ሰበር ዜና ፤ እነ ጃዋርን እና እነ ሥብሐትን ፣ በነሱ ክስ የተመዘገቡትን ሁሉ ከሞራል አንፃር ፈታናቸው ። ከሞራል አንፃር እነ ጃዋርን እነ ሥብሐትን ፈታናቸው ። ተባለ ። ለነጃዋር ፣ ለነሥብሐት ደጋፊዎች ይህ ታላቅ ድል ነው ። ሰበር ዜና ብቻ አይደለም ። ለብዙዎቹ ኢትዮጵያኖች ይኽ ዜና ሰበር አይደለም ። ልብ ሰባሪ እንጂ !! ስብሐት ነጋ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ ዓባይ ዘውዱ፣ አባዲ ዘሙ፣ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር፣ ኪሮስ ሐጎስ፣ ጃዋር ሞሐመድና በእሱ ክስ መዝገብ ሥር ያሉት በሙሉ ከሞራል አንፃር ተፈተዋል ። ከወንጀል አንፃር ግን በአእምሯቸው እንደታሰሩ ናቸው ። ተገቢውን መማሪያ ቅጣት ሳያገኙ ከእሥር በመለቀቃቸው ዳግም ወንጀል ከመሥራት የሚያመነቱ አይመሥለኝም ።
ልብ በሉ እነኝህ አገርን የካዱ ፣ ወገን ከወገኑ ጋር ደም እንዲቃባ ያደረጉ ፣ በልዩ ልዩ ወንጀል የተጠረጠሩ ፣ ከዘር ማጥፋት ጥቃት እስከ ሀገርን ያራቆተ ዝርፊያ ውሥጥ ተሰማርተው ፣ ህዝብንም ለሌብነት ያሰማሩ ። ሰውን ከሰው በነገድ ፣ በዘውግ ያገዳደሉ ። የዘውግ ክፍፍልን በማጦዝ ፣ የጠቅላይ ሚኒሥቴርነትን ወንበር ለማግኘት የቋመጡ ። ግለሰቦች ፣ እንዴት ነው ከሞራል አንፃር የሚፈቱት ?? የተወነጀሉበት ወንጀል ደግሞ በየትኛውም ሕግ ምሕረትም ሆነ ይቅርታ የሚያሰጥ አለመሆኑንም ልብ በሉ ። ታዲያ በምን ሂሳብ ነው ድንገት በሰበር ዜና ( የምንዱባኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ በሚሰብር ዜና ) የሥንት ንፁሐን ደም በእጃቸው ያለ ወንጀለኞችን ያለ ቅጣት ከሞራል አንፃር ብቻ አይቶ ከእሥር መልቀቅ የተፈለገው ??
ይህ ድርጊት ሆድ ብቻ ላልሆነው ፣ በሥጋ ና በፍራንክ ለማንገዛ ፤ ሞት ሁሌም ከእኛ ጋራ እንደሚያዘግም ለምንረዳ ፣ ዛሬ እንደምንሞት ጠንቅቀን ለምናውቅ ፣ በሰውነት እንጂ በዘር ሰውን ለማናውቅ ( አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ትግሬ ፣ ሱማሌ ፣ አፋር ፣ ወዘተ። ነን ለማንል ። እኔ ሰው ነኝ ለምንል ። ሰው ሁላ ወገናችን ለሆነ ። ) በእጅጉ ያሳዛነናል ።
በመላ ኢትዮጵያ በግፍ ለተጨፈጨፉት ፣ በአማረ ክልል ና በአፋር በጥይት ለተረሸኑት ንፁሐን ዜጎች ፤ በሳንጃ ለታረዱ የዋሆች ፣ በየጎጆቸው ለተቃጠሉ ምንዱባን አማሮች ፣ በባሎቻቸው እና በልጆቻቸው ፊት ለተደፈሩት ፤ በሻሸመኔ በየጎዳናው አሥከሬናቸው ለተጎተተ ፤ በሜንጫ ለተቆራረጡት ፤ ወዘተ ። ማነው ከመንግሥት ውጪ ፍትህ የሚሰጣቸው ? ማንሥ ነው ነገ ገንዘብ ህሊናውን ያናወዘው ፣ በቢሊዮን ዶላሩ የአሜሪካንን መንግሥት ድጋፍ ማግኘት የሚችል ፣ ለሰው ፈፅሞ ርህራሄ የሌለው ፣ ሰብአዊነት ፈፅሞ የሌለው ፣ በዘረኝነትና ለጥቅም ሲል በነገድ ፖለቲካ ያበደ ፣ ክቡሩን ሰው ፣ አገር ሰላም ነው ብሎ በተቀመጠበት ቤቱ ቢያርድ ፣ ሺዎችን ጎዳና ለጎዳና እያሳደደ ቢጨፈጭፍ ፤ ካለእኔ ነገድ ውጪ ሌሎቻችሁ ቁንጫ ና በረሮዎች ናችሁ በማለት ዘውግ እየለየ ቢያጠፋ ማን ሊከለክለው ይችላል ።
በዚች አገር ከትላንት እሥከዛሬ ፍትህ መሣቂያ መሆኖ ይገርመኛል ። ደግሞም ያለ አንዳች ተጨባጭ ወንጀል ፣ በጅምላ የትግራይ ተወላጆችን ማሰሩ ለምን አሥፈለገ ? ዛሬ እነ ሥብሐት ” ይቅርታ ጠይቀው ” ተፈቱ ማለት ጌታቸውም ሆነ ደብረፅዮን ነገ ይቅርታ ጠይቀው ከሰሩት ወንጀል ነፃ እንደሚሆኑ ማን ይጠራጠራል ? (…)
በዚች አገር በግብታዊነት የሚሰሩ ፤ ከፍትህ ጋር የሚጋጩ ፤ አሠራሮች ከትላንት እሥከዛሬ እየተከናወኑ ነው ። አብይ መራሹ መንግሥት የትላንትናዎቹን ህገ ወጥ ተግባራት ና “ ከመንግሥት በላይ መንግሥት “ የሆኑ ግለሰቦች ና “ በህቡ የተደራጁ “ ኃይሎች ያሥከተሉትን ውድመት በጊዜ ብዛት የረሳው ይመሥለኛል ። ጠ/ሚሩን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት የህግ የበላይነትን ለማሥከበር የሚሂዱበትን ርቀት ደጋግመው ገልፀዋል ። በኢትዮጵያም ድርድር እንደሌለ አሳውቀዋል ። እና ዛሬ ምን ተፈጥሮ ነው ፣ ከፈረሱ በፊት ጋሪው የቀደመው ?
እነዚህ ሰዎች እኮ የትግራይን ህዝብ ከአማራና ከአፋር ጋር ደም ያቃቡ ናቸው ። ጃዋርም ቢሆን ሰው ማለት ኦሮሞ እንጂ ሌላው በረሮ ነው ባይ ነው ። እምነተ ቢስ ነው ። አንድ በሬ በእሥልምና እና በክርስትና ሥም አርዶ ለፖለቲካ ፍጆታ ህዝብ በግድ የሚያሥበላ ነው ። ይኽንን ሃቅ መራራ መሥክሯል ። አብይን ለመጣል ትንሽ ሲቀራቸው በፊኒሽንግ ችግር ምክንያት እንደተሸነፉ ። እነዚህ ሰዎች ከሥልጣን የዘለለ ህልም የሌላቸው ናቸው ።ጃዋር የሚኒልክ ሀውልት ይፍረስ ብሎ በአማራ ጠልነት ሁሌም እንደ አበደ ውሻ የሚንከወከወ ለምንድ ነው በታላቅ ሁከትና ብጥብጥ ወደሥልጣን በመምጣት ለአንድ ቀን ጠ/ሚ ሆኜ ኢትዮጵያን መርቼ ( ኢትዮጵያዊያንን ገዝቼ ልሙት ። ) በማለት አይደለምን ? ጃዋር
ዛሬም ከአማራ ና ከኢትዮጵያ ጠልነቱ የተፈወሰ አይመሥለኝም ። በበኩሌ እንዲህ ዓይነት የወረደ ሂትለራዊ አቋም ያላቸው ነገም የዚች አገር አጥፊዎች መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁ ። አጥፊነታቸውንም በተግባር በቅርቡ ያሳዩናል ብዬ እጠረጥራለሁ ። አብይ ዛሬ ሥለፈታቸው ነገ ለአብይ ያዝናሉ ብላችሁ አጠብቁ ። … አብይ ታሪኩን በድንቅ ና በግሩም ታሪክ ጀምሮ በመጥፎ ታሪክ እንዲደመድመው የሚያደርጉት በግብፅ ዶላር የናጠጡት እነ ጃዋር እንደሆኑ ካልተረዳ እንደ እርግብ የዋህ ፣ እንደ እባብ ብልህ ሁን የተባለውን ጥቅሥ ዘንግቷል ና ቆም ብሎ መፀሐፍን ይመረምር ዘንድ ትሁት ምክሬን እለግሰዋለሁ ። ነገ ፣ ተነገ ወዲያ እውነቱ ይፋ ሥለሚወጣ የነገሬን እውነትነት ይገነዘባል ። … ምንም ድመት ብትመነኩስ አመሏን ትረሳለች ብሎ የሚያሥብም አይመሥለኝምና በወቅቱና በጊዜው እውነቱን ይረዳል ። ለሁሉም ጊዜ አለው። … ።
ለማንኛውም አሁን “ አውጣን ! “ ብቻ ነው ፣ ለማለት የምንችለው ። በተለይም ለኢትዮጵያ አንድነት ፣ ክብር ፣ ታላቅነትና ህልውና ሥንጮኽ የነበርን እና ዛሬም “ ኡ!ኡ! ቤት ይፈርሳል ። ቤት ይቃጠላል ። ሰው ዕለት ፣ ዕለት እየደኸየ ፣ ዘራፊ እየበለፀገ ይሄዳል ። አሜሪካንን ያመነ ጉም የዘገነ አንድ ነው ። “ ሥንል የነበርነው ።
ከዚህ ልብ ሰባሪ ዜና በኋላ ፤ መጪው ዘመን ለእኔ ከጦርነቱ የባሰ ጨለማ በመሆኑ “ አውጣን ። ኢዝጊኦ ! ፈጣሪያችን በታላቅ ምህረትህ ጎብኘን ። “ እላለሁ ።
እንኳን እኔ ፣ ሥለህግ በጥልቀት የማላውቀው የፍትህን ቁልፍ የጨበጡ በየክልሉ ያሉ ሃቀኛ የፍትህ ሰዎች በዚህ ድንገተኛ ድርጊት አውጣን ማለታቸው አይቀርም ። “ እንዴት እንዲህ ይደረጋል ? እንዴት ? በምን ዓይነትስ ሞራላዊ ግዴታ ፣ ግዴታ ፣ መንግሥት የተሰሩትን ፈታ ። በምን ዓይነት ሞራላዊ ግዴታ ? ግልፅ አይደለም ። በእሥክንድር ጉዳይ ከሆነ አዎ ሞራላዊ ግዴታ እንደሆነ እናምናለን ። በነሥብሐት ና በጃዋር የወንጀል ድርጊት ጉዳይ ግን የአያሌ የንፁሐን ሰዎች ደም ይጮኻል ና አፈታታቸው ሞራላዊ አይደለም ። ” በማለት ።
ይኽ ፀሐፊም በግል ማንንም አያውቅም ። ከማንም ጋር ቂምና ቁርሾ የለውም ። የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባልም አይደለም ። ከእውነት ጋር ለመቆምና ለመሰዋት የተዘጋጀ ነው ።እናም ማንኛውም ሰው ጠ/ሚሩን ጨምሮ ከህግ በታች እንደሆነ ያምናል ። ማንም ሰው ወንጀል ከሰራ ፣ ድርጊቱ ከተረጋገጠ በጥፋቱ ልክ ዜጎች ይማሩበት ዘንድ ተገቢውን ቅጣት ባልዘገየ መልኩ መቀጣት አለበት ብሎ ያምናል ።
ለአገራዊ እርቅ እነ ሥብሐትን እና ጃዋርን መፍታቱ አሥፈላጊ ነው ከተባለም ፣ በቀጥታ በደሉ የደረሰበት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ ፣ የአማራና የአፋር ክልል መወያየት ነበረበት ። ሰው እኮነው የሞተው ። ያውም ለመስማት በሚከብድ አገዳደል ።ግፉ የተፈፀመባቸው ክልሎቹ በምክር ቤቶቻቸው ፤ ህዝብንም ባሳተፈ ደረጃ አሥቀድሞ በመወያየት ከእሥር መፈታታቸውን መደገፍ ወይም መቃወም ወይም የተለየ አሥተያየት ሊሰጡ ይገባቸው ነበር ። ከሞራል አንፃር የሻሸመኔው ፣ የዴራው ፣ የቡራዩው ፣ የአዳማው ፣ የአዲስ አበባው ፣ የአጋርፋው ፣ የጉራ ፈርዳው ፣ ወዘተ ። ግፍ ፣ ተነሥቶ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ቤተሰቦች ለውይይት መጋበዝ ነበረባቸው ። ይኽ ባልቀደመበት ፣ በተዋከበ መልኩ በሐገር ክህደት ና በአሸባሪነት የተወነጀሉ ሰዎችን በይቅርታ መፍታት ፣ ያውም ወደፊት ለሚካሄድ የእርቀ ሠላም ወይይት ብሎ ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ማሥቀደም ነው ። ከሞራል አኳያ ተገቢ ና ትክክል የሚሆነው ከውይይቱ በኋላ ቢሆን በተሻለ ነበር ። መንግሥት በግዴለሽነት ና በሞራለ ቢስነት ” ለኢትዮጵያውያን ሞት ብርቃቸው አይደለም ።” እንደሚሉት እንደነ አሜሪካ የሚያላግጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ያለ አይመሥለኝም ። የአንድ ንፁህ ሰው ደም በከንቱ መፍሰስ ህሊና ያለውን ሰው ሁላ ፣ ያገበግበዋል ። ብዬ አምናለሁ ። እናም ከፈረሱ በፊት ሥለቀደመው ጋሪ ሁኔታ እንዴት አይነት አሳማኝ ማብራርያ መንግሥት እንደሚሰጠን ከቶም አላውቅም ። ደግሞም የእልፍ ንፁሐን የሰቆቃ እንባ ሳይታበሥ ፤ ደመ ቀዝቃዛ ጨካኞችን መፍታት ፍትሐዊ አይሆንም ።