January 25, 2022
15 mins read

ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ለነገዋ በኢትዮጵያ – አንዱ ዓለም ተፈራ

እሁድ፣ ጥር ፲ ፭ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (1/23/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤

አሁን ላይ ተቀምጦ የነበረን መመዘን፣ ያንን መፍረድና ማውገዝ ወይንም ማወደስ፤ በጣም ቀላል ነው። ይህ ወደኋላ ዞሮ የቀደሙ ነገሮችን መመዘን፣ መፍረድና ማውገዝ ወይንም ማወደስ፤ ለወደፊቶቹ የተተወ ነው። ዛሬ ላይ ሆኖ፤ ወደፊት የሚከተለውን መመዘን፣ መፍረድና ማውገዝ ወይንም ማወደስ፤ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን አንዳንዶቹ በጣም አፍጥጠው የሚታዩ በመሆናቸው፤ ዓይኖቻቸውን ገልጠው ለሚመለከቱ፤ ቀላል ናቸው። የአገራችን የፖለቲካ እውነታ ማብቂያ በሌለው አዙሪት ተጠምዶ፤ የሄድንበትን ጎዳና መልሰን እየሄድንበት፤ ወደፊት እየሄድን ነው ብሎ ማመን፤ የዋኅነት ብቻ ሳይሆን፤ ዲካ የሌለው ደደብነት ነው። ሀቅን አፍጥጦ ማየትና መቀበል፤ ያንን ይዞ ወደሚፈልጉበት መንገድ መምራት፤ ለነገ ማደርን ብቻ ሳይሆን፤ አድሮ ለመሰንበትም ይረዳል። ማወቅ ያለብን፤ አገራችን እየሄደችበት ያለው ጎዳና፤ ለነገ ሰላም፣ ልማትና ዕድገትን አያስከትልም። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና ፓርቲ፤ ሰላም፣ ልማትና ዕድገትን በኢትዮጵያ ሊያመጣ አይችልም። ይሄን አንድ ብለን እንውሰድ። ችግሩ፤ ባሁኑ ሰዓት ብልፅግናን የሚተካ ቀርቶ፤ ባጠገቡ እንኳ ሊቆም የሚችል ድርጅት አለመኖሩ ነው። ይሄን ሁለት ብለን እንውሰድ። አሁን በአገራችን ያለው የፖለቲካ ቀውስ፤ ውሎ አድሮ የአምባገነን መንግሥትን የሚያስከትል ነው። ቀውሱ ደግሞ የሚያበቃው፤ አምባገነንነቱ ሲያበቃ ነው። የተፈጥሮ ሕግንና የተፈጥሮ ዕውነታን ቦጫጭቆ መጣልና ማስወገድ አይቻልም። ይልቅስ ይሄንን አውቆ፤ ለመጪው መዘጋጀት አዋቂነት ነው። ይሄን እንድዘረዝርና በግልጥ እንዳስቀምጥ ያደረገኝ፤ ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው። እናም ሀቁን እንዳለ ማቅረብ ፈለግሁ። ይሄ ትንቢት አይደለም። የውስጥ አዋቂ ሆኜም አይደለም። አገሬን የምወድና የምችለውን ዕርዳታ ለማድረግ የፈለግሁ ግለሰብ ስለሆንኩ፤ ያለውን ተጨባጭ ሀቅ እንዳለ ማስቀመጡ ግድ ስለሆነብኝ ነው።

የብልፅግና ፓርቲ ለምን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት አያስከትልም? ብልፅግና ይሄን የማያስከትልበት መሠረታዊ ጉድለት አለው። በመጀመሪያ የዚህ ፓርቲ አመሠራረት ለዚህ ግብ አይደለም። ብልፅግና ኢሕአዴግ ሁለት ነው። ስሙን ቀየረ እንጂ ፍልስፍናውን ሆነ አስተዳደሩን አልቀየረም። ብልፅግና ይባአሉ እንጂ፤ አሁንም የክልል ድርጅቶች ናቸው። ይህ ተስፋ ሠጪ የሆነ ሰላም፤ ልማትና ዕድገትን ባገር ማስፈን ዓላማ፤ የዚህ ድርጅት ውስጠ-ክን አይደለም። ተግባሩም ይሄን አያመለከትም። የወደፊቱም ይሄ አይደለም። በተጨማሪ፤ ብልፅግና አንድ ፓርቲ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። በተለያዩት የየክልሉ የብልፅግና ፓርቲዎች፤ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት፤ የአገሪቱን እሴቶች ለኔ የበለጠ ይድረሰኝ! የለም ለኔ የበለጠ ይድረሰኝ! ቅርምት ሩጫ ብቻ ነው። የአንደኛው አባል በሌላው ክልል አባል ሆኖ ሊገባና በክልሉ የፖለቲካ ክንውን ሊሳተፍ አይችለም። እኒህ ተፎካካሪ የሆኑ የብልፅግና ፓርቲ አካሎች፤ የየክልላቸው አድራጊ ፈጣሪ ናቸው። የየራሳቸው ኃይል፣ ሕግና ስነ ሥርዓት አላቸው። በክልላቸው ውስጥ የፈለጉትን የማድረግ ሥልጣን አላቸው። ታዲያ ለምን? በምን ሂሳብ? ለኢትዮጵያ ያስባሉ? ኢትዮጵያስ የት አለችና! ክልላቸውን ማበልፀግና ክልላቸው ከሌሎቹ ክልሎች የበላይ እንዲሆን ከማድረግ የተረፈ፤ ዓላማ የላቸውም። አሁን ባለው ቅንብር፤ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ መሪ ብቻ ነው የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትርና ፈላጭ ቆራጭ የሚሆነው። ሀቁን ከተነጋገርን፤ ከሶማሊ፤ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ቤንሻንጉል፣ አዲስ አበባና ከጋምቤላ፤ ባሁኑ ስሌት፤ ምንም ቢሆን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አይወጣም። ይህ የማይሆነው፤ የፓርቲ አካሎቹ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ ቀርተው አይደለም! በብልፅግና ውስጥ ድምፅ የሚሠጠው፤ በክልል ሂሳብ ስለሆነና አብላጫ አለው ተብሎ የሚታመነው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ስለሆነ፤ ምንም ጊዜ ያ ሥልጣን ለዚህ ክልል የተተለመ ነው። በርግጥ አንገቱን ደፍቶ ለሚወክለው ወገኑ ሳይሆን ለሆዱ ያደረ ለይስሙላ በቦታው ሊቀመጥ ይችላል።

ሁለተኛውና በጣም አስከፊው ጉዳይ፤ ብልፅግናን የሚወዳደር ቀርቶ፤ ባጠገቡ እንኳ የሚደርስ ሌላ ፓርቲ አለመኖሩ ነው። ይሄ ከሁለት በኩል እክል ገጥሞታል። በመጀመሪያ ከብልፅግና ውጪ ያሉ ስብስቦች በሙሉ፤ አንድ የሆነ የጋራ ዓላማም ሆነ አገራዊ ግብ የላቸውም። እናም አንድ ወይንም ሁለት ጠንካራ ፓርቲዎች ማቋቋም ተስኗቸዋል። ጥቂቶቹ አሁን ብልፅግና የያዘውን ዓላማ እየወደዱና ተቀብለው፤ ከብልፅግና እኛ እንሻላለን ብለው በብልፅግና መንገድ ተወዳዳሪ ናቸው። ይሄ በአማራ ክልልና በኦሮሞ ክልል ይስተዋላል። እኒህን ዋጋ ቢስ እንበላቸው። ሌሎቹ ብልፅግና የያዘውን መንገድ እያወገዙ፤ ትክክለኛ አማራጭ ግን ለሕዝብ ማቅረብ የማይችሉ ናቸው። አገር አቀፍ ዓላማና ትክክለኛ የሆነ መንገድ እንከተላለን የሚሉት እንኳ፤ በጥቃቅን ልዩነቶች ዓይኖቻቸውን ተክለው፤ የየራሳቸው ዘውድ ጭንቅላቶቻቸው ላይ ጭነው፤ ፓርቲ ሳይሆን የጓደኞች ስብስብ ናቸው። ሌላው እክል ደግሞ፤ ከብልፅግና የሚመጣው ነው። እያንዳንዱ የክልል ብልፅግና፤ ክልሉን እወክላለሁ ብሎ ስለተነሳ፤ በዚያ በራሱ ክልል፤ ተወዳዳሪ እንዲኖር አይፈልግም። ምክንያቱም፤ ያ የክልል ፓርቲ የሚወክለው ክልሉን ስለሆነ፤ ሌላ አካል ያንን ክልል እንዲወክል አይፈቅድለትም። እናም በነዚህ ሁለት ምክንያቶች፤ አማራጭ ሌላ ፓርቲ ሊያድግና ሥልጣን ላይ ሊወጣ አይችልም።

ከላይ ያስቀመጥኳቸው ሁለቱ ጉዳዮች፤ አገራችን ወደ ከፍተኛ ቀውስ እየተንደረደረች እንደሆነች ያመለክታሉ። ባለፉት ሶስት ዓመታት፤ ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ከፍተኛ ተስፋ ሰንቀን ተነስተን ነበር። የሃምሳ ዓመታት ስቃዩ አለፈ! በማለት፤ አገር ቤት መተንፈስና ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ወዳገራችን መንጎድ ይዘን ነበር። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከነፖለቲካ ፍልስፍናው ካገራችን ተነቅሎ ይወገዳል! ብለን፣ የኢትዮጵያ ስምና አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማችን በየቦታው ሲውለበለብ፤ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ! ብለን በደስታ ተሞላን። ነገር ግን ሁላችንም ውለን አድረን እንደተገነዘብነው፤ የመሪ ለውጥ እንጂ የፖለቲካ ፍልስፍናውም ሆነ የአስተዳደር ዘይቤው እንደማይለውጥ አወቅነው። ክልሎቹ ሁሉ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የሠጣቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብና ክልላቸውን መግዛት ቀጠሉ። በተስፋ ብቻ፤ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ!” “ከምርጫ በኋላ ሁሉም ይደረጋል!” በሚል ሂሳብ አገር ተነዳ። የአንድ የፖለቲካ ሂደት ዕድሜው የሚለካው፤ በሂደቱ ሀቀኝነት ነው። “አድሮ ሊታይ አይደል!” አለች ተራቢ። ትክክለኛ የፖለቲካ ሂደት፤ ዕድሜው ረጅም ነው። ትክክለኛ ያልሆነ የፖለቲካ ሂደት ደግሞ፤ ዕድሜው አጭር ነው። ደርግና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያጋጠማቸው ይሄ ሀቅ ነው። እያደር እየጠራ የሄደው የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲካ፤ አገሪቱን አንድ የሚያደርግ ሳይሆን፤ የነበረን ድርጅት በአዲስ የድርጅት ስም የተካና የነበረውና ፖለቲካ አስቀጣይ መሆኑን እያሳየን ነው። እናም ይህን የመሰለ የፖለቲካ ቀውስ፤ ሊከተሉት የሚችሉ ሁለት ውጤቶች አሉት። አንደኛው ሕዝቡ በአመጽ ተነስቶ፤ ያለውን ሥርዓት የሚለውጥበት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ፤ ሕግና ሥርዓትን ለመጠበቅ በሚል ሂሳብ፤ ግድያንና እስርን መሳሪያ ያደረገ አምባገነን መንግሥት መከተሉ ነው። ባገራችን ያንዣበበው ሁለተኛው ዕጣ ነው። ይሄን ያልተስተካከለ ሂደት ይዘን ዴሞክራሲያዊ ነው! እያለን ጥቂትም ልንቆይ አንችለም። ይህ በቅርብ ይከሰታል። ከዚያም ነፃነታቸውን ብለው የሚነሱ ብዙዎች ያልቃሉ። እስከዛሬ ድረስ ከነበረው ጥፋት የበለጠ የከፋ ዘመን ይሆናል። ደም ይጎርፋል። ስደቱ ከምን ጊዜውም በበዛ ሁኔታ ይቀጥላል። ድርቅና ረሃብ በአገራችን ቤታቸውን ያሻሽላሉ። በበሽታና በማጣት የሚሰቃየው ወገናችን ቁጥሩ ይበዛል።

ሃሳቤን ለማጠቃለል፤ መርኅን የተከተለ፣ ፍትኅን ያዘለና እኩልነትን ያነገሠ መንገድ ሲኖር ብቻ ነው፤ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ባገር የሚነግሠው። ክፍፍልና የኔ ባይነት በነገሠበት አገር፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አይገኝም። እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት፤ ለፖለቲካ ተሳትፏችሁ ኢትዮጵያዊ ብቻ ናችሁ! ብሎ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያስተዳድራቸው ሕገ-መንግሥት ሲኖርና በኢትዮጵያዊነታቸው በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል መኖር፣ ሀብት ማፍራት፣ ባሉበት አካባቢ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ማድረግ ሲያስችላቸው ብቻ ነው አገራችን ውስጥ ሰላም፤ ልማትና ብልፅግና የሚመጣው። ለዚህ ደግሞ፤ ሕዝብን አስቀዳሚ፣ አገር ወዳድና ፍትኅን ፈላጊ የሆኑ ሰዎች ባንድ ተሰባስበው ላገር ማደር ይኖርባቸዋል። ይህ ሳይሆን፤ ሁሉም ሰላም ነው! ውጪሰው ኢትዮጵያዊያንም ገንዘባችሁን ብቻ ላኩልን! ስንፈልጋችሁ ደግሞ በያላችሁበት አገር በዲብሎማሲና በፖለቲካ ረገድ እርዱን! ማለቱ ዘለቄታ የሌለው ሂደት ነው። ይህ የኔ ስህተት ቢሆን በጣም ደስተኛ ነኝ። አድረን እንየው!

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ናት። ልጆቿ ይታደጓታል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop