጥ ራሱ ፈጣሪ በቸርነቱ በጨመረልኝ የአንድ ቀን እድሜ ላይ እንደማላገጥ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ግን ደግሞ ቢዘገይም የህዝብ ቁስል ተሰምቶት፣ ሰው በጠፋ ቀን ሰው ለመሆን እየሞከረ ያለ አንድ ሰው ቢገኝ በጅብ መንጋ ሲቦጫጨቅ ዝም ብየ ማየት አልችልምና ይህን ዘገምተኛ አእምሮ የለቀለቀውን መግለጫ እየከረፋኝም ቢሆን አንብቤ ጨርሸዋለሁ!
መግለጫው ሲጀምር እንዲህ ይላል “ለለውጡ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ህዝባዊ ጥያቄዎች በተለይም የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣……..የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮችን የመለየትና የማረም፣ የፀጥታ የፍትህና የደህንነት ተቋማት፣………የለውጡ አበይት ትሩፋቶች የታዩባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር እነዚህ የለውጡ ቱርፋት ታየባቸው ተብው የተገለፁ ነገሮች በሙሉ የአማራ ህዝብ አሳር መከራ እያየባቸው ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ብአዴን ቱርፋት አገኘሁበት የሚለው የወሰንና የማንነት ጉዳይ የአማራ ህዝብ በሮኬት በሞርተር የሚጠበስበት፣ህፃናት ልጆቹ እግራቸው በሞርተር ተገንጥሎ “አሻንጉሊት ቀጥሉልኝና ተነስቼ ልጫዎች” ሲሉ እየሰሙ ሞትን በሚያስመርጥ ሁኔታ የሚኖሩበን መዘዝ ያመጣ ነገር ነው፡፡ ይህ የአማራ ሕዝብ አሳር መከራ ግን የጅቦች ጉባኤ ለሆነው ብአዴን የለውጡ ቱርፋት ነው!
ሌላው ራስ የሚያዞር የብአዴን ቀልድ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች ተለይተው እርምት እየተሰጠ ነው ያለበት ነገር ነው፡፡እዚህ ንግግር ውስጥ ያለውን ከርሳምነት፣ጭካኔ፣ወራዳነት በምን ቃል እንደምገልፀው አላውቅም! በሃገራችን እንደውሻ በጅምላ ተገድሎ እንደቆሻሻ በአንድ ላይ ታጅሎ የሚቀበረው ህዝብ አማራ ብቻ የሆነው መሪዎቹ እነሱ በመሆናቸው መሆኑን እንዲያውቁ ወያኔ እንደዛ አልሰራቸውም! ወያኔ የሰራቸው በዓለም ላይ አስፈላጊው ነገር ከርስ ብቻ እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጎ ነው! ስለዚህ በስካቫተር ተጭኖ እንደቆሻሻ የተቀበረው በእነሱ ስም የተወከለው ህዝብ የሚበላ ስንዴ ወይ በቆሎ ይመስላቸዋል፡፡ ከወለጋ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ በየቀኑ በኦህዴድ ሸኔ የሚያልቀው ሰው የሰብዓዊ መብት አያያዙን መሻሻል የሚያጣጥም ቅንጦተኛ ካድሬ ይመስላቸዋል፡፡ በአማሮቹ ቀየ በነጋ በጠባ እላያቸው ላይ የታጣቂ እሳት ሲለቀቅ እንደ ሸራተን ርችት ቁጭ ብሎ የሚያየው የፀጥታ እና ደህንነት መስሪያቤት፣አማራውን የሚፈጁ ገዳየችን ቤተመንግስት ጠርቶ መኪና የሚሸልማ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ለበአዴን የፀጥታ ቱርፋት አብሳሪ ነው!
ከዕለታት አንድ ቀን ነቅቶ የአማራን ህዝብ መከራዎች የሚያሳልጠውን መንግስታዊ አውታር “ግፍህ ይብቃህ፣እንደመንግስት በመርህ ስራ” ብሎ የጠየቀ አንድ ሰው ከብአዴን መሃል ቢገኝ ስሙ የትህነግ ተላላኪ” ነው- እነሱ ለትህነግ ተላልከው የማያውቁ፣አሁንም ትህነግ ተመልሳ ብትመጣ ለመላላክ የሚያመነቱ ይመስል!
በአዴኖች ፈሪዎች ስለሆኑ የሚታገሉት የወደቀ አካልን ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም “መሪ ሆኜ በተቀመጥኩበት ፓርቲ ህዝቤ በስካቫተር ተዝቆ ሲቀበር በህይዎት ቆሜ ከማይ አብሬ ልሙት” የሚያሰኘውን ጥቃት እንደ ክብር ይቆጥሩታል፡፡ጭራሽ ይህ ጥቃት የተሰማውን ሰው ሁሉ በጌቶቻቸው ክንድ ተጠልለው ያሳድዳሉ! (በዘራችሁ አይድረስ ማለት ይሄን ነገር ነው!)
ብአዴኖች ሰው የፓርቲ አባል እና አመራር የሚሆነው ከሆነ ቦታ ብድር ለመውሰድ የድጋፍ ደብዳቤ ለማፃፍ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ ሶስት አመት ሙሉ በወያኔ እና ኦህዴድ ጥምር ባሩድ እየነደደ እነሱ ይህን ብድር ያሉትን ዘረፋ ዘርፈው ቤታቸውን ሰርተው የቁስ ሰቀቀናቸውን ብቻ እያስታመሙ፣ ለገዳዩ ኦህዴድ የእግር ውሃ እያሞቁ መኖርን “ከፅንፈኛ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ተላቆ በመሃለኛ ፖለቲካ ውስጥ መኖር” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ክብራቸው በውርደታቸው ነውና ይህን ወራዳ እሳቤያቸውን በእነሱው ምክንያት ቀን ለጨለመበት፣ሃገር ቀርቶ ክልል ለፈረሰበት የአማራ ህዝብ ፅፈው “መግለጫ ነው አንብብ” ይሉታል!
የአማራን ህዝብ ፍጅት በፈገግታ ለሚያስፈፅመው የበአዴግን ጌታ ኦህዴድ አቤት ወዴት ማለት ደከመኝ የህዝቤ ህመም አመመኝ ያለ ሰው ለበአዴን የዓለም ሁሉ ጠላት፤ስሙም ብዙ ነው ! ሌላው ቀርቶ “ብአዴን” የሚል ስም ከእነሱው ስም ሁሉ የማይገልፃቸው ጉዶች ይሰነዘርበታል:: ከእነሱ ጋር መቀጠል ክብር የሆነ ይመስል “ከእኛ ጋር አይቀጥልም” ብለው ሰሚን ሳይወድ ያስቃሉ!
በነገራችን ላይ አቶ ፀጋ አራጌ ያነሱት ጥያቄ ምን ማለት እንደሆነ ከበአዴኖች ውስጥ አንድስ እንኳን ሰው የሚረዳው አይመስለኝም፡፡ ሁሉም እኩል የሚረዱት አንድ ሃቅ ግን የአቶ ፀጋ አራጌ ጥያቄ በአማራ ህዝብ ጫንቃ ቁጭ ብሎ ዘረፋን ብድር እያሉ እየጠሩ ከርስ የመሙላቱ ዘመን ሊመሽበት እንደሚችል ነው! ይህን ለመረዳት አንስታይን ቢኖር እንኳን የሚቀድማቸው አይመስለኝም!
ለማንኛውም በውቢቷ ቅዳሜ ቀን እስካሁን ስለ እነዚህ ሰዎች ማውራቴ ራሱ እነሱን በጣም ጠቃሚ ነገር አድርጎ ማሰብ እንደሚመስል ቢገባኝም አላማየ ግን ሌላ ነው፡፡ አላማየ እንደ አንድ ዜጋ በተለይም ደግሞ እንደ አንድ ከአማራ ህዝብ የወጣ ሰው የማስተላልፈው መልዕክት አቶ ፀጋ አራጌ በዚህ አቋማቸው እስከ ፀኑ ድረስ የአማራ ህዝብ እንደ ክፉቀን ደራሽ ልጅ የሚያያቸው ሰው መሆናቸውን ውርደት ጌጡ በአዴኖች ሊያውቁ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡
ክብር የማያውቅ ሰው የሚያስከብረው መንገድ የቱ እንደሆነ አያውቅ ሆኖባቸው እንጅ አቶ ፀጋ የያዙት መንገድ (ያስጨርሳቸው እላለሁ ፣ የክብሩን መንገድ መጨረሳቸውን የምጠራጠራቸው ደግሞ ብአዴን ስለሆኑ ነው) የክብር መንገድ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የጅብ መንጋ መሃል ሆኖ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ማሰብ ራሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በበኩሌ በደምብ የምረዳው ነገር ነው፡፡ብአዴን በመለግጫው የጮኽው አጯጯህ ራሱ አቶ ፀጋ የነኩት ቦታ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሰውየው አሁን በያዙት መንገድ እስከተጓዙ ድረስ ሰውየውን ለማጥፋት የሚደረገው ማንኛውም ሙከራ ብድር የምትሉት ዘረፋችሁ ዋስትና የሆነውን ፓርቲ አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ልታውቁት ይገባል፡፡
የመብት ተሟጋች መምህርትና ጸሐፊ
መስከረም አበራ
——————-