ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ – አበበ ገላው

ከሁሉም በማስቀደም አንኳን ለብርሃነ ልደቱ ከእነ መላ ቤተሰብዎ በሰላም አደረስዎ ለማለት እወዳለሁ። ይቺን አጠር ያለች ደብዳቤ እንድጽፍልዎ ያነሳሳኝ ዋና ጉዳይ የሚከተለው ነው።

ኢትዮጵያ ከገባችበት ጥልቅ አገራዊ ቀውስ፣ ጦርነትና እልቂት ለማውጣት በአገራችን ብሄራዊ መግባባት ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ያለው አንዳንድ እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ እምነቴ ነው። በዚሁም መሰረት በእነ እስክንድር ነጋና በእነ ጃዋር መሃመድ የክስ መዝገብ ተከሰው በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉ ተገቢ መሆኑ ብዙም አያከራክርም የሚል እምነት አለኝ።

ይሁንና በተያያዥ ተሰብሰብው፣ አቅደውና ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ጥቅምት 24 2013 በውድቅት ለሊት በሰሜን ዕዝ ላይ የተቀናጀ ጥቃት እንዲሰነዘር ትእዛዝ በመስጠት በበርካታ ሺ የሚቆጠሩ የአገር መከላከያ አባላት ላይ ግድያ፣ ዘግናኝ ግፍ፣ የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው የአንበሳውን ድርሻ የተጫወቱትን የአሸባሪው የህወሃት ከፍተኛ አመራር አባላት የሆኑትን እነ ስብሃት ነጋን መንግስት መፍታቱን ስሰማ የተሰማኝ ሃዘን እጅግ ጥልቅ ነው።

በእነዚህ ግልሰቦች ውሳኔ ምክንያት በህዝባችን ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ ተፈጽሟል። ያም ሳያንስ በግለሰቦቹ ምክንያት አገራችን እስካሁን የጦርነት አረንቋ ውስጥ በመዳከር ላይ የምትገኝ ሲሆን ከመቶ ሺ በላይ ዜጎቻችን ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምስኪን ወገኖቻችን ከቀያቸው በመፈናቀል ለችግር፣ ርሃብና ቸነፈር ሰለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆነዋል።

ከዚህም በላይ በበርካታ ሺ የሚቆጠሩ እናቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶች ሰይጣናዊ መንፈስ በተጠናወታቸው የህወሃት ታጣቂዎች እንዲደፈሩና ለአካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ሰለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆነዋል። የግለሰቦቹ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀልና የሽብር ድርጊት ከማንም በላይ ለመንግስት ግልጽ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል

በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀሎችን የፈጸሙና ወደፊትም ከመፈጸም ፈጽሞ የማይቦዝኑ ግለሰቦችን በዘፈቀደ መፍታት የህዝባችንን ጉዳት፣ ህመምና፣ ቁስል ፈጽሞ እያዩ እንዳላዩ ከማለፍ ወይንም ከማቅለል የማይተናነስ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን በሃቅ በመቀበል ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይና ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን አይቶ እንዲወስን እንዲደረግ በተጎጂ ወገኖቻችን ስም እጠይቃለሁ። ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በእርቅና ሰላም ስም የፍትህ ፈላጊውን ህዝብ ስሜትና ፍላጎቶች እንዲሁም የአገርን ደህንነት ከሚጎዳ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባው እንደ ዜጋ ለማስገንዘብ እወዳለሁ።

ለአገራችሁና ለህዝባችሁ ህልውና ወደር በሌለው ፍቅር ነፍሳችሁንና ደማችሁን ሳትሳሱ የገበራችሁና ዛሬም ግንባራችሁን ያላጠፋችሁ የቁርጥ ቀን ልጆች ክብርና ምስጋና ይገባችሁዋል። ደማችሁና አጥንታችሁ የኢትዮጵያ መሰረትና ታዛ ነው። የእናንተን ጀግንነት ጊዜና ቦታ ፈጵሞ አይሽረውም!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሆይ!

መደመር በሚል ርእስ ባሰተሙት መጽሃፍ ገጽ 108 የሚከተለውን ጽፈው ነበር። “አንድ መሪ የተከታዮቹን ስሜት ካልተረዳና የስሜቶቹን ምክንያትና የሚያስከትሉትን ውጤት ካልመረመረ የስሜት ልቀቱ ላሽቋል ወይንም የስሜት ድቀት ውስጥ ገብቷል ማለት እንችላለን። ህዝብና ተከታይ ሲከፋ ለምን እንደተከፋ መመርመር፣ የስሜቱን መጠንና አቅጣጫ ማጤን፣ እንዲሁም ስሜቱ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ መገንዘብ አስፈላጊ ነው።…የህዝብን ብሶትና ንዴት በወቅቱና በተገቢ ሁኔታ ያልተረዳ መሪ ህዝብን እየገዛ እንጂ እየመራ አይደለም።”

እኔም እርስዎ በራስዎ ብዕር ከጻፉት ቁም ነገር የተለየ ሃሳብ ባይኖረኝም ቃልዎ ከተግባር ጋር መጣረሱን አስተውለው የመንግስትዎን ውስኔ መልሰው ይመርምሩ። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ በቀልን ባይፈልግም ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ ግን በፍርድ አደባባይ ማየትን እንደሚፈልግ አልጠራጠርም። ስለዚህም ይህ ውሳኔ የከፋ ጦስ ከማስከተሉ በፊት በጥሞና ተመርምሮ እንዲስተካከል ስል እንደ አንድ ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ መጠየቅ እወዳለሁ።

ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን መንግስት ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኪሳራ ሊደርስብት እንደሚችል ፈጵሞ አያጠያይቅም። በመሆኑም ውሳኔውን መልሶ ማጤንና በአስቸኳይ መቀልበስ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእስር ላይ የሚገኙት የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች መግለጫ በድምፃችን ይሰማ ይፋ ሆነ

በተረፈ እንደ ታቀደው በጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከክፍፍል ይልቅ ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን ምኞቴን እገልጻለሁ።

አበበ ገላው

1 Comment

  1. የአሜሪካው ቀልደኛ Mark Twain said ” History does not repeat itself, but it often rhymes”. የኢትዮጵያ ፓለቲካ የቆሻሻ ክምር ነው የምለው ለዚያ ነው። የሞተን የቆሰለን እየረሳ ወደ እሳት የገፏቸውን የሚሾም፤ የገደላትን ከእስር የሚፈታ፤ ሃገር አፍራሽን ዘይት የሚቀባ እልፎች አልቅሰው ጥቂቶች የሚፈነጩባት የእብዶች ምድር። ከእብደታችን ብዛት ምንም ያላረገን ወታደር በሃገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፊልድ ማርሻል” የሚል የውሻዎች የፓለቲካ ስብስብ ነው። የሞተው በፎቶው ላይ እንደሚታየው ታንክ የተነዳበት፤ በደቦ ወያኔ የጨፈጨፈው፤ የድሃ አደግ ልጅ በትግራይ፤ በአማራና በአፋር በረሃዎች ወድቆ ቀርቷል። ጠ/ሚሩ የሚሰራውና የሚናገረው ነገር የማይገናኝ ትክክለኛ የወያኔ ልክፍቱን ያሳየበት ይህ የአሁኑ ግርግር ራሱን ሳይቀር የሚላጨው እሳት ለመሆኑ ቀን ያሳየናል። በዚህ የፓለቲካ ጫወታ ውስጥ የተጎዳው ይተዘረፈው፤ የሞተውና አሁንም በወያኔ ጥይት የሚነዳው የአማራና የአፋር ህዝብ ነው። ራሱ ወያኔ ሽዋ ድረስ እንዲገባ የተደረገውም ሆን ትብሎ ነው ለማለት ያስችላል። እንዴት ባለ ሂሳብ ነው “ስብሃት ነጋና የዘመናት ደም አፍሳሾች ወደ 70 የሚጠጉ ወያኔዎች የተፈቱት”? እርቅና ሰላም ብሎ ነገር የለም ይለናል ጌታቸው ረዳ ከመቀሌ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማን ጋር እርቅ እንደሚያወርድ ሊገባኝ አልቻለም። አቶ ስብሃት እኮ በፊት የነበረውን አይነት አሁን በወያኔ የፓለቲካ አሰላለፍ ተሰሚነት የለውም? ኦነግ ሸኔና የኦሮሞ የኦሮሚያ ገንጣዪች በአሜሪካ መንግስት እየተረድ እሳት ማንደዳቸው እየታየ፤ ወያኔ በዚህም በዚያም ጦርነት ከፍቶና በግልጽ ውጊያችን አጠናክረን እንቀጥላለን አልፎ ተርፎም ኤርትራን እናጠቃለን እያለ በሚደነፋበት የወያኔን ደም አፍሳሾች በእርቅ ስም መፍታት በእውነተኛ ኢትዮጵያዊያን ደም መነገድ ነው። ኤርትራዊያንንም ለጥቃት ማጋለጥ ነው። ግን ይገባናል ይህ ሁሉ እብደት አሜሪካን ለማስደስት ነው። ለምን በጉልበትህና በእጅህ ተጎንብሰህ አትሄድም። አሜሪካና አውሮፓ ከራሳቸው የበላይነትና ጥቅም በስተቀር ለሃበሻው ምድር ደንታ የላቸውም። ጠ/ሚሩና በዙሪያው ያሉ የድህነት ካድሬዎች እንዴት ባለ ሂሳብ ነው እነዚህን ደም አፍሳሽ ወያኔዎችና ኦሮሞዎች ፈትቶ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ እስረኞችን እስር ቤት የሚያሳድረው? ፍትሁ የት ላይ ነው? ጠ/ሚሩ ስልጣኑን መልቀቅ አለበት። የትግራይ መንግስት እኮ አሁን ራሱን ገንጥሎ መንግስት ሆኗል። የአሁኑ ውጊያ እቃ ዘረፋና ድንበር ማስፋፋት መሆኑን እንዴት ጠ/ሚሩ መረዳት ይሳነዋል? ወያኔ የትግራይን ህዝብ ከቀረው የኢትዪጵያ ህዝብ እንደገነጠለ በግልጽ ነው የሚናገረው? ባይሆን እንኳን የተፈቱትንም ሆነ ወያኔ ናፋቂ የሆኑትን ሁሉ ወደ መቀሌ በመላክ በዚያው ለትግራይ መንግስት የሚችሉትን ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መላክ ነው። የጠ/ሚሩ መንግስት የወያኔን ደም አፍሳሾችና የኦሮሞ ጭራቆችን ( በሻሸመኔ የሆነው ግፍ ብቻ በቂ ነው) የፈታው በምላሹ ምን አግኝቶ ነው? ወያኔ የማረካቸው በህይወት ያሉ የኢትዪጵያ ወታደሮች የት አሉ? ማን ይድረስላቸው። የሃበሻው የቧልት ፓለቲካ ሁልጊዜም የሚያስለቅሰው ድሃውን ብቻ መሆኑ ታሪክ ራሱን መድገሙን ሳይሆን የዛሬውም እንደትናቱ በቃናውም በተግባሩም ባለህበት ሂድ እንደሆነ ያሳየናል። በሰዎች ደም የረሰረሰው፤ በእናቶችና በህጻናት እንባ የረጠበው፤ በዝርፊያና በግድያ የተደረመሰው የሃገሪቱ ሰሜናዊ ምድር ይፋረድ። ከአሁን በህዋላ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ገብቶ ህይወቱን የሚሰጥ ሰው እብድ እንጂ ጤነኛ አይደለም። በሰው ደም መነገድ ይሉሃል ይሄ ነው። እጅ በእጅ ከወያኔ ጋር የገቢያ ልውውጥ። አታድርስ። ጠ/ሚሩና በዙሪያው ያሉ ሁሉ በሽተኞች ናቸው። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share