ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ዓርብ፣ ጥር ፳፯፣ ፪ሺ ፲፬ ዓ.ም. (Feb. 4, 2022) ቅጽ ፱ ቁጥር ፬
እንደሚታወቀው ፋኖ የዐማራ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ቢሆንም፣ ፋኖ ማለት ሀገርና ወገን ከአደጋ፣ ከወራሪ ለመታደግ ሲል ከመንግሥት ጋር በመተባበርና በመናበብ ራሱን ለመሰዋት የሚነሳ የወገን አለኝታ ነው። ፋኖነት አገሩንና ወገኑን ከራሱ አብልጦ የሚወድ፤ ለዚህም ራሱ ወዶና ፈቅዶ፣ ትዳሩ፣ ልጆቹ፣ እናትና አባቱ፣ ቤተሰቡ፣ ቤት ንብረቱ በተለይም ውድ ህይወቱ ሳያሳሳው ለአገሩና ለወገኑ ደህንነት ሲል ራሱን የሚሰዋ ክቡርና ድንቅ ለጋሽ ማንነት ነው። ስለዚህ ፋኖነት ማንኛውም አገሩን፣ ወገኑንና ሰንደቅ አላማውን የሚያከብር በነገድ ዐማራ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚጋራው እሴትና ማንነት ነው።
ፋኖነት ጾታ አይመርጥምና ፋኖ የሴትም የወንድም ነው፤ ፋኖ የወል ስም ነው። ፋኖነነት የራሱ የሆነ ስነምግባር አለው። ከነዚህም ውስጥ ፋኖ፣ አገሩና ወገኑ ጥቃት ሳይፈፀምበት በሰላም ውሎ እንደሚያድር እርግጠኛ ከሆነ እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑ ፋኖ እንደማንኛውም ዜጋ አርሶ፣ ነግዶ፣ አስተምሮ፣ ቀድሶ ወዘተ በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ራሱንና ቤተሰቡን ያስተዳድራል። ፋኖ የስልጣን ተጋሪ ለመሆን ሲል ጦር አይመዝም። ፋኖ የሚታጠቀው ገበሬ እንኳን ቢሆን በሬውን ሽጦ መሳሪያ በመግዛት ሲሆን፣ መሳሪያም ከሌለው ከታጠቁት ጋር ጀሌ ሆኖ ዘምቶ ጠላትን ማርኮ ይታጠቃል። ፋኖ አገርና ወገን ለማጥቃት ታጥቆ የተነሳ ጠላት ካልሆነ በቀር፣ ህፃናት፣ የእድሜ ባለፀጋ አረጋውያን፣ ሴቶችና አቅመደካማዎችን አያጠቃም። ሴቶችን አይደፍርም። ፋኖ የፈለገ ቢቸገር ዘርፎ አይበላም። የመንግሥት ተቋማትን አያጠቃም። ባንክ አይዘርፍም። አገር አያወድምም። የገበሬ ክምር አያቃጥልም። በጥላቻ ተነሳስቶ ነገዱ ያልሆኑ ግለሰቦችን ቀርቶ የእነሱን የቤት እንስሳት አርዶ አይበላም። ተኩሶም በጥይት አይገድልም። በአጠቃላይ ፋኖነት ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪነት ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለወገን ሰላምና ደህንነት ሲባል እራስን ለመሰዋእትነት ማቅረብ ነው።
ፋኖ ለመሆን የስነልቦና ዝግጅትና የሞራል የበላይነት ያስፈልጋል። አሁን እንደሚታየው እያንዳንዱ ዐማራ ብሎም አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በተሰማራበት ሁሉ በስነልቦና ዝግጅቱ ፋኖ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ዛሬም በመንግስታዊ መዋቅርና ፖሊሲ በጠላትነት ተፈርጆ ፍዳውን የሚያየው የዐማራ ሕዝብ እጣ ፋንታ የማያሳስበውና ውለታ ቢሱ የኢህአዴግ/ብልፅግና አገዛዝ፤ በተለይም የዐማራ ህዝብ በዘሩ ሲጨፈጨፍ ለገዳዮቹ ድጋፍና ከለላ የሚሰጠውን የኦዴፓ ፕሬዚዳንት ካባ በማልበስ ዐማራን የሚያሸማቅቀው፣ አዴፓ/ብልፅግና ዛሬም እንደልማዱ ክህደት ፈፅሟል።
አዴፓ/ብአዴን/ብልፅግና ከኦነግ/ኦህዴድ/ብልጽግና ጋር በማበር “ሆይ ሆይ” ብሎ ያስጀመረው አውዳሚ ጦርነት በድል መጠናቀቁ ቀርቶ፣ መጨረሻው ሳይለይለት፤ ዐማራ በኢትዮጵያ አገሩ የመኖር መብቱ ተገፎ፣ በኦሮሙማ አራማጆችና በወያኔ ጣምራ ወረራ በጅምላ እየተገደለና እየተቀበረ፣ በጅምላ እየተፈናቀለ፣ ሴቶች ከህፃን እስከመነኩሴ በጨካን መንጋ እየተደፈሩ፣ ብዙ ጀግኖች ፋኖዎች ይህን ግፍ ተጠይፈው፣ የብልፅግናው አገዛዝም ድረሱልን በማለቱ በጦርነቱ ተማግደው ተሰውተው፣ ብዙዎቹ አካለ ጎደሎ ሆነው ባሉበት ሁኔታ አገዛዙ “የዐማራ ሕዝባዊ ኃይል፣ ፋኖን” ለማጥፋት ሲጣጣር ማየታችን አዴፓ እያለ የዐማራ ህዝብ መከራና ተደጋጋሚ ክህደቶች እንደማይቆሙ ካሁን በፊት ያልተገነዘቡ ሁሉ እንዲያውቁት አድርጓል።
ስለዚህ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ካልሆነ ዲንጋይ ነው ብለው ይጥሉሀል!” እንዲሉ የኢህአዴግ/ብልፅግና አገዛዝ እራሱንና ህዝብን ከከፋ ደም መፋሰስ ያድን ዘንድ፤
- አገርን በክብር የመምራት ሞራል ካለው፣ የአየር መቃወሚያ ሳይቀር ከባድ ጥፋት ከሚያደርሱ የሚካናይዝድ ጦር ተወንጫፊዎችና ትልልቅ የግሩፕ መሳሪያዎች የታጠቀው ወያኔ “በዐማራ ህዝብ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ” ብሎ የዐማራና የአፋርን ህዝብ እስከ አሁን በጅምላ እየጨፈጨፈ ስለሆነ እንደመንግሥት ይህን እንዲያስቆም፤ ይህም ካልሆነ የአማራ ህዝባዊ ኃይል / ፋኖ ወገኑን አገሩን የመጠበቅ ታሪካዊ ግዲታውን ማንም ሊያቆመው እንደማይችል መረዳት፤
- በኦሮሙማ የጥላቻ ፓለቲካ የተመረዙ መሉ ትጥቅና የመንግሥት ሽፋን ያላቸው የኦሮሞ ልጆች ስማቸውን ሼኔና ቄሮ እያሉ ከ 20 በላይ ባንክ ዘርፈው፣ ዐማራና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆችን በአይናችን አያሳየን ብለው የሚያደርሱት የግፍ ግድያና መፈናቀል እንዲቆም እንዲያደርግ፣ የዘር ማጥፋትንና የዘር ማጽዳት ወንጀሎችን በስልጣን ላይ ሆኖ አለመከላከል ከወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊው አካል በላይ በስልጣን ላይ ያሉትን ተጠያቂ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ወንጀል መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ፣
- በትግራይ ወያኔና በኦነግ ጣምራ ወረራ የተገደሉ፣ የወደሙና የተዘረፉ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ላይ የደረሰው የመሰረታዊ ልማቶችና የሰብአዊ ጉዳቶች ገለልተኛና ታማኝነት ባለው አካል ተጠንተው አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋምና የካሳ ክፍያ ባስቸኳይ መፈጸም እንዲጀመር ማድረግ፣ ለዚህ ተመደበ የተባለው የአምስት ቢሊዮን ብር አስቂኝ የጠብታ በጀት የችግሩን ስፋት ያልመጠነና ለተጎጂው ህዝብ ያለውን ግዴለሽነት የሚያሳይ መሆኑን መረዳት፣
- የትግራይ ወያኔ ወረራ ጨካኝ ጭፍጨፋ ደም ሳይደርቅ፤ በወለጋ፣ በሸዋ፣ በቤንሻንጉል ጎሙዝና በሌሎች አካባብያዎች አማራን በማንነቱ ተለይቶ በየቀኑ በኦሮሚማ / ኦነግ ኃይሎች የሚፈጽመውን ሰፊ ጭፍጨፋ የአብይ / ብልጽግና አገዛዝ እውቅና እንኳን መስጠት ባልቻለበት፤ “ምህረት” በሚል ስም እንደነ ስብሀት ነጋና አይነት ቱባ የውያኔ ፋሽስቶችን ነጻ መልቀቁ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ድርድርና ምክክር የሚለው የአገዛዙ የወቅቱ ልፈፋ ከለመድነው የኦሮሚማ ብልጣብልጥነትና ማጭበርበር ያለፈ ሆኖ ወጤት እንዲገኝ ከተፈለገ፣ ድርድሩም ሆነ ምክክሩ ከኢህአዴግ /ብልጽግና እጅ ወጥቶ እዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ሊደረግ ይገባል። በተለይም የአማራን ነገድ እና የአፋርን ነገድ እውነተኛ ተወካዮች ያላካተተ ድርድር ኢፍትሀዊ ኢንደሚሆን፤ አገዛዙ የሚለፍፈው ሰላምና ብልጽግናንም ህልም ሆኖ እንዲሚቀር መገንዘብ፣
- መጨረሻም የዐማራ ሕዝባዊ ኃይል “ፋኖ” ትግል የመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ትግል እንደሆነ አውቆ፣ አገዛዙ ያለወንጀሉ የሚያሳድደውን፣ ሀገሩንና ወገኑን ከጥፋት ከሚታደገው ፋኖ ላይ አይኑንም እጁንም እንዲያነሳ፤ እንዲሁም በጉያው ያቀፋቸውን ለሀገርና ለህዝብ ፀር በሆኑት ወንጀለኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡ ሰላም ያገኝ ዘንድ አገዛዙ ስህተቱን አርሞ በትኩረትና በጥንቃቄ መስራት እንዳለበት ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ከወዲሁ ያስጠነቅቃል።
አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ፤ ሁሉም ዐማራ ለዐንድ ዐማራ!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ዓርብ፣ ጥቅምት ፲፱፣ ፪ሺ ፲፬ ዓ.ም. (Oct 29, 2021) ቅጽ ፰ ቁጥር
www.moreshwegenie.org
[email protected]