ይህ ዘመን የጉድ ነው! – በላይነህ አባተ

ሔዋንና አዳምን በገነት ያሳተው፣
መለኮትን ክዶ ለሰይጣን ያደረው፣
እግዚአብሔር በቅጣት በሆዱ ያስኬደው፣
ሁለት እግር አውጥቶ ቆሞ እየሄደ ነው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

“ዓይንን የሚያበራ ጥበብ አለኝ” ሲለው፣
የእፀ በለስ ፍሬ እንዲገምጥ ሲሰብከው፣
ተጉድጓዱ ወጥቶ ፍልፈል ሞጭሞጪላው፣
እየፈነጠዘ ዘንዶን ተከተለው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

“እኔን ከሰማኻኝ ክንፍ ታወጣለህ” እያለ ሲሰብከው፣
እንሽላሊት ተካብ ጓጉንችር ተውሀው፣
ተግተልትሎ ወጥቶ እባብን አጀበው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

“በሰማይ አብርሬ አፈርን ተመቃም አድናለሁ” ሲለው፣
ምንም ሳያቅማማ ጥያቄም ሳይኖረው፣
የምስጥ ሰልፈኛ ዘንዶን ተከተለው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

“ምራቅ ቅብአ ቅዱስ መርዝም ፀበል” ሲለው፣
አሳማው ከርከሮው አመነና ጠጣው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

ከተራራ ወጥቶ ጌታን የፈተነው፣
ከተማ አሳይቶ ሊደልል የቃጣው፣
ዳሩ በመለኮት ድባቅ የተመታው፣
ዛሬ ስንቱን መንጋ በምላስ ጠረገው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

ጉንጭ ስሞ ጠቁሞ አሳልፎ ሰጪው፣
ከሺ ዓመታት በፊት የነበር ብቸኛው፣
ራሱን አባዝቶ እንደ ወስፋት ኮሶው፣
እንደ ዝናብ አብራ አገሩን ወረረው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

ክርስቶስን አስሮ በርባንን የፈታው፣
ዛሬም እየሄደ ሳጥናኤል በመራው፣
ዙፋን ላይ ቁጭ ብሎ አገሩን አወከው፣
የእግዚአብሔርን ሚዛን ፍትህን ሰበረው፡፡

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

ገነት ኃጥያት ሰርቶ ተምድር የተጣለው፣
በላብህ በወዝህ ግረህ ብላ ያለው፣
ዛሬም የእባብ ስብከት እያደመጠ ነው፣
ደሞ ተመሬት ላይ የት ሊወረወረ ነው?

ይህ ዘመን የጉድ ነው!

በላይነህ አባተ (([email protected])
ጥር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.